በቀሲስ መንግሥቱ ጐበዜ
ሉንድ ዩንቨርሲቲ ፣ ስዊድን
(ቀሲስ መንግስቱ ጎበዜ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አርኪኦሎጂ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና በሉንድ ዩንቨርስቲ የዶክትሬት የመጨረሻ ዓመት ትምህርታቸውን በታሪክ ዘመን አርክዮሎጂ በማጥናት ላይ ይገኛሉ)
የአክሱም ሐውልት
አክሱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ ስልጣኔ እምብርት፣ የጠንካራ መንግሥታዊ አስተዳደር ማዕከል እና የድንቅ ባህል መድረክ እንደነበረች ይታወቃል። የታቦተ ጽዮን መገኛ፣ የቅዱስ ያሬድ መፍለቂያ፣ የመጀመሪያው ጳጳስ አባ ሰላማ (ፍሬምናጦስ) መንበር፣ የዘጠኙ ቅዱሳን በዓት የነበረችው አክሱም በኢትዮጵያ የክርስትና ሐይማኖት ታሪክ ልዩ ክብርና ስፍራ አላት። አክሱም የመጀመሪያዎቹ የሙሃመድ ተከታዮች ከሃገራቸው በተሰደዱ ጊዜ በእንግድነት ተቀብላ መጠጊያ ስለሆነች በሙስሊሙ ዓለምም ውለታዋ የሚዘነጋ አይደለም።
የአክሱም መንግሥት በትንሹ ከመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ መኖሩ ሲታወቅ፤ ጠንካራ መሪዎችና የራሱ የሆነ የመገባበያ ገንዘብ እንደነበረውም ይታወሳል። በዚሁ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ዞስካለስ በመባል የሚታወቀው ንጉሥ የግሪክኛ ቋንቋን በደንብ የሚያውቅና የአዶሊስ ወደብን በዋና የንግድ ማዕከልነት ይጠቀም እንደነበር ተመዝግቧል። የአክሱም መንግሥት ኃያልነት ከ2ኛው እስከ 3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረው የአዶሊስ ሐውልት ጽሑፍ (Adulis Inscription) ላይ ተጠቅሷል። በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ማኒ የተባለ ፐርሺያዊ ጸሐፊ አክሱምን ከሮም፣ ከፐርሺያና ከቻይና ጋር በመደመር በዘመኑ ከነበሩት የዓለም ሃያላን መንግሥታት ተርታ አስቀምጧታል። ከ4ኛው እስከ 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለነበረው ከፍተኛ የሆነ የአክሱም መንግሥት እድገትና ብልጽግና ከበቂ በላይ የታሪክ ምስክሮች ይገኛሉ። የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ንጉሥ ኢዛና እና የ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ንጉሥ ካሌብ በቤተመንግሥትም ሆነ በቤተክህነቱ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ናቸው።
የአክሱም ስልጣኔ አንድአንዶች እንደሚመስላቸው አንድን ህብረተሰብ ብቻ የሚወክል ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የድምር እንቅስቃሲያቸው ውጤት ነው። ለምሳሌ ያህል አክሱም የሚለውን መሰረተ ሥርወ ቃል (etymology) መመልከት ተገቢ ይሆናል። አክሱም የሚለው ቃል ‘አኽ’ ከሚለው የአገውኛ ቃል (ትርጉሙ ውሃ ማለት ነው) እና ‘ስዩም’ ከሚለው የግዕዝ ቃል (የተሾመ፣ ሹም እንደ ማለት ነው) የተገኘ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት አለ። በአንድ ላይ ተጠቃሎ ሲነበብም ‘የውሃ ሹም’ የሚለውን ትርጉም ይሰጣል። እስከ ዛሬ ድረስ በአክሱም ‘ማይ ሹም’ (የውሃ ሹም) ተብሎ የሚታወቅ ቦታ መኖሩ የስያሜውን እውነትነት ያጠናክረዋል። ለረጅም ዘመን የዋግ (ሰቆጣ) መሪዎች ‘ዋግ ሹም’ በሚል የማዕረግ ስም ይጠሩ እንደነበርም ይታወቃል። ከላስታ ነገሥታት መካከልም ሁለቱ ‘ግርማ ስዩም’ (የንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ አባት) እና ‘ዛን ስዩም’ (የንጉስ ላሊበላ አባት) ተብለው ይጠሩ እንደነበር ልብ ይሏል። አክሱም የሚለው ቃል ስያሜ መሰረቱ የኩሽ (አገውኛ) እና የሴም (ግዕዝ) ቋንቋዎች ጥምረት ከሆነ የአክሱም መንግሥት፣ ሥልጣኔ እና ቅርሶቹ የኩሽና የሴም ሕዝቦች መስተጋብር ውጤት መሆናቸውን ከዚህ በላይ ማሳያ የለም።
ሆኖም ግን የታሪክና የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች እንደሚመሰክሩት የአገው ሕዝቦች በአክሱም ዘመነ መንግሥት አስተዳደርና እና የስልጣኔ ፈርጦቹ የነበራቸውን ከሁሉም የላቀ አስተዋጽኦ መካድ አይቻልም። ከጅምሩ አገዎች በቁጥር ብዙና በመልካዓ ምድራዊ አሰፋፈራቸውም ቀላል የማይባለውን የአክሱም መንግሥት ወሰነ ግዛት ያካተተ ነበር። አገዎች የመካከለኛውና የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ቀደምት ነዋሪዎችና አገር አቅኝዎች መሆናቸውም ይታወቃል። እነዚህ ሕዝቦች የአባይ ወንዝ መነሻ ከሆነው ከጣና ጀምሮ የጎጃም፣የጎንደር፣ የላስታ፣የዋግ (ሰአቆጣ) እና የትግራይ በርካታ አካባቢዎችን በማካተት የመረብን ወንዝ ተሻግረው እስከ ኤርትራ ግዛት ከረን ድረስ ሰፍረው ይኖሩ ነበር። ይህ ትልቅ የሕዝብ ቁጥርና ሰፊ የቦታ ይዞታ በራሱ አገዎች በዘመነ አክሱም ተጽእኖ የመፍጠር አቅም እንደነበራቸው አመላካች ነው።
አገዎች ዓይነተኛ በሆኑ ጥንታዊ የታሪክ መዛግብት (primary sources) ከተጠቀሱት ጥቂት ሕዝቦች መካከል አንዱ ናቸው። ከላይ በተጠቀሰው የአዶሊስ የሃውልት ላይ ጽሑፍ (Adulis Inscription)፣ የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የንጉሥ ኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ (Ezana Inscription)፣ እንዲሁም በ6ኛውመቶ ክፍለ ዘመን የኮስሞስ ጽሑፍ (Christian Topography of Cosmas Indicopleustes) የአገዎችን እንጅ በዘመናችን የሚታወቁ የሌሎች ሕዝቦችን ስም አናገኝም። ከአገው ሌላ አጋዚ የሚለው ስም በጥንቱ መዛግብት የተገለጸ ሲሆን ይኸውም የግዕዝ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን (አጋዝያን) የሚመለከት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። በአዶሊስ ሐውልት ጽሑፍ (Adulis Inscription) ላይ የአክሱም ንጉስ ከአጋዚ ነገድ ጋር እንደተዋጋ ተጥቅሷል። በሌላ በኩል ከአክሱም መንግሥት ሥልጣኔ ጋር የቅርብ ዝምድና ሊኖራቸው ይችላል ተብለው የሚታሰቡት ሕዝቦች ስማቸው በጥንቱ የአክሱም ዘመን የታሪክ ሰነዶች አልተካተተም። ለምሳሌ የትግራይ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ ተጠቅሶ የሚገኘው በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአክሱም መንግሥት ማክተም በኋላ ነው።
አገዎች በአክሱም መንግሥት የባህል፣ የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው የሚጠቁሙ አያሌ ማሳያዎች አሉ። ከነዚህም አንዱ አገዎች በአክሱም መንግሥት በከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያገለግሉ እንደነበር የሚያስረዳው የኮስሞስ ጽሑፍ ነው ። በዚህ የታሪክ ሰነድ ላይ እንደተገለጸው በንጉሥ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነትና እምነት የሚጠይቀውን ረጅም የወርቅ ንግድ መተላለፊያ መስመር የሚቆጣጠረው የአገው ሰው ነበር። በተለይ ደግሞ ለአክሱም ስልጣኔ መዳበር አገዎች የነበራቸውን ጉልህ ሚና የምንረዳው የራሳቸውን መንግሥት ላስታ ላይ ከመሰረቱ በኋላ የአክሱምን ሥልጣኔ አሻሽለው መድገማቸው ነው። የመንግሥት ማዕከሉ ከአክሱም ወደ ላስታ ከመሸጋገሩ ውጭ በሁለቱ ዘመናት የነበረው የአስተዳደር ዘይቤ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የውጭ ግንኙነት ወዘተ የጎላ ልዩነት ነበረው ብሎ ለመናገር አያስደፍርም። በአክሱምም በዛጉዬም ዘመናት ግዕዝን በዋና ቋንቋነት ይጠቀሙ ነበር። በአክሱምም በዛጉዬም ዘመናት ቤተ መንግሥትና ቤተክህነት እጅግ የጠበቀ ግንኙነት ነበራቸው። በርግጥ በዛግዬ ዘመን ነገሥታት ካህናትም ተፈጥረዋል። የአክሱም ነገሥታት በተለይ ከግብፅና ከኢየሩሳሌም ጋር የነበራቸው ግንኙነት በዛጉዬ ዘመንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። የአክሱም ዘመን የህንፃ አሰራር ጥበብ በዳበረ መልኩ በዛጉዬ ዘመን ተንፀባርቋል።
አገዎች የአክሱም መንግሥት አካል ስለነበሩ ድሮም የሚያውቁትን የኪነ ህንፃን ሥራ በረቀቀ መንገድ በላስታ ላይ አሳይተዋል። በተለይ ደግሞ የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ስንመለከት ከአክሱም ዘምን የህንፃ ጥበብ ጋር ያላቸው የቅርብ ዝምድና ሁለቱም ከአንድ ምንጭ የተቀዱ መሆናቸውን ለመረዳት አያዳግትም። ወጥ ዓለትን በመፈልፈል ለሚፈልጉት ዓላማ ማዋልን መሰረት ያደረገው ኢትዮጵያዊ ሥልጣኔ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከአገው ሕዝቦች ጋር የተዛመደ ስለመሆኑ ዋነኛ አመላካች ነው። መርዶክ የተባለው ጸሐፊ “ሁሉም ማስረጃዎች የሚጠቁሙት የአገው ሕዝብ በአፍሪካ በባህላዊ የፈጠራ ክህሎቶች የተካኑ መሆኑን ነው።” በማለት የገለጸው ከዚህ ተነስቶ ሳይሆን አይቀርም።
ሲጠቃለል የአክሱም ዘመን ስልጣኔ ውጤት የሆኑ መንፈሳዊና ባህላዊ ቅርሶችን የራሱ ብቻ እንደሆኑ አድርጎ የሚያስብ የህብረተሰብ ክፍል ቢኖር ታሪካዊ እውነታው አይፈቅድለትም። ያም ከሆነ ከአገው ሕዝብ በላይ የቀረበ ማንም እንደሌለ የሚመሰክሩ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ። አገዎችም ቢሆኑ በጊዜ ብዛት በተለይ በአማርኛ፣ በትግርኛ እና በኋላም ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተዋጡ (assimilated) ወይም ከነዚህ ሕዝቦች ጋር የተቀየጡ (mixed) በመሆናቸው ብዙውን የጥንቱን የአገው ማኅበረሰብ የምናገኘው በነዚህ ሕዝቦች ውስጥ ጭምር መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ደግሞስ አክሱም የሚለው ስያሜ ራሱ ከላይ እንደተመለከትነው በኩሽና በሴም ቋንቋዎች ጥምረት የተፈጠረ ቃል አይደል! ስለሆነም የጥንቱ የአክሱም ዘመን ስልጣኔ ቅርሶች የሁላችንም ቅድመ አያቶች ድንቅ የእምነት፣ የስራና የፈጠራ ውጤቶች መሆናቸውን ማስተባበል አይቻልም። አክሱማዊ ቅርሶቻችን የሁሉም ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሰርተውና ጠብቀው ያቆዩልን የጋራ ሀብቶቻችን ናቸው። ከዚህም በላይ የአክሱም መካነ ቅርስ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ቅርስነት ተመዝግቦ የሚገኝ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ሀብት መሆኑም ማወቁ ተገቢ ነው።
ማጣቀሻዎች
McCrindle, John Watson (ed.,tr), 1897. The Christian Topography of Cosmas, an Egyptian monk, London.
Merid Wolde Aregay, 1971. ‘Southern Ethiopia and the Christian Kingdom 1508-1708’. Unpublished PhD thesis, School of Oriental and African Studies, University of London.
Munro-Hay, S. 1991. Aksum. An African Civilisation of Late Antiquity. Edinburgh University Press, Edinburgh.
Munro-Hay, Stuart. 2003. ‘Aksum’, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden
Murdock, George P., 1959. Africa: Its people and their culture history, New York
Phillipson, D.W. 2009. Ancient Churches of Ethiopia, Fourth–Fourteenth Centuries. Yale University Press: New Haven/London.
Phillipson, D.W. 2004. The Aksumite roots of medieval Ethiopia. Azania 29: 77-89.
Quirin, James. 2003. ‘Agäw’, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden
Sergew Hable Selassie. 1972. Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270. United Printers: Addis Ababa.
Sima, Alexander. 2003. ‘Agazi’, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden
Smidt, Wolbert. 2010. ‘Tigray’, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden
Taddesse Tamrat, 1972, Church and state in Ethiopia, 1270-1527, Oxford.
Taddesse Tamrat, 1988. Process of Ethnic Interaction and Integration in Ethiopian History: the Case of the Agaw (Special Issue in Honour of Roland Oliver), the Journal of African History, 29, 1, 5-18.
No comments:
Post a Comment