ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, July 10, 2018

አንዳንድ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን ዲያስፖራዎች የአቶ ኢሳያስ ጋሬጣ ወይንስ አጋዥ? ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደፊት ሊያተኩሩበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ የቱ ነው?

ጉዳያችን/Gudayachn
ሐምሌ 3/2010 ዓም (ጁላይ 10/2018 ዓም)


አንዳንድ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን ዲያስፖራዎች የአቶ ኢሳያስ ጋሬጣ ወይንስ አጋዥ?


የኢትዮጵያ እና ኤርትራ የ1990 ዓም ግጭት መልሶ ለመፈጠሩ ምክንያቶች ላይ በጉዳዩ ዙርያ  የጠለቀ መረጃ  በነበራቸው ሰዎች  ብዙ ተብሏል።በጠራ መልኩ ደግሞ የታሪክ ፀሐፊዎች ወደፊት ያስነብቡናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በእዚህ ፅሁፍ ላይ ግን የማነሳው አንዱ ጉዳይ በውጭ የሚኖሩ በእድሜ የገፉ አንዳንድ የኤርትራ ተወላጆች ከአቶ ኢሳያስ ብሰው እና ለእራሳቸው ለአቶ ኢሳያስም መገራት ያስቸገሩበት ሁኔታ እንደነበር ዛሬ ላይ ማንሳቱ ለወደፊቱም ጠቀሜታ ያለው ይመስለኛል።ዛሬ ላይ በእድሜ የገፉ የምንላቸው የዲያስፖራ ኤርትራ ተወላጆች በመጀመርያ ለጀብሃ ቀጥለው ለሻብያ ገንዘብ በማዋጣት እና በውጭ ሀገር በሚደረጉ የገቢ ማሰባሰብያ ዝግጅቶች ላይ የመሳተፍ ሚና ብቻ ያላቸው ነበሩ።ሆኖም ግን በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ትልቅ፣የታሪክ፣የትውልድ፣የሃይማኖት እና የቤተሰባዊ ግንኙነት ወደጎን አድርገው ግንኙነቱ  እንዳይጠናከር አንዳንዶች ለማጠናከር ሲሞክሩም የኤርትራን ሃገራዊነት የሚያጠፋ አደጋ አድርገው ይቆጥሩ ነበር።በእዚህም ሳብያ በእምነት ድርጅቶች ውስጥ አመራርነት እየያዙ ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ወጣቶችን አብረው የእምነት ቦታዎቻቸው ላይ መታደማቸውን በእራሱ ሲበጠብጡት ኖረዋል።ይህ በተለይ ከኢትዮጵያ የዛሬ ሃያ ዓመት  ''ትውልደ ኤርትራውያን'' እየተባሉ በህወሓት ተባረው የወጡትን የአዲሱ ትውልድ አካላት  ቀደም ብለው በውጭ ሃገራት  በያዙት ማኅበራዊ መሠረትነት ሳብያ እነኝሁ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን አዲሶቹን ስደተኞች ከኢትዮጵያውያን ለመለየት ብዙ መጣራቸው ይታወሳል።ሆኖም ግን የማኅበራዊ  እና የሃይማኖት መሰረቶች ቀላል ስላልሆኑ ወጣቶቹ ፈፅመው አልተቀበሏቸው።

እነኚሁ በውጭ የሚኖሩ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን ትውልድ ከትውልድ ማስታረቅ ሲገባቸው ምን ያህል በሚያባብሱ ስራዎች ላይ የተጠመዱ እንደነበር በቀላሉ ለማሳየት  የአቶ ኢሳይሳን አስተዳደርም የተፈታተኑበትን አንድ ስብሰባ በማሳየት ለአብነት ላንሳ።አቶ ኢሣያስ በ1980ዎቹ መጨረሻ ገደማ በናይሮቢ ባደረጉት ጉብኝት ላይ ከላይ የተጠቀሱት አይነት ግለሰቦች በተገኙበት ስብሰባ ላይ አቶ ኢሳያስ ከኢትዮጵያውያን ጋር ግጭት የሚፈጥሩ እንዲታረሙ የሚል ሃሳብ ሲሰጡ ለብዙ ዓመት ውጭ የኖሩ ''ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ'' አይነቶቹ ግለሰቦች መልሰው አቶ ኢሳያስን እኛ ለስንት ዓመት ስናዋጣ የኖርን መሆናችንን ይወቁልን አይነት አስተያየት ይሰጣሉ። በእዚህ ጊዜ አቶ ኢሳያስ የመለሱላቸው መልስ ''እናንተ ገንዘብ ሰጠን ትላላችሁ ህይወቱን ለእኛ የሰጠ ኢትዮጵያዊም አለ'' በሕዝብ መሃል ግጭት መፍጠር አይገባም አይነት ቁጣ የተቀላቀለበት ንግግር ማድረጋቸውን ከአስር ዓመት በፊት ዑጋንዳ እያለሁ ስብሰባውን የታደመ ሰው የነገረኝን አስታውሳለሁ። 

እነኝሁ ወገኖች የፈጠሩት ችግር በውጭ ሀገር ብቻ ሳይሆን ሀገር ቤት ሲሄዱም ከሰባ ዓመታት በላይ አብረው የኖሩ፣አንድም ቀን ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ሌላ ሀገር ብለው አስበው የማያውቁትን ሁሉ ሪፍረንደም ላይ ካልተሳተፉ እንደሚገለሉ በመስበክ የፈጠሩት ውዥንብር አብሮ የነበረውን መልካም ሕዝብ ሰላሙን ያናጋ ነበር።ይህ ማለት በውጭ የኖሩት በእድሜ የገፉት የኤርትራ ተወላጆች ብቸኛ ተወቃሽ ናቸው ለማለት ሳይሆን፣ አንዳንዶች ያደረጉት አሉታዊ አስተዋፅኦ ለሌላው ዲያስፖራ ትምህርት ስለሆነም ነው።በነገራችን ላይ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የኤርትራ ተወላጆች እንደ ዲያስፖራው በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን የሚያስቡ አይደሉም።ይህንን መልካም አካባቢያዊ ሁኔታ የበከለው በውጭ በሴራ ፖለቲካ እና በጥላቻ የተካነው በእድሜ የገፋው የኤርትራ ተወላጅም ጭምር እንደነበር ለማስታወስ ነው።ይህ ጉዳይ ዛሬ ላይ ጥቅም የለውም ብሎ የሚያስብ ሊኖር ይችላል።አዎ! አሁን ያለፈውን ጉዳይ የምናወራበት አይደለም።ሆኖም ግን ለወደፊቱም ወጣቱ ትውልድ መጠንቀቅ ያለበት የእዚህ አይነት የተሳሳተ እሳቤ ካላቸውም ጭምር  መሆኑን ማሳሰቡ ጠቃሚ ነው።በሌላ በኩል ለወደፊት በጉዳዩ ዙርያ የሚያጠኑ በውጭ የሚኖሩ በእድሜ የገፉ ኤርትራውያን ነገሮችን ከማብረድ ይልቅ የማካረር ሚና በእራሱ አንዱ ሊጠና የሚገባ መሆኑንም ለመጠቆም ነው።


ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወደፊት ሊያተኩሩበት የሚገባው ዋናው ጉዳይ የቱ ነው?


የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መለያየት ፈፅሞ እንደማይሆን በተምኔታዊ ግምት ብቻ ሳይሆን ለ27 ዓመታት በተደረገ ሙከራ ተረጋግጧል።በማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሳይንስ መካከል ያለው ልዩነት ፣ የተፈጥሮ ሳይንስን በላብራቶሪ ውስጥ አስገብቶ እና ሞክሮ ውጤቱን ማወቅ ሲቻል የማኅበራዊ ሳይንስ ግን ያለፈውን ተሞክሮ በማየት እና አሁን እየሆነ ያለውን መረጃ በመሰብሰብ የሚደረስበት ድምዳሜ ነው።የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጉዳይም የማኅበራዊ ሳይንስ ጉዳይ እንደመሆኑ ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት ተለያይተው  መኖር እንደማይችሉ በሙከራም ጭምር አረጋግጠዋል። 

አሁን የተጀመረው መልካም ጅምር በሚገባ ለማስኬድ ከዝርዝር ግንኙነቶቹ በተጨማሪ የዜግነት ጉዳይ አንዱ መስተካከል ያለበት ነው።በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ያሉ ካለ አንዳች ገደብ የመስራት እና የመኖር ፍላጎት አላቸው።ይህንን ጉዳይ ግን ምንም አይነት ነፃ ቪዛ ቢደረግ እና ካለ ፓስፖርት መሄድ ይቻላል ቢባል መልሶ የሚይዝ ጉዳይ ለሁለቱም ሃገር ፖለቲከኞች እንደ ''ሽንፍላ'' የማይጠራው ጉዳይ የዜግነት ጉዳይ ነው።አቶ አሳያስም ሆኑ ዶ/ር አብይ ይህንን ጉዳይ አንድ አይነት ማሰርያ ማበጀት መቻል አለባቸው። አንድ ኤርትራዊ ለኢትዮጵያ የፀጥታ ስጋት እንደማይሆን፣አንድ ኢትዮጵያዊም ለኤርትራ የፀጥታ ስጋት እንደማይሆን ያለፈው ስምምነት አመላካች ነው።ከእራሱ ዜጋ ስጋት ያለበት ሀገር የለም።ምን ለማለት ነው? በምንም አይነት ሁለቱም ሀገሮች በአንድ አይነት መልክ ወደ ኮንፈድሬሽን የሚመጡበት እና ኢኮኖሚያዊ ውህደቱን በፖለቲካዊ ውህደት፣ወይንም ተወራራሽ ቅርፅ ካልሰጡት በተገደበ መልክ የሚኖር ግንኙነት ሁል ጊዜ የሁለቱንም ሀገር ዜጎች እንዳሳቀቀ የሚኖር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኞቻቸው የመከራከርያ አጀንዳ አድርገው ጊዜያቸውን እንዲያጠፉ የሚያደርግ '' ጉንጭ አልፋ'' ትንተና ውስጥ እንዲገቡ አያስፈልግም።

ባጠቃላይ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሐከል የተቀደደው የመለያየት መጋረጃ ታሪካዊ ነው።የህዝቡንም የፍቅር ጥማት በሁለቱም መካከል የታየ ብዙዎችን ያስለቀሰ ክስተት ነው።አቶ ኢሳያስም ዘግይተውም ቢሆን ምንም አይነት ልዩነት ለማውጣት የሚቸግር መሆኑን ቆይተውም ቢሆን የተረዱት ይመስላል።አሁን ካለፈው የመማርያ እና የወደፊቱን በጥልቅ መሰረት ላይ ለመጣል እንዲሁም ትውልድ ተሻጋሪ ሥራ ለመስራት ዕድል ያላቸው መሪዎች በጥልቅ ሊመለከቱት ይገባል። ሁለቱም ሀገሮች ወደ ፖለቲካዊ ሕብረት በመምጣት የዜግነት ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያዊ ቅኝት አንድ አይነት መልክ ማስያዝ አለባቸው።እንዴት? ለሚለው ጥያቄ አሁን ዝርዝር መልስ ለማስቀመጥ ጊዜ ይፈልጋል። ፖለቲካዊ ህብረት ማለት ግን በዋናነት የዜግነት ልዩነትን ማጥፋት እና ወደ ኢትዮጵያዊ ጎራ ገብቶ ባለቤት የመሆን ጉዳይንም ይጨምራል። አንዳንዶች ምጣኔ ሀብታዊው ግንኙነት እና ሕብረት በራሱ ወደ ፖለቲካዊው ያመራል ይላሉ።ይህ ግን በዘገምተኛ መልክ የሚሄደው የተለያየ ባህል ላላቸው ህዝቦች ነው እንጂ እንደ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ያለ ጥልቅ የባህል መመሳሰል ብቻ ሳይሆን ፍፁም አንድነት ላላው ሕዝብ አይደለም።በሁለቱ መካከል ያለው የምጣኔ ሀብት ግንኙነት በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ውስጥ ወደነበረበት ይሄዳል።በመቀጠል የፖለቲካ እና ዜግነት ጉዳይ ወድያው አፍጥጦ ይመጣል።ያን ጊዜ ይህንን በጎ ተግባር ያንገጫግጨዋል።ስለሆነም በተለይ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ  በእዚህ በኩል ያለውን እውነታ ወደ ጎን ሊሉት አይችሉም።ይህ ማለት ኤርትራን ከሚነጥል የፖለቲካ ግንኙነት ከኢትዮጵያ ጋር ወደ የሚደምር የፖለቲካ ግንኙነት መምጣት ወሳኝ ነው።ይህ ማለት በዲሞክራሲያዊ ሂደት ኢትዮጵያውያን ስለ ኤርትራው ፖለቲካ እኩል በጋር መልክ እንዲሳተፉ፣ኤርትራውያንም እንዲሁ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ የዲሞክራሲያዊ ሂደት እንዲሳተፉ ማድረግ እና ድህነታችንም ሆነ ሀብታምነታችን ተወራራሽ አብሮ የሚወድቅ እና የሚነሳ በእኩል ዜግነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው። እዚህ ላይ የአሰብ ወደብ እና ሌሎች ጉዳዮች በጣም ጥቃቅን ጉዳዮች አድርጌ ነው የማያቸው።ጥቃቅን የምለው ከጉዳዩ አስፈላጊነት አንፃር ሳይሆን እነኝህ ጉዳዮች ላለፉት 27 ዓመታት ተሞክሮም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ  ካልሰሩበት ወደቡ በራሱ  የበለጠ አደጋ ይዞ እንደሚመጣ አደጋው ደግሞ ለሁሉም የሚተርፍ መሆኑ ተመስክሯል። ስለሆነም ከምጣኔ ሃብቱ ጉዳይ ጋር እኩል የዜግነት ጉዳይ እንዴት አንዱ ከሌላው የተለየ እንዳልሆነ ሆኖ በሚያሳይ እና ትውልድ አሻጋሪ በሆነ መልክ በሕግ መቀመጥ ይችላል? የሚለው ወሳኝ ጉዳይ ነው።ይህ ጉዳይ አሁን በስልጣን ላይ ያሉት ወገኖች በቶሎ ካልፈቱት ሕዝብ በጉልበቱ ወደ እዚሁ መንገድ እንደሚያመጣው ማመን ይገባል። ጥያቄው የታሪኩ አካል የመሆን እና ያለመሆን ዕድል እና ክፉ ዕጣ ነው። 


አስመራ ላይ ለዘንድሮ አዲስ ዓመት በድምቀት የሚሰማው ሙዚቃ 
ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...