የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈታኝ ሁኔታ ላይ ነች። በሀገር ቤት የ ፓትርያሪክ ''ምርጫ'' በሚል በተጣደፈ እና ግልፅነት በሌለው መልክ እየተካሄደ መሆኑን ሁሉም እየታዘበ ነው። ከ እዚህ በፊት ይህንን የቤተክርስቲያን ፈተና በተመለከተ በእዚሁ ጡመራ ላይ http://gudayachn.blogspot.no/2013/02/blog-post_21.html እና http://gudayachn.blogspot.no/2013/01/blog-post_16.html ሃሳብ ስለተሰጠበት እዚህ ላይ መልሼ ለማንሳት አልፈልግም።ሆኖም ግን ከእዚሁ ከሰሞኑ የ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ጋር በተያያዘ በቤተክርስቲያንም ሆነ በምእመናንም ላይ የማይሽር ቁስል የሚተው ሌላ ጉዳይ መከሰቱ እየተሰማ ነው።
እውነት
ነው
እግዚያብሄር በቤተክርስቲያን እና በምመናኗ ላይ እየደረሰ ያለውን ያያል።''ሞት ቢዘገይ የቀረ ይመስላል'' እንደሚባለው በቤተክርስቲያን ላይ በመንፈስቅዱስ መራጭነት የሚከወነው የፓትርያሪክ ምርጫ ለህሊና በሚከብዱ ብዙ ስርዓት የለሽ አካሂያዶች ታጅቦ የምርጫው ውጤት ይህን ፅሁፍ ከምፅፍበት ሰዓት አንስቶ ከ 48 ሰዓታት በታች እንደቀረው ከቤተክህነት እየተነገረ ነው።ይህ በእራሱ ይዞት የሚመጣው ውስብስብ ችግር እንዳለ ሆኖ በእጃችን ስላለው ነገር ግን ለመግታት ስለሚቻለው ሌላው ቤተክርስቲያን እና ምዕመናንን ለበለጠ ችግር የሚጥል፣አሁን ያለውንም ሆነ መጪውን ትውልድ አንገት የሚያስደፋ ተግባር እንዳይፈፀም ልንጮህ ይገባል እላለሁ።
ጉዳዩ በውጭ ሀገር ከሚገኙ
አባቶች እና ሀገርቤት መንግስት እጁን በከተተበት የቤተ ክህነት መሃከል በተደረገው የቃላት ልውውጥ መሃከል በአንድ በኩል ያልተረጋገጠ ነገር ግን ሊደረግ አይቻልም የማይባል ተግባር ከወደ አዲስ አበባ ተሰምቷል።ይሄውም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በ አራተኛው የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፓትርያሪክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ላይ አብጠልጣይ ፊልም ሊያሳይ እንደሆነ እየተነገረ መሆኑ ነው።ጉዳዩ ሐሰት ነው እንዳይባል የህወሓት ልሳን ነው በሚባለው ''ትግራይ ኦን ላይን'' ድህረ ገፅ ላይ ''ዲ/ን'' ሙሉጌታ በሚል ስም ስር በአቡነ መርቆርዮስ ላይ ያወረደው ውርጅብኝ የ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ያዘጋጀዋል ስለሚባለው አብጠልጣይ ፊልም መንገድ ጠራጊ አስመስሎታል።
ይህንኑ
የ
ኢቲቪ
ፕሮግራም አስመልክቶ በውጭ ከሚገኘው ሲኖዶስ አቡነ መቃርዮስ የኢሳት ራድዮ ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ በእሳቸው በኩልም በሀገርቤት በሚኖሩ አባቶች የተፈፀሙ ብዙ ማስረጃ ያላቸውን መረጃዎች ለሕዝብ እንደሚለቁ አሳውቀዋል። መንግስት በሕዝብ ገንዘብ በሚያስተዳድረው ቴሌቪዥኑ በውጭ በስደትየሚኖሩ አባቶችም በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን:: አንዱ የአንዱን ሸክም ሲያወራ ማን ይጠቀም ይሆን? በተለይ ከሀገርቤት በኩል የሚለቀቀውን ሁሉም አባቶች ተስማምተው ነው ማለት የማይቻል ከመሆኑም በላይ ፊልሙ የሚቀናበረውም በ ደህንነት ክፍል ስለሚሆን ምዕመኑ በግልፅ ካልተቃወመ በስተቀር ቤተክህነት በራሱ በታገተበት ሁኔታ ችግሩን ለመፍታት የሚችልበት ሁኔታ ላይ ላለመሆኑ ለመረዳት አያዳግትም።በነገራችን ላይ አቡነመቃርዮስም በግላቸውመረጃዎቹን እንደሚለቁ እንጂ በውጭ በሚገኘው ሲኖዶስ ተወስኗል አለማለታቸው ከግንዛቤ ውስጥ ይግባልኝ።
አቡነ መቃርዮስ
ከእዚህ በፊት በጀርመን ራድዮም ሆነ በሌሎች የዜና ማሰራጫዎች ላይ ብዙ በቤተክርስቲያን ላይ ስለሚሰሩ ደባዎች ከመግለፅ ባለፈ የጳጳሳትን የግል ተግባራት በተመለከተ የሚለቀቁት ፊልሞችም ሆኑ የድምፅ ቅጂዎች ዞሮ ዞሮ ቤተክርስቲያን ወደማትወጣበት ችግር የሚከታት መሆኑን ልብ ሊሉት ይገባል። በሃገርቤት የሚገኙ አባቶችም በአቡነ መርቆርዮስ ላይ የሚቀርቡ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች በየትኛውም የሃገርውስጥ ሚድያ መንግስት እንዲያቀርብ ተባባሪ አለመሆን ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ እንዳይፈፀም መከላከል ይገባቸዋል። ምክንያቱም ከአብጠልጣዩ የአቀባባዩን ማስቆም አይቻላቸውምእና።
ከ አብጠልጣዩ የ
አቀባባዩ እንዳይብስ እጃችንንም
በእጃችን እንዳንቆርጥ
አብጠልጣዩ
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሆነ ''ብዙ ያላወጣሁት በማስረጃ የተደገፈ ጉድ አለ ለሕዝብ ለመልቀቅ እገደዳለሁ'' ያሉት አቡነ መቃርዮስ አንዳንቸው የአንዳቸውን ''ጉድ''ያሉትን ቢለቁ ቤተክርስቲያን ላይ የማይሽር ቁስል መተዉ የማይቀር ነው።ይሄውም:-
- ወደፊት በሁለቱ ሲኖዶሶች መሃከል የሚኖረው አንድነት ላይ ትልቅ ጋሬጣ ይጥላል፣
- ምዕመናን በቤተክርስትያናቸው እና በእምነታቸው ላይ ፈተና ይሆኑባቸዋል፣
- ቤተክርስቲያን ብዙ ምዕመኗን የማጣት እና ወደ ሌላ እምነት እንዲገቡ ይገፋቸዋል፣
- በቤተክርስቲያኒቱ ላይ በጎ አመለካከት የሌላቸው ሁሉ ቅጂውን በአንዲት ጀንበር ከዳር እስከዳር ስለሚያዳርሱት ከፍተኛ የሞራል ድቀት በምእመናን ላይ ይደርሳል፣
- የቤተክርስቲያን አለመቀፋዊ ግንኙነት በእጅጉ ይጎዳል።ይሄውም የምዕራቡ የዜና ማሰራጫዎች በካቶሊኩ አለም የተፈፀሙ ግድፈቶችን ለማቅረብ እንደሚጣደፉት ሁሉ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ሆነ በአቡነ መቃርዮስ የሚለቀቁ አንዳቸው የአንዳቸውን ''ገመና'' ያሉትን ማናቸውም ነገር በጣም ትኩረት በመስጠት ለመላው አለም ደጋግመው እንደሚያሰራጩት ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አይገባም።
በአውሮፓ የደረሰው በእኛ ላይ እንዳይደርስ ያሰጋል።በአውሮፓ በ አስራስድስተኛው ክፍለዘመን በጀርመናዊው ማርቲን ሉተር የተነሳው የ ፕሮቴስታንት አለም በ ካቶልኩ አለም ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍቶ ነበር።ይሄውም የ ካቶሊክን እምነት ለማጥላላት ተብሎ በተከታታይ የተሰራው የማጥላላት ዘመቻ የአውሮፓን ሕዝብ የፕሮቴስታንት ተከታይ እንዲሆን ሳይሆን ያደረገው ክርስትናን እራሱን እንዲጠላ ከማድረጉም በላይ አሁን ባብዛኛው ምንም አይነት ሃይማኖት የለሽ ትውልድ ተፈጥሯል።የማጥላላት ዘመቻ ውጤቱን አሁን መለካት ይከብዳል።በእኛም ላይ የእዚህ አይነት ፈተና መጋረጡ ላይቀር ይችላል።ቢያንስ ለመጪው
ትውልድ የሚሆን ሥራ መስራት ቢያቅተን ጭቅጭቃችንን
በተጠናቀረ ማስረጃ አያይዘን ማቆየት የነገዋ ቤተክርስቲያን ለሚነሱባት ፈታኞች ሌላ ድንጋይ ማቀበል ነው።በመሆኑም
በሃገርቤት በመንግስት ሞገስ ያገኙ የቤተክህነት ሰዎችም ሆኑ በተራ እልህ እየተነሱ ፊልም የሚያሳዩን የደህንነትም ሆኑ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች በአንድ በኩል እና አቡነ መቃርዮስም በሌላ በኩል እባካችሁ ይህ ተግባር የአሁኑን ትውልድ ብቻ ሳይሆን መጪውንም አንገት የሚያስደፋ ለቤተክርስቲያን ትልቅ ጠባሳ የሚጥል ብቻ ሳይሆን እጃችንን በእጃችን መቁረጥ ነው እና እንዳትሞክሩት አደራ።''አንዱ የአንዱን ሸክም ይሸከም''።
አምላከ ሙሴ ወአሮን
ከዘመኑ መከራ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይሰውር
ጌታቸው በቀለ
ኦስሎ