ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, September 28, 2012

የ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ድምፅ እና ምስል በ እየቤታችን ሳሎን

-ከ ክርስቶስ ልደት በፊት እግዚአብሄርን በማምለክ ከ እስራኤል ጋር የምትጠቀስ ሃገር ነች- ሃገራችን ኢትዮዽያ፤
-መጽሃፍ ቅዱስ ሲገልጡ ገና  በገጽ ሁለት ምዕራፍ ሁለት ላይ (ኦሪት ዘፍ ምዕ ፪) ገና አዳም በገነት በኖረበት ዘመን ከ አለም ሁሉ በፊት የመጀመርያ የ ሃገር ስም የሚጠራው ኢትዮዽያን ነው፤
-ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ስራውን ፈጽሞ ባረገ  (በ 33 ዓም)  በ አመቱ በ  34 ዓም  ክርስትናን የተቀበለች (ሐዋርያት ሥራ 8) የ አለም ቀደምት ሃገር ነች አሁንም -ኢትዮዽያ፤
-ከ ህዝብ ብዛትዋ ከ ግማሽ በላይ የሚሆነው የ ኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ነው፤
-ለ ሺህ አመታት ያህል ያበረከተችውን  አገልግሎት ባገናዘበ መልክ ምዕመኗን የምትደርስበት የመገናኛ ብዙሃን የላትም።
አሁን በጎ ጅምር ሊታይ ይመስላል።በ ኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን የ ቴሌቭዥን መርሃግብር እንደሚጀምር አስታውቋል። ርግጥ ነው በ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ደረጃ በ ማህበራት ደረጃ አንዳንድ መርሃግብሮችን በ ባህር ማዶ በሚገኙ የ ቴሌቭዥን ጣቢያዎች የማሳየት ስራዎች አልፎ አልፎ ታይተዋል።እንደዚህ በ ቤተክርስትያኒቱ መዋቅር ስር ባለ መልክ ተከታታይ የቴሌቭዥን መርሃግብር ሲቀረፅ ግን አዲስ ይመስለኛል።ስለ አዲሱ መርሃግብር መጀመር ከ ማህበረ ቅዱሳን ድረ-ገፅ ላይ የተገኘው ዜና እንዲህ ይነበባል:-



''በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ዘወትር በየሳምንቱ እሑድ ጧት ከ3፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት የሚቆይ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ሰርቪስ ቴሌቪዠን (EBS TV) ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለጠ፡፡በማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ፥ የሬድዮና ቴሌቪዠን ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ ለመካነ ድራችን በሰጡት መግለጫ፡- ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ላለፉት ሃያ ዓመታት በልዩ ልዩ የኅትመት ውጤቶች እንዲሁም በመካነ ድር (website) እና በሬድዮ አማካኝነት በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ በሳምንት አንድ ጊዜ የ30 ደቂቃ መርሐ ግብር ለመጀመር ትናንት መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም ከኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን የሥራ ሓላፊዎች ጋር ለአንድ ዓመት የሚቆይ ስምምነት ማኅበሩ መፈራረሙን ገልጸዋል፡፡'' 1 ይላል ።



ይህ በሃገር ቤትም በ ውጭም ለሚኖረው ለቀደመው ትውልድ፣አሁን ላለው ትውልድ እና ለመጪዎቹ ትውልዶች እጅግ ጠቃሚ ተግባር ነው።
ለቀደመው ትውልድ:-ስለ ቤተክርስቲያን የነበረውን አስተሳሰብ፣ይረዳበት የነበረውእይታ በበለጠ መንገድ  በስጋዊም መንፈሳውም ህይወቱ  የሚረዳበት ብሎም ለተቀረው ዓለም አንገቱን ቀና አድርጎ የሚያስረዳበት እንደሚሆን እገምታለሁ።
 
ለ አዲሱ ትውልድ :-የ እዚህ አይነት የ ቴሌቭዥን መርሃግብር  አዲሱን  ትውልድ ከዘመኑ ሉላዊነት (globalaization) ፈተናዎች አንዱ ከሆነው የ እራስን ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ሀብት የማስጣልና የ ባእዳንን አምላኪ  የመሆን አባዜ ለመከላከል፣ ሃገሩን እና ቤተክርስቲያኑን በሚገባ እንዲረዳ፣ ለሕዝቡ ችግሮች ሁል ጊዜ ከ ባህር ማዶ መፍትሄ ከመፈለግ ማንነቱን እንዲያውቅ ፣ በስጋውዊም ሆነ በ መንፈሳውው ሀብት  (በ ሁለት ሰይፍ የተሳለ) የመሆን እድሉን ከመክፈቱ በላይ ሰላማዊ፣ ስነ-ምግባር  የተላበሰ፣ ከ ችኩል ባህሪ የራቀ ፣በ እርጋታና በማስተዋል እንዲራመድ የሚረዳው እንደሚሆን ማስታወስ ተገቢ ነው።
 
 
ለሕፃናት :- ''መጭውን ዘመን እንድነግርህ ሕፃናቱን እንዴት እያሳደግህ እንደሆነ  ንገረኝ'' የሚለው አባባል ትልቅ ቁም ነገር የያዘ ነው። በሀገር ውስጥም ሆነ በ ውጭ በተለይ በከፋ መልኩ ማንነታቸውን የዘነጉ ልጆች ማግኘት ብዙ አስቸጋሪ አይደለም። ወላጅ ጊዜ ከማጣትም ሆነ እንዴት አድርጎ ማስተማር እንዳለበት ግራ በመጋባት ሳቢያ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር በ እጅጉ እየተራራቁ የሚሄዱበት ሁኔታ የሰፋ ነው። ለ እዚህ ሁሉ መፍትሄው እንደ እዚህ አይነት የ ቴሌቭዥን መርሃግብሮችን ለ ሕፃናት እንዲመለከቱ ማድረግ ነው።
 
 እርግጥ ነው  ቤተ ክርስቲያን  ቀደም ብሎ የ እዚህ አይነት ሚድያ በ ሃገር ቤት ሊኖራት ይገባ ነበር፤መንግስትም በ አንድ በኩል ልማትን ለማስፋፋት ፍጹም ቁርጠኝነት ካለው  ምዕመናኗ እንዳይታወኩ፤አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ተገቢውን እገዛ በማድረግ ብዙ ችግሮች ከወዲሁ እንዲመክኑ የማድረግ  ፤ በ ሌላ በኩል  ከ ቤተ መንግስት በር እስከ ገጠር መንደር ድረስ መዋቅር ያላትን ቤተ ክርስቲያን ከ ፖለቲካዊ መንፈስ በ ራቀ እና የ እራስዋን አስተዳደራዊ እና የ ልማት ስራዎችን እንድታከናውን ከ እዚህም በዘለለ መንገድ በነጻ ሊያገለግሏት የተዘጋጁትን በ ሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች እንድትጠቀም ያሉባትን ችግሮች በመቅረፍ ሂደት የማገዝ ሚና መንግስትም ሊኖረው  ይገባዋል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
 
እነኝህን ችግሮች ለመፍታት የ መገናኛ ብዙሃን ያውም ቴሌቭዥን አስፈላጊ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ስራ ደግሞ ሶስቱን መሰረታዊ ሃብቶች ማለትም ጊዜ፣የ ሰው ሃይል እና ገንዘብ መፈለጋቸው የግድ ነው። በ ሃገር ቤት ብቻ ሳይሆን በውጭ የሚኖሩ ምዕመናን በ እጅጉ ሊደግፉት የሚገባ፤ ከ ስጋዊም ሆን መንፈሳዊ ጸጸት የሚያድን እና  ለ ህሊናም የ ሃገርንም የቤተ ክርስቲያንንም ጉዳት እያዩ ከመቆጨት የሚያድን ትልቅ ተግባር ይመስለኛል።
ለ ቴሌቭዥን ፕሮግራም ማስታወቂያነት የተለቀቀውን አጭር ቪድዮ ይህንን በመጫን ይመልከቱ:-
 

Saturday, September 22, 2012

የ ኢትዮጵያን መጪ ዘመን የሚያመላክቱ ያለፉት የ 24 ሰዓታት ክስተቶች

ትናንት መስከረም 11 እና ዛሬ መስከረም 12/2005 ዓም ሀገራችን ፖለቲካ መድረክ ላይ መጪውን ዘመን የሚያመላክቱ ሶስት ሁኔታዎች ታይተዋል። ነገን በደንብ የሚያመላክቱ ኢትዮጵያውያን በውል ልንመለከተው የሚገባም ይመስለኛል።ኢህ አዲ ወደቀደመው መዝሙሩ አቶ መለስ ሞት በኋላ ሙሉ በሙሉ መመለሱን፣ ለለውጥ ዝግጁ አለመሆኑን በደንብ አረጋግጧል።በነገራችን ላይ አቶ ሃይለማርያም '' በመተካካት ኢህአዲግ ባህል መሰረት ወደ ስልጣን መጡ'' የሚለው ፈፅሞ ሐሰት ነው።መተካካት የሚባለው አቶ መለስ ፈቃዳቸው ስልጣን ለቀው ቢሆን ነበር እንጂ ሞት ሲለዩ በቦታቸው ሌላ ሰው ማስቀመጥ መተካካት አይባልም።
መጪውን የሚያመላክቱ ሁኔታዎች  

መጪውን አመላካች 1 :-  ''አሁንም አጨብጭቡ!''
መስከረም 11/2004 ዓም  (Sep.21/2012)  አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ በ ኢህአዲግ ምክርቤት ለማፀደቅ አቶ አባ ዱላ ምክርቤቱን እንዲያፀድቅ ሲጠይቁ ዝምታ ሰፈነ ቀጠሉና አባ ዱላ እንዴት እንደሚጨበጨብ ለማሳየት እጃቸውን እንደማጨብጨብ ሲያደርጉ የ ምክርቤቱ አባላት ማጨብጨብ ጀመሩ።
መጪውን አመላካች 2 - ''ጉድጓድ እስኪገባ?''
''መተካካት ማለት አዲሱን መሪ  በ ሩቅ  ሆኖ መታዘብ ማለት አደለም----- በሕይወት እስካለን ጉድጓድ እስኪገባ ድረስ ድጋፍ መስጠት አለብን---- የትም አንሄድም።----ህዝቡ እስካለ ድረስ አዲሱ አመራር ወለም ዘለም የሚልበት ዕድል አይኖረውም'' አቶ ስዩም መስፍን መስከረም 12/2005 ዓም  (Sep.22.2012) ለ ኢ ቴ ቪ  ከሰጡት መግለጫ።
መጪውን አመላካች 3 - ''ጓድ መለስ ፣ ጓድ መለስ ፣ ጓድ መለስ------!!!''
''ጓድ መለስ ፣ ጓድ መለስ ፣ ጓድ መለስ'' በማለት ከ 20 ጊዜ በላይ የጠራው የ ህዋሀት ማዕከላዊ ኮሚቴ መስከረም 12/2005 (Sep.22.2012) ዓም በ ኢ ቴ ቪ ያስነበበው መግለጫ። በመጨረሻ እንዲህ አለ:-
''በተግባር የተፈተነው የድርጅታችን መስመሮች  ጓድ መለስ እንዳለው በድርጅታችን መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር  በማንኛውም መንገድ ለ ድርድር እንደማይቀርብ ደግሞ ደጋግሞ ያረጋግጣል''
አሁንም አሳዛኝ ''ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ'' ነገር ገባን። ኢህአዲግ እራሱን ለማረም አልቻለም። ሁሉ ነገር እንደነበረ ይቀጥላል፣ ፖለቲካዊም፣ማህበራዊም ምጣኔ ሃብታዊም  ሽግርግር የለም።በ ኢህአዲግ  በ ክልል እና በ ቋንቋ የተከፋፈለ ትውልድ ነው የምንወርሰው? ይች ነች በ ኢህአዲግ  ቅኝት ውስጥ የምትኖረው ኢትዮጵያ?
 







 

Friday, September 21, 2012

አቶ ኃይለማርያምን'' አቃቢ ግንቦት ሃያውያን'' ካስቸገሩዋቸው ዶ/ር ነጋሶ በ ሄዱበት መንገድ...

አቶ ኃይለማርያምን'' አቃቢ ግንቦት ሃያውያን'' ካስቸገሩዋቸው ዶ/ር ነጋሶ በ ሄዱበት መንገድ ወደ ኢህአዲግ ተቃዋሚነት መቀየራቸው ላይቀር ይችላል።(ቪድዮ፡ የዛሬውን የ አቶ ሃይለማርያም ቃለመሃላ እና ንግግር)
በዛሬው ዓርብ መስከረም 11/2005ዓም የ አቶ ሃይለ ማርያም የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት  ምክር ቤት (99.6% ኢህአዲግ በሆነበት ምክርቤት )  ቀርቦ ጸድቋል።የ አቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ምክርቤቱ እንዲያጸድቅ አቶ አባ ዱላ የጠየቁት በማጨብጨብ ሲሆን የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን የ አቶ መኮንንን ግን ድምጽ እንዲሰጥበት እጅ እንዲወጣ በመጠየቅ ነበር።
  • ህወሃት ከጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ታዋቂው የ ምጣኔ ሀብት ጠቢብ አዳም ስሚዝ ''የማይታዩ እጆች'' ብሎ እንደ ሚጠራው የ ምጣኔ ሃብት አካላት  በ እርግጥም ከ እይታ ተሰውረዋል።
  • አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ በንግግራቸው  ደፈር ብለዋል፣
  • ባለፈው ቅዳሜ¨ምደባ¨ ያሉትን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣንን ዛሬ ¨ታላቅ ዕድል¨ ብለውታል፣
  •  ኢትዮዽያን ሲጠሩዋትም  አምሮባቸዋል። ''ኢትዮዽያችን!'' ነው ያሉት።
  • የትምህርት ጥራት አንስተዋል። ከ ዩንቨርስቲ አካባቢ መምጣታቸው ስለ ዩንቨርስቲ፣ምርምር፣ሳይንሳዊ አሰራር ወዘተ ያስጨነቃቸው እና ሾላ ድፍን አሰራር እንዳስመረራቸው ያስታውቃሉ፣
  •  የ ኢንዱስትሪውን ወሳኝነት ተወስቷል።የ ከተሞች መሰረታዊ ችግርን ፣የ ቤት ችግር  መፈታት ያለበት መሆኑን፣የ መንገድ ስራው፣የ ሃይል ማመንጫ ወዘተ እንደሳቸው አገላለፅ  ¨ጥርሳችንን ነክሰን¨መፈጸም አለብን ብለዋል፣
  •  ሙስናን እና ኪራይ ሰብሳቢነት ትልቅ እንቅፋት ነው በተለይ ከ መሬት ጋር የተያያዘ ጉዳይ መታየት አለበት ብለዋል፣
  •  የፍህ ስርዓቱን በተመለከተ ¨የ ፖሊስ፣የ ፍትህ አካል ሁሉ በ አግባቡ አገልግሎት መስጠት ይገባቸዋል።በ አንዳንድ አካባቢዎች በ ሙስናና ብልሹ ስነ ምግባር አካባቢ የሚፈጠሩ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው ሊሰመርበት ይገባል¨ብለዋል፣
  • ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋርም ተባብረን እንሰራለን የሚል ቃል አክለዋል።
የዛሬው ክንውን በ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ትልቅ ክስተት ባይባልም እንደ እኔ አመለካከት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ:-

  • ምክንያታዊነትን(rational) ከ ፓርቲ አባልነት አስቀድመው ውሳኔ መስጠት ከቻሉ፣
  • ፍትህን ለማስፈን ቆርጠው ከተነሱ፣
  • የ አባትነት ባህሪ  የተላበሰ ሁሉን ዜጋ እኩል ማየትን ገንዘብ ካደረጉ፣
  • ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ለ ሃይማኖቱ ሰዎች ብቻ ከተዉ፣
  • ሙስናን በድፍረት ነቅለው ታሪክ መስራት ከቻሉ ፣
  • የ ነፃ ፕሬስን እና ተቃዋሚዎችን በጠላትነት ከመመልከት ይልቅ የ ተለየ ሃሳብ ያላቸው ነገር  ግን ለ ሀገራችን አስፈላጊ ዜጎች መሆናቸውን ይዘው መምራትን ከጀመሩ  የ ዛሬውን ቀን ''በ አቃቢ ግንቦት ሃያውያን'' እና በ እውነተኛ የፍትህ እና የልማት ሰዎች መሃከል ደቡብን ባሳተፈ መልክ ትግል ተጀመረ ማለት የሚቻል ይመስለኛል። አቶ ኃይለማርያምን'' አቃቢ ግንቦት ሃያውያን'' ካስቸገሩዋቸው  ዶ/ር ነጋሶ  በ ሄዱበት መንገድ ወደ ኢህአዲግ ተቃዋሚነት መቀየራቸው ላይቀር ይችላል። በ ጭፍን  ኢህአዴግ ያለው ሁሉ ትክክል ነው የሚል  አስተሳሰባቸውን ግን አቶ ሃይለማርያም ዛሬ መሃላቸውን እንደፈፀሙ  የሚያወልቁት ይመስለኛል። ምክንያቱም በሕዝብ እይታ እንደገቡ እና ስልጣኑ እንደፀደቀ ኢህአዲግ ኮስሶ ህዝቡ ገዝፎ ይታያቸዋል።ለመወደድ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያውቃሉ።ይህ እንግዲህ ከ'' አቃቢ ግንቦት ሃያውያን'' በሁሉ ሁሉ ከዳኑ ነው።
''አቃቢ ግንቦት ሃያውያን'' ብዬ የምጠራቸው ታሪክ ተቦክቶ፣ኩፍ ያለው፣ የተጋገረውም ሆነ የተበላው በ ግንቦት ሃያ ነው ብለው ለሚያስቡ ከ እዛ ቀን በፊት የ ነበረችውን  ኢትዮጵያ ከ ዛሬ ሁነት ጋር ማዛመድ ላቃታቸው  ወገኖች ሁሉ ነው።


 

Tuesday, September 18, 2012

ሃገርን ማዳን እራስንም ማዳን ነው !

  • የታሰሩ የ ፖለቲካ እስረኞችን ይፈቱ ማለት ብቻ ሳይሆን ከተፈቱ በኋላ ለ እስር የዳረጋቸውን ጥያቄ መመለስ አለመመለሱ ነው ዋናው ቁም ነገር፣
  • ሃገርንም እራስንም ለማዳን ኢህአዲግም ሆነ አንዳንድ የ ኢህአዲግን ፖሊስ የሚቃወሙም ዋናውን ነገር እየዘነጉ በ ንዑስ ጉዳዮች ላይ ሲያተኩሩ ማየት እጅግ አሳሳቢ ነው፣
  •  የ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከ አድዋ መጣ፣ከ ጅጅጋ፣ከ ጎጃም መጣ ከ አሳይታ የ ፖሊሲው ማዕቀፍ ሳይስተካከል ኢህአዲግ ምንም ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ይረዳዋል፣
  • የሀገራቸውን አንድነት መሰረት ያደረጉ መሰረተ ሰፊ (Broad-based) እና ሀገር ወዳዱን፣ ምሁሩን  እስከ ገበሬ ያሳተፉ  ፓርቲዎች በ ሩቅ ምስራቅ ሃገራት ለ ሀገራቸው ልማት ታምር መስራት መቻላቸው የ ዘመኑ ክስተት ነው።


ባለፈው ቅዳሜ ከቀትር በሁዋላ ኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር አስራ አንድ ሰዓት ገደማ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ኢህአዲግ ምክር ቤት ድርጅቱ ሰብሳቢነት መምረጡን ሰበር ዜና ድህረ ገፆች ተረዳሁ በጎ ነገር ለሀገራችን ቢመጣ የማይወድ ማን አለ? ፖለቲካ ንትርኩ ሁሉ አንዲት ቀን እርቅ ቢጠናቀቅ የማይሻ ማን አለ? ችግሩ ግን መልካም ጊዜ ይሆናል ብሎ በተስፋ መኖር ?ወይስ እየሄድን ያለንበትን አደጋ እርግጡን በማውራት እውነታው ጋር እራስን ማስታረቅ? ጥያቄው ይህ ነው።እውነት ነው። አለፈው ቅዳሜ ወዲህ ባሉት ሶስት ቀናትም የተለያዩ አስተያየቶች መሰንዘራቸውን ቀጥለዋል።ግማሹ ኢህአዲግ '' ሰው ለውጥ አደረገ'' ሲል የተቀረው ''ምንም ለውጥ የለም አቶ ሃይለማርያም 'ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው' ''ይላል። ሌላው''ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ መሪአገኘች''ሲል የተቀረው '' ከደቡብ መሆኑ ስልጣን ክፍፍል በጎ ነው ይላል።''የእኔ አይነቱ ደግሞ ወደ ደርግ-መሰል የረቀቀ አስተዳደር የመግብያ ምዕራፍ ላይነን እላለሁ።አቦይስብሐትግን በፓልቶክባደረጉትገለፃላይእንዲህ ብለዋል ''እየተደዋወሉ ( ኢህአዴጎችማለት ነው) እንኳንደስ አለን!ትግሉፍሬ አፈራ! አማራም ሆነ ኦርቶዶክስ ያልሆነ መሪ መምጣቱ ትልቅ ድል ነው እየተባባሉ ነው '' ብለዋል።
ከ ሰላሳ ዓመት በኋላም የመሪ  መመዘኛው  የመጣበት  ክልል ነውን ? 
ኢህአዲግ ከ ደርግ ጋር በ ውግያ ላይ በነበረበት ጊዜ ሁሉ ''የ ኢትዮጵያ ችግር የ ብሄር ችገር ነው የ ገዢው መደብ መወገድ ብቻ ሳይሆን የ ፖለቲካው ስልጣን ብሄርን እና ቋንቋን መሰረት ማድረግ አለበት አለ። በመሰረቱ የ ብሔር ጥያቄ የችግሮች ቁልፍ መፍቻ ነው የሚለው የ ሶሻልስቱ ዓለም ስሙ በገነነበት ወቅት በ 1970 ዎቹ እአአ የተፈጠሩ የ ፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ፋሽን ስለነበር ያኔ መነሳቱ ላይደንቅ ይችላል። የሚደንቀው ከ ሰላሳ አምስት ዓመት በኋላም ዛሬም ድርጅቱ ሰብሳቢውን ሲመርጥ እና ለ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲያቀርብ የሚኩራራበት የመረጠውን ግለሰብ ችሎታ፣ልምድ፣ታማኝነት ከመጥቀስ ይልቅ የድርጅቱ አንጋፋ መስራች እና  በ አንዳንዶች ዘንድ '' የ ኢህአዲግ ፈጣሪ ኢንጅነር'' በተባሉት አቦይ ስብሐት ዘንድ ስለተመረጡት አቶ ሃይለማርያም የሚነገረው ክልላቸውን  እንደዋና መስፈርት ከመጠቀሱ በላይ '' ከ ሃሜት ዳንን'' በሚል ስሜት ትልቁ ድል ተብሎ የተወሳው''  ከ  እገሌ ክልል ሳይሆን ከ እገሌ መሆኑ ይህን ሃይማኖት የሚከተል ሳይሆን ያኛው መሆኑ'' መባሉ አሳፋሪ አነጋገር ብቻ ሳይሆን የድርጅቱን ታላቅ ዝቅጠት ያሳያል።

ሀገር አቀፍ ፖሊሲ  ያድናል ክልል አቀፍ ፖሊሲ  ይገላል

ኢህአዲግ ብቻ አደለም ብዙ የኢህአዲግን ስሜት የማይጋሩ ሰዎችም በሚሰጡት አስተያየት የ አቶ ኃይለማርያምን ክልል በመጥቀስ ብቻ  የተሻለ ነገር ይመኛሉ። መመኘት ጥሩ ነው። ምኞትን ግን በማስረጃ ማስደገፍ  ሌላ ነገር ነው።ኢህአዲግም የ እነኝህን ሰዎች ስሜት እያረገበ ለውጥ እንደመጣ መንገሩ አስገራሚ ነው። አንዳንዶች እዚህ ላይ ''ትንሽ ቸኮልክ ገና ምኑ ተያዘ እና'' ነው የሚሉ እንደሚኖሩ እረዳለሁ። በ እኔ አመለካከት ኢህአዲግ ለውጥ ያመጣል ብዬ ትንሽ የተስፋ ውልብታ ውስጥ የገባሁት አቶ መለስ ከተቀበሩ እስከ ጳጉሜን ወር ፍፃሜ ድረስ ነበር። የ ፍትህ  ጋዜጣ አዘጋጅን በድንገት መፍታት የ ነገሩ ድንገተኝነት '' አሁንስ በቃን ይህን ሕዝብ ስንት ጊዜ አንገላታነው? በጎ መስራት ለ እራስ ነው ክፉም እንዲሁ'' የሚል ሃሳብ ነገሰ ብዬ በጣም ተደስቼ ነበር። ቀጥሎ የነበረው ማን እንደሾማቸው ያልታወቁት የ ጦር ሹማምንት ጉዳይ ግን ፖለቲካውን ተረዳሁት ላለ ሰው ቀላል የሕግ አፈፃጸም ብቻ አይደለም የ ቡድን ስራው ያለ መሆኑን አመላካች ነው። ለምን ተሾሙ? የሚል ጥያቄ የለኝም። ለ አንድ ሀገር ዋስትናዋ ሕግ የተከተለ አሰራርን በማንገስ እና ባለማንገስ መሃል ግን ያለው አንደምታ ግልፅ ነው። ሚስጥራዊ  አሰራር በራሱ የ አምባገነናዊነት መሰረታዊ ባህሪ  ነው። ''ሁሉን ም ነገር ባንድ ጊዜ እንዴት?'' የሚሉትን እዚህ ላይ ማንሳት አልፈልግም ስራዬ አደጋው ታየኝ ሁሉም ሊ ታየው ይገባል ነውና።

ኢህአዲግ ምን ያድርግ?
ኢህአዲግ እኮ ብሄርን መሰረት ያደረገ ፖሊሲውን እንዲቀይር ያልመከረው የለም? ከድርጅቱ የወጡት የ ፋያናንስ እና የ ውጭ ግንኙነት ኃላፊው፣የ መከላከያ ሚንስትሩ ከሁሉም በላይ ፕሬዝዳንት አድርጎ የሾመው ሰው ሁሉ ፖሊሲውን ተቃወሙ።የትኛው ሀገር ነው የ እዚህን ያህል የ ፖሊሲ ተቃርኖ ከ እራሱ ከድርጅቱ መሃል በ እንደዚህን ያህል የ ስልጣን እርከን ያሉ ያጣጣሉት ፖሊሲ ? ይህ ትምህርት ካልሆነው ምን ትምህርት ሊሆነው ይችላል? እንደሚመስለኝ አሁን ኢህአዲግ ይህን  ወቅት የ መሰረታዊ ፖሊስ ለውጥ በማድረግ ሀገርንም ህዝብንም ማዳን የሚገባው ወቅት ላይ ነው እና የሚከተሉትን ለውጦች የማምጣት ድፍረት ካሳየ ብቻ ይመስለኛል ሕልውናውንም ሀገሪቱንም ከ ከፋ አደጋ የሚታደጋት።
1/ ከክልል መሰረት አስተሳሰብ ብሔራዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ መሆን
ይህ ሥራ ከየት ይጀመራል? ቢሉ   መልሱ  የ አባል ድርጅቶች ስምን ከመቀየር የሚል ነው። ''ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት)'' እስከመቼ የትግራይን ሕዝብ ብቻ ነፃ የሚያወጣ የሚል ስም ይዞ ይዘልቃል? ''ብሄረ አማራ ዲሞክራሳዊ ድርጅት (ብአዲን )'' እስከመቼ የ አማራ ግንባር ነኝ  እያለ ሲፎክር ይኖራል? የ ''ኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራስያዊ  ድርጅት (ኦህዴድ )'' እስከመቼ ለ ኦሮሞ መብት ብቻ ቆምያለሁ ይላል? ሌሎችም አንድ ላይ  ተዋህደው ይቀላቀሉ እና የ አራት ፣ አምስት ፣ ስድስት ፓርቲ ጥምረት ነው መባሉ ቀርቶ የ አንዲት ኢትዮጵያ ውሁድ ፓርቲ ሆነው ይምጡ ።የሀገራቸውን አንድነት መሰረት ያደረጉ መሰረተ ሰፊ (Broad-based) እና ሀገር ወዳዱን፣ ምሁሩን እስከ ገበሬ ያሳተፉ ፓርቲዎች በ ሩቅ ምስራቅ ሃገራት ለ ሀገራቸው ልማት ታምር መስራት መቻላቸው የ ዘመኑ ክስተት ነው። እነዚህ ፓርቲዎች ግን ብሄርን መስረት ያደረጉ አይደለም።

2/ ኢህአዲግ የሀገር ፓርቲ ከሆነ ፖሊስ አርቃቂም ነጋዴም ሊሆን አይችልም
ፖሊሲ አርቃቂ እና አስፈፃሚ ከ አፍሪካ ግዙፍ የሆነ የንግድ ተቋም ኢፈርት የተሰኘ የንግድ ድርጅት መስርቶ (ኢፈርትን አቶ ስብሐት ነጋ ከ አፍሪካ ግዙፍ የንግድ ድርጅት መሆኑን ለ አሜሪካ ራድዮ የ አማርኛው አገልግሎት መግለፃቸውን ልብ በሉ) ፍትሃዊ የ ምጣኔ ሀብት ስርዓት እንዴት ብሎ ነው በ ኢትዮጵያ የሚመጣው? ነገ የሚፀድቀውን  የንግድ ሕግ ቀድሞ ከሚያውቅ ነጋዴ ጋር ማን የ ገበያ ውድድር ይገባል።ሕግ አስፈፃሚውስ እንዴት ነው የሚቆጣጠረው? ኢህአዴግ ብዙ ጊዜ የሚ ናገረው'' በ ትግሉ ጊዜ ያፈራነው ሀብት ነው እና በሀገር ቤት መዋለ ንዋይን ማፍሰስ ምን ኃጢያት አለው? ወደውጭ አላሸሸንም '' የሚል መከራከርያ ነው።ስለ ውጭው ለጊዜው ይቆየን እና በ ሀገርቤት ግን ፖሊስ አውጭ አካል ነጋዴ ሆነ ማለት የሶሻሊስት የ አንድ እዝ ኢኮኖሚ ስርዓት በከፋ የ ሕዝቡን ባለቤትነት ባላረጋገጠ ለሙስና እና ለመጨቆኛ መልክ በተዘጋጀ መልክ ብቅ አለ ማለት ነው። ስለዚህ'' ኤፈርት '' በፍጥነት ለ ሕዝብ ሽርክና ተሸጦ ከ ፖለቲካው እና የወታደራዊ ኃይል ከያዙት ኃይሎች መላቀቅ አለበት።
ከላይ ከተጠቀሱት ሁለቱ መሰረታዊ ለውጦች ባሻገር ሌሎቹ ኢህአዲግ ተቀየረ የሚያሰኙት ነጥቦች:-
  • የፍትህ አካሉ ፍፁም ነፃ የሆነ ማድረግ፣
  • የ ጦርሃይሉን ተዋፅኦ ፍትሃዊ እና ከፓርቲ ታዛዝነት ወደ የ ሕዝብ ሀብትነት መቀየር፣
  • የመገናኛ ብዙሃንን ነፃነት ማረጋገጥ፣
  • አጠቃላይ እርቅ እና ምህረት በታመነ እና ዋስትና በሚሰጥ መልክ ማወጅ፣
  • ባለፈው የሀገሪቱ ታሪክ ላይ የሀገር አንድነትን፣የ ሕዝቡን መተማመን፣ነፃነት እና ፍትህ ላይ ያተኮሩትን ሕዝብ እንዲያውቅ ለ ዛሬው የ ሀገሪቱ ማንነት ከፍተኛ ተፅኖ እንዳለው መረዳትና መጠቀም፣
  • ነፃ የ ፓርቲዎች ውድድር ማከናወን፣
  • ዘላቂ የመንግስት ስርዓት ያለን መጭው ትውልድም ሊጠቀምበት የሚችል ህገ መንግስታዊ  ማሻሻያ ማድረግ እና 
  • ይህን ሁሉ ተግባራት ለመፈፀም አስፈፃሚ አካል መሰየም እና አፈፃፅሙም ለ ሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ የሚታይ በ ጊዜ የተለካ  እንዲሆን ማድረግ የሚሉት ከብዙ በ ጥቂቱ ናቸው።
             አቶ መለስ ዜናዊ እና አቶ ሃለማርያም ደሳለኝ በ ውይይት ላይ

ሃገርን ማዳን እራስንም ማዳን ነው
ኢህአዲግ ከደቡብ ሰብሳቢ በመመደቡ ለውጥ አመጣሁ የሚለው አሁንም በ ብሔር ፖለቲካ አይኑ እያየው (ከ ሰላሳ ዓመት በፊት በነበረበት አስተሳሰብ ተዘፍቆ ስለሚመለከተው  ነው እንጂ ) የ ኢትዮጵያ ሕዝብ ከ አድዋ መጣ፣ከ ጅጅጋ፣ከ ጎጃም መጣ ከ አሳይታ የ ፖሊሲው ማዕቀፍ ሳይስተካከል ኢህአዲግ ምንም ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል ይረዳዋል።ሃገርንም እራስንም ለማዳን ኢህአዲግም ሆነ አንዳንድ የ ኢህአዲግን ፖሊስ የሚቃወሙም  ዋናውን ነገር እየዘነጉ በ ንዑስ ጉዳዮች ላይ ሲያተኩሩ ማየት እጅግ አሳሳቢ ነው። አንዳንዶችም ኢህአዲግ ሊጠየቅ የሚገባውን ዋናውን ጥያቄ  በአንዳንድ እርምጃዎች ሲዘነጉ ማየት አሳዛኝ ነው።ስለዚህም ተቃዋሚዎችም ሊያተኩሩበት የሚገባው ዋና ዋና የ ፖሊሲ  እና የ ህገ መንግስታዊ ማሻሻያ ጉዳዮች ላይ እንጂ በ እለት እለት ተግባራት ላይ ብቻ መሆን የለበትም።ለምሳሌ :-
  • የታሰሩ የ ፖለቲካ እስረኞችን ይፈቱ ማለት ብቻ ሳይሆን ከተፈቱ በኋላ   ለ እስር የዳረጋቸውን ጥያቄ መመለስ አለመመለሱ ነው ዋናው ቁም ነገር፣
  • የ ኢህአዲግ ክልልን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ በ ሥራ ላይ በቆየባቸው እያንዳንዱ ቀናት ተጨማሪ አደጋ እየያዘ መሆኑን መረዳት፣ላልተረዱት ማስረዳት ነው ትልቁ ሥራ እና 
  • አደጋውን በጥናት በተደገፈ መረጃ በየዘርፉ ለ ህዝቡ ማስረዳት ለመፍትሔውም ከልብ መስራት የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው።
ኢህአዲግም መሪ ከ እገሌ ክልል እና እገሌ ሃይማኖት አመጣሁላችሁ እያለ የ ዛሬ ሰላሳ ዓመት በፊት በነበረ አስተሳሰብ ላይ ሆኖ  ከሚነግረን የተመረጡት ሰብሳብዬ ስብእና ፣ችሎታ፣ራእይ እና አቅም ይሄ ነው ብሎ መናገር ከ አንድ መንግስት የሚጠበቅ ትንሹ መስፈርት መሆኑን መረዳት ይገባዋል።
አበቃሁ 
ጌታቸው በቀለ 
ኦስሎ 





 

Friday, September 14, 2012

ከወታደራዊ ''ደርግ'' ወደ ሽምቅ ተዋጊ ''ደርግ '' ተሸጋገርን እንዴ?

  • ነገራችን ሁሉ '' የወታደራዊ ደርግ ውጣ የ ሽምቅ ተዋጊ ደርግ ግባ'' እንዳይሆን ሁለት ሶስት ጊዜ ማሰብ ይገባናል፣
  • አፍቃሪ ኢህአዴግም ሆኑ አባላቱ ያማይባቸው አንድ የጋራ የሆነ ባህሪ  አለ፣
  • ኢህአዴግ አሁንም 1983 ዓም ላይ ያለ ለመሆኑ ስራዎቹ እያሳበቁበት ነው፣
  • አሁን በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ሕዝብ የሚመራው ፍላጎቱ እና ሃሳቡ በሳይንሳዊ መንገድ በተደገፈ መረጃ እና የጥናት ውጤት እንጂ በዘፈቀደ የተወሰኑ ሰዎች ተሰብስበው እንደፍላጎታቸው በወሰኑት ሊሆን አይገባውም፣
  • በኢትዮጵያ በስልጣን ሽምያም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ከ ጥንት ጀምሮ ነገስታት እርስ በርስ ተዋግተዋል። አንዳቸውም ግን ከወገናቸው ጋር ላደረጉት ውግያ 'ግዳይ' እንደጣለ ማስታወሻ ሀውልት ያቆሙ የሉም።

የደርግ ትርጉም

ደርግ የሚለውን ቃል ትርጉም ውክፕድያ የተሰኘው እንሳይክሎፕድያ እንዲህ ይገልፀዋል:-

 ''The Derg or Dergue (Ge'ez: ደርግ), which means "committee" or "council" in Ge'ez, is the short name of the Coordinating Committee of the Armed Forces, Police, and Territorial Army that ruled Ethiopia between 1974 to 1987, taking power following the ousting of Haile Selassie I'' 1

'' ደርግ ወይንም ደርጉ ማለት በ ግእዝ  ኮሚቴ ወይንም ምክርቤት ማለት ሲሆን በ አጭሩ  ይህ ስም  የ ጦር  ኃይሎች የ ፖሊስ ሰራዊት እና የ ምድር ጦር አስተባባሪ ኮሚቴ እ አ አቆጣጠር ከ 1974 እስከ 1987 የ ቀዳማዊ ሃይለስላሴን መንግስት ተክቶ በኃይል ኢትዮጵያን የገዛ።'' ይለዋል።

ቀዳማዊ  አፄ ሃይለስላሴ በፈቃዳቸው ስልጣን ለቀቁ ማለት አንችልም?

ሰኔ 21/1966 ዓም  የተመሰረተው ደርግ መስከረም2፣ 1967 ዓም ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴን ገድሎ  በ ይፋ ስልጣን መያዙን አወጀ። ይህ ብቻ አይደለም ህዳር 13/1967  ለ ደርጉ የ ዘመቻ እና ጥበቃ መምርያ መኮንን በተፃፈ ደብዳቤ ጀነራል አማን አምዶምን እና በ ተለምዶ የ'' ስልሳዎቹ እልቂት'' ተብሎ የሚታወሰውን ሚኒስትሮቹን እና ባለሙያ ምሁራንን ሁሉ በ አንዲት ጀንበር የፈጀበትን  ፍርድ ፈረደ።


 በ እዚህም የደርግ ፍርደ ገምድልነት '' ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም! '' የሚለው መፈክር ሕልም መሆኑ ለየለት። እንደወቅቱ የታሪክ ተናጋሪዎች ከሆነ አፄ ሃይለስላሰም ሆኑ ከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው የ ጦር ኃይሉን ከመሰረቱ ጀምሮ ኮትኩተው ያሳደጉት ስለሆነ የከፋ ነገር ይፈፅማል ብለው አይጠብቁም ነበር። ብርጋዲር ጀነራል ደስታ ገመዳ ስለ ደርግ  አነሳስ እና  የ አፄ ሃይለስላሴን አመለካከት ሲገልፁ:-
'' እነ  ጀነራል አበበ ገመዳ የ ሰራዊቱን ሁኔታ አይተው  ጃንሆይን ' ልምታ?(ያመፁትን መኮንኖች )' አሉ። ጃንሆይ አይሆንም እንዳትነኩዋቸው አሉ።ምክንያቱም ጃንሆይ  ደም እንዲፈስ አይፈልጉም። ሚኒስትሮቹን ሁሉ ሂዳችሁ እጅ ስጡ ነው ያሉት።'' 2  ሲሉ ተናግረዋል ።

 ይህ ብቻ አይደለም በሰኔ  21/1966 የደርግ መመስረት ጋር ተያይዞ ኮለኔል ደበላ ደንሳ ለንጉሡ  ከደርግ መኮንኖች ጋር በ ቤተመንግሥታቸው ተገኝተው ባነበቡላቸው የደርግ ውሳኔ ላይ  ''የ ጦር ኃይሎች የ ፖሊስ ሰራዊት አስተባባሪ ደርግ ለ ግርማውነትዎ ጤንነት በሰፊው የሚያስብ ስለሆነ ለ ደህንነትዎ የተዘጋጀ ቦታ ስላለ  ወደዝያ እንዲሄዱልን  በትህትና እንለምናለን'' የሚል መልክት ነበር ።  ንጉሡም  የመለሱት  እንዲህ ነበር።
''በጠቅላላው የተናገራችሁትን ሰምተናል።የ ኢትዮጵያ ንጉሰ  ነገስት ስንሆን ስም ብቻ አይደለም።ህዝብንም ሀገርንም በሰላም ጊዜ የሚሰራበትን ጥፋትም ሲመጣ የሚመከትበትን በማሰናዳት መሆኑን ይህ በ ጦር ሰራዊታችን ውስጥ የታወቅ ሳይሆን ይቀራል ብለን አንጠረጥርም። ቢሆንም በየጊዜው የሚለዋወጠው ነገር ለሀገር የሚጠቅም ነገር እስካለበት የሀገርን ጥቅም በሌላ ለመለወጥ አይቻልምና ይህን ያነበባችሁትን ሰምተናል በእዚሁ ማቆም ነው።'' ብለዋል። 3
ቀዳማዊ አፄ ኃይለሰላሴ ደርግ ከ ቤተመንግሥታቸው ወደ አራተኛ ክፍለጦር በ ቫልስ ቫገን  መኪና ሲወስዳቸው።


በ እንዲህ አይነት ስልጣን የተቆናጠጠው ደርግ 'ስልጣኑን ለ ሕዝብ እመልሳለሁ' የሚል ቃል የገባ ቢሆንም በ ጎን ግን በ ሺህ የሚቆጠሩ''ሕዝባዊ መንግስት አሁኑኑ'' ያሉ ወጣቶችን  ደም ማፍሰስ  የ እለት ከ እለት ስራው ሆነ። ለቅሶ እና ዋይታ በ የስፍራው ተሰማ። ለ ሃገሩ እንግዳ ለ ህዝቡ ባዳ የሆነ የ ራሽያው ሶሽያሊዝም የሀገሪቱ መመርያ ነው ተባለ። ሰው ክብር የሚያገኘው በገደለው እና አላዋቂ በመሆኑ ብቻ ሆነ። እኔ ይህን ዘመን ክፉ ደግ ሳላውቅ በማለፉ ብቻ አምላኬን አመሰግነዋለሁ። ወላጆቻችን ሲጨነቁ  እኛ አና በ አኔ  እድሜ ያለን ሁሉ ምናልባት 'ሌባና ፖሊስ' እየተጫወትን ወይንም 'ድብብቆሽ' እንጫወት ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ የ ቤተሰቦቻችንን ፊት  መከፋት እያየን ለጥቂት ጊዜ በ ዝምታ ተውጠን መልሰን ወደ ጫወታችን ሄደን ይሆናል። ለ እኔ ወቅቱ የሚታወሰኝ ነገር ስለሌለ እና በጣም ልጅ ስለነበርኩ ትውስታ ብዬ የምለው የለኝም። ሆኖም ግን አንድ ሰው ስለ ግሪክ ታሪክ ለማውራት በ ግሪክ ዘመን  መኖር አይጠበቅበትም። ያነበበው፣ በማስረጃ የተደገፉ ታሪካዊ ሁነቶችን አጤኖ ብዙ ሊገነዘብ የ እራሱንም ፍርድ መፍረድ ይችላል።

ደርግ ስልጣን እንደክረሜላ እየጣመው መጣ። በ 1972 የ ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮምሽን (ኢሰፓአኮ)፣ ቀጥሎ በ 1977 ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ (ኢሰፓ)  በመጨረሻም የ ኢትዮጵያ ህዝባዊት ዲሞክራሳዊት ሪፑብሊክ (ኢ ህ ዲ ሪ) ሆኛለሁ አለ። ደርግ አይደለሁም አለ።ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ከ ክፍለ ሀገር አስተዳዳሪ እስከ ከፍተኛ ሊቀ መናብርት ድረስ በ ማረግ ያሉ የ ሰራዊቱ መኮንኖች ግን ሶሻሊዝም የገባቸው ተብለው ስልጣን ላይ ነበሩ።እንድያውም ኮለኔል መንግስቱ በ አንድ ወቅት''ደርግ ደርግ የምትሉት እውን አሁን ደርግ አለን?'' ብለው በ 17 ዓመት ታሪካችን ለመጀመርያ ጊዜ  ከት ብለን እንድንስቅ አረጉን። ይህ የወታደራዊ ደርግ ታሪክ ነው። አሁን ባለንበት ጊዜ የሚያሰጋኝ ''የወታደራዊው ደርግ'' ሳይሆን '' የ ሽምቅ ተዋጊ ደርግ'' የሚል ስያሜ የምሰጠው የሰሞኑ ስጋቴ ነው።
ኮለኔል መንግስቱ እና ፊደል ካስትሮ


ከወታደራዊ ደርግ ወደ ሽምቅ ተዋጊ ደርግ ተሸጋገርን እንዴ ?

ሰሞኑን የ 2004 ዓም  ተሰናብተን የ 2005 ዓም ተቀብለናል።'' የጎመን ምንቸት ውጣ የገንፎ ምቸት ግባ' ባልንበት  ነገራችን  ሁሉ  '' የወታደራዊ ደርግ ውጣ የ ሽምቅ ተዋጊ ደርግ  ግባ'' እንዳይሆን  ሁለት ሶስት ጊዜ ማሰብ ይገባናል። ሀገራችን ለ ከፋ የታሪክ ጠባሳ የዳረጋት  እና ብዙ የማደግ እድሏን የገታባት ወታደራዊው ደርግ ዛሬም በ አሳዛኝ መልኩ ብናስበውም  ከላይ እንደተጠቀሰው አፄ  ሃይለስላሴ ''ሀገርንም በሰላም ጊዜ የሚሰራበትን ጥፋትም ሲመጣ የሚመከትበትን በማሰናዳት መሆኑን ይህ በ ጦር ሰራዊታችን ውስጥ የታወቅ ሳይሆን ይቀራል ብለን አንጠረጥርም'' እንዳሉት። የሀገር አንድነትን በተመለከተ በ ብሔራዊ አንድነት ላይ እና በ ርዮተ ዓለም ላይ በነበረ አመለካከት ላይ በተመሰረተ ልዩነት እንጂ በ ዘር፣በ ክልል መከፋፈል የማያምን መሆኑ በራሱ የሚያስመሰግነው ነው-ደርግን ። በ እዚህ ፅሁፌ መግብያ ላይ የ ደርግ ትርጉምን ስንመለከት የ ደርግ ባህርያት የግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት ቢታይበትም በደርጉ ምክርቤት እየቀረቡ የወሰኑ የነበሩት ነገሮች አስደንጋጭ  እንደነበር ለመግለፅ ሞክርያለሁ።

አቶ መለስ ዜናዊ ከ እዚህ ዓለም በ ሞት ከመለየታቸውም ሆነ ከተለዩ በኋላ የስልጣን ውዝግቡ በ ኢህአዲግ ውስጥ ቀጥሏል።ይህ ብቻ አይደለም ማን ሀገሪቱን እየመራ ለማወቅ መብት የሌለን ህዝቦች ብቻ ሳንሆን። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዴት እንደታመሙ፣መቼ አንደታመሙ፣የት እንደታከሙ፣ስታከሙ ምን አንዳሉ፣ማን አንዳስታመማቸው፣አስከሬናቸው ከየት ሀገር ከየት ሆስፒታል ወደ አዲስ አበባ አንደገባ (ኢቲቪ የ አቶ መአስን አስከሬን የያዘው  አይሮፕላን አዲስ አበባ  ማረፉን አንጂ ከየት እንደገባ እስካሁን የተናገረ አይመስለኝም) ሁሉ ያልተነገርን ለመነገርም ያልተከበርን ሆነናል። ከአንዳንድ ዜናዎች እንደምንሰማው ሀገሪቱ ለ ይስሙለ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደፊት ኢህአዲግ የሚሾምላት ቢሆንም አመራሩ ግን ሰባት ኮሚቴ ባሉት የ ፓርቲው አባላት እንደሚያዝ ሳይታለም የተፈታ ሆኗል።ይህ ኮሚቴ ስራውን በይፋ ለመጀመሩም ማስረጃ የሚሆነው። ጠቅላይ ሚኒስትር እንምረጥ በሚል አንድ ጊዜ ምክርበቱን ሌላ ጊዜ ፓርቲው ተደጋጋሚ ስብሰባ አድርገው አለመሳካቱ በይፋ ከታወቀ በሁዋላ እና ፓርቲው እራሱ በ መስከረም የመጀምርያ ሳምንት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር  ማን እንደሚሆን እናሳውቃለን ብሎ በማሳወቅ 'ጠቅላይ ሚኒስትር አለን ይሆን እንዴ ?' እያልንየተጠራጠርንን ወገኖች ሁሉ በ ግልፅ 'የላችሁም በመስከረም የመጀምርያ ሳምንት ላይ አሳውቃለሁ' ያለን ኢህአዲግ በ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ እንዲሰሩ የታዘዙትን ስራዎችለምሳሌ ለ 37 መኮንኖችከፍተኛ የ ወታደራዊ ማረግ በመስጠቱ  የሽምቅ ተዋጊ ደርግ ስራውን ጀመረ እንዴ?  እንድል አድርጎኛል።

የኢትዮጵያ ጥያቄ በ ሽምቅ ተዋጊ ደርግ አይመለስም

ኢህአዴግ ሃያ አንድ አመታት የ ኢትዮጵያን ሕዝብ በደንብ ለመረዳት ከ በቂ በላይ የሆነ ጊዜ ከ አምላክ ተችሮታል።ከሀገሬ ከመውጣቴ (ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት) በሥራ አጋጣሚዎች የማገኛቸው አፍቃሪ ኢህአዴግም ሆኑ አባላቱ ያማይባቸው አንድ የጋራ የሆነ ባህሪ  አለ። ይሄውም ችግሮች መኖራቸውን ያውቃሉ። ግን በጊዜ የሚረሱ ይመስሏቸዋል።መፍትሄዎቻቸው ለዛሬ ህዝብን አታሎም ይሁን አስረስቶ ዛሬን ማለፍ ከተቻለ ነገ ችግር የለውም ብለው ያስባሉ። ዛሬ ያልተፈታ ችግር ነገ ተራራ ሆኖ የማይወጡት ዳገት ይሆናል ብሎ የሚያወራ ሁሉ እንደነሱ አገላለፅ ይህ ሰው ሌላ ሳይሆን  ''ጨለምተኛ'' አስተሳሰብ የያዘው ነው ይላሉ። ነገሮችን ሁል ጊዜ የሚመለከቱት ከደርግ ጊዜ ጋር በማነፃፀር ሲሆን ዲሞክራሲን በተመለከተ ህዝቡ ገና ብቁ አይደለም ፣ለ እዚህደረጃአልደረሰም፣የሚለውንፕሮፓጋንዳ መሰልነገር እንደ 'ነጠላ ዜማ' መልቀቅ አዲሱ ፋሽን ብቻሳይሆን ዝቅተኛ ገቢ  ባለው ሕብረተሰብ ዘንድ እና ለመረጃ ብዙምቅርብ ባልሆነው ሕዝብ መሃል ለማሳመን ጥረት የተደረገበትም ሙከራ መኖሩን አስታውሳለሁ።

መሰረታዊው የኢህአዴግ ችግር ግን ዘመኑን አለመዋጀት ችግር ነው

 ዛሬም 1983 ላይ ሆነን ካሰብን በጣም ተሳስተናል። በ ዓለም ላይ የሚገኙ የ ወታደራዊ ደርግም ሆኑ የ ሽምቅ ተዋጊ ደርጎች መሰረታዊ ስህተት የ ትውልዱ አስተሳሰብ መምጠቁን ሳይረዱ ባሉበት ጎርፍ ይዞ ወዳልፈለጉበት እና ወደ አልተመኙት ቦታ ይዞአቸው መሄዱ ነው። የ የትኛውም መግስት ትልቅነት የሚለካው ዘመኑን መዋጀት በመቻሉ እና በ  አዲሱ ትውልድ አስተሳሰብ ተገብቶ ማሰብ በመጀመር አና ባለመጀምሩ መሃል ባለው ልዩነት ነው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ኦባማን መመረጥ የማይፈልጉ በ ገንዘብም ሆነ ባማናቸውም ኃይል እና ጉልበት ያላቸው አሜሪካውያንን ይዛ ነበር አሜሪካ ኦባማን የመረጠችው። እነኝህ ኃይሎች ሕግ እና ስርዓት ብቻ ሳይሆን ያገዳቸው አንድ እውነታ ነበረ። የ አዲሱ ትውልድ ፍላጎት። እዲሱ ትውልድ ኦባማን ፈለገ በቃ። ሁሉ ነገር በ አዲሱ ትውልድ እና በ ህዝቡ ፍላጎት ብሎም ነገ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ዘመኑን የዋጁ መሆን አለባቸው እና ኦባማ ሰተት ብለው ሲገቡ ያልፈለጉአቸውም አብረው ዘመሩላቸው።ኢህአዲግ ሃያ አንድ ዓመት በ አዲስ አበባ ስቀመጥ  ከ አዲሱ ትውልድ በ ክልል መወለድ ሳይሆን በ ርዮተ ዓለም ደረጃ አሳምኖ ያመጣው  አንድ ሰው ካለው እስኪ ለ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ይቅርና  ለ አዲስ አበባ  ከንትባነት ያምጣ እና  ያሳየን።ይሄው ሃያ አንድ ዓመት ሙሉ  የድሮ ታጋዮች ብቻ ናቸው ሲቀያየሩ የሚታዩት።ከ አዲሱ ትውልድ አስተሳሰብ እና ከ ህዝቡ ጋር መች ተዋሐደ? ይህ የሚያሳየን የ ኢህአዲግ ፖሊሲዎች ሕዝቡን ይልቁንም አዲሱን ትውልድ ያገለለ መሆኑን ነው። በ አነስተኛና ጥቃቅን መደራጀት እና ፖሊስን መደገፍ ይለያያሉና።
ኢህአዴግ አሁንም 1983 ዓም ላይ ያለ ለመሆኑ  ስራዎቹ እያሳበቁበት ነው። ብዙ ማስረጃውችን ማንሳት ይቻላል።

ለምሳሌ አዲስ አበባ የገባበትን በዓል ግንቦት ሃያን  ሲያከብር አራትኪሎ ቁጭ ብሎ ልክ ከ ባዕድ ወታደር ጋር ተዋግቶ እንዳሸነፈ ሁሉ ቀን ሙሉ 'ግዳዩን' ሲያወራልን ይውላል።  በ እርስበርስ ጦርነት ዘመዶቻቸው የሞቱባቸው ግን ከስሩ ቁጭ ብለው የሞቱትን ያስባሉ። በኢትዮጵያ በስልጣን ሽምያም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ከ ጥንት ጀምሮ  ነገስታት እርስ በርስ ተዋግተዋል። አንዳቸውም ግን ከወገናቸው ጋር ላደረጉት ውግያ 'ግዳይ' እንደጣለ ማስታወሻ ሀውልት ያቆሙ የሉም።እዚህ ላይ ሃውልታቱ የ ጊዜውን ታሪክ ጠባሳነት  የሚያሳዩ ብቻ ተደርገው የተሰሩ ቢሆን ባልከፋ። ታሪክ የተጀመረው ከ እዚህ ነው የሚል አንደምታ ያለው ሥራ እና የ እርስ በርስ ጦርነትን እንደ ትልቅ ገድል ማቅረቡ ከፋ እንጂ።ይህ ብቻ አይደለም ባለፉት 20 አመታት ውስጥ ዓለም እንደነበረች አይደለችም። በዘመነ ኢህአዲግ ቴክኖሎጂ ለ ዓለም ካበረከታቸው እና ሕዝባችንም እየተጠቀመበት ያለው የ ኢንተርኔት እና የ ሳተላይት ዲሽ ቴቪ አገልግሎት የ ሕዝቡን የመረጃ የማግኘት እና በሌላው ዓለም ምን እየተደረገ እንዳለ ለማወቅ ትልቅ እድል መክፈት ብቻ ሳይሆን ከ ክልላዊ አስተሳሰብ ወደ ሃገራዊ ብሎም ወደ ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ መሸጋገሩን  እንዲሁም ለ እራሱ ብቻ ሳይሆን ለሌላ ሀገር ነዋሪዎችም ሕይወት እያሰበ እንዲመጣ ማድረጉን እንገነዘባለን። ኢህአዲግ ግን አሁንም 1983 ላይ ነው። ሁለት ክስተቶች ለ ኢህአዴግ የ ኢትዮጵያን ሕዝብ ለመረዳት ትልቅ ዕድል ፈጥረውለት ነበር።አንዱ የ 1997 ዓም ምርጫ  ሲሆን ሌላው የ ሰሞኑ የ አቶ መለስ ስርዓተ-ቀብር ናቸው።
አሁን በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ሕዝብ የሚመራው ፍላጎቱ እና ሃሳቡ በሳይንሳዊ መንገድ በተደገፈ መረጃ እና የጥናት ውጤት እንጂ በዘፈቀደ የተወሰኑ ሰዎች ተሰብስበው እንደፍላጎታቸው በወሰኑት ሊሆን አይገባውም።በ 1997 ዓም የተደረገውን ምርጫ እንደ ጥናታዊ (research ) መጠይቅ እናስበው። መጠይቁ ከተበተነላቸው ሰዎች ስንቶቹ በምን አይነት ሃሳባቸውን ሰጡ? ለምን ኢህአዴግን አልደገፉም? ትልቁ ጉድለት  ምንድን ነው? የትኛው ፖሊስ አያስኬድም? የቱ ጥሩ ነው? ብሎ የማሰብያ ጊዜ የሚሰጥ ትልቅ የጥናት ውጤት ነበር። ግን አልሆነም  ኢህአዲግ በተወሰኑ መድረኮች ይህን መሰል የዳሰሳ  ሥራ የሰራ ቢመስልም ድምዳሜው ግን ካድሬ ተኮር የሆነ እና መንገድ እና አነስተኛና ጥቅቅንን በደንብ እናስፋፋ ህዝቡ ያን ጊዜ  ይወደናል የሚል የተናጥል ድምዳሜ ላይ ተደርሶት አረፈው።

ሁለተኛው የአቶ መለስ የሰሞኑ የቀብር ስርዓት እና የህዝቡ ተሳትፎ ነው። ከላይ ለማውሳት እንደሞከርኩት ህዝቡ በ ሃያ ዓመት ውስጥ በተፈጠሩት የ ቴክኖሎጂ እድሎች ከ ሃገራዊ ጉዳዮች ሃሳብ አልፎ ዓለም አቀፍ አካልነቱ ገብቶታል።አቶ መለስን የምያወሳቸው  ''እጅ እንቆርጣለን፣መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ'' በሚሉት ንግግራቸው አይደለም።ኢትዮጵያን በመወከል በዓለም  አቀፍ ስብሰባዎች በመገኘታቸው እንጂ። አቶ መለስን ከ አድዋ አና ኤርትራ  መወለዳቸውን ህዝቡ የረሳው በ 1983 ''ይች ሀገር '' እያሉ ኢትዮጵያን መጥራት ሲጀምሩ ነው። በቃ! የ ኢትዮጵያ መሪ ናቸው ብሎ ነገር አለሙን  ትቶ ስለ ዓለም ማሰብ ጀመረ። ኢህአዲጎች:ግን:አቶ መለስ መሞቱን ሲነገረው የ:ህዝቡ ምላሽ  ምን ይሆን? እያሉ ሲያስቡ ዓለም አቀፉ ሕዝብ ስለ አፍሪካ፣ ስለ አየር ንብረት ጥበቃ ፣ ወዘተ አቶ መለስን እያነሳ ''ሞታቸው ያሳዝናል'' አለ።  ይህ ብቻ አይደለም ከ አሁን በሁዋላ ኢህአዲግ ወደ እኔ ዓለም አቀፍ አስተሳሰብ ይመጣል ብሎ ተስፋ አደረገ-ህዝቡ። ኢህአዴግም ፍንጭ አሳየ። የ ''ፍትህ'' ጋዜጣ አዘጋጅ ተመስገንን ብንን ብሎ እንዳሰረው ብንን ብሎ ''ወደቤትህ ሂድ'' ብሎ ፈታው። ሌሎች በ ሺህ የሚቆጠሩ እስረኞችን ፈታ።'' ዘንድሮ በግ እና ዶሮ ባልበላም ዘመኑ ጥሩ ሳይሆን አይቀርም'' አለ ህዝቡ። እርቅ ናፈቀው።በ አቶ መለስ ዘመን የጠፉ ነገሮች ሁሉ አሁን እናያቸዋለን ብሎ ጠበቀ።ትንሽ:እንደቆየን (በሰአታት:ልዩነት)'ለ:ሰላሳ ሰባት መኮንኖችየ ብርጋዴር ጀነራልነት እና:የ ጅነራልነት ማአረግ ኢህአዴግ ሰጠ  ተባለ።:በየትኛው:የ:ሕግ አግባብ?ይህ ተወሰነ?አቶ መለስ ያስወሰኑት ነው እንዳይባል አቶ መለስ ከታመሙ  ከሶስትወርበላይ ሆኗል።የ እዚህጊዜ ቢያንስ እንደ እኔ ግንዛቤአጥር ማጥበቅ መያዙካለፈው ታሪካችንገባኝ።ከሁሉም ደግሞ የሳምንት ጊዜጠብቆ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መርጦ ወደስራ ለመሄድ የተቸኮለው ''እውን  አሁን ደርግ አለን?''  ብለው ኮለኔ ል መንግስቱ ሃይለማርያም በ 1980ዎቹ መጀመርያ  አካባቢ እንዳሳቁን '' እውን ከ ወታደራዊ ደርግ ወደ ሽምቅ ተዋጊ ደርግ ተሻገርንን?'' የሚል ጥያቄ ጫረብኝ -ውስጤ ። እነሆ አሁንም ልብ እንገዛ ዘንድ ሕዝብ እና እግዚአብሔር ምስክር ሆነው ይመለከቱናል።
አበቃሁ።

ጌታቸው በቀለ 
ኦስሎ 
ማጣቀሻ 



 

Tuesday, September 4, 2012

የ አርባ ዓመቱ (ከ 1965 እስከ 2005 ዓም) የኢትዮዽያ የ መከራ ዘመን ያበቃል !

  • የ አርባ ዓመቱ (ከ 1965 እስከ 2005 ዓም)  የኢትዮዽያ የ መከራ ዘመን ያበቃል !
  • በ ኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የ አስራ አራት ቀናት ሱባዔ ታወጀ፤
  • የዛሬዋ ቀን ለመድረስ አርባ አመት ፈጀብን። በ አርባ ቀን የሚያልቀው ስራ በ እኛው ትዕቢት አርባ አመት አደረግነው። የ እስራኤላውያን ከ ግብጽ ወደ ከነአን ጉዞ የ አርባ ቀኑ አርባ አመት መሆኑን ልብ በሉ።ኢትዮዽያ በደስታዋም ሆነ በሃዘንዋ ከ አምላኳ በቀር የምታማክረው፣የምታለቅስበት ቦታ የላትም ፤
  • ባለፉት አርባ አመታት ወደ ዋይት ሃውስ ማልቀስ ለምደናል፤
  • ባለፉት አርባ አመታት ተፈጥሮን እንቆጣጠራለን (በስራ ለመትጋት የተጠቀምንበት ቢሆን ባማረ) ብለን ከ ፈጣሪ ጋር መገዳደር ለምደናል፤
  • ባለፉት አርባ አመታት ከ መገናኛ ብዙሃኖቻችን ጀምሮ ሁለት ጸጉር ያወጣው ሁሉ ከ ቤተ እምነቱ እስከ ቤተ መንግስቱ ድረስ ውሸት ለምዶብን ካልተዋሸ አይኖርም የምንል ደፋሮች ሆነናል፤
  • ባለፉት አርባ አመታት ኢትዮዽያውያን የምንታወቅበት ስርዓታችን፣እምነታችን፣ሰው አክባሪነታችን፣መልካም እሴቶቻችን ሁሉ ሙዜም ሊገቡ ዳር ዳር ብለዋል።
አሁን እነሆ አርባ የመከራ እና የ ጉድለት ዘመናችን ሊያልፍ የደረሰ መሰለ። እንዴት? በሉኝ።
 
በ አርባ አመት ለመጀመርያ ጊዜ በ ኢትዮዽያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የ አስራ አራት ቀናት ሱባዔ ታወጀ።ከ እዚህ በፊት አልታወጀም ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። እንደ እዚህ አምላክ በፈቃዱ ከ ቤተመንግስትም ከ ቤተ ክህነትም ሰው ወስዶ ምልክት ያሳየበት ዘመን የለንም:: ከ ሊቅ እስከ ደቂቅ የሚሳተፍበት፤ አምላክ ቢያንስ ከ አንድ በላይ ጻድቅ የሚያገኝበት፤ በትክክል ቤተመንግስቱን እና ቤተ ክህነቱን አንኳኩቶ የመጣ አምላክ ወደ እርሱ ከ አርባ አመታት መታተር በኋላ አቅማችንን አውቀን ከፊቱ ልንንበረከክ ነው እና በትክክል የሚሰማን ብሎም ህዝቡን በፍቅር፤ሃገራችንን በክብር፤ ለ ሁለት የተከፈለችውን ቤተ ክርስቲያን በቃልኪዳኑ ወደ አንድነት እንደሚመልስ እርግጠኛ እንሁን።
 
ቅዱስ ሲኖዶስ ሱባዔ ማወጅ አይደለም አንድ ሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ¨ልዩ ምህላ ስለ ሃገር እንያዝ¨ ብለው ገና ሲያስቡ ¨ሃገር አማን ነው ምን አስባችሁ? ነው¨ ተብለው በ ፖሊስ የተበተኑበትን አጋጣሚ (በ ጅማ ሰማዕታት ጊዜ) የነበረ መሆኑን ካልረሳን አሁን አምላክ በረቂቅ ጥበቡ ብሔራዊ የ ምህላ ጊዜ መታወጁ እጹብ ድንቅ ነው።
 
ይህንን ሱባዔ የምንችል ¨መታዘዝ ከመስዋዕትነት ይበልጣል¨ እንዳለን ቅዱስ መጽሃፍ ታዘን የተባለውን በስርዓት እንከውን።ይህ ካቃተን ግን ከመተቸት ተቆጥበን አንደበታችንን እንግታ። ዛሬ ምህላ ለምን? እያልን አንመራመር። የታወጀው አስራ አምስት አመት አደለም አስራ አምስት ቀን ነው።
 ቦሌ ደብረ ሳሌም መድሃኔ ዓለም፣መጥምቀ መለኮት ዮሃንስ ወ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን
 
ይህ ሱባዔ የ ቤተ ክርስቲያን የ አንድነት ተምሳሌትም ነውና ከውይይቱ በፊት ሱባዔ ያወጀው ቅዱስ ሲኖዶስን በመደገፍ በውጭ የሚኖሩ አባቶቻችንም በስራቸው ላሉት ካህናት ቢያሳስቡ እና አብሮ ሁሉም ለሃገር፣ለቤተ ክርስቲያን ብሎም ለ መላው አለም ከሁሉም በላይ ስለ እያንዳንዳችን በደል ¨ይቅር በለን!¨ ማለት ምን ሃጢያት አለው? እናም አባቶች በልጅነት አንደበት የምንጠይቃች ሁን ቸል ሳትሉ ብታሳስቡልን እንለምናችኋለን(እኔ ማለቴ ነው የሁሉም ምዕመን ሃሳብ እንደሚሆን እየገመትኩ)።

በፈቃዳችን ሳይሆን ፈቅዶልን፤ በችሎታችን ሳይሆን በደካማነታችን ደግፎን ከ ሊቅ እስከ ደቂቅ የሚጮህበት¨አምላከ ሙሴ ወአሮን ወ አምላከ ዕዝራ!¨ ብለን እንለምነው በ አርባ አመት የፈተና ዘመናችን የምናገኘው ነውና የ አርባ ዓመቱ የኢትዮዽያ የ መከራ ዘመን ያበቃል (ከ 1965 እስከ 2005 ዓም)::
መልካም አዲስ ዘመን ይሁንልን።
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ፣ ኖርዌይ

Read also http://www.dejeselam.org/2012/09/blog-post_5.html#more
 

Saturday, September 1, 2012

በ አቶ መለስ እረፍት ፣ የለቅሶ ሂደት እና በመጪው ጊዜ ዙርያ የ ህዝብ አስተያየት(ቪድዮ)

የ አንድ ሚድያ ተግባር ሚዛናዊ ዘገባ (እንደወረደ) የ ህዝቡን አባባል ማቅረብ ነው። ኢቲቪ ከ ኢሳት የሚማረው ብዙ ነገር መኖሩን የምንረዳው ይህን የ ህዝብ አስተያየት( ኢሳት በሚዛናዊነት ያቀረበውን) ከተመለከትን በኋላ ነው።
 Source    ESAT Television    (31. aug. 2012) 

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...