ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, August 29, 2023

ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል መሆኗ የአፍሪካ ሕብረት ከሀምሳ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተመሰረተ በኋላ የተገኘ የመጀመርያ ከፍተኛው የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

============
ጉዳያችን ምጥን
===========

ብራዚል፣ሩስያ፣ህንድና ደቡብ አፍሪካ በጥምረት የመሰረቱት ብሪክስን ለመቀላቀል ቬኒዝዌላ፣ኢንዶኔዥያና አልጀርያን ጨምሮ 23 ሀገሮች ያመለከቱ ቢሆንም በመጪው ጥር 1፣2024 ዓም እኤአ ጀምሮ ብሪክስ  የተቀበላቸው ሀገሮች ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ ስድስት ሀገሮችን ብቻ እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። እነርሱም ኢትዮጵያ፣ግብፅ፣ኢራን፣የተባበሩት አረብ ኢምሬት፣ሳውዳረብያ እና አርጀንቲናን ተቀብሏል።

ብሪክስ ኢትዮጵያን ከሳሃራ ሀገሮች በታች በብቸኝነት ሲመርጣት ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካን ሳንጨምር ከሁለቱ አንዱ ማለትም ከግብጽ ጋር መርጧታል። ይህ የብሪክስ ኢትዮጵያን የመቀበል ጉዳይ አንዳንድ የምዕራብ ሀገሮችን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሀገሮችም ለምሳሌ ናይጄርያ የመሳሰሉ ሀገሮች የተጽዕኖ አቅም በኢትዮጵያ በበለጠ ደረጃ ጥላ እንዳጠላበት በትልጽ ታይቷል። ጉዳዩ ኢትዮጵያ አሁን አሰላለፏ ከእነ ብራዚል፣ኢራን፣የተባበሩት አረብ ኢምሬትና አርጀንቲና ጋር ያለው ጠንካራ የሚባል ኢኮኖሚ አንጻር ያላትን መጪ የማደግ አቅም፣የፈተናዎች የመቋቋም አቅምም፣ ለዓለም ካበረከተችው ታሪካዊ አስተዋጽኦ፣ወሳኝ እና ስልታዊ አቀማመጥ፣የተፈጥሮ ሃብት፣ከአፍሪካ ሁለተኛ የህዝብ ብዛት እና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ሁሉ ኢትዮጵያ ተመራጭ ሀገር አድርጓታል።

''ሠላሳ ሚልዮን ህዝብን በአራት ሚልዮን ህዝብ የምንቀይር ሞኝ አይደለንም ''

ሠላሳ ሚልዮን ህዝብን በአራት ሚልዮን ህዝብ የምንቀይር ሞኝ አይደለንም ያሉት በ1969 ዓም በኢትዮጵያ የሩስያው አምባሳደር ነበሩ። ለእዚህ ምላሻቸው መነሻው ደግሞ ሩስያ ሱማልያን ስታስታጥቅ ቆይታ ለምን ወደ ኢትዮጵያ ፊቷን በፍጥነት አዙራ የኢትዮጵያ አጋር ሆነች? የሚል ጥያቄ ሲጠየቁ ነበር። በወቅቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዛት 30 ሚልዮን ሲሆን ሱማልያ 4 ሚልዮን ህዝብ ነበራት። ዛሬም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከናይጀርያ ቀጥላ ሁለተኛ የህዝብ ብዛት ያላት ባለ 123 ሚልዮን ህዝብ መሆኗ ብቻ በአፍሪካ ቀንድም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ያላት ተጽዕኖ በቀላሉ አይታይም። አንዳንዶች ብሪክስ ኤርትራ ካላት የጸረ ምዕራቡ አቋም አንጻር ለአባልነት ይጋብዛታል ብለው የሚያስቡ ነበሩ። ነገር ግን ጉዳዩ የ120 ሚልዮን ህዝብን የመምረጥ ስሌት ለብሪክስ አባላት ከባድ ሂሳብ አይደለም። 
 
ብዙ የአፍሪካ ሀገሮች የብሪክስ አባል ለመሆን ቢያስቡም የሩቅ ህልም ሆኖባቸዋል።

የብሪክስ አባል ሆኖ በቀጣይ ከምዕራብም ሆነ ከብሪክስ አባላት ጋር የልማት አጋርነትን ማጎልበት የብዙ አፍሪካ ሀገሮች ምኞት ነው። በእዚህም በኢትዮጵያ በብዙ በአዎንታዊ መልኩ ቀንተዋል። የናይጀርያ አንዳንድ ጋዜጦች መንደሪኑን ከዛፉ ለመቅጠፍ የዘለችው ጦጣ በዝላይ አለመድረሷን ስታውቅ ድሮም መንደሪኑ አይጣፍጥም ብላ ሳትቀምስ እንደሄደችው ዓይነት ነው። ናይጀርያ እንዴት አመልክታ አልገባችም ለሚለው አንዳንድ ምሁራን ምላሽ ለመስጠት ብሪክስ በቅርቡ ውጤቱ የሚታይ አይደለም በረጅም ጊዜ ነው የሚታየው የሚል ጽሑፍ በመጻፍ ምሁራኑን ለማጽናናት ሞክረዋል።

ከሳሃራ በታች ያሉ ሀገሮች ኢትዮጵያ ያላትን ያህል የምጣኔ ሃብት ነጻነት ስለሌላቸው ዘው ብለው ብሪክስ ውስጥ ቢገቡ በሚቀጥለው ቀን ከባንኮች እስከ ግዙፍ የምጣኔ ሃብት ተቋም ድረስ የተያዙት በውጪ ኩባንያዎች በመሆኑ እንደፈለጉ የመወሰን አቅማቸው የሚታሰብ አይደለም። የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በምንም መልኩ አሁንም በውጭ ብድር እና እርዳታ የታገዘ ቢሆንም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች አንጻር በአንጻራዊ መልኩ የተሻለ የተጽዕኖ መቋቋም አቅም ይታይበታል። ከሁሉም ደግሞ ቀድሞ ከነበሩት ሦስት መንግስታትም ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያ አሁንም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች አንጻር አንጻራዊ ነጻነት ያላት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፖሊሲ አውጪው የመወሰን አቅሙ የተሻለ ነው። የብሪክስ መስራቾችም በናይጀርያ እና በኢትዮጵያ መሃል ያለው የመወሰን የነበረ አቅም የገባቸው ይመስላል።

የብሪክስ አባል መሆን ማለት የምዕራብ ግንኙነትን ማራገፍ ማለት አይደለም።

ኢትዮጵያ ካለፉት ታሪኳ ልትማር ይገባል። ብሪክስም ይጠቅማታል፣ከምዕራቡ ጋርም ያላት ግንኙነት ይጠቅማታል።በቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ብዙ ሀገሮች ከአንዱ ጎራ እየተጠቀለሉ ሲገቡ እንደህንድ ያሉ ሀገሮች ደግሞ ገለልተኛ በሚል ድርጅት መስርታ የሁለቱንም የልማት ጥቅም በማግኘት ጊዜውን አልፋዋለች። ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገሮች ለምሳሌ ከህንድ እና ከደቡብ አፍሪካ አንጻርም ሲታይ የባህል እና የታሪክ ጋርዮሿ በራሱ ለልማስ ስኬት የሚያመጣው አዎንታዊ አስተዋጾ ቢኖረውም በሚልዮን የሚቆጠሩ ተወላጆቿ የሚኖሩበት እና የቴክኖሎጂ ግንኙነቷም እየሰፋ የመጣው የምዕራቡ ግንኙነቷን ፈጽሞ ገለል ማድረግ አትችልም። አንዳንድ ምሁራን እና ሚድያዎች ጉዳዩን ከቀኝ ወደ ግራ የመዞር ያህል አድርገው ለማቅረብ የሚሞክሩት ትንሽ ብስለት የጎደለው አካሄድ ትክክል አይደለም። በእርግጥ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ የመግባት ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ ጉዳዩ ከአንድ ጎራ ወደ ሌላ የመሄድ ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል። ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ የማደግ ተስፋዋን በአጋርነት ከቆሙት ጋር ሁሉ አብራ የምትሰራ መሆኗን በተግባር ማሳየት ነገር ግን የበለጠ የሚያግዟት ጋር ተባብራ መስራት አዋጪ መንገዷ ነው።

ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል መሆኗ የአፍሪካ ሕብረት ከሀምሳ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተመሰረተ በኋላ የተገኘ የመጀመርያ ከፍተኛው የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

የኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሆና ከቀዳሚ ስድስት የዓለማችን ሀገሮች ጋር መመረጧ ዛሬም ደጋግመን እኛ እራሳችንን ያላወቅን፣ከሆኑ ዓመታት በኋላ እራሳችንን ዝቅ አድርገን የምናይ እኛ ማን ነን? ማን ነበርን? ዛሬስ የት ላይ ነን? ወደፊስ የምንሄደው? እራሳችንን ሳናውቅ ሌሎች ያወቁን ምናችንን ነው? ብለን ደግመን የመጠየቂያ ጊዜ አሁን ነው። ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት ገደማ በዓለም ላይ ያላት የዲፕሎማሲ አቅም በተለይ ከንጉሱ ከስልጣን መውረድ በኋላ ደብዝዞ ኖሯል። በንጉሱ ዘመን ከተሰራው የኢትዮጵያን ማዕከልነት እና ዓለም አቀፋዊም ሆነ አህጉራዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ካጎሉት ውስጥ ጉልሁ እና አሁንም ድረስ ቀጣይ ፋና የሆነው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አሁን የአፍሪካ ሕብረት በአዲስ አበባ የመመስረቱ ጉዳይ ነበር።

የአፍሪካ ሕብረት ጉዳይ ኢትዮጵያን የግዙፍ አህጉራዊ ዲፕሎማሲ የማሳለጥ አቅሟን አሳድጎታል። ከአፍሪካ ሕብረት በኋላ ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ከመሆኗ እና በምግብ እራሷን ያለመቻሏ ሁሉ ተደማምሮ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ መሪነት አቅም በእጅጉ ከመፈታተን አልፎ ትናንሽ ሀገሮች ከኋላዋ ተነስተው የተሻለ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ተመልካች ሆናለች። ከእዚህ ሁሉ በኋላ ኢትዮጵያ ከእነብራዚል፣የተባበሩት አረብ ኢምሬት እና አርጀንቲና ጋር ተጋፍታ ከሳሃራ በታች ካሉ ሀገሮች በሁሉም መስፈርቷ ያለፈውን እና የመጪ ተስፋዋንም ጭምር በሚገባ መርምረው የብሪክስ መስራች ሀገሮች ሲመርጧት ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ ያላትን የዲፕሎማሲ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግርማ በፍጥነት አሳድጎታል። ይህንን በብዙ ማስረጃዎች ማስረዳት ይቻላል።በእርግጠኝነት ማለት የሚቻለው ግን ኢትዮጵያ በብሪክስ አባል መሆኗ የአፍሪካ ሕብረት ከሀምሳ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተመሰረተ በኋላ የተገኘ የመጀመርያ ከፍተኛው የዲፕሎማሲ ድል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በርካታ ንግግሮች፣ውይይቶች፣አቅምን አግዝፎ የማቅረብ የተለያዩ ስልቶች እና የነበረ እና ዘላቂ ወዳጅነትን ለማጽናት የተደረጉ በርካታ የዲፕሎማሲ እና ሁለንተናዊ ጥረቶች እንደነበሩ ለመረዳት ከባድ አይደለም።

ለማጠቃለል፣ አሁን የእኛ ቦታ ከእነብራዚል፣አርጀንቲና እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ጋር በእኩል ደረጃ መሆኑና ተፈላጊነታችን በእዚህ ደረጃ መናሩ ለእኛ አልታየን ከሆነ ለሌሎች መታየቱ ግልጽ ሆኗል። የእኛ እንደምንፈለገው ደረጃ መሆን ብቻ ሳይሆን እራሳችንን በምን ያህል የቀረንን ሞልተን በቶሎ ከመረጡንም ከተመረጡት ጋርም በፍጥነት አስተካክለን በፍጥነታቸው ልክ ለመሄድ ተዘጋጅተናል? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ነው ቁም ነገሩ። የማደግ ተስፋችን ከፊታችን ቆሞ እኛ ግን በብሄር ፖለቲካ እና በመንደርተኝነት እየተቧደኑ ከሚገፉን እና ሀገር ከሚበትኑ ጋር ከቆምን ዛሬም ኢትዮጵያ የገጠማትን የማደግ ተስፋ መልሰን የምናጨልም ሆነን የመጪውንም ትውልድ ዕድል ዘጊዎች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን። ኢትዮጵያ ከሁሉም አጋሮቿ ጋር አብራ እንድትለማ በውስጧ ጋሬጣ የሆኑ ሃሳቦች የሚዘሩባትን መጋፈጥ ብቸኛው አማራጭ ነው።
==================/////===============

Saturday, August 26, 2023

አዲሱ የአማራ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ ትናንት ዓርብ ነሐሴ 19/2015 ያደረጉት ሙሉ ንግግር።(ቪድዮ)

አቶ አረጋ በመቀሌ የአቶ ሽመልስ ተወካይ ነኝ በማለት ህዝብ ከህዝብ ለማጋጨት የሞከረ ንግግር ያደረጉትን ግለሰብ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ወቅሰዋል፣ አስጠንቅቀዋል። ሙሉውን ንግግር ይመልከቱ። 
የቪድዮ ምንጭ =አሜኮ


Thursday, August 17, 2023

''አንዱ ሲናገር ሌላው አያቋርጥ!'' የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክፍል ውስጥ የሚነገራቸው እና የሚያከብሩትን መመርያ ፓርላማው ገና አልተለማመደውም።

የተከበሩ አቶ ባያብል ሙላቴ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል።

======
ጉዳያችን
======

በእዚህ ሳምንት የተሰበሰበው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ብዙ ኢትዮጵያውያንን የስብሰባ አካሄዱ ደረጃውን የጠበቀ ሆኖ አላገኘውም።የተጀመረ ሃሳብ አዳምጦ ሃሳቡ ላይ ሌላ ሃሳብ ከመስጠት ይልቅ በማኅበራዊ ሚድያ አሉባልታ በሰሙት ወሬ እራሳቸውን እና የወከሉትን ህዝብ ክብር በማይመጥን ደረጃ ንግግሮችን ሲያቋርጡ እና ሃሳቦችም እንዳይሰጡ ሲሞክሩ ትዝብት ላይ ወድቀዋል።

የተወካዮች ምክርቤት አባላት የተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያንን ወክለው ነው። ኢትዮጵያውያንን መወከል ማለት ደግሞ የተከበረ ባሕል፣መከባበርና አስተዋይነት አብሮ ሊታይበት ይገባ ነበር። አንድ የምክር ቤት አባል ወደ ምክርቤቱ ሲገባ የፓርቲዬን ሃሳብ በእጅም በእግርም ብዬ ማሳለፍ ብቻ በሚል ከሃሳብ ሙግት ውስጥ የሚገኝ አዲስ ለሃገር የሚበጅ በጎ ሃሳብ ፈልቅቆ ለማግኘት የሚይስችል ስብዕና ይዞ ካልገባ ከሚቀመጥበት ወንበር ብዙ አይለይም። የሚባለውን ሁሉ እየተቀበለ ለማሳለፍ እንጂ በሃሳብ ለመሞገት ያልተዘጋጀ የፓርላማ አባል እቤቱ ቢቀመጥ እና በሌላ መገናኛ መንገድ ድምጹን መላክም ይችላል።

ህዝብ የፓርላማ አባል የመረጠው እንደራሴ ሆነህ በአፍህ ተናገርልኝ፣ሞግትልኝ በአዕምሮህ እኔን ሆነህ አስበህ ሃሳብ አፍልቅልኝ በማለት እንጂ ሌላው የሚናገረውን አዳምጦ በሚገባ እና አሳማኝ በሆነ ምክንያት ከማቅረብ ይልቅ ህጻናት የማያደርጉትን እየተንጫጫ የሚናገር ሰው እንዲያቋርጥ አይደለም።''አንዱ ሲናገር ሌላው አያቋርጥ!'' የሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች ክፍል ውስጥ የሚነገራቸው እና የሚያከብሩትን መመርያ ፓርላማው ገና ያልለመደው ትንሽ ቆይቶ በሱማሌ የምናየው ዓይነት የፓርላማ መንጫጫት እንዳናይ እየፈራን ነው። ትልቅ ሰው ባትፈሩ፣ልጆች እየተመለከቷችሁ ነው። እነርሱ በትምህርት ቤታቸው አስተማሪ አንዱ ተናግሮ ሳይጨርስ ሌላው አይናገርም! የሚለውን መመርያ ክፍላቸው ውስጥ አይጥሱትም።ከሰሞኑ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የቀድሞው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጸጥታ ጉዳይ አማካሪ ሲናገሩ የነበረው የፓርላማ አባላት የተባለው ትክክልም ይሁን አይሁን በአጽንዖት የማዳመጥ ትዕግስት የማጣት ሁኔታ በእርግጥም ከተራ ስነምግባርም ባለፈ የተባለውን ሰምቶ በምክንያት የመሞገት የአቅም ውሱንነት የታየበት ነው።

አሁን ያለው ፓርላማ ከኢህአዴግ/ህወሃት ዘመን ፓርላማ ጋር ሲነጻጸር በሰው ኃይሉ የትምህርት ዝግጅትም ሆነ በልምድ የተሻለ እና አንጻራዊ መሻል አለበት ብለው የሚያስቡ ነበሩ።በክርክር ሃሳብ ሰልቶ እንዲወጣ በማድረግ ለሃገር የተሻለውን መንገድ እንድትጠቁሙ የተቀመጣችሁ የፓርላማ አባላት ህዝቡ ውስጥ የሚሰማውን የተለያዩ ሃሳቦች፣ሙግቶች፣ድጋፎችም ጭምር ሲንጸባረቁ ማየት የምንፈልግበት ቦታ ፓርላማ ነው። ፓርላማው የአንድ የፓርላማ አባሉን ሃሳብ ወደደውም ጠላውም ለማዳመጥ እና ተናጋሪው ሲጨርስ ሃሳብ የመስጠት ትዕግስት ካጣ ህዝቡማ ከመነጋገር ይልቅ ዱላ ልምዘዝ ቢል ምን ሊፈረድበት ነው?

አሁንም አልረፈደም። ፓርላማው እንዴት መነጋገር፣መሞገት እና በነጻነት ሃሳቡን የማንሸራሸር መብቱን ቁጭ ብሎ መክሮ ያስተካክል። በ21ኛው ክ/ዘመን ተቀምጠን እንድ የህዝብ ተወካይ ሲናገር ለመስማት የሚያስችል ትዕግስት እንዴት እንደሚገኝ መማሩ እጅግ አስፈላጊ ነው።

በእዚህ ሳምንት የአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማጽደቅ በተተራው ስብሰባ ላይ አቶ ገንዱ አንዳርጋቸው ሲናገሩ የፓርላማ አባላት ላሳዩት ትዕግስት ያጣ የማቋረጥ ሙከራ የምክር ቤቱ አባል የተከበሩ አቶ ባያብል ሙላቴ እንዲህ በማለት አምርረው ገልጸውታል።



Tuesday, August 15, 2023

በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ ላይ የድሮን ጥቃት እንደሆነ የታመነው የመንግስት ጥቃት በጦር ወንጀለኝነት የሚያስጠይቅ ነው።በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴም ካስፈለገ መቋቋም ያለበትና በድርጊቱ የሚጠየቁትን በትክክል ለፍርድ ማቅረብ ይገባል።


የቪኦኤ አማርኛ አገልግሎት ሙሉ ዘገባ ከስር ተያይዞ ያገኛሉ።

=======
ጉዳያችን
=======


በምዕራብ ጎጃም ዞን ፍኖተሰላም ከተማ ላይ የድሮን ጥቃት እንደሆነ የታመነው የመንግስት ጥቃት እንደ የፍኖተሰላም ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ለቪኦኤ አማርኛ እንደገለጹት በጥቃቱ እስካሁን 26 መሞታቸው የተረጋገጠና 50 በላይ መቁሰላቸው ተረጋግጧል። ድርጊቱን አስመልክቶ የአሜሪካ ድምጽ ራድዮ የአማርኛው አገልግሎት የዐይን እማኞችን አነጋግሮ ያቀረበው ሪፖርት ደረጃውን የጠበቀ እና በስፍራው የነበረውን ሁኔታ ገለልተኛ በሆነ መልክ የተጠናቀረ ሪፖርት መልክ ያለው ነው።

ይህ ጥቃት እንደየዐይን እማኞች ገልጻ ቀደም ብሎ ድሮን በሰማይ ላይ ከመታየቱና ቃኚ አይሮፕላን ከማለፉ ጋር ተያይዞ እና በአካባቢው ሌላ ምንም ዓይነት የከባድ መሳርያ መጠመድ ባለመኖሩ የዐይን እማኞች የድሮን ጥቃት እንደሆነ እና በፒካፕ መኪናው ዙርያ ያልታጠቁ በርካታ ሰዎች መኖራቸው በግልጽ እየታየ የተፈጸመ ጥቃት መሆኑን በእዚሁ ዘገባ ላይ ነዋሪዎች ለቪኦኤ የአሜሪካ ራድዮ የአማርኛ አገልግሎት ተናግረዋል።

ይህ ማለት ድርጊቱ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቅና ይህ እንዲፈጸም ትዕዛዝ ያስተላለፈው ማን እንደሆነ መንግስት መርምሮ ጉዳዩን ለህዝብ መግለጽ ያለበት ጉዳይ ነው። በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴም ካስፈለገ መቋቋም ያለበትና በድርጊቱ የሚጠየቁትን በትክክል ለፍርድ ማቅረብ ይገባል።

የቪኦኤ አማርኛው አገልግሎት ሙሉ ዘገባ ሰኞ ነሐሴ 8፣2015 ዓም (ኦገስት 14፣2023 ዓም)



Friday, August 11, 2023

ጥያቄው እየመገብን ስናሳድግ የኖርነው ወደፊትም ማሳደግ የምንፈልገው የቱን ነው? የሚለው ነው። መጪው የኢትዮጵያ ዕጣም የሚወሰነው በእዚሁ ነው።



==========
ጉዳያችን ምጥን
==========

አባት እና ልጅ ዛፍ ስር ተቀምጠው ያወራሉ። ከዛፉ ስር ሁለት ድንቢጦች ጥሬ ይለቅማሉ። ከሁለቱ ድንቢጦች ፈንጠር ያለች ሌላ ድንቢጥ (እናት ድንቢጥ) ያገኘችውን አንዴ ለራሷ፣ሌላ ጊዜ ደግሞ ለሁለቱ ድንቢጦች እያመጣች እንዲበሉ ፊታቸው ታስቀምጣለች።ከሁለቱ ድንቢጦች ውስጥ አንዱ ተንኮለኛ ነው። ሦስተኛዋ ድንቢጥ እያመጣች ከሁለቱ ድንቢጦች ፊት የምትጥለውን ተንኮለኛው ድንቢጥ ሌላውን እየኮረኮመ ቀድሞ ይበላል። ሌላኛው አለምብላቱን የምታይ እናት ድንቢጥ ደግሞ ነገሩን እንደዋዛ አይታ ተመልሳ ሌላ ጥሬ ለማምጣት ትሄዳለች። አሁንም ግን መልሳ የምታመጣውን የሚበላው ተንኮለኛው ድንቢጥ ነው።

አባት እና ልጅ የድንቢጦቹን ድርጊት ይመለከታሉ። ልጅ በድንቢጦቹ ድርጊት እያየ ይስቃል።አባት ነገሩን በአንክሮ ይመለከታል። ከቆይታ በኋላ አባት ልጃቸውን፣ሰማህ ልጄ! እነኝህ ሁለት ድንቢጦች በእኛ ውስጥ ያሉ ሃሳቦች ምሳሌ ናቸው።ሁለቱ ድንቢጦች እንደ ባላንጣ ለሚበሉት እንደሚሻሙ ሁሉ በውስጣችንም ያለው ሃሳብ እንዲሁ እርስ በርሱ ይዋጋል። የእዚህ የውስጣችን ሀሳብ የመጣላት እና አንዱ አሸንፎ የመውጣቱ ፋይዳ የወደፊት እኛነታችንን ብቻ ሳይሆን በዙርያችን ያሉትንም ዕጣ ሁሉ ይወስናል።ጥሬውን የሚነጥቀው በውስጣችን ያለው የክፉ፣የጎሰኝነት፣ሌላውን የማጥላላት ምሳሌ ነው።የዋሁ እና ገሩ ድንቢጥ ደግሞ የመልካም፣ለሌላው የማሰብ፣ከጎጥ ይልቅ የሁላችን ኢትዮጵያ የሚለው ሀሳብ ምሳሌ ነው። በማለት አባት የድንቢጦቹን ምሳሌነት አፍታተው ነግረው የልጃቸውን ትኩረት ሳቡት። ልጅ ግን ጠየቀ፣ አባዬ ግን ከሁለቱ ሃሳቦች ማን ያሸንፋል? በማለት ጠየቀ።አባት መለሱ የበለጠ እየመገብን ያሳደግነው ያሸንፋል።የዘረኝነት፣የጎጥ እና የክፉውን ሀሳብ እየመገብን ካፋፋነው እርሷ ያሸንፋል።ኢትዮጵያ ለሁሉም፣ጎጠኝነት ይጥፋ፣እርስ በርስ አንጠፋፋ የሚለውን ሀሳብ እየመገብን ካሳደግነው ደግሞ እርሱ ያሸንፋል በማለት መለሱለት።

በኢትዮጵያ በህወሃት/ኢህአዴግ እና ኦነግ የተተከለው የጎሳ ፖለቲካ ትውልድ በክሎ ዛሬ ላይ በአማራ ብሔርተኝነት አገንግኖ ወጥቶ የኦሮሞንም ሆነ የትግራይን ብሄርተኝነት ወይንም የጎሳ ፖለቲካ የሚገዳደርበት ደረጃ ደርሷል።እዚህ ላይ ምንም ያህል ቢሽሞነሞን፣ ምንም ያህል የሌላው የበደል መጠን ጥግ ማለፍ ያስነሳው ቢሆን፣ምንም ያህል መድረሻው ኢትዮጵያዊነት ነው ቢባል፣ የአማራ ክልል የተነሳው እንቅስቃሴ ምድቡ ከብሄርተኝነት እንቅስቃሴ የሚመደብ ነው።ይህንን የሚያራምዱትም የሚክዱት አይደለም። እዚህ ላይ የብዙዎቻችን ለኢትዮጵያ ያለን ምኞትና ሕልም ግን ከየትም ጥግ፣ምንም ዓይነት መልኩን ቀይሮ ይምጣ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ኢትዮጵያን የሚያፈርስ አደገኛ የመርዝ ብልቃጥ መሆኑን አይቀይረውም።

ሩቅ የማያይ የዛሬው አይገባውም።ዛሬ የሚሆነውን እያየ ይህ ኢትዮጵያን ወዴት ነው የሚወስዳት ብሎ ማማተር ያልቻለ ከአፍንጫ እስከ ከንፈር ድረስ ብቻ የማሰብ የተሰናከለ አስተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያን ስናስባት የት እንድትደርስ የምናስብላትን መድረሻ እያሰብን ካልሄድን የፊት፣የፊትን እያዩ የመሄድ አደገኛ መንገድ የትኛውንም ኢትዮጵያዊ ሆነ ኢትዮጵያን ፈጽሞ አይጠቅምም።የኢትዮጵያ መጪ ዘመን የሚወሰነው እየመገብን ባሳደግነው ድንቢጥ ይወሰናል።

አሁንም ጥያቄው እየመገብን ስናሳድግ የኖርነው ወደፊትም ማሳደግ የምንፈልገው የቱን ነው? የሚለው ነው። መጪው የኢትዮጵያ ዕጣም የሚወሰነው በእዚሁ ነው።ለችግር መፍትሄ ተመሳሳይ ችግር በመድገም አይፈታም።በተቃራኒው በመሄድ ነው ማሸነፍ የሚቻለው። በሌላው በኩል ያለ ጎጠኝነት ጎዳን ተብሎ በተመሳሳይ መንገድ በመሄድ ለጊዜው ስሜትን ያረካ፣ንዴትን ያበርድ ካልሆነ በቀር ዘለቄታዊ መፍትሄ ለሀገር አይሰጥም።ከጎሰኝነት በተቃራኒው በፍጹም ኢትዮጵያዊነት መንገድ በመሄድ እና ስለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እና ኢትዮጵያ ከልብ በመነጨ የፍቅር ስሜት በመሄድ እና ለእዚህም እስከ የህይወት መስዋዕትነት ድረስ በመክፈል ሀገር ይቆማል።ስለሆነም ስንመግብ የኖርነውን አውቀን፣ወደፊት ለመመገብ የምናስበውን ከአሁኑ በምናቅደው ልክ የነገዋ ኢትዮጵያ ትታወቃለች። መሬት ላይ ያለው ትልቁ የአብዛኛው ህዝብ እውነት ዛሬም የጋራ የሆነች እና ከጎሰኝነት የተጣላች ከፍቅር የታረቀች፣ሁሉንም ወገኔ የምትል ኢትዮጵያን ማየት ነው።
================////===========

Sunday, August 6, 2023

መሬት ላይ ያለው እውነታ፣ መከላከያ ፋኖ ላይ መተኮስ አይፈልግም።ፋኖም መከላከያ ላይ መተኮስ አይፈልግም።መንግስት ጉዳዩን በሰላም በመፍታት ኢትዮጵያን ከእርስበርስ ጦርነት የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።

=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

ጦርነት ውስጣዊ ቁጣ እና ፍትሃዊ የሆነ የመዋጋት ስሜት ይፈልጋል። ከእዚህ በፊትም ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአማራ ክልል የተነሳው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ድንገት ደራሽ አይደለም።የእዚህ ዓይነት የትጥቅ ትግል መነሳት በማናቸውም ጊዜ ሊነሳ እንደሚችል ጉዳያችን ላይ የዛሬ 5 ዓመት ከእነምክንያቱ ተጽፎ ነበር። ሊንኩን እዚህ ላይ ተጭነው መመልከት ይችላሉ።

አሁን መሬት ላይ ያለው እውነታ

አሁን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ የሚያሳየው መከላከይ ፋኖ ላይ መተኮስ አይፈልግም። ፋኖም መከላከያ ላይ መተኮስ አይፈልግም። ለእዚህ ደግሞ ምክንያቱ ግልጽ ነው። መከላከያ የተዋቀረው በኢትዮጵያዊ ስሜት ነው። ፋኖንም በሀገር አንድነት ትግል ላይ ከህወሃት ጋር ሲያውቀው ኢትዮጵያን ሲያከብር እንጂ የማፍረስ ስሜት አላየበትም። ስለሆነም ከውስጥ የወጣ የጥላቻ ስሜት አብቅሎ አንዱ አንዱ ላይ ለመተኮስ ፈጽሞ የስሜት ጥላቻው በእዚያ ደረጃ የናረ ሁኔታ የለም።ይህ እንደ ሀገር ሲታይ ይህንን ጦርነት የሰው ህይወት ሳይጠፋ፣ንብረት ሳይወድም ለማስቆም የሚቻልበት እድል ትልቅ ነው ማለት ነው።

መንግስት ጉዳዩን በሰላም በመፍታት ኢትዮጵያን ከእርስበርስ ጦርነት የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት 

ይህ የእርስበርስ ጦርነት ነው። ውጤቱ ደግሞ በሁሉም ወገን ያለው የኢትዮጵያውያን ሞት የሚያመራው ኢትዮጵያን ይዞ ወደ ሌላ የመከራ ማጥ የሚያመራ ነው። እስካሁን ከደረሰው ጥፋት ሌላ ጥፋት ሳይከተል፣እዚህ ላይ ለማቆም በመጀመርያ ማናቸውንም ግጭት አስቁሞ ወደ መነጋገር መምጣት ያስፈልጋል። ከእዚህ ውጪ መከላከያ በአማራ ክልል ከተሞችን በመቆጣጠሩ ብቻ ድል ብሎ ሊቆጥር አይችልም።አሁንም መከላከያ የኢትዮጵያ ሃብት ነው።መከላከያ ኢትዮጵያን በዘመናዊ ጦርነት ለመከላከል እንጂ ከራሱ ወገን ታጣቂ ጋር ጉልበቱን አድክሞ ሀገርን ለውጭ ወረራ ማጋለጥ ሀላፊነት የሚሰማው ውሳኔ አይደለም። 

ይህ በእንዲህ እያለ በደብረማርቆስ ፖሊስ ኮሌጅ ውጪ እስካሁን ይህ ነው የሚባል የዝርፍያ ሁኔታ በሰሞኑ የአማራ ክልል እየተሰማ አይደለም። ለእዚህ ደግሞ የመረጃ እጥረት ካልሆነ በቀር እየተሰማ ያለው የታጣቂው ኃይል በተቻለ መጠን ለመንግስት እና የግለሰብ ንብረት ጥበቃ ለማድረግ እየሞከረ መሆኑ እንደሆነ እየተሰማ ነው። የደብረማርቆስ ፖሊስ ኮሌጅ ዘረፋ በተመለከተ የአንከር ሚድያ ላይ ቀርቦ የተናገረ አንድ ታጣቂ እንደገለጸው በደብረማርቆስ ፖሊስ ኮሌጅ የደረሰውን እንደሰማ እና ከዝግጅት ማነስ አንዳንድ ሌቦች አይኖሩም ማለት አይደለም በማለት ገልጾታል። ዝርፍያን እና ጸጥታ በተመለከተ የፋኖ ታጣቂዎች በፈለጉት መጠን ጸጥታ ለመጠበቅ ቢሞክሩም በቀጣይ ግን ፈተናዎች አይገጥሙም ማለት አይቻልም። እስካሁን ታጣቂዎች በገቡባቸው አካባቢዎች አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት የተቋረጡባቸው አካባቢዎች ቢኖርም የቀጥታ ስልክ ግን በአንዳንድ ቦታዎች ቢያስቸግሩም፣የእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ዛሬ እንዳረጋገጠውም በባህርዳር የቀጥታ ስልክ፣ውሃ እና መብራት አሁንም አገልግሎት አለ።

አሁን ላለው ወቅታዊ ሁኔታ ብዙ ጭቅጭቅ አያስፈልግም።የፋኖ ታጣቂ እጃቸው የገቡ የመከላከያ አባላት ላይ የደረሰውን ሞት አይደለም፣ መቁሰል እያሳዘናቸው እንደሆነ ዛሬ ዘሐበሻ በቪድዮ አስደግፎ ባቀረበው የአንድ የፋኖ አባል ቃለመጠይቅ አሳይቷል። በሌላ በኩል የአንከር ሚድያ ያነጋገረው የመከላከያ አባልም በተመሳሳይ የፋኖ ታጣቂዎች ለኢትዮጵያ ሲደሙ እንደሚያውቃቸው ገልጾ ፈጽሞ የመውጋት ፍላጎት እንደሌለው ገልጿል። አሁን ጥያቄው አንድ ነው።ተጨማሪ የሰው ህይወት ሳይጠፋ፣መከላከያንም ከህዝብ ጋር ደም ሳይቃባ እና ኢትዮጵያ ወደ የባሰ ግጭት ሳትገፋ፣ መንግስት ጉዳዩን በሰላም በመፍታት ኢትዮጵያን ከእርስበርስ ጦርነት የማዳን ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት።ጉዳዩን በኃይል ለመፍታት መሞከር በምንም መልኩ ኢትዮጵያን አይጠቅማትም።ከህወሓት እና ሸኔ ጋር ተቀምጦ የተነጋገረ መንግስት በአማራ ክልል ከተነሳው ታጣቂና ፋኖ ጋር ለመወያየት የሚያግደው ጉዳይ ምንድን ነው? ከእዚህ ጽሑፍ በፊት እና የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማወጁ በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሃላፊነት በተሰማው መንገድ በአማራ ክልል ለተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ መተግበር የሚገቧቸው ሦስት ተግባራት በሚሉት ሃሳብ ለማቅረብ ተሞክሯል።ይህንን ሊንክ በመጫን ማንበብ ይቻላል።

ለማጠቃለል አሁን ያለው ሁኔታ የሆነ ተአምር ይዞ የሚመጣ መስሎት በስሜት ውስጥ የገባውም ሆነ ብቻ እነእገሌ ይወገዱ እንጂ የሚሉ ሁሉም ጥቅሉን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ከእዚህ በፊት ሃገሪቱ ያለፈችበትን ተመሳሳይ የስሜታዊነት መንገድ ያልተገነዘቡ ኢትዮጵያ በምን ያህል ደረጃ በአካባቢዋ እና በውስጧ ሊያጠፏት የተጠመዱ የፈንጅ ዓይነቶች ካለማወቅ የሚመነጭ ነው።የውስጥ ቁርሾ ይበርዳል።በውስጥ ቁርሾ መከላከያን ማድከም ግን የማይሽር ጠባሳ ለሀገር ጥሎ ይሄዳል። ስለሆነም መከላከያን ማዳን እና አለማዳከም ከፋኖም ሆነ ከመንግስት የሚጠበቅ እኩል ሀገራዊ እና ታሪካዊ ሃላፊነት ነው። ሁለቱም ይህንን ታሪካዊ ሃላፊነት ሊወጡ የሚችሉበት መንገድ ደግሞ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ነው።

==================///============






Wednesday, August 2, 2023

በአማራ ክልል የተነሳው አለመረጋጋትን በፍትሐዊ እና ርቱዕ በሆነ መንገድ ለመፍታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ማድረግ የሚገባቸው ሦስት ተግባራት።




=========
ጉዳያችን
=========

ያለመተማመኑ መናር 

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ፣ደቡብ ጎንደር፣ጎጃምና ሰሜን ወሎ የፋኖ ታጣቂ ኃይል ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ግጭቶች መፈጠራቸውና አንዳንድ ቦታዎች ላይ ደግሞ ለሰዓታት የተራዘመ የተኩስ ልውውጥ መደረጉ ተሰምቷል። ይህ ድንገት ደራሽ ጉዳይ አይደለም።የእዚህ ዓይነት ህዝባዊ እንቅስቃሴ በድንገት ሊፈጠር እንደሚችል በተለያየ ጊዜ በኦሮምያ ክልል የተፈጸሙት ዘርን መሰረት ያደረጉ ማፈናቀሎች፣የክልሉ ባለስልጣናት ከኦነግ ሸኔ ጋር እየተናበቡ የፈጸሙት ህገ ወጥ ድርጊት ብቻ ሳይሆን ትዕቢት የተሞሉ ንግግሮች ሁሉ ሲሰሙ አንድ ቀን የህዝብ ቁጣ እንደሚያስገነፍል የሚጠበቅ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት በተለየ መልኩ በኦሮምያ ክልል በሚሆነው እና በሌሎች ተለዋዋጭ ጉዳዮች ሳብያ በተለየ መልኩ የአማራ ክልል ነዋሪ የነበረ እምነቱ ተሸርሽሯል። ይህ መሸርሸር ደግሞ ከህወሓት ጋር በፕሪቶርያ ከተደረገው ስምምነት ተከትሎ በርካታ ጉዳዮች ብዥታ ፈጥረዋል። በእዚህ ያለመተማመን እና የጥርጣሬ ስሜት ውስጥ የክልል ልዩ ኃይሎች እና ሌሎች ኢመደበኛ ታጣቂዎች ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ ሲመጣ ያለመተማመኑን ደረጃ በእጅጉ አናረው።

ይህ ዛሬ የተፈጠረው ሊፈጠር እንደሚችል የዛሬ አምስት ዓመት ግንቦት 1/2010 ዓም ጉዳያችን ላይ ''ሰሚ ያጣው የአማራ ዘርን የማፅዳት እኩይ ተግባር ፍትሃዊ የተባለ ጦርነት ሊያስነሳ ይችላል።'' በሚል ርዕስ የወጣውን ጽሑፍ መመልከት ለጊዜው በቂ ነው።አሁን እየሆነ ያለው ባጭሩ ድንገት ደራሽ አይደለም።


 ህዝባዊ እንቅስቃሴው ብሔርተኛ እንቅስቃሴ ነው ወይንስ ኢትዮጵያን የሚል እንቅስቃሴ ነው?

አንዳንዶች የአማራ ክልል ምንም ዓይነት የብሔር እንቅስቃሴ መነሻውን ቢያደርግም፣''አማራ ሁሌ ለኢትዮጵያ የቆመ ነው፣ኢትዮጵያን አይከዳም '' የሚል የተለመደ አነጋገር በተለይ ከአማራ ክልል ተወላጆችም ሆነ ከደቡብ ኢትዮጵያውያን የሚሰሙ አነጋገሮች ናቸው። ሆኖም የፖለቲካ እንቅስቃሴ በራሱ በእንቅስቃሴው ባሕሪ፣ አነሳስ እና የወደፊት አቅጣጫ እንጂ አንዱ ክልል የተለየ ቅዱስ እና ምንም ዓይነት የአክራሪ ብሔርተኞች መነሃርያ የማይሆን ሌላው ደግሞ የተለከፈ ብቻ የሚለው አካሄድ አያስኬድም። የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ከመነሳቱ በፊት በጀርመን የናዚ ዓይነት የከፋ መንግስት ይነሳል ብሎ ቢያንስ በእዚያ ደረጃ የጠበቀ የጀርመን ህዝብም ሆነ የውጭ መንግስታት እንዳልነበሩ ታሪክን በትንሹ በማገላበጥ መረዳት ይቻላል።  ይህ ማለት የአማራ ክልል እንቅስቃሴ ፍጹም ብሔርተኛ እና በአደገኛ ኃይሎች እጅ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ገባ ለማለት አሁን በህዝባዊ እንቅስቃሴ ደረጃ ከመሆን አልፎ አመራሩ ነጥሮ ስላልወጣ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ለማለት የማይቻል ቢሆንም እንቅስቃሴው ግን በምንም የመጠለፉ አደጋ ግን መቼም ሆነ መቼ የለም ለማለት አይቻልም። ለእዚህ አብነት የሚሆነው እና ማነጻጸርያ የሚሆነው በሰኔ 3፣2010 ዓም ''የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የተሰኘ አዲስ ንቅናቄ ባህርዳር ላይ ተመስርቷል።የንቅናቄው እድሎች እና ፈተናዎች ምንድናቸው?'' በሚል የቀረበው ጽሑፍ ስር ድርጅቱ ሊገጥሙት ከሚችሉት ዕድሎችና ፈተናዎች ውስጥ ፈተናዎች በሚለው ስር የሚከተሉት ተዘርዝረው ነበር።እነርሱም ፡ 
  • የከረረ ብሔርተኝነት ያላቸው ወደ አመራሩ ከመጡ ከኢትዮጵያዊነት ጋር አጣጥሞ ለመሄድ የመቸገር ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፣
  • በህወሓት ሰርገው እንዲገቡ የሚደረጉ ግለሰቦች የሚፈጥሩት አሉታዊ ስዕል በንቅናቄው ላይ የሚሰጠው መልካም ያልሆነ ስዕል እና ከሌሎች ብሔሮች ጋር ለማጋጨት የሚደረጉ ሙከራዎች፣
  • እራሱን በቶሎ ወደ ኢትዮጵያዊ ንቅናቄ ካልቀየረ በከረረ ብሔርተኝነት ስሜት የተመሰጡ አባላቱን ወደ ሃገራዊ አጀንዳ ባለቤትነት ለመቀየር የመቸገር ሁኔታ መፈጠር።የእዚህ አይነቱ ችግር አሁን ህወሓት እራሱ ገጥሞት የሚገኘው ችግር ነው።መግብያ ሲዘጋጅ መውጫው አብሮ መታየት አለበት።
  • በተሰሩ ግፎች እና ጥፋቶች ላይ ከሚገባው በላይ በመዘከር የይቅርታ እና የአንድነት መንገዶች እንዲከፈቱ ማድረግ ካልቻለ አማራን ብቻ ሳይሆን በብሔራዊ ደረጃ ወደ አደገኛ መንገድ የመሄድ አዝማምያ እንዳይኖር ጥንቃቄ ያስፈልጋል።የሚሉ ነበሩ።
አሁን ያለውን እንቅስቃሴ ከስሜት በተለየ በሚገባ ወዴት ሊሄድ ይችላል? ኢትዮጵያዊነት በተመለከተ ኢህአዴግ ውላጅ የሆነው ትውልድ ''አማራ ፊርስት '' የሚል ነው ወይንስ ''ኢትዮጵያ ፈርስት '' የሚል ነው? የሚለው አሁንም መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዳዩን በኃይል ከመፍታት ይልቅ ማድረግ የሚገባቸው ሦስት ተግባራት።

በእዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ ለማንሳት እንደተሞከረው በዘመነ ኢህአዴግም ሆነ ባለፉት አምስት ዓመታት በጀዋር መሐመድ ''ስልጣን ይዘናል '' ከሚለው ጽሑፍ እስከ አቶ ሽመልስ ''ሰበርናቸው'' የመስቀል አደባባይ ንግግር፣ከመቶ ሺዎች የወለጋ እና የሸገር መፈናቀል እስከ ፍትሕ ያጡ የደቡብ እና ሱማልያ ክልል ነዋሪዎች ጭምር የብሶቱ ጣርያ ከመጠን ያለፈ ነው። ይህንን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም፣መከላከያም፣ብልጽግናም ካለምንም ማጉረምረ ሊውጡት የሚገባ እውነት ነው። ለእዚህ እውነት እዚህ ላይ መዘርዘር ጊዜ ማጥፋት ነው። አሁን ያለውን ወቅታዊ ጉዳይ ለመተንተን የሚነሳ የመንግስት አካል መነሳት ያለበት ይህንን እውነት ከመቀበል ካልሆነ ቀጣይ የመፍትሄ ሂደቱ ሁሉ የተሳሳተ እና አለባብሶ የመሔድ ከንቱ ድካም ይሆናል። በመሆኑም ይህንን እውነት ጠቅላይ ሚንስትሩም አምነው እና ተቀብለው ወደ መፍትሔ መሄድ ተገቢ ነው። 

ወደ ሦስቱ የመፍትሄ መንገዶች ስንመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚከተሉትን ሦስት ተግባራት በፍጥነት መፈጸም አለባቸው። እነርሱም 

1) የመወቃቀሻ እና እውነቱን የማንጠርያ መድረክ ከአማራ ክልል እጅግ የተከበሩ ሽማግሌዎች፣የሃይማኖት አባቶች፣መከላከያ የኦሮምያ ክልል አመራሮች እና የፋኖ አመራሮች ጋር በፍጥነት መፍጠር።
  • መድረኩ ከውይይት በኋላ ለህዝብ መቅረብ ያለበት ለበለጠ ግጭት የማይዳርገው ክፍል ተለይቶ ነገር ግን ዋና ሃሳቡን ያልጣለ የመወቃቀሻ መድረኩ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ራድዮ በቀጥታ መተላለፍ አለበት።
  • በመወቃቀሻ መድረኩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ከአማራ ክልል ጋር በተያያዘ እና በኦሮምያ ክልል ለሆነው ሁሉ ያሳዩት ለዘብተኝነት ላይ በግልጽ ይጠየቁ፣እርሳቸውም ከእዚህ በፊት ያልሰማናቸውን ጉዳዮች ጨምረው ለምላሽ ይዘጋጁ።ውይይቱ ስሜት የሚነካ እና ፍጹም ግልጽነት የታየበት መሆን አለበት።
  • ሀገር በሆነ ባልሆነው ወደ ግጭት እየገባች የትውልድ ሞት ከሚከተል ለእዚህ ዓይነት መወቃቀስ መዘጋጀት እና ስህተትን ውጦ ለነገ ስህተትን አስተካክሎና መተማመንን በምንም ወጪ ቢሆን ከፍሎ ሀገርን ማስቀጠል ግዴታ ነው። 
  • ስለሆነም ይህ የመወቃቀሻ መድረክ እጅግ በፈጠነ መንገድ ማድረግ ብዙ ችግሮችን ያስወግዳል።
2) በኦሮምያም ሆነ በአማራ ክልል ያሉ አመራሮች በሙሉ እስከ መካከለኛ ድረስ ያሉትን ከባለሙያዎች ውጭ በሙሉ ከስልጣን ማንሳት እና አዲስ ከጎሳ ፖለቲካ አክራሪ የተሻለ አቋም ላይ ያሉትን መተካት።
  • አሁን በሁለቱም ክልል ያሉት አመራሮች በሴራ ሹክቻ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሙስና የተነከሩበት ደረጃ ማንም ወንጀለኛ የሚነዳቸው ስለሆኑ ያከረሩ የጸብና የግጭት መነሻ ናቸው።
  • በተለይ በኦሮምያ ክልል ያለው ከጎሳ ፖለቲካ መበስበስ አልፎ ፈጽሞ ለማንኛውም ኃይል ተገዢ ብቻ ሳይሆን የመሰረታዊ የኢትዮጵያ ዕይታቸው ከጥላቻ ባለፈ ወደ ፍጹም ፋሺሽታዊ መንገድ እየሄደ በመሆኑ 
  • በቀጣይ ኢትዮጵያ እንድትሄድበት ከሚፈለገው የአንድነት መንገድ አንጻር በሁለቱም ክልሎች ያሉ አመራሮች በብሄር ፖለቲካ የተደናበሩ ስለሆነ እና  
  • ወቅታዊ ችግሩን በአዲስ አሰራር በመቀየር ቁርጠኝነትን የማሳያ አንዱ መንገድ ስለሆነ።
3) የጎሳ ፖለቲካ የመጪዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫ እንዳልሆነ እና እስከዛሬ የነበረው በህወሓትና ኦነግ የተተረኩት የውሸት ትርክቶች ጉዳይ ምዕራፍ ለመዝጋት ግልጽ፣አሳማኝና ተግባራዊ ስራ መንግስት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጽ ብቻ ሳይሆን በቁርጠኝነት የማሳያቸው ጊዜ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን መጥቷል።
  • እዚህ ላይ ህገመንግስቱ ላይ ያሉት መሰረታዊ ችግሮች ማስተካካል። ሀገር በጦርነት ከሚታመስ ህገመንግስትን በማረም ማስተካከል ተገቢ ነው።
  • በአማራ ላይ፣በኦሮሞ ላይ እና ሌሎችም ላይ ያሉ ጸብ ጫሪ ትርክቶች በወንጀለኝነት የሚያስጠይቁ ማድረግ፣
  • የአኖሌን ሃውልት ከማፍረስ ማናቸውም የጎሳ ቀስቃሽ ንግግር ያደረገ እና የጻፈ በፍጥነት በህግ መቅጣጥ
  • ዲጂታል ጎሳ አልባ መታወቂያ ከታቀደው ጊዜ በፈጠነ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ
  • የክልሎች አከላለል ጎሳን መሰረት ያደረገ እንዳይሆን በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ። እዚህ ላይ በፍጥነት የሚለው ቃል የምጠቀመው ዘመን በማርዘም ችግር ከማባባስ ይልቅ በተግባራዊነቱ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ አግኝቶ ሀገር ማቆም ከሁሉ የተሻለው አማራጭ መሆኑ ቢያንስ ያለፉት አምስት ዓመታት አስተማሪ ስለሆነ ነው።
ለማጠቃለል 

የአማራ ክልል ህዝብ በግልጽ መወቃቀስ የነበሩትን ችግሮች በማስተካከል ለጋራ ሕግ አብሮ እንዲቆም ማድረግ ይቻላል። ለእዚህ አንዱ ማስረጃ ክልሉ ካለው ማኅበራዊ ባሕል አንጻር ህግ የማክበር ባሕሉ እጅግ የጠነከረ ነው።እስኪያምንህ ይዘገያል።ካመነህ አብሮ ይዘልቃል።አይቶ አይቶ ካላመነ በቃኝ ብሎ ይነሳል። ያላየበትን መንገድ በቅንነት እና በእንባ ጭምር ስታስረዳው መልሶ ይሰማሃል። አንዴ ከሰማህ በኋላ መልሰህ ስትዋሽ ካገኘህ ግን  ነገሩ አበቃ ማለት ነው። አሁን ያለበት ደረጃ መንግስት ስህተቱን አምኖ ለማስተካከል እድል እንዲሰጠው የማሳመን እና ለገባው ቃል ተግባራዊ እንዲያደርግ እድል ያለበት ጊዜ ነው። አሁን የተፈጠረው መከራ ብቻ አይደለም።ለተሰራው ስህተት ማረምያ፣የጎሳ ኃይሎችን ማስታገሻ አድርጎ ወደ መልካም ሀገራዊ ዕድል መቀየርም ይቻላል።

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ሀገር ገልብጠን፣ ነፍጥ ከመነቅነቅና መከላከያን ከመበተን መለስ ያለ ንግግር እና ስህተትን የማረም ሂደት አያስፈልግም የሚሉ እነ''በለው'' ባዮች አይነሱም ማለት አይደለም። ሆኖም ህዝብ በግልጽ ይመንበት፣ከደም መፋሰስ ይልቅ ስህተትን በማረምና ሀገራዊ አቅጣጫን ከማስተካከል መለስ ያሉ ካልበተን አናርፍም ለሚሉ እራሱ ህዝብ ምላሽ ይሰጣል።ከእዚህ በተረፈ ግን በአማራ ክልል የተከሰተው የጸጥታ ችግር በወታደር ኃይል ለመፍታት መሞከር አይቻልም።ጦርነት ውስጣዊ ስሜት እና ለመሞት እርግጠኛ የሆነ የስሜት ደረጃ ይፈልጋል።መከላከያ ደግሞ ከአማራ ክልል ጋር የሚያደርገው ጦርነት ፈጽሞ ምክንያታዊ አለመሆኑን ይረዳል። በመሆኑም በሙሉ ስነልቦና አይዋጋም። ይህ ማለት ግን መከላክያ ላይ የሚሆነውን ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ይቀበላል ማለት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ የመንግስት ኢፍትሃዊ አካሄድ ለችግሩ መፈጠር ምክንያት መሆኑን ስለሚያውቅ መንግስት በይቅርታ እና በማስተካከል ሥራ እንዲጀምር፣በፋኖ ታጣቂ በኩልም በመከላከያ ላይ ምንም ዓይነት ግጭት እንዳይፈጠር በሰላማዊ መንገድ ችግሮችን አንጥሮ በማቅረብ ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ በቅንነት መነሳት ይገባል።ከኢትዮጵያ መታወክ አይደለም ዜጎቿ ጠላቷቿም በሚገባ ቢያስቡት አይጠቀሙም።

==================//////===========







Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሃራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)

Beynouna Village - Ethiopia (Video) ባለፈው ሳምንት የተመረቀው መተሐራ እምብርት ላይ የተገነባው አስደናቄው የበይኑና ሪዞርት መንደር (ቪድዮ)