- ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ስለ ቀይባሕር አሁን የተናገሩት ''አቅጣጫ ለማስቀየር'' ነው የሚለው አሉባልታ ውሸት ለመሆኑ ግልጽ የሆኑ ማስረጃዎች አሉ።
=========
ጉዳያችን ምጥን
=========
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ስለ ቀይባሕር አሁን የተናገሩት አቅጣጫ ለማስቀየር ነው የሚለው አባባል ውሸት ለመሆኑ ግልጽ ማስረጃ
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሰሞኑን ከከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ላይ ገና ሙሉ ቪድዮው ያልተለቀቀ የቀይባሕርን አስመልክተው በተናገሩት ንግግር የቀይባሕር ጉዳይ የኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው ማለታቸውን የተለያዩ ዩቱበሮች የተለያዩ አስተያየቶች ሲሰጡ እየተመለክትን ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ ንግግር ገና አልተለቀቀም።ሙሉ ይዘቱ ሲለቀቅ የምንከታተለው ነው።
ይህ በእንዲህ እያለ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰሞኑን ስለ ቀይባሕር የተናገሩት አቅጣጫ ለማስቀየር ነው የሚለው ፈጽሞ ውሸት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን እንደመጡ በቅድምያ ከሰሩት ስራ ውስጥ የባሕር ኃይል መመስረት ነው።ከፈረንሳይ እስከ ዱባይ ለባሕር ኃይል ስልጠና ማነጋገር የጀመሩት፣ኢትዮጵያ ከ27 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የባሕር ኃይል አድሚራል ከመሾም ሰልጣኞች እስከ ማስመረቅ ያደረሱት ወደ ስልጣን እንደመጡ በጀመሩት ስራ ነው።
ይህ ብቻ አይደለም የመከላከያ ሚኒስትር ዓርማው ላይ የባሕር ኃይል ዓርማ ያከለበትም ከዓመት በፊት ነው። ከእዚህ በተጨማሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በፓርላማ የቀይ ባሕርን አስመልክተው የተናገሩት ንግግር ላይ ከአንድ ዓመት በፊት ሲናገሩ የቀይ ባሕር ጉዳይ የማይተው ጉዳይ ነው፣በሰላማዊ መንገድ ባሕር የማግኘት መብት እንዳለን፣ ይህንን አናደርግም የሚሉ ካሉ ቃል በቃል '' እኛም መረበሻችን አይቀርም '' የሚል ቃል አክለው ይህ ሰላም አያመጣም በሚል በግልጽ አማርኛ መንገራቸውን ጉዳያችን ታስታውሳለች።ከእዚህ ሁሉ በላይ ብልጽግና የኢትዮጵያ የእድገት አቅጣጫ የሚጠቁም ሰነድ አስመልክቶ ከአንድ ዓመት በፊት ስራ አስፈጻሚ ስብሰባ እንደተጠናቀቀ የወጣ መግለጫ ላይም የብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት እንደሚሰራ እና ይህ ተፈጥሯዊ መብቷ እንደሆነ አሁንም በግልጽ አማርኛ ጽፎ ነበር።
ይህ ሁሉ ማስረጃ እያለ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት ''አቅጣጫ ለማስቀየር ነው'' የሚለው አባባል ፈጽሞ ሚዛን አይደፋም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀድመው በግልጽ ተናግረዋል።አቶ ኢሳያስ ይህንን ተረድተው የአሰብ ወደብን ወግ ባለው መልክ ለኢትዮጵያ እንዲከፍቱ ለማግባባት ከሰላም ስምምነት እስከ የአሰብ ወሎ መንገድ ግንባታ እስከ በኤርትራ ላይ የተጣለው እቀባ ይነሳ ብሎ ተመድን እስከመጠየቅ ድረስ ተጉዘዋል። ይህም ሆኖ እስካሁን ለውጥ አለመምጣቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ወቅቱን አንብበው ቀድመው የጀመሩትን ሥራ እንደገፉበት የሰሞኑ ንግግራቸው ያሳያል እንጂ ድንገት ዛሬ የመጣ ሃሳብ እንደሆነ አድርጎ መናገር ሚዛን የማይደፋ እና ማስረጃ አልባ አገላለጽ ነው። ጉዳዩ እውነት ነው። ከአንድ መቶ ሃያ ሚልዮን ሕዝብ በላይ የሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በ30 ኪሎሜትር እርቀት ላይ ሆኖ የባሕር በር ሊነፈገው እንደማይገባ ይህ ፈጽሞ ሰላም እንደማያመጣ የኤርትራ ተወላጆችም ሆኑ አቶ ኢሳያስ ጠንቅቀው ያውቃሉ።
ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ መገኘቷን ከአሜሪካ እስከ ሩስያ፣ከቻይና እስከ ዱባይ የሚደግፉበት አምስት ምክንያቶች
- በዓለም ላይ የሚደረገው ንግድ አውሮፓን ከመካከለኛው ምስራቅና ከሩቅ ምስራቅ ጋር የሚያገናኘው የቀይ ባሕር በተባበሩት መንግስታት ግምት መሰረት በዙርያው አሁን ካለው ህዝብ ብዛት እኤአ 2050 ዓም 343 ሚልዮን የሚደርሰው ይህ አካባቢ አንድ ሺህ ኪሚትር እርዝመት ያለው የባሕሩ ክፍል አስር ሚልዮን የማይሞላ ህዝብ ባላት ኤርትራ ብቻ ሰላሙ ይጠበቃል ብለው ስለማያምኑ፣
- ቀይባሕርን ለመቆጣጠር አንዳንድ የመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት የያዙት አጀንዳ በምስራቁም በምዕራቡም ሀገራት በተለያየ የስጋት ደረጃ ላይ መውደቁ፣
- አሜሪካ፣ሩስያ ወይንም ቻይና በቀጥታ የቀይባሕርን በብቸኝነት መቆጣጠር ስለማይችሉ እና አንዳቸው አንዳቸውን ስለሚጠባበቁ ከእዚህ ሁሉ እንደኢትዮጵያ በህዝብ ብዛት ከ120 ሚልዮን ህዝብ ባላት ኢትዮጵያ ቢጠበቅ ያላቸው ፍላጎት መኖሩ፣
- አቶ ኢሳያስ የዕድሜያቸው መግፋት ተከትሎ በቀጣይ ኤርትራን የሚመራ ጠንካራ አመራር በሌለበት ሁኔታ አቶ ኢሳያስ በድንገት ቢያልፉ በኤርትራ በሚነሳው የስልጣን ሹክቻ ሀገሪቱ ወደየከፋ የእርስ በርስ ጦርነት ከገባች የቀይ ባሕር ባልተጠበቀ መልኩ በሽብርተኞች እጅ እንዳይወድቅ የሁሉም ኃያላን መንግስታት ስጋት ብቻ ሳይሆን የእስራኤልም ቀዳሚ ስጋት መሆኑ፣
- የመጨረሻው ምክንያት እጅግ ወቅታዊው የፍልስጤም እስራኤል ጦርነት መልሶ ማገርሸቱ፣አሜሪካ ጦሯን ወደ መካከለኛው ምስራቅ በብዛት መላክ መቀጠሏን አስታኮ የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት ከፈነዳ አንዱ ትኩረት የሚሆነው መንግስት አልባዋ የመንን የመፋለምያ ሜዳ አድርጎ ቀይባሕርን የማወከ ተግባሩ ስለሚባባስ ይህንን አሁንም ኤርትራ ለመቆጣጠር በሰው ኃይልም ሆነ በሃብት ፍሰት መቋቋም ስለማትችል አሁንም ለተለያዩ ኃይሎች ጋር በተለይ ጸረ ምዕራብ ከሆኑት ጋር የመዋዋል አደጋው አፍጥጦ በመምጣቱ፣
የሚሉት ዋና ዋና ሃሳቦች ውስጥ ሲሆኑ ቀይባሕር በህዝብ ብዛትም ሆነ በወታደራዊ ግንኙነት ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ያልተሞዳሞደ እና የተሻለ ኃይል ያላት ኢትዮጵያ በቀይባሕር መገኘቷ ለሁሉም አንዱ ገላጋይ ሃሳብ መሆኑን ያመኑበት ይመስላል።ለእዚህ ዓይነቱ ጉዳይ በቀዳሚነት የምትቀናቀን ግብፅ ስትሆን አንዳንድ የተዳከመች ኢትዮጵያን ማየት የሚፈልጉ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ከግብፅ ጀርባ የሚኮለኮሉ ይሆናሉ።
ለማጠቃለል ኢትዮጵያ መልሳ ከኤርትራ ጋር ወደ ደም መፋሰስ በባሕር ምክንያት እንድትገባ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የኤርትራ ተወላጆች ፍላጎት አይደለም። ይህ ግን ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር መውጫ የማግኘት መብትና እውነትን አይቀይረውም። ጉዳዩ ለትውልድ የሚሻገር ነው። ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍታት የሁሉም ግዴታ ነው። ጉዳዩን ግን ጠ/ሚ/ር ዐቢይ ሲናገሩት ስህተት፣ሌላው ሲያወራው እውነት ሊሆን አይችልም። እራሳቸው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የማይክዱትን እውነት ለማስተባበል አንሞክር።
===============////============