ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, February 24, 2018

የኢትዮጵያ የወቅቱ የለውጥ ማዕከሎች እነማን ናቸው? ኢትዮጵያንስ ወዴት ያደርሷታል? (ጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)


ጉዳያችን/Gudayachn
የካቲት 18/2010 ዓም (ፈብሯሪ 25/2018 ዓም)

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች ተካተዋል። እነርሱም : -

 - የኢትዮጵያ የወቅቱ የለውጥ ማዕከሎች እነማን ናቸው?
 - ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ለቀውስ ጊዜ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስፈልጋሉ።ህወሓት እንቅፋት ባይፈጥር ይሻለዋል። 
 - የሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የዶክትሬት ጥናት ፕሮፖዛል  በማኅበራዊ ዕሴት (ሶሻል ካፒታል) ላይ ያቀረቡት ቪድዮ እና 
 - የአቶ ለማ መገርሳ ንግግር በባህር ዳር  (ቪድዮ) ያገኛሉ።

የኢትዮጵያ አዲስ ክፍለ ዘመን ማለትም 21ኛው ክ/ዘመን ከተጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ወደ አዲስ መስመር (አዎንታዊ ወይንም አሉታዊ) የሚያስገባት እንደሚሆን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።ይህ መስመር ግን በጥንቃቄ ወደ በጎ ጎዳና የሚያስገባው የተባበረ የሕዝብ አቅም እና አመራር ይፈልጋል።አሁን ጥያቄው የለውጥ ማዕከሎቹ የት ናቸው ? እነኝህ የለውጥ ማዕከሎችስ ኢትዮጵያን ወዴት ያደርሷታል? የሚለው ጥያቄ ቁልፍ ጥያቄ ነው።

የኢትዮጵያ የወቅቱ የለውጥ ማዕከሎች እነማን ናቸው?

አሁን በኢትዮያ የለውጥ  ማዕበል ውስጥ የለወጥ ማዕከሎቹን በሶስት ክፍል ከፍሎ መመልከት ይቻላል። እነርሱም: -

1/ በኢህአዴግ በእራሱ ውስጥ ያለው የለውጥ ንቅናቄ 

የህዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተለይ በእራሱ በኦህዴድ በግልጥ እና በድብቅ የሚደገፈው በኦሮምያ በሥራ ማቆም እና ሰልፍ፣ በዐማራ ክልል በብአዴን በአብዛኛው በእራሱ በአባላቱ ልብ ውስጥ የገባው በመሳርያ የተደገፈ የትጥቅ ትግል እና የተቃውሞ ሰልፍ እና በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው የስልጣን ሽምያ እና የውሳኔ አሰጣጥ ላይ አለመስማማት፣ እነኝህ ሁሉ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የለውጥ ማዕከል ሆነው ቀርበዋል። እነኝህ የለውጥ ማዕከሎች ህወሓትን ክፉኛ አናግተውታል።በተለይ በኦሮምያ ያለው እራሱን በአደረጃጀት አጠንክሮ ከመምጣቱም በላይ የሌላውን ሕዝብ ቀልብ የሚስቡ ሃገራዊ የአንድነት አጀንዳዎችን ይዞ በመምጣቱ ህወሓት ሊጋፋው የማይችለው እንደሆነበት የሚታይ ነው።

በኢህአዴግ ውስጥ የመጣው የለውጥ ንቅናቄ አሁን ያለበት ደረጃ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሁን ወደሚለው  የስልጣን ጥያቄ ማደጉ ይታያል።ኦህዴድ በግልጥ ስልጣኑን መጠየቁን አቶ ለማ በእዚህ ሳምንት በሰጡት መግለጫ " ኦህዴድ የፈድራል ስልጣኑን ሰርቆ የኦሮሞን ሕዝብ ለማበልፀግ አይደለም" በማለት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ኦህዴድ ብሔራዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚጠቀምበት ገልጧል። በሌላ በኩል በህወሓት እና በብአዴን ውስጥ አይነቱ የተለያየ የውስጥ ቅራኔ እንዳለ መመልከት ይቻላል።ህወሓት የአባይ ወልዱ ቡድን፣የስብሐት ቡድን እየተባባለ በሙስና እና በጥቅም ጉዳይ የተከፋፈለ አካል ሲኖር ይሄው ቡድን አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ የቀውስ ሰዓቱን ጠብቆ የበለጠ በመዝረፍ ላይ መሆኑ እየተሰማ ነው።

2/ የሕዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል

የህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል በኢትዮጵያ የአሁኑ የለውጥ ማዕከል በእራሱ ማዕከል ሆኖ ወጥቷል።የህዝብ ጥያቄ የማስፈፀም አቅሙን "ካሮት እና ዱላ" ይዞ በመምጣት ለህወሓት አማራጭ አቅርቦለታል።ህወሓት ይህንን ፈተና ሊያልፍ የሚያስበው ''ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ የመውጣት'' አይነት መንገድ ይመስላል።ይሄውም በአንድ በኩል የለውጥ እርምጃ ላይ ያለ የሚመስል እስረኞችን የመፍታት፣ለዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ ለውጥ እያደረገ በመግለጥ እና የአቶ ሃይለማርያም ከቦታቸው መነሳትን እንደ ለውጥ እርምጃ እንዲታይ በመጣጣር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ሁሉ ገደል የሚከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ መዳረሻው ወታደራዊ አስተዳደር እንደሆነ ማመላከት ነው።ይህም ተባለ ሌላ የኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከል አንዱ መሰረቱን በእዚህ ሰዓት የሕዝባዊ ተቃውሞ ነው።የለውጥ ማዕከሉ በህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበልነት ሲከሰት በከተሞች በሰልፍ፣በገጠራማ ቦታዎች መንገዶችን በመዝጋት እና ወደ ዐማራ ክልል ስንሄድ ደግሞ የትጥቅ ትግል ከእራሱ ከገበሬው በመነሳቱ ሁሉ ይገለጣል።ንቅናቄው ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ እንድታመራ የማድረግ አቅም አለው።ሆኖም ግን በብዙ ግጭት ውስጥ አልፎ ሰለሚሆን ሌሎች ቅራኔዎችን ፈጥሮ መሄዱ አይቀርም። ስለሆነም ይህ ለውጥ በህወሓት ለለውጥ መዘጋጀት መጠን እየተለካ እና እየተመጠነ የሚቀርብ ንቅናቄ ነው።

3/  ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፉ ሚድያዎች፣የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እና መሰረቱን ኤርትራ ያደረገው የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ 

የኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከል ላይ ጉልህ አሻራቸው ከሚገለጠው ውስጥ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ፣ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፉ ሚድያዎች   እና መሰረቱን ኤርትራ ያደረገው የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ የእየራሳቸውን ድርሻ አላቸው።ይህንን ለመረዳት ግን ፖለቲካዊ ዕይታ ሊኖር ይገባል።ከላይ በተራ ቁጥር አንድ እና ሁለት ላይ ያሉት የለውጥ ማዕከላት በድንገት ከሰማይ የወረዱ አይደሉም።ለዓመታት የተሰሩ ስራዎች ውጤቶች ናቸው።የለውጥ ስሜት ለመፍጠር በሀገር ውስጥ ምን እየተሰራ እንደሆነ ለሕዝቡ በሚገባው መንገድ መንገር ይጠይቅ ነበር።ለእዚህም በቀዳሚነት በተለይ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን- ኢሳት  ድርሻው የጎላ ነው። ኢሳት በአማርኛ፣ኦሮምኛ፣ትግርኛ እና በእንግሊዝኛ በሚያስተላልፋቸው የራድዮ፣የቴሌቭዥን እና የድረ ገፅ መርሃ ግብሮች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ከገዢው ፓርቲ ላይ ፈልቅቆ የመውሰድ ያህል አድማሱን አስፍቷል።በእርግጥ ከእዚህ የበለጠ የሚጫወተው ሚና ማደግ አለበት የሚለው ሃሳብ አሁንም ብዙዎችን ያስማማል። ሆኖም ግን የግፉን መጠን እና ዲግሪ በማሳወቅ እና የመፍትሄ ሃሳቦችን በመጠቆም ኢሳት ቀዳሚ የለውጥ ማዕከልነቱን አስመስክሯል።ከኢሳት ጋር የኦሮሞ ሚድያ ኔትዎርክ በተለይ በኦሮምያ አካባቢ ላለው እንቅስቃሴ ህዝቡ ከደረሰበት የስርዓቱ በደል ጋር ተዳምሮ አስተዋፅኦ ነበረው።የኢሳትን የተለየ የሚያደርገው የአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ በመላው ሀገሪቱ ከመሆኑ አንፃር በብሔራዊ ደረጃ ቀዳሚ ተፅኖ ፈጣሪ ሆኖ ይገኛል።

መሰረታቸውን ውጭ ካደረጉ የመገናኛ ብዙሃን በተለየ በኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከልነት ላለፉት ሰባት ዓመታት ተፅኖ ፈጥሮ የቆየው እና ወደፊትም ተፅኖ እንደሚኖረው የሚገመተው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ነው። አንዳንዶች አርበኞች ግንቦት 7 በትጥቅ ትግል የትኛውን ቦታ ተቆጣጠረ? አንድ ነገር ሀገር ቤት ሲከሰት ወድያው በቀል የመሰለ እርምጃ ሲወስድ አላየነውም፣ወዘተ የሚል አስተያየት በማኅበራዊ ሚድያ በመስጠት የፖለቲካ ትንታኔ ለመስጠት የሚሞክሩ አሉ።ሆኖም ግን ይህ ከአጠቃላይ የፖለቲካው ክበባዊ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ አንዱን ቁንፅል ነጥብ አንስቶ የመከራከር ያህል ነው።

የህወሓት ሁለቱ ምሰሶዎች ማለትም ወታደራዊ እና ደህንነቱ በአንድ በኩል ምጣኔ ሃብታዊ በሌላ በኩል ሲሆኑ የወታደራዊው እና ደህነንቱ ምሰሶ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢያንስ በአደጋነት የሚያየው ከኤርትራ በኩል ይነሳል የሚለውን እንቅስቃሴ እና በሀገር ውስጥ በተለይ በሰሜናዊ ጎንደር፣ጎጃም እና በቅርቡም በወሎ ውስጥ ያላወኩት የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ ሕዝብ እያደራጀ ነው የሚለው ነው።በእዚህም ሳብያ ነው በአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነው አጠቁኝ ያላቸውን ስርዓቱ ወደ እስር ቤት የሚያግዘው።የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ እንደ ሕዝባዊ ማዕበሉ የአንድ ወቅት እንቅስቃሴ አለመሆኑን ድርጅቱ በስልት ደረጃ ያስቀመጣቸው የትግል መንገዶች በእራሳቸው በእረጅም ጊዜም ቢሆን ህወሓት ወደ  ዲሞክራሲያዊ መንገድ እስካልመጣ ድረስ የመታገያ መንገዶችን ድርጅቱ ይፋ ማድረጉ በተቃዋሚ ፖለቲካው መድረክ የእራሱ የሆነ ቀጣይ ሂደት መኖሩን የሚያመላክት ነው።ስለሆነም ስለወደፍቱም ስናወራ የህዝባዊ ማዕበሉ በሆነ መንገድ ቢደናቀፍ ቀጣይ አማራጭ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የለውጥ ማዕከል መሆኑን ማንም የፖለቲካ ተንታኝ የሚያስቀምጠው ነው።

በሌላ በኩል አሁን ባለንበት የ21ኛው ክ/ዘመን ውስጥ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሚና ለለውጥ ማዕከልነት በተለይ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ የእራሱ ድርሻ አለው።ኢትዮጵያ ቃላት ጅኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ ማለትም የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ድልድይነቷ፣በዓለም ረጅም የተባለው የአባይ ወንዝ ከ85% በላይ የምመነጭባት መሆኗ፣በአፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላት ተፅኖ የመፍጠር አቅም ስላላት፣ ከአካባቢው ሀገሮች በበለጠ የህዝብ ብዛት ባለቤት መሆኗ  እና ከሁለት ሺህ ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ያላት ተፈጥሮ አቀማመጥ የመካከለኛ ምሥራቅን እና የቀይ ባህርን በቀላሉ ኢላማ  ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ገዢ መሬት ባለቤት መሆኗ ሁሉ የዓለም አቀፉን በተለይ የሃያላኑን ቀልብ እንደሳበች አለች።ይህ ማለት የኢትዮጵያ አለመረጋጋት አካባቢያዊ ቀውስን ማስከተሉ እና በአካባቢው ላይ ጥቅም ያላቸው ሀገሮችን ንግድም ሆነ ትርፍ ስለሚነካ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንዲሁ ልተዉት የሚችሉት አይደለም።ይህ በእራሱ ለኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከልነት የእራሱን ጉልህ ድርሻ ይጫወታል። ይህ የሚሆነው ግን ሕዝብ በህብረት ለመልካም ለውጥ መነሳት እስከ ቻለ ድረስ ብቻ ነው።

ውጫዊ ተፅኖ ሁል ጊዜ የማገዝ እና የማቀጣጠል ሚና እንጂ የመጠንሰስ፣የማሳደግ እና ለውጥ የማምጣት ሚናው ውሱን ነው።ለውጥ ከውስጥ ነው የሚመጣው።ይህንን ለመረዳት በእንቁላል እና ጫጩት መፈልፈል መረዳት ይቻላል። እንቁላል ውስጥ ጫጩት ሊወጣ የሚችለው ከውጭ የመጣው ሙቀት ሳብያ ከእንቁላሉ ፈሳሽ ውስጥ በሚፈጠረው ጫጩት ነው።የውጭው ሙቀት ድጋፍ ቢኖርም ዋናው የለውጥ ማዕከል ግን እንቁላሉ ውስጥ ነው።ሀገርም እንዲሁ ነው። የውጭ ሚድያ፣በውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ሰጪ ሚና ብቻ ነው የሚኖረው።

ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ለቀውስ ጊዜ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስፈልጋሉ።ህወሓት እንቅፋት ባይፈጥር ይሻለዋል። 

የህወሓት የለውጥ ማዕከል በእራሱ ቅራኔ ምሕዋር ላይ እየተሽከረከረ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመወሰን እርስ በርስ የተፋተጠበት ሰዓት ነው።ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በቀዳሚነት ብቻ ሳይሆን ዕወቀት ላይ  በተመሰረቱ ንግግሮቻቸው ሕዝብ እያስደመሙ ነው።አቶ መለስ በክፍለ ዘመኑ ውስጥ ብቸኛ ጥበበኛ ናቸው እየተባለ ላደገ የህወሓት ካድሬ ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ ማየት ቢያስደነግጠው ልንፈርድበት አይገባም።ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ በንግግር ብቻ ሳይሆን ከእዚህ በፊት በመሯቸው መስርያቤቶች ጭምር ብቃት እንዳሳዩ የሚናገሩ እየተሰሙ ነው።ይህ ማለት ደግሞ እስከዛሬ ቢያንስ በህወሓት ዘመን ብቃት ያለው የአስተዳደር ሰው እንደሆኑ እየታየ ነው ማለት ነው።ስለሆነም በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ ማዕከል በህወሓት እስካልተኮላሸ ድረስ እና ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድም ቃላቸውን ጠብቀው በታማኘነት እስከቀጠሉ እንዲሁም ከእዚህ በፊት የወጡ የማያሰሩ የህወሓት ፖሊሲዎችን በቶሎ በተሻሉ ፖሊሲዎች እንዲቀየሩ ብቻ ሳይሆን የማስፈፀም አቅማቸውን አዳብረው መስራት ከቻሉ ለኢትዮጵያ ወጪው የቀነሰ የውለውጥ ዘመን አይሆንም ብሎ ማመን አይቻልም።ይህ የሚሆነው ግን ሌሎቹ የለውጥ ማዕከላት በመተጋገዝ በድጋፍ ሰጪነት እስከ ቆሙ ድረስ ነው።

 በአዋጅ ውስጥ በኩራት የቆመው የለውጥ ማዕበል  በህወሓት እስካልተደናቀፈ ድረስ ኢትዮጵያ አሁንም ተስፋ የላትም ማለት አይቻልም።አዋጁ በእራሱ ተቀባይነት ከውጭም ሆነ ከውስጥ እንዳላገኘ ታይቷል።ህወሓት መልሳ አዋጁን ለመሻር ያላትን ብቸኛ ''የማርያም መንገድ'' የተወካዮች ምክር ቤት ሲሰበሰብ እንዳይቀበለው ማድረግ ነው።ይህ ዕድል ካመለጠ ግን ህወሓት በአደባባይ በመዋረድ በግድ አዋጁን የምትሽርበት አጋጣሚ መፈጠሩ አይቀርም። ስለሆነም ይህንን '' የማርያም መንገድ'' መጠቀም ጠቃሚ ነው። አሁን መሬት ያለው ጥያቄም የአዋጁ መኖርን ተከትሎ  ህወሓት በሰላማዊ መንገድ የለውጡን ሂደት በሕዝብ ፍላጎት ላይ ብቻ ተመስርቶ ይሄዳል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው።ይህንን በውዴታ ባያደርገውም በግድ ማድረግ ግን ለእራሱም ሆነ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ብቸኛ መስመር ነው።እዚህ ላይ በህወሓት ውስጥ እራሱን የቻለ 'የአናርኪ' ቡድን በተዘረፈ ገንዘብም ሆነ መሳርያ እራሱን አደራጅቶ እራሳቸው ህወሓት ነን ብለው የሚያስቡትም ባላወቁት መንገድ አንዳንድ እርምጃዎች ከግንፍልተኘንት መውሰዳቸው አይቀርም። ለውጥን በአንድ ጊዜ ለመቀበል ለግልፍተኛው የህወሓት ክፍል ቀላል አይደለም።ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ1997 ዓም የቅንጅት ምርጫ ወቅት አቶ በረከት ስምዖን በተገኙበት ክርክር ወቅት ደጋግመው ያነሱት አንድ ነጥብ አሁን ላይ መነሳት ያለበት ነው። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ያሉት '' አሁን ለውጥ እየመጣ ነው ስርዓቱ አባላቱን ከስልጣን መልቀቅ እንዳለ በግልፅ አባላቶቻችሁ እንዲለማመዱ እና በስነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ንገሯቸው'' ነበር ያሉት። ይህ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።ይህንን እራሱ ህወሓት ውስጥ ያሉትም የሚፈሩት ነው። የእስረኞች መፈታት የሚያናድዳቸው እና ሌላ አዙሪት ተንኮል ሰርተው በዙርያቸው ባሉ ህወሓቶች ለመደነቅ የሚፈልጉ የከንቱ አስተሳሰብ ባለቤቶች አሁንም ህወሓት ውስጥ አሉ። እነኝህ በእራሳቸው አንዳንዴ የጦር ኃይሉም ሆነ ደህንነቱ መዋቅር የማያውቃቸው መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል።በህወሓት ውስጥ ሌላ ህወሓት መኖሩን ማወቅ ይገባል።ይህ ግን በሰበብነት እየተጠቀሰ ሕዝብ መከራ የሚያይበት መንገድ ሊኖር አይገባም። ህወሓት ውስጥ ያሉ ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉ ቀድመው መዋጋት ያለባቸው እውስጣቸው ያሉትን ለለውጡ በድብቅ እንቅፋት በመፍጠር የምረኩትን ትንንሽ አጋንንቶች ነው።እነኝህ በማንኛውም ጊዜ በተፈቱት እስረኞች ላይ ግድያ ለመፈፀምም ሆነ  ሌላ ተግባር በማድረግ ''ተጋዳላይ'' እያሉ ለመዝፈን የማይዳዳቸው ሰይጣን ብቻ የሚያደንቃቸው ፍጥረቶች ናቸው። በመጪው ዘመን የሚገጥመው አንዱ ፈተና ይህ ነው።ህወሓት እራሱን ማስተካከል ካለበት መጀመርያ ትንንሽ ሰይጣኖችን ማሰር እና ግቢውን ማስተካከል ይገባዋል።ከእዚህ በኃላ ስለለውጥ ሂደቱ መስመር ውስጥ መግባት ይችላል።በነገራችን ላይ እነኝህ በህወሓት ውስጥ የተፈጠሩ ትንንሽ ''ሰይጣኖች'' የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ፣የፖለቲካ ብስለታቸው በጠበንጃ ላይ  የተመሰረተ እና ስሜታዊነት ብቻ የሚመራቸው ስለሆኑ ለእራሳቸው በህወሓት ውስጥ ለለውጥ የሚያስቡትንም ከመብላት አይመለሱም።ሁኔታውን ወደፊት የምናየው ይሆናል።

በመጨረሻም በመጪው ሳምንት በሚደረገው የኢህአዴግ ስብሰባ እንደ ''አዲስ ስታንድአርድ'' የእንግሊዝኛ ጋዜጣ የትናንት ዘገባ ከሆነ ከመጪው ቅዳሜ በፊት በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ያስታውቃል።ይህ 21ኛው ክ/ዘመን ነው። ትውልዱ ብዙ ልቆ ሄዷል።ቢያንስ ወደ ዋናው እና ሁለንተናዊ ለውጥ ኢትዮጵያ እስክትመጣ ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ አይነት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢያንስ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የቀውስ መንገድ ሐዲድ የማስገባት እና ሃሳቦችን የማመንጨት አቅም ያለው ሰው ያስፈልጋል።ኢትዮጵያ እና አካባቢው ያለው እንቅስቃሴ ከወታደራዊ እውቀትም ሆነ ከደህንነት እውቀት ያልራቀ ሰው ለጊዚያዊ የፖለቲካ ቀውስም ቢሆን የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።ስለሆነም ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ መመረጥ ላይ ህወሓት ባያንገራግር እና በውስጡ የተፈጠሩ ጀብደኞችን አስታግሶ መሄዱ ለእራሱም የሚበጀው ነው የሚሆነው።በጅማ አጋሮ ያደጉት እና የተማሩት ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ ግጭቶች ምክንያታቸው እና መፍትሄዎቻቸውን ተመልክተዋል።ከእዚህ በታች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ፕሮፖዛል የሰሩበት ሶሻል ካፒታል ቪድዮ ይመልከቱ።

የሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የዶክትሬት ጥናት ፕሮፕዛል በማኅበራዊ ዕሴት (ሶሻል ካፒታል) ላይ በቪድዮ ሲያቀርቡ 
L/Co.Dr.Abiy Ahmed phd proposal in title Social Capital and its role in traditional Conflict resolution in Ethiopia(The case of jimma zone)


የአቶ ለማ መገርሳ ንግግር በባህር ዳር  (ቪድዮ)


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...