ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, April 20, 2019

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር በማያዳግም መልኩ ለመፍታትት ሁሉም ይነሳ!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ  ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ እና ብፁዕ አቡነ አብርሃም ቡራኬ ሲቀበሉ 

ጉዳያችን / Gudayachn
ሚያዝያ 12/2011 ዓም (አፕሪል 20/2019 ዓም)


በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚከተሉት ርዕሶች ስር ሀሳቦች ተነስተዋል።እነርሱም : -

>> የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ከአሁን በኃላ አንዲት የዶሮ ላባ መሸከም አይችልም ፣
>> የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር መፍትሄ ከውስጥ ይምጣ ወይስ ከውጭ?
>> የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ችግር አለመፈታት ማለት የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ማለት ነው፣
>> የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ችግሯን ለመፍታት ማን፣መቼ፣ምን  ያድርግ? 
>> በ21ኛው ክ/ዘመን ''የአይቲ''  (የዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ክፍል (ዲፓርትመንት) በመዋቅር ደረጃ የሌላት በሚልዮን የሚቆጠር ምዕመን የያዘች ቤተ ክርስቲያን -የአስተዳደር ችግሯ አንዱ መገለጫ

በ1953 ዓም ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ የተፃፈው ፍኖተ አእምሮ - የዕውቀት ጎዳና የተሰኘው መፅሐፍ  ምዕራፍ 24 ስለ እግዚአብሔር ፍቅር በሚለው ርዕስ ስር እንዲህ ይላል : -
''ሰው በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ የሚጨመረውን የፍጥረትን ፍቅር ያላግባብ ካደረገው ወደድኩህ በሚለው በፈጣሪው መዘበት ይሆናል።ምነው እግዚአብሔርን ቢወድ ዘበተ እንዴት ይባላል? ቢሉ ምላሹ - ሰው እግዚአብሔርን የሚወድበት ምክንያት ንብረቱ ስለ ሞላለት፣ ወይም እንዲሞላለት፣ ወይም ዕድሜው እንዲረዝምለት፣ ወይም ልጅ ስላገኘ፣ የሚወደውን ተድላ ስላደረገለት፣ ወይም እንዲደረግለት እንደሆነ። ይህ ሰው ፈቃደ ስጋውን ወደደ ይባላል እንጂ፣ እግዚአብሔርን ወደደ አያሰኘውም እንዲያውም ስጋዊ ነገር ሲደረግለት፣የሚወድ ስጋው ነገር ሲቀርበት የሚጠላ ነውና ስለዚህ ለእግዚአብሔር የታመነ ወዳጅ አይባልም። እግዚአብሔርን መፍቀደ ሥጋን ሲደርግ ቢወዱት እንዲያደርግ ቢለምኑት ስለምን ዘበትና የማይገባ ይሆናል? ቢሉ ምላሹ - እንዲህ ያለው ጠባይ በፊት በእስራኤል ዘንድ ልማድ ሆኖ የሚኖር ነበር። በየጊዜው ከክህደት አደረሳቸው እንጂ አልረባቸውም።በተደረገላቸው ወራት እየወደዱ ባልተደረገላቸው ወራት እየጠሉ መጎዳታቸውን አሳዩ።የእዚህ ዓለም ገንዘብ እንደ ትርፍ እንደ ጉርሻ ለበጎዎችም ለክፉዎችም የሚደረግ ነውና መንግስተ ሰማያትን ለምኑኝ እንጂ ይህን ዓለምስ እንዲያውም አትለምኑኝ ማለቱ መወደሻውና መጠያው በእዚህ ምክንያት እንዳይሆን ነውና ። '' 

ከላይ የቀረበው ፅሁፍ ታትሞ ከወጣ ሀምሳ ስምንት ዓመታት ሆኖታል።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ምዕመናን ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸው ግንኙነት በምድራዊ ምቾት እና ቁሳዊ ነገር የማግኘት እና አለማግኘት ጋር አብሮ የሚለካ መሆን እንደሌለበት ለማመናቸው አንዱ ማሳያ ነው።በስጋዊ ምቾት አብዛኛው ምዕመንም ሆነ አገልጋይ ካሕናት ደልቷቸው የሚኖሩ አይደሉም።ይልቁንም በፍፁም ዕምነት ከምድራዊ ምቾት ጋር ባልተገናኘ ፍፁም እግዚአብሔርን የመውደድ  ታላቅ ሀብት የቤተክርስቲያኒቱ እና የተከታዮቿ አንዱ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበቁ ቅዱሳን፣ለስጋቸው ሳይሆን ለነፍሳቸው ያደሩ ሊቃውንት ዛሬም  ከአጥብያ ቤተ ክርስቲያን እስከ ገዳማት፣ከገዳማት እስከ በረሃ ተሰውረው የሚኖሩባት፣ስለ ሰውልጅ እና መላው ዓለም የሚፀልዩ፣ስለ እራሳቸውም ሆነ ስለ ሀገራቸው እግዚአብሔር ጋር ጧትና ማታ የሚነጋገሩ ምዕመናን ሁሉ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዛሬም ድረስ የታደለቻቸው ፀጋዎቿ ናቸው። ይህንን መንፈሳዊ ሀብት በሰው አዕምሮ መለካት ፈፅሞ አይቻልም።እግዚአብሔር በሚለካበት ምስጢራዊ መለክያው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ሀብት ይለካዋል።

ከላይ ከተጠቀሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ሀብት በተቃራኒው ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን በውስጧ ተሰግስገው የወጠሯት ሶስት ዓይነት አስተዳደራዊ ችግሮች አሉ። እነርሱም ዘመናዊ የአስተዳደር ስርዓት እጦት፣የገንዘብ ምዝበራ እና የጎሰኝነት አስተሳሰብ ያላቸው ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሰረተ ዕምነት ውጭ አገልግሎቷንም ሆነ አስተዳደራዊ መዋቅሯን ማወካቸው የሚሉት ቀዳሚ ናቸው።እነኝህ ሶስቱ ችግሮች ከእዚህ በፊት በሰፊው በተለያዩ መንገዶች ሲወሱ ስለነበሩ ስለምንነታቸው መዘርዘሩ እዚህ ላይ ብዙ ጊዜ ማጥፋት ነው።ከእዚህ ይልቅ ወደ መሰረታዊ መፍትሄዎቹ ላይ ላተኩር።

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ከአሁን በኃላ አንዲት የዶሮ ላባ መሸከም አይችልም 

አንድ ነገር ከእዚህ በኃላ ሊቀጥል አይችልም። የሚለውን አባባል ለመግለጥ በቁልሉ ላይ አንድ የዶሮ ላባ ብታስቀምጥበት ቁልሉ ይናዳል የሚለው አገላለጥ ጥሩ አገላለጥ ነው።አባባሉ ከእዚህ በላይ ምንም አይነት ችግር ለማስተናገድ አቅም የማጣት ደረጃ የሚገለጥበት ጥሩ አባባልም ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ላለፉት ሶስት አስር ዓመታት በተለይ ያሳለፈችው አስተዳደራዊ ፈተና ይህ ነው የሚባል አይደለም።የቤተ ክርስቲያኒቱ ንብረት እና ሀብት በግለሰቦች የግል ኩባንያ መመስረቻ ብቻ ሳይሆን የማያልቅ የሚታለብ ጥገት ሆኖ ኖሯል።አሁንም የደረሰውን ስንዘረዝረው ብንውል ቀናት አይበቁንም።

ዛሬ ላይ ሆነን ግልጥ የሚሆነው ጉዳይ ግን የነበረው የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ችግር ውሎ ለማደር የአንዲት የዶሮ ላባ ያህል ሊሸከም አይችልም።ቢያንስ በማያዳግም ደረጃ እንዲፈታ አስፈላጊው ሥራ መልክ ባለው መንገድ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ሁሉን ባሳተፈ መንገድ መጀመር አለበት።ለእዚህም ከቤተ ክህነት እስከ አጥብያ ቤተ ክርስቲያን፣ከሰንበት ትምህርት ቤት እስከ አብነት ትምህርት ቤቶቿ፣ከምእመናን እስከ መንፈሳዊ ማኅበራት በአንድነት የሚቆሙበት ጊዜ አሁን ነው።

የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር መፍትሄ ከውስጥ ይምጣ ወይስ ከውጭ?

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ይህንን ያህል እየባሰ ለምን ምዕመናኗ እንደ ሩስያው የጥቅምት አብዮት ሆ! ብለው ወጥተው አልተፋለሙም? የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ማኅበራትስ ለምን መስቀል አደባባይ  አልተሰለፉም? ወይንም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዘራፊዎች ጋር ዱላ አልተማዘዙም? የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች አንዳንዶች ሲያነሱ ይሰማሉ።እነኝህ ጥያቄዎች በተለይ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግሮች የአንድ ሰሞን የዜና ርዕሶች ሲሆኑ የሚነሱ ጉዳዮች ናቸው። እነኝህ ጥያቄዎች ግን የሚነሱት በቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግሮች ብቻ ያሉ የሚመስሏቸው እና የበለጠ የሚያናጉ ጉዳዮች በተለይ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች እንዴት በገንዘብ ምዝበራው እና በዘረኝነት መስመሮች ስር እያለፉ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደተወሳሰበ ችግሮች ለመክተት ይዳዱ እንደነበር ካለመረዳት ነው። 

ቀደም ባሉ ዓመታትም ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግሮቿን ለመፍታት መፍትሄው ከውስጥ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ብቻ መምጣት አለበት? ወይንስ ከውጭ? የሚሉት ጥያቄዎች ሁል ጊዜ የሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው።ከውስጥ ማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ በራሷ ባላት ከፍተኛ መዋቅር ማለትም በቅዱስ ሲኖዶስ በራሱ አስተዳደራዊ ችግሮቹን ለመፍታት አስፈላጊውን ሥራ እንዲሰራ ሲሆን ከውጭ ማለት ምዕመናን አስተዳደራዊ ችግሮቹን ወደ አደባባይ አውጥተው እና አስገድደውም ቢሆን ቤተ ክርስቲያኒቱን የሚመዘብሩትን በሙሉ ለሕግ በማቅረብ እና መንግስትም በጉዳዩ ላይ እንዲገባ ማድረግ የሚለው መንገድ ነው። እውነታው ግን ላለፉት በርካታ ዓመታት ውስጣዊ መፍትሄ ይመጣል ተብሎ ቢጠበቅም ቀደም ባሉት ዓመታት ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀሩ የቤተክርስቲያንቱን ንብረት እና ሀብት ተካፋይ ስለነበሩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ይፈታ የሚሉትን ሁሉ የፖለቲካ እና የጎሳ ስም እየተለጠፈባቸው ብዙ ፈተና ሲቀበሉ ኖረዋል። አሁን ቢያንስ የፖለቲካ ቅብ ለመቀባት የወቅቱ የሥርዓት ለውጥ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ለውጥ ያልተነሱት ከውስጥ ብፁዓን አባቶች፣ከውጭ ደግሞ ምዕመናን መሆናቸው ግልጥ ሆኗል። ስለሆነም የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ችግር መፍትሄ በቅንጅት ማለትም ከውስጥ፣ከውጭ እና ከመንግስት በአንድነት የሚሰሩት ተግባር ውጤት ነው።

መንግስት -

መንግስት ለአስተዳደር ችግሩ መፍትሄ ለመስጠት የተነሱትን አካላት ደኅንነት ከመጠበቅ አንስቶ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባስቀመጠችው መንፈሳዊ መፍትሄ ያጠፉትን በሕግ አግባባ የመዳኘት ሥራ ሁሉ የመንግስት ሥራ ነው።መንግስት ለቤተ ክርስቲያኒቱ መፍትሄ ማገዝ፣መስራት እና መከላከል ግዴታው ነው።እዚህ ላይ መንግስት ማለት ከሌላ ቦታ የመጣ ልዩ አካል ማለት ሳይሆን መንግስት ውስጥ ያሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት መንግስትን ወክለው እና የአስተዳደራዊ ለውጡን አግዘው እንዲገኙ ማድረግ በቀላሉ የመንግስት እገዛ ማለት ነው።

ከውስጥ -

ከውስጥ ደግሞ ለመፍትሄ የሚነሱትን የሚያደናቅፉትን አጥብቆ መቃወም እና እውነት እና እግዚአብሔርን ይዘው ለአስተዳደራዊ መፍትሄው የሚሰሩ አባቶች ያስፈልጋሉ።በተለይ ትልቁ ችግር እና አደናቃፊው ጉዳይ ከውስጥ ከመሆኑ አንፃር የነበረ አስተዳደራዊ ችግርን ሰብረው የሚወጡ አባቶች ያስፈልጋሉ።ከእዚህ በኃላ ቤተ ክርስቲያኒቱ የአንድ ዶሮ ላባ ያህል በንበረባት የአስተዳደራዊ ችግር ላይ የመሸከም አቅም እንደሌላት መረዳቱ ወሳኝ ነው። ይህ ካልሆነ ግን ከውጭ ከሚመናንም ሆነ ከልዩ ልዩ አካላት የሚመጣው ግፊት ባልታሰበ ሰዓት እና ጊዜ በግድ አስተዳደራዊ ችግሩን ለመፍታት መምጣቱ ስለማይቀርና ይህ ደግሞ የሚያስከትለው ብዙ መፋተጎች ስለሚኖሩ የውስጡ ቢያንስ ከእዚህ ከግንቦቱ የሲኖዶስ ጉባኤ ያላለፈ ወሳኝ ስራዎችን መስራት ይጠበቅበታል።እዚህ ላይ ከእዚህ በፊት ኮሚቴ ተመስርቷል፣ውሳኔው እየተጠና ነው እና የመሳሰሉት የመጎተት ሥራ ከአሁን በኃላ ብዙ የሚያስኬድ አይመስለም።ይልቁንም ይህ ጉዳይ ውጫዊው ኃይል ሰብሮ እንዲመጣ በር የሚከፍት ነው። 

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ችግር አለመፈታት ማለት የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ማለት ነው።


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አንፃር ቆመው የንብረቷ ተጠቃሚ የሆኑ ነቀርሳዎች ሰንሰለታቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም።ይህ በራሱ ሰፊ ጥናት ይፈልጋል።ይህ ማለት ግን ያጠኑት የሉም የማይታወቅ ነው ማለት ደግሞ አይደለም።ስለሆነም የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ ችግር በማያዳግም ደረጃ ለመፍታት የውስጥ፣የውጭው እና መንግስት ከምንጊዜውም በላይ መነሳት ያለባቸው ጊዜ አሁን ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሀምሳ ሚልዮን በላይ ምዕመን፣ከአምስትመቶ ሺህ በላይ አገልጋይ ካህናት እና በአስር ሚልዮኖች የሚቆጠሩ ወጣት ተከታዮች፣በሺህ የሚቆጠሩ ምሑራን የያዘች የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ፖለቲካዊ፣ምጣኔ ሀብታዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላት ነች።ይህ ማለት የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳደራዊ ችግር አለመፈታት ማለት የኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ማለት ነው። ሌላው ቀርቶ ላለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ ቦታዎች የተነሱት የጎሳ ቁርሾዎች ይህንን ያህል የተባባሱት  መንግስት በሚገባ ፀጥታውን የማስከበር ኃላፊነቱን አለመወጣቱ ብቻ ሳይሆን  ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግሯን ፈትታ በብዙ ቦታዎች ለምመናኗ መንፈሳዊም ሆነ ስጋዊ ችግር የመድረስ አቅሟ መመናመኑ እና በሚያጠቁት አካላት አንፃር ምእመናኗን አስተባብራ ተፅኖ የመፍጠር አቅሟን አለመጠቀሟ እንዲሁም ችግሩ ከደረሰ በኃላ በፍጥነት ሰፊ ሀብት አንቀሳቅሳ ለመርዳት ያላት አቅም አለመጠቀም የሚያስቆጭ መሆኑን መዘንጋት አይገባም።

የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ ችግሯን ለመፍታት ማን፣መቼ፣ምን  ያድርግ? 

ማን  ያድርግ?

ችግሩን ለመፍተት ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ከውስጥ ቅዱስ ሲኖዶስ እና ካህናት ከውጭ ምዕመናን እና መንግስት በአንድ ልብ በተናበበ መንገድ ስራቸውን ሊሰሩ ይገባል።

ምን ያድርጉ?

የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ችግር ለመፍታት ከእዚህ በፊት ኮሚቴ፣ጥናት እየተባለ የተሞከሩ የግብር ይውጣ ስራዎች ነበሩ።አሁን ግን በእዚህ አይነቱ ሂደት እየሄዱ በእግዚአብሔር ላይ ''ማላገጥ'' የሚቻልበት ጊዜ ሊሆን አይገባም።ሊደረግ ከሚገባው ጉዳይ ውስጥ አንዱ በቅዱስ ሲኖዶስ አፋጣኝ ስብሰባ፣በምዕመናን ቆራጥ እና አፋጣኝ ውሳኔ እና በመንግስት ልዩ ተከታታይ አካል ጥምር ልዩ ቢሮ ማዋቀር እና አስተዳደራዊ ጉዳዩን ወደ ዘመናዊ አሰራር ማሻገር ነው። በቅርቡ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ለአደባባይ ሚድያ እንደተናገረው ''ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ መስርያቤቶች ስንት ጊዜ አስተዳደራዊ መዋቅራቸውን ወደ ዘመናዊ እና ተጠያቄ አሰራር ሲቀይሩ እንደነበረ ከመቶ ዓመት በፊት እንዳለ የምታገኘው የቤተ ክህነቱ ዘመናዊነት የሌለበት አስተዳደራዊ አሰራር ነው'' ነበር ያለው። ይህ የሚያሳየው ጉዳዩ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት ሃይማኖታዊ ዶግማ እና ሥርዓቷን ሳይሆን አስተዳደራዊ አሰራሯን ቤተ ክርስቲያን ለማዘመን መነሳት እና የገንዘብ መዝባሪዎቿን በሙሉ ነቅላ ስርዓት ማስያዝ ወሳኝ ሥራ መሆኑን ነው።

 ከላይ የተጠቀሰው ልዩ ቢሮ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ምዕመናን፣የአስተዳደር ባለሙያዎች፣የፋይናንስ ባለሙያዎች፣የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች፣የሕግ ሰዎች እና የፖሊስ እና ፀጥታ ክፍል ሰራተኞች ሁሉ ያቀፈ ሆኖም ግን ሁሉም በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የተጉ ወይንም በቤተ ክርስቲያኒቱ ዕምነት ውስጥ ያሉ አባላት ያሉት ጠንካራ የቤተ ክርስቲያኒቱን የአስተዳደር እና የገንዘብ ብክነት ሁሉ የሚመለከቱ እና የመፍትሄ ሃሳብ ከማቅረብ ጋር መዋቅሩን አስተካክሎ እስከ የሰው ኃይል ቅጥር ድረስ መልክ አስይዘው የሚሄዱ ሙሉ የማስፈፀም አቅም ያላቸው መሆን አለባቸው።

የእዚህ አይነቱ ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኒቱን ዶግማ እስካልነካ ድረስ ምንም አይነት አደጋ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አያደርስም።ምክንያቱም ከመንግስትም ሆነ ከምእመናን የሚመጡት የኮሚቴው አባላት በሙሉ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ከእዚህ በፊት በአንድም በሌላም ሲደክሙ የነበሩ ናቸውና።

በ21ኛው ክ/ዘመን ''የአይቲ''  (የዘመናዊ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ) ክፍል (ዲፓርትመንት) በመዋቅር ደረጃ የሌላት በሚልዮን የሚቆጠር ምዕመን የያዘች ቤተ ክርስቲያን -የአስተዳደር ችግሯ አንዱ መገለጫ 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መዋቅሯ ከቤተ መንግስት እስከ ታች የገበሬው ጎጆ ድረስ ቢሆንም ይህንን አገልግሎቷን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማስተሳሰር ሌላው ቀርቶ አጥብያዎች ለሀገረ ስብከታቸው ጋር የሚገናኙበት የኔትወርክ ሥራ አለመኖሩ የገንዘብም ሆነ የአስተዳደራዊ ሪፖርቶች የሚቀርቡበት መንገድ ዘመናዊ አይደለም።ከእዚህ ይልቅ በቤተክርስትያኒቱ ስር ያሉ ማኅበራት ለምሳሌ የማኅበረ ቅዱሳን መንፈሳዊ ማኅበር የአገልግሎት ክፍሎች የኢንፎርሜሽን መዋቅር ዘመኑን የዋጀ ሆኖ ይታያል።ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿን አቅርባ ለመጠቀም የአስተዳደራዊ ችግሯ ቀስፎ እንደያዛት ጉልህ ማስረጃ ነው።በ21ኛው ክ/ዘመን ላይ ሆነን አጥብያዎች ለሀገረ ስብከታቸው ሪፖርት በፖስታ ከመላክ ወጥተው የኢንፎርሜሽን አገልግሎቱ መላው አጥብያን የሚያገናኝ እና የቤተ ክርስቲያኒቱ አጥብያዎች በሚደርሱበት  በመላው ዓለም ከቤተ ክህነቱ ጋር የማገናኘት እና አገልግሎቱን የቀለጠፈ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው አንገብጋቢ አንዱ ተግባር ነው።

ማጠቃለያ 

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር ከአሁኑ የግንቦቱ ርክበካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ወሳኝ መፍትሄ የሚያገኝበት ካልሆነ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው ችግሩ አንዲት የዶሮ ላባ መጣያ ቦታ የለውም።ይህ ማለት ደግሞ ጠቅላላ ምዕመናን በገፋ መልኩ የሚጠይቁበት እና ችግሩ ወደ አልተፈለገ መፋተግ የመድረስ አደጋው ግልጥ ነው።ይህ ደግሞ በሀገሪቱ ላሉ የፖለቲካ እና የጎሳ ግጭቶች ሌላ መልክ ያስይዘውና ጉዳዩ ወደ ተለያዩ ፍላጎት ወዳላቸው አካሎች እጅ እንዲገባ እና መንግስትም ሆነ ቤተክርስቲያኒቱ ሊቆጣጠሩት  ወደ ማይችሉት መንገድ ያመራል።ስለሆነም ወግ ባለው መልኩ ምእመናንም ሆኑ መንግስት የቤተ ክርስቲያኒቱ የአስተዳደር ችግሮች እንዲቀረፉ ከልብ ሊነሱ ይገባል።ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ካህናት ባጠቃላይ፣ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ምዕመናን እና መንፈሳዊ ማኅበራት  እንዲሁም መንግስት በሙሉ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ችግር  ለመፍታት የሚነሱበት ወሳኝ ጊዜ ነው። እዚህ ላይ ትዕግስቱ እና ምሕረቱን ላሰፋልን የቤተ ክርስቲያን ራስ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ምስጋና ይድረሰውና ከአሁን በኃላ ግን እርሱም የዶሮ ላባው ያህል ጥፋት በቤተ ክርስቲያን ላይ የማይታገስበት ጊዜ መሆኑን አውቀን ለማይቀረው አስተዳደራዊ ችግር መፈታት አካል ለመሆን እንነሳ!

================///============

Saturday, April 13, 2019

አዲስ አበባ ሜክሲኮ እና ትዝታዎቿ በኢቢኤስ ቲቪ (ቪድዮ)

አዘጋጅ እና አቅራቢ  ጋዜጠኛ ዮናስ ከበደ 
ምንጭ - ኢቢኤስ ቲቪ 
ቪድዮ አንድ 

ቪድዮ ሁለት 



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Sunday, April 7, 2019

ኦነግ ያለው ኦዴፓ ውስጥ ነው።ኦዴፓ ከኦነግ ጎን መሰለፍህን አሳውቅ! ወይንም ያስጠለልከውን ኦነግ ቆርጠህ ጥለህ ከኢትዮጵያ ጋር ወግን!


ጉዳያችን /Gudayachn
መጋቢት 30/2011 ዓም (April 8/2019) 
==================
በእዚህ ፅሁፍ ስር : -
የከረሙ ወንጀለኞች ዳቦ ሲጠግቡ፣
''በብረት የመጣ በብረት ነው የሚመለሰው'' የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ፣
-  ኦነግ ያለው ኦዴፓ ውስጥ ነው፣
የሰሜን ሸዋው የኦነግ ጥቃት ዓላማ፣
መወሰድ ያለባቸው አምስት መፍትሔዎች  በሚሉ ርዕሶች ስር የተከፋፈሉ አጫጭር ፅሁፎች ያገኛሉ።
========================
የከረሙ ወንጀለኞች ዳቦ ሲጠግቡ 

ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ በሰሜን ሸዋ ማጀቴ፣አጣዬ እና ካራቆሬ እንዲሁም በወሎ ከሚሴ የኦነግ ጀሌዎች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል።የሰሜን ሸዋውን ግጭት ተከትሎ እስካሁን ቢያንስ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት መቀጠፉን መሰረቱን እንግሊዝ ያደረገው 7D የዜና አገልግሎት እሁድ ምሽት ሽብርተኝነት እና የፀጥታ ጉዳዮች በሚል ንዑስ አምዱ ስር ዘግቦታል።በኦነግ ስር የተጠለሉ ፅንፈኞች የከረሙ ወንጀለኞች ናቸው።ላለፉት ሠላሣ አምስት  ዓመታት ''ሐበሻ '' ''ሰሜኖች'' ''ነፍጠኞች'' እና ሌላም ስም እየሰጡ  ብዙ ንፁሃን የዓማራ ተወላጆችን ገድለዋል።የኦነግ ወለድ ትውልድ እና ተከታዮቹ በንፁሃን ላይ አሰቃቂ ግድያ መፈፀማቸው ለሕዝብ የተነገረው በኮ/ል መንግስቱ ዘመን አሶሳ ላይ ''አማሮች'' ናችሁ ተብለው በአንድ ቤት ውስጥ ተዘግቶባቸው እንደ ጧፍ የነደዱት ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ዛሬ ድረስ ሐውልት አልተሰራላቸውም።በመቀጠል በህወሓት ኢህአዴግ የስልጣን የመጀመርያ ዓመታት በአርሲ፣አርባጉጉ ፣በበደኖ የተፈፀሙት ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ናቸው።የሁሉም የዘር ማጥፋት ድርጊት አመራር ሰጪዎች ዛሬ እንደ ጵላጦስ እጃቸውን ታጥበው በፖለቲካ ድርጅቶች ስም ተሰይመው በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እየተንፈላሰሱ ይገኛሉ።መፅሐፍ ዓለም ከምትናወጥባቸው ምክንያቶች አንዱ ሰነፍ እንጀራ ሲጠግብ ነው ይላል።አሁን ባለንበት ዘመን የከረሙ ወንጀለኞች ዳቦ የጠገቡበት ዘመን ነው።

''በብረት የመጣ በብረት ነው የሚመለሰው'' የሰሜን ሸዋ ሕዝብ 

በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ወደ ሀገር ቤት ገባሁ ያለው ኦነግ የጅላጅል እና የአጉል ብልጣብልጥነት ፖለቲካ ለማራመድ ሲውተረተር ይታያል።ፈሪ ሁል ጊዜ ጨካኝነት የጅላጅል ማምለጫ መንገዱ ነች።ላለፉት አርባ ዓመታት ያልተሳካለት ኦነግ በአይሮፕላን ወደ ሀገር ቤት ገብቶ አንዴ በወለጋ፣ሌላ ጊዜ በጌድዮ አሁን ደግሞ በሰሜን ሸዋ ላይ የትንኮሳ እና የሽብር ሥራ እየሰራ ነው።የእዚህ አይነት በጠበንጃ የመጣ ጀሌ በብዕር  አይመለስም።በብረት የመጣ መነጋገርያው ብረት ብቻ ነው።የትዕቢት መንፈስ ካልበረደ ጠበኛ የሰላም መንገድ አይታየውም።

ኦነግ ያለው ኦዴፓ ውስጥ ነው

ኦነግ የት እንዳለ እራሱን ለመደበቅ ብዙ ይጥራል።ኦነግ ያለው ፅንፈኛ አክትቪዝቶች ውስጥ ነው፣ኦነግ ያለው አክራሪ የእስልምና መንግስት ለማቆም ከሚውተረተሩ የለየላቸው አሸባሪዎች ጋር ነው።ኦነግ ይለው በብሮክራሲ እራሱን ደብቆ ኦዴፓ (ኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ) ውስጥ ነው።ለእዚህም በኢትዮጵያ ባለፉት አንድ ዓመታት የተፈፀሙት ግድያዎች፣ሕዝብ የማፈናቀል እኩይ ተግባራት እና የኦዴፓ የተሳከሩ ዋልታ ረገጥ መግለጫዎችን መመልከት ይበቃል። ኦነግ በቅርብ እንደ አንድ ስልት መጠቀም የጀመረው በእርግጥ ቀደም ባሉ ዓመታትም በኦህደድ ስም ተሰግስገው ነገር ግን ፅንፍ ይዘው በብሮክራሲው ውስጥ ሕዝብ ያስለቀሱ የኦነግ ፅንፈኛ አስተሳሰብ አራማጆች ነበሩ።አሁን ግን ጉዳዩን የከፋ የሚያርገው የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ዩኒፎርም የለበሱ ነገር ግን በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች በሰላማዊ ሕዝብ ላይ እያደረሱት ያለው ጥቃት ነው።
 ኦዴፓ በብሮክራሲውም ሆነ በአስተሳሰብ ይህንን ያህል ከኦነግ ጋር የተሞዳሞደበት ምክንያት በራሱ ለስልጣን ካለ ጥማት የሚመነጭ ነው።ኦዴፓ በምርጫው ለማሸነፍ ከኦነግ የተሻልኩ ነኝ የሚል አማራጭ ስልት ይዞ ከሆነ በጣም ተሳስቷል።አሁን የሚታየው ይልቁንም እራሱ ኦዴፓ እየከሰመ ኦነግ በኦዴፓ ቢሮክራሲ ውስጥ እየታየ ነው።ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆርጦ ኦዴፓን እንዲዋጋው ያደርገዋል።በእዚህም የለውጡ ሂደት ሙሉ በሙሉ ሐዲዱን የመሳት አደጋ አለው። 

የሰሜን ሸዋው የኦነግ ጥቃት ዓላማ  

በእዚህ ሳምንት በማጀቴ፣አጣዬ እና ካራቆሬ ሰሜን ሸዋ እና ወሎ ከሚሴ  ሰላማዊ ሕዝብ ላይ የተከፈተው ጦርነት በቅጥረኘንት ኦነግ በተከፋፈለ አንጃዎቹ እና በህወሓት የውስጥ ድጋፍ ጭምር እንዲሁም ኦዴፓ ውስጥ በተሰገሰጉ የብርክራሲው አካላት ስልታዊ እና የመረጃ ድጋፍ የተቀናበረ ነው።የጥቃቱ ዓላማ ፍርሃት ነው።ፍርሃት ብቻ አይደለም። ኦነግ ከፅንፈኛ አቅትቪስቶች ጋር በፈፀመው ቁርኝት ጭምር የዶ/ር ዓብይን መንግስት መጣል ያስባል።ይህንን ሲያደርግ እንደ ቀዳሚ ስጋት የሚያየው የሰሜን ሸዋ ሕዝብ ነው።ይህ ሕዝብ ለአዲስ አበባ ካለው ቅርበትም ጭምር ቢያንስ ለማሸበር ታቅዷል።እዚህ ላይ ግን ኦነግ ትልቅ ስህተት ማድረጉን እረስቶታል።በዓማራ ክልል በተለይ በሰሜን ሸዋ አይደለም ቤተ ክርስቲያን የሚያቃጥል ጀሌ መጥቶ ህዝቡ ዋጋ የሚሰጠው ለጀግና እንጂ ለፈሪ አይደለም።ወንዱ ቀርቶ ሴቷ ነብር ነች።ይህንን ያማይውቅ ብዙ ሊያወራ ይችላል።በአርሲ አርባ ጉጉ ኦነግ በፈፀመው የግፍ ሥራ በናዝሬት/አዳማ በኩል ዞረው የኦነግን ሰራዊት የቀጡት ከሰሜን ሸዋ ተነስተው የሄዱ አርበኞች ናቸው።ይህ አካባቢ እጅግ ሕግ አክባሪ ነገር ግን ፍትህ ለመጉደሉ እርግጠኛ ሲሆን ደግሞ ታቦት ይዘህ የማታቆመው ሕዝብ ነው።ኦደፓ እስካሁን በብሮክራሲው ውስጥ አቅፎ የያዛቸው የኦነግ ጀሌዎችን በግልጥ ቆርጦ መጣል አለበት።ይህ ካልሆነ ኦዴፓ ሙሉ በሙሉ በኦነግ ስር መግባቱ ተረጋግጦ የኢላማው አካል ይሆናል ማለት ነው። 

መወሰድ ያለባቸው አምስት መፍትሔዎች 
የእዚህ አይነት ፀብ ጫሪ ድርጊቶች በተለይ ንዝረቱ በሌሎች አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ እና ዓማራ ተወላጆች ላይ እንዳይንፀባረቅ ከፍተኛ ጥረት ያስፈልጋል።የኦነግ ፅንፈኛ ሰራዊት በኤርትራ በኩል ሲገባ የምሳ ግብዣ አድርገው እንደሚባለውም አስታጥቀው የላኩት አቦይ ስብሐት እና የህወሓት ፅንፈኛ አካል አሁንም ስስ የሚሉትን አካባቢ እየመረጡ ግጭቶች የመፍጠር ስራዎችን ዛሬም አይሰሩም ማለት አቻልም።ይህ በሰሜን ሸዋ ሕዝብ ላይ የተፈፀመው ጥቃት  በሰላማዊ ሕዝብ ላይ የተፈፀመ ግልጥ ጥቃት ነው።ለሁሉም ችግሮች መፍትሄዎች አሉት።ይህም ችግር የሚተገብረው ቢያገኝ መፍትሄ አለው።ስለሆነም መፍትሄውቹ - 

1ኛ) ኦዴፓ ከኦነግ ጋር የመሞዳሞድ ስራውን ቆርጦ መጣል ወይንም እራሱን በኦነግ አሸባሪነት መድቦ መውጣት፣

2ኛ) ዶ/ር ዓቢይ ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ ጠፍቶ ሃገራዊ ፓርቲ ይኖረናል ያሉትን ንግግር በቶሎ ወደ ፊት ማምጣት በፓርቲያቸው ውስጥ  የተሰገሰገውን ኦነግ ወደ ጎን አድርገው ለማለፍ ያላቸው አንዱ የመውጫ ኮሪደር ነው፣

3ኛ) በኦሮምያ እና በፌድራል ደረጃ ያለው የቢሮክራሲ መዋቅር መልሰው ከኦነግ ማጥራት።

4ኛ) የፀጥታ ሁኔታን በተመለከተ አዲስ የተሻሻለ መመርያ ለጦር ሰራዊቱ መስጠት ሕዝብ እንዲያውቀው ማድረግ እና 

5ኛ) በጎሳ ስም የተደራጁ የቴሌቭዥን እና ራዲዮ ጣቢያዎች በሙሉ ከጎሳ ስም ከፋፋይ ወደ አልሆነ ስም እንዲቀይሩ እና አሰራራቸው ላይም ምንም አይነት ግጭት የሚቀሰቅስ ተግባር እንዳይፈፅሙ ተቆጣጣሪ ቦርድ መመስረት።

መንግስት እነኝህን ተግባራት ካላከናወነ ግን በሁሉም በኩል ያሉት የፅንፍ ኃይሎች ኢትዮጵያን ወደ ለየለት የጦርነት አውድማ የመውሰድ አቅም አላቸው።በኦነግ ስም በግልጥ የታጠቀ ኃይል እየተንቀሳቀሰ እና በንፁሃን ላይ አደጋ እያደረሰ በሌላ በኩል ያለው ሕዝብ በዝምታ ያልፋል ብሎ ማሰብ አይቻልም።ይልቁንም ጥቃቱ የበለጠ ሰላማዊ ሕዝብ ወደ ትጥቅ ትግል እንዳይሄድ እና ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ ያሰጋል።አሁንም እውነታው አንድ ነው። ኦነግ ያለው በኦዴፓ እቅፍ ውስጥ ነው።መፍትሄው ደግሞ ኦዴፓ እራሱን ከኦነግ ለይቶ በግልጥ ማውገዝ የገባዋል።መንግስት እንደመንግስትም  ከአድሏዊ አሰራሮች እራሱን ጠብቆ አሸባሪዎችን መቅጣት ካልቻለ አደገኛ ነው።የዶ/ር ዓቢይ መንግስት በኦነግ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ ካልወሰደ ኢትዮጵያን ወደ አደገኛ ብሔራዊ  የፀጥታ ችግር ብቻ ሳይሆን በውጭ ኃይል የመጠቃት አደጋም ሊያጋጥም ይችላል።ስለሆነም መሞዳሞዱ ይብቃ!


  
ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Thursday, April 4, 2019

የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ፣ በኦስሎ ያደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ ጭብጥ

የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ለመጋቢት 21/2011 ዓም ስብሰባ ከወር በፊት የለቀቀው ማስታወቂያ 
ETIOPISK FELLES FORUM I NORGE (Ethiopian Common Forum in Norway) meeting held in Oslo, Norway on March 30/2019.

ጉዳያችን / Gudayachn
መጋቢት 27/2011 ዓም (አፕሪል 5/2019 ዓም)
==============
የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ባሳለፍነው ቅዳሜ መጋቢት 21/2011 ዓም  በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተስፋዎቹና ተግዳሮቶቹ በሚል ርዕስ በኖርዌይ ዋና ከተማ በኦስሎ በሚገኘው የእንስሳት ሕክምና ምርምር ማዕከል (Veterinærhøgskole) በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ ላይ ከኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ፣በፖለቲካ ድርጅት አመራርነት፣በኖርዌይ የሴቶች ማኅበር፣የኖርወጅያን ምክር ቤት ለአፍሪካ እና ምሑራን ተገኝተውበታል።

በውይይቱ ወቅት በርካታ ጉዳዮች ከመነሳታቸው አንፃር ሃሳቦቹን በተወሰኑ ነጥቦች ጨምቆ ማቅረብ ብዙ ሐሳቦች እንዲደበቁ ስለሚያደርግ ከተሳታፊዎች የተነሱትን ነጥቦች እንደወረዱ (በዘጋቢው ያልተተነተነ ጥሬ መረጃ ) ማቅረቡ በተለይ ለለውጡ ኃይልም በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ምን እያለ እንደሆነ አንድ ግብዓት ሊሆን ይችላል።ስለሆነም በተሳታፊዎች የተባሉትን እንደሚከተለው ለመዘርዘር እሞክራለሁ።



  • በኢትዮያ የሚድያ ችግር አለ።የሚያርቅ ሚድያ ማግኘት ችግር ሆኗል ፣
  • በፖለቲካ ትንታኔ ላይ ድፍረት መብዛቱ እና ሁሉም ካለሙያው እየገባ መፈትፈቱ አንዱ ችግር ነው ፣
  • ዶ/ር ዓቢይ ኢትዮጵያን ከስሟ ጀምሮ ከዘመናት በኃላ በማንሳቱ ከፍ ያለ ክብር እንሰጠዋለን፣
  • ከስር ያለው የቀድሞው የህወሓት (ኢህአዴግ) መዋቅር አለመነሳቱ ዋናው የፀጥታ ችግር ነው፣
  • አክራሪዎች ሀገር እያጠፉ ያሉት በተከፈተው የዲሞክራሲ ቀዳዳ ነው፣
  • ዶ/ር ዓቢይ አንዳች የተደበቀ አጀንዳ አላቸው የሚል ግምት የለንም።ለእዚህም ማስረጃው እስካሁን ከመጀመርያ ጀምሮ ያለው ቃላቸው አለመቀያየሩ እና ወጥ መሆኑ ነው፣
  • የቡራዩ አደጋ አንድ የትግል አቅጣጫ አስቀያሪ ሆኗል።ለፅንፈኛው አካል ዕድል ሰጥቷል፣
  • ለውጡን የሚጎዳ አንዳችም ነገር እንዳይፈፀም መከላከል አለብን፣
  • በፅንፈኛው እና በለዘብተኛው መሐል መሃል ሆኖ የኢትዮጵያን ታላቅነት የምሰብከው አካል ቦታ እያጣ ነው ፣
  • ዲያስፖራው ሀገር ቤት ባለው ፖለቲካ እንዴት ተደራሽ እንደሚሆን ማሰብ አለበት።ለምሳሌ በምርጫው ሂደት ታዛቢ የመላክ መብት አለው፣
  • ህወሓት አሁንም ያልሞት ባይ ተጋዳይ ሥራ በሶስት መንገድ እየሰራ ነው። እነርሱም: - 1ኛ) የጎሳ ድርጅቶችን በማብዛት 2)ተቃዋሚዎችን የለዘቡ እንዲሆኑ ማቅረብ እና 3)በሶሻል ሚድያ ላይ መስራት የሚሉት ናቸው።
  • እንዴት ሰው አውሮፓና አሜሪካ እየኖረ የዘር ፖለቲካ ያራምዳል? አንድ ተሳታፊ የጠየቁት።
  • The silence majority የሚታወከው በጥቂት noise ፈጣሪ ነው፣
  • መጪው ምርጫ በሚገባ መሄዱን ለማረጋገጥ በውጭ ያለው ማኅበረሰብም መወያየት አለበት፣
  • አሁን የኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ኢትዮጵያ የለችም ከሚል ፅንፈኛ ጋር ነው።ይህም በራሱ ሶስት ተግዳሮቶች ይዞ መጥቷል። እነርሱም - ማለቂያ የሌለው የፅንፈኛ ሁሉን የእኔ የሚል ጥያቄ፣በትልልቆቹ ብቻ ሳይሆን በአናሳዎች ውስጥ ያሉ የጎሳ ግጭቶች እና እነርሱን ተከትሎ የሚመጣው የከፋ ድኅነት ናቸው፣
  • በኢትዮጵያ ኢምባሲ በኩል ያለውን አሰራር ትክክለኛ እና ዘርን ያልተከተለ መሆኑን የመቆጣጠር ሥራ የዲያስፖራውም ጭምር ነው፣
  • ፅንፈኛ እያልን የምንጠራው አካል ጋር የተቀላቀሉትን ጊዜ ሰጥቶ መስማት እና በማወያየት ወደጤነኛ ፖለቲካ ማምጣት ያስፈልጋል።የናይጀርያው ''ቦኮሃራም'' ወደ ሰላማዊ መንገድ ለማምጣት የተሄደበት አካሄድ በተሞክሮነት ቀርቧል፣
  • የኖርዌይ መንግስት በኢትዮጵያ ያሉትን የፅንፈኛ እንቅስቃሴዎች ለማጥናት ከፍተኛ በጀት መድቦ እያጠና ነው፣
  • ወጣቱን ዝም ብሎ መውቀስ ይታያል።ከእዚህ ይልቅ ወጣቱን የተማሩት ቀረብ ብለው ማስተማር ነበር የሚገባቸው፣
  • ብዙዎች ኢትዮጵያ እንላለን እንጂ ቅንነት የጎደለው ፖለቲካ ነው የምናራምደው እንታረም፣
  • በጎሳ ፖለቲካ አንዳንዶች ከወያኔ ያልተለዩ ናቸው።አውሮፓ እና አሜሪካ እየኖሩ የጎሳ ፖለቲካ ማራመድ ጠነኛነት አይደለም፣
  • ለውጥ ቀስ እያለ ነው የሚሞቀው።ብዙ ስለሆን ፍላጎታችን በእዚያው መጠን ይለያያል እና ትግስት ያስፈልጋል፣
የሚሉ እና ሌሎች ሃሳቦች ተሰንዝረዋል።በመጨረሻም የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ ላለፉት አራት ዓመታት በአዲሱ ሥራ አስፈፃሚ አስተባባሪነት በተዘጋጁት የውይይት መርሐግብሮች ላይ ሶስት ግብዓት ብቻ ማለትም የአስተባባሪዎች ጊዜ፣ዕውቀት እና ነፃ የመሰብሰብያ አዳራሾችን በማፈላለግ ካለ ምንም የገንዘብ ወጪ እና ድጋፍ ሲያዘጋጅ መቆየቱ ተነግሮ ወደፊት ስራውን በተሻለ መንገድ ለማቀላጠፍ ሌሎች ምሁራን ለማሳተፍ ተከታታይ ውይይቶች ማድረጉን እና የጋራ መድረኩ ርዕይ፣ተልዕኮ እና መዋቅር በበለጠ ደረጃ የማደራጀት ሥራ በመስራት መሆኑ ለተሰብሳቢዎቹ ተጠቅሶ ስብሰባው ከምሽቱ 12 ሰዓት ተኩል ላይ ተፈፅሟል።



ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...