ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, February 21, 2013

የ ፓትርያሪክ ስየማ -''ሰኞ ተወለድኩ ማክሰኞ እንጨት ለቀማ ሄድኩ''

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተከርስቲያን በማዕበል በተሞላው አለም ውስጥ ከወድያ ወዲህ እየንተንገላታች እነሆ ሁለትሺ አምስት ዓመተምህረትን ፆመ ነነዌ ልትቀበል ቀናትን እየቆጠረች ትገኛለች። ወደ ግማሽ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ምዕመናኗ  እንደ ሌላ እምነት ተከታዮች ሁሉ በሀገሪቱ የሚከሰቱት ፖለቲካዊው፣ማህበራዊው እና ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች   እጅጉ እየጎነትሏቸው አንዳንዴም  የመኖር ትርጉሙ ግራ እስኪያጋባቸው ድረስ  በፈተና ላይ ፈተና እየተጫናቸው ወርሃ የካቲትን ማጋመስ ይዘዋል። ብዙሃኑ ሕዝብ (ትኩረቴ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመን ላይ መሆኑ ልብ ይባልልኝ) እንዲህ በመምሸት እና በመንጋት መካከል ልዩነቱ እስኪጠፋው ድረስ ይባክን እንጂ በሌላው ጎን ግን የሚታየው መምነሽነሽ ግርምትን ይፈጥራል።ይህ የመኖር ጥያቄ ገዝፎ እና አድጎ ቤተክርስቲያኒቱ የአንድነት እርቅ ሂደት ላይም ሆነ መንግስት ''ይደልዎ'' በሉ እያለ በሚያስፈራራበት አዲስ ፓትርያሪክ ስያሜ ላይ ብዙ አድርባዮችን አፍርቷል።አቦይ ስብሐት የቤተክርስቲያንቱን ችግር ለመፍታት ከመድከም ይልቅ እንደፈለጉ እንዲናገሩ የአድርባይ አባቶች መብዛት ተመችቷቸዋል።


ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትርያሪክ ፅህፈት ቤት 

የአቦይ ስብሐት ለእርቅ የተነሱ  አባቶች ''ይሰቀሉ'' አንደምታ 


በመንፈሳዊ አለም ውስጥ ብዙ የዋሃንን ማግኘት ይቻል ይሆናል።በፖለቲካው አለም ግን በተቃራኒው ብዙ ብልጣብልጦች ተትረፍርፈዋል።በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የአባቶች እርቅ ሂደትም ሆነ የመንግስት ፓትርያሪክ ስየማ ሂደት ላይ የታዩት አመለካከቶች የእነኚህ ሁሉ ድምር ሆኖ ነው የተሰማኝ።አንድ ጊዜ አንድ ቀድሞ በኢህአዴግ አቀንቃኝነት የሚታወቅ እና የድርጅቱን ባህሪ በደንብ የተረዳ ሰው የተናገረውን እዚህ ላይ መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል።ለግለሰቡ የቀረበለት ጥያቄ ''ለምንድነው ኢህአዲግን ተቃዋሚዎች በሚገባ ሊቃወሙት ያልቻሉት? ለምንስ አላሸነፉትም?'' የሚል ሲሆን የመለሰው መልስ '' ኢህአዲግ በውጊያ እየገደለ ነው አዲስ አበባ የገባው የኢህአዲግ ተቃዋሚዎች አመራሮችን ፐርሰናሊቲ ብንመለከት በጎ በማድረግ፣በማስተማር፣ወዘተ ህይወታቸውን ፈጅተው ፍትህ ሲጎድል የተነሱ ናቸው።ለምሳሌ ፕሮፌሰር አስራትን ውሰዱ እኚህ ሰው እድሜ ልካቸውን ሁሉ በህክምና ሰው ሲያድኑ ነው የኖሩት እኚህ ሰው እንዴት ነው የኢህአዲግ ተቃዋሚ ሆነው ኢህአዲግን የሚገዳደሩት ኢህአዲግ የሚመጥነው ተቃዋሚ አላገኘም።የሰብአዊ መብት ኢህአዲግ ምኑ ነው?----'' ማብራርያው ይቀጥላል።ቤተክህነቱ ውስጥ ሰርገው የገቡት የመንግስት አፈቀላጤዎች እና በአገልጋይ ካህናቱ መካከል ያለው ልዩነት ይሄው ነው።


በቤተክህነቱ ጉዳይ ውስጥ እንደፈለጉ የሚናገሩት  አቦይስብሐት ''ለእርቅ ያሰቡም ሆነ የደከሙ የቤተክርስቲያኒቱ አባቶች መሰቀል ይገባቸዋል'' ብለው ሀገርቤት ለሚታተም መፅሄት ሲናገሩ የቤተክህነቱ ሰዎች አራትኪሎ ሻይ እየጠጡ በየዋህነት ይስቁ ነበር። የሃይማኖት ሰዎች እምነት ስላላቸው ሰዎች ሁሉ እነሱ በሚያስቡት መጠን ደጎች ይመስሏቸዋል።አቦይ ስብሐት ሰዎችን ያውም ለእርቅ የተነሱ የቤተክርስቲያን አባቶችን ''መሰቀል''ይገባቸዋል ሲሉ ከልባቸው እንደሆነ የሚረዳላቸው ምናልባት የተሰቀለ እና ነፍሱ በአፀደ ነፍስ ያለ ብቻ ነው።እሳቸውም አሰቃቀሉ በእንጨት ይሁን በገመድ በኃላ በኮሚቴ የሚወሰን ስለሆነ ወደ ዝርዝር አሰቃቀል ሂደት አልገቡም።በእዚህ በኩል አንድ ''ደግነት'' ታይቶባቸዋል። 

አቦይ ስብሐት የሚያህል ከሱዳን እስከ ትግራይ ቀጥሎም 'አዲስ አበባ በደርግ ዘመን እየገቡ ይወጡ ነበር' የሚባሉ ሰው ስለ ቤተክህነቱ መናገር የሚገባቸውን መርጠው መናገር አቅቷቸው የሚመስለው ካለ እርሱ እንደተታለለ ይወቅ። አቦይ ስብሐት ይህን ያሉት የመንግስት የፓትርያርክ ስየማ ከመገለፁ በፊት በቤተክርስቲያኒቱ ዙርያ ያሉትን ከአባቶች እስከ ማህበራት ዝም ለማሰኘት ነው። የሚገርመው ነገር ይህን የተባሉ አባቶች በግልፅ ምላሽ መስጠት የሚገባቸው የነበረ መሆኑ እና  አሁንም ቢሆን አለመርፈዱ ይሰማኛል። አንድወቅት አቶ ተፈራ ዋልዋ '' ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የነፍጠኞች አስተሳሰብ ያላት ነች'' አዘል ልንግግር ተናግረው በውቅቱ የነበሩት የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች እስከ ቢሯቸው ድረስ በጥያቄ አጣድፈዋቸው የነበረ መሆኑን እና ይህም ለሌሎች ባለስልጣናት ''ሃይማኖት የህዝብ ሥስ  ብልት ነው'' የሚለው አባባልን በሚገባ የተረዱበት የነበረ መሆኑን አስታውሳለሁ። አይሁድ  ክርስቶስን  ይሰቀል ብለው  ለመፍረድ የጵላጦስን  ምስክርነት እና የህዝብ ዳኝነት ለማግኘት ሲጥሩ ሕጉን ጣሱ እንዳይባሉ ስለተጨነቁ ነበር።አቦይ ግን እርቅ ባሰቡ አባቶች ላይ ''ይሰቀሉ'' ሲሉ ዳኛም ወቃሽም የለባቸውም።የ አይሁድን ያህል ሕግን ለመጠበቅ አለመሞከራቸው አሰቃቂ ነው።ከፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እረፍት በኃላ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ቀድሞ በውጭ ከሚኖሩ  አባቶች ጋር የተጀመረው የእርቅ ሂደት ብዙ ተስፋን አጭሮ የነበረ ለመሆኑ ዳላስ ምእመናን ከሀገርቤትም ሆነ እዚያው አሜሪካ ለሚገኙት አባቶች ያደረጉት በእንባ የተቀላቀለ  ልዩ አቀባበል እና መስተንግዶ አመላካች ነው። በእዚህ የእርቅ ሂደት ላይ በተለይ ከአዲስ አበባ ብዙ መደናገጦች እና እርቁን ያለመፈለግ ሂደት ብዙዎቻችን ከጠበቅነው በላይ ታይቷል።ሁኔታው በተለይ የእርቅ ሂደቱ ለሌላ ቀጠሮ ሎስአንጀለስ ላይ ተቀጥሮ ሲለያይ መንግስት ቀደም ብሎ ቤተክርስያኒቱ ላይ ያቀዳቸው የቆዮ ድብቅ እቅዶች መበላሸታቸውን ስላወቀ ፕሬዝዳንት ግርማ ''ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ ይመለሱ'' የሚለው ደብዳቤ ላይ ድምፁን አጥፍቶ የነበረ የመሰለው መንግስት ከሎሳንጀለሱ ቀጠሮ በኃላ በግልፅ አስታራቂው  ኮሚቴ አባላትን ማዋከብ ያዘ።ለእዚህም ማስረጃ የሚሆነው አስታራቂ ኮሚቴው የካቲት 13/2005ዓም የእርቅ ሂደቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዲህ የሚል መገኘቱ ነው።
  ''የሰላምና አንድነት ጉባኤው አባላት ፍጹም ሰላማውያን መሆናቸው እየታወቀ ለቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት አብዝቶ መድከም እንደ ወንጀል ተቆጥሮ ብዙ እንግልት ደርሶባቸዋል።እንደሚታወቀው የዕርቀ ሰላሙን ሒደት ለማሰናከል የፈለጉ ጥቂት አባቶችናየቤተ ክርስቲያንባለሥልጣናት የሆኑ ግለሰቦች ለመንግሥት አካላት የተዘባ መረጃ በመስጠት የሰላም ልዑካኑ ከሀገር በግዳጅ እንዲወጡና እንዲጉላሉ ተደርጓል። ከዚህም ጋር በሰላም ልዑካኑ ስም ከሰላሙ በቀር አንዳችም አጀንዳ የሌለውን ጉባኤያችንን የማይወክል የሐሰት ወረቀት በመበተን ያለስማቸው ስም ለመስጠት ተሞክሯል። ለዚህ ሁሉ ግን የቤተ ክርስቲያን አምላክ ራሱ በጊዜው እንደሚመልስና እንደሚፈርድ ወደፊትም ታሪክ እንደሚያስታውሰው ስለምናምን ሁሉንም በአኰቴት እንቀበለዋለን።''http://www.dejeselam.org/2013/02/blog-post_20.html 


  መንግስት ፓትርያሪክ ስየማ ''ሰኞ ተወለድኩ ማክሰኞ እንጨት ለቀማ ሄድኩ''


 ከደደቢት ጀምሮ በድብቅ  ተወያቶ በአደባባይ ሌላ በማውራት የተካነው ኢህአዲግ የህወሓት 38 አመት ከመከበሩ በፊት  ''የፓትርያሪክ ምርጫ'' ቀን በቤተክህነት ውስጥ ባሉ ወኪሎቹ አማክይነት አስነገረ። በ እዚሁም መሰረት '' ጥቂት ቀናት  ውስጥ ፓትርያሪክ  ይመረጣል።'' መሰል ማስታወቂያ ሲነገር ያላዘነ የቤተክርስቲያኒቱ ልጅ የለም።''ሰፈራችን የዕድር  ሰብሳብያችንን ስንመርጥ  እንዲህ አልተዋከብንም'' ያሉት የአንዲት ምዕመን አገላለፅ የሚያሳየው የሂደቱን እፍትሃዊነት  ብቻ ሳይሆን  ምርጫው ከምርጫነት ወደ የመንግስት ስያሜነት መቀየሩን ነው።በትክክል ሂደቱን የሚገልፀው ካለ ደግሞ 'ሰኞ ተወለድኩ ማክሰኞ እንጨት ለቀማ ሄድኩ' የሚለው  አባባል ብቻ ነው።


 እርግጥ ነው በፓትርያርክ ምርጫ ዙርያ የሚነሱ ብዙ ተቃራኒ ሃሳቦች አሉ።ከ እነዚህ ውስጥ 
- ገና ለገና አባቶች አይታረቁም እና ቤተክርስቲያን ካለ መሪ ስንት አመት ልትጠብቅ ነው?
- ቤተክርስቲያን በብዙ መከራ ውስጥ እያለች ስንት የሚሰራ ሥራ እየጠበቃት በፓትርያርክ ጉዳይ ላይ መነታረክ ይገባልን?
- አቡነ ጳውሎስ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ይህን ያህል ያልተናገሩ ሰዎች ለምን ዛሬ ከሀያአንድ አመት በኃላ ጉዳዩን ያነሳሉ?
- ቤተክርስቲያን ወትሮም በንጉሱም ሆነ ደርግ ዘመን የመንግስትን ይሁንታ ያገኙ ናቸው ፓትርያርክ የሆኑት ምነው ዛሬ ተጋነነ?
- አሁን የሚፈለገው የቤተክርስቲያንቱን ችግሮች በተለይ የገንዘብ አስተዳደር እና የሙስናን ችግር የሚፈታ ፓትርያርክ ከተገኘ ቅድምያ እርሱን መፍታት እና ሌላውን በሂደት መመልከት ተገቢ ነው የሚሉ እና ሌሎች አስተያየቶችን መጥቀስ ይቻላል።


በተለይ በአንዳንድ ድህረገፆች ላይ የምዕመኑ ዝምታ ምንድነው? የሚሉ ብዙ ጥያቄዎች ከመነሳታቸውን አንፃር በመንግስት የፓትርያርክ ስየማ ጉዳይ ላይ   ምእመናንም ሆነ የአባቶች አመለካከት ከሚከተሉት አስተሳሰቦች አንፃር እንደሚሆን እገምታለሁ።እነርሱም-

/ ለመንግስት ካላቸው ታማኝነት አንፃር

መንግስት ያለው ሁሉ ልክ ነው ብሎ ከማሰብ። እነኚህ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ቢሆኑም የመንግስትን መኖር ከእነርሱ መኖር ጋር አስተሳስረው የሚኖሩ ናቸው፣

/ ከወንዛዊ ስሜት በመነጨ

ሰውን በሰውነቱ እና በሚያደርገው በጎ ሥራ መለካት ያቃታቸው መንፈሳዊ የሆኑ ሲመስላቸው፣ ግን በወንዛዊ ስሜት የተዋጡ፣ በቤተክርስቲያኒቱ የተለያየ የስልጣን ተዋረድም ሆነ ምዕመናን ብሎም ማህበራት ውስጥ ሁሉ ሳይቀር መኖራቸው እሙን ነው።ያፈጠጠ እውነትን ለመናገር እንቅ ስቃሴ  ለማድደርግ ደካማ ''የወንዜ'' ስሜት ታስቸግራቸዋለች።

/ እግዚያብሔር የፈቀደውን ያድርግ የሚሉ

 እነኝህ መንፈሳዊ ናቸው ግን በብዙ የኑሮ ውጣውረድ ውስጥ የቤተክርስትያኒቱ ጉዳይን አጀንዳ አድርገው ከመወያየት ወይንም መፍትሄ ከመሻት ይልቅ ''እግዚአብሔር የፈቀደውን ያድርግ'' የሚሉ ናቸው። ''ንስሐ አለ ተብሎ ኃጢያት አይሰራም፣ወጌሻ አለ ተብሎ ገደል አይገባም'' እንዲሉ የሚሉትን ያህል እምነት ደረጃ ሳይደርሱ የቸልተኝነት መሸፈኛ እግዚያብሄር መሆኑ ቅር ያሰኛል።

/ ምጣዱ ከሚሰበር አይጧ ትለፍ  የሚሉ

እነኚህ ስለ በተክርስቲያኒቱ ችግር ከስር የተረዱ፣ሌላው የማያውቃቸው ችግሮች ባላቸው ቦታ እና የመረጃ ምንጭነት የሚጨነቁ፣ለእራሳቸው ብዙ የማይጨነቁ ግን ጉዳዩን እየተከታተሉ ቤተክርስቲያኒቱ  እንደምንም ብላ መፍታት ያለባትን ችግሮች ትፍታ ሌላው የትም አያመልጥም ይሚሉ ናቸው። በተለይ  የሚያስጨንቃቸው መንግስት መድቦትም ሆነ ተመርጦ የሚመጣው አባት ሕዝቡን ካስደሰተ፣ሙስና ካጠፋ፣ቤተክርስቲያኒቱ ከመንግስትም ጋር ሆነ ከተለያዩ  አካላት ጋር ይሚገጥሟት ተግዳሮቶችን በጥበብ እና በመንፈሳዊ አፈታት ዘዴ የሚፈታ ከሆነ እዳውገብስ ነው ባዮች ናቸው። 

 የእዚህ ሁሉ መፍትሄ ምን ይሁን?

ከላይ የተወሱት ሁኔታዎች ሁሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ነው።የአባቶች የዕርቅ ሂደት ለጊዜውም ቢሆን ቆሟል።መንግስትን ተገን ያደረጉ አባቶች አዲስ ፓትርያሪክ ለመሰየም ቀናት እየቆጠሩ ይገኛሉ።በውጭ የሚገኙ አባቶች ከሀገርቤት የፓትርያርክ ስየማ  በኃላ ምን እንደሚያደርጉ ለጊዜው አልታወቀም። ምናልባት የበለጠ የሀገረስብከት ማጠናከር እና ይበልጥ የሲኖዶሱን ማዕከልነት  የመሳብ ሁኔታ ሊኖር ይችላል።በ እዚህ ሁሉ ፈተና መሃከል የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ሚና ምን መሆን ይገባዋል? ፈታኙ ጥያቄ ነው።እንደ እኔ አስተሳሰብ መፍትሄውን መደረግ  የሚገባቸው እና የማይገባቸው ጉዳዮች ብዬ በመክፈል ለማቅረብ እፈልጋለሁ።

መደረግ የሚገባው ጉዳይ 

- ቤተክርስቲያንን ከመንግስት ጋር ለማጋጨትም ሆነ ከመንግስት እግር ስር እንድትሆን አሳልፈው የሰጡ አካላትን በሙሉ ማጋለጥ እና ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ማድረግ፣
- መንግስት እጁ አንዳለበት ፀሐይ የሞቀውን ፓትርያሪክ ስየማ ቢያንስ ህዝበ ክርስትያኑ ሳይስማማ፣የዕርቅ ሂደቱ ወግ ባለው ሁኔታ ሳይፈፀም፣ የምርጫ ሂደቱ ግልፅነት፣እርጋታ፣ከሰዎች ሃሳብ ይልቅ የመንፈስቅዱስ ሥራ የሚታይበት እንዲሆን ዕድል ሳይሰጥ እና ቢያንስ ሂደቱ የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንትን አስተያየት ቅዱስ ሲኖዶስ ምእላተ  ጉባኤ ጋር ሳይጣጣም በአንድወር ጥሪ መደረጉን  አበክሮ መቃወም ለወደፊቱም ቤተክርስቲያን ተመሳሳይ ችግር እንዳይገጥማት ዘለቄታዊ ሥራ መስራት፣
- ''ቀድሞም ቤተክርስቲያን የመንግሥታት ተፅኖ ነበረባት አይገርምም'' ለሚሉ የምንኖረው ሃያንደኛው ክፍለዘመን መሆኑን አበክሮ መንገር። የቀደመው አሰራር በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ ጋር አብሮ የሚወቀስ እና የሚሞገስ መሆኑን እና የአሁኑን የከፋ የሚያደርገው መንግስት በመንፈስቅዱስ ሥራ ላይ መግባቱ መሆኑ እና የቀደሙት ቤተክርስቲያንን ቢቀርቡ አምነውባት፣ተቆርቁረውላት እና ሊፅድቁባት አስበው እንጂ አልመው እና  አቅደው ህዝብን ለማታለያ እንደ አንድ ስልት የያዙበት ሁኔታ  አለመኖሩን ማሰብ ተገቢ መሆኑን የማሳወቅ ሥራ መስራት እና 
- ቤተክርስቲያኒቱ እና ሀገሪቱ የገጠሟት ችግሮች ተመሳሳይ ባህሪ ስላላቸው እና እያንዳንዱ ንዑስ ችግሮች ላይ ከማተኮር በአጠቃላይ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ አተኩሮ ተግቶ መስራትእና ትውልዱም ለእዚሁ ሥራ እንዲነሳ ማብቃት የሚሉት ሲሆኑ።

መደረግ የማይገባው ጉዳይ


የቤተክርስቲያንቱን እምነት የተከተለ ሁሉ ከቅን በሚሰጣቸው ሃሳቦች ላይ ቀድሞ አለመፍረድ።በተለይ በእዚህ ወቅት በቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን መሃከል  የሚኖረው የሃሳብ ልዩነት ወደሰፋ ጉዳይ እንዳያመራ  ወቀሳዎችን ግለሰባዊ አለማድረግ።ለምሳሌ በፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ላይ ሂደቱን እና የበተርክስትያንቱን የእርቅ ሂደት ላይ ቅድሚያ የመስጠት አስፈላጊነትን እንጂ ግለሰቦችን አለመውቀስ።ይህ ማለት ጎልተው የሚታዩ ለቤተክርስቲያኒቱ ፈተና የሆኑትን ግለሰቦች  ከማስረጃ ጋር በማቅረብ ጥንቃቄ እንዲደረግ መንገር አስፈላጊ ቢሆንም ለሀገርም ሆነ ለቤተክርስቲያን ብዙ የሚሰሩ ሃብቷየሆኑትን ልጆቿን በሆነ ባልሆነ ለመውቀስ አለመቸኮል።ይህ ልዩነትን የመፍጠር እና የማስፋት ሂደት በተለይ መንግስትን ጨምሮ እጃቸውን በቤተክርስቲያን ላይ ለመጫን የሚያስቡ  ሁሉ  የተካኑበት አካሂያድ ስለሆነ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባ ይመስለኛል። 


ይቆየን 

ጌታቸው 

ኦስሎ 1 comment:

Anonymous said...

bzuwoch yebete krstyan sewoch zimtachew yigermal.le poletikawu bzuyemiayweru church stcheger lemn zmalu? tamr new.