ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, October 1, 2021

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት - በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ (ከክፍል 1 እስከ 4)

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር ተፈትተው በመኖርያ ቤታቸው ሲገቡ 

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከወታደራዊው መንግስት ወደስልጣን መምጣት ጀምሮ እስከ የአሁኑ የለውጥ ሒደት ድረስ ከሰላማዊ ትግል እስከ የትጥቅ ትግል ተሳትፈዋል።በቅርቡ በፌስ ቡክ ገፃቸው ላይ'' ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት'' በሚል እስከ ዛሬ ድረስ በአራት የተለያዩ ክፍሎች እየፃፉ እያስነበቡን ነው።ጉዳያችን ከክፍል አንድ እስከ አራት ክፍሎች ከፋፍለው የፃፉትን ከእዚህ በታች ታስነብባችኃለች። መልካም ንባብ -

ክፍል አንድ

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት (ክፍል 1)

አንዳንዴ በአንዳንድ አጋጣሚዎች በመናገር ከምናመጣው ጥቅም የምናመጣው ጉዳት ያመዝናል ብለን ስናስብ ዝምታ እንመርጣለን። ግራ ቀኙን እያገላበጠን፣ ይጠቅማል አይጠቅምም እያልን፣ ስለቅርብና እሩቅ ፋይዳው እያሰላሰልን የሆዳችንን በሆዳችን ይዘን እንቀመጣለን። ሆኖም ግን የመታገስ፣ የመቻል፣ የይሉኝይታ ባህላችን እና ባህሪያችን የሚጠቅሙበት ጊዜ እንዳለ ሁሉ የሚጎዱበት ወቅትም እንዳለ ማወቅ አለብን። በተለይ ባላንጣችን ምንም ለማድረግ የሞራልና የግብረገብ ለከት የሌለው፣ ሃፍረትና ይሉኝታ የማይሰማው ከሆነ ጉዳቱ የበለጠ ያመዝናል።
ወያኔዎች እንዲህ አይነት ባላንጣዎች ናቸው። ሃፍረት፣ ይሉኝይታና ጨዋነት አያውቁም። ቅንነት፣ ሃቀኛነትና ታማኝነት የሚባል ነገር አልዘራባቸውም። ዝም ስላልናቸው ወያኔዎች የሚደጋግሙት ውሸት እውነት ከሚመስልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። እነሱም የገዛ ውሸታቸውን ደጋግመው በመስማት እውነት ነው ብለው ማመን ጀመረዋል። በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አይናቸው በጨው ታጥበው ለሚያሰራጩት ቅጥፈት መልስ መስጠት ተገቢ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

የወያኔ መሪዎች ከአማራ ልሂቃን ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን የሚል ነጠላ ዜማ ለቀው ደጋግመው ሲዘፍኑት እያዳመጥን ነው። ከእዚህ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ጥቂት ጥያቄዎችን አንስቼ መልስ መስጠት እፈልጋለሁ። ለመሆኑ ወያኔዎች የአማራ ልሂቃን ሲሉ ምን ማለታቸው ነው? ለምንድነው የአማራ ልሂቃንን ከሌሎች የኢትዮጵያ ልሂቃን ለይተው ሂሳብ ማወራረድ የፈለጉት? የአማራ ልሂቃን እውነት ወያኔዎች እንደሚሉት የሚወራረድ ሂሳብ አለባቸው ወይስ ይህ አባባል ወያኔያዊ ይሉንታ ቢስነት የወለደው ቅጥፈት ነው? እውነተኛው የሂሳብ ማወራርድ ስራ በገለልተኛ ሂሳብ አጣሪ ቢሰራ ምን ይመስላል? ማን ይሆን ያልተወራረደ ሂሳብ ያለበት? ይህ ጽሁፍ እነዚህን ጥያቄዎች በተመለከተ ምላሽ ለመስጠት በአጭሩ የተዘጋጀ ነው።

1) የአማራ ገዥ መደብ፣ የአማራ ልሂቃን

ለአማራ ህዝብ ሆነ ለሌላውም ኢትዮጵያዊ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነጥብ አለ። ወያኔ የአማራ ገዥ መደብ ወይም ልሂቅ ሲል የአማራ ህዝብ ማለቱ ነው። ይህን በምን ታውቃለህ ለምትሉኝ? መልሴ እነሆ።
በ1970 አ.ም በትግራይ ምድር ወያኔ ነጻ መሬት በሚል ስም በሰጣቸው አካባቢዎች ለአንድ አመት ያህል ቆያቻለሁ። ብዙውን ጊዜ ያሳለፍኩት አዲ ፍታዎ በምትባል የአድዋ አውራጃ መንደር ውስጥ ነበር ። የወያኔ መሪዎችና የወያኔ ካድሬዎች ከእኔና ከሌሎች በቦታው ከነበርን ጥቂት ግለሰቦች ጋር ሲያወሩ የአማራ ገዥ መደብ የሚል ቃል ይጠቀሙ ነበር። የትግራይን ህዝብ በስፋት ሰብስበው በዲስኩርና በዘፈን ቅሰቀሳ ሲያደርጉ ግን ገዥ መደብ የሚለውን ቃል ትተው የትግራዋይ ጠላት አማራ( አምሃራይ) እንደሆነ ነበር ሲያስተምሩና ሲቀሰቅሱ ውለው የሚያድሩት። እኛም ይህን ጉዳይ አንስተን፣ “እንዴት አንድ ህዝብ የሌላ ህዝብ ጠላት አድርጋችሁ ታስተምራላቹህ?” የሚል ተቃውሞ በተደጋጋሚ አቅርበናል። የወያኔ መሪዎችም በተደጋጋሚ “የካድሬዎች ስህተት ነው” ከማለት አልፈው የትግራይ ህዝብ የአማራን ህዝብ እንደ ህዝብ እንዲጠላ የመቀስቀስ ስራቸውን አቁመው አያውቁም።

ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ አንዳንድ ትልልቆቹ የድርጅቱ መሪዎችና በርካታ ተራ ካድሬዎችና የሰራዊት አባላት ድርጅታቸው ይህን የአማራ ጥላቻ ትርክት ለትግራይ ህዝብ ሲያስተምር እንደነበር፣ ከዛም አልፈው ድርጊቱ ትክክል አንዳልነበር ምስክርነታቸውን የሰጡበት ጉዳይ ነው። በመሆኑም ወያኔዎች የአማራ ገዥ መደብ ሲሉ የአማራ ህዝብ ማለታቸው እንደነበር ሁሉ፣ ዛሬም ለሚድያ ፍጆታ የአማራ ልሂቃን ይበሉ እንጂ ሂሳብ የማወራረድ ፋላጎት ያላቸው ከመላው የአማራ ህዝብ ጋር ነው።

ወያኔዎች በ27 አመት የግፍ አገዛዝ ዘመናቸውና ከዛም ቀጥለው በመጡትና ባለፉት 3 አመታት ሂሳብ ሲያወራርዱ የነበረው ወደፊት እንደማሳየው እዳ ከሌለበት የአማራ ሊሂቅ ጋር ብቻ ሳይሆን በመስኪኑና ደሃው የአማራ ህዝብ ላይ ነው። እንዳውም ልሂቁን በቀላሉ እዳ ማስከፈል የሚችሉበት እድል ስላልነበራቸው፣ የተወሰነውም በሎሌነት የገባላቸው ስለነበር፣ የጭካኔና የግፍ በትራቸው ሲያርፍ የነበረው በምስኪኑ ሰፊው የአማራ ህዝብ ላይ ነበር። ስለዚህም አማራን በልሂቅና ልሂቅ ባልሆነ ክፍሎች ለመከፋፈል ወያኔዎች ሊያጃጅሉን ሲሞክሩ መልሳችን “ሞኛችሁን ፈልጉ” መሆን ያለበት።

2) ወያኔ የአማራን ህዝብ ለምን ከሌላው ህዝብ ለይቶ ሂሳብ ማወራረድ እፈልጋለሁ ይላል?

ወያኔ በ27 አመት የግፍና የዘረፋ የአገዛዝ ዘመኑ ሰቆቃ የፈጸመው በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ነው። የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም። አፋሩ፣ ሱማሌው፣ ኦሮሞው፣ ሲዳማው፣ ወላይታው፣ በጥቅሉ ደቡቡ፣ ጋምቤላው፣ ቤንሻንጉሉ፣ አማራውና ሌላውም በወያኔ አገዛዝ በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ተመድቦ ተዋርዶ፣ ተረግጦ ተገዝቷል። እስከ አጥንቱ ተግጧል። በድህነት ተቆራምዶ፣ ሰማይ ተደፍቶበት ኖሯል። ግፍ መከራ ሲበዛበት የተሻለ ህይወት ፍለጋ በገፍ ተሰዷል። ካሰበበት ሳይደርስ በረሃና ባህር በልቶት የትም ቀርቷል። የትም የቀረው ዜጋ ቁጥሩ ስንት እንደሆነ ቤቱና ወላጆቹ ያውቁታል። ይህን አሰቃቂ ጉድ የረሱ ወያኔዎች ብቻ ናቸው። እነሱ በዳዮች ናቸውና። የበዳዮች የማስታወስ ችሎታ ደግሞ ደካማ ነውና።

ዛሬ ደግሞ ወያኔዎች አይናቸውን በጨው ታጥበው እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ሲገዙት የነበረውን ከአማራ ክልል ውጭ ያለውን ህዝብ “ከአንተ ጋር ጠብ የለንም ጠባችን ከአማራው ጋር ነው” እያሉት ነው። ይህን የሚሉት፣ አማራውን አጥፍተን አዲስ አበባ ብንደርስ ከአንተ ጋር ጠብ ስለሌለን ምንም አናደርግህም የሚል መልእክት በማስተላለፍ የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔ በአማራና በአፋር ክልል የጀመረውን ጥቃት የኔ ጥቃት አይደለም ብሎ የዳር ተመልካች እንዲሆን በማሰብ ነው።

ወያኔዎች እራሳቸውን ብቻ ብልጥ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ደደብ አድርጎ የሚያይ በሽተኛ ህሊና አላቸው። የእነሱ ብልጣብልጥ ስትራተጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ተራ በተራ እየከፋፈሉና እያስገበሩ፣ ቢቻል ከቀድሞ የዘረፋና የጭቆና ዙፋናቸው ላይ መመለስ፣ ካልሆነም ኢትዮጵያን በማፍረስ ሃገሪቱን የህዝቧ ሲኦል እንድትሆን ማድረግ ነው። ይህን ተልእኮ ለማሳካት ምስኪኑን የትግራይን ህዝብ ለስቃይና ለእልቂት እየዳረጉት ነው። ኢትዮጵያ ሲኦል ስትሆን ደግሞ ለወያኔዎች የምትመች ገነት የሆነች ትግራይ የምትባል ሃገር የመፍጠር ጅላ ጅል ህልም ይዘው ነው።

ሌላው ወያኔ አማራውን በጠላትነት የፈረጀበትን ምክንያት እንድሚከተለው አቀርበዋለሁ። የአማራ ክልል ህዝብ “ወያኔ ያነጣጠረው በኔ ላይ ብቻ ነው” በሚል አመክኖ እራሱን ከሌላው የሀገሪቱ ህዝብ ነጥሎ ትግሉን የወያኔዎችና የአማራ ህዝብ እንዲያደርገው በማሰብ ነው። እዚህ ላይም ወያኔዎች የረሱት ሌላ ሃቅ አለ። የአማራ ህዝብ የራሱን ሽንፈት የኢትዮጵያ ህዝብ ሽንፈት እንደሆነ የሚረዳ፣ ወያኔ ዳግመኛ የባርነት ስርአቱን በኦሮሞው፣ በሶማሌው፣ በደቡቡ፣ በጋምቤላው ወዘተ ላይ መጫን የሚችለው በአማራ ህዝብ አስከሬን ላይ ተረማምዶ እንደሆነ የሚያውቅ ህዝብ ነው። ሰለዚህም ነው የአማራ ህዝብ በየግንባሩ በዘመተበት ቦታ ሁሉ ከወያኔ ጋር የሚደረገውን ትግል የአማራ ህልውናን ብቻ የማስጠበቅ ሳይሆን የኢትዮጵያንም ህልውና የማስጠበቅ እንደሆነ አጥብቆ የሚናገረው። ስለዚህም ነው ከወያኔ ጋር የሚደረገው ወቅታዊ ትግል “በአማራና በአፋር ክልል ይደረግ እንጂ በነዚህ ክልሎች ላይ የተሰነዘረው ጥቃት በሁሉም ህዝብ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ነው” የሚለው። ለእዚህም ነው ሁሉም የሃገሪቱ ህዝብ ወያኔ በአማራና በአፋር ህዘብ ላይ የከፈተውን ጥቃት በሁሉም የሃገሪቱ ህዝብና በኢትዮጵያ ላይ የተደረገ ጥቃት አድርጎ የተመለከተው። ቀፎ እንደተነካበት ንብ በጋራ የተቆጣው።

ሌላው ወያኔ የአማራን ህዝብ ለይቶ ለማጥቃት የወሰነበት ምክንያት የሚከተለው ነው። ወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመዘርጋት የሞከረውን ዘርን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ስርአት በወያኔ የአገዛዝ ዘመን አምሮ የተቃወመው አማራ በመሆኑ ነው። ወያኔ መላውን የኢትዮጵያን ህዝብ በዘር ከፋፍሎ፣ ህዝቡ በዘር ጥርጣሬና ፍጥጫ ውስጥ እንዲወድቅ አቅዶ የሰራ ድርጅት ነው። የእቅዱ አላማ የወያኔን የዘረፋና የጭቆና አገዛዝ ዘላለማዊ ማድረግ ይቻላል የሚል ነበር። “እርስ በርሱ የሚጠራጠር ህዝብ በጋራ በወያኔ ላይ ማመጽ አይችልም” ከሚል ስሌት የተሰራ እቅድ ነው። በእነዛ ዘመናትም ወያኔ የአማራን ህዝብ በጠላትነት መፈረጅ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ህዝቦች የአማራን ህዝብ በጠላትነት እና በጥርጣሬ እንዲያዩ ያላደረገው ጥረት አልነበረም። የአማራ ህዝብም መስፈሪያ የማይገኝለት ዋጋ እንዲከፍል ተደርጓል። በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እንደ ቅጠል ረግፏል፣ መፈናቀል፣ መዘረፍና መሰደድ የአማራ ህዝብ እጣ ሆኖ ቀጥሏል። ይህም ሆኖ በወያኔ የዘላለማዊ የስልጣን ባለቤትነት ህልሙ ፊት ደንቃራ ሆኖ ያገኘው የአማራን ህዝብ ነው።

በመጨረሻም የወያኔን የግፍ አገዛዝ እድሜ ያሳጠረው፣ ፋኖ እና ቄሮ ተናበው በወያኔ ላይ ማመጻቸው እንደሆነ ይታወቃል። “የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው” የሚለው፣ የወያኔን ከፋፋይ የዘር ግርግዳ ያፈረሰው፣ የወያኔን የግፍና የዘረፋ የአገዛዝ ዘመን ማብቃቱን ያበሰረው መፈክር ባለቤት የሆነው አማራው ስለሆነ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። በራሱ በኢህአዴግ ውስጥ አማራና ኦሮሞው በጋራ አሲረዋል። ወያኔ ሳያስበው፣ አማራው የራሱ እጩ የሆነውን አቶ ደመቀ መኮንን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩነት አውጥቶ፣ ድምጹን በሙሉ ኦሆዴድ ላቀረበው እጩ ለዶ/ር አብይ ሰጥቷል። ይህን በማድረግ በተዘዋዋሪ መንገድ የወያኔን እድሜ ሊያስቀጥል የሚችል የወያኔ ተላላኪ የሆነ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስልጣን እንዳይዝ አድርጓል።

ወያኔዎች ተላላኪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከላይ አስቀምጠን ሃገር እየዘረፍን ህዝብ እየረገጥን ዝንተአለም እንኖራለን ብለው የነደፉትን ትልም መና በማስቀረት አማራ ትልቅ ሚና ነበረው። ወያኔዎች ዘላለማዊ ነው ብለው ተኩራርተው ከተቀመጥንበት ዙፋን እንዲፈነግሉ ያደረጋቸው ዋንኛ ባላንጣ “አማራ ነው” ብለው የሚያምኑ መሆናቸውን በአደባባይ ተናግረዋል። “የፈነገለን አማራ ነው” የሚል ቂም መቋጠራቸው የአደባባይ ሃቅ ነው። ይህን ቂም አጼ ዮሃንስ ሲሞቱ ለትግራይ ይገባው የነበረውን ንግስና አማሮች ቀምተው ለአጼ ሚኒሊክ አደረጉት ከሚለው የቆየ ቂም ጋር አዋህደው ወያኔዎች ለአማራ ያላቸውን ጥላቻ ማጠናከሪያ አድርገውታል።
እንግዲህ ከላይ የጠቀስናቸውና ሌሎችም በአደባባይ ወያኔዎች ያልነገሩን ምክንያቶች በአንድ ላይ ተደምረው ነው የሰሞኑ የወያኔ ነጠላ ዜማ “ከአማራ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን” የሚል የሆነው። በሚቀጥለው ዝግጅቴ በክፍል 2 እውነት በሃቅ ላይ የተመሰረተ የሂሳብ ማወራረድ ስራ ብንሰራ ማን በእዳ ብዛት ተቀብሮ እንደሚቀር የሚያሳይ ዝርዝር ዘገባ አቀርባለሁ። የጀመሩት ወያኔዎች ስለሆኑ ለመጨረሱ የምናፍርበት ምክንያት አይኖረም። እስከዛው በቸር እንገናኝ።

ክፍል ሁለት

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት (ክፍል 2)

በሃቅ ላይ የቆመ ሂሳብ ሲወራርድ፣ በታሪክ ማእቀፍ፤ ትንሽ ሃፍረት የሌላቸው ወያኔዎች ምንም ሳይሳቀቁ ከአማራው ጋር የሚያወራርዱትን ሂሳብ ማስላት የሚጀምሩት ከመቶዎች አመታት በፊት የተከሰቱ ታሪኮችን እያጣቀሱ ነው። ስለሆነም እኛም ሳንወድ በግድ ወደ ኋላ ተመልሰን ሂሳቡን በመስራት እስከአለንበት ወቅት መዝገቡን ወቅታዊ ማድረግ ይኖርብናል።

ወያኔዎች አንዱ አማራን የሚከሱት “የኛን ታሪክ ወስዶ የራሱ ታሪክ አደረገው” የሚል ነው። ይህን ክስ ሁለት ቦታ ከፍለው ያቀርቡታል። የመጀመሪያው፣ “የአክሱም ስልጣኔ እና ታሪክ የእኛ ታሪክ ሆኖ ሳለ አማሮች የኛ ታሪክ ነው ብለው ወሰዱት” የሚል ነው። ሌላው ክስ በዋንኛነት ከአጼ ዮሃንስ ንግስና በኋላ በመጣው የታሪክ ዘመን ውስጥ ከተከሰቱ ኩነቶች ጋር በተያያዘ የሚያቀርቡት ክስ ነው። ሁለቱንም ክሶች “አማሮች ታሪካችንን ወስደው የኛ ነው ስላሉ፣ ታሪካችንን ለማስመለስ ትግራዋይ እንታገል” በሚል ባህላዊ ዘፈን ህዝቡን ሲቀሰቅሱ በቦታው ነበርን። የ1970ው “ታሪህና ወሲዶም፣ ነአ ነአ ኢሎም ንቃለስ ትግራዋይ ንመልስ ቅያና” (ታሪካችንን ወስደው የኛ የኛ ብለው እንታገል ትግራዋይ ታሪካችንን ለማስመለስ) የሚሉ ስንኞች የነበሩትን፣ ከላይ የጠቀስኳቸውን ነጥቦችና “አድዋ፣ ተንቤን፣ ሽሬ እንዳባጉና ሌሎችም ቦታዎች ላይ ከጣሊያን ጋር የተደረጉ ተጋድሎዎችን አንዳቸውም ሳይቀሩ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ያልተሳተፉበት፣ አማሮች ከትግሬዎች ቀመተወ የራሳቸው ድል አደረጉት የሚል ክስ የሚያቀርብበትን ዘፈን ዛሬም እናስታውሰዋለን። እነሱ ግን ካሴቱ ሲጠፋ የሚያስታውሰው ሰው የጠፋ መስሏቸው ነበር። ይህን ካልን እነዚህን ክሶች ተራ በተራ እንያቸው። በቅድሚያ ግን ለሂሳብ ማወራረድ እንዲመች ስል የተወሳሰበውን የኢትዮጵያን ታሪክን እንዳው በደምሳሳው እያቀረብኩት እንደሆነ ይታወቅልኝ።

በማስረጃ የተደገፈው የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚነግረን በስድስተኛው ምእተ አመት መጨረሻ የአክሱም ስርወ መንግስት ስልጣን መዳከም ሲጀመር፣ ስልጣኑን ከአክሱሞች የቀሟቸው፣ እራሳቸው አክሱማውያን እየወረሩና እያስገበሩ፣ እያገቡና እየተዋለዱ የተዋሃዱአቸው አገዎች እንጂ አማሮች አልነበሩም። (እግረ መንገዴን የአክሱም ስልጣኔ የትግሬዎች ስልጣኔ ለመሆኑ እስካሁን መረጃ የለም። ቋንቋቸው ግእዝ የነበረ ነገስታት ስልጣኔ ነው።) የዛጉዬ ስርወ መንግስት የአክሱማውያኑን ስርወ መንግስት ተክቶ እስከ 13ኛው ምእተ አመት መጨረሻ የደረሰ ቢሆንም በመጨረሻ ራሱን የአክሱም ሰርወ መንግስትና ስልጣኔ ወራሽ ነኝ በሚልና ራሱን የአክሱም ስርወ መንግስት አስቀጣይ አድርጎ የሚያይ፣ ዩኩኖ አምላክ የተባለ የሸዋ ንጉስ የዛጉዬን ንጉስ በጦርነት አሸንፎ ነገሰ። በወቅቱ ይህን የንጉሱን ድርጊት ርእዮተአለማዊ ሽፋን በመስጠት በዋንኛነት የተባበሩት የትግራይ የቤተክህነት ልሂቃን እንደሆኑ ይታወቃል። ከዩኩኖ አምላክ ዘመን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ንጉስ ሃይለስላሴ ድረስ የመጡ ነገስታት በሙሉ ራሳቸውን የአክሱም ስልጣኔ እና የአክሱም ስርወ መንግስት ወራሾችና የአክሱምን ገናናነትና ስልጣኔ የራሳቸው የክብርና የኩራት ምንጭ አድርገው ያለፉ ናቸው።

ከዚህ የታሪክ ሃቅ ጋር ተያይዞ ወያኔዎች የሚያቀርቡት ጉደኛ ክስ “አማሮች የአክሱምን ስልጣኔና ታሪክ የራሳቸው አደረጉት” የሚል ነው። ልብ በሉ አማሮች “አራከሱት” አይሉም። “የዚህ ስልጣኔ ባለቤቶች አማሮች ብቻ ናቸው የትግራይ ህዝብ የለበትም ይላሉ” አይልም ክሱ። አማሮች ላይ የቀረበው ክስ “የአክሱምን ስልጣኔ ኢትዮጵያ ለሚባል ሃገር፣ የኩራትና የስልጣኔ ምንጭ አደረጉት” የሚል ነው። “የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው” የሚለው ዝነኛውና በድንቁርና የተሞላው የመለስ ዜናዊ አባባል መነሻው ይህ የተንሸዋረረ የታሪክ እይታ ነው። በወቅቱ ለዚህ አባባል “የአንድ ሃገር ህዝብ ታሪክ፣ ያ ሃገር እንደሃገር እስከቀጠለ በዛ ሃገር የሚኖሩ ዜጎችና ህዝቦች ሁሉ ታሪክ ነው።” በማለት የሰጠሁት ምላሽ ወያኔዎች በአማሮች ላይ ለሚያነሱትም ክስ በምላሽነት የሚሰራ እንደሆነ መታወቅ ይኖርበታል።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ወያኔዎች የአክሱም ስልጣኔን በተመለከተ በአማራው ላይ የሚያቀርቡት ክስ እጅግ የሚያስገርም ሆኖ እናገኘዋለን። ሁላችንም እንደምናውቀው በአለም ላይ ከታሪክ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ጭቅጭቅ፣ በኛ ሃገርም ሳይቀር በተለያዩ አክራሪ ብሄረተኛ የፖለቲካ ልሂቃን የሚነሳ ክስ “ታሪካችንን ተንኳሰሰ፣ እንዲጠፋ ተደረገ፣ በቦታው የእኛ ያልሆነውን ታሪክ ትጫነብን” የሚል ክስ እንጂ ታሪካችንን ወስደው ኮራበት። የራሳቸው የህልውናው መሰረት፣ የኩራታቸውና የክብራቸው ምንጭ አደረጉት” የሚል አይደለም።
እንኳን የአማራ ህዝብ፣ የአለም ህዝብ ጭምር የአክሱምን ስልጣኔ የራሱ አድርጎ ቢኮራበት በወያኔዎች ሊወደድ ሊፈቀር የሚገባው ተግባር እንጂ ሊጠላ የሚገባው ነገር አልነበረም። በጥላቻ ላበደው ወያኔ ግን በአማራው ላይ ጥላቻ ለመፍጠር መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል።

ቀጥሎ ደግሞ ወያኔዎች በአማራው ላይ ክስ ወደሚያቀርቡበት የቅርብ ዘመን ታሪክ እንምጣ።ዘመነ መሳፍንት እንዲያበቃ እና ኢትዮጵያ በአንድ ማእከላዊ መንግስት ስር እንድትተዳደር መሳፍንቶችን በማስገበር እርምጃ የወሰዱትን ንጉሰ ነገስት ቴዎድሮስን ከተኩት የአጼ ዮሃንስ ዘመነ መንግስት እንነሳ። ጉልበት ያለው፣ ተቀናቃኞቹን አሸንፎ ንጉስ መሆን በሚቻልበት ሃገር አጼ ዮሃንስም እንደ አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን በጉልበት ንጉሰ ነገስት እንዳደረጉ ይታወቃል። የአጼ ዮሃንስ ጉልበት ግን የኢትዮጵያ መሳፍንት እርስ በርሳቸው በሚያደርጉት ፍልሚያ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የመጀመሪያው ሃገራቸውን በውጭ ወራሪዎች እንድትወረር ከእንግሊዞች ጋር ተመሳጥረው በአጼ ቴዎድሮስ አስከሬን ልዋጭ ከእንግሊዞች ባገኙት ዘመናዊ መሳሪያና እንግሊዞች ባሰለጠኗቸው ተዋጊዎች ከመጣ ጉልበት የተገኘ ንግስና እንደሆነ የታወቀ ነው።
አጼ ዮሃንስም እንደ ቴዎድሮስ “የአክሱም ነገስታት ዝርያ ነኝ። የስርወ መንግስቱ ወራሽ ነኝ” አሉ። እንደ ምኒሊክ አይነቶችም በወቅቱ ንጉሰ ነገስት የመሆን ህልም የነበራቸው የሸዋ ንጉስ የአጼውን ጉልበት አይተው ገበሩላቸው። ንጉስ ምኒሊክ ድንጋይ ተሸከመው ለአጼ ዮሃንስ በመገበራቸው ያኮረፈ፣ ቂም የያዘ አማራ አለ? የለም።

አጼ ዮሃንስ ለእንግሊዞች አድረው በቴዎድሮስ ላይ አሲረው መሳሪያ ቢቀበሉም መልሰው በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስትነታቸው ከቱርኮች፣ ከግብጾች፣ ከጣሊያኖች ጋር ተዋግተው በማሸነፋቸው የአማራ ህዝብ እንደራሱ ጀግና አድርጎ ከማየት ውጭ ያደረገው ነገር የለም። አጼ ዮሃንስ “የነገስታቱ ከተማ ጎንደር ተደፈረ ቤተክርስቲያን በደረቡሾች ነደደ” ተብሎ ሲነገራቸው ወደ ምጽዋ ጀመረውት የነበረውን ጉዟቸውን ገትተውና ገስግሰው መተማ ላይ ደርቡሾችን ገጥመው በመሰዋታቸው ፤ንጉሱ በአማራ ህዝብ ላይ የወሰዷቸው በጭካኔ የተሞሉ እርምጃዎች እንዳሉ ሆነው፤ የአማራ ህዝብ ህልፈታቸውን በቁጭት ሲያየው የኖረ መሆኑን ማንም የማይክደው ሃቅ ነው።
“የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ
አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዩሃንስ”
በማለት የተቀኘላቸው አማራው አልነበረም?
ስልጣን ከዮሃንስ ወደ ምኒሊክ የሄደው፤ ከቴዎድሮስ በኋላ ስልጣን ወደ አጼ ዮሃንስ በሄደበት ተመሳሳይ ሂደት ነው። ቴዎድሮስ በእንግሊዞች ተገደሉ። ዮሃንስም በመሃዲስቶች ተገደሉ። ዮሃንስ በቴዎድሮስ ቦታ ራሳቸውን መተካት የቻሉት በጉልበት ባላንጣዎቻቸውን አስገብረው ነበር። ጉልበቱ በሃገር ክህደት የተገኘ ቢሆንም!
አጼ ምኒሊክም፣ አጼ ዮሃንስን መተካት የቻሉት ጉልበታቸው ከባላንጣዎቻቸው በላይ በመሆኑና ባላንጣዎቻቸውም እንዲገብሩላቸው በማድረጋቸው ነው። ምኒሊክ ድንጋይ ተሸክመው ዮሃንስ እግር ስር እንደወደቁ ሁሉ በኋላ ደግሞ የምኒሊክ እጣ የገጠማቸው የትግራዩ ራስ መንገሻ ዮሃንስ ድንጋይ ተሸክመው ምኒሊክ እግር ስር ወድቀው የምኒሊክን ንጉሰ ነገስትነት ተቀብለዋል። ይህ አሰራር በነገስታቱ ዘመን ይሰራበት የነበረ ነው። ለሃይለኛ መንበርከክ ለንጉስ ምኒሊክ ሲሆን የሚሰራበት ለራስ መንገሻ ሲሆን የማይሰራበት ምክንያት አይኖርም።
አጼ ዮሃንስ ስልጣን ከአክሱማውያን እጅ ከወጣ ከሺ አመት በኋላ የመጡ ብቸኛው ከትግራይ የተነሱ የኢትዮጵያ ንጉስ ናቸው። የነገሱትም ለ17 ብቻ አመታት ነው። ከአጼ ዮሃንስ በፊትም ሆነ በኋላ ንጉሰ ነገስትነት ከሸዋው ንጉስ ዩኩኖ አምላክና ከአክሱም ነገስታት ጋር “የዘር ግንድ አለን” በሚሉ ነገስታት ተይዞ የቆየ ነው።

እነዚህ ነገስታት የአንድ ዘር የደም ጥራት ያልነበራቸው ከተለያዩ ዘሮች ጋብቻና መቀላቀል የተገኙ ናቸው። ከአጼ ዮሃንስ ሞት በኋላ የዮሃንስ ልጅ መንገስ ሲገባው፣ አማሮች ስልጣናችንን ያለአግባብ ቀምተው ምኒሊክን አነገሱ ለሚለው የወያኔ ክስ ዮሃንስ የማን ልጅ ሆኖ ነው የነገሰው? በመወለድ ከሆነ የቀድሞ ንጉሰነገስት ቴዎድሮስ ሲሞቱ ልጃቸው ወይም የቅርብ ዘመዳቸው መንገስ አልነበረበትም ወይ ? የሚል ጥያቄ ማንሳት ይቻላል።

በተለይ የአጼ ቴዎድሮስ ህጻን ልጅ፣ ልኡል አለማየሁ በእንግሊዞች ተይዞ፣ የሺ አመታት እድሜ ከነበራቸው የኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶች ጋር በምርኮ ስም ወደ ሃገረ እንግሊዝ ሲወሰድ፣ አጼ ዮሃንስ እንደ አንድ ኩሩ ኢትዮጵያዊ እንዴት ተደርጎ አላሉም። እንዲያውም መንገድ መሪና አስተባባሪ በመሆን የተባበሩት አጼ ዮሃንስ አልነበሩም ወይ? ይህን አስነዋሪ ድርጊት ንጉሱ የፈጸሙት ለስልጣን ብለው አልነበረም ወይ? ለነዚህ ጥያቄዎች ወያኔዎች ምን መልስ ይኖራቸው ይሆን?

አጼ ቴዎድሮስም ቢሆኑ ባላንጣቸውን በሃይል አስገብረው ነገሱ እንጂ ንጉሰነገስት ከነበሩ አባታቸው ስልጣን በውርስ አላገኙም። በመሆኑም ይህን ጉዳይ ወስደው ወያኔዎች በአማራ ላይ ክስ ማቅረብ አይችሉም። ሆኖም ግን አንዱ ወያኔ በአማራ ላይ የጥላቻ ዘመቻ የሚያካሂደው “አማራው ስልጣን ያለአግባብ ከትግራይ እንድትወጣ አድርጓል” የሚል ነው። የንግስና ስልጣን በጉልበት በሚወሰንበት ዘመን የተከናወኑ ኩነቶችን አንስቶ በህዝብ ላይ የጥላቻ መቀሰቀሻ ማድረግ አሳፋሪ የሚሆነውም ለዚህ ነው።

ሌላው የታሪክ ሃቅ ፍጹማዊ የሆነ ወያኔያዊ ይሉኝታ ቢስነት የተጠናወተው ነው። አድዋ ላይ በጣሊያኖች ላይ የተገኘው ድል አጼ ምኒሊክ ከመላው ኢትዮጵያ ባሰባሰቡት ተዋጊ ሰራዊት የተገኘ ድል ነው። ሃቁ ራስ መንገሻ ዮሃንስ አድዋ ላይ በራሳቸው አቅም አነስተኛ ቁጥር የነበረውን የጣሊያን ሰራዊት መመከት አቅቷቸው፣ ጣሊያን አድዋን አልፎ መቀሌን ተቆጣጥሮ የትግራዩ ገዥ መቀመጫ አጥተው በሚንከራተቱበት ወቅት ከመላው ኢትዮጵያ ተሰባስቦ የመጣው ጦር የትግራይን መሳፍንት፣ መኳንንትና ህዝብ ከመጨረሻው የነጭ ተገዥነትና ውርደት ያዳነ መሆኑ ነው። ወያኔዎች ይህን የአድዋን የጦርነት ሃቅ ክደው ድሉ “የኛ ብቻ ነው” እያሉን ነው። ይህን ለትግራይ ህዝብ ሲያስተምሩ በጆሯችን ሰምተናል። ቀደም ብዬ የጠቀስኩት ዘፈን ስንኞች ይህንኑ ነበር የሚሉት።

በመጨረሻም ራስ መንገሻ በጣልያን አማካኝነት ለደረሰባቸው ውርደት ከጣሊያን ጋር ተሰልፈው የነበሩ ኤርትራውያን ናቸው በማለት፣ አጼ ምኒሊክ ለነጩ ወራሪ ለጣሊያን ሳይቀር ያሳዩትን ከአሸናፊነት የመጣ ሰብአዊነት ኤርትራውያኑ እንዲነፈጋቸው አድርገዋል። ራስ መንገሻ የምርኮኞቹ ኤርትራውያን ወታደሮችን አንድ እጅና እግር ካልተቆረጠ ሞቼ እገኛለሁ በማለት ምኒሊክ የጭካኔ ውሳኔ እንዲወስኑና የኢትዮጵያም የጀግንነትና የድል ታሪክ በራስ መንገሻ ግፊት ጥቁር ጥላሸት እንዲቀባ ሆኗል። እውን ወያኔ እንደሚለው “ አድዋን አማሮች ቀምተው “የእኛ እኛ” ብለው የሰረቁት ታሪክ ነው? ወይስ ያለ ምኒሊክ ሰራዊት የትግራይ እጣ ምን ይሆን እንደነበር ወያኔዎች አጥተውት?” በዳግማዊ ምኒሊክ የተመራው ከመላው ኢትዮጵያ የዘመተው ተዋጊ ድል ባያደርግ ኖሮ የትግራይ ህዝብ እጣ የጣሊያን ባሪያ ከመሆን አያመልጥም ነበር። ሃቁ ይህ እና ይህ ብቻ ነው።

በሁለተኛው የጣሊያን ወረራ (ማይጨው ጦርነት) ወቅትም የሆነውን እንመልከት። ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ያስታጠቃቸውን በአስር ሽህዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ይዞ ደጅአዝማች ሃይለስላሴ ጉግሳ ከጣሊያን ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ለመውጋት ገና ጦርነቱ ሳይጀመር ወደ ኤርትራ አልሸሸም እንዴ? የራስ ካሳ ጦር ተንቤን አቢ አዲ ላይ ሲዋጋ፣ የራስ እምሩ ጦር ሽሬ እንዳባጉና ላይ ሲዋጋ፣ ወጣቱ አብቹና ወንድሞቹ ከሰላሌ ዘምተው፣ አብቹ ወንድሞቹን ትግራይ ምድር ላይ ሲገብር፣ እነደጃች መሸሻ የከንባታውን ጦር እየመሩ በጀግንነት ተዋግተው በትግራይ ምድር ሲሰው፣ ትግራይ ውስጥ የወያኔ ቅድመ አያቶችና አያቶች በዛን ወቅት ምን ይሰሩ ነበር?
ጣሊያን ያሰለፋቸው ኤርትራውያን ጣሊያን በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ በመቃወም በተለይ በደቡብ ግንባር መሳሪያቸውን እየያዙ ጣሊያንን እየከዱ ከኢትዮጵያዊያን አርበኞች ጎን ተሰልፈው ጣሊያንን ሲዋጉ የወያኔ አያቶች በሰሜን ግንባር ከክህደት በስተቀር ምን ፈየዱ? በሰሜኑ ግንባር የወያኔ ቀደምቶች ከጣሊያን በከፋ መልኩ ኢትዮጵያዊ ወገናቸውን እየገደሉ መሳሪያውን፣ ስንቁን አልገፈፉም?
ለመሆኑ በጣሊያን ወረራ ወቅት በመላው ኢትዮጵያ የተካሄደው የአምስት አመት የአርበኝነት ታሪክ ሲወሳ፣ በትግራይ ምድር የበቀሉ የሁለት አርበኞች ስም መጥራት ይቻል ይሆን? ይህን የትግራይ መሳፍንቶች የክህደት ታሪክ አማራው አራገበው? ይህን የክህደት ታሪክ እየቆሰቆሰ፣ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በትግራይ ወንድሞቹ ላይ ቂም እንዲቋጥር ተጠቀመበት? ወይስ ይህ “የውሰጣችን ገመና ነው” ብሎ ሸፍኖ ሸፋፍኖ ቀበረው?

ወያኔዎች “የአማራ” የሚሏቸው ተከታታይ መንግስታት በእነዚህ የወያኔ አያቶችና አባቶች ሸፍጥ፣ ቂም ይዘው የትግራይን መሳፍንትና መኳንንት በኋላም የትግራይን ልሂቃን ከሃብት፣ ከስልጣን፣ ከሹመት አገለሏቸው? አላገለሏቸውም። በአጼ ሃይለስላሴ መንግስት ውስጥ ከነበሩ 40 ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ውስጥ 11 ከመቶ የሚሆኑት ትግርኛ ተናጋሪዎች የነበሩ መሆኑን እዚህ ላይ እናስታውሰው። ከዚህ ጉዳይ ጋር በወያኔ ዘመን የሆነውን በተመለከተ በቦታው እንመለስበታለን።

ከትልልቅ ስልጣን ባለቤትነት ውጭስ ቢሆን የትግራይ ተወላጆች በመላው ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሰው፣ አርሰው፣ ነግደው፣ በሲቪልና በወታደራዊ ተቋማት ተቀጥረው መስራትና መኖር የሚችሉበትን ሁኔታ ያመቻቸው ወያኔዎች “የአማራ” በማለት የሚከሱት የኢትዮጵያ መንግስት አልነበረም? የአማራ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ምክንያቶች፣ ከትግራይ የሚፈልሰውን ወገኑን እንደራሱ ወስዶ፤ ሰርቶ የሚኖርበትን ትዳርና ቤተሰብ የሚመሰርትበትን ሁኔታ ሲያመቻች እንደኖረ ይታወቃል። ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ከትግራይ ተሳደው፣ መጠጊያቸውን የአማራ ህዝብ ያደረጉ ለትልቅ ሃብትና ክብር የበቁ ታሪክ የሚያውቃቸው በርካታ ግለሰቦች አሉ። በግልባጩስ ብንመለከተው፤ በየትኛው ዘመን ነው አማራው፣ ወደ ትግራይ ሄዶ መሬት ወስጄ ልረስ፣ ሱቅ ከፍቼ ልነግድ፣ በግልና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ልቀጠር ያለው? ለመሆኑ በትግራይ ምድር ለአማራ ህዝብ የተዋለ ውለታ በታሪክ ተፈልጎ ይገኝ ይሆን? ይህን ቆየት ካለው ታሪካችን ጋር የተሳሰረ ጉዳይ በእዚሁ እንቋጨው። በክፍል ሶስት ቀረብ ወዳሉት ዘመናት በመምጣት ሂሳብ የማወራረዱን ስራ እንቀጥላለን።

ክፍል ሦስት
ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት (ክፍል 3)

የ1968ቱና የ2013ቱ የወያኔ ስነዶች ተመጋጋቢነት ወያኔዎች በ1968 አም የህወሃት የድርጅት ፕሮግራም አዘጋጁ። ይህ ፕሮግራም የ1968ቱ ማኒፌስቶ በመባል የሚታወቀው ሰነድ ነው። የዚህ ሰነድ አዘጋጆች ሶስት ሲሆኑ ሁለቱ በህይወት የሉም። ለገሰ (መለስ) ዜናዊና አምሃ (አባይ) ጸሃዬ። አንዱን በሽታ፣ ሌላውን ጥይት ወስዷቸዋል። ሶስተኛው ሰው ስብሃት ነጋ ከተምቤን ዋሻ ተጎትቶ ወጥቶ በስተርጅና አዲስ አበባ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ይገኛል።

ከዚህ ሰነድ የምናነሳው ነጥብ ሂሳብ ከማወራረዱ ስራችን ጋር አይን ባወጣ መንገድ የተያያዘውን ብቻ ነው። ሰነዱ “የትግራይ ህዝብ፣ ኢትዮጵያ በሚል ሽፋን የሚያጭበረብር “አማራ” በተባለ ብሄር በቅኝ ግዛትነት የተያዘ” እንደሆነ በግልጽ ያስቀምጣል። ከዚህ ተነስቶ የህወሃት የትግል አላማ “ትግራይን ከአማራ/ኢትዮጵያ ቅኝ አገዛዝ ነጻ አውጥቶ” የትግራይ ሪፐብሊክ መመስረት እንደሆነ ያትታል።
ይህ ሰነድ በዋንኛነት በወጣቶቹ (በወቅቱ 25 አመት ያልሞላቸው ነበሩና) በመለስና በአባይ ጸሃዬ ድንቁር እና ድፍረት ወይንስ በጎልማሳው በስብሃት ነጋ መሰሪነት የተጻፈ ይሁን የማውቀው ነገር የለም። የድንቁርና እና የመሰሪነት ድምር ውጤትም ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ይህ ሰነድ፣ በወቅቱ ሌሎቹን የወያኔ አመራሮች ሳይቀር የሚያሳምን ሰነድ አልሆነም። ይህን ተረት የሰማ የትግራይ ህዝብም በወቅቱ የጠየቀውን ጥያቄ እነ ስብሃት ነጋ ሊመልሱለት ያልቻሉት ነበር። “ይቺ በአማራ/ኢትዮጵያ በቅኝ የተያዘች የምትሏት ጥንታዊት የትግራይ ሃገር ስሟ ማን ነበር?” ስብሃትና ውርንጭላዎቹ መልስ አልነበራቸውም። “እኛ ኢትዮጵያውያን ካልሆንን ማነው ታዲያ ኢትዮጵያዊ?” መልስ አልነበረም። ማኒፌስቶው በሌሎች የወያኔ አመራሮች፣ በሰፊው ታጋይና በትግራይ ህዝብ ፈጽሞ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።

በዚህ ማኒፌስቶ ምትክ ህወሃት ሌላ ሰነድ ይዞ ብቅ አለ። በዚህ ሰነድ “ወያኔ በኢትዮጵያ ውስጥ ለትግራይ ህዝብ ብሄራዊ እኩልነት የሚታገል ድርጅት እንደሆነ” ተነገረ። ሆኖም ግን የእኩልነቱ ጥያቄ መልስ የማያገኝ ከሆነ፣ ወያኔ “ትግራይን ገንጥሎ ሃገር የመመስረት መብት” ያለው መሆኑን አዲሱ የድርጅቱ ፕሮግራም በማያሻማ ቋንቋ ግልጽ አድርጓል። የ1968ቱን ማኒፌስቶ የተካው የወያኔ የድርጅት ፕሮግራም አቀራረቡ እንጂ ይዘቱ የእነመለስና የስብሃት ነጋን የነጻ ሃገርና ሪፐብሊክ ምስረታ ህልም እንደያዘ ነበር። ወያኔ በትግል በቆየባቸው 17 እና ቀጥሎም ስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 አመታት ሲመራ የነበረው አማራን በቅኝ ገዥነት በፈረጀበትና ትግራይን ነጻ ማውጣት የሚለው ህልሙን ባሰፈረበት የ1968ቱ ማኒፌስቶ አማካኝነት እንደነበር የሚያሳዩ በቂ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።
በቦታው የምንመለስበት ቢሆንም፣ የትግራይን ግዛት በአማራና በአፋር ህዝብ የግዛት ኪሳራ ማስፋት፣ ልዩነትን መሰረት ያደረገና የመገንጠልን መብት የሚፈቅድ ህገ መንግስት መደንገግ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በዘር ከፋፍሎና በጥላቻ እርስ በርሱ እንዲጠራጠርና እንዲናቆር የሚያደርግ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ስርአት መዘርጋት፣ በተለይ ለነስብሃት ነጋ ኢትዮጵያን የማፈራረስና ትግራይ የምትባል ነጻ ሃገር ምስረታ ህልም እንቅፋት ይሆናል ያሉትንና “ቅኝ ገዥ” በማለት የፈረጁትን አማራ ነጥሎ የሚያዳክም ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ጥቃቶችን መፈጸም፣ ቁልፍ የሆኑ የወታደራዊ፣ የደህንነትና ሌሎችን መንግስታዊ ተቋማት በወያኔዎች ቁጥጥር ስር ማዋል፣ በመንግስት እና በግል የተያዘውን የሃገሪቱ ኢኮኖሚ በጥቂት የወያኔ አባላትና ከወያኔ ጋር ቅርበት ባላቸው ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ማስያዝ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ አጥንቱ እስከሚቀር በመጋጥ፣ ሃብቱን መዝረፈና ከሃገር ማሸሽ፤ ወያኔ ለ27 አመታት ያለ እረፍት ያከናወናቸው ድርጊቶች ናቸው። ርእዮተአለማዊ መሰረታቸው የ1968ቱ ማኒፌስቶ ነው።

እነዚህን ድርጊቶች በደንብ ላጤናቸው አንድ የውጭ ወራሪ አንድን ሃገር በቅኝ ሲይዝ በተግባር የሚያውላቸው እንጂ በእኩልነት በአንድ ሃገር ውስጥ ለመኖር የወሰነ የአንድ ድርጅት ተግባራት እንዳልሆኑ ግልጽ ነው። ይህ ማኒፌስቶ 1968 አም ላይ ተቀብሮ እንዳልቀረ፣ መስከረም 30 2013 አም ወያኔ ያወጣውን የ86 ገጽ፣ ኢትዮጵያን የማፈራረስና የትግራይን ሃገር የመመስረት የስትራተጂ ሰነድ ማየት ብቻ በቂ ነው። ልዩነቱ በ1968 አም ወያኔ፣ “ትግራይ የኢትዮጵያ/አማራ ቅኝ ነበረች” ባለበት ወቅት በትግራይ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው የህዝብና የትግራይ ልሂቃን ሰፊ ተቃውሞ ዛሬ አለመኖሩ ብቻ ነው።

“ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል እንወርዳለን” የሚል ንግግር የሚናገሩና “ኢትዮጵያ ስትፈርስ ለማየት የሚያስችል ዘመን ውስጥ በመፈጠራቸው እድለኛ እንደሆኑ በአደባባይ የሚናገሩ የእነመለስና የስብሃት ጸረ ኢትዮጵያ ቫይረስ ተሸካሚዎች በሃገር ውስጥና በውጭ ሃገራት የተበራከቱበት ዘመን ላይ ደርሰናል። ይህ ሃቅ የትግራይን ህዝብ ከገዛ ታሪኩና ማንነቱ ጋር የተጣላ ለማድረግ በ1968 የተጀመረው ስራና ሴራ ምን ያህል እንደተሳካ የሚያሳይ ነው። ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ይህን ሃቅ አሳንሶ ማየት ማንንም አይጠቅምም።
ከላይ የጠቀስኩት 86 ገጽ ሰነድ ወያኔ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ ከአንድ ወር በፊት የተዘጋጀ ስለሆነ ከዛ በኋላ የተገደሉትና ዛሬ በእስር ቤት የሚገኙት እነስብሃት ነጋ፣ እንዲሁም ከእስራትና ከሞት ያመለጡት እነደብረጽዮን እና ጻድቃን በጋራ የመከሩበትና ውሳኔ ያሳለፉበት እንደሆነ ይታወቃል። በፕሮፓጋንዳ ደረጃ ከአማራ ህዝብ ጋር ሂሳብ እናወራርዳለን ከሚለው የወያኔዎች ድንፋታ አንስቶ በተግባር በአማራ ህዝብ ላይ ወያኔዎች እያካሄዱት ያለው ወረራ፣ ጭፍጨፋ፣ ዘረፋና ውድመት ወያኔዎች “ቅኝ ገዥ” ያሉትን አማራ ለመበቀል ከ40 አመታት በላይ የተዘጋጁበት መርሃ ግብር አካል እንደሆነ ይህ ሰነድ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

ወደ ተነሳንበት ቁም ነገር ስንመለስ፣ የ1968ቱን ማኒፌስቶ የተካው የህወሃት ፕሮግራም፣ የትግራይ ህዝብ ለዘመናት “በአማራ ገዥዎች/ አስከፊ ብሄራዊ ጭቆና እና መደባዊ ብዝበዛ ሲደርስበት እንደነበር በማብራራት ትግሉ በቅድሚያ ከአማራ ብሄራዊ ጭቆና ነጻ መውጣት መሆኑን ይገለጻል። በሂደት እንደታየው ወያኔ ብሄራዊ ጭቆና ወይም ቀደም ብሎ በማኒፌስቶው ቅኝ መገዛት የሚለው ነገር በመሰረቱ ልዩነት የሌላቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ነው።

ቀጥሎ የምንመለከተው የቅኝ ተገዥነት ሆነ የብሄራዊ ጭቆና የወያኔ ትርክት ከአማራ ጋር ሂሳብ ማወራረጃ መነሻ ሆኖ ስለሚቀርብ የሂሳብ ማወራረዱ ስራ ማንን ባለእዳ አድርጎ እንደሚያርፈው ወደማሳየት ነው። ወያኔ ስልጣን ከያዘ በኋላ የተከተለውን ከቅኝ ገዥዎች ያልተለየ ጸረ አማራና ጸረ ኢትዮጵያ ድርጊቶቹን እያስታወሰን ወደዛው እንሻገር።

ኢትዮጵያ የአማኞች ሃገር ናት። ሁለቱም የሃገሪቱ ጥንታዊና ግዙፍ እምነቶች መነሻቸው ወያኔዎች “የኛ” ከሚሉት መሬትና “የኛ” ከሚሉት ታሪክ ጋር የተሳሰረ ነው። ክርስትናም ሆነ እስልምና በመላው ኢትዮጵያ ለመስፋፋት መነሻው አክሱም ነው። ይህን አይነት የእምነት ሃገራዊ የበላይነት በየትኛውም አለም በቅኝ የተገዙ ወይም በብሄራዊ ጭቆና ስር የወደቁ ህዝቦች ሲያከናውኑት ታይቶ አይታወቅም።

በትግራይ ምድር ወደምትገኘው አክሱም ጺዮን ሄዶ፣ ዘውድ ያልደፋ ንጉስ ወይም ንጉሰ ነገስት ሆኖ የማይታይበትን ለሺ አመታት የዘለቀ መንግስታዊ ስርአት የተከለ አካል ቅኝ ተገዢ ወይም ብሄራዊ ተጨቋኝ እንዴት ሊሆን እንደሚችል ወያኔዎች ሊያስረዱን አይችሉም። ቀደም ብዬ በክፍል ሁለት የጠቀስኩትን ለሽህ አመታት የዘለቀውን በይኩኖ አምላክ የተጀመረው ሰሎሞናዊ ስርወ መንግስት የአክሱም ታሪክና ስልጣኔ ወራሽ ተደርጎ እንዲታይና ርእየተአለማዊ ቅቡልነት እንዲያገኝ የትግራይ ቀሳውስት የተጫወቱትን ወሳኝ ሚና እዚህ ላይ ጨምረን ስንመለከተው እኛ እንደ ወያኔዎች እንጥመም ብንል “መንፈሳዊ ቅኝ ገዥዎቹ ብሄራዊ ጭቆና ፈጻሚዎቹ” አማሮች ሳይሆኑ የወያኔ ቀደምቶች ነበሩ ማለት እንችላለን። ታሪክ ውስብስብ ነውና እኛ እንደዛ አንልም። ከወያኔ ትርክት ይልቅ ለእውነታው የሚቀርበው የኛ ሃቅ መሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል። ይህን ጉዳይ አሳንሰን ማየት የለብንም። ለሽህ አመታት የዘለቀ የአንድን ሃገር መንፈሳዊና ርእዮተአለማዊ ህይወት የተቆጣጠሩ እሴቶችና እይታዎች ዋና ባለቤት ተሁኖ “ቅኝ ተገዛሁ፣ በብሄራዊ ጭቆና ስር ወደቅሁ” የሚል ይሉኝታ ቢስ ክርክር ቦታ የሌለው መሆኑ የሚያሳይ ነውና።

ወያኔዎች ይህን ስንላቸው ክርክራቸውን ቁሳዊ ወደ ሆነው አለም መመለሳቸው አይቀርም። ቀጥሎ አጠር ባለ መልኩ የምንፈትሸው ይህንን ነው። ወያኔዎች “እራሳችንን በራሳችን እንዳናስተዳድር ተደርገናል። ቋንቋችን ባህላችን እንዳያድግ ተደርጓል። በኢኮኖሚ ተበዝብዘናል ብሄራዊ ጭቆና የምንለው ይህን ነው” ይሉናል። ይህ የጭቆና ታሪክ በ2013ቱ የመስከረም ወር ሰነድ ላይ ተጽፎ እናገኘዋለን።

በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን፣ የመጀመሪያው የወያኔ አመጽ በከሸፈበት ማግስት ራስ አበበ አረጋይ ለአጭር ጊዜ የትግራይ የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳዳሪ ሆነው ተሹመው ነበር። ራስ አበበ አረጋይ በወያኔዎች የዘር መነጽር ሲታዩ የተዋቂው ኦሮሞ የምኒሊክ የጦር መሪ የነበሩት የእውቁ የራስ ጎበና ዳጬ የልጅ ልጅ መሆናቸውን ማስታወሱ ተገቢ ነው። ከዚህ ወቅት በስተቀር ትግራይ ከራሷ መኳንንቶች፣ መሳፍንቶች ወይም ንጉሶች ውጭ ከሌላ አካባቢ በመጡ የመንግስት ባለስልጣናት ተገዝታ ወይም ተዳድራ አታውቅም። በደርግ ጊዜ ሳይቀር የትግራይ አስተዳዳሪዎች የትግራይ ተወላጆች ወታደራዊ መኮንኖች ነበሩ። ከደርግ ውድቀት የመጨረሻዎቹ ጥቂት ወራት በስተቀር።

በጣም የጥንቱን ትተን፣ ከዘመነ መሳፍንት መግቢያ ጀምሮ ያለውን ዘመን ስንመለከት እንደ ራስ ሚካኤል ስሁል አይነቶች የትግራይ መሳፍንት እንዳሻቸው ጎንደር ላይ ማን እንደሚነግስና እንደማይነግስ ይወሰኑ እንደነበር ይታወቃል። ወያኔዎች ኢትዮጵያ የሚባል “ኢምፓየር አጼ ምኒሊክ በጉልበት ፈጠሩት” ከሚሉበትና ወሳኝ ከሆነው የታሪክ ወቅት ስንነሳ የምናገኘው ስእል ወያኔዎች ሊያሳምኑን ከሚሞክሩት በጣም የተለየ ነው። አጼ ምኒሊክ ሆኑ አጼ ሃይለስላሴ ልጆቻቸውን ለትግራይ መሳፍንትና መኳንንት እየዳሩ የትግራይን ሃገረ ገዥነት ከትግራይ ተወላጆች ውጭ እንዳይወጣ አድርገው በከፍተኛ ክብርና እንክብካቤ የያዙበት ሁኔታ እንጂ ትግራይን የሚያሳንስ ወይም የሚበድል ስራ ሲሰሩ ታይቶ አይታወቅም። ምኒሊክ ልጃቸውን ሸዋረጋን ለአጼ ዮሃንስ ልጅ፣ አጼ ሃይለስላሴም ልጃቸውን ልእልት ዘነበወርቅን ለደጃዝማች ሃይለስላሴ ጉግሳ አርአያ ድረው እንደነበር ይታወቃል። የመጨረሻው የትግራይ ልኡል የራስ መንገሻ ስዩም ባለቤት የአጼ ሃይለስላሴ የልጅ ልጅ ልእልት አይዳ ደስታ እንደነበሩ ማስታወስ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ነገስታት የትግራይ መሳፍንት ግንኙነት በእኩዮችና በአቻዎች አመለካከት እንጂ በቅኝ ገዥና ተገዥ፣ በብሄራዊ ናቂና ተናቂ ዙሪያ የተገነባ እንዳልነበር ከዚህ በላይ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም። የነበረውን እውነታ በጥቅሉ ስናየው፣ በአስተዳደራዊ ተጽእኖ ፈጣሪነት፣ ትግራይ በህዝብ ብዛትም ይሁን በኢኮኖሚ ለሃገሪቱ ከምታዋጣው በላይ የፖለቲካ ተጽእኖ ፈጣሪ የነበረች መሆኗን ነው።

ይህን የሚያነቡ ወያኔዎች፣ “እኛ የምናወራው ስለመሳፍንቱና መኳንንቱ ግንኙነት አይደለም” እንደሚሉ እናውቃለን። ከነገስታቱ፣ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ በታች ወዳለው የህብረተሰብ ክፍል ስንወርድም የምናገኘው ሃቅ የወያኔ የጭቆና ትርክት ሃሰት መሆኑን ነው። የትግራይ ገበሬ በሌሎች የሃገሪቱ ግዛቶች እንደነበሩ ገበሬዎች ለማእከላዊ መንግስት እንዲገብር ወይም በጭሰኝነት እንዲወድቅ አልተደረገም። ገዥዎቹ በሙሉ የራሱ የትግራይ መሳፍንቶችና መኳንንቶች ነበሩ። የሚገብረውም ለነሱ ብቻ ነበር። ለመሳፍንት የመገበር ስርአት ከሆነ ወያኔዎች የሚጠሉት “ቅኝ ገዥ” የሚሉት የአማራ ህዝብ የቀረለት ጉዳይ አልነበረም። ድህነት፣ የአስተዳደር በደል፣ የፍትህ እጦት የትግራይ ህዝብ እንደ አማራ ህዝብ የዘመናት እጣው ነበር። ይህ የሰቆቃ ህይወት የሁለቱም ህዝቦች የጋራ እጣቸው እንጂ ወያኔዎች እንደሚሉት የተለየ የትግራይ ህዝብ እጣ ብቻ አልነበረም።

በ1981አም ወያኔ ከትግራይ ወጥቶ በአማራ ግዛት በስፋት መንቀሳቀስ ሲጀምር ታጋዮችን ያስገረማቸው ነገር የአማራ ህዝብ እንደ ትግራይ ህዝብ በድህነት የተቆራመተ፣ ከቋንቋ ልዩነት በስተቀር፣ በእምነቱ፣ በባህሉ፣ በአኗኗሩ፣ በአስተራረሱ በሁለመናው ከትግራይ ህዝብ ጋር አንድ እንደሆነ በመገረም ተናግረዋል። እንዳውም በጆሮዬ የሰማሁት የዛን ዘመን የወያኔ ታጋዮች ትዝብት የአማራ ህዝብ ከትግራይ በከፋ ሁኔታ የሚኖር ሆኖ እንዳገኙት ነበር። ለዚህ የሰጡት ምሳሌ የትግራይ ገበሬ በድህነት የተቆራመተ ቢሆንም ለእግሩ መጫሚያ የነበረው ሲሆን የአማራ ገበሬ ግን በባዶ እግሩ የሚሄድ እንደሆነ ነበር። (የጫማ ጉዳይ ጣሊያኖች በኤርትራ ካስፋፉት ባህል ወደ ትግራይ የዘለቀ መሆኑ ይታወቃል።) እነዚህ የወያኔ ታጋዮች በወያኔ ፕሮፓጋንዳ የተነገራቸው ጠላታቸው አማራና በመሬት ላይ ያገኙት አማራ አንድ እንዳልሆነ በወቅቱ በአደባባይ ሲናገሩ ስምተናቸዋል።

እንግዲህ አንድ በወያኔዎች እጅ የቀረ ጉዳይ የቋንቋ ጉዳይ ነው። በቋንቋ ቢሆንም አማርኛና ትግርኛ አንድ አይነት ፊደል የሚጠቀሙ፣ ከአንድ ግንድ የተመዘዙ ናቸው። የአማርኛ ቋንቋ ሃገራዊ ቋንቋ በመሆን የበላይነት ማግኘት የጀመረበት ዘመን ሩቅ ሲሆን ሂደቱም ከሴራ ጋር የተያያዘ አልነበረም። እንኳን ከሰማኒያ በላይ ቋንቋዎች በሚነገሩባት የአሁኒቱ ኢትዮጵያ ቀርቶ፤ ኢትዮጵያ ቁጥራቸው አናሳ የነበሩ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በነበሩበት ወቅት ሳይቀር ሃገራዊ የስራ ቋንቋ ሳይኖር እንደ ሃገር መቆም አትችልም ነበር። ስልጣን ለመያዝ እድል ያገኙ እንደነ አጼ ዮሃንስ አይነቶቹ ሳይቀሩ ይህን ሃቅ በመረዳታቸው ነው፣ አማርኛን የስራ ቋንቋቸው አድረገው የቀጠሉት።
አማርኛ ኦፊሴሊያዊ ሃገራዊ ቋንቋ በመሆን ተጽእኖ ካደረገባቸው ሌሎች የሃገራችን ቋንቋዎች ጋር ሲነጻጸር በጣም አነስተኛ ተጽእኖ ያረፈበት ቋንቋ ትግርኛ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ስለዚህም ወያኔዎች የፈጠሩት የሃሰት ትርክት ሲከሽፍባቸው የመጨረሻ መንጠልጠያ ሊያደርጉት የሚሞክሩት የቋንቋ ጉዳይም የትም አያደርሳቸውም። ወያኔዎች “ቅኝ ገዥ፣ ደመኛ የትግራይ ጠላት” እያሉ ሂሳብ በማወራረድ ስሌት ዘር ማንዘሩ እንዲጠፋ እኩይ ድግስ የሚደግሱለት፣ በዘሩ ተለይቶ በየቦታው እንዲታረድ ጠላት የሚያደራጁለት፣ የሚያስታጥቁለት፣ መልካም ስብእናውን ስሙን የሚያራክሱት አማራ የሚባል ህዝብ እውን ወያኔዎች እንደሚስሉት የትግራይ ህዝብ ስትራተጂያዊ ጠላት ነውን? በሚቀጥለው ክፍል ከሁሉ አስከፊ ወደሆነው የወያኔ ዘመን ጠጋ ብለን የሂሳብ ማወራረዱን ስራ እንቀጥላለን። ይህ ዘመን ከሌሎቹ ሁሉ የከፋ፣ ብዙዎቻችን በወሬ ወይም በታሪክ የምናውቀው ብቻ ሳይሆን የኖርንበት ዘመን ነው። በቸር እንገናኝ።

ክፍል አራት

ከወያኔዎች ጋር ሂሳብ አወራርዶ ወያኔን ለዝንተአለሙ የመቅበር አስፈላጊነት (ክፍል 4)

ታሪክን በሚገባ ለፈተሸ፤ ኢትዮጵያ ግዛቷ ሲጠብና ሲሰፋ ለሺ አመታት በዘለቀው ፈታኝ ጉዞዋ፤ አንድ ላይ ሲንገታገቱ፣ ሲወድቁና ሲነሱ አብረው ከዘለቁ ጥቂት የተለያዩ ማህበረሰቦች መካከል በዋንኛነት የሚጠቀሱት አማሮችና ትግሬዎች ናቸው። በእምነት፣ በባህል፣ በትውፊት፣ በስነልቦና፣ በአካላዊ ቁመና፣ በአለባበስ፣ በአመጋገብ፣ በአኗኗር እንዲሁም በአመራረት ዘይቤ ይህ ነው የሚባል ልዩነት የሌላቸው እነዚህ ሁለት ማህበረሰቦች፤ በጋራ በመፈተን፣ በጋራ በመውደቅና በጋራ በመነሳት፣ እንደ ታላቅና ታናሽ ወንድማማቾች/እህትማማቾች (ማን ታላቅ ማን ታናሽ እንደሆነ አልተናገርኩም) ለረጅም ዘመናት በአንድ ላይ ኖረዋል። ስለ ሁለት ማህበረሰቦች የማንነት ተመሳሳይነት እንነጋገር ቢባል ከእነዚህ ሁለት ህዝቦች ይበልጥ የሚቀራረብ አይኖርም።
ሆኖም ግን “ወያኔ” የሚባል ድርጅት ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ አማራ የትግራይ ህዝብ ዋንኛ ጠላትነት ሆኖ ተፈረጀ። ይህ ፍረጃ በብዙ ሰው አእምሮ ውስጥ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ማስነሳቱ ይታወቃል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ስንል በተከታታይ ጽሁፎች ብዙ ነገሮችን ፈትሸናል። በመጨረሻም ወያኔዎች ከኢትዮጵያ ታሪክ ኩነቶችን እየመዘዙ “በአማራ ተበድለናል” በሚል በትግራይ ህዝብ ውስጥ ያሰራጩት ትርክት፤ አይን ባወጣ ቅጥፈትና ይሉኝታቢስነት የተሞላ መሆኑን ማየት ችለናል። ቀጥለን የምንሸጋገረው ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በህይወት ያሉ ወገኖቻችን ምስክርነታቸውን መስጠት ወደሚችሉባቸው ጉዳዮች ይሆናል። የሂሳብ ማወራረዱ ስራም የሚቀጥለው በዚሁ አግባብ ይሆናል።
ወያኔ ከ1966 አም አብዮት መፈንዳት ጋር ተያይዞ የተመሰረተ ድርጅት ነው። መሪዎቹ፤ በእድሜም፣ በልምድም፣ በእውቀትም፣ እንጭጮች ነበሩ። በተለይ ወደኋላ ጎላ ብለው የወጡት፤ በወቅቱ ከ25 አመት እድሜ በታች ነበሩ። ከስብሃት ነጋ ውጭ 30 አመት እድሜ የነበረው መሪ አልነበራቸውም። በእድሜ የገፉ፣ ልምድና እውቀት የነበራቸው የትግራይ ተወላጆች ሙሉ በሙሉ ሃገር አቀፍ በሆኑ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ በስፋት የሚሳተፉ ነበሩ።
እንደ ኢህአፓ (ኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ) አይነቶቹ የ66 አብዮት ወደ አደባባይ ያወጣቸው ግዙፍ የፖለቲካ ድርጅቶች በርካታና ከፍተኛ የትግራይ ምሁራንን ያካተተ ነበር። ከዛም ተሻግሮ ወሳኝ የነበሩት ብዙዎቹ የድርጅቱ የአመራር ቦታዎች በትግራይ ምሁራን የተያዙ ነበሩ።
በኢህአፓ ውስጥ ሁሉም የኢትዮጵያ ምሁራን እና ወጣት ተማሪዎች ዘርን ሳይለዩ በመቶ ሽዎች እንደተሳተፉ እናውቃለን። በዛሬው የወያኔ የዘር መነጸር እንመርምረው ቢባል አብዛኛው የኢህአፓ አባላት የብሄረሰቦች ውህድ እና አማሮች ነበሩ። እነዚህ የኢህአፓ አባላት፤ የድርጅቱ ከፍተኛ መሪዎች አብዛኛዎቹ ትግሬዎች መሆናቸው አሳስቧቸው አያውቅም። ለእነዚህ መሪዎች ይሰጡት የነበረው ክብር፣ ፍቅርና ታማኝነት ወጣቶች የበቀሉበትን ማህበረስብ ቀናነትና የስብእና እድገት የሚያንጸባርቅ ነበር። እዚሁ ላይ በኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ዝነኛ የነበሩ በርካታ የተማሪ መሪዎች የትግራይ ተወላጆች የነበሩ መሆናቸውን እና አንዳንዶቹ በትግሉ ወቅት ለከፈሉት መስዋእትነት ተማሪው በጣኦት ደረጃ ያመልካቸው እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ነው።
ወያኔ ለአማራ ካለው ጥላቻ ይህን በከፍተኛ የትግራይ ምሁራን ሲመራ የነበረን ድርጅት፤ የአማራ ድርጅት፣ ትግርኛ ተናጋሪ ከፍተኛ መሪዎቹንም የሸዋ ትግሬዎች፣ የአማራ ቡችላዎች (ኩርኩር አምሃራ) የሚል ስም በመስጠት ነው ህወሃትን የመሰረተው። ኢህአፓ “ታላቂቱ ኢትዮጵያ (አባይ ኢትዮጵያ)” የሚል “አጭበርባሪ የአማሮች ድርጅት ነው” በማለት ወያኔ በትግራይ ውስጥ ሲያካሂድ የነበረውን ፕሮፓጋንዳ ሁላችንም እናስታውሰዋለን። “ታላቋ ኢትዮጵያ ባዮች እነዛ ብልጣብልጦች አሲምባ ተቀምጠው ለጭቁን ነን ባዮች፣ (“አባይ ኢትዮጵያ እቶም ተበለጽቲ አሲምባ ኮፍ ኢሎም ንውጽኡ በአልቲ” ) በትግራይ ገጠሮች በኢያሱ በርሄ የምትመራው የወያኔ የባህል ክፍል ከበሮ እየደለቀች ታጋዩን ስታስጨፍርበት የነበረ ሙዚቃ እንደነበር እናስታውሳለን።
ይህ የወያኔ አመለካከት፤ ውሎ አድሮ ከመላው ኢትዮጵያ የደርግን የቀይ ሽብር እርምጃ፣ እስራትና ሰቆቃ አምልጠው ትግራይ አሲምባ በሚባል ቦታ ላይ ተሰባስበው በነበሩ የኢህአፓ ታጋዮች ላይ ወያኔ ጦርነት እንዲያውጅ አድርጎታል። ከደርግ ጥይት በስንት መከራ ያመለጡ ወጣቶች በትግራይ ምድር በወያኔ ጥይት ያለቁት፣ ኢህአፓን “የአማራ ድርጅት” ብሎ በመፈረጁና በአማራው ላይ ከቋጠረው ጥላቻ በመነሳት ነው። እግረ መንገዳችንን ወያኔ “የአማራ” የሚል ታርጋ ለሁሉም “ኢትዮጵያ” የሚል ስም ላላቸው የፖለቲካ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ መንግስታት መለጠፍ ልማዱ ነው። ከየትኛው ብሄር ምሁርና ተማሪ ይልቅ በደርግ ጥይት ያለቀው የአማራ ምሁርና ተማሪ ሆኖ ሳለ ደርግ ሳይቀር ለወያኔ የአማራ መንግስት ነበር። ዛሬም ለወያኔዎች የዶ/ር አብይ መንግስት የአማራ መንግስት ነው። ወያኔ ለአማራ ህዝብ ያለው ጥላቻ ወደ እብደት እየመራው እንደሆነ ማስረጃው የኤርትራን መንግስትና ፕሬዚደንቱን ኢሳያስ አፈወርቂን ሳይቀር የአማራ አጀንዳ አስፈጻሚዎች አድርገው እነጻድቃን እና ጌታቸው ረዳ እየለፈፉ መሆኑ ነው።
ሃቅ ስለሆነ የምንነጋገረው፤ አማራው የሰዎችን ዘር ሳይመለከት፣ ሰዎች የቆሙለት አላማ ቀና ነው ብሎ እስካመነ ድረስ መሪነታቸውን ለመቀበል ችግር የሌለበት ህዝብ መሆኑን በተደጋጋሚ በታሪኩ ያሳየ ሲሆን ወያኔዎች ግን ከሰው መልካምነት ይልቅ የዘሩ የትግሬ ጥራት የሚያሳስባቸው እንደሆነ ነው። ወያኔዎች ግን ሁሌም የራሳቸው ዘር የበላይነት ባልያዘበት፣ በዘር የመጠቃቀም እድል በማይፈጥርላችው ማናቸውም የሰዎች ስብስብ ውስጥ በእኩልነት መሳተፍ የማይፈልጉና የማይችሉ ኋላቀር ፍጥረቶች ናቸው። ባለፉት 27 አመታት በተግባር የፈጸሙት ይህንኑ ነው። ከለውጡ በኋላም በእኩልነት ለመኖር የተፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ መጠቀም አቅቷቸው የኢትዮጵያን ህዝብ አላስፈላጊ ወደ ሆነ ግጭት የጎተቱት ለዚህ ነው።
“ትግራይ ለትግሬዎች ብቻ” በሚል ብሂል ወያኔዎች ከትግራይ ምድር ወግተው ያስወጡት ኢህአፓን ብቻ ሳይሆን ሌላውን ኢትዮጵያ በሚል ስም ሲንቀሳቀሰ የነበረውን ኢዲህን (ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት) ነበር። ሆኖም ግን ወያኔዎች ይህን አድርገው ከትግራይ ወጥተው በአማራ መሬቶች ውስጥ ያለምንም ይሉኝታ ለመንቀሳቀስ ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ወቅቱ የአማራ ህዝብ በደርግ ላይ የተማረረበት ወቅት ስለነበር፣ ወያኔዎችም “ያስመረረህን ደርግ በጋራ ታግለን እንጣለው” በማለታቸው የአማራ ህዝብ ከጥቂት አመታት በፊት ወያኔዎች “ትግራይ ለትግራይ ብቻ” በሚል ብሂል በአማራ ተወላጆች ላይ የፈጸሙትን ግፍ በማስታወስ ቂም ይዞ ወግዱ አትድረሱብኝ አላላቸውም። ቂም ያልያዘው ወያኔዎች እንደሚያስቡት እነሱ ስላሞኙት አልነበረም። አማራው የመቻል፣ የመታገስ፣ ለሰዎች ስህተት የራሱን ምክንያት በመደርደር ጥፋታቸውን የማሳነስ፣ “ስላልገባቸው ነው፤ ባያውቁት ነው። በሂደት ይማራሉ” የሚል የባህል መሰረት ያለው ህዝብ በመሆኑ ብቻ ነበር። የቅርቡን ሳይሆን የሩቁን፣ ጠባቡን ሳይሆን ሰፊውን፣ መንደሩን ሳይሆን ሃገሩን እያሰበ፣ የአማራ ህዝብ ልጆቹን በታጋይነት ከወያኔ ጎን አሰልፎ፣ በጉልበቱና በሃብቱ እያገዘ፣ የወያኔን አቅም አጠናክሮ የደርግን ውድቀት በማፋጠን አዲስ አበባ እንዲገቡ አደረገ። ለእንዲህ አይነቱ የአማራ ህዝብ ቀና እና ወገናዊ ድጋፍ የወያኔ ምላሽ ምን ሆነ? (በነገራችን ላይ የአማራ ህዝብ ትብብር ባይገኝ ወያኔ እንኳን አዲስ አበባ መግባት አይደለም ነጻ አወጣሁት የሚለውን ትግራይ ይዞ የመቀጠል እድል እንዳልነበረው መገንዘቡ ተገቢ ነው። ወያኔ አዲስ አበባ የመግባቱን ሃቅ ከአማራ ህዝብ ትብብር ገንጥሎ ወርቅ በሆነው የትግራይ ጀግና ሰራዊቱ ተጋድሎ እንደሆነ ደጋግሞ ለራሱ በመናገሩና ራሱን በማሳመኑ ተከታታይ ለሆኑ ውርደቶች ራሱን አጋልጧል። አሁንም “በጀግኖች የትግራይ ተዋጊዎቼ አዲስ አበባ እገባለሁ” የሚል ቅዥት ውስጥ የወደቀው ወያኔ በታሪኩ ላገኛቸው ድሎች የአማራን ህዝብ ወሳኝ ሚና በመዘንጋቱ ነው።)
ሃተታ ላለማብዛትና ለሂሳብ ማወራረዱ እንዲቀል የአማራ ህዝብ ወያኔን አቅፎና ደግፎ አራት ኪሎ ቤተ መንግስት ካስገባ በኋላ በልዋጩ በወያኔ ለውለታው የተከፈለው በጥላቻ መርዝ የተለወሰ ክፍያ ምን እንደሚመስል በተራ ቁጥር እንዘረዝረዋለን።
1) በብዙ ሃገራዊ መስዋእትነት፤ ብዙ ዘመናትን ለግንባታ የወሰደውን፤ በህብረ ብሄራዊነቱ ወያኔ ከፈጠረው የራሱ መከላከያ ሃይል የላቀ የነበረውን፤ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሃይል “የአማራ መንግስት መከላከያ ሃይል ነው” በሚል ሰበብ ሙሉ በሙሉ በማፍረስ፣ በተለያዩ አውደ ውጊያዎች ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ሃገራዊና ህዝባዊ ግዴታውን ሲወጣ የነበረውን ሰራዊት በመበተን፣ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የሰራዊቱን አባላት የጎዳና ተዳዳሪ እንዲሆኑ ማድረግ፣
2) ወያኔ እራሱን ነጻ አውጪ፣ የብሄሮች፣ የቋንቋ፣ የእምነት እኩልነት አምጪ አድርጎ በማቅረብ፤ እንዲህ አይነቱን የእኩልነት ጥያቄ የሚጻረሩ አማሮች ናቸው የሚል የሃሰት ትርክት (የሃሰት ትርክት የምንለው በኢትዮጵያ ወስጥ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት እንዲዘረጋ፣ የቋንቋ፣ የእምነት የባህል እኩልነት በኢትዮጵያ እንዲሰፍን፣ ገባርነትና ጭሰኛነት እንዲወገድ ኢትዮጵያ ለሁሉም ዜጎቿ የምትመች የበለጸገች ሃገር እንድትሆን በኢትዮጵያ ታሪክ የአማራ ምሁርና ተማሪ የከፈለውን መስዋእትነት ያክል የሌሎች ብሄርና ብሄረሰቦች ምሁራን እና ተማሪዎች እንዳልከፈሉ ስለምናውቅ) በመላው ሃገሪቱ በሚገኙ ማህበረሰቦች ውስጥ በማሰራጨት፣ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተበትኖ የሚኖረው አማራ፣ በሌሎች ወገኖቹ በጥላቻ አይን እንዲታይ፣ የአሰቃቂ ግድያዎች፣ የዘረፋ፣ የመፈናቀል ሰለባ እንዲሆን ማድረግ ነው። (እዚህም ላይ ቀደም ብሎ ኢህዴን በኋላ ብአዴን የሚል ስም የወሰደው የነታምራት ላይኔ ድርጅት ከወያኔ ጋር በመደመር ታሪክ የማይረሳውን ጸረ አማራ ድርጊት መፈጸሙን ማስታወስ ይገባል።) ይህ የግድያ፣ የዘረፋ፣ የማፈናቀል ድርጊት ወያኔ ስልጣን ከመያዙ ጥቂት አመታት በፊት ጀምሮ ከሰላሳ ለሚበልጡ አመታት የዘለቀ ሆኗል።
3) የአማራ ህዝብ በተገቢ ደረጃ በሃገራዊና በራሱ ክልል ጉዳይ ሳይቀር ትልቅነቱን እና ማንነቱን የሚመጥን ውክልና እንዳይኖረው በማድረግ፣ ከሃገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገለል ማድረግ፤ ህገ መንግስቱ ሲረቅ ሁሉም ብሄረሰቦች ሲወከሉ የአማራ ህዝብ ያለ ውክልና እንዲቀር፣ ህገ መንግስቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በመላው ሃገሪቱ የሚኖሩ አማሮችን ሃገር አልባ፣ ንብረት አልባ፣ መብት አልባ ያደረገ መንግስታዊና ክልላዊ አወቃቀር እንዲኖረው ማድረግ፤ ወያኔ የአማራ ህዝብ ላሳየው ቀናነት ከሰጣቸው እኩይ ምላሾች መካከል መጠቀስ የሚገባቸው ናቸው።
4) በጉልበት አስቀድሞ ወያኔ የያዛቸውን፤ ነባር የአማራ ህዝብ መኖሪያዎችን ህገ መንግስታዊ ሽፋን በመስጠት በአዲስ መልክ ለተደራጁ ክልሎች በማከፋፈል፣ የአማራ ህዝብ መልካምድራዊ አሰፋፈሩን በማጥበብ ብዛቱንና አቅሙን ማሳነስ፤ ወያኔ ወልቃይትና ራያን በትግራይ ስር ሲያካልል አላማው ትግራይ ነጻ ሃገር ስትሆን በምግብ ራሷን እንድትችል በሚል እሳቤ ብቻ ሳይሆን አማራውን የማዳከሚያ ስትራተጂ ጭምር ነው። መተከልም ወደ ቤንሻንጉል የተካለለው ወያኔ ለአማራ ካለው ጥላቻና የማዳከም እቅድ የተነሳ ነው።
5) ወያኔ በአካዳሚክ ተቋማት፣ በንግድ ስራ መስክ፣ ቁልፍ በሆኑ የፌደራል መንግስታዊ ስልጣኖች፣ በውጭ ሃገርና በአለም አቀፍ ድርጅቶችና ሌሎች ተቋማትና የስራ ዘርፎች ውስጥ ብቃትና ችሎታ ያላቸው አማሮች እንዳይገኙ፣ ቁጥራቸው እንዲመናመን ጥላቻን ነዳጁ አድርጎ በ27 አመታት የስልጣን ዘመኑ ሲሰራው የቆየ እኩይ ተግባሩ ነው። በ2002 አም እኔው ራሴ ባጠናሁትና በመረጃ አስደግፌ ባቀረብኩት ጥናት “የኢትዮጵያ” የሚል ስም በተሰጠው ምኑም ኢትዮጵያን በማይመስለው የመከላከያ ተቋም ውስጥ የሚገኙ 42 የክፍለ ጦር አዛዦች ውስጥ 41 የሚሆኑት ትግሬዎች ሲሆኑ አንድም አማራ የክፍለ ጦር አዛዥ እንዳልነበር ነው። ወያኔ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 42 መምህራንን በ1985 አም ሲያባርር ለምን የሚል ጥያቄ ላነሳነው ሰዎች በወቅቱ የወያኔ ጫማ መጥረጊያ ምንጣፍ የነበሩት እነታምራት ላይኔ፣ ዳዊት ዮሃንስና ተፈራ ዋልዋ የመሳሰሉ የኢህዴን መሪዎች የሰጡን ምላሽ “ትምክህተኞች አማሮች ስለሆኑ ነው” የሚል እንደነበር እናስታውሳለን። የአማራ ባለሃብቶች ጥንትም ብዙ ከማይሳተፉበት የንግድ እንቅስቃሴ ለማስወጣት፣ ለማቀጨጭ በወያኔ ያልተሸረበ ሴራ ያልተሰራ በደልና ግፍ የለም። እዚህ ግባ የሚባል ሃብት የሌለውን የአማራ ህዝብ ምክንያት በማድረግ ገበሬ መሬት የመሸጥ የመለወጥ መብት ሊኖረው ይገባል የሚለውን ሃሳብ መለስ ዜናዊ ሲቃወም “መሬቱን የሚገዙት አማሮች ይሆናሉና አይቻልም” የሚል እንደነበር ለወያኔዎች ልናስታውሳቸው ያስፈልጋል። በሂደት ግን መሬት የመንግስት ነው በሚል ሽፋን የሃገሪቱን ገበሬ ከመሬቱ ያፈናቀሉት የከተማና የገጠር መሬት ለጉድ የዘረፉት ወያኔዎችና ዘመዶቻቸው እንደሆኑ ይታወቃል።
6) ባላፉት 27 አመታት ወያኔ ጥላቻን መሰረት በማድረግ በአማራው ላይ የፈጸመው ጥቃት፣ የአማራ ህዝብ ከተራ ባተሌዎቹ አንስቶ እስከ ከፍተኛ ምሁራኑ ከየትኛውም ብሄር ህዝብ በላይ በገፍ ሃገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ፣ በሰው ሃገር ተዋርደውና ባይተዋር ሆነው እንዲኖሩ አድርጓል። በተለይ እውቀት ተሞክሮ ያላቸው የአማራ ምሁራን በገፍ እንዲሰደዱ፣ በሃገር ውስጥ እንዲገለሉ በማድረግ ወያኔ በሃገር ደረጃ ብሎም በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ሃገሪቱም ሆነ ክልሉ ዛሬ ለሚገኙበት አሳዝኝ ደረጃ ዋናው ምክንያት መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።
7) ወያኔ ስልጣን ሲይዝ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የነበረው የኗሪው የብሄራዊ ተዋጽኦ በደርግ ዘመን ተደርጎ በነበረው ጥናት መሰረት፣ 57 ከመቶው አማራ እንደሆነ የሚያሳይ ነበር። ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የከተማው አማራ ወያኔ ስልጣን ከያዘበት ከቀን አንድ ጀምሮ ጥርስ የተነከሰበት ሆኗል። “አዲስ አበባ ስገባ የሞቀ አቀባበል ያላገኘሁት ከተማው በአማሮች የተሞላ በመሆኑ ነው” የሚል ቂም ወያኔ ይዞ እንደነበር እናስታውሳለን። ወያኔ በ1997 አም ምርጫ በአዲስ አበባ ውስጥ ማንንም ማስመረጥ ባለመቻሉ፤ የዚህ ምርጫ ሽንፈት ምክንያት አማራው ነው ብሎ በማመኑ፤ ከ1997 አም ጀምሮ የአማራውን ቁጥር በከተማው ውስጥ ለማመናመን ብዛት ያላቸውን ትግሬዎች ሆን ተብሎ በተዘጋጀ ፖሊሲ አማካኝነት ከትግራይ እንዲፈልሱ በማድረግ፣ (ከራሳቸው ከወያኔ መሪዎች የሰማነው ግማሽ ሚሊዮን የሚደርሱ) የከተማ ቤቶችንና እና መሬትን የመንግስት የሚያደርገውን ህግ በመሳሪያነት በመጠቀም የቤት፣ የመሬት ባለቤቶች እንዲሆኑ አድርጓል። ነባር የከተማ ኗሪዎችን መሬታቸውን በመቀማት፣ በልማት ስም በማፈናቀል፣ የዘመናት የአብሮነት ህይወት የነበራቸውን የአንድ ሰፈር ሰዎች ከመሃል ከተማ በማንሳት ወደ ከተማው ዳርቻዎች በሁሉም አቅጣጫዎች በመበተን፣ ማህበረሰባዊ አቅማቸውን ለማዳከም ብዙ ነገሮችን ወጥኖ ተግባራዊ አድርጓል። ዛሬ ባለቤት አልባ የሆኑ ከ300 በላይ የሚሆኑ በግንባታ ላይ የሚገኙ ህንጻዎች የቆሙበት መሬትና ሌሎችም ግንባታቸው የተጠናቀቁ በሽዎች የሚቆጠሩ በከተማው እምብርት ላይ በወያኔና በሸሪኮቻቸው የተሰሩ ውድ ሆቴሎችና አፓርትመንቶች የቆሙት አዲስ አበባ ስትመሰረት ጀምሮ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ከኖሩበት ቦታ በወያኔ ሆን ተብሎ እንዲፈናቀሉ በተደረጉ አማሮች ርስት ላይ ነው። “ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” እንዲሉ በከተማው የብሄራዊ ተዋጽኦ 17 ከመቶ ድርሻ በመያዝ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የጉራጌ ማህበረሰብም የአማራ (የነፍጠኛ) ተለጣፊ የሚል ታርጋ በወያኔ የተለጠፈለት በመሆኑ ቤት ንብረቱን የማጣትና የመፈናቀል ሰለባ ሆኗል። ወያኔ ሃጥያተኛ አድርጎ ላየው የከተማው አማራ የመጣው ቅጣት ከጉራጌው ውጭ ላሉት ወያኔ ጻድቃን አድርጎ ለሚያያቸውም የሌሎች ብሄረሰቦች የከተማ ኗሪዎችም አልቀረላቸውም።

ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ካለቀውና ከተፈናቀለው አማራ በተጨማሪ ከ1997 አም ምርጫ በኋላ ወያኔ በወሰደው ሰፊ እመቃ በሚዛን ሲቀመጥ አሁንም ቢሆን ትልቁን የግፍ ገፈት የቀመሰው አማራው ነው። ቅንጅት ህብረ ብሄራዊ ድርጅት እንደሆነ እየታወቀ ወያኔ ቅንጅትን የአማራ “የነፍጠኛ” ድርጅት ብሎ በመፈረጅ በአማራ ክልል፣ በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልል የተካሄደው እመቃ በዋንኛነት በአማራ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነበር። በዚህ ወስጥ የቅንጅት አባላት የሆኑ የሌሎች ብሄረሰብ ተወላጆች አልታሰሩም፣ አልተገደሉም፣ አልተሰደዱም ማለት ሳይሆን ወያኔ ሁሉንም የቅንጅት አባላት የሚያይበት መነጸር በአማራ ጥላቻ የተቃኘ መሆኑን አንርሳ ለማለት ነው። ከዚህ አሳዛኝ ታሪክ ጋር በተያያዘ ከወያኔ ጋር በመተባበር ብዙ አሳፋሪ ስራ የሰሩ አማራዎችን ጨምሮ፤ ከተለያዩ ብሄረሰቦች የተውጣጡ ተላላኪዎች እንደነበሩ እያስታወስን በዝምታ የምናልፋቸው ዛሬ ወያኔ ሂሳብ ለማወራረድ የሚፈልገው ከነዚህ አካላትን ጨምሮ መሆኑን ስለተገነዘብን ነው።
9) ወያኔ እና ዘረፋ፤ በ2015 አም የተባበሩት መንግስታት፣ የቀድሞውን የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ታምቦ ኢምቤኬን በሊቀመንበርነት ሰይሞ፤ ከኢትዮጵያ እየተዘረፈ በሚወጣው ሃብት ላይ ባስደረገው ጥናትና በወጣው ሪፖርት ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ 30 ቢሊዬን ዶላር ከሃገሪቱ ተዘርፎ የወጣ መሆኑን ይገልጻል። ይህ ሃብት ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ በውጭ መንግስታት ለሀገሪቱ ከተሰጠው 30 ቢሊዮን ዶላር ጋር መሳ ለመሳ መሆኑን ሪፖርቱ አስረድቷል። ይህን መረጃ ይዞ የወጣው ፍሮብስ የተባለው ታዋቂ የአሜሪካ መጽሄት ዘረፋው የተካሄደው የሃገሪቱን ስልጣን እና ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ በተቆጣጠረው ጠባብ የገዢ ክሊክ ነው በማለት በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጦታል። ቁም ነገሩ ያለው ሪፖርቱ ላይ ሳይሆን ይህን አይነት አይን ያወጣ ዘረፋ ኢትዮጵያን ከመሰለ ደሃ ሃገር ላይ ማካሄድ ትርጉሙ ምን ያህል አስከፊ መሆኑ በሚገባ ከመረዳቱ ላይ ነው። ብዙ ሰዎች ይህ የተዘረፈ ገንዘብ፣ ስድስት የህዳሴ ግድብ እንደሚያሰራ ወይም በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ዩኒቨርስቲዎች እና ፋብሪካዎች እንደሚያስገነባ፣ ወዘተ በመግለጽ ሃገሪቱ በድህነት እንድትማቅቅ ዘረፋው እኩይ አስተዋጽኦ ያለው ለመሆኑ ለማስረዳት ሞክረዋል። ይሁንና እነዚህ ምሳሌዎች የወያኔን ወንጀል በደንብ ስለማያሳዩ ዘረፋውን በሰብአዊ ዋጋው መለካት አስፈላጊ ነው።

በወያኔ ዘረፋ የተነሳ ስንት ህጻናት በቂ የምግብና የጤና እንክብካቤ ባለማግኘታቸው አለቁ? ስንት እናቶች በአቅራቢያቸው የማዋለጃ ስፍራዎች ባለማግኘታቸው ህይወታቸው አለፈ? ስንት ዜጎች በቀላሉ ሊፈወሱ ከሚችሉ በሽታዎች ወይም ሊድኑ ይችሉ ከነበሩ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መዳን ሳይችሉ ቀሩ? ስንት ቤተሰቦች በንጹህ የመጠጥ ውሃ ፣ በኤሌክትሪክ ፣ በትራንስፖርት አለመኖር፣ ኑሯቸው የስቃይና የመከራ እንዲሆን ተደረጉ? እነዚህ እና ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት ነው፤ የወያኔን የዘረፋ የግፍ ለከት እውነተኛ ሚዛኑን መለካት የሚቻለው። ወያኔ በጥይት ደብድቦ የገደላቸውን፣ በየእስር ቤቱ እያጎረ ያሰቃያቸውን ዜጎች ቁጥራቸው በመቶሺዎች እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህጻናትን፣ ወጣቶችን፣ ጎልማሶችንና አረጋውያንን በቀጥታ በመዝረፍ ህይወታቸው በመከራ የተሞላ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን የጅምላ እልቂት እንዲደርስባቸው ማድረጉን ያስታወሰው የለም። የወያኔ ዘረፋ፤ በረሃብ፣ በበሽታ፣ በሌሎችም በገንዘብ እጥረት የተነሳ በወያኔ ዘመን ላለቁ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የጅምላ እልቂት ዋናው ምክንያት ነው። የአማራ ህዝብ ደግሞ በወያኔ የጥላቻ አይን ተለይቶ የሚታይ በመሆኑ የዚህ የጅምላ ግድያ ዋና ሰለባ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ሂሳብ ማወራረድ ብለዋልና ሂሳቡ የሚያሳየው ይህንኑ ነው።
የጀመርነውን ክፍል ለመሰብሰብ ወያኔ ከአማራ ጥላቻ በመነሳት በአማራ ህዝብና ከዛም አልፎ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰውን ጥቃትና ጉዳት ዘርዝረን መጨረስ አንችልም። ለጊዜው ለማሳያ ያክል እስካሁን ያልነው ይበቃል። ወያኔን የምንጠይቀው የዘረዘርነውን አንድ መቶኛ የሚሆን፤ አማራው በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸማቸውን እኩይ ድርጊቶች እንዲያቀርብ ነው። ማቅረብ እንደማይችል ግን እናውቃለን። በሚቀጥለውና በመጨረሻው ክፍል፣ ይህን ሁሉ ወንጀል በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመ እኩይ ድርጅት ከሶስት አመት በፊት በህዝብ ትግል ሲወድቅ ለመሆኑ ይህ ሁሉ በደል የተፈጸመበት የአማራ ህዝብ ምን አለ? የወያኔ ገዳዮቹን፣ ዘራፊዎቹንና አፈናቃዮቹን ምን ይደረጉ አለ? ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጠው ምላሽ የወያኔን እና የተባባሪዎቹን ይሉኝታቢስነትና አደገኛነት አጉልተው የሚያሳዩ ይሆናሉ። በመጨረሻው ክፍል ይህን ሃተታ ይዘን እንቀርባለን። እስከዛው በቸር እንገናኝ።

=============///================

No comments: