Tuesday, July 10, 2018

አንዳንድ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን ዲያስፖራዎች የአቶ ኢሳያስ ጋሬጣ ወይንስ አጋዥ? ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደፊት ሊያተኩሩበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ የቱ ነው?

ጉዳያችን/Gudayachn
ሐምሌ 3/2010 ዓም (ጁላይ 10/2018 ዓም)


አንዳንድ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን ዲያስፖራዎች የአቶ ኢሳያስ ጋሬጣ ወይንስ አጋዥ?


የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የ1990 ዓም ግጭት መልሶ ለመፈጠሩ ምክንያቶች ላይ በጉዳዩ ዙርያ  የጠለቀ መረጃ  በነበራቸው ሰዎች  ብዙ ተብሏል።በጠራ መልኩ ደግሞ የታሪክ ፀሐፊዎች ወደፊት ያስነብቡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በእዚህ ፅሁፍ ላይ ግን የማነሳው አንዱ ጉዳይ በውጭ የሚኖሩ በእድሜ የገፉ አንዳንድ የኤርትራ ተወላጆች ከአቶ ኢሳያስ ብሰው እና ለእራሳቸው ለአቶ ኢሳያስም መገራት ያስቸገሩበት ሁኔታ እንደነበር ዛሬ ላይ ማንሳቱ ለወደፊቱም ጠቀሜታ ያለው ይመስለኛል።ዛሬ ላይ በእድሜ የገፉ የምንላቸው የዲያስፖራ ኤርትራ ተወላጆች በመጀመርያ ለጀብሃ ቀጥለው ለሻብያ ገንዘብ በማዋጣት እና በውጭ ሀገር በሚደረጉ የገቢ ማሰባሰብያ ዝግጅቶች ላይ የመሳተፍ ሚና ብቻ ያላቸው ነበሩ።ሆኖም ግን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ትልቅ፣የታሪክ፣የትውልድ፣የሃይማኖት እና የቤተሰባዊ ግንኙነት ወደጎን አድርገው ግንኙነቱ  እንዳይጠናከር አንዳንዶች ለማጠናከር ሲሞክሩም የኤርትራን ሃገራዊነት የሚያጠፋ አደጋ አድርገው ይቆጥሩ ነበር።በእዚህም ሳብያ በእምነት ድርጅቶች ውስጥ አመራርነት እየያዙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ወጣቶችን አብረው የእምነት ቦታዎቻቸው ላይ መታደማቸውን በእራሱ ሲበጠብጡት ኖረዋል።ይህ በተለይ ከኢትዮጵያ የዛሬ ሃያ ዓመት  ''ትውልደ ኤርትራውያን'' እየተባሉ በህወሓት ተባረው የወጡትን የአዲሱ ትውልድ አካላት  ቀደም ብለው በውጭ ሃገራት  በያዙት ማኅበራዊ መሠረትነት ሳብያ እነኝሁ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን አዲሶቹን ስደተኞች ከኢትዮጵያውያን ለመለየት ብዙ መጣራቸው ይታወሳል።ሆኖም ግን የማኅበራዊ  እና የሃይማኖት መሰረቶች ቀላል ስላልሆኑ ወጣቶቹ ፈፅመው አልተቀበሏቸው።

እነኚሁ በውጭ የሚኖሩ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን ትውልድ ከትውልድ ማስታረቅ ሲገባቸው ምን ያህል በሚያባብሱ ስራዎች ላይ የተጠመዱ እንደነበር በቀላሉ ለማሳየት  የአቶ ኢሳይሳን አስተዳደርም የተፈታተኑበትን አንድ ስብሰባ በማሳየት ለአብነት ላንሳ።አቶ ኢሣያስ በ1980ዎቹ መጨረሻ ገደማ በናይሮቢ ባደረጉት ጉብኝት ላይ ከላይ የተጠቀሱት አይነት ግለሰቦች በተገኙበት ስብሰባ ላይ አቶ ኢሳያስ ከኢትዮጵያውያን ጋር ግጭት የሚፈጥሩ እንዲታረሙ የሚል ሃሳብ ሲሰጡ ለብዙ ዓመት ውጭ የኖሩ ''ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ'' አይነቶቹ ግለሰቦች መልሰው አቶ ኢሳያስን እኛ ለስንት ዓመት ስናዋጣ የኖርን መሆናችንን ይወቁልን አይነት አስተያየት ይሰጣሉ። በእዚህ ጊዜ አቶ ኢሳያስ የመለሱላቸው መልስ ''እናንተ ገንዘብ ሰጠን ትላላችሁ ህይወቱን ለእኛ የሰጠ ኢትዮጵያዊም አለ'' በሕዝብ መሃል ግጭት መፍጠር አይገባም አይነት ቁጣ የተቀላቀለበት ንግግር ማድረጋቸውን ከአስር ዓመት በፊት ዑጋንዳ እያለሁ ስብሰባውን የታደመ ሰው የነገረኝን አስታውሳለሁ። 

እነኝሁ ወገኖች የፈጠሩት ችግር በውጭ ሀገር ብቻ ሳይሆን ሀገር ቤት ሲሄዱም ከሰባ ዓመታት በላይ አብረው የኖሩ፣አንድም ቀን ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሌላ ሀገር ብለው አስበው የማያውቁትን ሁሉ ሪፍረንደም ላይ ካልተሳተፉ እንደሚገለሉ በመስበክ የፈጠሩት ውዥንብር አብሮ የነበረውን መልካም ሕዝብ ሰላሙን ያናጋ ነበር።ይህ ማለት በውጭ የኖሩት በእድሜ የገፉት የኤርትራ ተወላጆች ብቸኛ ተወቃሽ ናቸው ለማለት ሳይሆን፣ አንዳንዶች ያደረጉት አሉታዊ አስተዋፅኦ ለሌላው ዲያስፖራ ትምህርት ስለሆነም ነው።በነገራችን ላይ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የኤርትራ ተወላጆች እንደ ዲያስፖራው በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን የሚያስቡ አይደሉም።ይህንን መልካም አካባቢያዊ ሁኔታ የበከለው በውጭ በሴራ ፖለቲካ እና በጥላቻ የተካነው በእድሜ የገፋው የኤርትራ ተወላጅም ጭምር እንደነበር ለማስታወስ ነው።ይህ ጉዳይ ዛሬ ላይ ጥቅም የለውም ብሎ የሚያስብ ሊኖር ይችላል።አዎ! አሁን ያለፈውን ጉዳይ የምናወራበት አይደለም።ሆኖም ግን ለወደፊቱም ወጣቱ ትውልድ መጠንቀቅ ያለበት የእዚህ አይነት የተሳሳተ እሳቤ ካላቸውም ጭምር  መሆኑን ማሳሰቡ ጠቃሚ ነው።በሌላ በኩል ለወደፊት በጉዳዩ ዙርያ የሚያጠኑ በውጭ የሚኖሩ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን ነገሮችን ከማብረድ ይልቅ የማካረር ሚና በእራሱ አንዱ ሊጠና የሚገባ መሆኑንም ለመጠቆም ነው።


ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደፊት ሊያተኩሩበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ የቱ ነው?


የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መለያየት ፈፅሞ እንደማይሆን በተምኔታዊ ግምት ብቻ ሳይሆን ለ27 ዓመታት በተደረገ ሙከራ ተረጋግጧል።በማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ መካከል ያለው ልዩነት ፣ የተፈጥሮ ሳይንስን በላብራቶሪ ውስጥ አስገብቶ እና ሞክሮ ውጤቱን ማወቅ ሲቻል የማኅበራዊ ሳይንስ ግን ያለፈውን ተሞክሮ በማየት እና አሁን እየሆነ ያለውን መረጃ በመሰብሰብ የሚደረስበት ድምዳሜ ነው።የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጉዳይም የማኅበራዊ ሳይንስ ጉዳይ እንደመሆኑ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ተለያይተው  መኖር እንደማይችሉ በሙከራም ጭምር አረጋግጠዋል። 

አሁን የተጀመረው መልካም ጅምር በሚገባ ለማስኬድ ከዝርዝር ግንኙነቶቹ በተጨማሪ የዜግነት ጉዳይ አንዱ መስተካከል ያለበት ነው።በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ያሉ ካለ አንዳች ገደብ የመስራት እና የመኖር ፍላጎት አላቸው።ይህንን ጉዳይ ግን ምንም አይነት ነፃ ቪዛ ቢደረግ እና ካለ ፓስፖርት መሄድ ይቻላል ቢባል መልሶ የሚይዝ ጉዳይ ለሁለቱም ሃገር ፖለቲከኞች እንደ ''ሽንፍላ'' የማይጠራው ጉዳይ የዜግነት ጉዳይ ነው።አቶ አሳያስም ሆኑ ዶ/ር አብይ ይህንን ጉዳይ አንድ አይነት ማሰርያ ማበጀት መቻል አለባቸው። አንድ ኤርትራዊ ለኢትዮጵያ የፀጥታ ስጋት እንደማይሆን፣አንድ ኢትዮጵያዊም ለኤርትራ የፀጥታ ስጋት እንደማይሆን ያለፈው ስምምነት አመላካች ነው።ከእራሱ ዜጋ ስጋት ያለበት ሀገር የለም።ምን ለማለት ነው? በምንም አይነት ሁለቱም ሀገሮች በአንድ አይነት መልክ ወደ ኮንፈድሬሽን የሚመጡበት እና ኢኮኖሚያዊ ውህደቱን በፖለቲካዊ ውህደት፣ወይንም ተወራራሽ ቅርፅ ካልሰጡት በተገደበ መልክ የሚኖር ግንኙነት ሁል ጊዜ የሁለቱንም ሀገር ዜጎች እንዳሳቀቀ የሚኖር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኞቻቸው የመከራከርያ አጀንዳ አድርገው ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ የሚያደርግ '' ጉንጭ አልፋ'' ትንተና ውስጥ እንዲገቡ አያስፈልግም።

ባጠቃላይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሐከል የተቀደደው የመለያየት መጋረጃ ታሪካዊ ነው።የህዝቡንም የፍቅር ጥማት በሁለቱም መካከል የታየ ብዙዎችን ያስለቀሰ ክስተት ነው።አቶ ኢሳያስም ዘግይተውም ቢሆን ምንም አይነት ልዩነት ለማውጣት የሚቸግር መሆኑን ቆይተውም ቢሆን የተረዱት ይመስላል።አሁን ካለፈው የመማርያ እና የወደፊቱን በጥልቅ መሰረት ላይ ለመጣል እንዲሁም ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ ለመስራት ዕድል ያላቸው መሪዎች በጥልቅ ሊመለከቱት ይገባል። ሁለቱም ሀገሮች ወደ ፖለቲካዊ ሕብረት በመምጣት የዜግነት ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያዊ ቅኝት አንድ አይነት መልክ ማስያዝ አለባቸው።እንዴት? ለሚለው ጥያቄ አሁን ዝርዝር መልስ ለማስቀመጥ ጊዜ ይፈልጋል። ፖለቲካዊ ህብረት ማለት ግን በዋናነት የዜግነት ልዩነትን ማጥፋት እና ወደ ኢትዮጵያዊ ጎራ ገብቶ ባለቤት የመሆን ጉዳይንም ይጨምራል። አንዳንዶች ምጣኔ ሀብታዊው ግንኙነት እና ሕብረት በራሱ ወደ ፖለቲካዊው ያመራል ይላሉ።ይህ ግን በዘገምተኛ መልክ የሚሄደው የተለያየ ባህል ላላቸው ህዝቦች ነው እንጂ እንደ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያለ ጥልቅ የባህል መመሳሰል ብቻ ሳይሆን ፍፁም አንድነት ላላው ሕዝብ አይደለም።በሁለቱ መካከል ያለው የምጣኔ ሀብት ግንኙነት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደነበረበት ይሄዳል።በመቀጠል የፖለቲካ እና ዜግነት ጉዳይ ወድያው አፍጥጦ ይመጣል።ያን ጊዜ ይህንን በጎ ተግባር ያንገጫግጨዋል።ስለሆነም በተለይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ  በእዚህ በኩል ያለውን እውነታ ወደ ጎን ሊሉት አይችሉም።ይህ ማለት ኤርትራን ከሚነጥል የፖለቲካ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ወደ የሚደምር የፖለቲካ ግንኙነት መምጣት ወሳኝ ነው።ይህ ማለት በዲሞክራሲያዊ ሂደት ኢትዮጵያውያን ስለ ኤርትራው ፖለቲካ እኩል በጋር መልክ እንዲሳተፉ፣ኤርትራውያንም እንዲሁ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የዲሞክራሲያዊ ሂደት እንዲሳተፉ ማድረግ እና ድህነታችንም ሆነ ሀብታምነታችን ተወራራሽ አብሮ የሚወድቅ እና የሚነሳ በእኩል ዜግነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው። እዚህ ላይ የአሰብ ወደብ እና ሌሎች ጉዳዮች በጣም ጥቃቅን ጉዳዮች አድርጌ ነው የማያቸው።ጥቃቅን የምለው ከጉዳዩ አስፈላጊነት አንፃር ሳይሆን እነኝህ ጉዳዮች ላለፉት 27 ዓመታት ተሞክሮም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ  ካልሰሩበት ወደቡ በራሱ  የበለጠ አደጋ ይዞ እንደሚመጣ አደጋው ደግሞ ለሁሉም የሚተርፍ መሆኑ ተመስክሯል። ስለሆነም ከምጣኔ ሃብቱ ጉዳይ ጋር እኩል የዜግነት ጉዳይ እንዴት አንዱ ከሌላው የተለየ እንዳልሆነ ሆኖ በሚያሳይ እና ትውልድ አሻጋሪ በሆነ መልክ በሕግ መቀመጥ ይችላል? የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው።ይህ ጉዳይ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች በቶሎ ካልፈቱት ሕዝብ በጉልበቱ ወደ እዚሁ መንገድ እንደሚያመጣው ማመን ይገባል። ጥያቄው የታሪኩ አካል የመሆን እና ያለመሆን ዕድል እና ክፉ ዕጣ ነው። 


አስመራ ላይ ለዘንድሮ አዲስ ዓመት በድምቀት የሚሰማው ሙዚቃ 
ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Saturday, July 7, 2018

በክቡር ጠ/ሚንስትር ዶ/ር ዓብይ እና ኢትዮጵያዊነት አንፃር የቆመው እሳቤ።

ጉዳያችን/Gudayachn
ሐምሌ 1/2010 ዓም (ጁላይ 8/2018 ዓም)

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ 
- በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ያሉት ሁለቱ ሃሳቦች እና ኃይሎች፣
የኢትዮያ መጪ የፖለቲካ መንገድ ዋስትናው እና መፍትሄው በሚል ርዕስ ፅሁፎች እና 
የአዲስ ሙላት አዲስ ነጠላ ዜማ(ቪድዮ) ያገኛሉ።

ኢትዮጵያ የክፍለ ዘመኑ አንዱ እና አይነተኛ የለውጥ ሂደት ላይ ነች።ለውጡ አንድ እየሞተ ያለ ሐሳብ እየሸኘ አዲስ ሀሳብ እያስተዋወቀ የሚሄድ የለውጥ ሂደት ነው።እየሞተ ያለው ሐሳብ ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመን  ኢትዮጵያን ሲያምስ የኖረው '' ከእኔ ሃሳብ ጋር የማይስማማ ሁሉ ጠላቴ ነው እና ደምስሰው'' የሚለውን ሃሳብ ሲሆን እያስተዋወቀ ያለው ሃሳብ ደግሞ ''የእኔን ሃሳብ የማይቀበል ሁሉ ጠላት አይደለም።ችግሩን በውይይት መፍታት ይቻላል'' የሚለው ሃሳብ ነው። አዲሱ ሃሳብ በእራሱ በቂ ቦታ ለማግኘት በቀደመው ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ፅንሰ ሃሳቦች አራማጆች አሁንም መኖራቸው እና ወራሾችም ከአዲሱ ትውልድ ውስጥ መኖራቸው የለውጥ ሂደቱ በጥንቃቄ እንዲራመድ እና ጥንቁቅ አራማጅም የሚፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ነው። አንዲት ሀገር በእዚህ አይነት የለውጥ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ስትሆን የተለያዩ ሃሳቦች ሰፊውን ምህዳር ለመያዝ የተለያዩ ስልቶች ከመቀየስ እስከ አላስፈላጊ መንገድ ውስጥ የመግባት አደጋዎች እንዳይኖሩ የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ኃላፊነቱን የመወጣቱ ፋይዳ እጅግ ወሳኝ ነው።

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ያሉት ሁለቱ ሃሳቦች እና ኃይሎች

በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ያሉት ሃሳቦችን በሁለት ኃይሎች ከፍሎ በማየት መጠቅለል ይቻላል። የመጀመርያው ሕብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያን የሚያቀነቅነው እና በኢትዮጵያዊነት የወል ስም ሃሳብ ስር ያለው እና  ብሔርተኝነትን ዋስትናዬ የሚለው ሃሳብ እና ኃይል ነው። 

ሕብረ ብሔራዊነት እና ኢትዮጵያዊነት

የመጀመርያው ሕብረ ብሔራዊነት እና ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅነው ኃይል ካለምንም ማጋነን በስፋቱ፣በርካታውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከማቀፉ እና እሳቤው በራሱ ያለው የኃላ እና የወደፊት መሰረት ጥልቀት አለው። ይህ ማለት ወደ ኃላ ስንመለከት ኢትዮጵያ በኖረችበት የመንግስትነት ስሪት ታሪክ ውስጥ የፖለቲካው መሪ ተዋናይ እሳቤ ኢትዮጵያዊ እሳቤ መሆኑ ነው።የወደፊቱንም ስንመለከት እንደሀገር በጋራ ለመኖር ሌላ አማራጭ እሳቤ ለጊዜው ከኢትዮጵያዊ እሳቤ የተሻለ እንዳልተሰማ ብዙ ማስረጃ ማምጣት አይሻም።የህብረ ብሔራዊ እና ኢትዮጵያዊ እሳቤ ያለፈ እና የመጪው እሳቤ አካል ብቻ አይደለም የዘመናዊነት እሳቤ አካልም ነው።በዘመናዊው ዓለም በፈጣን ቴክኖሎጂ ምርት አሳድጎ ሰፊ ገበያ የመፍጠር እሳቤ የሚጋራው አሁንም ሰፊ የሕዝብ አንድነት እና ስምምነት ፈጥሮ የገበያ አድማስን ማስፋት ከሚለው ዘመናዊ አስተሳሰብ ጋር የሚጣጣም ነው።

ይህ የህብረ ብሔራዊነት እና ኢትዮጵያዊነት እሳቤ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ያህል እንዲጎሳቆል ያልተደረገበት ሙከራ አልነበረም።

እሳቤውን በራሱ ያለፈ እና ያረጀ ስርዓት እሳቤ ነው ብሎ ከማጥላላት እስከ የሃሳቡ ተጋሪዎችን ማሰር እና መግደል ድረስ ያልተፈፀመ የግፍ አይነት በህወሓት/ኢህአዴግ ስርዓት  አቀንቃኞች ሁሉ ሲፈፀምበት ኖሯል።ይህም ሆኖ ግን ሃሳቡ ገዢ ሃሳብ ሆኖ መኖሩን የሚገታው ኃይል አልተገኘም።ለእዚህ ምክንያቱ ደግሞ መሬት ላይ ያለው ዕውነታ ነው። ምክንያቱም በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሃብቱ መስክ ሁሉ ለሚገጥሙ ችግሮች መፍትሄው ምንድነው? ለሚለው ፈታኝ ጥያቄ መልሱ ሁሉ የሚያመራው ወደ አንድ ነጥብ ብቻ መሆኑ ነው። ይሄውም ሕብረ ብሄራዊት ኢትዮጵያ የሚለው መልስ ነው። ይህ በእንዲህ እያለ ነው እንግዲህ በኢህአዴግ የውስጥ ቅራኔ አይሎ የዶ/ር አብይ ቡድን ነጥሮ እንዲወጣ ዕድል የሰጠው።ይህ ቡድን ደግሞ በኢህአዴግ ውስጥ ሆኖ የኢትዮጵያን ችግር በሚገባ ለማየት የቻለ አካል ነበር እና የሕብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት እሳቤን በአማራጭ የፖለቲካ መሪ ሃሳብ ይዞ መውጣቱ ሳይንሳዊ እና ተሞክራዊ እንጂ ድንገት ደራሽ ሃሳብ አይደለም። ዶ/ር አብይ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር በተረከቡበት ቀን መጋቢት 24/2010 ዓም ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር በሕዝብ ውስጥ የነበረውን የህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት እሳቤ መግነጢሳዊ በሆነ መልክ በሕዝብ ውስጥ የነበረውን ስሜት አንፀባረቁት።በደቂቃዎች ውስጥም ሚልዮኖች ከጎናቸው አሰለፉ።ይህ ማለት ለሕዝብ የነገሩት አዲስ እሳቤ ስለሆነ አይደለም።ይህ ቢሆን ኖሮ ሀሳባቸው ሕዝብ ዘንድ ደርሶ ድጋፍ ለማግኘት አመታትን በጠበቀ ነበር።ሆኖም ግን ሕዝብ ውስጥ ሲንተከተክ የነበረው የህብረብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት ስሜት የመተንፈሻ ቀዳዳ ሲያገኝ ፈንቅሎ ወጣ እንጂ ስሜቱ ቢቆይ ኖሮ በአብዮት ወይንም በሌላ መልኩ ገንፍሎ መውጣቱ የማይቀር እንደነበር መረዳት ይገባል።

 ብሔርተኝነትን ዋስትናዬ የሚለው ሃሳብ እና ኃይል 
ሁለተኛው እሳቤ እና ኃይል ብሔርተኝነት ዋስትናዬ የሚለው እሳቤ ነው።የእዚህ እሳቤ ዋነኛ መነሻ እና ምክንያት ስጋት እና ስጋት ነው።ስጋቱ የሚነሳው ላለፈው ሩብ ክፍለ ዘመን በህወሓት እና አጋሩ ኢህአዴግ እንዲሁም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ተቃዋሚ ግን ብሄርተኝነትን የሙጭኝ ያሉ ኃይሎች ተከታታይ የፕሮፓጋንዳ ሥራ በአንድ ትውልድ ላይ የፈጠረው ያለመተማመን እና  የስጋት ውጤት ነው። የእዚህ እሳቤ አቀንቃኞች ሁል ጊዜ የሚሰጉት ኢትዮጵያዊነት እና ሕብረ ብሔራዊነት የእነሱን የብሔር እይታ የሚጋርድ ብቻ ሳይሆን ሊያጠፋን ይችላል በሚል ስጋት የተሞላ ነው።ይህንን ስጋት ደግሞ ከሃምሳ እና መቶ ዓመታት በፊት የነበሩ የታሪክ ትርክቶችን የተለያየ ቀለም በመቀባት በአይነት በአይነት እየመተረ የልዩነቱን ጎራ ብቻ እያጎላ ስለኖረ ከስጋት ሊወጣ ፈፅሞ አልቻለም። ሆኖም ግን አስከፊው ጉዳይ ከስጋት ለመውጣት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ወደፊትም ስጋቱ የሚርቀው የራሱ የብሔር ኃይል የስልጣን እርከኑን ሲቆጣጠር ብቻ መሆኑን ያስባል።እዚህ ላይ ግን የስልጣን እርከን ተቆጣጠረ የሚባለው የቱን የፖለቲካ ኃይል ሲይዝ መሆኑን እራሱም ጥርት አድርጎ ማስቀመጥ አይችልም።ምክንያቱም የእዚህ አይነቱ የስልጣን አላማ እሳቤ በራሱ መለክያ የለውም።ሁሉንም የስልጣን እርከን ቢቆጣጠርም ተቆጣጠርኩ ብሎ እንደማይረካ ግልጥ ነው።ይህ የስጋት ፖለቲካ ዋና ጠባይ ይህ ነው።ስልጣን ላይ ሆኖም እንዳልሆነ ቆጥሮ ሌላ ግንባር ይከፍታል።በብሄርተኝነት እሳቤ ውስጥ ያሉት የህወሓት፣የኦሮሞ እና የአማራ ብሔርተኝነቶች ተጠቃሽ ናቸው።እዚህ ላይ ግን የህወሓት የብሄርተኝነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የገንዘብ እና የስልጣን ጥማት ያላቸው እና በልዩ ልዩ ወንጀል ውስጥ የገቡ ብሔርተኝነትን እና የትግራይን ሕዝብ እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ለመጠቀም የሚያስበው አካል ፍፁም ብሔርተኘነት ስሜት ያለው ነው ለማለት የሚያስቸግርበት ደረጃ ደርሷል።ይህ ደግሞ ከብሄርተኝነት አልፎ ወደለየለት የፋሽሽት ኃይል ለመቀየር በማኮብኮብ ላይ ያለ ምናልባትም የተቀየረበት ደረጃ እንደሆነ በጥልቀት አጥንቶ በማስረጃ ማቅረብ ይቻላል።ከእዚህ በተለየ ግን የኦሮሞ፣አማራ እና ትግራይ ብሄርተኛ እሳቤዎች ብቸኛ ችግር መጪውን ዋስትና የማግኘት ጥማት ነው።በእዚህ ውስጥ ግን ሁሉም ውስጥ የስልጣን እና የግል ''ኤጎ'' ስሜቶች የሉም ማለት አይቻልም።ይህንን በሚገባ ለመመርመር ግን  እንደ እየቡድኖቹ አመራሮች ጠባይ በዝርዝር መመልከትን ይፈልጋል።

የኢትዮያ መጪ የፖለቲካ መንገድ ዋስትናው እና መፍትሄው

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው በአሁኗ ኢትዮጵያ ያሉት የፖለቲካ እሳቤዎች በሁለቱ ማለትም በሕብረ ብሔራዊ እና የብሔርተኝነት እሳቤዎች ስር መሆኑን መረዳት ይቻላል።አሁን ጥያቄው የኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ መንገድ ዋስትናው እና መፍትሄው ምንድነው? የሚል ነው።

ከመጋቢት 24/2010 ዓም ዶ/ር ዓብይ ወደ ስልጣን የመጡበት መንገድ እና ከሁሉም በላይ ያነሱት የህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነት እሳቤ የኢትዮጵያ እጅግ ውድ የሆነ መልካም ዕድል ነው።ይህ ማለት መጪው የለውጥ ሂደት ሕዝብ ከህዝብ ሳይጣላ፣ኢትዮጵያ የጀመረችው የልማት ሂደት ሳይቆም እና የመንግስት ስሪቷ ሳይበጠስ ስለለውጥ እና አዲስ የፖለቲካ ሂደት ለመወያየት እና ወደ ውጤት ለመድረስ ፋታ አገኘን ማለት ነው።ይህንን ዕድል የህብረ ብሔራዊውም ሆነ የብሄርተኛ አቀንቃኙ በሚገባ ሊጠቀሙበት ይገባል።ስለሆነም ለመጪው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ዋስትናው እና መፍትሄዎቹ የሚከተሉት ናቸው። እነርሱም

  • የህብረ ብሔራውውም ሆነ የብሔረሰብ አቀንቃኞች ዋስትናቸው የሕግ የበላይነት እና ከሴራ ፖለቲካ የራቀ የዲሞክራሲያዊ ሂደት ውጤት መሆኑን ማመን፣
  • ለሕግ የበላይነት እና የዲሞክራሲያዊ ሂደት ውጤት ስኬት ሃሳብን በጨዋነት የመግለጥ እና ሃሳብን ለሕዝብ ግምገማ በመግለጥ ማመን፣ለእዚህም እንዲረዳ የሚድያው ሚዛናዊ ሂደት ሁሉም እኩል መግባባት እና መጠበቅ መቻል፣
  • የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጦር ሰራዊት፣የደህንነት መዋቅር እና የፍትህ ሂደት ውስጥ ምንም አይነት ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ተፅኖ አለመፍጠር። ምክንያቱም ሶስቱም አካላት ለሁሉም እኩል የሚያገለግሉ መሆናቸውን ማረጋገጥ በእራሱ አንዱ የዋስትና ምንጭ ስለሆነ፣
  • ካልሰለጠነ እና ኃላ ቀር አስተሳሰብ እና ተራ ንትርክ እንዲሁም ብሽሽቅ ወጥቶ በሰለጠነ ሃሳብን የማንሸራሸር፣የመግለጥ እና የላቀ የሃሳብ ማመንጨት ልዕልና መሸጋገር፣ 
  • በህብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያዊነትም ሆነ በብሄርተኝነት ስም የተደራጁ ሁሉ በእየቦታው በሃሳብ የሚመሳሰሉ ግን በቁጥር የተለያዩ ድርጅቶች ከማብዛት ሁሉም በሃሳብ ወደሚመስላቸው ስብስብ በመጠቃለል ሁለት ግዙፍ የፖለቲካ ድርጅቶች ወይንም መድረኮች ፈጥረው ለምርጫ የመቅረብ ዝግጅት ማድረግ እና  
  • ለኢትዮጵያ እኩል የመጠንቀቅ፣የመቆርቆር እና ህልውና መቆምን በተግባር ሁሉም ወገን ማሳየት እንዲህም ለጋራ የሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉም ልዩነት ሳይኖራቸው የሚቆሙበት የጋራ ሃገራዊ ህገ መንግስት ላይ ማሻሻል አድርጎ ፍፁም ታዛዥነትን ከግደታ ማስገባት የሚሉ ናቸው።
ባጠቃላይ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት የፖለቲካ ሁኔታ እጅግ ተስፋ ሰጪ፣የትውልድ ሽግግር የሚታይበት እና ኢትዮያ ተስፈንጥራ ለመነሳት ኃይል የመስጠት አቅም ያለው ነው።በእዚህ ሁሉ ሂደት ላይ ግን በብልጣብልጥነት አንዱ ጠቅልሎ ለመያዝ የሚደረጉ ሙከራዎች እጅግ አደገኛ ብቻ ሳይሆን መልሶ ወደ አልተፈለገ  ግጭት ውስጥ የሚቀት ነው።ለእዚህ ደግሞ አደጋው ያለው በአጉል ጀብደኘንት የሴራ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ ሂደቱን ለማሰናከል ከሚመኘው ከህወሓት በኩል ያለው የመጀመርያው አደጋ ሲሆን በመቀጠል ከአንዳንድ የብሄርተኛ አካላት ዘንድ ተመሳሳይ ምልክቶች አሉ።የእዚህ አይነቱ ሙከራ ለመጭዋ ኢትዮጵያ የማይመጥን ጊዜው ያለፈበት አንዲት ስንዝር የማያስኬድ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው።በእዚህ አይነት የተሳሳተ መንገድ ለሚያልሙ ደግሞ ሁለት አይነት መንገዶች መጠቀም ይቻላል።የመጀመርያው በተቻለ መጠን የተሳሳተ ሕልም ለሚያልሙ የሴራ ፖለቲከኞች በሙሉ በግልጥ ማስጠንቀቅ ያስፈልጋል።ማስጠንቀቁን አልፎ ሂደቱን ለማደናቀፍ ለሚሞክር ደግሞ የሚመጥን ምላሽ አስፈላጊ ነው።ከእዚህ ውጭ ግን በህብረ ብሔራዊውም ሆነ በበሄርተኛ እሳቤ ባለቤቶች በካከል የሚደረጉ የሃሳብ ልውውጦች አንዳንዴም  ከሰንደቅ አላማ ጀምሮ እስከ ዜግነት ድረስ የሚነሱ የሃሳብ ክርክሮች አንዳንዴም መወራረፎች ጨዋነትን ባለፈ መልኩ እስካልተቀየሩ ድረስ አደጋዎች አይደሉም።በእርግጥ ለእኛ ሀገር ፖለቲካ የእዚህ አይነት የሃሳብ ክርክሮች ካለማዳበራችን አንፃር የዓለም የመደናገጥ፣ተስፋ የመቁረጥ ስሜቶች አንዳንዶች ቢያሳዩ አይገርምም።እአየቆየ ግን ልምዱን እያዳበርን በሃሳብ ልዩነቶች መካከል መኖር አደጋ ሳይሆን እውነታውን ማየት ግን በሃሳብ የማሸነፍ አስፈላጊነትን ብቻ እንደሚያሳይ ስንረዳ ሁሉም ቀላል ይሆናል።አዎን ሁሉም ቀላል ይሆናል።መልካም መንገድ ላይ ነን።የበለጠ ደግሞ የላቀው የፍቅር፣በልዩነት አንድነት እና የመተሳሰብ ፖለቲካችን ያድጋል።ዋናው ቁምነገር እያንዳንዱ የዳር ተመልካች ከመሆን የእኔ ሚና በፖለቲካው ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሃብቱ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶች ሁሉ ምን ለስራ ብለን ወደ ተግባር መግባት አስፈላጊ እና ጊዜ የማይሰጠው ነው።

የአዲስ ሙላት አዲስ ነጠላ ዜማ(ቪድዮ) 
======================
አብይ አብይ ሲሉ ያው ፆሙን ነው ብዬ፣
ሰውም አብይ አለው አረ እናንተ ሆዬ።
 


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Friday, July 6, 2018

ክቡር ጠ/ ሚ/ር ዶ/ር ዓብይ አህመድ ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን የሚረዱበት አዲስ የመነሻ ሃሳብ ዛሬ አቀረቡ።ሀሳባቸውን በስምንት ደቂቃ ቪድዮ ይመልከቱ።

ጉዳያችን/Gudayachn
ሰኔ 29/2010 ዓም (ጁላይ 6/2018 ዓም)

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ለዲያስፖራ ይህንን መነሻ ሃሳብ (ፕሮፖዛል) ያቀረቡት በተወካዮች ምክር ቤት የ2011 ዓም በጀት ማብራርያ ከሰጡ በኃላ በልዩ መነሻ ሀሳብነት በመጪው ዓመት ብንሰራው ብለው ያቀረቡት ዓብይ የመነሻ ሃሳብ ነው።ሃሳቡን ባቀረቡ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ የዲያስፖራው ማኅበረሰብ በማኅበራዊ ሚድያ አዎንታዊ ምላሻቸውን መስጠት ጀምረዋል።ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Tuesday, July 3, 2018

የሆለታ ገነት የጦር አካዳሚን ስም ማን ሰወረው?

ጉዳያችን/Gudayachn
ሰኔ 26/2010 ዓም (ጁላይ 4/2018 እኤአ)

ሆለታ እና የጦር አካዳሚዋ

ከአዲስ አበባ ስላሳ አምስት ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የሆለታ ገነት ከተማ ከአዲስ አበባ ባልተናነሰ ታሪካዊ መነሻ አላት።በ1903 ዓም የመጀመርያው በውሃ ኃይል የሚሰራ ወፍጮ የተተከለባት ታሪካዊ ከተማ መሆኗን የታሪክ ምሁሩ ሪቻርድ ፓንክረስ ፅፈውላታል።የከተማው ስም ሆለታ (ኦለታ) ሲባል ገነት የሚለውን ስም የሰጧት ግን አፄ ምንሊክ እንደነበሩና  ከቦታው ማራኪነት የተነሳ እንደነበር ታሪኩን የሚያውቁ ይናገራሉ።አፄ ምንሊክ ቤተ መንግስታቸውን አዲስ ዓለም እና ሆለታ ላይ እንደሰሩ ይታወቃል።ቤተ መንግስታቸው ጋር ተያይዞም አሁን ማሰልጠኛው ባለበት ግቢ የኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ትገኛለች።
ሆለታ ገነት ጦር የምትገኘው የኪዳነ ምህረት ታቦት በጦር ሰራዊቱ ታጅባ ወደ ጥምቀተ ባህር ስትሸኝ።

የሆለታ ገነት ጦር አካዳሚ በ1928 ዓም በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ስም በአምስት የስዊድን መኮንኖች አሰልጣኞች እገዛ ስራውን ጀመረ።ሆኖም ግን ወድያው የፋሽሽት ጣልያን ሀገራችንን መውረር የጦር ማሰልጠኛው በአግባቡ ስራውን ማከናወን አቃተው።በወቅቱ ስልጠና ይከታተሉ የነበሩ ሰልጣኞች የመጀመርያ ዘመናዊ ጦር ሰልጣኝ ስለነበሩ ብርቅ ተዋጊዎች ነበሩ።ከማሰልጠኛው ውስጥ የነበሩ ሰልጣኞችም ሆኑ ስልጠናውን ያጠናቀቁ የጥቁር አንበሳ ጦር በሚል አዲስ የአርበኞች እንቅስቃሴ በተለይ በምዕራብ ኢትዮጵያ ጀመሩ።
የጥቁር አንበሳ ጦር በፋሽሽት ጣልያን ወረራ ወቅት  በአርበኝነት የተሳተፉ የሆለታ ገነት ጦር ምሩቃን እና በውጭ የተማሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን የመሰረቱት ፀረ ፋሽሽት እንቅስቃሴ በጣልያን ላይ ዘመናዊ የጦር ውጊያ በማሳየት ብቻ ሳይሆን በጥንታዊ መንገድ ለሚዋጋው የኢትዮጵያ ገበሬ አርበኛ ዘመናዊ ውግያ ስልትን በማስተማር የጥቁር አንበሳ ጦር ያደረገው አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም።የጦር አካዳሚው ተመልሶ የተመሰረተው ጣልያን ከሀገራችን ተባርራ ንጉሰ ነገስቱ ተመልሰው ከመጡ በኃላ በ1935 ዓም ነበር።የጥቁር አንበሳ የጦር አካዳሚ ሆለታ ገነት ጦር አካዳሚ የሚል ስያሜ ያገኘው ደርግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኃላ ነበር።

የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ስም ማን ሰወረው?

የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት በአፍሪካ አንጋፋው በዓለማችንም ከሁለተኛ  ዓለም ጦርነት በፊት ከተመሰረቱ ጥቂት የጦር ትምህርት ቤቶች ውስጥ አንዱ ነው። ይህ ለሀገራችን የጦር ሰራዊት ታሪክ አንዱ እና አይነተኛ ቅርስም ነው።ይህ የጦር ትምህርት ቤት በዘመነ ህወሓት/ኢህአዴግ በ1990 ዓም ከሕግ ውጭ በሆነ መንገድ ለግማሽ ክፍለ ዘመን የሆለታ ገነት ጦር አካዳሚን ስም  አቶ መለስ ደምስሰው ሐየሎም አርአያ የጦር ማሰልጠኛ አሉት።ጉዳዩ በወቅቱ ከፍተኛ ተቃውሞ በተለይ ከጦር ትምህርት ቤቱ ከተመረቁ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ቢነገርም ሰሚ አላገኘም።


ለማጠቃለል ማንንም መንግስት ለሚያደንቀው የጦር ሰው በስሙ ማሰልጠኛ መሰየም መብቱ ነው ብለን የምንናገር እንኖራለን።ሆኖም ግን ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ዝነኛ ማሰልጠኛን ታሪካዊ መሰረት በምንድ መልኩ በአንድ ሰው ስም መሰየም ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም።የሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት የህዝብ፣የሀገር ከፍ ሲል ደግሞ የአፍሪካም ነው።ቀድሞ የነበረው ስም የግለሰብ ስም አይደለም።አሁንም ስሙ በክብር ሊመለስለት ይገባል።አቶ መለስ ለሐየሎም አዲስ ማሰልጠኛ ከፍተው መሰየም መብት ነበራቸው።ከጣልያን ፋሽሽት ጀምሮ ገድል የሰራ ታላቅ አፍሪካዊ የጦር አካዳሚን ታሪካዊ ዳራ በሚያጠፋ መልኩ ስሙን መቀየራቸው ግን ወንጀል ነው። አሁንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ይህንን የስም ጉዳይ እንዲስተካከል ማድረግ አለባቸው።የሆለታ ከተማ ልጆችስ ለምንድን ነው ይህንኑ የሚጠይቅ የማኅበራዊ ሚድያ ጥያቄ የማትጀምሩት። ሆለታ ገነት ጦር ትምህርት ቤት ስምሽን ማን ሰወረው?

ጥቁር አንበሳ በድምፃዊ አብዱ ኪያር 


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

GUDAYACHN BLOG started on August 28/2011 ኢሜይል አድራሻዎን በመሙላት ጽሁፎቹን መከታተል ይችላሉ/Follow by Email

በብዛት የተነበቡ/Popular Posts

ጉዳያችን በፌስ ቡክ ገፅ / GUDAYACHN ON FACE BOOK

https://www.facebook.com/gudayachn/?pnref=story