ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, February 28, 2017

የዓድዋ ድል እና የቤተክርስቲያን ሚናከመንግሥቱ ጎበዜ
ሉንድ ዩንቨርስቲ፣ ስዊድን

  • አፄ ምኒልክ አዋጅን ካስነገሩ በኋላ በአዲስ አበባ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተገኝተው የተሳሉት ስዕለት “አምላከ ቅ/ጊዮርጊስ ድሉን ቢሰጠኝ ይህን የቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሣር ክዳኑን ለውጨ ባማረ ሕንፃ አሠራዋለሁ ” የሚል ነበር፡፡ 
  • ይህንም ስእለታቸውን ከድል በኋላ ፈጽመውታል፡፡
  • ሊቀጳጳሱ አቡነ ማቴዎስና በእጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ በመላ ሀገሪቱ ጸሎት፣ ኀዘንና ምህላ አውጀው ነበር።
  • ቤተክርስቲያን  የአዝማች  ኮሚቴ አቋቁማ ነበር፣ 
  • ከዘመቻው በፊት ዘማች  አብያተክርስቲያናትም  ተለይተዋል፣  
  • በዘመቻውም ታቦት፣መስቀል፣ ንዋያተ ቅድሳት ቃጭል፣ጥላዎች እና ድባቦች ይዘው ሊቃውንቱ እና ካህናት ዘምተዋል።
                                                          
የአድዋ ጦርነት የምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች የመስፋፋትና አፍሪካን የመቀራመት ህልማቸው ውጤት ነው፡፡ እነዚሁ ምዕራባውያን አፍሪካን የመቀራመት ሩጫቸው ወደ ፀብ ሲያመራቸው ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት በርሊን ላይ ከ1977-1978 ዓ.ም ለረጅም ጊዜ ስብሰባ ተቀመጡ::የበርሊኑን ጉባኤ ተከትሎ ምዕራባውያኑ መጀመሪያ አፍሪካ ላይ የያዙት ቦታ መጀመሪያ ስለማያዛቸውና የነሱ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ማስረጃ ፍለጋ ጀመሩ፡፡በዚህም የተነሳ አፍሪካ ውስጥ ብዙ የተጨበረበሩና የማታለያ  ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ በ1881 ዓ.ም በኢጣሊያዊ ተወካይ አንቶሎኒና በአፄ ምኒልክ መካከል የተደረገው ስምምነት ለዚህ ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡ 

ለውጫሌ  ስምምነት ሃያ  አንቀጾች ያሉትና በሁለት ቋንቋዎች የተጻፈ ሲሆን የግጭቱ መንስኤ የሆነው በኢጣሊያንኛ ቋንቋ የተጻፈው 17ኛው አንቀጽ ነበር፡፡ የአማርኛው ውል ፡-የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የውጭ ግንኙነቱን  በኢጣሊያ አጋዥነት  ማድረግ ይቻላቸዋል በማለት ምርጫው የአፄ ምኒልክ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን  የጣሊያንኛው ትርጉም ደግሞ  አፄ ምኒልክ የውጭ ግንኙነቱን  በሙሉ በኢጣሊያ በኩል ማድረግ ይገባዋል በማለት ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ ያደርጋታል፡፡  በዚህም የተነሳ 17ኛውን አንቀጽ አዛብተው በመተርጐም ኢትዮጵያ በኢጣሊያ የሞግዚትነት አስተዳዳር ሥር ሆናለች ብለው ለዓለም መንግሥታት  ማሳወቅ ጀመሩ:: ከሩስያ በስተቀር መላው የወቅቱ ሃያላን መንግሥታት ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ የውጫሌ ውል ሰጥቶኛል የምትለውን ሥልጣን እውቅና ለመስጠት ዝግጁ ነበሩ፡፡ የሆነ ሁኖ ግን የውጫሌ ውል የተጭበረበረ መሆኑ ከታወቀ በኋላ በእነ አፄ ምኒልክ ተቀባይነት በማጣቱና ውሉን በማፍረሳቸው የአድዋ ጦርነት ሊመጣ ግድ ሆኗል፡፡

የመጀመያው ውጊያ አምባላጌ ላይ  በኅዳር 29 ቀን 1888 ዓ.ም ተደረጎ በራስ መኰንንና  በፊታውራሪ ገበየሁ የጦር መሪነት በድል ተጠናቀቀ፡፡ ሁለተኛው የጠላት ጦር መቀሌ መሽጐ ነበርና በእቴጌ ጣይቱ ዘዴ ውኃ የሚያገኝበት ምንጭ ስለተዘጋ  ለቆ እንዲወጣ ተገደደ፡፡ ዋናው የአድዋው ጦርነት የካቲት 23 ቀን በዕለተ ሰንበት በ6 ሰዓት ውስጥ በኢትዮጵያ የበላይነትና ድል አድራጊነት ተጠናቀቀ፡፡ በብዙ የታሪከ ጸሐፊዎች  ዘንድ የኢጣሊያን ጦር  ለሽንፈት ዳርገውታል ተብለው የሚወሰዱት  ዓበይት ምክንያቶች  የተሳሳተ የንባብ ካርታ፣ የመንገድ መሳሳት ፣ በሁሉም መስክ (በዘመናዊ መሳሪያና ትጥቅ ፣በሰለጠነ ሰራዊትና በመሳሰሉት) የበላይነት ስለነበራቸው ለኢትዮጵያውያን የሰጡት አነስተኛ ግምት በመኖሩ ፣ ኢትዮጵያውያን በሰንበትና በድርብ በዓል ጦርነት አይገጥሙም ብለው ሂሳብ መስራታቸው የሚሉት ናቸው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያን ሠራዊት ድል እንዲቀዳጅ የረዱት ነገሮች ጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜት፣ ጦርነቱ ለአገርና ለሃይማኖት ጭምር  መሆኑን ሠራዊቱ ማመኑ፣ የላቀ የጦር ስልትና አመራር መኖሩ፣ ጠንካራ የሠራዊት ሞራልና የስነ ልቦና ዝግጅት፣ ሕዝብን የማንቀሳቀስና የመምራት ብቃት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የአድዋ ድል  በአገራችን  ከተካሄዱት በርካታ የጦርነት ድሎች ልዩ የሚያደርጉት ባህርያት አሉት፡፡ የመጀመሪያውና ዋነኛው በአራቱም አቅጣጫ የሚገኙ መላ ኢትዮጵያውያን የተሳተፋበት የጦርነት ድል መሆኑ ነው፡፡ የአድዋ ድል የዘር፣  የብሔር፣ የቋንቋ፣ የፆታ፣ የሐይማኖት ወዘተ  ልዩነት ሳይኖር  በድፍን ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት የተገኘ ውጤት ነው፡፡ ሁለተኛው አስደናቂ የአድዋ ድል ልዩ ገጽታ ደግሞ እስከ አፍንጫው ድረስ ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀንና የሠለጠነውን  የኢጣልያን ሠራዊት እጅግ ኋላቀር በሆነ መንገድና መሣሪያ ያልሰለጠነው የኢትዮጵያ ጦር ማሸነፍ መቻሉ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ አድዋ በዓለም ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁሮች ነጮችን ያሸነፉበት ዓብይ ወታደራዊ ድልም ነው፡፡ በተጨማሪም የአድዋ ጦርነት የድል ውጤት የኢትዮጵያን ነፃነት ከማረጋገጥ አልፎ ዓለምአቀፋዊ እንቅስቃሴን የፈጠረ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ 

የአድዋ ድል ለዘመናት ተከብሮ የኖረውን የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ሀገርነትና ነፃነትን ከማረጋገጡም በላይ ለሀገራችን ዓለምአቀፍ ዝናን አጐናጽፏታል፡፡ የአድዋ ድል የቅኝ ገዥዎችን ቅስም በመስበር  ፖሊሲያቸውንም እንደገና እንዲመረምሩ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያን ለመቀራመት በጎረቤት አገሮች አሰፍስፈው የነበሩት ቅኝ ገዥዎች ከኢትዮጵያ ጋር በአቻነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ግንኙነት ለመመሥረት ተገደዋል፣ በቅኝ ግዛቶቻቸውና በኢትዮጵያ መካከል  የድንበር መካለል እንዲደረግ ወስነዋል፣ ኤምባሲዎችን በአዲስ አበባ በመከፍት የዲኘሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ጀምረዋል፡፡ የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን የትብብር፣ የአንድነት፣ የኩራትና የክብር ምንጭ ከመሆኑ ባሻገር  የድሉ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ ለጥቁሮች ነፃነትና የክብር ፋና ለመሆን በቅታለች፡፡ የአድዋ ድል ምሳሌነት አፍሪካውያን በቅኝ ገዥዎቻቸው ላይ አንዲነሱ ምክንያት ሆኗል፣ ለፓን አፍሪካን እንቅስቃሴ መፋፋምም ጉልህ አስተዋጽኦ አበርከቷል፡፡ ከዚህ አልፎ የአድዋ ድል  ከነጮች ተፅዕኖ ነፃ የሆነ የጥቁሮች የሃይማኖት እንቅስቃሴ እንዲጀመር ምክንያት እስከ መሆን ደርሷል፡፡  ለአብነትም ኢትዮጵያኒዝም እየተባለ ይጠራ የነበረውና  በተለይ በአሜሪካና በደቡብ አፍሪካ  የነበረውን እንቅስቃሴ መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

ለአድዋ ድል መገኘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሚና እጅግ የላቀ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህች ጥንታዊ ቤተክርስቲያን  በአድዋ ጦርነት ወቅት ከመነሻው እስከመጨረሻው፣ ከዘመቻው እስከ ድሉ፣ ከዋዜማው እስከጦርነቱ በመሪነትና በተሳታፊነት ነበረች፡፡ ቤተክርስቲያኗ ሕዝቡን በመቀስቀስ፣ አመራር በመስጠት፣  አብራ በመዝመት፣ የስነ ልቦና ዝግጅት እንዲኖር በማድረግ፣ በጦርነቱ በመሳተፍ፣ መረጃ በመስጠትና በማስቀመጥ ባደረገችው አስተዋጽዖ ተወዳዳሪ አልነበራትም፡፡  ለረጅም  ዘመናት ይዛ በቆየችው ልዩ ልዩ አገራዊ ሓላፊነትና ሚናዋ ምክንያት፣ አገር ያለ ሃይማኖት ሃይማኖት ያለ አገር የለም በሚለው እሳቤ፣በቀደሙት የጦርነት ታሪኮች ከሁሉም  በላይ ጥቃት   የደረሰባት  እርሷ በመሆኗ ( ለአብነት ያክል የአህመድ ግራኝን ጥፋት፣የመቅደላን የቅርስ ዝርፊያ ፣ የደርቡሾች ጥቃት መጥቀስ ይቻላል) እና በተለይ ደግሞ የወራሪው መንገድ ጠራጊዎች አባ ማስያስን የመሳሰሉ ሚሲዮናውያን በመሆናቸው ቤተክርስቲንዋ በጦርነቱ የነበራትን ጉልህ ተሳትፎ ምክንያታዊ ያደርገዋል፡፡   

በአደዋ ጦርነት ወቅት ቤተክርስቲያኗ  የነበራትን  የላቀ  ሚና ለመረዳት  የአፄ  ምኒልክን የክተት ዐዋጅ ብቻ መመልከት በቂ ነው፡፡ አዋጁ ጦርነቱ ከቤተክርስቲያን፣ ከእግዚአብሔር እና ከወላዲት አምላክ ጠላት ጋር እንደሆነና የመጣው ጠላት አገር የሚያፈርስ ብቻ ሳየሆን ሃይማኖት የሚለውጥ ጭምር መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡ በመሆኑም የጦርነቱ አዋጅ ሐይማኖታዊ ቅርጽ ነበረው፡፡ አዋጁ እንደሚከተለው ነበር፡፡

 ስማ፣ ስማ፣ተሰማ የማይሰማ የእግዚአብሔር እና የወላዲት አምላክ ጠላት ነው፡፡ ስማ፣ ስማ      
ተሰማማ፣የማይሰማ የእግዚአብሔርና የቤተክርስቲያን ጠላት ነው፡፡ ስማ፣ስማ ተስማማ፣ የማይሰማ የእግዚአብሔርን የንጉሡ ጠላት ነው፡፡እግዚአብሔር ወሰን እንዲሆን የሰጠንን ባሕር አልፎ ሃይማኖት የሚለውጥና ሀገር የሚያጠፋ ጠላት መጥቶአል፡፡ እኔ ምኒልክ በእግዚአብሔር ርዳታ ሀገሬን ለጠላት አሳልፌ አልሰጥም፡፡ ያገሬ ሰው! ከአሁን ቀደመ የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ርዳኝ፣ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በኅዘን ርዳኝ፡፡ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፣ አልተውልህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነው፡፡ 

አፄ ምኒልክ አዋጅን ካስነገሩ በኋላ በአዲስ አበባ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ተገኝተው ጸሎት ማድረሳቸውና ብፅዓት ማድረጋቸው ወይም ስዕለት መሳላቸው የጦርነቱ መንፈሳዊ ዝግጅት አካልና ለቤተክርስቲያኗ ልዩ መልእክት የነበረው ነው፡፡ ስዕለታቸውም “አምላከ ቅ/ጊዮርጊስ ድሉን ቢሰጠኝ ይህን የቅ/ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ሣር ክዳኑን ለውጨ ባማረ ሕንፃ አሠራዋለሁ ” የሚል ነበር፡፡ ይህንም ስእለታቸውን ከድል በኋላ ፈጽመውታል፡፡ የክተት አዋጁን  ተከትሎም  በሊቀጳጳሱ አቡነ ማቴዎስና በእጨጌ ወልደ ጊዮርጊስ በመላ ሀገሪቱ ጸሎት፣ ኀዘንና ምህላ ታወጀ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቤተክርስቲያን አስተምህሮው ተጠናከሮ ቀጠለ፡፡ አገር ከሌለ ሃይማኖት የለም፣ ሃይማኖትና ነፃነትን ማጣት ሽንፈት ነው፣ ወደ ፈጣሪ ለአገርና ለሃይማኖት ታግሎ መሔድ ሰማዕትነት ነው፣ ኢትዮጵያን  ያህል አገር ማጣት እግዚአብሔርን ከሚያህል ጌታ መለየት ሞት ነው፣ ስለ አገር፣ ሃይማኖትና ነፃነት መሞት ክብር ነው ወዘተ የሚሉት የአስተምህሮው አንኳር ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ከዚያም በቤተክርስቲያን  የአዝማች  ኮሚቴ ተቋቋመ፣ ዘማች  አብያተክርስቲያናትም  ተለይተው ታወቁ፡፡ በዘመቻውም ታቦት፣መስቀል፣ ንዋያተ ቅድሳት ቃጭል፣ጥላዎች እና ድባቦች ይዘው ከሊቃውንቱና ካህናቱ ጋር እንዲዘምቱ ተወሰነ፡፡ 

ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ በነበረው የዘመቻ ጉዞ  ቤተክርስቲያኗ ግምባር ቀደም ሆና  ሕዝቡን ከጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ጋር  በአንድነት በመምራት በአስተምህሮዋ፣ የዘማቹን ወኔ በመገንባት፣ ስለአገር ፍቅር በመሰበክ፣ በጾምና በጸሎት  ወደፊት ትገሰግስ ነበር፡፡  በጉዞው ወቅት በሊቀጳጳሱ አቡነ ማቴዎስና በእጨጌ ወ/ጊዮርጊስ አስተባባሪት መንፈሳዊ አገልግሎቱ በመዓልትና በሌሊት በሰዓታት፣ በማኅሌት፣ በቅዳሴ በነግህና በሰርክ ጸሎት ሳይቋረጥ ይከናወን ነበር፡፡ ዘማቾቹም  በሰንበት ቀን አለመጓዝ፣ ዓበይት በዓላትን ማከበር፣ለድኃው መመጽወት እና የመሳሰሉትን ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ያከናውኑ ነበር፡፡ የጦር መሪዎቹ ሳይቀር  በጸሎታቸው የተጉ የመንፈሳዊ  ልእልና ያላቸው ነበሩ፡፡ ልዑል ራስ መኰነን አምባላጌን  ለማስለቀቅ በነበራቸው ምኞት በጦርነቱ ኃይልና ድል እንዲሰጣቸው ለአምላከ ቅ/ጊዮርጊስ ጸሎታቸውን አቀርበዋል፡፡ በመጨረሻም በአንገታቸው ላይ ባለው የወርቅ መስቀል አማትበው ጦርነቱን ለመግጠም እንደወሰኑና ድል አደረገው አምባላጌን ነፃ እንደአወጡ  ይነገራል፡፡ እቴጌ ጣይቱ በመቀሌ የመሸገውን ጠላት የውኃ ምንጩ እንዲያዝ ዘዴውን ከፈጠሩ በኋላ ሌሊቱን ሙሉ ”ጌታዬ እኔን ባርያህን አታሳፍረኝ በነገሬም ግባበት ርዳታ ትችላለህና” እያሉ ይጸልዩ እንደነበር ታውቋል፡፡ 

በየካቲት 14 ቀን 1888 ዓ.ም አፄ ምኒልክ አድዋ ሲደርሱ ከመላው ትግራይ የተውጣጡ ካህናትና ሊቃውንት የየደብራቸውን ታቦታት ይዘው ልብሰ ተክህኖ ለብሰው በደማቅ ሁኔታ ተቀብለዋቸዋል ፡፡ ከዚያም በመላ ትግራይ ለአንድ ሱባኤ ምህላ ታዟል፡፡ አጤ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ሱባኤ ይዘው የቆዩት በእንዳ አባ ገሪማ ገዳም ነበር፡፡ ለጦርነቱ ዝግጅትና መሰናዶ ሲጀመርም አስቀድሞ የታወጀው የጸሎትና የምህላ ዓዋጅ ነበር፡፡ ወደ  ጦር ግንባር ሲዘምቱ ታቦታት፣ መስቀሎችና ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት ተይዘው ነበር፡፡ የሃይማኖት አባቶችና የቆሎ ተማሪዎች ሳይቀር በጦርነቱ ተሳትፈዋል፡፡ በመጨረሻም ለመላው ዘማች ለሰባት ቀናት የቁም ፍታት ተካሂዷል፡፡ ጀግናው  አውአሎም ሀገረጎት እና  መሰል አርበኞች ለኢጣሊያን  የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ለአድዋ ድል አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወቃል፡፡  ከጦርነት አንድ ቀን በፊት የካቲት 22 ቀን እቴጌ ጣይቱ ለአውአሎም ምግብ  አቅርበው  “እንካ ይህን እንጀራ እንደ ሥጋ ወደሙ ቆጥረህ ብላው ብትከዳ እግዚአብሔር ይፈርድበኋል ”  ብለው እንደ ሰጡት ይነገራል፡፡የካቲት 22  ለየካቲት 23 አጥቢያ በአውአሎም መረጃ ምክንያት  ጥላት ከምሽጉ እንዲወጣ ስለተደረገ ሌሊት ሲጓዝ አድሮ አድዋ እንደገባ በመረጋገጡ ቅዳሴው ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ እንዲፈጸም ተወሰነ፡፡    

በጦርነቱ ዋዜማ አፄ ምኒልክ ፣  ንጉሥ ተ/ሃይማኖት፣ ራስ መኰንን፣  ራስ መንገሻ ፣  ፊታውራሪ ገበየሁ  ዓድዋ በሚገኘው የቅዱስ ገብኤል ቤተክርስቲያን  ያስቀድሱ ነበር፣  ቅዳሴውም የተመራው በጳጳሱ በአቡነ ማቴዎስ ነበር፡፡ አቡነ ማቴዎስ “ልጆቼ ሆይ ዛሬ የእግዚአብሔር ፍርድ የሚፈጸምበት ቀን ነውና ሂዱ ለሃይማኖታችሁ ለአገራችሁ ሙቱ እግዚአብሔር ይፍታህ” ሲሉ መኳንንቱ ሁሉ እየተሽቀዳደሙ የአቡኑን መስቀል ተሳልመው ወደጦርነት መሄዳቸው፣ ሊቀጳጳሱም ወደ ጦርነት የሚገባውን ወታደር ሁሉ እግዚአብሔር ይፍታህ እያሉ ይናዝዙ እንደነበር ይነገራል፡፡  አፄ ምኒልክም በበኩላቸው ነጋሪት እያስጐሰሙ ሠራዊቱን “ጦርነትና የጦርነት ድምፅ ብትሰሙም አትደንግጡ፣ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ሆኖ ጠላቶቻችሁን ስለሚዋጋ አትፍሩ፣ እግዚአብሔር አምላካችሁ በፊታችሁ እየኼደ ጠላቶቻችሁን ስለሚዋጋላችሁ እናንተንም ስለሚያድናችሁ ከፊታቸው አትሽሹ” በማለት ያበረታቱ ነበር፡፡  ከዚህ ሁሉ በኋላም አንጸባራቂው የአድዋ ድል በየካቲት 23 ቀን በዕለተ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተበሰረ፡፡ 

የአድዋ ድል ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በነጻነት የግዛት አንድነቷ ተጠብቆ ዳር ደንበሯ ተከብሮ ለዚህ ትውልድ እንድትደርስ በማድረግ በኩል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያደረገችው የላቀ፣ ዘመን ተሻጋሪና ዘርፈ በዙ አስተዋጽኦ  አንዱና ዋነኛው ማሳያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን  አባቶችና እናቶች ታሪክና ቅርስን ብቻ ሳይሆን በከፈሉት መሰዋዕትነት ሀገርንም አቆይተውልናል፡፡ ይህ ትውልድ እንደ አባቶቹ ታሪክ መሥራት ባይችልም እንኳ ታሪኩንና ቅርሱን ማወቅና መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ የቤተክርስቲያንንም አስተዋጽኦና ውለታ መርሳት የለበትም፡፡ የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊ አንድነታችን ውጤትና ምልክት በመሆኑ ጎሰኝነትን ለሚያቀነቅነው ትውልድ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከታሪክ የማይማር ትውልድ መነሻ  እንደሌለው ሁሉ መድረሻም የለውም፡፡ 

ማጣቀሻ ዎች

ቤካ ናሞ፣  አደዋና ምኒልክ::  አርቲስትክ ማተሚያ ቤት (1956)

ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣  አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት :: ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት (1983)

ተወልደ ትኩእ ፣  የኢትዮጵያ አንድነትና ኢጣልያ:: አዲስ አበባ (1990)

ገብረ ሥላሴ ወልደ አረጋይ፣   ታሪክ ዘዳግማዊ  ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ :: አዲስ አበባ፣
አርቲስትክ ማተሚያ ቤት (1959)

ጳውሎስ ኞኞ፣   ዳግማዊ አጤ ምኒልክ:: (1984)

Marcus, Harold, 1975. The Life and Times of Menelik II of Ethiopia 1844-1913.
Oxford: Clarendon Press

Milkias, Pawlos & Metaferia, Getachew (ed.) 2005. The Battle of Adowa: Reflections on Ethiopia’s Historic Victory against European Colonialism. New York: Algora Publishing

Weldegebreil, Biniam, 2004. ‘Memories of the Victory of Adwa: A Focus on Its commemoration (1941-1999)’. A Thesis Presented to the School of Graduate Studies of Addis Ababa University In Partial Fulfillment of the Requirements of Masters of Arts in History.