- ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
- የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው?
- የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት ተሰናበቱ ብሎ ታሪክ ይመዝግብ?
- ለጄነራል ጻድቃንን እና ጌታቸው ረዳ ሐብል ያጠለቀች ሀገር ለሣህለወርቅ ዘውዴ የማታጠልቅበት ምክንያት ሊኖር አይገባም።
======
ጉዳያችን
======
ኢትዮጵያ በወታደራዊው መንግስት ትመራበት ከነበረው የፕሬዝዳንታዊ የመንግስት ስሪት ወደ የጠቅላይ ሚኒስትር አመራር የመጣችው በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ ዘመን ነው። በእዚሁ የጠቅላይ ሚንስትር አመራር ዘመን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የማንኛውም ፓርቲ አባል ያልሆነ እና በስራ እና የትምህርት ዝግጅት የተ|ሻሉ የተባሉት እና ባለው ስርዓት አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ፕሬዝዳንቶች ሲሰየሙ ቆይተዋል።
በዘመነ ኢህአዴግ ከተሰየሙት ፕሬዝዳንቶች በተለየ እና ለረጅም ጊዜ በዲፕሎማሲው ዓለም አንቱ የተባለ ልምድ ያላቸው እና የመጀመርያ ሴት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ናቸው።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በቆዩባቸው ያለፉት ስድስት ዓመታት ዘመናት ሴቶች ወደ አመራርነት የመምጣታቸው አስፈላጊነት እና ይህንንም ውጤታማ እንዲሁን የበኩላቸውን ጥረት አድርገዋል። በእዚህ ጉዳይ ላይ ከሃገር ውስጥ እስከዓለም አቀፍ መድረኮች በርካታ ስብሰባዎች ላይ ይህንኑ ጉዳይ አስተጋብተዋል።
ያለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ባሳለፈቻቸው የውስጥ ፈተናዎች ፕሬዝዳንቷ በመንግስት የስራ አስፈጻሚው የዕለት ተዕለት ስራ ውስጥ መግባት ህጉም ስለማይፈቅድላቸው በአንዳንድ መንግስታዊ የሀገር ውስጥ ውስኔዎች የራሳቸውን ሃሳብ ለማንጸባረቅ እና እንዲህ ቢሆን የሚሉ ሃሳቦች እንደነበሯቸው አልፎ አልፎ በሚናገሯቸው ንግግሮች ተንጸባርቀዋል። ይህም ሆኖ ግን ፕሬዝዳንቷ በኢትዮጵያን መውደድ፣አንዱን ወገን ከአንዱ ላለማስበለጥ እና ለሰላም የጸና እምነት እንዳላቸው ማንም ጥያቄ አያነሳም።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 25፣2017 ዓም በትዊተር ገጻቸው ላይ የድምጻዊ መሐሙድ አሕመድ ''ዝምታ ነው መልሴ'' እና ''ለአንድ ዓመት ሞከርኩት'' የሚሉ ቃላት ያለው መልዕክት ከለጠፉ ጀምሮ መነጋገርያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።የሣህለወርቅ ዘውዴ ትዊተር ባሉበት ደረጃ ያሉ ችግሮችን በእዚህ መልክ መግለጽ አለባቸው ብዬ አላምንም። ለምሳሌ የማይስማሙበት ጉዳይ ሲኖር በስልጣን ዘመናቸው ውስጥ ሳሉ ስልጣን እለቃለሁ ማለት ይችላሉ።ወይንም ይህንን ያህል ከተጓዙ በኋላ የፓርላማ ስብሰባ ሊደርገ አንድ ቀን ሲቀረው በትዊተር ላይ ያለፉ ጉዳዮች ከሚያነሱ።አስተማሪ እንዲሆኑ ከፕሬዝዳንትነታቸው በኋላ በመጽሐፍ መልክ አልያም በሚድያ ቃለ መጠይቅ ያላቸውን ሃሳብ መግለጽ ይችሉ ነበር ብዬ አምናለሁ።ከእዚህ በተለየ ግን ክብርት ፕሬዝዳንቷ የመንግስት ስራ አስፈፃሚ የሚወስናቸው ውሳኔዎች እና የችግር አፈታት ላይ የተለየ አስተሳሰብ መያዛቸው ጤነኛ አስተሳሰብ ነው።መርሳት የሌለብን ክብርት ፕሬዝዳንቷ የብልፅግና አባል አይደሉም።ስለሆነም በአንድ ፓርቲ አስተሳሰብና ፕሮግራም አልታሰሩም። በኢትዮጵያ ሕገ መንግስትም ፕሬዝዳንት የሚሆነው ከፓርቲ አባልነት የተለየ ነው።
ክብርት ፕሬዝዳንቷ የግጭቶች አፈታት ላይ በጣም የለሰለሱ አካሄድ መከተል እንደሚገባ በተለያዩ ጊዜ ንግግሮቻቸው ገልፀዋል። ይህ የተለየ ሀሳባቸውን ለመግለፅ ቢፈልጉ የመንግስት ስራ አስፈፃሚ "እኛ ይህን የወሰንነው ብዙ ነገሮች አይተን ነው" ወዘተ በሚል አንዳንድ የመንግስት እና የፓርቲው የቡድን ውሳኔዎች ላይ አይግቡ ብሎ ይሆናል። ክብርት ፕሬዝዳንት ደግሞ የጉዳዮች አካሄዶች ሊያስጨንቋቸው ይችላሉ።
እዚህ ላይ ክብርት ፕሬዝዳንቷን ለማንቋሸሽ ብልፅግና ያላዘዛችሁን ክጣርያ በላይ ለመጮኽ የምትሞክሩ ከካድሬ በላይ ካድሬ ለመሆን የምትጋጋጡ አደብ ብትገዙ።በሌላ ጫፍ ደግሞ ክብርት ፕሬዝዳንቷ ይህን አሉ እያላችሁ የዩቱብ ፕሮፓጋንዳችሁ የማረጋገጫ ማኅተም የተመታላችሁ ይመስል "እምቧ ከረዩ" የምትሉ እና የዘር የብልቃጥ መርዛችሁን ለመነስነስ የምትሞክሩ ብትሰክኑ ጥሩ ነው።
ክብርት ፕሬዝዳንት የሀገር ሀብት ናቸው።ቢቆጡ፣ለምን ይህ አልሆነም ቢሉ በሀሳቡ ላይ መነጋገር እንጂ መነታረክ አያስፈልግም። ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ፣ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅን አክብረው ለማነጋገር፣ለሚሰማቸው ቅሬታና ጥያቄም በትሕትና ለማስረዳት የሞራልና የግብረ-ገብነት ችግር ያለባቸው አይደሉም። ስለሀገር ሲባል ብዙ ከተሳደበ ጌታቸው ረዳ ጋር ለማውራት ዐቢይ አልተቸገሩም። ክብርት ፕሬዝዳንት የተከበሩ ሰው ናቸው።የተለየ ሀሳብ ሊኖራቸው ይችላል። ሀሳቦቻቸውን ከፕሬዝዳንት ዘመናቸው በኋላም ማካፈላቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ።የሀሳብ ልዩነት ለዘላለም ይኑር! ይህ በእንዲህ እያለ ሰኞ መስከረም 27/2017 በኢትዮጵያ ፓርላማ የተደረገው የአዲስ ፕሬዝዳንት ስየማ ላይ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የስንብት ንግግር ሲያድርጉ አለመታየታቸው ብቻ ሳይሆን መንግስታዊ የሆነ የምስጋና ቃላት ከአፈ ጉባዔውም ሆነ የፕሬዝዳንት ስየማውን አስመልክተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ባስተላለፉት የትዊተር መልዕክት ላይ አልገልትጹም። ይህ በጣም አሳፋሪ አሰራር ነው። ይህ በኢትዮጵያ ልክ የታሰበ አስተሳሰብ አይደለም። ለጄነራል ጻድቃንን እና ጌታቸው ረዳ ሐብል ያጠለቀች ሀገር ለሣህለወርቅ ዘውዴ የማታጠልቅበት ምክንያት ሊኖር አይገባም። በትዊተር ላይ ያውም ያልተብራራ ነገር ተጻፈ ብሎ የሚያኮርፍ ኢትዮጵያን የተረከበ መንግስት ከረሜላውን እንደነጠቁት ህጻን ሲያኮርፍ ማየት ያሳፍራል። መንግስት ስንሆን እንቻል እንጂ፣ዲሞክራሲን ስናሽቀነጥር በእዚህ ልክ መከስከስ ዋጋ ያስከፍላል።አይደለም ፕሬዝዳንት ማንም ሃሳቡን ቢገልጽ ለምን በመንግስት ደረጃ የሃገር ሃላፊነት የወሰዱ በተራ ካድሬ ልክ ለማሰብ እንደሚሞክሩ አይገባኝም።
አሁንም ነገሮችን ማረም ይገባል።ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ በፓርላማ የስንብት ንግግር ቢናገሩ ምን የተለየ የሚያስፈራ ነገር ይናገራሉ? ቢበዛ ስለሰላም አስፈላጊነት፣ስለሙስና፣ስለ ዜጎች መፈናቀል ነው። ይህንን እርሳቸው ባይናገሩስ ጸሃይ የሞቀው ጉዳይ አይደለም ወይ? አሁንም ቢቻል ፓርላማው እንደገና ተሰብስብስቦ የመሰናበቻ ንግግር እንዲያደርጉ መፍቀድ።በመቀጠል ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሌ በብሔራዊ ቤተመንግስት ለቀድሞ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የክብር ሽኝት እንዲደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም እንደልጅ ዝቅ ብለው ሰላምታ ሲለዋወጡ ማየት እንፈልጋለን። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት ተሰናበቱ ብሎ ታሪክ ይመዝግብ? ነገሮች ታርመው ፕሬዝዳንቷ በፓርላማ ንግግር ማድረጋቸው እራሱ የነገሮች የማረም ታሪክ ሆኖ ይጻፋል። ዛሬ ሣህለወርቅ በፓርላማ የስንብት ንግግር ባያደርጉ የሚሉት ነገር ካላቸው ከቤተመንግስት ሲወጡ ሁሉን ይሉታል። ያለነው በ21ኛው ክ/ዘመን ነው። አሁንም የምለው የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።
==================/////===============
No comments:
Post a Comment