ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, September 28, 2012

የ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ድምፅ እና ምስል በ እየቤታችን ሳሎን

-ከ ክርስቶስ ልደት በፊት እግዚአብሄርን በማምለክ ከ እስራኤል ጋር የምትጠቀስ ሃገር ነች- ሃገራችን ኢትዮዽያ፤
-መጽሃፍ ቅዱስ ሲገልጡ ገና  በገጽ ሁለት ምዕራፍ ሁለት ላይ (ኦሪት ዘፍ ምዕ ፪) ገና አዳም በገነት በኖረበት ዘመን ከ አለም ሁሉ በፊት የመጀመርያ የ ሃገር ስም የሚጠራው ኢትዮዽያን ነው፤
-ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ስራውን ፈጽሞ ባረገ  (በ 33 ዓም)  በ አመቱ በ  34 ዓም  ክርስትናን የተቀበለች (ሐዋርያት ሥራ 8) የ አለም ቀደምት ሃገር ነች አሁንም -ኢትዮዽያ፤
-ከ ህዝብ ብዛትዋ ከ ግማሽ በላይ የሚሆነው የ ኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ነው፤
-ለ ሺህ አመታት ያህል ያበረከተችውን  አገልግሎት ባገናዘበ መልክ ምዕመኗን የምትደርስበት የመገናኛ ብዙሃን የላትም።
አሁን በጎ ጅምር ሊታይ ይመስላል።በ ኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን የ ቴሌቭዥን መርሃግብር እንደሚጀምር አስታውቋል። ርግጥ ነው በ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ደረጃ በ ማህበራት ደረጃ አንዳንድ መርሃግብሮችን በ ባህር ማዶ በሚገኙ የ ቴሌቭዥን ጣቢያዎች የማሳየት ስራዎች አልፎ አልፎ ታይተዋል።እንደዚህ በ ቤተክርስትያኒቱ መዋቅር ስር ባለ መልክ ተከታታይ የቴሌቭዥን መርሃግብር ሲቀረፅ ግን አዲስ ይመስለኛል።ስለ አዲሱ መርሃግብር መጀመር ከ ማህበረ ቅዱሳን ድረ-ገፅ ላይ የተገኘው ዜና እንዲህ ይነበባል:-''በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ማኅበረ ቅዱሳን ከጥቅምት 4 ቀን 2005 ዓ.ም ጀምሮ ዘወትር በየሳምንቱ እሑድ ጧት ከ3፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት የሚቆይ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ሰርቪስ ቴሌቪዠን (EBS TV) ለመጀመር ሙሉ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገለጠ፡፡በማኅበረ ቅዱሳን ኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ፥ የሬድዮና ቴሌቪዠን ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ዲያቆን ሄኖክ ኀይሌ ለመካነ ድራችን በሰጡት መግለጫ፡- ማኅበሩ ከተመሠረተበት ጊዜ አንሥቶ ላለፉት ሃያ ዓመታት በልዩ ልዩ የኅትመት ውጤቶች እንዲሁም በመካነ ድር (website) እና በሬድዮ አማካኝነት በሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ትምህርት ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው፤ አሁን ደግሞ በልዑል እግዚአብሔር ፈቃድ በሳምንት አንድ ጊዜ የ30 ደቂቃ መርሐ ግብር ለመጀመር ትናንት መስከረም 11 ቀን 2005 ዓ.ም ከኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን የሥራ ሓላፊዎች ጋር ለአንድ ዓመት የሚቆይ ስምምነት ማኅበሩ መፈራረሙን ገልጸዋል፡፡'' 1 ይላል ።ይህ በሃገር ቤትም በ ውጭም ለሚኖረው ለቀደመው ትውልድ፣አሁን ላለው ትውልድ እና ለመጪዎቹ ትውልዶች እጅግ ጠቃሚ ተግባር ነው።
ለቀደመው ትውልድ:-ስለ ቤተክርስቲያን የነበረውን አስተሳሰብ፣ይረዳበት የነበረውእይታ በበለጠ መንገድ  በስጋዊም መንፈሳውም ህይወቱ  የሚረዳበት ብሎም ለተቀረው ዓለም አንገቱን ቀና አድርጎ የሚያስረዳበት እንደሚሆን እገምታለሁ።
 
ለ አዲሱ ትውልድ :-የ እዚህ አይነት የ ቴሌቭዥን መርሃግብር  አዲሱን  ትውልድ ከዘመኑ ሉላዊነት (globalaization) ፈተናዎች አንዱ ከሆነው የ እራስን ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ሀብት የማስጣልና የ ባእዳንን አምላኪ  የመሆን አባዜ ለመከላከል፣ ሃገሩን እና ቤተክርስቲያኑን በሚገባ እንዲረዳ፣ ለሕዝቡ ችግሮች ሁል ጊዜ ከ ባህር ማዶ መፍትሄ ከመፈለግ ማንነቱን እንዲያውቅ ፣ በስጋውዊም ሆነ በ መንፈሳውው ሀብት  (በ ሁለት ሰይፍ የተሳለ) የመሆን እድሉን ከመክፈቱ በላይ ሰላማዊ፣ ስነ-ምግባር  የተላበሰ፣ ከ ችኩል ባህሪ የራቀ ፣በ እርጋታና በማስተዋል እንዲራመድ የሚረዳው እንደሚሆን ማስታወስ ተገቢ ነው።
 
 
ለሕፃናት :- ''መጭውን ዘመን እንድነግርህ ሕፃናቱን እንዴት እያሳደግህ እንደሆነ  ንገረኝ'' የሚለው አባባል ትልቅ ቁም ነገር የያዘ ነው። በሀገር ውስጥም ሆነ በ ውጭ በተለይ በከፋ መልኩ ማንነታቸውን የዘነጉ ልጆች ማግኘት ብዙ አስቸጋሪ አይደለም። ወላጅ ጊዜ ከማጣትም ሆነ እንዴት አድርጎ ማስተማር እንዳለበት ግራ በመጋባት ሳቢያ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር በ እጅጉ እየተራራቁ የሚሄዱበት ሁኔታ የሰፋ ነው። ለ እዚህ ሁሉ መፍትሄው እንደ እዚህ አይነት የ ቴሌቭዥን መርሃግብሮችን ለ ሕፃናት እንዲመለከቱ ማድረግ ነው።
 
 እርግጥ ነው  ቤተ ክርስቲያን  ቀደም ብሎ የ እዚህ አይነት ሚድያ በ ሃገር ቤት ሊኖራት ይገባ ነበር፤መንግስትም በ አንድ በኩል ልማትን ለማስፋፋት ፍጹም ቁርጠኝነት ካለው  ምዕመናኗ እንዳይታወኩ፤አስተዳደራዊ ችግሮች እንዲፈቱ ተገቢውን እገዛ በማድረግ ብዙ ችግሮች ከወዲሁ እንዲመክኑ የማድረግ  ፤ በ ሌላ በኩል  ከ ቤተ መንግስት በር እስከ ገጠር መንደር ድረስ መዋቅር ያላትን ቤተ ክርስቲያን ከ ፖለቲካዊ መንፈስ በ ራቀ እና የ እራስዋን አስተዳደራዊ እና የ ልማት ስራዎችን እንድታከናውን ከ እዚህም በዘለለ መንገድ በነጻ ሊያገለግሏት የተዘጋጁትን በ ሚልዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች እንድትጠቀም ያሉባትን ችግሮች በመቅረፍ ሂደት የማገዝ ሚና መንግስትም ሊኖረው  ይገባዋል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
 
እነኝህን ችግሮች ለመፍታት የ መገናኛ ብዙሃን ያውም ቴሌቭዥን አስፈላጊ ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ ስራ ደግሞ ሶስቱን መሰረታዊ ሃብቶች ማለትም ጊዜ፣የ ሰው ሃይል እና ገንዘብ መፈለጋቸው የግድ ነው። በ ሃገር ቤት ብቻ ሳይሆን በውጭ የሚኖሩ ምዕመናን በ እጅጉ ሊደግፉት የሚገባ፤ ከ ስጋዊም ሆን መንፈሳዊ ጸጸት የሚያድን እና  ለ ህሊናም የ ሃገርንም የቤተ ክርስቲያንንም ጉዳት እያዩ ከመቆጨት የሚያድን ትልቅ ተግባር ይመስለኛል።
ለ ቴሌቭዥን ፕሮግራም ማስታወቂያነት የተለቀቀውን አጭር ቪድዮ ይህንን በመጫን ይመልከቱ:-
 

No comments: