ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, January 31, 2017

የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ በኢትዮጵያዊነት እና የዐማራ አደረጃጀት ዙርያ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ በአቶ ልዑል መኮንን የቀረበ

የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ቅዳሜ ጥር 20፣2009 ዓም በኦስሎ በኢትዮጵያዊነት እና የዐማራ አደረጃጀት ዙርያ አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር።በዝግጅቱ ላይ  በዶ/ር ተክሉ አባተ፣በአቶ ደባሱ መሰሉ እና በአቶ ልዑል መኮንን የመነሻ ፅሁፎች ቀርበዋል።ባለፉት ሁለት ተከታታይ ቀናት የዶ/ር ተክሉ አባተ እና የአቶ ደባሱ መሰሉ የቀረበ ሲሆን በእዚህ ክፍል የአቶ ልዑል መኮንን  ከእዚህ በታች ቀርቧል።

ምንጭ :  ETNK


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Monday, January 30, 2017

የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ በኢትዮጵያዊነት እና የዐማራ አደረጃጀት ዙርያ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ በአቶ ደባሱ መሰሉ የቀረበ

የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ቅዳሜ ጥር 20፣2009 ዓም በኦስሎ በኢትዮጵያዊነት እና የዐማራ አደረጃጀት ዙርያ አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር።በዝግጅቱ ላይ  በዶ/ር ተክሉ አባተ፣በአቶ ደባሱ መሰሉ እና በአቶ ልዑል መኮንን የመነሻ ፅሁፎች ቀርበዋል።በትናንትናው እለት የዶ/ር ተክሉ አባተ የቀረበ ሲሆን በእዚህ ክፍል የአቶ ደባሱ መሰሉ  ከእዚህ በታች ቀርቧል።
በቀጣዩ ቀን የአቶ ልዑል መኮንን ይቀርባል
ምንጭ :  ETNK



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Sunday, January 29, 2017

የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ በኢትዮጵያዊነት እና የዐማራ አደረጃጀት ዙርያ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ከኦስሎ ዩንቨርሲቲ በዶ/ር ተክሉ አባተ የቀረበ

የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ቅዳሜ ጥር 20፣2009 ዓም በኦስሎ በኢትዮጵያዊነት እና የዐማራ አደረጃጀት ዙርያ አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር።በዝግጅቱ ላይ  በዶ/ር ተክሉ አባተ፣በአቶ ደባሱ መሰሉ እና በአቶ ልዑል መኮንን የመነሻ ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን

በእዚህ ክፍል የዶ/ር ተክሉ አባተ ከእዚህ በታች ቀርቧል።

በቀጣይ ቀናት የቀሩት በተከታታይ ይቀርባሉ።
ቪድዮ ከኢትዮ ኖርዌይ ቲቪ


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Wednesday, January 25, 2017

ሰበር ዜና ከዋሽንግተን ወደ አዲስ አበባ በረራ የጀመረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አይሮፕላን ካናዳ እንዲያርፍ ተገደደ


Ethiopian Airlines flight diverted from Addis Ababa to St. John's

ጉዳያችን / Gudayachn
ጥር 17፣2009ዓም  (ጃንዋሪ 25፣2017)
================================
ዛሬ ሮብ ከሰዓት በኃላ  ከዋሽንግተን ወደ አዲስ አበባ ለመብረር መንገድ የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይሮፕላን በረራ ቁጥር 501 ካናዳ ሴንት ጆንስ አየር መንገድ እንዲያርፍ ተገዷል። አይሮፕላኑ ለምን ለማረፍ እንደተገደደ እና ለምን ያህል ጊዜ በሴንት ጆንስ አየር መንገድ እንደሚቆይ የታወቀ ዝርዝር ነገር የለም። እስካሁን የተሰጠው ምክንያት የሕክምና ጉዳይ ብቻ ነው።ማን እና ለምን ድንገተኛ ሕክምና አስፈለገ? አይሮፕላኑ ውስጥ ምን ተፈጠረ? እና ሌሎች ጥያቄዎች ገና አልተመለሱም።የሴንት ጆንስ አየር መንገድ ቃል አቀባይ ኤሪካ ከላንድ አይሮፕላኑ ከሰዓት በኃላ በካናዳ ሰዓት አቆጣጠር 10 ሰዓት ላይ ማረፉን ብቻ ተናግረዋል።  

A medical emergency aboard a flight bound for Ethiopia's capital city diverted a plane to St. John's on Wednesday.

Ethiopian Airlines Flight 501 landed in St. John's at about 4 p.m NT, according to Erika Kelland, a spokesperson at the St. John's International Airport.

Kelland said there was a medical emergency on board, but had no other information about the incident or how long the plane would remain in St. John's.

The plane left Washington, D.C. at 11:30 NT and was set for a flight of about 13 hours to Addis Ababa.
Source : CBC News


ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

Tuesday, January 17, 2017

ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት በጥንታዊ ዘመነ ታሪክ



                                                        

ከመንግሥቱ ጎበዜ

ሉንድ ዩንቨርስቲ፣ ስዊድን 


1. ምክንያተ ጽሑፍ


በቀደመው ዘመን ኢትዮጵያዊነት መከበሪያ፣ መታፈሪያ እና ተፈልጎ የማይገኝ ማንነት ነበር፡፡ አገራችን ኢትዮጵያም የፍትህ አደባባይ፣ የስደተኞች መጠጊያ፣ ለግፉዓን ዘብ የምትቆም፣ በእምነቷ የምትታወቅ መንፈሳዊት ሀገር ነበረች፡፡ዛሬ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ኀያላን መንግሥታት እንደ ሀገር ሳይቆሙ እና መኖራቸውም ሳይታወቅ ኢትዮጵያ ኀያል ገናና እና በስልጣኔዋ የታወቀች ስለመሆኗ የጥንት መዛግብት ተባብረው ይመሰክራሉ::

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝ በኢትዮጵያዊነትና በአገር አንድነት ዙሪያ በማኀበራዊ የመገናኛ ብዙኀን እየተደረጉ ያሉ ሙግቶች ናቸው፡፡ በማኅበራዊ ገጾች ከሚሰራጩት ጽሑፎች መረዳት እንደሚቻለው በስደት ባሉ አንድአንድ ወገኖች ኢትዮጵያዊነት ከጎሰኝነት በታች የሆነ: ከዚህም አልፎ በጥቂቶች የተጫነ ማንነት ተደርጎ በመወሰድ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአብሮነት ልዩነትን: ከትልቅነት ትንሽነትን መርጠው የፈጠራና የተዛባ ታሪክ በመጥቀስ ኢትዮጵያዊነትን በማንኳሰስ ጎሰኝነትን ለማንገስ እና የአገር አንድነትን ለማፍረስ ሲቃዡ ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ ከሦስት ሺህ ዘመናት በላይ በአያት ቅድመ አያቶቻችን ዘርፈ ብዙ መስዋእትነት ተከብሮ የኖረው ኢትዮጵያዊነትና የአገር አንድነት አዲስ እንደተፈጠረ ማንነት የመነጋገሪያ ርእሰ ጉዳይ ሆኖ ከማየት በላይ ምን የሚያሳፍር ነገር አለ? 

በመሆኑም ያለውን የወረወረ ፈሪ አይባልምና እኔም በኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መነሻ ዙሪያ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት ይህችን መጣጥፍ ሳቀርብ የጎደለውን ሞልታችሁ የተሳሳተውን አርማችሁ በጥሞና እንደምታነቡልኝ ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ የጽሑፉ ዋና አላማ ኢትዮጵያዊነት እና ኢትዮጵያ በጥንቱ መዛግብት እንዴት እንደተገለፁ ማሳየት እንጂ መረጃዎችን መተንተን ወይም መተቸት አይደለም።

2. ስያሜ


እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እጅግ ጥንታዊ የሆነና ያልተቋረጠ ረጅም የመንግሥትነት ታሪክ ያላት አገር ነች፡፡ ብዙዎቹ እንደሚስማሙበትና የታሪክ ድርሳናት እንደሚነግሩን የኢትዮጵያ የመንግሥትነት ታሪክ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ይሳባል፡፡

አገራችን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን የስያሜዋን ምክንያት በተመለከተ ሦስት አይነት ትውፊታዊ ግምቶች ይገኛሉ፡፡ የመጀመሪያው ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ከግሪክኛ ቋንቋ የተወሰደና ትርጉሙም ፊቱን ፀሃይ ያቃጠለው (burned face) ማለት ነው ይላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በቅዱስ መጽሐፍ በኦሪት ዘፍጥረት የተጠቀሰውና ኢትዮጵያን ያቀና ነው ተብሎ የሚነገርለት የካም ልጅ ኩሽ  (ዘፍ 10÷6) “ኢትዮጵስ” በሚባለው ሌላኛው ስሙ ምክንያት አገራችን ኢትዮጵያ ተብላ መጠራት እንደጀመረች ያትታል፡፡ ሦስተኛው በቅድመ ልደት ክርስቶስ በአገራችን ከነበሩ ነገሥታት መካከል አንዱ ’ኢትዮጵስ’ ይባል ስለነበር አገራችንም በኢትዮጵስ ኢትዮጵያ የሚለውን መጠሪያ አግኝታለች የሚለው ግምት ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ’ኢትዮጵያ’ የሚለውን የአገራችን መጠሪያ ስም ከክርስቶስ ልደት ስምንት መቶ ዓመታት በፊት ጀምሮ በጽሑፍ መዛግብት ሰፍሮ እናገኘዋለን፡፡

ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ለመጠቀም ጥንታውያን ግሪኮች የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ለዚሁም ከክርስቶስ ልደት ስምንት መቶ ዓመታት በፊት የነበረው የታላቁ ባለቅኔ ሆሜር ኦልያድና ኦዲሴ የተባሉ ድርሰቶችና የታሪክ አባት ተብሎ የሚጠራው ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ ዓመታት በፊት የነበረው የሄሮዶቱስ መጽሐፍ ዓይነተኛ ምስክሮች ናቸው፡፡ ከጥንት ግሪኮች በፊት ኢትዮጵያ በጥንት ግብፃውያን የኩሽ ምድር ተብላ ትጠራ እንደነበር የሚያመክቱ ማስረጃዎችም አሉ፡፡ አገራችን አቢሲኒያ: ምድረ ሀበሻ ወዘተ የሚባሉ ሌሎች መጠሪያዎችም እንደነበሯት ይታወቃል፡፡ 

ኢትዮጵያ የሚለው ስም በቅዱስ መጽሐፍ ከአርባ ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል፡፡ ለአብነት ያህል በእብራውያን (አይሁዶች) ዘንድ ቶራህ ተብሎ በሚታወቀው እና ከክርስቶስ ልደት በፊት በ1400 ዓመተ ዓለም ገደማ እንደተጻፈ በሚታመነው በመጀመሪያው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ክፍል በኦሪት ዘፍጥረት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ቀድማ በሁለተኛነት ተጠቅሳለች (ዘፍጥረት 2÷13)፡፡

ኢትዮጵያ ከሚለው ጥንታዊ መጠሪያ ጋር የቀደምት ነዋሪዎቹ (የሕዝቦቹ ) ማንነት ጉዳይ ተያይዞ መነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ በቁጥር ቀላል የማይባሉ ሰዎች ኢትዮጵያ ማለት በግሪክኛ ፊቱን ፀሃይ ያቃጠለው (burned face) ማለት ስለሆነ ቀደምት ነዋሪዎቹም ጥቁር (deep dark skin) ሕዝቦች ነበሩ ብለው ይገምታሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ተጨማሪ የታሪክ መዛግብትን በአስረጅነት በመጥቀስ ኢትዮጵያ ከመሠረቱ ጥቁሮችን ጨምሮ ስብጥር መልክ (mixed color) ሕዝቦች መኖሪያ ነበረች ይላሉ፡፡ ለምሳሌም በቅዱስ መጽሐፍ ነብዩ ኤርምያስ ‹‹ኢትዮጵያዊ መልኩን: ነበር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን››  (ኤር 13÷23) የሚለውን በመጥቀስ በንፅፅር የተነገረ የኢትዮጵያውያንን ሕብረ ቀለም (መልከ ብዙኀነት) የሚያመለክት ነው ይላሉ፡፡ ግሪካዊ ሆሜር በኦልያድ ቅኔው የኢትዮጵያ  ሰዎች በውበት የተደነቁ ናቸው በማለት ገልጿቸዋል፡፡ የታሪክ አባት ሄሮዶቱስ ደግሞ በሦስተኛው መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን ከሰዎች ሁሉ በውበትና በቁመት የሚበልጡ ኃያላን ናቸው ይላል፡፡ ከነዚህ እና ከመሳሰሉት ጥንታዊ መዛግብት በመነሳት አገራችን ‹‹ኢትዮጵያ›› የሚለውን ስያሜ ያገኘችው በዚያን ዘመን  በነበረው መልከዓ ምድራዊ ክልል ይኖሩ የነበሩ የቀደምት የሕዝቦቿን ህብረ መልክዕ (ስብጥር የቆዳ ቀለም) መሠረት በማድረግ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ግምት አለ፡፡

3. ወሰነ ክልል 


የጥንቷን ኢትዮጵያ ወሰነ ክልል በተመለከተ ከዚህ እስከዚህ ድረስ ነበር ብሎ በትክክል ለመናገር አያስደፍርም፡፡ እንደ ጥንታዊ መዛግብቱ ከሆነ እጅግ ሰፊ የሆነና በተለያየ ዘመናት አንዴ ሲሰፋ ሌላ ጊዜ ጠበብ ሲል የነበረ ሆኖም ግን የዛሬዋን ኢትዮጵያ ማዕከል ያደረገ እንደነበር መረዳት አያዳግትም:: ከክርስቶስ ልደት በፊት 1400 ዓ.ም. ገደማ የተጻፈው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ (ኦሪት ዘፍጥረት) ከኤደን ገነት የሚመነጨው ሁለተኛው ወንዝ ጊዮን የኢትዮጵያን መሬት ይከባል በማለት የዛን ጊዜዋ ኢትዮጵያ መሠረቷ የአሁኗን ኢትዮጵያን ጭምር እንደሚያካትት ይጠቁማል (ዘፍ. 2÷1):: በሌላ የብሉይ ኪዳን  የዕብራውያን መጽሐፍ ‹‹አርጤክስ ከህንድ ጀምሮ እስከ ኢትዮጵያ ድረስ በ127 አገሮች ላይ ነገሠ (አስቴር 1÷1÷8÷9) በማለት መልክዓ ምድራዊ ፍንጭ ሰጥቷል:: ከክርስቶስ ልደት በፊት 687 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረው ነብዩ ኢሳያስ ደግሞ ቲርሐቅ የተባለው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ግብፅ ድረስ ያስተዳድር እንደነበረ ገልጿል (ኢሳ. 37 ÷9-11፣ 1ኛ ነገሥት 19:9)፡፡ የዚህ ጥቁሩ ፈርኦን በመባል የሚታወቀው ኢትዮጵያዊ ንጉስ በአርኪኦሎጂ ጥናትም የተረጋገጠ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ690-664 ዓ.ዓ. ግብፅን ያስተዳድር አንደነበር ተመዝግቧል፡፡

የጥንት ግሪኮች ኢትዮጵያ ደግሞ ሰፊ መልከዓ ምድራዊ ግዛትን ያካለለ ሲሆን ከግብፅ በስተደቡብ ያለውን አጠቃላይ የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ ክፍል ‹‹ኢትዮጵያ›› በማለት ይጠሩት ነበር፡፡ ሆሜር በድርሰቶቹ ኢትዮጵያ ትሮይንና የዓረቡን ምድር ትገዛ እንደነበር ገልጿል፡፡ ሄሮዱቱስ ስለኢትዮጵያ ሲያነሳ የአባይ ወንዝና ትልቁን ሐይቅ በማመልከት የመልከዓ ምድራዊ ጥቆማ ሰጥቷል፡፡ ፕሊኒ የተባለው ሌላው ግራካዊ ኢትዮጵያ በጥንቱ ዘመን ሃያልና ዝነኛ እንደነበረችና ሶሪያንና እስከ ሜድትራኒያን የባህር ዳርቻ ድረስ ትቆጣጠር እንደነበር ጽፏል፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት 60 ዓ.ዓ. ገደማ የነበረ ዲኦዶረስ ሲኩለስ የተባለ ጸሐፊ ደግሞ ኢትዮጵያ የግብፅ ትውፊትና ስልጣኔ መነሻ መሆኗንና ኢትዮጵያውያን እስከ ህንድ ውቅያኖስ ድረስ ያስተዳድሩ እንደነበር ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ዘመን የነበረ ትራቦ የተባለ ሌላኛው የግሪክ ጸሐፊ የኢትዮጵያ ግዛት ዓረብን ብቻ ሳይሆን እስከ አውሮፓ ድረስ እንደሚዘልቅ አመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ የግዛት ክልል ቀይ ባህርን ተሻግሮ ደቡብ ዓረቢያ ድረስ ይዘልቅ እንደነበር የታዋቂዎቹ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት የ4ኛው መቶ ክ/ዘመኑ ኢዛናና የ6ኛው መቶ ክ/ዘመኑ ካሌብ የመታሰቢያ ሃውልት ጽሑፎች አይነተኛና ህያው ምስክሮች ናቸው፡፡ አስቀድሞ እንደተገለጸው ምንም እንኳ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ወሰነ ክልል በትክክል ለመናገር ባይቻልም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ3ኛውና ከ4ኛው መቶ ክ/ዘመን ጀምሮ ያሉ ማስረጃዎች የዚያን ጊዜዋ ኢትዮጵያ አክሱምን ማዕከል ያደረገና ከአሁኑ ኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይነት ያለው እንደነበር ያመለክታሉ፡፡

4. የጥንት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን መታወቂያዎች


የጥንቷ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በሌሎች ዘንድ የተከበሩ፣ የሚታፈሩ፣ የሚደነቁ፤ በእምነታቸው ቀናኢነት፣ በፍትሃዊነት፣ በደግነት፣ በትህትና እና በሌሎች መሰል መልካም ምግባራት የሚታወቁ እንደነበር የሚመሰክሩ በርካታ መዛግብት አሉ፡፡ ግሪካዊ ባለቅኔ ሆሜር ኢትዮጵያውያን በጠባይ ጭምቶችና ትህትናን የተሞሉ ናቸው በማለት ጽፏል፡፡ ሆሜር በማከልም ኢትዮጵያውያን በፍትሃዊነት እና እኩልነት የታወቁ በመሆናቸው አምላክ ከመኖርያው ከሰማይ ወርዶ ዘወትር እነርሱን ይጎበኝ ከእነርሱም ጋር በዓል ያደርግ ነበር ብሎ ገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ6ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረው የቢዛንታይኑ እስጢፋኖስ ኢትዮጵያውያን በፍህታዊነታቸው ምክንያት በአምላክ የተወደዱ ነበሩ በማለት ገልጿል፡፡ በመቀጠልም ይሕ ጸሐፊ ኢትዮጵያ በምድራችን መጀመሪያ የተመሠረተች አገር ነች፡፡ ኢትዮጵያውያንም አምልኮተ እግዚአብሔርን በማስተዋወቅና ህግን በመስራት  በዓለም የመጀመሪያ ህዝቦች ናችው ብሏል፡፡

በቅዱስ መጽሐፍ ኢትዮጵያውያን በእምነታቸው የታወቁ በምግባራቸው የተደነቁ እንደነበሩና አገሪቱም ሀገረ እግዚአብሔር እንደሆነች በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› (መዝ. 67 (68)÷31) በማለት የገለጸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ እስራኤላውያንን ከግብፅ የፈርኦኖች አገዛዝ ነፃ ያወጣቸውና ባህረ ኤርትራን ከፍሎ ያሻገራቸው ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን ለጋብቻ መርጧል (ዘኁልቁ 12÷1)፡፡ ከኢትዮጵያዊ አማቱም ልዩ ልዩ ምክሮችን ይቀበል ነበር፡፡ በቤተመንግሥት ባለሟል የነበረው ኢትዮጵያዊ አቤሜሌክ ነብዩ ኤርምያስን ከጉድጓድ እንዲወጣ አድርጎ ከሞት አትርፎታል (ኤር. 38÷7¬-13)፡፡ በትንቢተ አሞፅም “የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁም” (አሞፅ 9÷7) በማለት በእግዚአብሔር ዘንድ ልቀው የተገኙ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ ነብዩ ኢሳኢያስ ግብፅን ይገዛ የነበረው ቲርሐቅ የተባለው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ ኢየሩሳሌምን ከአሦራውያን ጥፋት እንዳዳነ ጽፏል (ኢሳ. 137÷10-11)፡፡ ነብዩ ናሆም ኢትዮጵያና ግብፅ የነነዌ ጠንካራ ደጋፊዎች እንደነበሩ ገልጿል (ናሆም 3÷9)፡፡ የሰለሞንን ጥበብ ለማየት ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘችው ንግሥት ሳባ ‹‹አንተን የወደደ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን›› (1ኛ ነገ.10÷25) በማለት እምነቷን ገልፃለች: ፈጣሪዋን አመስግናለች፡፡ በትንቢተ ሶፎንያስ ‹‹ከኢትዮጵያ ወንዞች ማዶ የሚማልዱኝ የተበተኑት ሴት ልጆቼ ቁርባኔን ያመጡልኛል›› (ሶፎንያስ 3÷10) በሚል ተመዝግቧል፡፡ መዝሙረኛው ንጉሥ ዳዊት ኢትዮጵያውያንን የፅዮን ልጆች ብሎ ጠርቷቸዋል (መዝ 86(87) ÷ 4-5) ፡፡በዘመነ ሃዲስ የትንቢተ ኢሳኢያስን መጽሐፍ በማንበብ ላይ የነበረውን ኢትዮጵያዊውን የንግሥት ህንደኬ ባለሟል (ጃንደረባው) ሐዋርያው ፊሊጶስ የምታነበውን ታስተውለዋለህን ብሎ ሲጠይቀው የሚመራኝ (የሚነግረኝ) ሳይኖር ይህ እንዴት ይሆናል በማለት የመለሰው መልስ ፍፁም ትህትናውንና መንፈሳዊነቱን ይገልጻል (የሐዋ. ሥራ 8÷26-40) ፡፡

ስለነብዩ ሙሐመድ የህይወት ታሪክ በሚያወሳው ታላቁ የእስልምና የትውፊት መጽሐፍ ነብዩ ሙሐመድ በወገኖቻው በመካ ቋሪሾች ሲሳደዱ ለነበሩት ተከታዮቹ ‹‹ወደ አቢሲኒያ ብትሄዱ ማንንም የማያሳድድ ደግ ንጉሥ ታገኛላችሁ:: ይህ አገር የእውነተኞች ምድር በመሆኑ እግዚአብሔር ከመከራችሁ ያሳርፋችኋል›› በማለት ወደ ኢትዮጵያ እንደላካቸው ተዘግቧል፡፡ በወቅቱ የነበረው ክርስቲያኑ የኢትዮጵያ ንጉሥም ከየት መጣችሁ፣ እነማን ናችሁ፣ እምነታችሁ ምንድን ነው ሳይል በክብር ተቀብሎ ማረፊያ በመስጠት ክፉውን ቀን እንዲያሳልፉ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚያ ቀደም ብሎ ከልዩ ልዩ የግሪክና የሮማ ግዛት በሃይማኖታቸው ምክንያት የተሰደዱ ክርስቲያን መነኮሳት ኢትዮጵያ መጠጊያ እንደሆነቻቸውና እነርሱም በምድረ ኢትዮጵያ ገዳማትን በማስፋፋትና መጽሐፍትን በመተርጎም ታላቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል፡፡ እንደነዚህ ታሪኮች ከሆነ ኢትዮጵያ እምነት፣ ቀለምና ዘር ሳትለይ የስደተኞችን መብት በማክበር በዓለማችን ቀዳሚዋ አገር ሳያደርጋት አይቀርም፡፡

በርካታ ጥንታዊ መዛግብት ኢትዮጵያ ሃያል አገርና በልዩ ልዩ ማዕድናት የበለፀገች ምድር እንደነበረች ይገልፃሉ፡፡ ግሪካዊ ባለቅኔ ሆሜር ኢትዮጵያውያን በጉልበት ሃያላን ነበሩ በማለት ጽፏል፡፡ ሄሮዶቱስ ደግሞ የአባይ ወንዝ የሚመነጭበት፣ የወርቅ ማዕድን በብዛት የሚገኝበት ትልልቅ ዝሆኖች ያሏት እና የተለያዩ ዓይነት ዛፎች (ዕፅዋቶች) የሚበቅሉባት አገር እንደሆነች መዝግቧል፡፡ ዴኦዶሮስ የተባለው  ጸሐፊ ደግሞ ኢትዮጵያ ሀብታም፣ በወርቅ ማዕድን የበለፀገች፣ ጠንካራ አስተዳደር ያላት፣ በጠንካራ ነገሥታትና በህግ የምትመራ አገር እንደነበረች ገልጿል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ዛራህ የተባለ ኢትዮጵያዊ የጦር መሪ በሚሊዮን የሚቆጠር ሰራዊት ይመራ እንደነበር ተገልጿል (2ኛ ዜና 14÷9)፡፡ የሳባ ንግሥት ለጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን በርካታ የከበሩ ማዕድናትን በስጦታ ማበርከቷ ተጽፏል (1ኛ ነገሥት 10÷1-13)፡፡ በነብዩ ኢዮብ ደግሞ ኢትዮጵያ ከጥበብ ጋር የተነፃፀረ ቶጳዝዮን የተባለ የከበረ ማዕድን መገኛ እንደሆነች ተጠቁሟል (ኢዮብ 28÷9)::  

ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን የነበረው ማኒ የተባለው ጸሐፊ አክሱምን ማዕከል ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ኃያላን መንግሥታት መካከል በሦስተኛ ደረጃ አስቀምጧታል (መንግሥታቱም ሮም፣ ፐርሺያ፣ አክሱምና ቻይና ነበሩ)፡፡ የቢዛንታይኑ ንጉሥ ኮንስታንቶስ 2ኛ (ነገሠ እ.ኤ.አ 335-336 ዓ.ም) ኢትዮጵያን ከጎኑ ለማሰለፍ የዲፕሎማቲክ መልዕክት በመላክ ጥረት አድርጓል፡፡ ሌላኛው የቢዛንታይን ንጉሥ ጁሰቲን ቀዳማዊ (ነገሠ እ.ኤ.አ 518-526 ዓ.ም) በደቡብ ዓረቢያ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ከአይሁድ መከራ እንዲታደጋቸው ለኢትዮጵያዊ ንጉሥ አፄ ካሌብ ተማፅኖ  ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ አፄ ካሌብም ባደረገው ዘመቻ ክርስቲያኖችን ነፃ አውጥቷል፡፡ ተከታዩ የቢዛንታይን ንጉሥ ታዋቂው ጁስቲንያን (ነገሠ እ.ኤ.አ 526-565 ዓ.ም) ደግሞ ከፐርሺያ ጋር ሊያካሂድ ላሰበው ጦርነት የኢትዮጵያን ድጋፍ ለማግኘት የዲፕሎማቲክ መልዕክተኞቹ መላኩ ታውቋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ማሳያዎች አገራችን ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ሕዝቦችና አገሮች ደህንነትና ነፃነት ታደርግ የነበረውን ድጋፍና በወቅቱ የነበራትን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት፣ ክብርና ሚና የሚያመለክቱ ናቸው፡፡

በጥንቱ የታሪክ ዘመን ስለነበረው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ብዙ ነገር ለማንሳት ቢቻልም አንባቢን ላለማሰልቸት ስል በቀጥታ ወደማጠቃለያየ አልፋለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ በወፍ በረር የተነሱት እስከ 6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ያሉት የተወሰኑ ታሪካዊ ኩነቶችና ማስረጃዎች ስለሆኑ እግዚአብሔር ዕድሜና ጤና ከሰጠኝ ሌሎች ያልተነሱ ጉዳዮችንና የቀጣይ ዘመናት ታሪካዊ ክስተቶች በሌላ ጽሑፍ የምመለስባቸው ይሆናል፡፡

5. ማጠቃለያ


አስቀድሞ ከቀረበው  ጽሑፍ መረዳት እንደሚቻለው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ምሥረታ በጥቂት ጎሳዎች፣ በውስን የቦታ ክልል፣ በጥቂት ቋንቋ ተናጋሪዎች ወዘተ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ከታሪክ እንደምንማረው የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የመሠረት ድንጋይ ለማስቀመጥ ዘር፣ ቋንቋ፣ ጎሳ፣ ቀለም፣ የተወሰነ የቦታ ክልል በመስፈርትነት አልተቀመጠም፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሁሉም የአገራችን ሕዝቦች መኖሪያና ማንነት እንጅ ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ መስጠት ያልተጻፈ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ራስን የመግደል/ አጥፍቶ የመጥፋት/ ወንጀል መፈጸም ነው፡፡ በዘመናችን የሚገኙ አንድ አንድ ጎሰኞች ወደኋላም ወደፊትም መሄድ የማይችሉ የአእምሮ ህሙማን በመሆናቸው ዛሬ የሆነ ነገር ላይ ተቸክለው ከትናንት የማይማሩ ለነገ ደግሞ የማይኖሩ ናቸውና ሊታዘንላቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ሰዎች ትናንትን ስለማያውቁ መሰረት የላቸውም ነገንም እንዳያዩ ርእይ አልባ ናቸው፡፡

የጥንቱ ዘመን ኢትዮጵያ ግዛት አልፎ አልፎም ቢሆን በስተሰሜን እስከ ግብፅ ድረስ፣ ቀይ ባህርን ተሻግሮ እስከ ደቡብ አረቢያ እንዲሁም በርካታ የምስራቅ አፍሪካ አካባቢዎችን ያካትት እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ፡፡ በአንፃሩ በዘመኑ የምንገኝ ሰዎች የዛሬዋን ኢትዮጵያ እንደ ገና ዳቦ ሸንሽነን ሸንሽነን /በሃሳብም ቢሆን/ የት ልናደርሳት እንደሆነ አይታወቅም፡፡ የቀድሞዋ ኢትዮጵያ የስደተኞች መጠጊያ፣ የደካሞች ምርኩዝ፣ የችግረኞች ተስፋ፣ የፍትህ ማዕከል፣ የእውነተኞች ምድር እንዳልነበረች፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ልጆቿ መጠጊያ የሌላቸው ስደተኞች፣ ርዳታ የሚለምኑ ርሃብተኞች፣ የሌሎችን ድጋፍ የሚሹ ደካሞች፣ በፍትህ እጦት የሚሰቃዩ ምስኪኖች ሆነዋል፡፡

በጥንቱ ዘመን ምድቧ ከኃያላን መንግሥታት ጋር ሆኖ በማንነቷ ታፍራና ተከብራ የዓለም ቁንጮ የነበረችው አገር ዛሬ በማናቸውም መስፈርት የዓለም ግርጌ ላይ ተቀምጣ ልጆቿ አንገታቸውን ሲደፉ በየሄዱበት ሲገፉ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ እርስ በርሷ የምትለያይ መንግሥት ትጠፋለች እንደተባለው: ለዚህ ሁሉ ውርደትና መከራ ካበቁን ነገሮቸ አንዱና ዋነኛው ከአብሮነት ልዩነትን፣ ከመተባበር መነቃቀፍን፣ ከአንድነት መነጣጠልን፣ ከኢትዮጵያዊነት ጎሰኝነትን፣ ከቅንነት ምቀኝነትን፣ ከመደጋገፍ መጠላለፍን መምረጣችን ነው፡፡ አሁንም ከታሪክና ከሌሎች የማንማርና በዚሁ የምንቀጥል ከሆነ አወዳደቃችን የከፋ እንዳይሆን ያስፈራል፡፡ ስለሆነም የአብሮነታችንን ጥንታዊ መሠረት እንወቅ፣ የጎሰኝነት ድሪቷችን እናውልቅ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችን እናጥብቅ፡፡ 
በመሠረቱ መታወቅ የሚገባው:-

ኢትዮጵያዊነት ከፈጣሪ የተሰጠን ፀጋ እንጅ ለድርድር የሚቀርብ የሸቀጥ ዕቃ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያዊነት የደም ማተባችን እንጅ ሲያሻን የምናጠልቀው ሳንፈልግ የምናወልቀው  
        አርቴፊሻል ጌጥ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያዊነት ሳንፈልገው በግድ የተጫነብን ዕዳ ሳይሆን የተዋብንበት ጌጣችን፣ የከበርንበት 
        ዘውዳችን፣ የወረስነው ቅርሳችን ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ክብር እንጅ ውርደት ሽልማት እንጅ ቅጣት አይደለም፡፡

ኢትዮጵያዊነት አንድነት በብዙኀነት ብዙኀነት በአንድነት የሚመሰጠርበት የህብር ቅኔ፣ 
       በጎሰኞች የማይፈታ ሰምና ወርቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት የማይነቃነቅ ፅኑ መሠረት፣ ዘመን የማሽረው ማንነት፣ የማይቋረጥ ጅረት ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ዘመንን ከዘመን ትውልድን ከትውልድ የሚያገናኝ ህያው ድልድይ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት በጎሰኞች ጫጫታ የማይፈርስ  በደም የተገነባ የመስዋዕትነት ታሪካችን ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት በወጀብና አውሎ ነፋስ የሚፈርስ የድቡሽት ቤት ሳሆን በፅኑ መሠረት ላይ 
        የተጣለ የአብሮነት  ሃውልት ነው፡፡
                          

ማጣቀሻዎች /References/ 

Budge, Wallies E.A., 1928. History of Ethiopia, Nubia and Abyssinia (Vol. I). Routledge: Taylor and  Francis Group.

Ethiopian Orthodox Tewahdo Church Holy Synod, 1990. Today’s Ethiopia is Ethiopia of the Holy Scriptures, History and Antiquity: Resolution of the Holy Synod of the Ethiopian Orthodox Tewahdo Church. Addis Ababa.

Frank M. & Snowden, Jr. 1970. Blacks in Antiquity: Ethiopia in the Greco-Roman Experience. The Belknap Press of Harvard University Press; Cambridge, Massachusetts, London.

Levine, Donald N. 1974. Greater Ethiopia: the Evolution of a Multiethnic Society. The University of Chicago Press: Chicago and London.

Mohammed Girma, 2012. Understanding Religion and Social Change in Ethiopia: Toward a Hermeneutic of Covenant. Palgrave: Macmillan 

Sergew Hable Sellassie, 1972. Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270. Addis Ababa.
Tekeste Negash, 2016. Woven into the Tapestry: How Five Women Shaped Ethiopian History.

The Holy Bible (Amharic Version)
http//www.taneter.org/Ethiopia.htm/

Friday, January 13, 2017

በጎንደር እና ጎጃም ሕዝብ ላይ በአዲስ መልክ የታወጀውን የሕወሓት የደም ማፍሰስ እና የዘር ማጥፋት ዘመቻ የማይቃወም ኢትዮጵያዊ እና የኢትዮጵያ ክፍል የህዝቡ ደም በእጁ ላይ እንዳለ ይወቅ! (የጉዳያችን ማሳሰቢያ)

ጉዳያችን / Gudayachn
www.gudayachn.com
=============================================================
በጎንደር የገጠር እና ከተማ ነዋሪ ሕዝብ ላይ ሕወሓት አዲስ እልቂት ለመፈፀም ሰራዊት እያስገባ ነው።ለኢሳት ዛሬ መለጫ የሰጡት የጎንደር ሕብረት ሰብሳቢ አቶ አበበ ንጋቱ የጎንደር ሕዝብን ደም ለማፍሰስ በ40 መኪና ተጭኖ ከተለያየ አቅጣጫ ወደ ጎንደር የተለያዩ መሬቶች ገብቷል። ይህ የኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤት ከሆነው ክፍል ውስጥ አንዱ በሆኑት በጎንደር እና በጎጃም ላይ  የመዝመት እና የማጥፋት ዘመቻ ነው።

የኢትዮጵያውያን ደም በከንቱ ሲፈስ እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ተግባር ሊሆን አይችልም።ጉዳዩ በዝምታም፣በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ መንገድ የሕዝቡ ደም ሲፈስ የተሳተፉ ሁሉ በእጃቸው ላይ የንፁሃን ደም እንዳለ ሊያውቁት ይገባል።ይህንን እልቂት ለማስቆም ከአዲስ አበባ እስከ ወለጋ፣ ከወለጋ እስከ አክሱም፣ከአክሱም እስከ ሞያሌ እና ጅጅጋ ያለ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በቸልታ ሊያልፈው አይገባም። ሕወሓት ስልጣኑን እንደሚያጣ ሲያውቅ የዘር ማጥፋት ዘመቻ በጎንደር እና ጎጃም ላይ እንደሚያውጅ ቀድሞም ይታወቅ ነበር።አሁን በአዲስ መልክ ሊፈፅመው እየተዘጋጀ ያለው የእልቂት ድግስ በመጪዋ ኢትዮጵያ ላይ ጥሎ የሚሄደው ጠባሳ ጥሎ የሚሄድ ታሪካዊ ስህተት ነው። በሌላ በኩል  እነኝህን አካባቢዎች ማጥፋት ኢትዮጵያ ካሏት ልዩ ልዩ አሻራዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን    የማጥፋት ተግባር በሕወሓት እየተከናወነ እንደሆነ ማወቅ ይገባል።

ባጭሩ በጎንደር እና ጎጃም ላይ የተደገሰውን አዲስ የደም ማፍሰስ እና የዘር ማጥፋት የሕወሓት ዘመቻ በዝምታ መመልከት እና ሕወሓትን በሁሉም አቅጣጫ አለመቃወም በጎንደር እና ጎጃም ሕዝብ ደም ላይ እጅን መንከር ነው።


ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Wednesday, January 11, 2017

አባቴ ይሙት እንዳትለኝ ! አንተን ሲወልድ ነው ሞቱ! (የ2 ደቂቃ ድንቅ ቪድዮ)

በእዚህ ሳምንት በአማኑኤል ደመቀ ለማለዳ ኮከቦች ለውድድር የቀረበ  የጥበብ ሥራ።
ከማለዳ ኮኮቦች ውድድር ላይ የተወሰደ Yemaleda Kokeboch Season 3 Ep 3



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

በጎንደር እስክስታ፣ ፈረንጁ ሲረታ! Ethiopia - Gondar dance



ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Tuesday, January 3, 2017

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትሄድበትን መንገድ እያየን የነገ መውጫውን ካሁኑ መተለም የግድ ይላል (ክፍል 2 እና የመጨረሻው)



የአርባ ሶስት አመታቱ የፖለቲካ አለመረጋጋት 

ከእዚህ ፅሁፍ በፊት በተመሳሳይ ርእስ በክፍል አንድ ላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ሂደት ላይ መስራት እንደሚያስፈልግ እና ለእዚህም ሃሳብ ማምጣት እንደሚገባ ለመግለፅ ተሞክሯል።እንደ ኢትዮጵያ ባለ ከአርባ አመታት በላይ ባልተረጋጋ፣በአምባገነን እና የጎጥ ፖለቲካ ሲታመስ ለኖረ ሀገር እና ሕዝብ መጪ ጉዳይ ላይ የመስራት አስፈላጊነት ላይ መነጋገር እና ኃላፊነቱ የማን እንደሆነ ማውሳት ከጊዜው የቸኮለ ሃሳብ ሊመስል ይችላል።ለእዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ስልጣንን በተደጋጋሚ ከህዝብ ነጥቀው በሕዝብ ደም የታጠቡ መንግሥታት ከአንዴም ሁለቴ ኢትዮጵያን የመምራታቸው እውነታ ነው።በ1966 ዓም የተነሳው የኢትዮጵያ ግብታዊ አብዮት በኃይል የነጠቀው ወታደራዊ ደርግ  መስከረም 2፣1967 ዓም የቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴን መንግስት ከስልጣን ማውረዱን ሲያውጅ ¨ኢትዮጵያ ትቅደም ካለምንም ደም¨ የሚል መፈክር በታንኮቹ ላይ ሁሉ እየሰቀለ ነበር።ሆኖም ግን ደርግ ስልጣን ለሕዝብ እመልሳለሁ ያለውን ቃል አጥፎ በ1972 ዓም ኢሰፓአኮ (ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን)፣ በ1977 ዓም ደግሞ ኢሰፓ (ኢትዮጵያ ሰራተኞች ፓርቲ) መሰረትኩ ብሎ ከኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማርያም ሊቀመንበርነት ጀምሮ እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ እራሱ ወታደሩ ስልጣኑን ተቆጣጠረ።

ከደርግ በከፋ መልኩ ሕወሓት በ1983 ዓም አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ¨ዲሞክራሲ የህልውናችን መሰረት ነው¨ የሚል ማባበያ ንግግር እየተጠቀመ የህዝብን ስልጣን ብቻ ሳይሆን የንግድ እና ምጣኔ ሀብት መዋቅር  በሙሉ በአንድ መንደር እና ስብስብ ስር እንዲውል አደረገ።ኢትዮጵያ የጥቂቶች የግል ንብረት እስክትመስል ድረስ ከመሬት እስከ ጉልት ንግድ ድረስ ለሕወሓት ታዛዥ የሆኑ ብቻ እንደፈለጉ የሚሆኑበት ሆነ።የሕወሓት እኩይ ተግባራት ከደርግ የከፋ የሆኑበት አያሌ ነጥቦችን መጥቀስ ይቻላል።ደርግ በሙስና ተግባር እና የኢትዮጵያን ሕዝብ የዜግነት መብት በመግፈፍ አይታወቅም።ሕወሓት ግን በሙስና እና ኢትዮጵያውያን የዜግነት መብታቸውን በጎሳ ስም በመግፈፍ ወደር አልተገኘለትም።በደርግ ዘመን አንድ ሰው በሀገሩ የትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሶ ለመስራት ጎሳው አይጠየቅም።በሕወሓት ዘመን አንድ ሰው ከአንዱ ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ተንቀሳቅሶ ለመስራት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ከኖሩበት መሬት በጎሳ ስም የተፈናቀሉበት ዘመን ነው።ደርግ ከ17 አመታት አገዛዝ በኃላ ስልጣኑን ሲለቅ፣ሕወሓት ደግሞ ከ26 አመታት አገዛዝ በኃላ ላለመውደቅ እየተንገዳገደ ነው።መንግሥታት ይመጣሉ ይሄዳሉ። ትልቁ ቁምነገር ግን ኢትዮጵያን እንዴት በኢትዮጵያዊነቷ እንድትቀጥል እናድርግ? የነገዋ ኢትዮጵያ ባለፉት 43 አመታት ከነበረችበት የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዴት መውጣት ትችላለች? ከፖለቲካው በተጨማሪ ሌላው ቁልፍ ተግባር ምን መሆን አለበት? የሚሉት ጥያቄዎች  መመለስ መቻሉ ነው።

ከአርባ ሶስት አመታት በኃላም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙርያ የሚታዩት ሶስቱ ክፍሎች 

ኢትዮጵያ ላለፉት አርባ ሶስት አመታት ያህል በጦርነት፣በርሃብ፣በፍትህ እጦት እና በስደት ከተጎሳቆልን በኃላም  ¨የኢትዮጵያ ፖለቲካ¨ ተብሎ በሚጠራው አስተሳሰብ ዙርያ ያሉት የአስተሳሰብ ጥጎች በሶስት የግለሰብ እና ማኅበረሰብ አስተሳሰቦች ማጠቃለል ይቻላል።እነኝህ ሶስቱ አስተሳሰቦች:

1/ በወደፊቷ ኢትዮጵያ  ሁኔታ  ላይ ተስፋ ብቻ የተሞሉ 
በእዚህ ክፍል ውስጥ ይካተታሉ የምላቸው በመጪው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ በጎ ተስፋ ያላቸው ናቸው።ለተስፋቸው መነሻ ነጥባቸው ግን ድፍን ተስፋነት ይታይበታል።በድፍኑ ሕወሓት ይወድቃል፣መጪው የኢትዮጵያ ፖለቲካም ላለፉት አመታት ያየነውን አይነት ሊሆን አይችልም የሚል እሳቤ ይይዛል። ይህ ግን እንዴት ሊሆን ይችላል? ለሚለው ጥያቄ ግልፅ የሆነ መልስ አልያዙም።ብዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእዚህ ተስፋ ውስጥ እንዳለ መገመት ይቻላል።ተስፋው በእራሱ በጎ ነገር ቢሆንም በእዚህ ተስፋ ውስጥ ያሉ ሁሉ ግን የእራሳቸው ድርሻ ካልተጨመረበት የነገዋ ኢትዮጵያን በብሩህ ተስፋ ማየት እንደማይቻል አለመታሰቡ ነው ክፋቱ።በእዚህ ሃሳብ ስር በውጭ ሀገር የሚኖሩ ምሁራን፣የንግድ ሰዎች፣በሀገር ቤት በልዩ ልዩ ሙያ የተሰማሩ ሁሉ ይካተቱበታል።በአቅም ደረጃም የደረጁ እና ለሀገራቸው የበለጠ አስተዋፅኦ ለማድረግ የአሁኑ ስርዓት መውረድን በጉጉት የሚጠብቁ እና ሀገራቸውን የሚወዱም ናቸው።

2/ በወደፊቷ ኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ከተስፋ ባሻገር ድርሻ እንዳላቸው የሚያምኑ

ይህ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ላለፉት አርባ ሶስት አመታት ከገባችበት አጣብቂኝ የማውጣት አጀንዳ መቅደም እንዳለበት ያራምዳል።አጣብቂኙ የአምባገነን ስርዓት፣የፍትሕ እጦት፣የአንድ ጎሳ የበላይነት ሁሉ ይጨምራል።በእዚህ ሃሳብ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያውያን ኢትዮጵያን ከእዚህ አጣብቂኝ ለማውጣት ድርሻዬን መወጣት አለብኝ የሚል ቁርጠኝነት የያዙ ግለሰቦች እና የማኅበረሰብ ክፍሎች ናቸው።በእዚህ ዙርያ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ ጋዜጠኞች፣የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አባሎች፣ አክትቪስቶች፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚሰሩ እና ሃሳብ የሚያፈልቁ ምሁራን ሁሉ ይጠቀሳሉ።

3/ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ አያገባኝም የሚሉ አስተሳሰቦች  

የእዚህ አይነቱ አስተሳሰብ ሰለባዎች ስደት የሚሄደውን ኢትዮጵያዊ ለምን ተሰደደ? ብለው የማይጠይቁ፣ የኢትዮጵያ የውጭ ብድር እየጨመረ እና የውጭ ምንዛሪ በባለስልጣናት እየተዘረፈ መሆኑን እየሰሙ ቃላት የማይተነፍሱ እና ኢትዮጵያ በሕወሓት የጎሳ ፖለቲካ ስትታወክ አይመለከተኝም በሚል ስሜት በቸልተኝነት የሚኖሩ ናቸው። እነኝህ የሀገራችን ዜጎች ስለሃገራቸው የማይጨነቁ ሆነው አይደለም።ሆኖም ግን ግማሾቹ ፖለቲካ ደክሟቸዋል።የተቀሩት በእለት ከእለት ኑሮ ውስጥ ተውጠዋል።ከፖለቲካ ውጭ የሚሰሯቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን እና እነኝህ ተግባራት ደግሞ ለነገዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ መሆኑን ያልተረዱ ናቸው።

ሶስቱም ክፍሎች ለኢትዮጵያ ያስፈልጋሉ 

ከላይ የተጠቀሱት በሙሉ ተስፋ ውስጥ ያሉትም ሆኑ፣ ድርሻቸውን አውቀው እየሰሩ ነገን  በተስፋ የሚያዩት እና የፖለቲካ ጉዳይ አያገባኝም ያሉት ሁሉ ለኢትዮጵያ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ናቸው።አንዳንዶች ስለፖለቲካ አያገባኝም የሚሉትን የኢትዮጵያ ጠላት አድርገው የሚፈርጁ አሉ።አንዳንድ ጊዜ ፖለቲካ አያገባኝም ያሉ ሰዎች ለሕብረተሰባቸው፣ለሀገራቸው እና ለዓለም ምን እየሰሩ ነው ብለን ጠጋ ብለን ስንመለክት በማኅበራዊ  ወይንም በምጣኔ ሀብት ዘርፍ ትልቅ ሥራ ላይ እንደሆኑ ትመለከታላችሁ።ይህ ማለት በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት ፖለቲካ ባያንፀባርቁ ለኢትዮጵያ ግን ዛሬም ነገም ጠቃሚ እሴቶች ናቸው። በእርግጥ እኔም ለመመለስ የምቸገርበት በከፍተኛ አቅም ያሉት እነኝህ ኢትዮጵያውያን   ፖለቲካ ያሉትን ባይነኩት የሰብአዊ መብት ሲጣስ እና ፍትህ ስትረገጥ ዝምታው ለነገ ትውልድም ጭምር ዋጋ እንደሚያስከፍል ምን ያህል ከግንዛቤ አስገብተውታል? የሚለው ጥያቄ አሁንም የሚነሳ እና ምላሽ የሚሻ ነው። ቁም ነገሩ ግን አሁንም ሶስቱም ክፍሎች ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ናቸው የሚለው ሃሳብ ነው።ችግሩ ሶስቱንም እንዴት ለሀገር ጥቅም እንጠቀምባቸው? ሶስቱ አስተሳሰብ ውስጥ ያሉት አንዳቸው ከአንዳቸው ሳይጋጩ እንዴት ያላቸውን አቅም ለነገዋ ኢትዮጵያ ህልውና እንደየዝንባሌያቸው እንጠቀምባቸው? የሚለው ነው። 
 

የኢትዮጵያ የነገን  ፖለቲካ ለማስተካከል ማን ምን የስራ?

ኢትዮጵያ አጠገባችሁ ነች።

ብዙዎች ለኢትዮጵያ ምን ለስራ? የእኔ ሚና እና ድርሻ ምንድነው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሲቸገሩ ይታያሉ።አሁን ባለንበት ጊዜ ለኢትዮጵያ መስራት ማለት ከሕወሓት ጋር ግብ ግብ መፍጠር ብቻ የሚመስላቸውም አሉ።በርግጥ ኢትዮጵያን ወደ ሚቀጥለው የተሻለ ደረጃ ለማሻገር አሁን በጎጥ ሕዝብ እና ሀገር ከፋፍሎ የሚገዛው ስርዓት መወገድ ጥያቄ ውስጥ አይገባም።ሁሉም ሰው ግን እኩል ተሰጥኦ እና ችሎታ አለው ማለት አይቻልም።ኢትዮጵያን ስናስባት ከሕወሓት ውድቀት በኃላ ስለምትኖረውም ማሰብ ስንጀምር ዛሬ መሰራት ያለባቸው ስራዎች ፍንትው ብለው ይታዩናል።ስለሆነም ከላይ ተራ ቁጥር 1 እስከ 3 በተጠቀሰው ስር የሚገኙ ሁሉ በየትኛውም ጥግ ላይ ቢቆሙ ለነገዋ ኢትዮጵያ መስራት የሚገባቸው በርካታ ስራዎች አሉ።ከእነዚህ ውስጥ በዋናነት ለእዚህ ፅሁፍ ላተኩርበት የምፈልገው የተዳከመውን ማኅበራዊ አንድነት ለመጠገን እና ያለውን ለማጠንከር ድርሻን መወጣት በሚለው ነጥብ ላይ ነው።

የተዳከመውን ማኅበራዊ አንድነት ለመጠገን እና ያለውን ለማጠንከር ድርሻን መወጣት 

ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን አደጋ ላይ ከሚጥሉት አደጋዎች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያውያንን ማኅበራዊ አንድነት መናጋት ነው።ብዙውን ጊዜ ሀገር የሚፈርሰው ድንበር ሲጣስ እና የውጭ ወራሪ ሲመጣ ብቻ የሚመስለን ጥቂቶች አይደለንም።አሁን ባለንበት ዓለም ግን በርካታ ስልታዊ ስራዎች በማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዘርፍ ላይ በመስራት በአንድ ሀገር ላይ ከባድ ጥፋት ማስከተል ይቻላል። ስለሆነም ኢትዮጵያ ነገን እንድትሻገር በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ጎሳን መሰርት ያላደረገ ማኅበራዊ አንድነትን ማጠንከሩ አንዱ አስፈላጊ ጉዳይ ነው ማለት ነው። በየትኛውም እድሜ ክልል ቢሆኑ ኢትዮጵያ ወደተሻለ ደረጃ እንድትደርስ ሊነሱ የሚገባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች አሉ። እነርሱም: በሰፈርዎ የሚሰሩ ምን ስራዎች አሉ? የሰፈርዎ ዕድር ፈርሷል? የሚኖሩበት የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ (ኮሚኒቲ) ተዳክሟል? ምን አይነት ኢትዮያጵያዊ ስብስቦች አሉ? የእርስዎስ ድርሻ በስብስቦቹ መጠናከር ዙርያ ምንድን ነው? የኢትዮጵያውያንን ህብረት፣መተሳሰብ እና አንድነት የሚይጥላላ ወይንም የሚያዳክም ተግባር አለ? ይህ የማዳከም ተግባር ካለስ እርስዎ ምን የመከላከል ሥራ ሰሩ? እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ፖለቲካዊ ያልሆኑ ነገር ግን ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትውልድ ማሻገር የሚችሉ ተግባራት አሉ።ብዙዎች እነኝህ የሚንቁት ምናልባትም ብዙ አንገብጋቢ ስራዎች የማይመስሏቸው ተግባራት ናቸው።በኢትዮጵያ ውስጥ ግን የጎሳ ፖለቲካ 26 ዓመታት ሙሉ ታውጆብን እንደ ሕዝብ በህብረት ያቆመን የማኅበራዊ አንድነታችን  ሙሉ በሙሉ ያለመፍረሱ እና መኖር ነው። 

የማኅበራዊ አንድነት አሁን ባለንበት ዘመን እራሱን የቻለ አንዲት ሀገር ከሚኖራት ሀብት መካከል የሚቆጠር ነው። ማኅበራዊ አንድነት በሀብት መልክ ሲገልጥ ደግሞ ማኅበራዊ ካፒታል ይባላል። ማኅበራዊ ካፒታል የአንድ ሕዝብ የማይዳሰስ ሀብት ውስጥ የሚመደብ እና የህዝብ የእርስ በርስ የመተማመን ደረጃ ሁሉ የሚገለጥበት አይነተኛ መንገድ ነው።

ማኅበራዊ ካፒታል መንከባከብ፣መጠበቅ እና መጎልበት ይፈልጋል።ይህ ካልሆነ በተቃራኒው እየቀጨጨ እና እየደከመ የመምጣት ዕድል ይገጥመዋል።ይህ ማለት ሀገር እና ሕዝብ በጋራ የሚቆሙለት የጋራ እሴት ሁሉ እየመነመነ ይመጣል ማለት ነው።ማህበራዊ ካፒታሉ የላላ ሕዝብ ደግሞ አምባገነኖችን ሊዋጋ ቀርቶ ወደ እርስ በርስ ግጭት የመግባት መጥፎ ዕድል ይገጥመዋል።

ባጠቃላይ ዛሬ ኢትዮጵያ የምትሄድበትን መንገድ እያየን የነገ መውጫውን ካሁኑ መተለም ማለት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከሀገር ቤት እስከ ባህር ማዶ ያለው ሁሉ አካባቢውን በአግባቡ እንዲቃኝ ማስቻል ነው።ዛሬ በአካባቢያችን ባሉ ኢትዮጵያውያን ዙርያ ያልሰራናት ኢትዮጵያ ነገ ከየትም አናገኛትም። ምናልባት ለመልካም ሥራ ስንነሳ በእራሳችን ላይ የሚደርሱብን አያሌ በደሎች በጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኞች እና በሕወሓት ስውር ተንኮል ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። ሆኖም ግን መመልከት ያለብን ጥቂት ደካማ አስተሳሰብ ያላቸው ግለሰቦች ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የማይወክሉ መሆናቸውን ነው።በመሆኑም ከሕወሓት በኃላ የምትኖር ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር የግለሰቦችን በደል ወደ ጎን ትቶ ስለ ትልቅ ኢትዮጵያ ለመስራት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በአካባቢው የፈረሰውን ወይንም የተዳከመውን የኢትዮጵያውያን የጋራ ማኅበራዊ እሴት በሙሉ ለማጠናከር ቆርጠው መነሳት እና ወደ ሥራ መሰማራት አለባቸው። ያን ጊዜ የዛሬዋን ብቻ ሳይሆን የነገዋ ኢትዮጵያ የማይጎረብጣት ለም መሬት አዘጋጀን ማለት ነው።በእዚህም የኢትዮጵያን የቅርብም ሆነ የሩቅ ጠላቶችን ሕልም የማምከን ስልታዊ ሥራ መስራት ይቻላል።ማኅበራዊ አንድነታችንን እና እሴቶቻችንን እናጠናክር፣እንንከባከብ፣ አስፈላጊ ሲሆንም እንመስርታቸው።


ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...