ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, February 24, 2018

የኢትዮጵያ የወቅቱ የለውጥ ማዕከሎች እነማን ናቸው? ኢትዮጵያንስ ወዴት ያደርሷታል? (ጉዳያችን ልዩ ማስታወሻ)


ጉዳያችን/Gudayachn
የካቲት 18/2010 ዓም (ፈብሯሪ 25/2018 ዓም)

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች ተካተዋል። እነርሱም : -

 - የኢትዮጵያ የወቅቱ የለውጥ ማዕከሎች እነማን ናቸው?
 - ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ለቀውስ ጊዜ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስፈልጋሉ።ህወሓት እንቅፋት ባይፈጥር ይሻለዋል። 
 - የሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የዶክትሬት ጥናት ፕሮፖዛል  በማኅበራዊ ዕሴት (ሶሻል ካፒታል) ላይ ያቀረቡት ቪድዮ እና 
 - የአቶ ለማ መገርሳ ንግግር በባህር ዳር  (ቪድዮ) ያገኛሉ።

የኢትዮጵያ አዲስ ክፍለ ዘመን ማለትም 21ኛው ክ/ዘመን ከተጀመረ ወዲህ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበት ሁኔታ ወደ አዲስ መስመር (አዎንታዊ ወይንም አሉታዊ) የሚያስገባት እንደሚሆን የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።ይህ መስመር ግን በጥንቃቄ ወደ በጎ ጎዳና የሚያስገባው የተባበረ የሕዝብ አቅም እና አመራር ይፈልጋል።አሁን ጥያቄው የለውጥ ማዕከሎቹ የት ናቸው ? እነኝህ የለውጥ ማዕከሎችስ ኢትዮጵያን ወዴት ያደርሷታል? የሚለው ጥያቄ ቁልፍ ጥያቄ ነው።

የኢትዮጵያ የወቅቱ የለውጥ ማዕከሎች እነማን ናቸው?

አሁን በኢትዮያ የለውጥ  ማዕበል ውስጥ የለወጥ ማዕከሎቹን በሶስት ክፍል ከፍሎ መመልከት ይቻላል። እነርሱም: -

1/ በኢህአዴግ በእራሱ ውስጥ ያለው የለውጥ ንቅናቄ 

የህዝብ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተለይ በእራሱ በኦህዴድ በግልጥ እና በድብቅ የሚደገፈው በኦሮምያ በሥራ ማቆም እና ሰልፍ፣ በዐማራ ክልል በብአዴን በአብዛኛው በእራሱ በአባላቱ ልብ ውስጥ የገባው በመሳርያ የተደገፈ የትጥቅ ትግል እና የተቃውሞ ሰልፍ እና በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው የስልጣን ሽምያ እና የውሳኔ አሰጣጥ ላይ አለመስማማት፣ እነኝህ ሁሉ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የለውጥ ማዕከል ሆነው ቀርበዋል። እነኝህ የለውጥ ማዕከሎች ህወሓትን ክፉኛ አናግተውታል።በተለይ በኦሮምያ ያለው እራሱን በአደረጃጀት አጠንክሮ ከመምጣቱም በላይ የሌላውን ሕዝብ ቀልብ የሚስቡ ሃገራዊ የአንድነት አጀንዳዎችን ይዞ በመምጣቱ ህወሓት ሊጋፋው የማይችለው እንደሆነበት የሚታይ ነው።

በኢህአዴግ ውስጥ የመጣው የለውጥ ንቅናቄ አሁን ያለበት ደረጃ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ይሁን ወደሚለው  የስልጣን ጥያቄ ማደጉ ይታያል።ኦህዴድ በግልጥ ስልጣኑን መጠየቁን አቶ ለማ በእዚህ ሳምንት በሰጡት መግለጫ " ኦህዴድ የፈድራል ስልጣኑን ሰርቆ የኦሮሞን ሕዝብ ለማበልፀግ አይደለም" በማለት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ኦህዴድ ብሔራዊ ጥያቄዎችን ለመፍታት እንደሚጠቀምበት ገልጧል። በሌላ በኩል በህወሓት እና በብአዴን ውስጥ አይነቱ የተለያየ የውስጥ ቅራኔ እንዳለ መመልከት ይቻላል።ህወሓት የአባይ ወልዱ ቡድን፣የስብሐት ቡድን እየተባባለ በሙስና እና በጥቅም ጉዳይ የተከፋፈለ አካል ሲኖር ይሄው ቡድን አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ የቀውስ ሰዓቱን ጠብቆ የበለጠ በመዝረፍ ላይ መሆኑ እየተሰማ ነው።

2/ የሕዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል

የህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበል በኢትዮጵያ የአሁኑ የለውጥ ማዕከል በእራሱ ማዕከል ሆኖ ወጥቷል።የህዝብ ጥያቄ የማስፈፀም አቅሙን "ካሮት እና ዱላ" ይዞ በመምጣት ለህወሓት አማራጭ አቅርቦለታል።ህወሓት ይህንን ፈተና ሊያልፍ የሚያስበው ''ሁለት እግር አለኝ ብሎ ሁለት ዛፍ የመውጣት'' አይነት መንገድ ይመስላል።ይሄውም በአንድ በኩል የለውጥ እርምጃ ላይ ያለ የሚመስል እስረኞችን የመፍታት፣ለዲፕሎማሲ ማኅበረሰብ ለውጥ እያደረገ በመግለጥ እና የአቶ ሃይለማርያም ከቦታቸው መነሳትን እንደ ለውጥ እርምጃ እንዲታይ በመጣጣር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ሁሉ ገደል የሚከት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ መዳረሻው ወታደራዊ አስተዳደር እንደሆነ ማመላከት ነው።ይህም ተባለ ሌላ የኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከል አንዱ መሰረቱን በእዚህ ሰዓት የሕዝባዊ ተቃውሞ ነው።የለውጥ ማዕከሉ በህዝባዊ የተቃውሞ ማዕበልነት ሲከሰት በከተሞች በሰልፍ፣በገጠራማ ቦታዎች መንገዶችን በመዝጋት እና ወደ ዐማራ ክልል ስንሄድ ደግሞ የትጥቅ ትግል ከእራሱ ከገበሬው በመነሳቱ ሁሉ ይገለጣል።ንቅናቄው ኢትዮጵያ ወደ ለውጥ እንድታመራ የማድረግ አቅም አለው።ሆኖም ግን በብዙ ግጭት ውስጥ አልፎ ሰለሚሆን ሌሎች ቅራኔዎችን ፈጥሮ መሄዱ አይቀርም። ስለሆነም ይህ ለውጥ በህወሓት ለለውጥ መዘጋጀት መጠን እየተለካ እና እየተመጠነ የሚቀርብ ንቅናቄ ነው።

3/  ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፉ ሚድያዎች፣የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እና መሰረቱን ኤርትራ ያደረገው የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ 

የኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከል ላይ ጉልህ አሻራቸው ከሚገለጠው ውስጥ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ፣ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፉ ሚድያዎች   እና መሰረቱን ኤርትራ ያደረገው የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ የእየራሳቸውን ድርሻ አላቸው።ይህንን ለመረዳት ግን ፖለቲካዊ ዕይታ ሊኖር ይገባል።ከላይ በተራ ቁጥር አንድ እና ሁለት ላይ ያሉት የለውጥ ማዕከላት በድንገት ከሰማይ የወረዱ አይደሉም።ለዓመታት የተሰሩ ስራዎች ውጤቶች ናቸው።የለውጥ ስሜት ለመፍጠር በሀገር ውስጥ ምን እየተሰራ እንደሆነ ለሕዝቡ በሚገባው መንገድ መንገር ይጠይቅ ነበር።ለእዚህም በቀዳሚነት በተለይ ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን- ኢሳት  ድርሻው የጎላ ነው። ኢሳት በአማርኛ፣ኦሮምኛ፣ትግርኛ እና በእንግሊዝኛ በሚያስተላልፋቸው የራድዮ፣የቴሌቭዥን እና የድረ ገፅ መርሃ ግብሮች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምህዳር እንዲሰፋ ከገዢው ፓርቲ ላይ ፈልቅቆ የመውሰድ ያህል አድማሱን አስፍቷል።በእርግጥ ከእዚህ የበለጠ የሚጫወተው ሚና ማደግ አለበት የሚለው ሃሳብ አሁንም ብዙዎችን ያስማማል። ሆኖም ግን የግፉን መጠን እና ዲግሪ በማሳወቅ እና የመፍትሄ ሃሳቦችን በመጠቆም ኢሳት ቀዳሚ የለውጥ ማዕከልነቱን አስመስክሯል።ከኢሳት ጋር የኦሮሞ ሚድያ ኔትዎርክ በተለይ በኦሮምያ አካባቢ ላለው እንቅስቃሴ ህዝቡ ከደረሰበት የስርዓቱ በደል ጋር ተዳምሮ አስተዋፅኦ ነበረው።የኢሳትን የተለየ የሚያደርገው የአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ በመላው ሀገሪቱ ከመሆኑ አንፃር በብሔራዊ ደረጃ ቀዳሚ ተፅኖ ፈጣሪ ሆኖ ይገኛል።

መሰረታቸውን ውጭ ካደረጉ የመገናኛ ብዙሃን በተለየ በኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከልነት ላለፉት ሰባት ዓመታት ተፅኖ ፈጥሮ የቆየው እና ወደፊትም ተፅኖ እንደሚኖረው የሚገመተው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ነው። አንዳንዶች አርበኞች ግንቦት 7 በትጥቅ ትግል የትኛውን ቦታ ተቆጣጠረ? አንድ ነገር ሀገር ቤት ሲከሰት ወድያው በቀል የመሰለ እርምጃ ሲወስድ አላየነውም፣ወዘተ የሚል አስተያየት በማኅበራዊ ሚድያ በመስጠት የፖለቲካ ትንታኔ ለመስጠት የሚሞክሩ አሉ።ሆኖም ግን ይህ ከአጠቃላይ የፖለቲካው ክበባዊ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ አንዱን ቁንፅል ነጥብ አንስቶ የመከራከር ያህል ነው።

የህወሓት ሁለቱ ምሰሶዎች ማለትም ወታደራዊ እና ደህንነቱ በአንድ በኩል ምጣኔ ሃብታዊ በሌላ በኩል ሲሆኑ የወታደራዊው እና ደህነንቱ ምሰሶ በከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢያንስ በአደጋነት የሚያየው ከኤርትራ በኩል ይነሳል የሚለውን እንቅስቃሴ እና በሀገር ውስጥ በተለይ በሰሜናዊ ጎንደር፣ጎጃም እና በቅርቡም በወሎ ውስጥ ያላወኩት የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ ሕዝብ እያደራጀ ነው የሚለው ነው።በእዚህም ሳብያ ነው በአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ ውስጥ ሆነው አጠቁኝ ያላቸውን ስርዓቱ ወደ እስር ቤት የሚያግዘው።የአርበኞች ግንቦት 7 እንቅስቃሴ እንደ ሕዝባዊ ማዕበሉ የአንድ ወቅት እንቅስቃሴ አለመሆኑን ድርጅቱ በስልት ደረጃ ያስቀመጣቸው የትግል መንገዶች በእራሳቸው በእረጅም ጊዜም ቢሆን ህወሓት ወደ  ዲሞክራሲያዊ መንገድ እስካልመጣ ድረስ የመታገያ መንገዶችን ድርጅቱ ይፋ ማድረጉ በተቃዋሚ ፖለቲካው መድረክ የእራሱ የሆነ ቀጣይ ሂደት መኖሩን የሚያመላክት ነው።ስለሆነም ስለወደፍቱም ስናወራ የህዝባዊ ማዕበሉ በሆነ መንገድ ቢደናቀፍ ቀጣይ አማራጭ የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የለውጥ ማዕከል መሆኑን ማንም የፖለቲካ ተንታኝ የሚያስቀምጠው ነው።

በሌላ በኩል አሁን ባለንበት የ21ኛው ክ/ዘመን ውስጥ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ሚና ለለውጥ ማዕከልነት በተለይ አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ የእራሱ ድርሻ አለው።ኢትዮጵያ ቃላት ጅኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ ማለትም የመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ድልድይነቷ፣በዓለም ረጅም የተባለው የአባይ ወንዝ ከ85% በላይ የምመነጭባት መሆኗ፣በአፍሪካ እና በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላት ተፅኖ የመፍጠር አቅም ስላላት፣ ከአካባቢው ሀገሮች በበለጠ የህዝብ ብዛት ባለቤት መሆኗ  እና ከሁለት ሺህ ሜትር ከባህር ጠለል በላይ ያላት ተፈጥሮ አቀማመጥ የመካከለኛ ምሥራቅን እና የቀይ ባህርን በቀላሉ ኢላማ  ውስጥ ሊያስገባ የሚችል ገዢ መሬት ባለቤት መሆኗ ሁሉ የዓለም አቀፉን በተለይ የሃያላኑን ቀልብ እንደሳበች አለች።ይህ ማለት የኢትዮጵያ አለመረጋጋት አካባቢያዊ ቀውስን ማስከተሉ እና በአካባቢው ላይ ጥቅም ያላቸው ሀገሮችን ንግድም ሆነ ትርፍ ስለሚነካ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንዲሁ ልተዉት የሚችሉት አይደለም።ይህ በእራሱ ለኢትዮጵያ የለውጥ ማዕከልነት የእራሱን ጉልህ ድርሻ ይጫወታል። ይህ የሚሆነው ግን ሕዝብ በህብረት ለመልካም ለውጥ መነሳት እስከ ቻለ ድረስ ብቻ ነው።

ውጫዊ ተፅኖ ሁል ጊዜ የማገዝ እና የማቀጣጠል ሚና እንጂ የመጠንሰስ፣የማሳደግ እና ለውጥ የማምጣት ሚናው ውሱን ነው።ለውጥ ከውስጥ ነው የሚመጣው።ይህንን ለመረዳት በእንቁላል እና ጫጩት መፈልፈል መረዳት ይቻላል። እንቁላል ውስጥ ጫጩት ሊወጣ የሚችለው ከውጭ የመጣው ሙቀት ሳብያ ከእንቁላሉ ፈሳሽ ውስጥ በሚፈጠረው ጫጩት ነው።የውጭው ሙቀት ድጋፍ ቢኖርም ዋናው የለውጥ ማዕከል ግን እንቁላሉ ውስጥ ነው።ሀገርም እንዲሁ ነው። የውጭ ሚድያ፣በውጭ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች እንቅስቃሴ እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ሰጪ ሚና ብቻ ነው የሚኖረው።

ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ለቀውስ ጊዜ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ያስፈልጋሉ።ህወሓት እንቅፋት ባይፈጥር ይሻለዋል። 

የህወሓት የለውጥ ማዕከል በእራሱ ቅራኔ ምሕዋር ላይ እየተሽከረከረ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመወሰን እርስ በርስ የተፋተጠበት ሰዓት ነው።ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ በቀዳሚነት ብቻ ሳይሆን ዕወቀት ላይ  በተመሰረቱ ንግግሮቻቸው ሕዝብ እያስደመሙ ነው።አቶ መለስ በክፍለ ዘመኑ ውስጥ ብቸኛ ጥበበኛ ናቸው እየተባለ ላደገ የህወሓት ካድሬ ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ ማየት ቢያስደነግጠው ልንፈርድበት አይገባም።ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ በንግግር ብቻ ሳይሆን ከእዚህ በፊት በመሯቸው መስርያቤቶች ጭምር ብቃት እንዳሳዩ የሚናገሩ እየተሰሙ ነው።ይህ ማለት ደግሞ እስከዛሬ ቢያንስ በህወሓት ዘመን ብቃት ያለው የአስተዳደር ሰው እንደሆኑ እየታየ ነው ማለት ነው።ስለሆነም በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ ማዕከል በህወሓት እስካልተኮላሸ ድረስ እና ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድም ቃላቸውን ጠብቀው በታማኘነት እስከቀጠሉ እንዲሁም ከእዚህ በፊት የወጡ የማያሰሩ የህወሓት ፖሊሲዎችን በቶሎ በተሻሉ ፖሊሲዎች እንዲቀየሩ ብቻ ሳይሆን የማስፈፀም አቅማቸውን አዳብረው መስራት ከቻሉ ለኢትዮጵያ ወጪው የቀነሰ የውለውጥ ዘመን አይሆንም ብሎ ማመን አይቻልም።ይህ የሚሆነው ግን ሌሎቹ የለውጥ ማዕከላት በመተጋገዝ በድጋፍ ሰጪነት እስከ ቆሙ ድረስ ነው።

 በአዋጅ ውስጥ በኩራት የቆመው የለውጥ ማዕበል  በህወሓት እስካልተደናቀፈ ድረስ ኢትዮጵያ አሁንም ተስፋ የላትም ማለት አይቻልም።አዋጁ በእራሱ ተቀባይነት ከውጭም ሆነ ከውስጥ እንዳላገኘ ታይቷል።ህወሓት መልሳ አዋጁን ለመሻር ያላትን ብቸኛ ''የማርያም መንገድ'' የተወካዮች ምክር ቤት ሲሰበሰብ እንዳይቀበለው ማድረግ ነው።ይህ ዕድል ካመለጠ ግን ህወሓት በአደባባይ በመዋረድ በግድ አዋጁን የምትሽርበት አጋጣሚ መፈጠሩ አይቀርም። ስለሆነም ይህንን '' የማርያም መንገድ'' መጠቀም ጠቃሚ ነው። አሁን መሬት ያለው ጥያቄም የአዋጁ መኖርን ተከትሎ  ህወሓት በሰላማዊ መንገድ የለውጡን ሂደት በሕዝብ ፍላጎት ላይ ብቻ ተመስርቶ ይሄዳል ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው።ይህንን በውዴታ ባያደርገውም በግድ ማድረግ ግን ለእራሱም ሆነ ለኢትዮጵያ የሚበጅ ብቸኛ መስመር ነው።እዚህ ላይ በህወሓት ውስጥ እራሱን የቻለ 'የአናርኪ' ቡድን በተዘረፈ ገንዘብም ሆነ መሳርያ እራሱን አደራጅቶ እራሳቸው ህወሓት ነን ብለው የሚያስቡትም ባላወቁት መንገድ አንዳንድ እርምጃዎች ከግንፍልተኘንት መውሰዳቸው አይቀርም። ለውጥን በአንድ ጊዜ ለመቀበል ለግልፍተኛው የህወሓት ክፍል ቀላል አይደለም።ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በ1997 ዓም የቅንጅት ምርጫ ወቅት አቶ በረከት ስምዖን በተገኙበት ክርክር ወቅት ደጋግመው ያነሱት አንድ ነጥብ አሁን ላይ መነሳት ያለበት ነው። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ያሉት '' አሁን ለውጥ እየመጣ ነው ስርዓቱ አባላቱን ከስልጣን መልቀቅ እንዳለ በግልፅ አባላቶቻችሁ እንዲለማመዱ እና በስነ ልቦና ዝግጁ እንዲሆኑ ንገሯቸው'' ነበር ያሉት። ይህ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።ይህንን እራሱ ህወሓት ውስጥ ያሉትም የሚፈሩት ነው። የእስረኞች መፈታት የሚያናድዳቸው እና ሌላ አዙሪት ተንኮል ሰርተው በዙርያቸው ባሉ ህወሓቶች ለመደነቅ የሚፈልጉ የከንቱ አስተሳሰብ ባለቤቶች አሁንም ህወሓት ውስጥ አሉ። እነኝህ በእራሳቸው አንዳንዴ የጦር ኃይሉም ሆነ ደህንነቱ መዋቅር የማያውቃቸው መሆናቸውን መገንዘብ ይገባል።በህወሓት ውስጥ ሌላ ህወሓት መኖሩን ማወቅ ይገባል።ይህ ግን በሰበብነት እየተጠቀሰ ሕዝብ መከራ የሚያይበት መንገድ ሊኖር አይገባም። ህወሓት ውስጥ ያሉ ለውጥ ያስፈልጋል የሚሉ ቀድመው መዋጋት ያለባቸው እውስጣቸው ያሉትን ለለውጡ በድብቅ እንቅፋት በመፍጠር የምረኩትን ትንንሽ አጋንንቶች ነው።እነኝህ በማንኛውም ጊዜ በተፈቱት እስረኞች ላይ ግድያ ለመፈፀምም ሆነ  ሌላ ተግባር በማድረግ ''ተጋዳላይ'' እያሉ ለመዝፈን የማይዳዳቸው ሰይጣን ብቻ የሚያደንቃቸው ፍጥረቶች ናቸው። በመጪው ዘመን የሚገጥመው አንዱ ፈተና ይህ ነው።ህወሓት እራሱን ማስተካከል ካለበት መጀመርያ ትንንሽ ሰይጣኖችን ማሰር እና ግቢውን ማስተካከል ይገባዋል።ከእዚህ በኃላ ስለለውጥ ሂደቱ መስመር ውስጥ መግባት ይችላል።በነገራችን ላይ እነኝህ በህወሓት ውስጥ የተፈጠሩ ትንንሽ ''ሰይጣኖች'' የትምህርት ደረጃቸው ዝቅተኛ፣የፖለቲካ ብስለታቸው በጠበንጃ ላይ  የተመሰረተ እና ስሜታዊነት ብቻ የሚመራቸው ስለሆኑ ለእራሳቸው በህወሓት ውስጥ ለለውጥ የሚያስቡትንም ከመብላት አይመለሱም።ሁኔታውን ወደፊት የምናየው ይሆናል።

በመጨረሻም በመጪው ሳምንት በሚደረገው የኢህአዴግ ስብሰባ እንደ ''አዲስ ስታንድአርድ'' የእንግሊዝኛ ጋዜጣ የትናንት ዘገባ ከሆነ ከመጪው ቅዳሜ በፊት በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ አዲሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ያስታውቃል።ይህ 21ኛው ክ/ዘመን ነው። ትውልዱ ብዙ ልቆ ሄዷል።ቢያንስ ወደ ዋናው እና ሁለንተናዊ ለውጥ ኢትዮጵያ እስክትመጣ ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ አይነት ጠቅላይ ሚኒስትር ቢያንስ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የቀውስ መንገድ ሐዲድ የማስገባት እና ሃሳቦችን የማመንጨት አቅም ያለው ሰው ያስፈልጋል።ኢትዮጵያ እና አካባቢው ያለው እንቅስቃሴ ከወታደራዊ እውቀትም ሆነ ከደህንነት እውቀት ያልራቀ ሰው ለጊዚያዊ የፖለቲካ ቀውስም ቢሆን የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው።ስለሆነም ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ መመረጥ ላይ ህወሓት ባያንገራግር እና በውስጡ የተፈጠሩ ጀብደኞችን አስታግሶ መሄዱ ለእራሱም የሚበጀው ነው የሚሆነው።በጅማ አጋሮ ያደጉት እና የተማሩት ሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አሕመድ ግጭቶች ምክንያታቸው እና መፍትሄዎቻቸውን ተመልክተዋል።ከእዚህ በታች የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ፕሮፖዛል የሰሩበት ሶሻል ካፒታል ቪድዮ ይመልከቱ።

የሌ/ኮ/ል ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የዶክትሬት ጥናት ፕሮፕዛል በማኅበራዊ ዕሴት (ሶሻል ካፒታል) ላይ በቪድዮ ሲያቀርቡ 
L/Co.Dr.Abiy Ahmed phd proposal in title Social Capital and its role in traditional Conflict resolution in Ethiopia(The case of jimma zone)


የአቶ ለማ መገርሳ ንግግር በባህር ዳር  (ቪድዮ)


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Monday, February 19, 2018

ጉዳያችን በእንግሊዝኛ ኦድዮ በቅርቡ ሥራ ትጀምራለች።Gudayachn audio in English is coming soon!




- ለምን የእንግሊዝኛ ዜና አስፈለገ?
ለምን ኦድዮ?
የእንግሊዝኛው ዝግጅት ከአማርኛው ዜና አቀራረብ በምን ይለያል?

ጉዳያችን ከ2003 ዓም ጀምሮ በድረ ገፅ በአማርኛ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና በመጠኑ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ዜናዎች እና መጣጥፎችን ለአማርኛ አንባቢዎች አቅርባለች።በእዚህም መሰረት ከአንድ ሚልዮን የሚልቁ ኢትዮጵያውያን ገፁን የጎበኙ ሲሆን ቁጥሩ በእዚህ ዓመት የበለጠ ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል።

አሁን ጉዳያችን ከአማርኛ ፅሁፎች ጎን የእንግሊዝኛ ኦድዮ ዜናዎች በተለይ አትዮጵያን በተመለከቱ ዜናዎች እና ጉዳዮች ባብዛኛው ኢትዮጵያን የተመለከቱ ዜናዎችን ለማቅረብ ታስባለች።

ለምን የእንግሊዝኛ ዜና አስፈለገ?

የእንግሊዝኛ ዜናው ያስፈለገበት ምክንያት ስለሶስት ምክንያት ነው።

1ኛ) ስለ እኛ እኛ መናገር ስላለብን : -

የኢትዮጵያ ጉዳይ ለቀረው ዓለም መንገር ያለብን እኛው መሆን አለብን።ሌሎች ስለኛ በተናገሩ ቁጥር ከባህላችን፣ታሪካችን እና ማንነታችን አንፃር ብዙ የማይረዱት ጉዳይ ስላለ ሌሎች በሚገባ የእኛን ጉዳይ ማቅረብ ያለብን እኛው ነን።

2) በውጭ የተወለዱ እና በማደጎ የመጡ  ትውልደ ኢትዮጵያን ስለ ሀገራቸው መረጃ እንዲያገኙ ለማድረግ 
በውጭ የተወለዱ እና በማደጎ የመጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር በባህር ማዶ ቀላል የሚባል ቁጥር አይደለም።ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ ደግሞ በአማርኛ የሚተላለፉ ዜናዎችን አይረዱም። ይህ ማለት ለኢትዮጵያ ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚችለው የሰው ኃይል ሀብት ከመረጃ ውጭ ሆነ ማለት ነው።በተለይ እንደ ሰሞኑ የሀገራችን ጉዳይ በእየጊዜው ሲቀያየር ይህ ትውልድ ከመረጃ ውጭ ሆነ ማለት ነው።

3) ለውጭው ዓለም እራሳችንን በሚገባ አለማስተዋወቃችን 

በርካት የውጭ ሀገር ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ለማወቅ አብዛኛው ከኢትዮጵያዊ የሚወጡት ዘገባዎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ ስላልሆኑ ከውጭው ዓለም ጋር ያለን ግንኙነት በሚገባው ደረጃ አይደለም።ስለሆነም የእንግሊዝኛ ኦድዮ አስፈላጊ መሆኑ ታመነበት።

ለምን ኦድዮ?

ኦድዮ የሆነበት ምክንያት የዘመኑን ተንቀሳቃሽ ትውልድ ተቀምጦ ከሚያነበው ይልቅ በመንገድ ላይ በመኪናው ውስጥም ሆነ በሕዝብ መመላለሻ ትራንስፖርት ውስጥም ሆኖ በቀላሉ በጆሮ ማዳመጫ  በመስማት መከታተል ያመቸዋል።

የእንግሊዝኛው ዝግጅት ከአማርኛው ዜና አቀራረብ በምን ይለያል?

በእንግሊዝኛ የሚቀርበው ዜና ባብዛኛው ጉዳያችን እራሷን ችላ በእራሷ የምታመጣው ዜና ላይሆን ይችላል።ሆኖም ግን በአማርኛ የሚዘገቡት ዜናዎችን ሀገርኛውን ቋንቋ ለማይረዳው ወገን መልሶ ማሰማት ጭምር እራሱ የመረጃ የማቅረቡ ሂደት አካል ነው። ከእዚህ በተለየ አቅም በፈቀደ ስለ እራሳችን ለቀሪው ዓለም እና ለአፍሪካውያን እንዲደርስልን የምንፈልገውን መልዕክት ለምሳሌ ታሪካችንን፣እምነታችንን እና ማንነታችንን የሚገልጡ በእንግሊዝኛ የተፃፉ ፅሁፎች በድምፅ  ይቀርቡበታል።
እዚህ ላይ የእንግሊዝኛው ዝግጅት ከአማርኛው በምን ይለያል? ለሚለው መልስ የሚሆነው የእንግሊዝኛው ለባዕዳንም ጭምር ስለሚደርስ ኢትዮጵያዊ ተቋሞቻችን እና እሴቶቻችን ላይ የበለጠ ጥንቃቄ ለማድረግ ይሞከራል።ለምሳሌ የውጭውን ስነ ልቦና የማይመጥኑ አገላለጦች በተቻለ መጠን ለማስወገድ እና ጨዋነት የተላበሱ ቃላት ለመጠቀም ይሞከራል።

ባጠቃላይ እራሳችንን ለቀሪው ዓለም የምንገልጥበት መንገድ በማነሱ ሳቢያ የሚጀመረው በድምፅ መረጃ ለቀረው ዓለም የማድረስ ሥራ በእናንተ አስተያየት እና ምክርም ጭምር ለፍሬ የሚያበቃ ሥራ እንደሚሆን ከፍ ያለ እምነት አለኝ።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Friday, February 16, 2018

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከህወሓት ውጭ ሌሎች የኢህአዴግ ድርጅቶች አልተስማሙበትም።ህወሓት በለየለት የዕብደት ሥራ ውስጥ ገብቷል። (ጉዳያችን አጭር ዘገባ)

 ጉዳያችን / Gudayachn
  የካቲት 10/2010 ዓም (ፈብሯሪ 16/2018 ዓም) 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመታወጁ ጉዳይ የህወሓት እና የህወሓት ፍላጎት ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ከአዲስ አበባ ያሳያሉ።ባለፈው ዓመት በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳት ላይ በከፍተኛ ደረጃ የአዋጁን መነሳት ሲቃወሙ የነበሩት የህወሓት ጎራ የሚገኙ ከፍተኛ ባለ ሀብቶች፣የወታደራዊ እና ጥቂት የኤሊቱ ወገን እንደነበር እና ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ጫና እና የውጭ ምንዛሪ ላይ ተፅኖ በመፍጠሩ መነሳቱ ይታወቃል።ሆኖም ግን አሜሪካ፣አውሮፓ እና ቦሌ ቅምጥል ህንፃዎች ውስጥ ተቀምጠው የሚሞተው ሕዝብ የማይገዳቸው "አዋጅ ነው ለእዚህ ሕዝብ መድሃኒቱ" በሚል ስላቅ የአሁኑ አዋጅም እንዲታወጅ አዋጁ ከመነገሩ አርባ ስምንት ሰዓታት በፊት በትግራይ ኦን ላይን ድረ ገፅ እና በፌስ ቡክ ሰራዊታቸው አማካይነት ማሰራጨት ጀምረው ነበር። ዛሬ የካቲት 9/2010 ዓም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ለጋዜጠኞች ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ መግለጫ እንደሚሰጥ ገልጦ ጋዜጠኞችን እስከ ምሽት ድረስ አስቀምጦ አዋጁ መውጣት እና አለመውጣት ላይ ሲከራከሩ ያመሸው ህወሓት መሩ ስብሰባ ያለውጤት በመቆየቱ ጋዜጠኞች እንዲመለሱ መልዕክት ከተነገረ በኃላ ምሽት ላይ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እና ራድዮ አዋጁ እንደወጣ ተነገረ።የሆነው ይሄው ነው።በእዚህ ላይ ኦህዴድም ሆነ ብአዴን ያሉት ነገር እየቆየ የሚታይ ጉዳይ ነው የሚሆነው።ጉዳዩ ግን የሚያመለክተው አሁንም የኢትዮጵያ ችግር እያጠነጠነ ያለው በህወሓት አጉል ጀብደኝነት እና ትዕቢት ዙርያ መሆኑን መረዳት ይቻላል።

ህወሓት ኢትዮጵያን ከቀውስ ወደ ቀውስ እየወሰዳት ነው።የእዚህ አይነት አዋጅ ትናንት ከስልጣን ለቅቅያለሁ አንዳንድ ስራዎች እንዳይቆሙ እስካስረክብ ብቻ ኃላፊነት እወጣለሁ ያለ ጠቅላይ ሚኒስትር ያለው እና ከኃላፊነት የወረዱበት ካቢኔ የእዚህ አይነት አዋጅ ያውም ምክር ቤቱ ባልተወያየበት ደረጃ ማውጣት ይችላል ወይ? ይህ ጥያቄ ለጦር ሰራዊቱ ፊደል ቆጥረናል ለሚሉ ይቅረብልኝ።

 የዛሬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውሎ ብቻ የሚያሳየው ህወሓት  የትግራይ ኦን ላይን የመሰሉ ድረ ገፆችን  እና ጥቂት በስልጣን እና ሙስና ያበዱ ግለሰቦችን ይዞ የለየለት የእብደት ሥራ ውስጥ እንደገባ  እየታየ ነው።ሌላው ቀርቶ ከአሁን በኃላ በህወሓት አፈቀላጤ የሆኑ ድረ ገፆች እና ማኅበራዊ ሚድያ ላይ የሚተላለፉት መልክቶች የእራሱ የህወሓት ሙሉ ስምምነት ላይ ያልተደረሰባቸው ይልቁንም ጥቂት ደፋር ነን ባዮች በፈጠሩት የአናርኪ ቡድን የሚንቀሳቀስ መሆኑን ማወቅ ይቻላል።ይህ ማለት ካለው ህወሓት ውስጥ እራሱ ሌላ ጀብደኛ ነኝ ባይ ትንሽ ህወሓት እንደፈጠረ አመላካች ነው።በሌላ በኩል አቶ ገዱ ከስልጣን ወርደዋል የሚለውን ዜና እራሱ ሐሰት መሆኑን አሁንም ከሀገር ቤት የሚመጡ ዜናዎች ይጠቁማሉ።ይህንኑ ዜና ዛሬ ሲያሰራጩ የዋሉት ግን አሁንም የህወሓት አፈቀላጤ ማኅበራዊ ሚድያዎች ናቸው።  የአቶ ገዱን እና አቶ ደመቀ ከስልጣን ተነሱ የሚለው ዜና ውሸት መሆኑን የክልሉ ቃል አቀባይ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በፌስ ቡክ ገፃቸው ''ዶሮ ብታልም ጥሬዋን'' በሚል ርዕስ በሰጡት ምላሽ ዜናው ሐሰት መሆኑን ሲያብራሩ 
'' በሰበር ዜና ለሚያሰሙን ህልመኞች መሪውን የሚመርጠው ድርጅቱ እና የአማራ ህዝብ ስለሆነ መመኘት ይቻላል ፤ እዉነት ግን ወዲህ አለች ” እንላለን።ህዝባችንም ይህንን አይነት ዘመቻ የተለመደ ስለሆነ የድርጅቱን ውሳኔዎች ውይይታችን በሚቀጥሉት ቅርብ ቀናት እስኪጠናቀቅ እና ትክክለኛው መረጃ በድርጅቱ በኩል እስኪሰጥ ድረስ ለሚለቀቁ እንዲህ ዓይነት የህልም ዜናዎች ጆሮ እንዳይሰጥ እንጠቁማለን።
“ዶሮ ብታልም ጥሬዋን”  ብለዋል። (የአቶ ንጉሡ ምላሽ ይህ ፅሁፍ በሌሎች ድረ ገፆች ከወጣ በኃላ የተጨመረ ስለሆነ የጉዳያችን ዜና በወጣባቸው ሌሎች ገፆች ላይ ባታገግኙት ከድረ ገፆቹ ስህተት አለመሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን)።

ባጠቃላይ ህወሓት አሁንም ኃላፊነት የተሰማው ተግባር እየፈፀመ አይደለም።ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር እጅግ የሚጎዳት ነው።አሁን ሁለተኛው ምዕራፍ የነፃነት ትግል እንደተጀመረ አመላካች ሁኔታዎች አሉ። የመጀመርያውን ምዕራፍ ሕዝብ አይኑን እንዲገልጥ ለነፃነቱ እንዲናገር እንዲደፍር ጥቂቶች እነ እስክንድር ነጋ፣በቀለ ገርባ፣ እና ሌሎች በፈንጅ ላይ የመራመድ ያህል ተረማምደው የህዝብ ልቦና አንቅተዋል።አሁን ሁለተኛው ምዕራፍ ላይ በአንደኛው ምዕራፍ ላይ ዝም ያልን በሙያችን እና ባለን አቅም ሁሉ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ፍቅር፣እና ሰላማዊ ሽግግር እንነሳ።ኢትዮጵያን እንደ ሀገር መልሰን እናቁማት።ህወሓት ከጋረጠባት አደጋ እንታደጋት።

ኢትዮጵያ ሀገሬ 



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Thursday, February 15, 2018

ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሁኔታ ስልጣን በእጁ ያለው ህወሓት በፍጥነት እና በድፍረት መውሰድ ያለበት አስራ ስድስት ቁልፍ እርምጃዎች ( ጉዳያችን)


አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ጥይቄ የህወሓት ከስልጣን የመውረድ ብቻ አይደለም።የኢትዮጵያ የግዛት እና የሕዝብ አንድነት ጥያቄም ጭምር ነው።ስለ አቶ ኃይለማርያም ቀደም ብሎ የወጣውን ፅሁፍ ከፃፍኩ ከተኛሁ በኃላ ስለ ኢትዮጵያ ተጋድሜ ማሰላሰል ጀመርኩ።እንቅልፍ በአይኔ አልዞረም።ሰዓቱ ሌሊቱ አልቆ ሊነጋ ነው።ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ነች።ስለ ህወሓት ከስልጣን አለመልቀቅ ስላስከተለው ምስቅልቅል ሁኔታ ብዙ ተፅፏል።ህወሓት የሰራው ስህተት እዚህ አድርሶናል።አሁን ጥያቄው ግን የአንድነት አደጋም ጭምር ነው።

ስለሆነም እንደ ሀገር የተደቀነውን አደጋ ለማስወገድ ለጊዜው ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ስልጣኑ በህወሓት ስር እስካለ ድረስ ህወሓት የብዙሃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ አዎንታ ያስገኘ ለውጥ ለመጀመር የሚችለው በመጀመርያ ያለፈ የጎሳ ፖለቲካው ስህተት መሆኑን በግልጥ አምኖ የሚከተሉትን አስራ ስድስት ነጥቦች በድፍረት መተግበር ከቻለ ነው።

1/ በጎሳ ስም የፖለቲካ ድርጅት መመስረት በመላ ሀገሪቱ መከልከል አለበት፣

2/ ከእዚህ በፊት በጎሳ ስም የተደረጁ ጥምረት ፈጥረው ወይንም ለብቻቸው ሃገራዊ ስም ወይንም የቃላት ሐረግ መርጠው እንዲሰየሙ መታዘዝ አለባቸው ፣

3/ ህወሓት ስሙን በፍጥነት ሃገራዊ ስም መስጠት አለበት ማንም ኢትዮጵያዊ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ትግሪኛ ተናገረም አልተናገረ አባል መሆን መቻል አለበት፣

4/ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት መመስረት እና ህገ መንግስቱን ማሽሻል፣

5/ የብሔራዊ ዕርቅ ኮሚሽን ከሀገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች እና ሴቶች የተውጣጣ ካለ ምንም የፖለቲካ ተፅኖ መመስረት እና ሥራ ማስጀመር፣

6/ ለዲሞክራሲ ሂደቱ ዋስትና የሚሆኑትን ሚድያ በነፃ እንዲዘግቡ ማድረግ፣

7/ የፍትህ ስርዓቱን በገለልተኛ ባለሙያዎች እንዲመራ ማድረግ 

8/ የሃማኖት አካላት በሙሉ ነፃነት እንዲሰሩ መፍቀድ በውስጣቸው ያለውን ንቅዘት እንዲነቀል ከሕዝቡ ጋር በቅንነት መስራት፣

9/ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ወደ ሀገር በነፃነት የመግባት ፍቃድ መስጠት።ከእዚህ በፊት በፖለቲካ የተከሰሱት ሁሉ ነፃነት ማወጅ 

10/ የጦር ኃይሉን እና የደህንነት መዋቅሩን ሁሉን አቀፍ ማድረግ ይህንንም የሚያረጋግጥ ልዩ የህዝብ ኮሚሽን መሰየም፣

11/በሙስና ያጠፉ፣በሰብዓዊ መብት ረገጣ እና በልዩ ልዩ ወንጀል የሚጠየቁ አካላትን በሙሉ ለፍትህ ማ1ቅረብ ህዝብን እና ትውልድን አስተማሪ በሆነ መልኩ ይያለፈ ስህተትን ማረም፣

12/ የሰማዕታት ሃውልት በማለት የተሰሩት ሐውልቶች ሙሉ በሙሉ የቅርፅም ሆነ የይዘት ለውጥ ተደርጎባቸው በሃያኛው ክፍለ ዘመን በደርግም ሆነ በህወሓት ወይንም በኢህአፓም ሆነ በኢድዩ ወይንም በኦነግ ስር ሆነው  ለሞቱት የሃውልቱ ሁሉ የጋራ መታሰቢያ እንዲሁን አዲስ ስያሜ ለምሳሌ  በእርስ በርስ ጦርነት ህይወታቸውን ላጡ ወይንም ሌላ የወል ስም ተፈልጎ እንዲሰየም ፣

13/ ኢትዮጵያ አንድ የብሔራዊ ክብር ቀን እንዲኖራት በእዚህም ቀን ያለፈ የእርስ በርስ ጦርነት ምዕራፍ መዝጊያ መታሰቢያ ቀን ሆኖ ቀኑ የዕርቅ እና የአንድነት ቀን ሆኖ እንዲታስብ እንዲታወጅ ፣

14/ ህወሓት በስሩ ያሉትን የኤፈርት ንብረቶች ወደ ሕዝብ ንብረትነት እንዲቀየሩ እንዲያደርግ ፓርቲዎች የሚኖራቸው ሀብት በሕግ እንዲወሰን  

15/ ኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ ፍትሃዊ የሆነ እንዲሆን እና ኢትዮጵያ የፕረዝዳንታዊ ሀገር እንጂ በጠቅላይ ሚኒስትር የምትመራ ሀገር መሆኗ እንዲቆም ቢደረግ እና 

16/ አሁን ያለው የጎሳ አከላለል ስርዓት ጎሳን ሳይሆን  በጅኦግራፍ፣ታሪክ እና ባህልን መሰረት ያደረገ የፌድራል አከላል ስርዓት እንዲዘረጋ እንዲያደርግ የሚሉት ናቸው።

ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት ለመከወን ህወሓት አሁን ባለው የሰው ኃይል ወይንም ሕዝቡን ደጋግመው ሲዋሹ በተያዙ ባለስልጣናቱ  ማከናወን አይችልም።ስለሆነም አዲሱ ትውልድ ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱን መውሰድ አለበት።ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ህወሓት እራሱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እንደሚጥላት ሳይታለም የተፈታ ነው።

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

የጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ስልጣን መልቀቅ ለውጭው ዓለም፣ተራው የጦር ሰራዊት አባል እና ለገጠሩ ነዋሪ ያለው መልዕክት። የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ምን አሉ? (ጉዳያችን)


ጉዳያችን/Gudayachn 
የካቲት 10/2010 ዓም (ፈብሯሪ 16/2018)

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሚከተሉት ንዑስ ርዕሶች ይነበባሉ። እነርሱም : -

- የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በዛሬዋ እለት ስለአቶ ኃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ አስታከው ምን  
  አሉ? (ሊንኮቹን በመጫን ማንበብ ይችላሉ)፣
- የአቶ ሃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል፣በተራው የጦር ሰራዊቱ አባል 
  እና  ለውጭው ዓለም ያለው መልዕክት፣
- ህወሓት እራሱ በውስጡ በሁለት  "ከይሲ" ኃይሎች ተወጥሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ የካቲት 8/2010 ዓም ከስልጣን መልቀቃቸውን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሰበር ዜና አስታውቀዋል።አቶ ሃይለማርያም በንግግራቸው ውስጥ የተጋጩ በርካታ ቃላት አሉበት።ከእዚህ ውስጥ ስልጣን የሚለቁት "የለውጡ ሂደት አካል ለመሆን ነው" የሚለው አባባል ነው። የለውጡ ሂደት አካል ለመሆን ከጠቅላይ ሚኒስትርነት እና ከደቡብ ህዝቦች ግንባር መውጣት አስፈላጊ መሆኑን እየገለጡ ነው እንዴ? ማለት ያስፈልጋል። ይህ የብዙ ነገሮች አመላካች ነው። በመጀመርያ በኢህአዴግ ውስጥ ሆኖ በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ ሆነህም ለውጥ ልታመጣ አትችልም የሚል መልዕክት ሲኖረው በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓትን መታገል እና የለውጥ አካል መሆን የሚቻለው በውስጡ ሳይሆን ወጥቶ በተቃራኒ በመቆም ነው የሚል መልዕክት ያለውም ይመስላል።

የአቶ ኃይለማርያም ሌላው በንግግራቸው ውስጥ የጠቀሱት ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያ በአስከፊ ሁኔታ ላይ መሆኗን ይገልጣሉ።አስቸጋሪ ማለት ሲያብራሩ በመገናኛ ብዙሃን የተነገሩትን የህዝብ መፈናቀል እና ሞት ጠቀሱ እንጂ የውጭ ምንዛሪው ማለቁን፣ምጣኔ ሃብቱ ከእዚህ በላይ አለማስኬዱን አላብራሩም።

የአቶ ሃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል፣በተራው የጦር ሰራዊቱ አባል እና  ለውጭው ዓለም ያለው መልዕክት

ለገጠሩ ክፍል

በማኅበራዊ መገናኛዎች የአቶ ኃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ በበርካታ ቀልዶች ታጅቦ ሃሳብ እየተሰጠበት ነው።ሆኖም ግን ኢትዮጵያን በደንብ ከተረዳናት እያንዳንዱ የኅብረተሰብ ክፍል መንግስት የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ ከሚሰጠው ትርጉም አንፃር የእራሱ የሆነ ትርጉም የለውም ማለት አይላችልም።ኢትዮጵያ ከ85% በላይ ሕዝብ የሚኖረው በገጠር ነው።በተለይ በገጠር እና ጠረፋማ አካባቢዎች አቶ ኃይለማርያም በቂ ስልጣን እንደሌላቸው የማያውቅ የለም ብለን ባንገምት ከፍተኛ ቦታ ላይ ቢያንስ በስም መሆናቸውን ይረዳል።ይህ ማለት ለአንዳንድ የገጠር አካባቢዎች እና ጠረፋማ ቦታዎች ትርጉሙ መንግስት ፈረሰ ነው።

በሌላ አገላለጥ ለአካባቢው አስተዳደር አለመታዘዝ እና ግብር በወቅቱ ላለመክፈል መዘግየት አስፈላጊ መሆኑ ላይ ባለሀገሩ ያስብበታል።ይህ ማለት የአካባቢ አስተዳደሮች ቀድሞም የነበረው ደካማ የአስተዳደር አቅም በፍጥነት የማስፈፀም አቅም መውረድ ላይ ይወድቃል።ይህ እንግዲህ በስነ ልቦና ሂደት ብቻ የሚመጣ ነው።ከእዚህ ሁሉ በላይ ግን በገጠሩ የኢትዮጵያ ክፍል መንግስት እየፈረሰ መሆኑን ከመረዳት በላይ ከተቃዋሚዎች ጋር መሰለፍ አስፈላጊ መሆኑን የገጠሩ ሕብረተሰብ ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያምንበት ወቅት ነው።ይህ  ማለት በከተማው የእዚህ አይነት ስሜት አይፈጠርም ማለት አይደለም።ሆኖም ግን በገጠር ያለው ሁኔታ እና ትኩሳት ቀላል አይሆንም።

ለውጭው ዓለም

የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መልቀቅ ለውጭው ዓለም ከምንጊዜውም በላይ ትልቅ ደውል አስተላልፏል።ይሄውም የህወሓት መንግስት እያበቃለት መሆኑን ከምንጊዜውም በላይ የተረዱበት ወቅት ነው ለእዚህም ነው የአቶ ኃይለማርያምን መልቀቅ ቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ጨምሮ አመፁን ተከትሎ መልቀቃቸውን እየገለጡ ያለው።ይህ ማለት አቶ ኃይለማርያም ስልጣን የለቀቁት በአመፁ ግፊት እንደሆነ ደምድመዋል።በአጭሩ የአቶ ኃይለምርያም መልቀቅ የበርካታ ሀገሮችን የውጭ ፖሊሲ ከምር እንዲመለከቱ የሚያደርግ ነው።ይህ ማለት የህወሓት መንግስት በፍጥነት ሊወድቅ እንደሚችል እና መጪው ግንኙነት ምን፣እንዴት እና ከማን ጋር መሆን እንዳለበት አሁንም ከምር እንዲያስቡ ያስገድዳል።

በተራው የጦር ሰራዊት አባል ውስጥ

በአሁኑ ሰዓት ያለው የኢትዮጵያ ሰራዊት መካከለኛ እና ከፍተኛ መኮንኖች በህወሓት አባላት እና አፍቃሪዎች የተሞላ ቢሆንም ተራው ሰራዊት ግን አሁንም ከሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።ይህ ማለት በኢትዮጵያ የሚደረጉት የግፍ ስራዎች ሁሉ ይመለከታል፣ይሰማል፣ስሜቱ ከሁኔታዎች ጋር ይቀያየራል።የአቶ ኃይለማርያም ከስልጣን መልቀቅ ለተራው ሰራዊት አንድ ነገር ግልጥ ያደርግለታል። እዚህ ላይ ሰራዊቱ ሌላው ሕዝብ ከማኅበራዊ ሚድያም በተባራሪ የሚደርሰው መረጃ ለእርሱ ብርቅ ነው።የእርሱ መረጃ ከመንግስት ሚድያ እና ከካምፕ ሲወጣ ከሚገናኘው ቤተሰብ እና ወዳጅ ነው።ዛሬ አቶ ኃይለማርይም ስልጣን በፈቃዳቸው ለቀቁ ማለት ለምን? የሚል ጥያቄ ይጭራል። ለሰራዊቱ ቢያንስ አንድ ነገር እርግጠኛ ይሆናል።ቤተ መንግስት ውስጥ ችግር አለ የሚለው እና በህወሓት እና በሌሎች ተጣማሪ በነበሩት መሃል ያለው ችግር ከሚገባው በላይ ተካርሯል ማለት ነው ይላል።ይህ መረጃ የሚያሳየው ጉዳይ መጪው ጊዜ የለውጥ መሆኑን ያሳየዋል።ውጤቱ ምን ይሆናል የሚለውን ወደፊት የሚታይ ነው።

ህወሓት እራሱ በውስጡ በሁለት  "ከይሲ" ኃይሎች ተወጥሯል


ብዙ ቅን ፖለቲከኞች ወይንም አስተያየት ሰጪዎች ከአሁን በኃላ ህወሓት ወደ ሽግግር መንግስት እንዲሄድ  ይገድዳል፣ነገሮች ሳይበላሹ ስልጣን ህወሓት ይለቃል ወይንም ነፃ ምርጫ ይሳተፋል ብለው ያስባሉ። ይህ ግን የህወሓትን ባሕሪ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው።ህወሓት እራሱ በውስጡ በሁለት "ከይሲ" ኃይሎች ሃሳብ ተወጥሯል።ከይሲ የሚለውን ቃል የክፉ ክፉ በሚል ትርጉም ውሰዱልኝ።የመጀመርያው የህወሓት ከይሲ ቡድን መሃል ሃገሩን ለጊዜው ለቀቅ እናድርግ እና ትግራይ ላይ እናተኩር።ትግራይ ላይ ስናተኩር ግን የዐማራ አዋሳኝ ቦታዎች ይዞታዎቻችንን ማጠናከር እና የመሃል ሀገር ጥቅማችንን ፖለቲካውን በተወሰነ ደረጃ በመልቀቅ ምጣኔ ሃብታዊ የበላይነት ላይ እናተኩር የሚል ሲሆን ይህ ቡድን አቶ ኃይለ ማርያም በህወሓት ሰው ካልተተኩ የመሃል ሀገር አስተዳደር እንዲዳከም ዘረፋ እንዲስፋፋ እና ሕዝብ ህወሓት ተመልሶ እንዲመጣ እንዲለምነው ተስፋ ያደርጋል።ይህም ማዕከላዊ መንግስትን ለተወሰነ ጊዜ  በማላላት ለተደራጀው ህወሓት የዘረፋ ጊዜ መግዛት የሚል ሃሳብ ነው። በመሆኑም በብሄር መካካል ጠብ መባባስ ላይ እና የዘረፋ ዜናዎች በብዛት እንዲሰሩ ያስባል።

ሁለተኛው ከይሲ ቡድን ተደፈርን ባይ ነው።ትናንት የተፈቱት እስረኞች የህወሓት ሞት ነው ባይ ነው። የእዚህ ቡድን አባሎች በከፍተኛ ዘረፋ የናጠጡ በሀገር ውስጥ እና ውጭ ሀገር እየኖሩ የሚፎክሩ ሲሆን በከተሞች አካባቢ ህወሓት ያስታጠቃቸውን መሳርያ ቁምሳጥን ውስጥ አስቀምጠው ዘራፍ የሚሉ ናቸው።ይህ ቡድን በህወሓት ውስጥ ነገሩ አለማስከዱን አምነው ለውጥ ለማምጣት ዳር ዳር የሚሉትን ቁም ስቅል የሚያሳዩ ቡድኖች እነኝህ ናቸው። አቶ መለስ በ1997 ዓም የቅንጅት መሪዎች ባይታሰሩ ኖሮ እልቂት ነበር እያሉ የተሳለቁት እነኝህን ቡድኖች ጋር ከተመካከሩ በኃላ ነው።በአፍሪካ የእዚህ አይነት ቡድኖች የተለመዱ ናቸው።በብሔራዊው ጦር መተማመን ያልቻሉ አምባገነኖች እና የጎሳ ቡድኖች ሁል ጊዜ የእዚህ አይነት ከይሲ ቡድን የስልጣናቸው መጠበቂያ ያደርጉታል።ሆኖም ግን የእዚህ አይነት ቡድኖች የሰሩት ወንጀል ስቆለል እና ህሊናቸው በእራሱ ጥፋት ሲበሳሳ የሞራል ልዕልናቸው ተንኮታኩቶ ሕዝብ እጅ የወደቁ ቀን ዝናብ የመታት ዶሮ መሆናቸው ከግብፅ እስከ ኢራቅ የታየ ነው።

የሁለቱ ብድኖች እነኝህን የከይሲ ስራዎች ለመስራት በማገቻነት የሚጠቀሙት የትግራይን ሕዝብ ነው።ለእዚህም ሕዝቡን በማናቸውም መንገድ ከቀረው ሕዝብ ጋር ማጋጨት ብቸኛ አማራጭ መንገዳቸው ነው።ጭር ካለ እንደ አደጋ ያዩታል።ለምሳሌ ሰሞኑን በሰሜን አሜሪካ የትግራይ ልማት ማኅበር የአሜሪካ ድምፅ ራድዮ እና ኢሳትን ለመክሰስ መወሰኑ አንዱ ምክንያት በሰሜን አሜሪካ የሚኖረው የትግራይ ተወላጅ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንዳይተባበር አንድ አይነት ማኅበራዊ ግጭት ማስነሻ ጉዳይ ለመፍጠር ሁለተኛው የከይሲ ቡድን የመክሰስ የሚል ሃሳብ ይዞ ብቅ አለ።በነገራችን ላይ የትግራይ ልማት ማኅበር በእዚህ ሳብያ ገንዘብ ለማሰባሰብ እና በሙስና የተጨማለቀው አመራር ኪስ ለማድለብ የታለመ ነው።አሁንም ግን የትግራይ ማኅበረሰብ ከእዚህ በላይ በጥቂት ከይሲ አስተሳሰብ አራማጆች ባይታለል በጣም ጥሩ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁለቱ ከይሲ ቡድኖች እንደሚያስወሩት ሳይሆን በነገዋ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው ከትግራይ ሆነ ከጅጅጋ  በመሆኑ ብቻ አንዳች በደል እንደማይደርስበት ዋስትና የማትሰጥ ሆና እንደማትሰራ ከአሁኑ ማመን ተገቢ ነው።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢም ተስፋ ሰጪም ደረጃ ላይ ነው ያለው።አሳሳቢነቱ የህወሓት ከይሲ ቡድኖች ከጀርባ እንደ ባዕድ የሚሸርቡት ተንኮል ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ መስመር የመውሰድ አደጋ አለው።ለምሳሌ ዛሬ የሚናፈሰው ከአቶ ኃይለማርያም የመልቀቅያ ጥያቄ ተከትሎ አዋጅ ለማወጅ እያሰበ ነው የሚል በእራሱ የማኅበራዊ ሚድያ መስመር በኩል እየተሰማ ነው።ይህ ኢትዮጵያን ሆን  ብሎ ወደ እርስ በርስ ትርምስ ለመክተት በህወሓት የተወሰነ ውሳኔ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።ምክንያቱም ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በእራሷ የፀጥታ ችግር የለባትም።የፀጥታ ችግሯ የህወሓት ስልጣን ጠቅልሎ መያዝ የጎሳ እና አድሏዊ ስርዓት ያደረሰው ጥፋት ነው።ይህንን ለመፍታት የችግሩ መፍትሄ በውድም ሆነ በውድ ህወሓት ስልጣን ለሕዝብ  እንዲያስረክብ ማድረግ ነው።ይህ የአዋጅ ጋጋት እና  የአስከሬን ክምር አያስፈልገውም። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ተስፋ ሰጪም ነው። ይህ ማለት ሕዝብ በኅብረት ተነስቷል።በቃኝ ያለ ሕዝብ በእራሱ መድረሻው ምን ይሁን ምን አልገዛም ብሏል።ይህ የኢትዮጵያ ተስፋ ነው።ሌላው ተስፋ ኢትዮጵያ ይህንን የሁለት ከይሲ ቡድኖች ተንኮል ከተሻገረች ብሩህ የሆነ ሕብረት የመፍጠር ዕድል አላት።ይህ ዕድል የበለጠ የሚሳካው ደግሞ የቀና ሃሳብ ያላቸው የህወሓት  አባላት ሁለቱን የከይሲ ቡድኖች አስተሳሰብን ማምከን ችሎ መራመድ ከቻለም ጭምር ነው።

የዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች በዛሬዋ እለት ስለአቶ ኃይለማርያም ስልጣን መልቀቅ አስታከው ምን አሉ? (ሊንኮቹን በመጫን ማንበብ ይችላሉ)

ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

Tuesday, February 13, 2018

ኢትዮጵያ ከአሁን በኃላ ከነፃነት ውጭ አንድም ቀን መቆየት አትችልም።የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሃገራዊ ወይንም ብሔራዊ ጥያቄ ላይ ያተኮሩ አድርጎ መነሳት ይገባል። (የጉዳያችን ማሳሰቢያ)



 በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉት ሃሳቦች በአጭር ንዑስ ርዕሶች ስር ተነስተዋል።እነርሱም : -
  • ከህወሓት በኃላ ኢትዮጵያን የመቅረፅ አቅም ያላቸው ሶስቱ ኃይሎች እነማን ናቸው?
  • የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሃገራዊ  ወይንም ብሔራዊ ጥያቄ ላይ ያተኮሩ አድርጎ መነሳት ይገባል
  • በኦሮምያ ያለው እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉት ሁለቱ  አስተሳሰቦች 
  • “ኧረ አምሳለ” በገጣሚት ምልእቲ ኪሮስ (ቪድዮ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት ሩብ ክፍለዘመን በህወሓት የጎሳ ፖለቲካ ተጭኖባት፣ ህዝቧ እርስ በርሱ እንዲከፋፈል በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር በርካታ ደባዎች ተሰርቶበታል።ይህ ሁሉ ደባ ተሰርቶበትም ግን ህዝቡ ዛሬም ባገኘው መንገድ ሁሉ ለነፃነቱ እየተዋደቀ ነው።

ለነፃነቱ የሚዋደቀው በተለይ አዲሱ ትውልድ እጅግ አስደማሚ እና አስደናቂ ሂደቶችን እየሄደ በብዙ የምጣኔ ሀብት ድቀት፣የመገደል እና የመታሰር ፈተና ውስጥ እያለፈ ዛሬም ድምፁን ከፍ አድርጎ ለነፃነቱ እየታገለ መሆኑን በተግባር አሳይቷል።ለእዚህም በኦሮምያ፣ዐማራ እና ሌሎች ቦታዎች የታዩት የትግል ሂደቶች ሁሉ መጥቀስ ይቻላል።ሆኖም ግን እስካሁን የሚደረጉት ትግሎች ሁሉ በህወሓት ከስልጣን መውረድ ላይ ቢስማማም ሃገራዊ የጋራ አጀንዳ ላይ አተኩሮ የሚደረጉ ትግሎች እየተቀነቀኑ ያሉት በሁሉም ዘንድ አይደለም።

በኦሮምያ ያለው እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉት ሁለቱ  አስተሳሰቦች


በኦሮምያ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ በሁለት ክፍል ከፍሎ መመልከት ይቻላል።እነርሱም : -

 ሀ) በኢትዮጵያዊነት እና የግዛት አንድነት ጉዳይ ጥብቅ አመለካከት ያላቸው

በእዚህ ክፍል ያለው አብዛኛው የኦሮም ሕዝብ ከደመነፍሱ እስከ ተግባራዊ ሃሳቡ ድረስ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ላይ ጥልቅ ስሜት ህዝቡ ውስጥ አለ።አንዳንዶች ባለፈው 26 ዓመታት በኦሮምያ ትውልዱ ተቀይሯል ብለው ይናገራሉ።ይህ ግን ከሕብረተሰብ አቀያየር ሂደት በራቀ መልክ የሚደመድሙት የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። ለእዚህ ማስረጃ የሚሆኑ ነጥቦች ማንሳት ይቻላል።

የመጀመርያው ማስረጃ የኦሮምያ ክልል በእራሱ የያዘው የህብረተሰብ ክፍል የቅርብ ታሪክ መመልከት በቂ ነው።በኦሮምያ ክልል ውስጥ አሁን በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት ወጣቶች የተቀረፁት እና እየሰሙ ያደጉት ለኢትዮጵያ አንድነት ለአመታት ሲፋለሙ የነበሩ የቀድሞ ጦር ሰራዊት አባላት (አሁን በእርግና እድሜ የሚገኙ) ጭምር ነው። ኦሮምያ በቀደሙት የኢትዮጵያ ሰራዊት ከከፍተኛ ማዕረግ እስከ ተራ ወታደር ትልቅ ተሳትፎ ነበራት።በእያንዳንዱ የኦሮምያ መንደር ውስጥ የቀድሞ ሰራዊት አባላት፣በቀድሞ ስርዓቶች በከፍተኛ የኑሮ ደረጃ የነበሩ እና በዘመነ ህወሓት ወቅት ከብሄራዊ ጥቅሞች ሁሉ የተገፉ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚነግሩት ህወሓት ያመጣው ድህነት እንጂ ኢትዮጵያ ያመጣችው ድህነት አይደለም በማለት ነው።ለእዚህ አብነት የሚሆነን የአምቦ እና የቢሸፍቱ ከተሞች ናቸው።እነኝህ ከተሞች በርካታ የጦር ሰራዊት መኮንኖች መኖርያ ከተሞች ናቸው።ልጆቻቸው ዛሬ ደርሰው የኢትዮጵያ አንድነት ጠላቶች ናቸው ብሎ የሚያስብ ነገሮችን ጠለቅ አድርጎ ማየት የተሳነው ነው።

በሁለተኛ ደረጃ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት እና የግዛት አንድነት በኦሮምያ ውስጥ ለመኖሩ ማሳያው ህዝቡ ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ያለው ጠንካራ ማሕበራዊ ትስስር  ነው።ማኅበራዊ ትስስር ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው።በኦሮምያ ከአስር ሚልዮን የሚበልጥ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ መሆኑ መጥቀሱ በእራሱ አንዱ የትስስር ማሳያ ነው።ይህ ትስስር ከገበያ እስከ ቤተሰባዊ ትልቅ ታሪካዊ ትስስር ያለው ነው።እነኝህ ሁለት የትስስር አይነቶች ለመግለጥ ያስፈለገው በቀላሉ ነገሮች ለማስረዳት እንጂ ወደ ጠለቀው የኢትዮጵያዊነት ትስስር ስንገባ በርካታ ታሪካዊ እና የማይበጠስ የደም ትስስር ያለው ሕዝብ ነው።ኢትዮጵያን ከኦሮሞ ሕዝብ ውጭ ማሰብ አይቻልም።ስለሆነም ለኢትዮያዊነት ለመመስከር ከኦሮሞ ማኅበረሰብ በላይ ሌላ ሊመጣ አይችልም።አቶ ለማ መገርሳ የኦሮምያ የወቅቱ ፕሬዝዳንትም የመሰከሩት ይህንኑ ነው።አሁን የምናምነው በሚናገሩት ነው።የተናገሩትም '' የኢትዮጵያ አንድነት ከአህያ ቆዳ የተሰራ አይደለም ጅብ ስጮህ የሚፈራርስ።ኢትዮጵያን የገነቡት አባቶቻችን ናቸው" ነው ያሉት።ይህ ማለት በእዚህ በኩል የሚቀርበው ስጋት በጣም የተጋነነ እና ሚዛኑ የሚደፋ አይደለም ለማለት ነው።ይህ ማለት ግን በኦሮምያ ስም የሚነግዱ አልተፈጠሩም ማለት አይደለም።

 ለ) በኢትዮጵያዊነት እና አንድነት ጉዳይ ለዘብተኛ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች

በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ለዘብተኛ እና ቅድምያ ለክልሉ ብቻ በመስጠት የፖለቲካ ግብ መምታት ይቻላል የሚለው አስተተሳሰብ በውስጡ ሁለት አይነት ኃይሎች በአንድነት ተባብረውበት ይታያል።እነርሱም የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ከወያኔ በኃላ የሚነሳ ጉዳይ ነው ቅድምያ ወያኔ መውረድ ላይ እናተኩር የሚሉ እና ወያኔ ከወረደም በኃላ የኢትዮጵያ አንድነት ብሎ ነገር አይታሰብም "ሰባብረን እንሰራታለን" ባዮች ናቸው።ሆኖም ግን ከቁጥር አንፃር በኢትዮጵያ አንደነት ላይ አሉታዊ ስሜት ይዘው የሚሄዱት ከቁጥር አንፃርም ሆነ ከህዝብ ድጋፍ አንፃር ቁጥራቸው ብዙ አይደለም።ሆኖም ግን በአደረጃጀት እና ድብቅ አጀንዳቸውን አቆይተው የህዝቡን ስሜት አይተው ለመንቀሳቀስ ያደፈጡ ናቸው ማለት ይቻላል። ይህንን እውነታ ከህዝብ ደብቆ መሄድ ፈፅሞ አይቻልም።እውነታው አለ ሆኖም ግን የህዝብ ሃሳብ አሉታዊውን አስተሳሰብ እንደሚሞርደው ማመን ይቻላል።

የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ሃገራዊ  ወይንም ብሔራዊ ጥያቄ ላይ ያተኮሩ አድርጎ መነሳት ይገባል


አሁን ቀዳሚው ጉዳይ የነፃነት ጥያቄ ነው።ኢትዮጵያ ከአሁን በኃላ ከነፃነት ውጭ አንድም ቀን መቆየት አትችልም።ሕዝብ ከበቂ በላይ ታግሷል።ከበቂ በላይ ተገድሏል፣ታስሯል፣ክብሩ በባዕዳን ተዋርዷል፣ሀብት ንብረቱ ተዘርፏል፣የበይ ተመልካች ሆኗል።ከእዚህ በኃላ በእዚህ አይነት ሁኔታ ወደፊት የመቀጠል አቅም ያለው የለም።የነፃነት ቀን ነገ አይደለም።ዛሬ! ነው።


በነፃነት ጥያቄ ሂደቱ ውስጥ ሁለት አበይት ነጥቦች አስፈላጊ ናቸው።ከላይ የተጠቀሱት በተለይ በኦሮምያ ክልል ውስጥ ከሚታየው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አንፃር መታየት የሚገባቸው ሁለት ነጥቦች ጥያቄዎችን ብሔራዊ አጀንዳ ማድረግ እና የፖለቲካ ምህዳሩን ክልላዊ ሳይሆን ብሔራዊ ወይንም ሀገር አቀፋዊ ማድረግ የሚሉት ናቸው። ከቅርብ አመታት ወዲህ ባለው ትግል ውስጥ ቀዳሚ አጀንዳዎችን ብሔራዊ ወይንም ሃገራዊ አድርጎ አለማቅረብ  አርዝሞታል።ለሀገራዊ አጀንዳዎች ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር የመነሳት አቅማቸው ቀላል አይደለም።ከላይ ከተጠቀሱት ለዘብተኛ አመለካከት ያላቸው ጥያቄዎችን ከኦሮምያ አንፃር ብቻ በመቃኘት እና በማጥበብ ሌላው ኢትዮጵያጵያዊ በርቀት እንዲመለከት እና ሌላ መስመር እንዲከተል ያደረጉበት ሂደት ያስከፈለው የሰው እና የጊዜ ሀብት ቀላል አይደለም። ከአሁን በኃላ ይህንን ስህተት ማረም ተገቢ ነው። በእርግጥ ሁለት እውነታዎችን መካድ አይቻልም።አንዱ በኦሮምያ በኩል በተለያየ አስተሳሰብ ውስጥም ቢሆኑ በተቀናጀ መልክ መዋቅር በመፍጠር እና ቄሮ በሚል ግንኙነት የተፈጠረው ሕዝባዊ እምቢተኝነት ለሰላማዊ ትግል አንዱ ምሳሌ ሆኗል።ይህ አንዱ የኢትዮጵያ አቅም ነው።

በሌላ በኩል በዐማራ ክልል ውስጥ ከፍተኛ የትጥቅ ትግል ለማካሄድ የሚችል የታጠቀ እና በበረሃ እና በከተማ አድፍጦ ያለ ኃይል አለ።ይህ ኃይል ከአቅም አንፃር እስካሁን በሰሜን ጎንደር እና በሱዳን ድንበር እንዲሁም በኤርትራ ሳይቀር ይገኛል።ይህ ኃይል ምንም ቢዘገይ በኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ የሚናቅ አይደለም።እንደ ኢትዮጵያ ላለ ስልጣን በጠብ መንጃ ብቻ ለሚፈራረቅባት ሀገር እና እንደ ህወሓት በኃይል ብቻ ለሚያምን ቡድን በዐማራ ክልል ያለው ሕዝብ ባብዛኛው ጦረኛ የሆነ ባህሉ በእራሱ በአግባቡ ከተያዘ በጎ ነገር ይዞ መምጣት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በበጎ ለማይመለከቱ ሁሉ አንዱ እና አይነተኛ ኃይል ነው። ለኢትዮጵያ ሰራዊትም ከደጀን እስከ ግንባር አጋዥ ነው።

ከህወሓት በኃላ ኢትዮጵያን የመቅረፅ አቅም ያላቸው ሶስቱ ኃይሎች እነማን ናቸው?


ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ኃይሎች ማለትም በኦሮምያ ያለው የቄሮ እንቅስቃሴ እና በዐማራ ያለው የፋኖ ታጣቂ ኃይሎች በአግባቡ በበሳል የፖለቲካ አመራር መመራር አለባቸው።ይህ ነው እንግዲህ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ ትውልድ በክብር የማስተላለፉ ፈታኝ ሥራ የሚሆነው።ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ብለን ብንጠይቅ ከኢትዮጵያ አንፃር የሶስት  ወሳኝ አካላት መናበብ እና ቆርጦ መነሳት ያስፈልጋል።እነርሱም በሳል የፖለቲካ፣ምጣኔ ሀብት እና ማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና በሳል የሚድያ ሰዎች ናቸው።

እነኝህ ሶስቱ የኢትዮጵያን ሕዝብ መጪ አቅጣጫ የመቅረፅ አቅም አላቸው። የፖለቲካ፣ምጣኔ ሀብት እና ማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች የፖለቲካ ድርጅቶችን ወደ ኅብረት የማምጣት እና የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት በጠበቀ መልኩ የፖለቲካ መስመሩን የመቅረፅ ሚና ይኖራቸዋል።የሃይማኖት መሪዎች በቅድምያ የጎደፈ መልካቸውን በመልካም መቀየር እና ከሕዝቡ ጋር መሆናቸውን ማሳየት በመቀጠልም የህዝቡን እርስ በርስ ትስስር ማጥበቅ ይጠበቅባቸዋል።የሚድያ ሰዎች ደግሞ ሁሉም አካላት ከህዝብ ያፈነገጠ እና ኢትዮጵያን የሚጎዳ ተግባራት ሲሰሩ በፍጥነት ለሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ መስጠት እና የሕዝብ አመለካከት ኢትዮጵያዊ በሆነ እና የእርስ በርስ ፍቅሩን በሚያጠነክር መስመር ላይ እንዲሄድ ፈር ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል።

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ያለበት ደረጃ ለነፃነት ፍሬ ሊያሳይ በሚችል መስመር ላይ ነው።ለነፃነት ቀጠሮ ከሰጠ ግን የተደገሰለትን የመከፋፈል መርዝ ለመጠጣት የመዘጋጀት ያህል አደገኛ ነው።ሕዝብ ከህወሓት አገዛዝ መውጣት አለበት።በመቀጠል እራሱን የቻለ ሌላ ምዕራፍ ይኖራል።ይህ ምዕራፍ ግን በህወሓት ውስጥ በመኖር ከሚደርስበት አደጋ ጋር የሚመጣጠን ፈፅሞ ሊሆን አይችልም።በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት የምሁራን፣የሃይማኖት መሪዎች እና የሚድያ ሰዎች ትጋት እጅግ  እጅግ አስፈላጊ ነው።

“ኧረ አምሳለ” ግጥም በገጣሚት ምልእቲ ኪሮስ (ቪድዮ)



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Wednesday, February 7, 2018

የዘመነ አክሱም ስልጣኔ ቅርሶች የማን ናቸው?


በቀሲስ መንግሥቱ ጐበዜ
ሉንድ ዩንቨርሲቲ ፣ ስዊድን
(ቀሲስ መንግስቱ ጎበዜ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ አርኪኦሎጂ እና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር እና በሉንድ ዩንቨርስቲ የዶክትሬት የመጨረሻ ዓመት ትምህርታቸውን በታሪክ ዘመን አርክዮሎጂ በማጥናት ላይ ይገኛሉ)
የአክሱም ሐውልት
አክሱም የጥንታዊ ኢትዮጵያ ስልጣኔ እምብርት፣ የጠንካራ መንግሥታዊ አስተዳደር ማዕከል እና የድንቅ ባህል መድረክ እንደነበረች ይታወቃል የታቦተ ጽዮን መገኛ የቅዱስ ያሬድ መፍለቂያ የመጀመሪያው ጳጳስ አባ ሰላማ (ፍሬምናጦስ) መንበር የዘጠኙ ቅዱሳን በዓት የነበረችው አክሱም በኢትዮጵያ የክርስትና ሐይማኖት ታሪክ ልዩ ክብርና ስፍራ አላት አክሱም የመጀመሪያዎቹ ሙሃመድ ተከታዮች ከሃገራቸው በተሰደዱ ጊዜ በእንግድነት ተቀብላ መጠጊያ ስለሆነች በሙስሊሙ ዓለምም ውለታዋ የሚዘነጋ አይደለም

የአክሱም መንግሥት በትንሹ ከመጀመርያው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ መኖሩ ሲታወቅጠንካራ መሪዎችና የራሱ የሆነ የመገባበያ ገንዘብ እንደነበረውም ይታወሳልበዚሁ በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ዞስካለስ በመባል የሚታወቀው ንጉሥ የግሪክኛ ቋንቋን በደንብ የሚያውቅና የአዶሊስ ወደብን በዋና የንግድ ማዕከልነት ይጠቀም እንደነበር ተመዝግቧል። የአክሱም መንግሥት ያልነት 2ኛው እስከ 3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በነበረው የአዶሊስ ሐውልት ጽሑፍ (Adulis Inscription) ላይ ተጠቅሷልበ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረ ማኒ የተባለ ፐርሺያዊ ጸሐፊ አክሱምን ከሮምከፐርሺያና ከቻይና ጋር በመደ በዘመኑ ከነበሩት የዓለም ሃያላን መንግሥታት ተርታ አስቀምጧታል4ኛው እስከ 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለነበረው ከፍተኛ የሆነ የአክሱም መንግሥት እድገትና ብልጽግና ከበቂ በላይ የታሪክ ምስክሮች ይገኛሉየ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ንጉ ኢዛና እና የ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመኑ ንጉ ካሌብ በቤተመንግሥትም ሆነ በቤተክህነቱ ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው ናቸው

የአክሱም ስልጣኔ አንድአንዶች እንደሚመስላቸው አንድን ህብረተሰብ ብቻ የሚወክል ሳይሆን የብዙ ኢትዮጵያውያን አሻራ ያረፈበት የድምር እንቅስቃሲያቸው ውጤት ነው። ለምሳሌ ያህል አክሱም የሚለውን መሰረተ ሥርወ ቃል (etymology) መመልከት ተገቢ ይሆናል አክሱም ለው ቃል አኽ ከሚለው የአገውኛ ቃል (ትርጉሙ ውሃ ማለት ነው) እና ስዩም ከሚለው የግዕዝ ቃል (የተሾመ ሹም እንደ ማለት ነው) የተገኘ ሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት አለ በአንድ ላይ ተጠቃሎ ሲነበብም የው ሹም የሚለውን ትርጉም ይሰጣል እስከ ዛሬ ድረስ በአክሱም ማይ ሹም (የውሃ ሹም) ተብሎ የሚታወቅ ቦታ መኖሩ የስያሜውን እውነትነት ያጠናክረዋል ለረጅም ዘመን የዋግ (ሰቆጣ) መሪ ዋግ ሹም በሚል ማዕረግ ስም ይጠሩ እንደነበርም ይታወቃል ከላስታ ነገሥታት መካከልም ሁለቱ ግርማ ስዩም (የንጉሥ ይምርሃነ ክርስቶስ አባት) እና ዛን ስዩም (የንጉስ ላሊበላ አባት) ተብለው ይጠሩ እንደነበር ልብ ይሏል አክሱም የሚለው ቃል ስያሜ መሰረቱ የኩሽ (አገውኛ) እና የሴም (ግዕዝ) ቋንቋዎች ጥምረት ከሆነ የአክሱም መንግሥት ሥልጣኔ እና ቅርሶቹ የኩሽና የሴም ሕዝቦች መስተጋብር ውጤት መሆናቸውን ከዚህ በላይ ማሳያ የለም

ሆኖም ግን የታሪክና የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች እንደሚመሰክሩት የአገው ሕዝቦች በአክሱም ዘመነ መንግሥት አስተዳደርና እና የስልጣኔ ፈርጦቹ የነበራቸውን ከሁሉም የላቀ አስተዋጽኦ መካድ አይቻልምከጅምሩ አገዎች በቁጥር ብዙና መልካዓ ምድራዊ አሰፋፈራቸውም ቀላል የማይባለውን የአክሱም መንግሥት ወሰነ ግዛት ያካተተ ነበርአገዎች የመካከለኛውና የሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ቀደምት ነዋሪዎችና አገር አቅኝዎች መሆናቸው ይታወቃል እነዚህ ሕዝቦች የአባይ ወንዝ መነሻ ከሆነው ከጣና ጀምሮ የጎጃም፣የጎንደር፣ የላስታ፣የዋግ (ሰአቆጣ) እና የትግራይ በርካታ አካባቢዎችን በማካተት የመረብን ወንዝ ተሻግረው እስከ ኤርትራ ግዛት ከረን ድረስ ሰፍረው ይኖሩ ነበር ይህ ትልቅ የሕዝብ ቁጥርና ሰፊ የቦታ ይዞታ በራሱ አገዎች በዘመነ አክሱም ተጽእኖ የመፍጠር አቅም እንደነበራቸው አመላካች ነው።

አገዎች ዓይነተኛ በሆኑ ጥንታዊ የታሪክ መዛግብት (primary sources) ከተጠቀሱት ጥቂት ሕዝቦች መካከል አንዱ ናቸውከላይ በተጠቀሰው የአዶሊስ የሃውልት ላይ ጽሑፍ (Adulis Inscription)የ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የንጉሥ ኢዛና የድንጋይ ላይ ጽሑፍ (Ezana Inscription)እንዲሁም በ6ኛውመቶ ክፍለ ዘመን የኮስሞስ ጽሑፍ (Christian Topography of Cosmas Indicopleustes) የአገዎችን እንጅ በዘመናችን የሚታወቁ የሌሎች ሕዝቦችን ስም አናገኝምከአገው ሌላ አጋዚ የሚለው ስም በጥንቱ መዛግብት የተገለጸ ሲሆን ይኸውም የግዕዝ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን (አጋዝያን) የሚመለከት እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታልበአዶሊስ ሐውልት ጽሑፍ (Adulis Inscription) ላይ የአክሱም ንጉስ ከአጋዚ ነገ ጋር እንደተዋጋ ተጥቅሷልበሌላ በኩል ከአክሱም መንግሥት ሥልጣኔ ጋር የቅርብ ዝምድና ሊኖራቸው ይችላል ተብለው የሚታሰቡት ሕዝቦች ስማቸው በጥንቱ የአክሱም ዘመን የታሪክ ሰነዶች አልተካተተምለምሳሌ የትግራይ ሕዝብ ለመጀመሪያ ጊዜ በጽሑፍ ተጠቅሶ የሚገኘው በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከአክሱም መንግሥት ማክተም በኋላ ነው።

አገዎች በአክሱም መንግሥት የባህልየምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው የሚጠቁሙ አያሌ ማሳያዎች አሉ ከነዚህም አንዱ አገዎች በአክሱም መንግሥት በከፍተኛ የአስዳደር ኃላፊነት ያገለግሉ እንደነበር የሚያስረዳው የኮስሞስ ጽሑፍ ነው በዚህ የታሪክ ሰነድ ላይ እንደተገለጸው በንጉሥ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነትና እምነት የሚጠይቀውን ረጅም የወርቅ ንግድ መተላለፊያ መስመር የሚቆጣጠረው የአገው ሰው ነበር በተለይ ደግሞ ለአክሱም ስልጣኔ መዳበር አገዎች የነበራቸውን ጉልህ ሚና የምንረዳው የራሳቸውን መንግሥት ላስታ ላይ ከመሰረቱ በኋላ የአክሱምን ሥልጣኔ አሻሽለው መድገማቸው ነው። የመንግሥት ማዕከሉ ከአክሱም ወደ ላስታ ከመሸጋገሩ ውጭ በሁለቱ ዘመናት የነበረው የአስተዳደር ዘይቤየባህልየቋንቋየውጭ ግንኙነት ወዘተ የጎላ ልዩነት ነበረው ብሎ ለመናገር አያስደፍርምበአክሱምም በዛጉዬም ዘመናት ግዕዝን በዋና ቋንቋነት ይጠቀሙ ነበርበአክሱምም በዛጉዬም ዘመናት ቤተ መንግሥትና ቤተክህነት እጅግ ጠበቀ ግንኙነት ነበራቸውበርግጥ በዛግዬ ዘመን ነገሥታት ካህናትም ተፈጥረዋል። የአክሱም ነገሥታት በተለይ ከግብፅና ከኢየሩሳሌም ጋር የነበራቸው ግንኙነት በዛጉዬ ዘመንም ተጠናክሮ ቀጥሏል። የአክሱም ዘመን የህንፃ አሰራር ጥበብ በዳበረ መልኩ በዛጉዬ ዘመን ተንፀርቋል

አገዎች የአክሱም መንግሥት አካል ስለነበሩ ድሮም የሚያውቁትን የኪነ ህንፃን ሥራ በረቀቀ መንገድ በላስታ ላይ አሳይተዋል በተለይ ደግሞ የቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ እና የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ስንመለከት ከአክሱም ዘምን የህንፃ ጥበብ ጋር ያላቸው የቅርብ ዝምድና ሁለቱም ከአንድ ምንጭ የተቀዱ መሆናቸውን መረዳት አያዳግትም ወጥ ለትን በመፈልፈል ለሚፈልጉት ላማ ማዋልን መሰረት ያደረገው ኢትዮጵያዊ ሥልጣኔ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከአገው ሕዝቦች ጋር የተዛመደ ስለመሆኑ ዋነኛ አመላካች ነው መርዶክ የተባለው ጸሐፊ ሁሉም ማስረጃዎች የሚጠቁሙት የአገው ሕዝብ በአፍሪካ በባህላዊ የፈጠራ ክህሎቶች የተካ መሆኑን ነው በማለት የገለጸው ከዚህ ተነስቶ ሳይሆን አይቀርም

ሲጠቃለል የአክሱም ዘመን ስልጣኔ ውጤት የሆኑ መንፈሳዊና ባህላዊ ቅርሶችን የራሱ ብቻ እንደሆኑ አድርጎ የሚያስብ የህብረተሰብ ክፍል ቢኖር ታሪካዊ እውነታው አይፈቅድለትም ያም ከሆነ ከአገው ሕዝብ በላይ የቀረበ ማንም እንደሌለ የሚመሰክሩ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች አሉ። አገዎችም ቢሆኑ በጊዜ ብዛት በተለይ በአማርኛበትግርኛ እና በኋላም ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተዋ (assimilated) ወይም ከነዚህ ሕዝቦች ጋር የተቀየጡ (mixed) በመሆናቸው ብዙውን የጥንቱን የአገው ማኅበረሰብ የምናገኘው በነዚህ ሕዝቦች ውስጥ ጭምር መሆኑ መዘንጋት የለበትም ደግሞስ አክሱም የሚለው ስያሜ ራሱ ከላይ እንደተመለከትነው በኩሽና በሴም ቋንቋዎች ጥምረት የተፈጠረ ቃል አይደል! ስለሆነም የጥንቱ የአክሱም ዘመን ስልጣኔ ቅርሶች የሁላችንም ቅድመ አያቶች ድንቅ የእምነት የስራና የፈጠራ ቶች መሆናቸው ማስተባበል አይቻልም አክሱማዊ ቅርሶቻችን ሁሉም ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሰርተውና ጠብቀው ያቆዩልን የጋራ ሀብቶቻችን ናቸው ከዚህም በላይ የአክሱም መካነ ቅርስ በአሁኑ ጊዜ ለም ቅርስነት ተመዝግቦ የሚገኝ የዓለም ሕዝብ ሁሉ ሀብት መሆኑ ማወቁ ተገቢ ነው

ማጣቀሻዎች
McCrindle, John Watson (ed.,tr), 1897. The Christian Topography of Cosmas, an Egyptian monk, London.

Merid Wolde Aregay, 1971. ‘Southern Ethiopia and the Christian Kingdom 1508-1708’. Unpublished PhD thesis, School of Oriental and African Studies, University of London.

Munro-Hay, S. 1991. Aksum. An African Civilisation of Late Antiquity. Edinburgh University Press, Edinburgh.

Munro-Hay, Stuart. 2003. Aksum, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden

Murdock, George P., 1959. Africa: Its people and their culture history, New York

Phillipson, D.W. 2009. Ancient Churches of Ethiopia, Fourth–Fourteenth Centuries. Yale University Press: New Haven/London.

Phillipson, D.W. 2004. The Aksumite roots of medieval Ethiopia. Azania 29: 77-89.

Quirin, James. 2003. Agäw, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden

Sergew Hable Selassie. 1972. Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270. United Printers: Addis Ababa.

Sima, Alexander. 2003. Agazi, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden

Smidt, Wolbert. 2010. Tigray, Encyclopaedia Aethiopica, I, Siegbert Uhlig, ed., Wiesbaden

Taddesse Tamrat, 1972, Church and state in Ethiopia, 1270-1527, Oxford.

Taddesse Tamrat, 1988. Process of Ethnic Interaction and Integration in Ethiopian History: the Case of the Agaw (Special Issue in Honour of Roland Oliver), the Journal of African History, 29, 1, 5-18.

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...