ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ከሊቃነ ጳጳሳት ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ
ጉዳያችን/Gudayachn
ሐምሌ 11/2010 ዓም (ጁላይ 18፣2018 ዓም)
በያዝነው የሐምሌ ወር 2010 ዓም በኢትዮጵያ የፖለቲካም ሆነ ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ሶስት ቁልፍ ጉዳዮች መልክ ይይዛሉ ተብሎ ይጠበቃል።የመጀመርያው እና ባሳለፍነው ሳምንት የተከናወነው ጉዳይ ከኤርትራ ጋር የነበረው ችግር በመሪዎቹ የተጀመረው ፖለቲካዊ ግንኙነት ታፍኖ የነበረውን የህዝብ ለሕዝብ ፍቅር አገንፍሎ መሪዎቹን እስከሚያስደነግጥ ድረስ ስሜት በሚነካ መልኩ ተፈፅሟል።የቀሩት ሁለት አበይት ተግባሮች ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ እርቅ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉት ጉብኝት ናቸው።
ሲኖዶሳዊው እርቅ
ላለፉት ሃያ ስድስት አመታት ለሁለት ተከፍሎ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አንድ ለማምጣት አዲስ ዙር ንግግር በአሜሪካን መዲና ዋሽንግተን ውስጥ በመጪው ሐሙስ ሐምሌ 12 ይጀመራል። ለውይይቱም በውጭም ሆነ በሀገር ቤት ባሉት ሲኖዶሶች አንፃር ሶስት ሶስት አባቶች ተመድበዋል።ከእዚህ በተጨማሪ ላለፉት አስራ ሁለት ወራት ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት አስታራቂ ኮሚቴ አባላትም ለስኖዶሳዊው እርቅ ዋሽንግተን መግባት መጀመራቸውን ለማወቅ ተችሏል።
ይህ ሲኖዶሳዊ እርቅ የመጨረሻ መሆን እንዳለበት ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት እያሳሰቡ ነው።አሁን ወቅቱ ያለፈውን እያነሳን የምንወቅስበት አይደለም።የወደፊቱ ላይ ማተኮር ግን አስፈላጊ ነው።ይህ ማለት ያለፈው ስህተት ይሸፈን ማለት አይደለም።ትኩረት ችግሩን ፈትቶ ወደ አንድ ሲኖዶስ መምጣቱ እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው።ለሲኖዶስ መከፈል አንዱ እና ዋናው ምክንያት የህወሓት መንግስት በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት እና አሰራር ውስጥ ጣልቃ በመግባት በአቡነ መርቆርዮስ ላይ ያደረሰው ከመንበራቸው የመግፋት እኩይ ተግባር እንደነበር ይታወቃል።ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ደግሞ የውጭውን ሲኖዶስ ለስኖዶሳዊ እርቅ የሚወክሉት አቡነ ኤልያስ ስዊድን ከተማ ሉንድ ውስጥ በተደረገ አውሮፓ አቀፍ ጉባኤ ላይ የ1984 ዓም የፓትርያርኩን እና የጳጳሳቱን ስደት አስመልክተው ለምእመናን እንደተናገሩት -
''ምእመናን! በወቅቱ (የነበረውን ስውር የመንግስት እጅ ማለታቸው ነው) ሊገድሉን እንደነበረ ታውቃላችሁ?'' ካሉ በኃላ ''ወጣቱ የችግሩን መንስኤ በሚገባ ማወቅ አለበት። እግዚአብሔር ይህንን ዶ/ር ዓብይን አመጣው።ይህ የሰው ሥራ እንዳይመስላችሁ።የእግዚአብሔር ተአምር ነው።አሁንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግር ለመፍታት ለምናደርገው ሁሉ ምዕመናን ፀልዩልን።እኔ በምእመናን ፀሎት አምናለሁ።እግዚአብሔር የሚያውቃቸው ሰው የማያውቃቸው የሚፀልዩ አሉ'' ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሁሉም ወገኖች በጉጉት የሚጠበቀው ሲኖዶሳዊ እርቅ ከተከናወነ በኃላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ስራዎች ይጠብቃታል።የመጀመርያው ተግባር መዋቅሯን፣ከቤተ ክህነት ውስጥ ያለውን አሰራር፣የአጥብያዎች የቢሮ አሰራር፣የአገልጋይ አመዳደብ፣የገንዘብ አያያዝ እና በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ አጥብያዎች እና ሃገረ ስብከቶች መካከል ያሉ አሰራሮች በሙሉ ማዘመን እና ተጠያቂነትን በሚገባ ያሰፈነ ማድረግ ሁሉ አንገብጋቢ ተግባራት ናቸው።ከእዚህ በተለየ ቅዱስ ሲኖዶስ ከዘመኑ ጋር የገጠሙ የቀኖና ስርዓቶች መቀነን እና ምእመናን እንዲመሩበት ማድረግ ሌላው አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ከእዚህ በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያኒቱ ተልዕኮ ሀገር አቀፍ፣ አፍሪካ አቀፍ እና ዓለም አቀፍ እንዲሆን መስራት ያሉባት በርካታ ተግባራት አሉ።የቤተ ክርስቲያን ሚና ለሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ሚናም ማሳደግ ሌላው እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።
ሐሙስ ሐምሌ 12 የሚጀመረው ሲኖዶሳዊ እርቅ በተመለከተ የእርቅ ሂደቱ ሲጀመር እና በሂደት ላይ እያለ ምዕመናን ከስሜት፣እና ከወገንተኝነት የፀዳ ስሜት ሆነው መከታተል እንጂ ቀድመው አላስፈላጊ ሃሳቦችን በማህበራዊ ሚድያ ከመግለጥ መቆጠብ ይገባቸዋል።ይህ ማሳሰብያ ሚድያዎችንም ይመለከታል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በሐምሌ ወር ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በሚደረገው የአሜሪካ ጉዞ ውስጥ ከተካተተው መርሃ ግብር ውስጥ አንዱ በስደት የሚገኙትን የኢትዮያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስን መጎብኘት እና የስኖዶሳዊ እርቁን ተከትሎ ባለው ውጤት መሰረት ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና አስታራቂ ኮሚቴ ካህናት አባቶች እና ምዕመናን ጋር መወያየት ነው።ከእዚህ በፊት በተደረጉ ሲኖዶሳዊ እርቅ ሙከራዎች ውስጥ አንዱ እንቅፋት ሆኖ የቆየው የመንግስት ፈቃደኝነት አለማሳየት ብቻ ሳይሆን ወደ እርቅ የቀረቡ ሂደቶችን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማደናቀፍ እንደነበረ ይታወቃል።ለምሳሌ ከአራት አመታት በፊት በዳላስ ቅዱስ ሚካኤል ተሞክሮ የነበረው ሲኖዶሳዊ እርቅ በወቅቱ በነበሩት ፕሬዝዳንት ግርማ የድጋፍ ደብዳቤ አባቶች ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ የሚያዝ ቢሆንም በመሀከል በተለየ መልክ የህወሓት ከፍተኛ አባላት በተለይ አቦይ ስብሐት በቀጥታ ጣልቃ በመግባት እና በስደት የሚገኙትን አባቶች ቃል በቃል ''ሊሰቀሉ ይገባል'' የሚል እና ሌሎች አሳፋሪ ንግግሮች በመናገር እንዲሁም የወቅቱ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የፃፉትን ደብዳቤ እንዲስቡ ተፅኖ በመፍጠር ሂደቱ እንዲደናቀፍ መደረጉ ይታወሳል። በአሁኑ ሲኖዶሳዊ እርቅ ሂደት ግን የመንግስት ድጋፍ ከፍተኛ ከመሆኑ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በቀጥታ በጉዳይ በመግባት እና በማበረታታት እንዲሁም ወደ ሀገር ቤት ከስደት ለሚመለሱ አባቶች ዋስትና በመስጠት ጭምር እጅግ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው።አባቶቻችንም ይህንኑ መልካም ጉዳይ ከዳር አድርሰው የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ወደነበረበት እንደሚመልሱ ተስፋችን ከፍ ያለ ነው።ከእዚህ ሁሉ ሂደት ጋር ግን በስደት ያሉ አባቶች ወደ ሀገር ቤት ሲገቡ የቤተ ክርስቲያኒቱን መዋቅር በጠበቀ መልኩ መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ነው።ይህ ማለት ሀገር ቤት ከቤተ ክህነቱ የተለየ ሌላ ፅህፈት ቤት ወይንም ቢሮ መክፈት በሚል የሚመክሩ አንዳንድ በውጭ ያሉ በስደት ላሉ አባቶች የሚቆረቆሩ የሚመስሉ አካላት በሀገር ቤት ያለውን ምእመንም ሆነ ነባራዊ ሁኔታ ካለመረዳት የሚመነጭ መሆኑ መታወቅ አለበት።ይህ አካሄድ ቤተ ክርስቲያንን ለበለጠ መለያየት የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ እንደ ሀገርም ወደ አደገኛ እና የባሰ ሁኔታ የሚመራ መሆኑ መረዳት ተገቢ ነው።
የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ የአሜሪካ ጉዞ
ዘንድሮ አሜሪካ ኢትዮጵያውያን ለስደት ከወጡባት ምናልባትም ላለፉት አርባ አመታት ያህል አይታ የማታውቀውን አዲስ ክስተት ታስተናግዳለች።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በሶስት ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ይጎበኛሉ።ጉብኝቶቹ በሁለት መልክ የሚደረጉ እንደሆነ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ቡርቱካን አያና የሚመራውና ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጸሐፊነት የሚገኙበት፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉብኝት አመቻች ኮሚቴ አዲስ አበባ፣ዋሽንግተን እና ሎስ አንጀለስ ላይ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።ይሄውም በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሚገኙባቸው እና ከተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎች የተውጣጡ ስብስቦች ጋር የሚደረጉ ውይይቶች ናቸው።ይህ ''ግንቡን እናፈርሳለን፣ ድልድዩን እንገነባለን'' በሚል መርህ የሚደረገው ጉብኝት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት እራሳቸውን ያገለሉ ባለሙያዎች እና ሀገር ወዳዶች እንደሚሳተፉ ሲጠበቅ በሌላ በኩል በውጭ የተወለዱ እና በማደጎነት የሄዱ ከፍተኛ ሃገራዊ ፍቅር ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ለመጀመርያ ጊዜ በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚሰባሰቡበት ድንቅ የሆነ ስብስብ እንደሚሆን ይጠበቃል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካንን ምድር ሲረግጡ በርካታ ቁጥር ያለው ኢትዮጵያዊ ከአየር መንገዶች ጀምሮ የሚያደርገው አቀባበል ከፍተኛ የዓለም አቀፍ ዜና አውታሮችን እንዲስብ ተደርጎ መዘጋጀቱ ለኢትዮጵያ የሚሰጠው መልካም ስም የጉብኝት አመቻች ኮሚቴ ቢያስብበት ጥሩ መሆኑን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። በሌላ በኩል ድልድይ መገንባት በሀገር ቤት እና በውጭ ባለው ማኅበረሰብ መሃከል ጭምርም ስለሆነ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የሁሉንም ከተሞች ዝግጅቶች በቀጥታ ስርጭት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለመላው ዓለም ቢያዳርስ ለእዚህም የማስታወቂያ ስፖንሰሮች መሰረታቸውን አሜሪካ ካደረጉ የኢትዮጵያውያን ንግድ ድርጅቶች ማግኘት እንደሚችል ቢያስብ መልካም ይሆናል።ይህ ማለት ኢቲቪ ስንት ዓመት ሲያስከፋን እንዳልኖረ በውጭ ከሚኖረው ኢትዮጵያዊ ጋር በእዚህ ሰበብ ቢደመር ይሻለዋል።ይህ ድልድይ አንዴ ከተሰራ ኢቲቪ ቢሮውን ዋሽንግተን ላይ መክፈት እና በትርፍ ጊዜ አገልጋዮች የዲያስፖራውን ስሜት እየተከተለ የሚሰራቸውን መርሃ ግብሮች ማስፋት ሁሉ ይጠበቅበታል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉዞ መርሃ ግብር ቀን እና አድራሻ
ሐምሌ 21(July 28) ዋሽንግተን ዲሲ
ሐምሌ 22(July 29) ሎስ አንጀለስ
ሐምሌ 22(July 29) ሎስ አንጀለስ
ሐምሌ 23(July 30) ሜኔሶታ
በዋሽንግተን ዲሲ
ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓም
July 28, 2018
አድራሻ
ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓም
July 28, 2018
አድራሻ
Walter E. Washington Convention Center
801 Mt Vernon Pl NW, Washington, DC 20001
801 Mt Vernon Pl NW, Washington, DC 20001
በሎስ አንጀለስ
ሐምሌ 22 ቀን 2010 ዓም
July 29, 2018
አድራሻ
Los Angeles convention center 1201s Figueroa st.Los Angeles CA 90015
ሐምሌ 22 ቀን 2010 ዓም
July 29, 2018
አድራሻ
Los Angeles convention center 1201s Figueroa st.Los Angeles CA 90015
በሜኔሶታ
ሐምሌ 23(July 30)
July 30/2018
600 N 1st Ave.
Minneapolis MN 55403
starting at 10 AM
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ቡርቱካን አያና የሚመራውና ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በጸሐፊነት የሚገኙበት፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካ ጉብኝት አመቻች ኮሚቴ
ከእዚህ በተጨማሪ በሁሉም ከተሞች የጠቅላይ ሚኒስትሩ መርሃግብር ላይ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተጋበዙ ሲሆን ለሁሉም ከተሞች መግብያ በነፃ ነው።
ለማጠቃለል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አስመልክተው ከተናገሩት በመጥቀስ ሪፖርቱን እደመድማለሁ።
"በውጭ ሀገር የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን ሀገራችሁን ተሸክማችሁ እንደሄዳችሁ እንረዳለን። ኢትዮጵያውያንን ከኢትዮጵያ ታወጧቸው ይሆናል እንጅ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያውያን ልብ ልታወጧት አትችሉም የሚባለውን ለዚህ ነው። የጋራ ሀገራችንን በጋራ ልንገነባ ይገባል። ከመወቃቀስ ወጥተን መተባበር ይገባናል። በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትኖሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከልብ ታርቀንና ብሔራዊ መግባባትን ፈጥረን ለጋራ ሀገራችን ልንሠራ ይገባል። ዘረኝነትና መከፋፈልን እናጥፋለን። ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች። ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ
www.gudayachn.com
No comments:
Post a Comment