ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, February 22, 2019

ይድረስ ለተከበሩ ለአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ

 Bildergebnis für takele uma

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ 

ጉዳያችን /Gudayachn
የካቲት 16/2011 ዓም (ፈብሯሪ 23/2019 ዓም)
  • ክቡር ምክትል ከንቲባ ስድስት መቶ ሐያ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ የኦሮምያ ተወላጆችን ከሱማሌ ኦሮምያ ድንበር ብቻ ከሚያስመጡ የጎንደር ተፈናቃዮችንም፣የጉጂ ዞን ተፈናቃይም፣የቤንሻንጉል ተንከራታችንም እና ሌሎችንም አምጥተው በአዲስ አበባ ዙርያ አስፍሩልን እና አዲስ አበባ የበለጠ ሕብረ ብሔርነቷን ታድምቅልን።

ክቡር ምክትል ከንቲባ -

በቅድምያ የከበረ ሰላምታ እያቀረብኩ።ለጤናዎ እንዴት ሰነበቱ? ክቡር ምክትል ከንቲባ ለአዲስ አበባ ያለዎት መልካም ምኞት እና በሚያሳዩት ትጋት በአንክሮ እና በደስታ እየተከታተልን ነው።ቀደም ብለው ከኪነጥበብ ሰዎች ጋር የአዲስ አበባ ማኅበራዊ ችግር አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር ለስራው ያለዎትን ቁርጠኝነት እና ችግሩን በምን ያህል ደረጃ እንደተረዱት ገልጠው ነበር።ይህንኑ ንግግርዎን ተከትሎም በአዲስ አበባ የጎና ተዳዳሪዎች ዙርያ የተጀመሩት ስራዎች እና እርስዎም የአዲስ አበባ የምሽት ብርድ ሳይበግርዎት የጎዳና ተዳዳሪዎችን በማሰባሰቡ ሥራ ላይ ሁሉ መሳተፍዎ እንደማንም  በጎ እንደሚያስብ ኢትዮጵያዊ እኔንም አስደስቶኛል።ወደፊትም ይህ ቅዱስ ተግባር ሊቀጥል እንደሚገባው ከሚያስቡት ሰዎች ውስጥ ነኝ።

በቅርቡ ከአዲስ አበባ መምህራን ጋር ባደረጉት ውይይትም የገበሬ ልጅ መሆንዎን እንዴት ተቸግረው እንደተማሩ እና የአንድ መምህር አስተዋፅኦ ለአንድ ተማሪ ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን አንድ የስድስት ኪሎ አካባቢ ያለ ትምህርት ቤት መምህር ማበረታቻ የእርስዎን ሕይወት እንደቀየረ ሲያብራሩ መምህራኑን በሀሳብ ይዘዋቸው እረጅም እርቀት ሄደው ነበር።

ክቡር ምክትል ከንቲባ -
ከላይ የጠቀስኩት መንደርደርያ ዛሬ ለመላክ ከፈለኩት ጉዳይ ጋር ቀጥታ ተያያዥ አይደለም።የዛሬው መልዕክቴ ዋዜማ ራድዮ ላይ የተገለጠው አስደሳች ዜና ይመለከታል።ዜናው ''ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች በአዲስ አበባ እና በዙርያዋ በቋሚነት እንዲሰፍሩ በከተማው ቦታዎች እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው'' ይላል ዜናው።ይህ ዜና ትክክል ከሆነ እሰይ! ወንድሞቻችን ሊመጡልን ነው።አብሮ መብላት፣አብሮ መኖር፣ተሳስቦ እና አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ብሎ ክፉ ዘመንን ማሳለፍ በጣም አስደሳች ነው። ወትሮም የኢትዮጵያውያን ባህል ነው።ከደቡብ ምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ስድስት መቶ ሐያ ኪሎሜትር ርቀት ከጅጅጋ የምትርቀው አዲስ አበባ ላይ እነኝህን ወገኖቻችንን በብዙ ወጪ አሳፍረው አምጥተው ለአዲስ አበባ ዙርያ ውበት እንዲሆኑ ለማድረግ እየሰሩ መሆኑ ለኢትዮጵያውያን ሌላ አስደሳች ዜና ነው።

አዲስ አበባ እንደሚያውቁት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ተሰብስቦ የሚኖርባት ድንቅ ከተማ ነች። እንደሚያስታውሱት በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ስፍራዎች በርካታ ሕዝብ ተፈናቅሏል።ጎንደር አዘዞ ብቻ ከአርባ ሺህ ሕዝብ በላይ ተፈናቅሏል።ደቡብ ጉጂ ዞን እና ቴፒ፣ወደ ምዕራብ ስንሄድ ቤንሻንጉል እና ወለጋም ሕዝብ ተፈናቅሏል።

ክቡር ምክትል ከንቲባ : -
ከአዲስ አበባ ስድስት መቶ ሐያ ኪሎሜትር ርቀት የነበሩ ወገኖቻችን የኦሮሞ ተወላጆችን በአዲስ አበባ ዙርያ እንዲሰፍሩ ሲያደርጉ አርባ ሺህ የጎንደር ተፈናቃዮችንም አደራ አይርሷቸው።አዲስ አበባ ዙርያ አምጥተው ያስፍሩልን።ከጉጂ ዞን የተሰደዱትንም እንዲሁ በሌላው የአዲስ አበባ መውጫ በኩል አምጥተው ያስፍሩልን። ለምሳሌ ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉትን ከገርጂ ማዶ ካለው ተራራ ላይ ቢሰፍሩ፣ከጉጂ ዞን የተፈናቀሉትን በቡራዩ መስመር፣ ከጎንደር የተፈናቀሉትን ደግሞ በቢሸፍቱ መስመር ከቢሸፍቱ ማዶ እንዲሰፍሩ ቢደረግ  እና ከቴፒ የተፈናቀሉትን ከቡራዩ ወጣ አድርገው ቢያሰፍሩልን አዲስ አበባን እንዴት የበለጠ ውበት በጨመረላት ነበር ብዬ አስባለሁ። ሰፈራውን ከሱማሌ የመጡ የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ ከሚያደርጉ እንዲህ  ሕብረ ኢትዮጵያዊ ዙርያዋን በከበባት አዲስ አበባ በራሱ መኖር ለአዲስ አበቤ ትልቅ ዕድል ይመስለኛል። በተለይ ሰፋሪዎቹ የልዩ ልዩ ሙያ ባለቤት ስለሆኑ ለአዲስ አበባ አዲስ የኢኮኖሚ ጥቅም ያስገኛል።ለምሳሌ ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ በከብት እርባታ ስልጡን ስለሆኑ የአዲስ አበባ ሕዝብ የወተት እና ሥጋ ችግሩ ተፈታ ማለት ነው።ከጎንደር ተፈናቅለው በአዲስ አበባ የምያሰፍሯቸው ደግሞ የሩዝ እና የጤፍ እርሻ ጎበዞች ናቸው አሉ።ይህ ማለት ለአዲስ አበባ ሕዝብ መንግስት ሩዝ ከሕንድ ማስመታት ቀረለት ማለት ነው።ሱፐር ማርኬቶችም የፈረንጅ ሩዝ ከማገላበጥ የጎንደር ገበሬ ያመረተውን በጆንያ ማገላበጥ ጀመሩ ማለት ነው። ከቴፒ የተፈናቀሉት ደግሞ በቅመማ ቅመም እርሻ የሚያክላቸው የለም አሉ።ይህ ማለት ከደቡብ እየተጫነ የሚመጣ ቅመማ ቅመም በአዲስ አበባ ዙርያ ሲመረት የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ እንዴት እንደሚያስመነድገው አይታይዎትም?

ስለሆነም ክቡር ምክትል ከንቲባ ስድስት መቶ ሐያ ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ የኦሮምያ ተወላጆችን ከሱማሌ ኦሮምያ ድንበር ብቻ ከሚያስመጡ የጎንደር ተፈናቃዮችንም፣የጉጂ ዞን ተፈናቃይም፣የቤንሻንጉል ተንከራታችንም እና ሌሎችንም አምጥተው በአዲስ አበባ ዙርያ አስፍሩልን እና አዲስ አበባ የበለጠ ሕብረ ብሔርነቷን ታድምቅልን።

አክባሪዎ የጉዳያችን ገፅ አዘጋጅ

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Wednesday, February 20, 2019

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ሆነ በአቶ ለማ በኩል ከኢትዮጵያዊነት የወጣ የመስመር ለውጥ አለ ብዬ አላምንም።



ጉዳያችን / Gudayachn
የካቲት 14/2011 ዓም (ፈብሯሪ 21/2019 ዓም)
======================

ብዙዎች አጠቃላይ የለውጡን ሂደት በተናጥል ባለስልጣናት ድርጊት ለመለካት ፈጥነው ጫፍ የያዘ አመለካከት ለማንፀባረቅ ሲጥሩ መታዘብ ችያለሁ።በመጀመርያ የለውጡ ሐዋርያዎች የገብቡአት የፖለቲካ ከባቢ ሁኔታ በሚገባ የተረዳነው አይመስለኝም።ለውጡ ከተጀመረ ጀምሮ በሱማሌ ክልል የነበረው መፈናቀል፣የቤንሻንጉል ግድያ እና መፈናቀል፣የሲዳማ ግጭት፣የቡራዩ እልቂት፣በጠቅላይ ሚኒስትሩ  የተሞከረው የግድያ ሙከራ፣የወታደሮች ወደ ቤተ መንግስት ገብተው ለመረበሽ ያደረጉት ጥረት፣የሰሞኑ የለገጣፎ ማፈናቀል ሁሉ ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው።አንድ የለውጥ ሂደቱን በማደናቀፍ ከተጠያቂነት ለመዳን የሚጥሩ ኃይሎች ሥራ እና በሌላ በኩል ፅንፈኛ የኦዴፓን እጅ ለመጠምዘዝ የሚሞክሩ አክራሪዎች ናቸው።

አሁን ብዙ ሰው የሚጠይቀው ለምን ከስር ያሉ በደሎች ሲፈፀሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይንም አቶ ለማ ቶሎ እንዲታረም አያደርጉም? የሚል ተገቢ ጥያቄ ነው።አዎን ይህ መሆን አለበት።ሆኖም  አንድ እውነታ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አለ።ተቃዋሚዎች በሙሉ ወደ ሀገር ሲገቡ እና በእስር የነበሩ በሙሉ ሲፈቱ ቀድመው በኦህደድ ስር የነበሩ ከፅንፈኛ ዓለም አቀፍ አሸባሪ እንቅስቃሴ ተሳታፊዎች እስከ መሬት የቸበቸቡ ወንጀለኞች ቀስ በቀስ የኦህደድን ታችኛው መዋቅር እንደ ሸረሪት ድር  በማድራት ስፍራ ይዘዋል።

እነኝህ ግለሰቦች ደግሞ መዋቅራቸው ከሀገር ውስጥ እስከ ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ያደሩ ናቸው።በእየቦታው ብቅ የሚሉ ኢትዮጵያዊ ላይ በተለይ ''የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ስልታዊ ጠላቶች አከርካሪውን እንስበረው'' የሚሉትን ኢትዮጵያዊ ብሔር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ማድረግ ዋነኛ ተልዕኮ አድርገው ተያይዘውታል።በኢትዮጵያ ሱማሌ ውስጥ ባለፈው ግርግር እጃቸውን የነከሩ የውጭ መንግሥታት ነበሩ።ጉዳዩ እንደማይቻል ሲመለከቱ እጃቸውን ሰበሰቡ። ሰሞኑን ከቱርክ ይነሳል የሚባለው የጦር መሳርይ ጎርፍ በሚልዮን የሚቆጠር ዶላር የመደበ የባዕድ ሀገር ከወያኔ  እየተቀባበለ እና የወያኔ  የቀድሞ ደህንነት በሚያውቀው መስመር እያሳለፈ ካልሆነ በእዚህ መጠን እንዴት ሊገባ ይችላል?  መንግስትም የውጭ ኃይሎች መኖራቸውን አምኖ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሱዳን እና ቱርክ ጋር ንግግር ለማድረግ ማቀዱን እንስከመግለጥ የደረሰበት ጊዜ ነበር።

የለገጣፎ ጉዳይም የእጅ ጥምዘዛ ውጤት እንደሆነ መረዳት ቀላል ነው።ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና አቶ ለማ ተስማምተውበት ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ቢኖር  ተሳስቷል።ምክንያቱም ደብረ ፅዮን መቀሌ ላይ እየዛተ ምን ያህል ሞኝ ቢሆኑ ወይንም ቅድምያ የሚሰጠው ጉዳይ ሳይገባቸው ነው ስልሳ ሺህ ሕዝብ የሚፈናቀልበት ጉዳይ ላይ በውሳኔ ይስማማሉ  ብሎ ማሰብ የሚቻለው? ይህ  ከተራ የፖለቲካ ስሌትም አንፃር ጉዳዩ የእነርሱ ስምምነት ውጤት ነው ለማለት ይከብዳል።ይህ ማለት ግን የፅንፈኛው የሸረሪት ድር እያደራ በሁኔታዎች እንዳይከላከሉ ያደረጋቸው ጉዳይ አለ ወይ? ብሎ መመርመር  አይቻልም ወደሚል ጥያቄ አያመራም ማለት አይደለም።

በፖለቲካዊ ውሳኔ ሳትስማማ ግን በቡድን ውሳኔ ስትጠመዘዝ አስፈፃሚው ከህዝብ ጋር እንዲላተም ትተወዋለህ።ሌላ አማራጭ የለህማ! ውሳኔው የቡድን ሲሆን ደግሞ ክፋቱ በእርሱ መላተም አንተም መወቀስህ አይቀርልህም።ሆኖም ግን አሁንም  ሌላ አማራጭ የለም።ወዲህ የክልል ሕግ ጠርንፎ ይዞሃል፣ወዲያ ፅንፈኛ ተደራጅቶ ሕዝብ ይበጠብጣል፣ ማዶ የቀድሞ ገዢ ጦር ሊሰብቅ ያንኮራፋል።ይህ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እና አቶ ለማ የገቡበት  እውነተኛ ሁኔታ ነው።ይህንን በሚገባ መረዳት እና እንደ ለገጣፎ አይነት ግፍ የሰራው የታችኛው አካልን ሕዝብ ወጥሮ መያዙ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ለአቶ ለማ ጠቃሚ የሚሆነው እና ለውጡን ለማገዝ የሚረዳው ለእዚህ ነው።

መፍትሄው 
========
መፍትሄው ሁለት ነው።አንዱ ኢትዮጵያዊው ኃይል ፅንፈኛውን የማናፈጥ ሥራ መስራት አለበት።ፅንፈኛው ስርዓት እና ደንብ የሚገባው አይደለም።በዕብሪት እያስፈራራም ሊኖር አይገባም።እያከበርከው ለሀገር ሰላም ብለህ ብትኖርም አይረዳልህም።ይልቁንም ትዕቢቱ ያይላል። እንዳለፈው የነውጥ ትውልድ እስኪማር ሌላ አርባ ዓመታት  የመጠበቅ አቅም ደግሞ ኢትዮጵያ ያላት አይመስለኝም።ሕግ ጥሶ ሲመጣ  ከማናፈጥ ሌላ ምንም የቃላት ድርድር አያስፈልገውም።በእዚህ ለውጡን ትጠብቃለህ።ኦነግ ወደ አዲስ አበባ በመስከረም ወር 2011 ዓም የገባ ጊዜ አዲስ አበባን ለመበጥበጥ የታዩትን ሙከራዎች ሕዝብ በማክሸፉ በዕለቱ ብፁዕ አቡነ መርቆርዮስን ለመጠየቅ ድንገት የተከሰቱት ዶ/ር አብይ ያሳዩት ደስታ ከፊታቸው ለመረዳት የሰጡትን ቃለ መጠይቅ ተመልሶ ማዳመጥ ይጠይቃል።

ሁለተኛው መፍትሄ ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ ኢትዮጵያ የጎሳ ፈድራሊዝም ፈፅሞ እንደማይጠቅማት ግልጥ ባለ አነጋገር መናገር እና ፈድራልዝሙ በጎሳ መከለሉ የችግሮች ሁሉ መነሻ መሆኑን እንዲሁም  ፈድራሊዝም አስፈላጊ መሆኑን ግን በጎሳ መከለሉ ስህተት እንደሆነ ደግመው ለሕዝብ ማረጋገጥ አለባቸው።መስመራቸውን በግልጥ አለማስረገጥ ለደጋፊያቸውም ግራ ያጋባባቸዋል። በኦሮምያም፣ደቡብ፣ጋምቤላ፣አማራ፣አፋር እና መሃል ሀገር ያሉ የትግራይ ተወላጆች ሳይቀሩ ትልቁ ስጋት የጎሳ ፈድራሊዝም ነው።ይህንን በግልጥ መኮነን ማለት ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ የምርጫ ዘመቻቸውን በመጀመር ሕዝብ ከአሁኑ ከጎናቸው አሰለፉ ማለት ነው።

ባጠቃላይ ዶ/ር አብይ እና አቶ ለማ የፅንፈኛ የጎሳ ፖለቲካ አራማጅ ልሁን ቢሉም ሁኔታው ፈፅሞ አይፈቅድላቸውም።እነርሱም የእዚህ አይነት ድብቅ አጀንዳ ፈፅሞ ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ እኔን አያሳምነኝም።የወሰን አከላል ኮሚሽን አመራረጥ፣የሚድያ ነፃነት፣የጦር ሰራዊቱ እና ደህንነቱ አወቃቀር ላይ እየተሰራ ያለው ሁሉ ይህንን አያመለክትም።ይልቁንም ለፅንፈኛ አካል የሚያመች ሜዳ አይደልም።ሆኖም ግን ፅንፈኛው አካል ባገኘው ቀዳዳ ሁሉ በፍፁም አረመኔነት የሚወስደው እርምጃ የጎሳ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ አሸባሪ አክራሪዎች ሁሉ ወደ ኦዲፓ  ታችኛው መዋቅር ውስጥ እንደገቡ አመላካች ነው።ይህንን የታችኛውን መዋቅርም ለማፅዳት አቶ ለማ ብዙ መቶ አመራሮች በወረዳ ደረጃ ካባረሩ ገና ወራት መቆጠሩ ነው።ባጭሩ ለውጡ ከላይኛው አካል እንደመጀመሩ ታችኛው አካል የሞት ሽረት ትግል እንደሚያደርግ የታወቀ ነው።ኦዲፓ ፅንፈኛው አካሉን ድል ካላደረገ ሁሉን ነገር እንዳበላሸ ሊያውቀው ይገባል።

አሁን ያለውን የፖለቲካ አሰላለፍ እና አደጋዎች በተመለከተ ጉዳያችን ላይ ''መጪው የኢትዮጵያ ዘመን ብርሃን ወይንም ጨለማ ነው።ለሁለቱም እያንዳንዳችን ተጠያቂ ነን (የጉዳያችን ልዩ ወቅታዊ ትንታኔ)'' በሚለው ፅሁፍ ስር በረጅሙ ለማብራራት ስለሞከርኩ እርሱን አንብቡት 
=======/////===========


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Tuesday, February 19, 2019

የካቲት 12 ሰላሳ ሺህ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት የሰማዕታት ቀን የተወካዮች ምክር ቤት በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር እንዲወስን ይፈርሙ።

የተወካዮች ምክር ቤት እንዲወስን ፊርማዎን እንዲያሳርፉ በሰማዕታቱ ስም ይለመናሉ።
የካቲት 12 /1929 ዓም አዲስ አበባ ከሰላሳ ሺህ በላይ ነዋሪዎችዋ በ አንዲት ጀንበር ሰማዕትነት የተቀበሉባት ቀን ነበረች።በዓሉ ላለፉት አርባ ዓመታት በተለየ ደግሞ ላለፉት ሀያ ስምንት ዓመታት አከባበሩ ደብዝዟል።አከባበሩ መደብዘዙ አደጋ መሆኑን የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የካቲት 12/2011 ዓም ባቀረበው የምሽት ዜና እወጃ ላይ የታሪክ ባለሙያዎችንም አነጋግሮ አረጋግጧል።
በዓለማችን ላይ አይደለም ለሰላሳ ሺህ ሰማዕት ለአንድ ሰማዕትም ብሔራዊ በዓል ተደርጎ ታስቦ ይውላል።በኢትዮጵያም እስከ 1968 ዓም ድረስ የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀን ትምህርት ቤቶች ተዘግተው በመንግስት መስርያቤት ሳይቀር በከፍተኛ ደረጃ ተከብሮ ይውል ነበር።በ1968 ዓም በዓሉ አከባበሩ ዝቅ ብሎ ታስቦ ብቻ እንዲውል ያደረገው የደርግ መንግስት ነው።ከደርግ ዘመን በኃላ ላለፉት 28 ዓመታት በባሰ መልኩ በዓሉ የመገናኛ ብዙኃንን ሽፋን ሳይቀር በበቂ መልኩ ሳያገኝ ቀርቷል። ይህ በእራሱ ብሔራዊ አደጋ ነው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 12 ብሔራዊ የሰማዕታቱ የመታሰቢያ ቀን ሆኖ በብሔራዊ ደረጃ በመላዋ ኢትዮጵያ በአዋጅ እንዲከበር እንዲያደርግ ይህንን ፊርማ ማሰባሰብ አስፈላጊ ሆኗል።
የበዓሉ በብሔራዊ ደረጃ የመከበሩ ፋይዳ የአዲስ አበባ ከተማ እጅግ አሰቃቂ ውጣ ውረድ አልፋ እዚህ መድረሷን ብቻ የሚያሳይ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ዘር፣ቋንቋ እና ኃይማኖት ሳይለያያቸው በደም በተለወሰ መስዋዕትነት የገነቧት ሀገር መሆኗን ለትውልዱ የማስተማርያ አይነተኛ መንገድ ነው።
ስለሆነም ይህንን ፊርማ በመፈረም እና ላልሰሙም በማካፈል ኃላፊነትዎን ይወጡ!
የካቲት 12 ሰላሳ ሺህ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት የሰማዕታት ቀን በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር የተወካዮች ምክር ቤት እንዲወስን ፊርማዎን እንዲያሳርፉ በሰማዕታቱ ስም ይለመናሉ።
ለመፈረም ይህንን ማስፈንጠርያ (ሊንክ) ይጫኑ http://chng.it/ZNT87PstCq 
ጉዳያችን / Gudayachn 


በፈድራሊዝም ስርዓት የኢትዮጵያ ሕዝብም አይደራደርም።የኢትዮጵያ ሕዝብም ለተጨማሪ ድል ይሰራል።ፈድራሊዝም ግን የጎሳ ፈድራሊዝም ብቻ አይደለም።

ጉዳያችን / Gudayachn
የካቲት 12/2011 ዓም (ፈብሯሪ 19/2019 ዓም)
===================
አቶ ለማ በሊቀመንበርነት የሚመሩት የኦዲፓ (የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ) ባወጣው መግለጫ ''
‘’በፌዴራሊዝም ስርዓት አንደራደርም፤ለተጨማሪ ድል እንሰራለን’’ በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ዙርያ በርካታ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።እዚህ ላይ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በዶ/ር ዓብይ እና አቶ ለማ የተንፀባረቀው ኢትዮጵያዊነት ቀዳሚ አጀንዳ ጋር በተቃርኖ የሚያነሱት ወገኖች መሰረታዊ የመረዳት ችግር የሚመስለኝ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ከገባበት ጣምራ ተግዳሮት አንፃር ካለመመልከት የሚመነጭ ነው።

ኦዲፓ  በአንድ በኩል በህወሓት በሌላ በኩል በፅንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲከኞች በራሱ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚነዛ ፕሮፓጋንዳ አለ።ይሄውም ኦዲፓ ወደ ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ (ኢትዮጵያዊ ፖለቲካ ፈድራልዝምን ይቃረናል የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳለ ሆኖ) አዘንብሎ የነበረውን የፈድራሊዝም ስርዓት ሊያናጋ ነው በእዚህም የኦሮሞ ሕዝብ የነበረ መብቱን ሊያስወስድ ነው የሚል ፕሮፓጋንዳ ነው።ይህ ፕሮፓጋንዳ ጠለቅ ብሎ ለማያውቀው የከተማ ወጣት እና የገጠር ሕዝብ ደግሞ ይብሱን ተጣሞ ይቀርባል።እነ ለማ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባለፈው ሳምንት በወለጋ ጉብኝት ወቅትም ይህንን ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል እንደሄደ ተረድተውታል።ስለሆነም ከሁለቱም አካላት የሚነሳውን ፕሮፓጋንዳ ለመመከት በፈድራሊዝም አንደራደርም የሚል መግለጫ ማውጣት አለባቸው። ስለሆነም የዛሬው ‘’በፌዴራሊዝም ስርዓት አንደራደርም፤ለተጨማሪ ድል እንሰራለን’’ የሚል መግለጫ አውጥቷል። ይህ የማብረጃ ፕሮፓጋንዳ ካልሆነ በቀር ለራሱ ለኦዲፓ የጎሳ ፈድራሊዝም የትም ያህል እንደማያስኬደው በግልጥ የሚያውቀው ጉዳይ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ኢትዮጵያዊነትን ባያነሱ ኖሮ ዘጠኝ ወሮች በስልጣን ላይ ባገኙት አመኔታ ደረጃ ስልጣን ላይ ሊቆዩ አይችሉም ነበር።

ይህ ማለት ግን ኦዲፓ ውስጥ ፅንፍ የያዙ አስተሳሰቦች በኦዲፓ ላይ የሉም ማለት አይቻልም።በሁሉም መስክ ኦዲፓን ለመውረር የማይደረግ እንቅስቃሴ የለም።ይህ ፅንፍ የያዘ አካሄድ ግን ወደ ጠብ የሚያመራ መሆኑን የማይረዳ የፖለቲካው ዓለም ተዋናይ የለም።ሆኖ ግን ካለው ተቃርኖ ብዛት አንፃር ጉዳዮችን እያረገቡ መሄድ እንደወቅታዊ ስልት የመያዝ አዝማምያ ይታያል።

መጪዋ ኢትዮጵያ አሃዳዊ መንግስት ይኖራታል ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ብዙ አይመስለኝም።የፈድራል አስተዳደር አስፈላጊ መሆኑን ከሳይንሱም ከሕዝቡ ነባራዊ እና ወቅታዊ ሁኔታም መረዳት ይቻላል።ይህ ማለት ግን የጎሳ ፈድራሊዝም ብቸኛ አማራጭ ነው ብሎ መሄድ ከግንብ ጋር መልሶ የመላተም ያህል አደጋ ነው። ላለፉት 28 ዓመታት የደረሰው የአንድ ጎሳ አስተዳደር በሌላ ጎሳ አስተዳደር የመተካት ያህል ፌዝ ነው የሚሆነው። 

ኦዲፓ ‘’በፌዴራሊዝም ስርዓት አንደራደርም፤ለተጨማሪ ድል እንሰራለን’’ እንዳለው ሁሉ የኢትዮጵያ ህዝብም በፌድራል ስርዓት አይደራደርም! ለተጨማሪ ድልም ይሰራል።ሕዝብ ፈድራሊዝም ሲል ግን በጎሳ ፌድራሊዝም ብቻ ቆርቧል ማለት አይደለም።የጎሳ ፌድራሊዝም ኢትዮጵያን ሊበታትናት ደርሶ ኢትዮጵያዊነት ሱሴ ነው በሚል አጭር ቃል  ነው ሕዝብ መልሶ የተሰባሰበው። የጎሳ ፌድራሊዝም አደገኛ መርዝ ነው። ሳይንስም የጎሳ ፈድራሊዝም የበታኝነት ሚናውን ያረጋገጠው ነው።በመሰረቱ የፈድራሊዝም መሰረታዊ ፅንሰ ሐሳብ የማዕከላዊ መንግስት ፈላጭ ቆራጭነት ሚና ተገድቦ ሕዝብ በዜግነቱ ኮርቶ እና መብቱ ተከብሮለት አካባቢውን እራሱ እንዲያስተዳድር የሚያደርግ የአስተዳደር ስርዓት ነው። 

''Federalism, essentially a defense mechanism against a central government that is too powerful and oppressive, is based on common interests.'' The Dangers of Ethnic Federalism,Berouk Mesfin,Institute for Security Study, Addis Ababa, 2008.

''ፌድራሊዝም በመሰረቱ የማዕከላዊ መንግስትን ከልክ ያለፈ ኃይል እና የመጨቆን አሰራር ተከላክሎ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ አስተዳደር ነው'' 

ስለሆነም አንዳንዶች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፀረ ፈድራሊዝም አለመሆኑን ማስረዳት ከሁሉም ወገን ይጠበቃል።ፈድራሊዝም ግን የጎሳ ፈድራሊዝም መሆን እንደሌለበት ማስመር ደግሞ ተገቢ ነው።የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግስት በተግባር ላለፉት ዘጠኝ ወራት የኢትዮጵያዊ አጀንዳ ቀዳሚ መሆን እንዳለበት በወሰዳቸው እርምጃዎችም ሆነ  በሄደባቸው መንገዶች ሁሉ መረዳት ይቻላል።የመንግስት ድርጅቶች ላይ እየታዩ ያሉት የአደረጃጀት ለውጦች እና የምክር ቤቱ የመሰረታቸው የወሰን ጉዳይ የሚመልከተው ኮሚሽንም ሆነ ለማኅበራዊ አካላት የሚሰጠው ትኩረት አበረታች ናቸው።በተግባር ኢትዮጵያዊ መንገዶች ያየንበት አስተዳደር በሁለት አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ያወጣው መግለጫ ፕሮፓጋንዳ ተግባር ቢሆንም ፌድራሊዝም ስትል ምን አይነት ፈድራሊዝም? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።መግለጫው የወጣው ከፅንፈኛ አካላት ለተሰነዘረ ፕሮፓጋንዳ የተሰጠ ምላሽ ለመሆኑ ማስረጃው ደግሞ የመግለጫውን ቃል በቃል ማንበብ ይጠቅማል። እንዲህ ይነበባል - 
''አሁን ያለው መንግስት የፌዴራል ስርዓቱን ለማፍረስ እንሚሰራ በማስመሰል ህዝቡ ሌላ ድል ማግኘቱ ቀርቶ ቀድሞ ያገኘውንም ሊያጣ እንደሆነ በመናገር ህዝቦች ለውጡንና የለውጡን መሪዎች እንዲጠራጠሩ ሰፊ ፕሮፓጋንዳ እየተነዛ ነው።'' ይላል የኦዲፓ መግለጫ።

ሮፓጋንዳ እየነዙ ስለሆነ እኔ ፈድራሊዝም ላፈርስ አልመጣሁም  ነው የመልእክቱ ጭብጥ። ከእዚህ በተለየ የኦዲፓ መግለጫ የተለየ መስመር የያዘ አድርጎ መተርጎም ምንም ፋይዳ የለውም።ከእዚህ የተለየ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲል አይጠበቅም።ፈድራሊዝም ሲል ጎሳን መሰረት ያደረገ አለመሆኑን ተመራምሮ እንደደረሰበትም ቆየት ብሎ እንዲነግረን አባላቱን እንዲያስረዳ ግን የሁሉም ምኞት ነው።ከእዚህ ውጭ  በአንድ አዳር አቶ ለማ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የተቀየሩ አስመስሎ ማውራት አይጠቅም።ስልጣን ሕዝብ እጅ እንዳለ ለማሳየት ዛሬም መደራጀት ሃሳብን በነፃ መግለጥ እና ፅንፈኛ አስተሳሰቦችን ማጋለጥ ላይ ማተኮር ይገባል።

ስለሆነም ለፌድራሊዝም ዘብ የሚቆመው የኢትዮጵያ ህዝብም ነው።ለጎሳ ፌድራሊዝም ሳይሆን ለሕዝቡ አመቺ የሆነ መልክዓ ምድራዊ፣ታሪካዊ እና  ለሕዝቡ አስተዳደራዊ መንገድ አመቺነትን ያገናዘበ ፌድራሊዝም  ሕዝብ ዘብ ይቆማል። 


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Saturday, February 16, 2019

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን ጋዜጠኞች በሚሊንየም አዳራሽ ቪድዮዎች

Ethiopian Satellite Television (ESAT) in Addis Ababa Millennium hall videos 
ጉዳያችን / Gudayachn
የካቲት 10/2011 ዓም (ፈብሯሪ 17/2019 ዓም)

ከእዚህ በታች ባሉት አራት ቪድዮዎች ውስጥ 
- ጋዜጠኞቹ ወደ አዳራሽ ሲገቡ የነበረው ትዕይንት ፣
- የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ንግግር ፣
- የጋዜጠኛ አበበ ገላው ንግግር ፣
- የጋዜጠኛ መሳይ መኮንን ንግግር ፣
- የጋዜጠኛ መታሰብያ ቀፀላ ንግግር  እና
- የጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደው  ንግግር  እና 
- የአና ጎሜዝ ንግግር ቪድዮ ይመለከታሉ።

1) ጋዜጠኞቹ ወደ አዳራሽ ሲገቡ የነበረው ትዕይንት


2)የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በሚሊኒየም አዳራሽ ያደረገው አስደናቂ ንግግር


3) የጋዜጠኛ አበበ ገላው ንግግር በሚሊንየም አዳራሽ 


4) የጋዜጠኛ መሳይ ፣አፍወርቅ እና መታሰቢያ በሚሊኒየም አዳራሽ ያደረጉት ንግግር


 5) የአና ጎሜዝ ንግግር - Anna Gomez


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Saturday, February 9, 2019

የኢትዮጵያ እና የኖርዌይ ግንኙነት (ፎቶዎች እና ቪድዮዎች) Etiopia og Norge forholdet (bilder og videoer)

ጉዳያችን / Gudayachn
የካቲት 3/2011 ዓም / 10. februar 2019

የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ጉብኝት በኖርዌይ 1954 እኤአ Etiopisk kong Majesty Haile Selassie besøk til Norge i 1954
የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር ሲወያዩ የካቲት 3/2011 ዓም Norges statsminister møter etiopisk statsminister 9 februar 2019




ኖርዌይ በንጉሡ ዘመን የመጀመርያውን የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ያሰለጠኑ ናቸው።Norge er den første trener til Etiopias marine hær 1940s








የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር ሲወያዩ የካቲት 3/2011 ዓም Norges statsminister møter etiopisk statsminister 9 februar 2019
===============================
ቪድዮ (ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ  በኖርዌይ ንጉስ የራት ግብዣ  ተደርጎላቸው ያደረጉት ንግግር)
Etiopisk kong Majesty Haile Selassie tale i Oslo under sitt besøk til Norge i 1954

ቪድዮ (የኖርዌይ ንጉስ ጉብኝት በኢትዮጵያ)  Norge kong  besøk til Ethiopi  i 1950s


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Tuesday, February 5, 2019

መጪው የኢትዮጵያ ዘመን ብርሃን ወይንም ጨለማ ነው።ለሁለቱም እያንዳንዳችን ተጠያቂ ነን (የጉዳያችን ልዩ ወቅታዊ ትንታኔ)


በእርስ በርስ ጦርነት የፈረሰችው የሶርያን ከተማ ቆሞ በትካዜ የሚመለክት ሶርያዊ  ወታደር (ከማኅበራዊ ሚድያ የተገኘ) 

ጉዳያችን GUDAYACHN 
ጥር 29/2011 ዓም (ፈብሯሪ 6/2019 ዓም) 
============================

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች ተብራርተዋል - 

አሁን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታ ያሉት ስድስት አደገኛ ጉዳዮች እና 

የችግሮቹ  ሶስት መፍትሄዎች 

ወቅቱ 1928 ዓም ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ የሚወስደው ባቡር  የኢትዮጵያ ከፍተኛ ስልጣን የይዙትን ንጉሰ ነገሥቱን እና ጥቂት ባለስልጣናት አብረው እየሄዱ ነው።ትካዜ፣ሃዘን እና ተስፋ መቁረጥ በባቡሩ ውስጥ የተሳፈሩት ሁሉ ላይ ሰፍኗል።ንጉሡ በያኔው የፈረንሳይ ቅኝ የነበረችው በቀድሞ ስሟ አፋር እና ኢሣ የዛሬዋ ወደ ጅቡቲ እያመሩ ነበር።ጉዞው በጅቡቲ የሚቆም አልነበረም። ከጅቡቲ ወደ እየሩሳሌም በመቀጠል ወደ ጄኔቭ  ተጉዘው ለያኔው የዓለም ማኅበር (የአሁኑ የተባበሩት መንግሥታት) የፋሽሽት ጣልያንን የግፍ ወረራ አቤት ለማለት እየሄዱ ነበር።በጉዞ መሃል ባቡሩ የቆመበት ድሬዳዋ ከተማ ሲደርስ ንጉሡ ጣብያው ላይ ወርደው ቀጣይ ጉዞ ከማድረጋቸው በፊት በስልክ ወደ አዲስ አበባ ደውለው ሁኔታውን መከታተል ፈልገው በወቅቱ ቀጥታ ስልክ ባለመኖሩ በኦፕሬተሩ በኩል ከአዲስ አበባ ጋር እንዲያገገናኛቸው ይጠይቃሉ።የታዘዘው ኦፕሬተር  ከእዚህ በፊት በድምፅ ያውቁታል። ጣልያን ከመምጣቱ በፊት አክብሮ ያናግራቸው ነበር።ያን ቀን ሲያናግራቸው ግን ስርዓት በያዘ መልክ አልነበረም።ጣልያን እየመጣ መሆኑን ያወቀው ኦፕሬተር ጥርት ባላለ አማርኛው ክብር በማይሰጥ አነጋገር ሲናገር ንጉሡ ሰሙት።ንጉሡ ይህ ሰው ጊዜ ያዘነበለ መስሎት ስርዓት ባጣ መልኩ በመናገሩ ሃገሩን ከአሁኑ መክዳቱ ተሰምቷቸዋል።ጣልያን ምን ይዞ እንደመጣ ያላወቀ የምስራቅ ኢትዮጵያ ሰው ስርዓት ያጣ የስልክ አነጋገር እና ድፍረት በራሱ ለንጉሡ  ሌላ ሃዘን ነበር።

ከላይ የተጠቀሰው ታሪክን ንጉሡ ከነፃነት በኃላ ተመልሰው በፃፉት ''ሕይወተኛ የኢትዮጵያ ርምጃ'' በሚለው መፅሐፋቸው ላይ ጠቅሰውታል። ታሪኩን የእዚህ ፅሁፍ መግቢያ ያደረኩበት ምክንያት ኢትዮጵያ በዘመኗ እንዲህ አይነት የሐዘን ሰዓታት አሳልፋ ነበር።ጣልያን ከሰሜን እየመጣ፣ንጉሷ በጅቡቲ እየወጡ።ያንን ወቅት ዛሬ ላይ ሆነን በምናባችን ብናስበው የንጉሡ ልብ ምን ያህል ያዘነበት፣አንዳንዶች ኢትዮጵያ አበቃላት ያሉበት፣ሌሎች በእኔ አጥንት ላይ ተረማምደው ብቻ ነው የኢትዮጵያን ሞት የሚያረጋግጡት ያሉ አርበኞች የተነሱበት  ፈታኝ ወቅት ነበር።ይህ ማለት ኢትዮጵያ ምንም የማይነካት ካለ አንዳች እንከን የምትኖር ሀገር ነች ብሎ ደምድሞ መቀመጥ አይቻልም።የሚሆነው ሁሉ በዛሬ ስራችን፣ትጋታችን እና ተግባራችንም የሚወሰን መሆኑን ማወቅ እንጂ በተዓምር  ብቻ ምንም አትሆንም በሚል መዝናናት ስሕተት መሆኑን ለመጠቆም ነው።በ1928 ዓም በፀሎት የማይተጉ የሃይማኖት አባቶች ኢትዮጵያ ስለሌላት አይደለም።ሆኖም ግን የደረሰባት ሁሉ ደረሰባት።ነገር ግን ተመልሳ በመለኮታዊ ኃይልም በመርዎቿ ትጋትም ተነስታለች።ዛሬም ላይ ሆነን በሶርያ የደረሰ የማይደርስብን ልዩ ሀገር ነን አልያም ኢትዮጵያ ፈፅሞ ምንም አትሆንም የሚለውን አባባል ትተን አሁን የመጣውን መልካም ዕድል  ኢትዮጵያ እንድትጠቀም የእያንዳንዱ ሚናውን ዝቅ አድርጎ የሚያይ ግለሰብ ሁሉ  መጪው የኢትዮጵያ ዘመን ብርሃን ወይንም ጨለማ መሆኑን የዘነጋ ሰው ብቻ ነው ።ለሁለቱም  መጪዎች ግን እያንዳንዳችን ተጠያቂ እንደሆንን መሰብ አለብን።መስራት ያለብንን ትንንሽ ድርሻ ባለመስራት።

አሁን በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ሁኔታ ያሉት ወቅታዊ ስድስት አደገኛ ጉዳዮች 

መጋቢት 24/2010 ዓም ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ለኢትዮጵያ ፓርላማ ካደረጉት አቅጣጫ ቀያሪ ንግግር ወዲህ ኢትዮጵያ እጅግ ግዙፍ የሆኑ ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት መንግድ ጀምራለች።የሚሰሩት ስራዎች ዘለቄታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸው በራሱ ኢትዮጵያን እጅግ ተስፋ ያላት ሀገር እንድትሆን ማድረጉን  አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ከገጠር እስከከተማ የሚያምንበት ዕውነታ ነው።ይህ መልካም ጅምር በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ቢሆንም ግን የሚያሰጉኝ ስድስት አደገኛ ሁኔታዎች አሉ።እነኝህ ጉዳዮች በአግባቡ መፍታት ደግሞ የመንግስት ስራዎች ብቻ አይደሉም።የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ግን ናቸው።እነኝህ ስድስት ጉዳዮች : -

1ኛ) የሕዝብ እና ፊት ቀደም ሀገር ወዳድ የነበሩ ግለሰቦች የምቾት ቀጠና (comfort zone) መግባት 

ለውጡ ከመጣ ገና አንድ ዓመት አልሆነውም።ይህ ለውጥ በበርካታ ቅራኔዎች የኖረው የኢትዮጵያ ፖለቲካው ውስጥ በድንገት ብቅ ሲል የሚገጥመው ተግዳሮት ከቀድሞው ስርዓት ህወሓት እና ደጋፊ የኢሕአዴግ አባላት ጋር ብቻ አይደለም።ከአርባ ዓመታት በላይ የነበሩ የፖለቲካ ቅራኔዎች ሁሉ እንዲፈታ እና ኢትዮጵያን ወደተሻለ ዲሞክራሲ እና የሃሳብ ልዕልና ማሸጋጋር ሁሉ የሚጠበቅበት ግዙፍ ሃገራዊ ፕሮጀክት ነው።ይህ ሆኖ ግን በሕዝብ ዘንድ የሚታይ የምቾት ቀጠና መግባት እና ጉዳዮችን በንቃት ከመከታተል መዘናጋት ብቻ ሳይሆን ነገ እንዴት እንሂድ ለሚለው ሃገራዊ ጥያቄ የራስን ሚና አሁንም አደራጅቶ አለመጠበቅ በሕዝብ ዘንድ ይታያል። ይህ አደገኛ ሁኔታ ነው።ሕዝብ እንደ ሕዝብ ግለሰብም እንደ ግለሰብ መንግስት ዛሬ ምን አለ? ከሚል ስሜት ብቻ የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንን ዜና ከመከታተል ባለፈ የሚጠበቅ ትጋት ያስፈልጋል። ይህ የምቾት ቀጠና የመግባት አደጋ በጋዜጠኞች፣የፖለቲካ ሰዎች የኪነ ጥበብ ሰዎች ሁሉ ዘንድ ይንፀባረቃል።የእዚህ አይነት ለውጥ ጋዜጠኞች ልዩ ሥራ የሚያሳዩበት፣የኪነጥበብ ሰዎች ከአእምሮ የማይጠፋ ሥራ ብቻ ሳይሆን ብስለት ያለው አቅጣጫ አመላካች ስራዎች ሁሉ ሊታዩ የሚገባበት ወቅት ነበር ።

2ኛ) አንዳንድ ወጣቶች በፅንፍ አመለካከት የተሞላ ፖለቲካ ውስጥ መዘፈቅ 

ነገ የሚመነዘረው በዛሬው ወጣት አመለካከት ነው።በኢትዮጵያ አሁን ለመጣው ለውጥ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለው ወጣት ባብዛኛው በማዕከላዊ አስታራቂ፣ይቅር ባይ እና ቀጣዩ ላይ የማትኮር ፖለቲካ ላይ በመስማማት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ሃሳብ የተቀበለ ቢሆንም የተወሰኑ ኃይሎች በተለይ በዓማራ  ክልል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣በኦሮሞያ ደግሞ ከቄሮ ጋር በተያያዘ ''ዋልታ ረጋጭ'' (ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባለፈው ሳምንት ለየት ያሉ ሃሳቦችን ለመግለጥ የተቀሙበትን ቃል ተውሼ ነው) የሆነ ሃሳብ የያዙ አካሎች እንዳሉ ግልጥ ነው።የቄሮ ጉዳይ አሁንም በፓርቲነት ተገልጦ አይውጣ እንጂ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ለውጥ ተደስተው ከለውጡ ጋር በመልካም መንገድ የሚሄዱ ብዙዎች ቢኖሩም በአክትቪስትነት የሚታዩት ግን ግባቸውም ሆነ መድረሻ የፖለቲካ ዓላማቸው አሁንም ቢያንስ ለእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ግልጥ አይደለም። 

ይህ በራሱ ምን ያህል ያስኬዳል? የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ የነገ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ብዥታ  ግን አይሆንም ማለት አይቻልም።ጥርት ያለ የፖለቲካ ግቡ የማይታወቅ እና በህጋዊ መልክግ ተደራጅቶ ሃሳቡን የማይገልጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ደግሞ ባልሆነ የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ አድፋጭ ኃይል የመጠለፍ እድሉ ቀላል አይደለም።ይህ ጉዳይ እራሱ ቄሮ ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ የመረጃ ክፍተት ስለሚኖርባቸው በራሳቸው ስለራሳቸው እንቅስቃሴ አንዳንዴ ትክክል በመዋቅር መስመር ላይ የቱ ጋር እንድተጠለፈ ለማወቅ የሚቸገሩበት ወቅት አይገጥምም ማለት በራሱ ከባድ ነው። ቄሮ በህወሓት እና በቀድሞው ታዛዥ ኦህደድ ላይ ዲሞክራሲ፣መብት፣ፍትሕ የሚሉ ጥያቄ የያዙ ወጣቶች እንቅስቃሴ ቢሆንም ዋልታ የረገጡ አስተሳሰቦች ማለትም በኢትዮጵያ ያለፈው ታሪክ ንትርክ ውስጥ በተዘፈቁ አክትቪስቶች  አገናኝነት ላይ ጥገኛ በመሆኑ የእነርሱን አስተሳሰብ የቄሮ (የኦሮሞ ወጣት) አስተሳሰብ እንደሆነ እየተደረገ የመወሰድ የተሳሳተ አስተሳሰብ አደጋ ተጋርጦበታል። 

በሌላ በኩል በዓማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጉዳይ ነው።የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አሁን በአማራ ክልል ከሚገኘው አማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዲፓ) ከሚያራምደው ለዘብ ያለ ፖለቲካ በአንፃራዊ መልኩ ''የከረረ'' የሚባል (የከረረ የሚለው አገላለጥ በራሱ ቢያከራክርም) ፖለቲካዊ ሃሳቦችን እንደሚያንፀባርቅ የሚሰማቸው ጥቂቶች አይደለም።በተለይ አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ ፓርቲዎችን በተለያየ ጊዜ ሲወርፍ ተደምጧል።እንደ አብን አገላለጥ የዜግነት ፖለቲካ ''ላም በሌለበት ኩበት ለቀማ'' አይነት ሃሳብ አለው።''ሀገሪቱ በሙሉ በዘር ፖለቲካ ስለተዋቀረች የዜግነት ፖለቲካ አማራውን ሊያዘናጋ ነው'' የሚል ትርክትም አብን ያስቀምጣል።እዚህ ላይ ግን ቤተ መንግስቱ እና ህወሓት ሰራሽ ፖለቲካ ላለፉት 28 ዓመታት በዘር ፖለቲካ ስለተዋቀረ፣ተራው የኢትዮጵያ  ሕዝብ ውስጥ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የቤተ መንግስቱ በሽታ ሙሉ በሙሉ ግልባጭ ነው፣ ሕዝቡም በቤተ መንግስቱ ደረጃ የጎሳ ፖለቲካ ተጋብቶበታል ብሎ ማመን የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የሚገልጥ ትክክለኛ አገላለጥ ነው ወይ? ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ አብን በማስረጃ ማሳየት አልቻለም።ይልቁንም ዶ/ር ዓቢይ ያነሱት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ሚልዮኖችን ማሰለፉ በራሱ ኢትዮጵያዊነት ከጎሳ ፖለቲካ በተሻለ መልክ ገዢ ሃሳብ ለመሆኑ እንደ ትልቅ የጥናት ውጤትም መታየት የነበረበት መልካም ዕድል ነበር።

የሆነው ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ካላት መጪ አደገኛ የፖለቲካ ሁኔታዎች ውስጥ የወጣት ፅንፍ የያዙ ( ዋልታ ረጋጭ) ሃሳቦች ተጠተቃሾች ናቸው።አደጋው ደግሞ ሁለቱም ለዘብተኛ እና አሁን ላለው ለውጥ ዋና ተዋናይ የሆኑትን ኃይሎች ለመቀናቀን የሚያቀርቡት የፖለቲካ መስመር ምንም አይነት ስም ብንሰጠው አንፃራዊ አክራሪ አስተሳሰብ የያዙ መሆናቸው ነው።ይህ ደግሞ ወደ ርዕዮተ ዓለም አልባ እና ግብ የለሽ ክርክር ኢትዮጵያን እንዳይከታት ያሰጋል።

3ኛ) ከፍተኛ ሥራ አጥ ወጣት መኖር፣የሕዝብ ብዛት መጨመር፣ከገጠር ወደ ከተማ ያለው ፍልሰት መኖር 

4ኛ)  ኢትዮጵያ የአፍሪካም ሆነ ለመካከለኛው ምስራቅ አቅጣጫ አስቀያሪ ስልታዊ ሀገር መሆኗ በዓለማችንም ሆነ ሃያላን ሀገሮች ሁሉ ዓይን ስር መሆኗ 

ይህኛው የሀገራችን ሚና ብዙ የተባለለት ቢሆንም አሁን አካባቢያዊ ኃያላን መንግሥታት ሹክቻ ለምሳሌ ኢራን እና ሳውዲአረብያን መጥቀስ ይቻላል። የእነርሱ ሹክቻ እና የጥቅም ፍላጎት ኢትዮጵያን በትኩረት ያሚያስመለክታት መሆኑ እና የቆየው የአረብ ናሽናሊዝም እንቅስቃሴ የገባበት አጥብቂኝ በተለይ ከኒውዮርኩ  የሽብር ጥቃት በኃላ የደረሰው ክፍፍል እና የክፍፍሉ እና የአረብ ሊግ መዳከም ሁሉ ኢትዮጵያ ላይ የሚያመጣው  የራሱ ተፅኖ አለው።በተከፋፈለ  የመካከለኛው ምስራቅ ሁኔታ እያንዳንዱ ተፎካካሪ የኢትዮጵያን ፅንፈኛ እንቅስቃሴዎች በተለይ በየትኛውም አዋኪ ፖለቲካ ለመደገፍ የሚደረገው እሽቅድምድም ሁሉ የራሱ የሆነ የኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ፈተና ነው።በእርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ በእዚህ ፅሁፍ አቅራቢ መሰረት የምዕራቡ ዓለም አሁን የኢትዮጵያ መረጋጋት እና ወደተሻለ ደረጃ ማለፍ ለመካከለኛው ምስራቅ እና የአፍሪካ ቀንድ የኃይል ሚዛን መጠበቅያነት ብቻ ሳይሆን እንደ ስጋት ከሚያያት ሱዳን ጋር ያለውን ስጋት ሚዛን መጠበቅያ ኢትዮጵያን ማጠናከር የተሻለ መሆኑን ያመኑበት ይመስላል።የምዕራቡ  ዓለም በየመን፣ሊብያ፣ሶርያ ያሉት ቁርሾዎች ለምዕራቡ ዓለም የቦታ ሽግሽግ እንጂ ትርፍ እንዳላስገኘ ስለተረዳ ኢትዮጵያ ላይ ይህ እንዲደገም አልፈቀዱም።ስለሆነም ኢትዮጵያ አሁን ካለው ለውጥ እንድትጠቀም ካደረጋት ውጫዊ ዕድሎች ውስጥ ይህ የምዕራቡ አስተሳሰብ ተጠቃሽ ሳይሆን እንደማይቀር አለመጠርጠር አይቻልም።

በሌላ በኩል የአቶ ኢሳያስ ፖለቲካ ነው።አቶ ኢሳያስ ከኢትዮጵያ ጋር ተጋግዞ ከመሄድ በላይ ምንም አይነት በጎ ዘመን በተለይ ከገበያ አንፃር ብቻ ሳይሆን በመካከለኛው ምስራቅ ካቆጠቆጡት ትንንሽ ጉልበተኞች አንፃር አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የቀይ ባሕር መጠበቅ ከባድ መሆኑን በሚገባ ተረድተውታል።ይህንን የኃይል ሚዛን ለመጠበቅ አቶ ኢሳያስ የመቶ ሚልዮን ሕዝብ እና የተሻለ የገንዘብ አቅም  ያላት ኢትዮጵያ ያውም ባህል፣ታሪክ እና ፈተና ሁሉ ዘመናት አብረው ካሳለፈች ሀገራቸው ጋር በሆነ መልክ ስምምነት መፍጠሩ  አማራጭ እንደሌለው እያሰላሰሉ ነበር ተቃዋሚዎችን ሲረዱ የኖሩት።ስለሆነም አጋጣሚው የዶክተር አብይ መንግስት መምጣት የልባቸውን ጭንቀት ገላገለው። ወደፊትም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጉዳይ በስጋት የሚያስቡ ሰዎች ይህንን ስልታዊ ትስስር ለኢትዮጵያም ሆነ ለኤርትራ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማመን ብልህነት ነው።ቀይባህር ካለ መቶ ሚልዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕገዛ አደጋ ላይ ነው።ኢትዮጵያም ኤርትራ ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ጋር በሚስጥር እየመከረች ሰላም የላትም።ስለሆነም ምጣኔ ሃብቱ እና የውጭ ፖሊሲ  እንዲሁም ወታደራዊ ጉዳዮች ሁሉ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በብልህነት አጣምረው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ አድርገው ካላስኬዱት  ለሁለቱም አደጋ አለው። ቀድሞውንም ቢሆን የኤርትራን መገንጠል አንዳንድ የአረብ ሃገራት ከቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ጊዜ ጀምሮ ሽንጣቸውን ገትረው የደገፉት ቀይ ባህርን  ኤርትራን ብቻዋን ካገኙ እንደሚቆጣጠሩት ስለሚያውቁ ነው።ከወራት በፊት የዶክተር ዓብይ አስመራ ድንገት መግባት አንዳንድ የአረብ መንግስታትን መጋኛ እንደመታው  ሰው ቢያስደነግጣቸው መገረም የማይገባው ለእዚህ ነው።

5ኛ) የሴቶች ዝምታ  

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ተሳትፎ እና የፊት የመምራት በተለይ ሕዝብ በማደራጀት፣በማንቃት፣ማኅበራዊ እሴቱን በመጠበቅ በአክትቪስቱ ሥራ ሁሉ እና በመሳሰለው ሁሉ የሴቶች ዝምታ ለኢትዮጵያ መጪ ፖለቲካ አደጋ ነው።አንዳንዶች በቅርቡ ዶ/ር አብይ ካብኔያቸውን ባብዛኛው በሴቶች መሞላቱ መልካም ጅማሮ እና የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ መልካም ተፅኖ ቢኖረውም እታች ህዝቡ ጋር ባሉ የፖለቲካ ጉዳይ ግን ሴቶቹ ዝምታቸው በዝቷል።ይህ ደግሞ የደፈረ ፖለቲካ እንዳይራመድ በተለይ በኢትዮጵያዊነት ዙርያ ዕንቅፋት አልሆነም ማለት አይቻልም።

6ኛ) የትግራይ ሕዝብ በህወሓት እንደታገተ መገኘቱ 

ህወሓት አፈገፈገ እንጂ ሙሉ በሙሉ ለዲሞክራሲያዊ ሃገራዊ ጉዳይ እጁን አልሰጠም።ይህ በራሱ ለኢትዮጵያ አደገኛ ሁኔታ ነው። አደጋው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለኤርትራ እንዲሁም ለአፍሪካ ቀንድ ባጠቃላይ አደገኛ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ መዳረጉ አልቀረም።በርግጥ የህወሓት ጉዳይ የትግራይ ተወላጅ በሙሉ በፍጥነት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተባብሮ ህወሓት ወደ ዲሞክራሲ እንዲመጣ ማስገደድ የግድ አስፈላጊ ተግባር ሊሆን ይገባል። ይህ ካልሆነ ህወሓት ከባዕዳን ኃይሎች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንባር በመግጠም  የኢትዮጵያ ዲሞክራሲም ሆነ ሉዓላዊነት አደጋ የማይጥል ሁኔታ አይፈጠርም ብሎ ማሰብ ከህወሓት ተፈጥሯዊ ባህሪ አንፃር አይቻልም።

የችግሮቹ  ሶስት መፍትሄዎች  

ከላይ የተጠቀሱት ስድስት አደገኛ የፖለትካችን እና የሉዓላዊነታችን አደጋዎች ሶስቱ መፍትሄዎች  : -

1) ንቃት   

በሕዝብ መሃል የነቁ ጥቂቶች ናቸው።አብዛኛው ሕዝብ አሁን የመጣው ለውጥ ምንም አይነት ተግዳሮች የማይገጥመው እና መንግስት ሁሉን ሥራ ይሰራል ብሎ የሚጠብቅ ነው።ይህ ጉዳይ አደገኛ ስሜት ነው።ስለሆነም ሕዝብ መስራት የሚገባው ጥቃቅን ስራዎች ሳይንቅ እንዲሰራ እና በመረጃም ከመንግስት ጋር ተባብሮ የሚሰራበት ልዩ መንገዶችን  በሚገባ መዘርጋት ይገባል።ይህ ደግሞ ህዝብን በመገናኛ ብዙሃን ሁሉ ማንቃት ሲቻል ነው።የነቃው ለራሱ ጠቅላላ ዕውቀት ከመቀመጥ ከሰፈሩ ጀምሮ ባለው ነፃነት ተጠቅሞ ሕዝቡን በሁሉም መስክ ማንቃት እና አዲሱን ለውጥ እንዲደግፍ እና ደጀን እንዲሆን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።

2) ትጋት 

የነቃው ትጋት ያንሰዋል።የነቃው ጋዜጠኛ፣ፖለቲከኛ፣የፖለቲካ ፓርቲ፣አክቲቪስት፣ባለሀብት፣የጦር ሰራዊት አባል፣የኪነ ጥበብ ባለሙያ፣መምህሩ፣ተማሪው  ሁሉ ለውጡ ከመጣ በኃላ ሁሉ ነገር ያበቃ ይመስል በተከፈተው ዕድል ተጠቅሞ በመደራጀት፣አስደማሚ ስራዎችን በመስራት እና መንግስትን በሙሉ ኃይል ከመደገፍ ይልቅ ትጋት በጎደለው መልክ ከሚጠበቀው ትጋት ባነሰ ደረጃ ላይ እንደሆኑ ይሰማኛል።ይህንን በልኬት ለማስቀመጥ መለክያው በራሱ አስቸጋሪ ሊሆን ይቻላል። ትጋቱ ግን ለውጡን ለመጠበቅ መከፈል ያለበት ትጋት ደረጃ አይደለም።ለእዚህ ማሳያ እንዲሆን እነኝህን ጥያቄዎች በማስቀመጥ ላብራራ።
- ነፃነቱ ከመጣ በኃላ የበሰሉ ጋዜጠኞች ሀገር ውስጥ የሚድያውን አየር ቀየሩት? ጋዜጠኞች በምን ያህል ደረጃ እየተጉ ነው? ብቃት የሌላቸው የመንደር ወሬዎች የሚጠይቁ እርባና ቢስ ቃለ መጠይቆች በማሰማት ጊዜያችንን የሚያጠፉ ጋዜጠኞች ምን እየሰሩ ነው? እጅግ የበሰሉ ባለሙያዎች ወደ ሚድያው መጡ?
- የኪነ ጥበብ ሰዎች ለውጡን አስመልክቶ ሕዝብ አዕምሮ የተቀመጠ እጅግ ልዩ የሆነ አቅጣጫ አመላካች የበሰለ ሥራ አለ? እና ሌሎች ጥይቄዎች ብናነሳ የትጋት ማነስ አሁንም መኖሩ ያመላክታል።

3) የመንግስትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃን የጋራ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስማሙበት ቻርተር መፈራረም  እና የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ሥራ መስራት 

በኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ችግሮች ባብዛኛው በፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ወታደራዊ ጥራት እና ብቃት የሚፈታ ቢሆንም አሁን ባለንበት ዓለም የእነኝህ ሁሉ ጉዳዮች ማሰርያ የመገናኛ ብዙሃን ነው።የመገናኛ ብዙሃን ህዝብንም ሆነ መንግስትን የማረቅ፣የመግራት እና ሃሳብ የማፍለቅ ሚናቸው ትልቅ ነው።በመገናኛው ብዙሃን በኩል አሁን በኢትዮጵያ ያለው አንዱ ችግር ደግሞ የተለያዩ ዋልታ ረገጥ አስተሳሰቦች በርቀት እና በእርቀት የሚመሩ መሆናቸው ነው።ይህ ችግር ደግሞ የምርጫ ወቅት በቀረበ ቁጥር ሚድያዎቻችን የእርስ በርስ ጦርነት ምንጮች እና ቀስቃሾች ላለመሆናቸው ምንም ዋስትና የለንም።ይህ ደግሞ በምርጫው ሰሞን የመሸነፍ እና የማሸነፍ ጫፍ ሲደረስ የሚፈጠሩ ስሜታዊ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ሚድያዎቻችን ወዴት እንደሚወስዱን  ስናስብ የብርድ ቆፈን ይይዘኛል። ይህ ችግር ለመፍታት የመንግስትም ሆነ የግል መገናኛ ብዙሃንን መንግስት በአንድ ምክክር ጠርቶ የጋራ ሃገራዊ ቻርተር ላይ እንዲፈራረሙ እና በእዚህ ቻርተራቸው መሰረት መረጃ እንዲያቀርቡ ማድረግ መቻል እጅግ አስፈላጊ ነው።ቻርተሩ ሕዝብ በጎሳ ለመከፋፈልም ሆነ ሀገራዊ ፀጥታን አደጋ ላይ የማይጥሉ ጉዳዮች ላይ አደጋ እንዳይፈጥሩ ቃል የሚገቡበት ሰነድ ይሆናል።ይህ ጉዳይ የሚድያ ነፃነት ዞሮ ማፈን አይደለም ወይ? ብለው የሚያስቡ ይኖራሉ።ሆኖም ግን በጋራ እራሳቸው ተመካክረው የሚስማሙበት ቻርተር ማድረጉ እና የሚዳኛቸው የሀገር ሕግ ብቻ ሳይሆን የራሳቸው የጋራ ቻርተር መኖሩ አስፈላጊ ነው።በተለይ ሚድያ በክልል ደረጃ የመሰረተች ሀገር አንድ አይነት ማሰርያ ሳታስቀምጥ ነገሮች በተካረሩ ወቅት  ሁሉ ሚድያው የውሸት መረጃ አገኘሁ በማለት ህዝብን በማስደንበር ጭምር ኢትዮጵያን  ወደ ግጭት አይመራም ብሎ ማሰብ አይቻልም።ስለዚህ ነው የሚዳኙበት እና የሚያከብሩት የጋራ ሰነድ ምድያዎቹን በተመለከተ የሚያስፈልገው።ሰነዱ ሀገራዊ ኃላፊነት የሚያሳይ የጎሳ ፖለቲካ ማንፀባረቂያ ሚድያዎች እንዳይሆኑ ያስገድዳቸዋል።

ከሚድያው ጋር መታየት ያለበት ሌላው መፍትሄ የምጣኔሀብት መዋቅራዊ ሥራ መስራት ያስፈልጋል።አሁንም የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ቅኝት በህወሓት ሰራሽ መሰረት ላይ የወደቀ ነው።የሚንቀሳቀሰው ሀብትም ሆነ አደረጃጀት የነበረው ነው።በእርግጥ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ተአምር እንዲፈጠር አይጠበቅም።ሆኖም ግን መሰረታዊ የሆኑት ጉዳዮች ላይ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት አደጋውን መከላከል ብቻ ሳይሆን ምጣኔ ሃብቱን ለማስፈንጠር እና ወደተሻለ ደረጃ ለመውሰድ ይረዳል።ለምሳሌ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ባለ ሀብቶች ወደ ሀገር ቤት መዋለ ንዋያቸውን ይዘው እንዲገቡ ልዩ ጥቅም መስጠት ሁሉ ይመለከታል። በሌላ በኩል ሃገራዊ ጥናት እና ምርምር የሚሰሩ ሀገር በቀል ድርጅቶችን ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል።ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር  የመሳሰሉ  ሃገራዊ ድርጅቶች ያለውን የምጣኔ ሀብት ጉድለት እና መጪ አደጋዎች እንዲጠቁሙ በሰው ኃይልም ሆነ በገንዘብ መደገፍን ሁሉ አስፈላጊ ነው።

ለማጠቃለል ኢትዮጵያ በመጪው የፖለቲካ መንገዷ ብርሃንም ሆነ ጨለማ ይታያሉ።ስላልደረስንበት ብርሃንም ሆነ ጨለማ የለም ማለትም ስህተት ነው። ዕድሉም ሆነ ርግማኑ ግን እያንዳንዱ ሰው በሚሰራው ሥራ የሚወሰን ነው።በዝምታ ብቻ ካለ አንዳች ንቃት እና ትጋት በዝምታ ብርሃን እየጠበቅን ከሆነ ተሳስተናል።ለውጡ በትክክል እንዲሄድ መንግስትን በሚገባ ማገዝ እና ጉልበት መሆን ከሁሉም ይጠበቃል።አንዳንዴ የሚጠበቀው ከባድ ላይሆን ይችላል።አንድ ዶላር በቀን ለማዋጣት ችላ ማለት የንቃትም የትጋትም ችግር ነው።ይህ እንግዲህ በዝቅተኛ ደረጃ የቀረበ ሃገራዊ ጥሪ ያውም በውጭ ላለው የቀረበው ነው።ከሀገር እስከ ባህር ማዶ ያለው ኢትዮጵያዊ ግን ነገ ጨለማን ሳይሆን ብርሃንን ለማየት በፅንፍ የቆሙ ሃሳቦች ላይ የእርግማን ውርጅብኝ ከማውረድ ይልቅ ወደ ማዕከላዊ እና የብዙሃኑ ጉዳይ ላይ እንዲመጡ የመተማመኛ መደላድሎችን በማመቻቸት ለማምጣት መሞከር ከሃይማኖት መሪ እስከ ዕድር ፀሐፊ ሚናቸውን ሳይንቁ የሚሰሩት ብዙ ተግባር አለ።ስለሆንም ጨለማ የለም ብሎ ተደላድሎ መቀመጥም ሆነ ብርሃን ላይ ነን ምንም አደጋ የለም ብሎ ጊዜን በፉጨት ማሳለፍ፣ሁለቱም አደጋዎች ናቸው።ሶርያን የተመለከተ በዲሞክራሲ አይቀልድም።ለሁሉም ደግሞ ተጠያቂ መንግስት ብቻ ነው ብሎ የመደምደም አባዜ መላቀቅ እና ሁላችንም ተጠያቂ ነን ብሎ ከማሰብ እና ወደ ሥራ ከመግባት ብርሃኑን የበለጠ የማቅረብ ሥራ ይጀመራል።ዛሬ ይህንን የዲሞክራሲ ወጋገን በሚገባ እንዲያበራ  መሰራት ያለበት ሕዝብ ተግቶ መስራት አለበት።ውጤቱን በጋራ ለማግኘት ደግሞ እያንዳንዱን ሰው እንደ ግለሰብ፣ሕብረተሰብ ደግሞ እንደስብስብ ኃላፊነቱን መወጣት ይገባዋል።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Friday, February 1, 2019

የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ የመታሰብያ ሃውልት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መስርያበት በመጪው ሳምንት መጨረሻ ይመረቃል


ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ 
ጉዳያችን ልዩ ዜና /Gudayachn special report
ጥር 25/2011 ዓም (ፈብርዋሪ 2/2019 ዓም) 

  • የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ወ/ሮ አርና ሶልበርግ፣ ቢልንየሩ ቢል ጌት  እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ  አንቶንዮ ጉተረስ ወደ አዲስ አበባ ያመራሉ። 

ሠላሳ ሁለተኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች መደበኛ ስብስባ በመጪው ሳምንት መጨረሻ የካቲት 2 እና 3/2011 ዓም (february 9 & 10/2019) አዲስ አበባ ላይ ይከፈታል።በቅዳሜው መክፈቻ ስብሰባ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ''በአፍሪካ ጤና ላይ መዋለ ንዋያችንን እናፍስስ'' በሚል ርዕስ የሩዋንዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ፖል ካጋሜ በሚመሩት እና በሸራተን አዲስ በሚደረገው  ልዩ የከፍተኛ ልዑካን ስብሰባ ላይ ከአፍሪካ መሪዎች በተጨማሪ የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ወ/ሮ አርና ሶልበርግ እና ቢልንየሩ ቢል ጌት በልዩ እንግዳነት ይገኛሉ። ይህ ከቀትር በኃላ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከ9 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት የሚደረገው ስብሰባ ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአፍሪካ ሕዝብ ከጤና አገልግሎት የማያገኝ ከመሆኑ አንፃር ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል።የመሪዎቹ ስብሰባ በሌላ በኩል የያዘው ዓብይ አጀንዳ የአፍሪካ ስደተኞች (ወደውጭ እና በሀገራቸው የተፈናቀሉትን) አስመልክቶ የሚያደርገው ውይይት የስብሰባው አንዱ አካል እንደሆነ ተሰምቷል። 

በተያዘው መርሐግብር መሰረት  የዕሁዱ ማለትም የካቲት 3/2011 ዓም የጧት የመሪዎች ስብስባ መርሐግብር በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከረፋዱ 5 ሰዓት ከሩብ ጀምሮ ያለው ጊዜ የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሐውልት በሕብረቱ ፅህፈት ቤት በሚገኝበት ቦታ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት የሚመረቅበት ጊዜ ነው።የአፍሪካ መሪዎች ከእዚህ ቀደም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ ኅብረትነት ሲሸጋገር የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ሐውልት ቻይና ሰራሽ በሆነው በአዲሱ የኅብረቱ ፅህፈት ቤት ለመስራት ፍላጎት በድርጅቱም ሆነ በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ቢኖርም በወቅቱ የነበሩት አቶ መለስ ደስተኛ አለመሆናቸው በርካታ አፍሪካውያንን እና ኢትዮጵያውያውንን ያሳዘነ ጉዳይ ሆኖ አልፏል። ለእዚህም ማስረጃው አቶ መለስ በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ የጋናው ክዋሜ ንኩማ  ሃውልት ምን ያህል ከቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ በላይ  አስፈላጊ እንደሆነ ለማስረዳት የደከሙበት መንገድ ከፍተኛ ትዝብት ላይ ጥሏቸው አልፏል።

በግንቦት ወር 1963እኤአ  ዓም የአፍሪካ ኅብረት ምስረታ ጉባኤ ላይ  ልዩነቶችን በመዳኘት ቻርተሩን ሳንፈርም አንወጣም የሚለው  የንጉሡ ተማፅኖ ለድርጅቱ መመስረት ወሳኙ ጉዳይ ነበር። 

ሆኖም ግን አቶ መለስ ከእዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኃላ የአፍሪካ ሕብረት መስርያ ቤትም ሆነ አፍሪካውያን መሪዎች እንዲሁም የንጉሡ የልጅ ልጅ ልዕልት ማርያም ስነ አስፋወሰን ታሪክ ተቀብሮ መቅረት የለበትም በሚል ሲሟገቱ የነበሩ ሲሆን በሌላ በኩል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሃውልቱ ይሰራ የሚል የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ ሰርተው መንግሥትን ሞግተዋል።ቀድሞም የአፍሪካ ኅብረት እንደዋና ቢሮም ሆነ የአፍሪካ መሪዎች ፍላጎት የነበረው የሃውልቱን መስራት ጉዳይ አሁን ለኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ዋጋ የሰጠው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ መንግስት ዘመን ሃውልቱ ለምርቃት የበቃበት ሁኔታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን የሚያስደስት ተግባር እንደሚሆን የሁሉም ዕምነት ነው። ይህ ታሪክ የመላው የኢትዮጵያውያን ታሪክ ብቻ አይደለም።የአፍሪካውያን ታሪክም ነው።ኢትዮጵያውያን በክብር ልንጠብቀው የሚገባን ቅርሳችን ነው። 
የቀ/አፄ ኃይለስላሴ  የልጅ ልጅ ልዕልት ማርያም ስነ አስፋወሰን እና የአፍሪካ ኅብረት ምክትል ሊቀመንበር  አምባሳደር ክወሲ ካርታይ (Kwesi Quartey)  ፎቶ የአፍሪካ ኅብረት (Photo=Africa Union) 

በመጨረሻም ልዕልት ማርያም ስነ አስፋወሰን  የአፍሪካን  ኅብረት ለማመስገን እኤአ ጥር 22/2019 ዓም  በድርጅቱ ፅህፈት ቤት በተገኙበት  ወቅት የአፍሪካ ኅብረት ምክትል ሊቀመንበር  አምባሳደር ክወሲ ካርታይ (Kwesi Quartey) የንጉሰ ነገሥቱን ሃውልት ምረቃ አስመልክተው  ሲናገሩ የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ሃውልት መሰራት የፓን አፍሪካ መኖርን ያሳያል ብለዋል። ልዕልት ማርያም ስነ አስፋወሰን በበኩላቸው የአፍሪካ ኅብረት ሃውልቱን ለመስራት መወሰኑና መተግበሩ በራሱ የአፍሪካ መሪዎች አንድነትን አመላካች ነው ብለዋል።ንጉሰ ነገስቱ የደርግ አባላት ልይዟቸው ወደ ቤተ መንግስታቸው በሄዱበት በ1966 ዓም የክረምት ወር ሃምሳ አለቃ ደበላ ዴንሳ ንጉሡን ወደ ማረፍያ ክፍል ለመውሰድ እንደሚያስቡ ሲነግሯቸው የሰጡት ምላሽ '' ካልተሳካላችሁ የእኔ ታሪክ እንደ አዲስ ይነሳል'' የሚል ንግግር አድርገው ነበር።አርባ ዓመት ያልተሳካላት ኢትዮጵያ እንዳሉት የእርሳቸው ታሪክ ተነሳ ማለት ነው።ይህ ማለት የድሮው ስርዓት ተመልሶ መጣ ማለት አይደለም።ሀገር በፍቅር፣በአንድነት እና በመተሳሰብ የመምራት ጥበብ እንደገና ትንሣኤ የማግኘቱ ፋይዳ ነው። ዛሬ ሰዎች ስለ ክልላቸው እና ጎጣቸው በማውራት ብቻ ሳይሆን ጎጥ ፖለቲካ በሆነባት ሀገር  ላይ ሆነን ኢትዮጵያን አንድ አንድ የማድረግ ልዩ የፖለቲካ እና መንፈሳዊ ፀጋ ብቻ ሳይሆን አፍሪካን አንድ የማድረግ ጥበብ ያሳዩን ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን የማናደንቅበት ምን አዕምሮ አለን? ሃውልታቸው ለትውልድ ብዙ ማለት ነው።አዲስ አበባም  መሃል አደባባይ ላይ አንድ የንጉሡ ሃውልት ያስፈልጋታል።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...