የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እየደረሰባት ያለውን ቃጠሎ፣ምእመናኖቿን ላይ የደረሰው እንግልት እና ስደት እንዲቆም ሶስት ዓላማዎች የያዘ ጥያቄ መንግስትን ለመጠየቅ ለመስከረም 4 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የነበረው ዕቅድ ለጥቅምት 30 መተላለፉን አስተባባሪው ኮሚቴ ዛሬ መስከረም 2/2012 ዓም ገልጧል።ሰልፉን በተመለከተ ጉዳያችን ላይ የወጣው ዝርዝር ዘገባ ለማንበብ
ከላይ የተጠቀሱት መልካም ገፅታዎች የድል መጨረሻ ተደርገው የሚቆጠሩ አይደሉም። በትንሽ ነገር የረኩ መስሎ መቅረብ በራሱ ትልቁ ችግር ነው።በአሁኑ ደረጃ ምንም የተሰራ ነገር የለም።ከላይ የተጠቀሰው መልካም ተፅኖ እንዳለ ሆኖ ፣በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያጠላው ጥላ ግን ገና አልተገፈፈም።ይልቁንም በእንቅስቃሴው ሳብያ የኦሮዶክሳውያኑ መነቃቃት ለበታኝ ኃይሎች እንደ ድንገተኛ መብረቅ አስደንግጧ ቸዋል።ቀድሞም በስጋት ሲያዩአት የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ለመጉዳት አሁን በደነበረ መንፈስ ምንም ከማድረግ አይመለሱም።ከእዚህ በተጨማሪ መንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉት የፅንፍ ኃይሎች የመንግስትን ፖሊሲ የሚያስፈፅሙ መስለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመጉዳይ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።ሰሆነም አሁንም ችግሩ ገና ግዙፍ ነው።
1ኛ) የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ እራሱን በሚገባ ማጠናከር አለበት።ይሄውም ግብ እና የውስጥ መተዳደሪያውን አዘጋጅቶ ከኮሚቴ በዘለለ ስያሜውን ከፍ አድርጎ እና የስራ ዘርፍ አውጥቶ መንቀሳቀስ፣
3ኛ) ከኮሚቴ ከፍ ባለ ደረጃ የተደራጀው ኮሚቴ ውጫዊው የቤተ ክርስቲያኗ ጉዳይ ላይ ከማትኮሩ በተጨማሪ የማኅበራት ሕብረት ከመፍጠር ባለፈ የቤተክርስቲያን ውስጣዊ አስተዳደር ማዘመን ላይም በውስጡ ያሉትን አካላት የማስተባበር ስራውን መቀጠል፣
4ኛ) የጥያቀዎቹ ምላሾች በተለይ ቤተ ክርስቲያንቷን ከሚገዳደሯት አካሎች አንፃር ፈረንጆቹ እንደሚሉት ''የካሮት እና ዱላ'' ፖሊሲ መከተል ።ቤተ ክርስቲያንን የሚገዳድሯት አካሎች በፀሎት እና በልመና የሚመለሱ አይደሉም።በሰላማዊ መንገድ ካሮት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ተፅኖ መፍጠርያ ልዩ ልዩ መንገዶች ማቀድ ያስፈልጋል።ከእዚህ ውስጥ አንዱ ሰልፍ ሊሆን ይችላል።ሰልፍ ግን ባብዛኛው ትልቅ የተፅኖ መፍጠርያ መንገድ ይሆናል እንጂ ሌሎች ሰላማዊ የተቃውሞ መንገዶች እና የሕግ አገልግሎት ሁሉ የያዘ ጠንካራ አካሎች ያስፈልጋሉ። ይህ አሰራር በተለይ በመንጋ ለሚያስቡ የፅንፍ ኃይሎች ትምህርት ሰጪ በሆነ መንገድ የማስፈፀም አቅሙን ያሳድገዋል፣
5ኛ) ኦርቶዶክሳዊነት ላይ ያጠሉት ጥላዎች ፅንፍ የያዙ አክራሪ እስልምና ኃይሎች፣ የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) እና ሌሎች ስጋቶች ዙርያ ጥርት ያለ መረጃ ኮሚቴው መስጠት ወይንም ልዩ የማንቅያ ትምህርቶች እንዲሰጡ መግፋት።
6ኛ) እንቅስቃሴው ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ መልክ እንዲይዝ እና ሁሉን አቃፊ እንዲሆን ማድረግ እና ከመንግስት የተጠየቁት ምላሾች ከተገኙ በኃላ ኮሚቴው እራሱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ እና በአባቶች ቡራኬ ማቆየት የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።
ምዕመናን ሁለት ቁልፍ ተግባራት ይጠበቅባቸዋል። አንድኛው በሕበረትም ሆነ በግል በየትኛውም ቦታ በሀገር ፍቅር ጉዳይ፣በሀገር አንድነት ጉዳይ ላይ ሁል ጊዜ ቀዳማዊ ተፅኖ ፈጣሪ መሆን እና ከአስተባባሪ ኮሚቴው የሚመጡ መመርያዎችን በማክብበር በህብረት ተፅኖ የመፍጠር አቅሙን ማሳደግ። የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።
አዎን! ኦርቶዶክሳዊው ማኅበረሰብ ላይመለስ ተነስቷል።ለኦርቶዶክሳዊውም ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ አጀንዳ የለም። ኦርቶዶክሳዊው ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነቱን ደግሞ ማንም እንዲነጥቀው ዕድል መስጠት የለበትም።የኢትዮጵያን ዕጣ ከሚወስኑት የሀገሪቱ ባለመብት ዜጎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኦርቶዶክሳውያንን ዘሎ ምንም አይነት ፖሊሲ መቅረፅ እንደማይቻል አሁንም ትምህርት ሰጪው መሆን ያለበት ኦርቶዶሳዊው ወጣት ነው። በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሕይወት ውስጥ ሁሉ የኦርቶዶክሱ ማኅበረሰብ መብቱን የማስከበር ሚና በከፍተኛ ደረጃ የማሳደግ ስራው አሁንም የሁሉም ባለ ድርሻ አካል ግዴታ መሆኑን ማወቅ አለብን።ስለሆነም የሰላማዊው ሰልፍ ወደ ጥቅምት 30/2012 መራዘም ከላይ የተጠቀሱትን ተባራት ከማከአወን ባለፈ የመደራደር አቅምን የሚያሳድግ ዕድል ከመስጠቱ በላይ አደረጃጀቱ እስከ ገጠር ድረስ የመድረስ እና ተፅኖ የመፍጠር አቅም ማሳደግ አስፈላጊ ነው።
ከመስከረም 4 ቀን በአዲስ አበባ የተጠራው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
++++++++++
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ካህናት፣ ሰባኪያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ኅብረት፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ና ምሩቃን እና የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች እና በመስከረም 4 ቀን በዲስ አበባ ሊካሄድ የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች ሰላማዊ ሰልፉን አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
በአገራት የታሪክ ግንባታ ላይ የሃይማኖት የተቋማት አስተዋጽኦ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተለይ ተቋማቱ ከአገራቱ እድሜ የማይተናነስ የዘመን ርዝማኔ ሲኖራቸው ከሚተረከው የአገሪቱ ታሪክ ላይ የእነርሱ እጅ ያልገባበትን፣ አሻራቸው ያላረፈበትን ዘርፍ ለይቶ ለማውጣት እስኪከብድ ድረስ የአገር ታሪክ እና የሃይማኖት ተቋሙ ታሪክ እንደ ድርና ማግ የተገመደ ሲሆን ይስተዋላል፡፡
በአገራችን በኢትዮጵያ ያለውም እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የሌሎቹ እምነቶችና ባህሎች አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያን ያለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማሰብም ሆነ የወደፊት እጣዋንም በአዎንታዊ መንገድ መተለም ፈጽሞ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ የቤተ ክርስቲያኗን ስም ሳያነሱ ለመተረክ መሞከር እስከሚያዳግት ድረስ ቤተ ክርስቲያን የአገር የልብ ትርታ ሆና ኖራለች፡፡ በአገራችን ስልጣኔ ላይ ዘርዝሮ ለመጨረስ የሚያዳግት አሻራን አሳርፋለች፡፡
ምእመኗን ሌት ከቀን ስለሳላም በማስተማር እርስ በእርሱ በመከባበር እና በፍቅር ከመኖር አልፎ የሌላውን እምነት እና ባሕል አክብሮ እንዲኖር አድርጋለች፡፡ ትምህርት የመንግስት የፖሊሲ አካል ባልነበረበት ዘመን ትምህርት ሚኒስተር፣ ባህል እና ቱሪዝምን ማሳደግ ቦታ ባለገኝበት ዘመን የባህል እና የቅርስ ጠባቂ ሆናለች፡፡
አገር በተወረረበት ዘመን ጽላቷን ሳይቀር ተሸክማ ከጦሩ ፊት ተሰልፋለች፡፡ ዓለምና አገር ለሥነ- ጽሑፍ፣ ለሥነ ሥዕል፣ ለኪነ- ጥበብ፣ ለኪነ-ሕንጻ እና መሰል ጥበቦች ባእድ በነበረበት ዘመን ለአገራችንና ለዓለም እስከ ዛሬ የሚመራመርበትን የጥበብ ፋና አብርታለች፡፡ ከግብርና እስከ ሥነ ከዋክብት፣ ከዘመን አቆጣጠር እስከ መድኃኒት ቅመማ፣ ከሕግ ቀረጻ እስከ ደን ልማት፣ ከቤተሰብ አስተዳደር እስከ ስነ-መንግሥት፣ ከዜማ ፈጠራ እስከ ማኅበራዊ እሴት ግንባታ ያላትን ኃብተ ጥበብ ሁሉ ለኢትዮጵያ እያበረከተች ከራሷ ሕልውና በላይ ስለ አገር ኖራለች፡፡ በየትኛውም የታሪክ ዕይታ እና መንገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ሊደራደር ከመጣ አካል ጋር ለውይይት የተቀመጠችበት ዘመን የለም፡፡ እርሷ እየነደደች እና እየከሰመች አገርን አጽንታለች፡፡ ለዚህ ውለታዋ ግን ወሮታ የጠየቀችበት፣ ለዚህ መስዋእትነቷ ዘካሪ የሻተችበት ዘመን የለም፡፡
ይሁንና ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጡት የመንከስ ያህል አጠያያቂ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ካህናት እና ምእመናን ተወልደው ባደጉባት ምድር ታርደዋል፣ ያፈሩት ሃብት ንብረትም ሁሉ የእሳት አሊያም የቀማኛ ቀለብ ሆኗል፤ከሕጻን እስከ አረጋዊ፣ ካልጋ ቁራኛ እስከ ነፍሰ ጡር ድረስ ኦርቶዶክሳዊያን አንስቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍረዋል፡፡ መከራ የበረታባቸው ለዘመናት የኖሩበትን ቀየ ለቀው ወደማያውቁት ቦታ ተሰደዋል፡፡ በጠረፉ የኢትዮጵያ ክፍል የተጀመረው ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ወደ መሃል ከተማ በሚያስደንቅ ፍጥነት እየገሰገሰ ይገኛል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ምእመናን ከዛሬ ነገ ጉዳዮን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ይፈቱታል በሚል ተስፋ የየመንግስት ተቋሙን በር ስናንኳኳ ቆይተናል፡፡ ቢሆንም ጩኽታችንን በሚፈለገው ፍጥነት የሚሰማ የሚፈታም ሆነ መልስ የሚሰጥ አካል አልታየም፡፡ ከዚህም ሲያልፍ ለሁሉም ችግር ኃይል እና ነውጥ መፍትሔ ተደርጎ በሚወሰድበት በዚህ ዘመን ለሰላም እና ለአገር ባለን ጥልቅ ፍቅር ሕጋዊ ጥያቄ አቅርበን በሕግ ከተሾመው ሕጋዊ አካል ሕጋዊ መፍትሔ መፈለጋችን በሚያሳዝን ትርጉም እየተሰጠው እና ከፍርሃት እየተቆጠረ መሳለቂያ ከመሆን የዘዘለ ጠብ የሚል መፍትሔ ሊመጣ አልቻለም፡፡
በመሆኑም እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ከተማ የምንገኝ ካህናት፣ የሰባኪያን እና ዘመሪያን ኅበረት፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ፣ የመንፈሳዊ ማኅበራት ማኅበራት፣ የወጣቶች እና የጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት፤ የነገረ መለኮት ምሩቃን እና የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ኅብረት፡ በመስከረም 4 ቀን 2012 ዓ/ም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ጥሪ ማድረጋችን ይታወቃል፡፡
ይህ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ከቀረበበት ማግስት ጀምሮ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ራስ ከሆነው ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጀምሮ፣ በአገርም ይሁን በውጩ ዓለም ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በአንድ ልብና መንፈስ በታላቅ ቁጭት ያሳየውን የመንፈስ ዝግጅት እና ተነሳሽነት በቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ነበር፡፡ ከብረት የጠነከረው ይህ የኦርቶዶክሳዊያን ኅብረት እና ተነሳሽነት እናቱ ስትታመምበት እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ አርፎ እንደማይተኛ እና የትእግስቱን ያህል ቁጣውም ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ ለብዙዎች ትልቅ ትምህርት የሰጠ እንደሆነ ሁሉም የተረዳው እውነታ ነው፡፡
በተጨማሪም ስለ አገር ሰላም፣ ስለ ሕዝቦች አንድነት፣ ፍትሕና እውነተኝነት የሚገዳጋቸው የሌሎች እምነቶች ተከታይ ወንድም አኅቶቻችን ሁሉ ህመማችንን ተጋርተው ከጎናችን እንደሚቆሙ እየገለጹልን ይገኛሉ፡፡
ዛሬ በጋራ መሰለፋችን እና ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ክብር በአንድ መቆማችን በብዙ ልመና ሊከፈቱ ያልቻሉ ጠንካራ በሮችን ለማስከፈት ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት አስተባባሪ ኮሚቴው
1. ጳጉሜ 5/ 2011 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት ተወካይ፣ ከፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ከአዲስ አበባ ም/ከንቲባ እና ጽ/ቤት ተወካዮች ጋር
2. ጳጉሜን 6/2011 ከኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር
3. መስከረም 2/2012 ዓ/ም ከኦሮምያ፣ ከደቡብ፣ ከአማራ፣ ከሶማሌ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር በአካል ተገናኝተን ውይይቶችን የጀመርን ሲሆን ከሐረሪ እና ቤኒሻንጉል ክልሎች እና ከድሬዳዋ መስተዳድር ጋር ለውይይት ቀጠሮ ተይዟል፡፡
4. መስከም 2/2012 ዓ/ም ከፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ አዲስ አበባ፣ ኦሮምያ፣ አማራ፣ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ ድሬዳዋ እና ሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በነዚህ ውይይቶችም ከአሥር ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ኮሚቴው ይዞት የተነሳውን እና ቤተ ክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለመፍታት በየክልሎቹ ዝርዝር ማስረጃ ቀርቦ ውይይት እንዲደርግባቸው እና ለጥቄዎቹምምላሽ እንዲሰጣቸው እና በቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ከላይ ከተጠቀሱት የመንግስት አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በባለቤትነት ችግሩን ለመፍታት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ .
በመንግስት ጥያቄያችንን ሁሉ ይመልሰዋል የሚል እምነት ባይኖረንም በየደረጃው ያሉ አካላት ቸልታ እና የማናለብኝነት ስሜት ወጥተው ለቤተ ክርስቲያናችን ዘብ ሲቆም መመልከት እንሻለን፣ አገራችን ደጋግመን እንደምለው አንዳንዱ የፈለገውን ከሕግ የተጻረረ ተግባር በተለይ በኦርቶዶክሳዊያን ላይ እየፈጸመ ያለአንዳች ጠያቂ የሚኖርባት ሌላው ደግሞ ስለአገር እና ስለአንድነት በሚወስደው ኃላፊነት የተሞለበት አካሄድ እየተገፋ ከሌሎች ጋር ሲገነባት በኖራት አገር ላይ ባይተዋር ሆኖ የሚሰደድባት አገር መሆኗ ተቋጭቶ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እጁን ያነሳ ሁሉ የሚጠየቅባት፣ ጣቱን የቀሰረው ሁሉ የሚሰበስብባት ለፍትህ የሚተጋ መንግስት ያለባት አገር ስትሆን መመልከት ሕልማችን ነው፡፡
እየጮህን ያለነው የኦርቶዶክሳዊያን ብቻ ሰላም ይከበር ብለን አይደለም፣ የእምነት ነጻነት ሰፍኖ አገራችን በእምነታቸው የተነሳ የተደፉ አንገቶች ቀና ብለው ሁሉም በመከባበበር የሚኖርባት ሰላማዊ አገር ስትሆን ለመመልከት ነው፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ከራሳችን እምነት ተከታዮች ጎን ብቻ ሳይሆን በእምነታቸው የተነሳ ከሚገፉት ጎን ሁሉ በማስመሰል መንፈስ ሳይሆን ከአያት ቅድም አያቶቻችን በወረስነው ለፍትህ የመወገን መንፈስ አብረን እንቆማለን፡፡ ለዚህ ነው ጉዟችን ኦርቶዶክስን ብቻ ሳይሆን አገርን ጭምር ለመታደግ የታለመ ነው የምንለው፡፡ በመሆኑም ስለሃይማኖታችን እና ሥለአገራችን ሰላም ስንል እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎቻችን እንኪመለሱ ድረስ ትግላችንን በሰላማዊ መንገድ እንደምንቀጥል ቃላችን የጸና ነው፡፡
የተከበራችሁ ኦርቶዶክሳያን እና ኦርቶዶክሳዊያት በዚህ መንፈስ እና ዓላማ ተቃኝቶ የተጀመረው የኅብረት ጉዟችን ከገዳም እስከ ከተማ ድረስ ካሉ አባቶች ጋር በመመካከር እና በጸሎታቸው በመታገዝ ከዚህ አድርሰነዋል፡፡ በብዙዎቻችሁ ውስጥ ያለው የመንግስት አካላት ቃል ከመግባት የዘለለ እርምጃ ላይሄዱ ይችላሉ የሚለው ስጋት ግን በእኛም ውስጥ ስላለ፤ ከላይ ያልናቸውን ጥያቄዎቻችንን በቅድመ ሁኔታ ጭምር አቅርበን እስክንወያይ እና የሚመጣውን ተግባራዊ ለውጥ ለመመልከት እስክንበቃ ድረስ ለመስከረም 4 ቀን 2011 ዓ/ም የጠራነውን ሰላማዊ ሰልፍ በሁለት ወራት በመግፋት የተገባልን ቃል የማይተገበር ከሆነ አሊያም የሚያረካ ካልሆነ ለጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ/ም ሰላማዊ ሰልፉ የሚደረግ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
እኛ የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች በሚደረገው በየትኛውም ውይይት ላይ ከራሳችን ፍላጎትም ይሁን አንዳንዶች ከሚሰጉት የፍርሃት መንፈስ በጸዳ ስሜት የቤተ ክርስቲያናችንን እና የእናንተን የእምነቱን ተከታይ ኦርቶዶክሳያን ፍላጎት እና ጥያቄ ብቻ አስቀድመን የምንቆም መሆናችንን በህያው እግዚአብሔር ስም ቃል እየገባን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ልጆች ሁሉ ያሳያችሁት ተነሳሽነት እና ኅብረት ሳይሸራሸፍ ለችግራችን ሁሉ ቁልፍ መፍትሔ በሆነው ጸሎታችሁ፣ በሃሳባችሁ እና በቻላችሁት ነገር ሁሉ ከጎናችን እንድትቆሙ በእናት ቤተ ክርስቲያን ስም ጥቄያችንን እናቀርባለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በምናደርገው እና በምናቀርበው ጥያቄ ዙሪያ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር የምንመካከርባቸው ሰፋፊ መድረኮችን የምናዘጋጅ እንዲሁም ቢያንስ በአሥራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ የተለያዮ መንፈሳዊ እና ሕዝባዊ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የእያዳንዱን የውይይት ሂደት፣ውሳኔ፣ውጤት እና ቀጣይ አቅጣጫ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ምእመናን እና የኦርቶዶክሳዊያን ሰላም እና ድኅንነት የሚያስጨንቃቸው አካላት ሁሉ የውይይቱ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ የምንጥር መሆናችንን ቃል እንገባለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የቤተ ክርስቲያናችንን እና የአገራችንን ሰላም ይመልስልን!!!!
መስከረም 4 ቀን በአዲስ አበባ የተጠራው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ
መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ