ከጥንትም የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው ''አውርቶ አደር'' ማንነት
የኢትዮጵያ የታሪክ ስብራት ዋነኛዎቹ ምክንያቶች አውርቶ አደሮች ናቸው።ይህ አደር የሚለው የአማርኛችን ቃል ከፊት አንድ ቃል እያስከተለ ''አደር'' የሚለውን ቃል ብዙ ፍቺ ያሰጠዋል። ወቶአደር(ወታደር)፣ላብአደር፣ ሰርቶአደር፣ወዝአደር የሚሉትን ቃላት እናውቃቸዋለን። በስማቸው ያልጠራናቸው እና መጥራትም የሚገባን ''አውርቶአደር'' የሚባሉትን ነው።
ኢትዮጵያን ወደፊት ለማስፈንጠር የተጉቱ የቀደሙ የኢትዮጵያ ነገስታት፣ምሑራን፣ሃሳብ አመንጪ ዜጎችን ሁሉ አላሰራ ያለ አፉን በነጠላ ሸፍኖ አንዳች ፍሬ ነገር ሳይሰራ እያልጎመጎመ ሲያወራ ውሎ የሚያድረው አውርቶ አደር ነው። አፄ ቴዎድሮስ ከዘመናቸው ቀድመው የሚያስቡ መሪ ነበሩ።ሌላው ቀርቶ መጪው የሀገር መከላከያ በዘመናዊ መሳርያ ካልታገዘ ሃገር መጠበቅ አዳጋች መሆኑን ስላወቁ መድፍ እንዲሰራላቸው ትዕዛዝ ሲሰጡ፣አውርቶ አደር ያወራ ነበር።
ዳግማዊ ምንሊክ አውርቶ አደር ሳይሆኑ ሰርቶ አደር ነበሩ።ከዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ እስከ የትራንስፖርት ስራ፣ከአካባቢ ጥበቃ እስከ ዘመናዊ ጦር ማደራጀት፣ከስልክ እና መኪና ማስመጣት እስከ አብያተክርስቲያናት ግንባታ ሰርቶ አደር ነበሩ። አውርቶ አደሩ ግን በዘመናቸው ሰላም የነሳቸው ጊዜ በቀላሉ የሚቆጠር አልነበረም። በእያንዳንዱ ስራቸው አውርቶ አደር እየገባ ለሀገራቸው የሚሰሩትን ለማደናቀፍ ሲያወራ ውሎ ሲያወራ ያድር ነበር። ዳግማዊ ምንሊክ መኪና አስመጥተው የመጀመርያው ነጂ ሲሆኑ፣ሊገዝቱ የቃጡ ነበሩ። ሲኒማ ቤት ከፍተው ለሕዝብ ሲያሳዩ አውርቶ አደር ''የሰይጣን ቤት'' ብሎ ሲያወራ ዋለ። መጪው የታያቸው ዳግማዊ ምንሊክና እቴጌ ጣይቱ የመጀመርያውን ዘመናዊ ሆቴል ጣይቱ ከፍተው ንጉሱና ንግስቲቱ እየገቡ ሰውን ለማለማመድ ሲሞክሩ አውርቶ አደሩ ሴት እንዴት ሆቴል ገብታ ትበላለች? እያለ ይሳለቅ ነበር። አውርቶ አደር በየዘመኑ ነበር። በዘመናችንም ጨምሮ።
አሁን ባለንበት ዘመን አውርቶ አደር እንደቀድሞው አፉን በኩታ ሸፍኖ የሚንሾካሾክ ወይንም ጠላና ጠጅ ቀኑን ሙሉ እየጠጣ ሲያወራ የሚውል አይደለም። የማኅበራዊ ሚድያ ላይ ተጥዶ ለኢትዮጵያም ለወገኑም አንድ ሳይሰራለት ብቻ ሳይሆን የሚሰሩትን ሲያብጠለጥል ሲሳለቅ የሚውል በአውርቶ አደርነቱ ደግሞ ዩቱብና ሌሎች የማኅበራዊ ሚድያ ተቋማት ገንዘብ ስጡኝ እያለ ሲማጸን የሚኖር ነው።
የዘመናችን አውርቶ አደር ከተማ ጸዳ፣መብራት ተተከለ ሲባል ሰርቶ አደሩ በሰራው የሚነቅፍበትን ሲያስብ ያድራል። የአድዋ ሙዜም ሊሰራ ነው ሲባል፣ የምንሊክን ሃውልትን ሊነቅሉት ነው ይላል፣ ይሄው አውርቶ አደር።ሃውልቱም ደምቆ ያልነበረ ሙዜም ተሰርቶ ሲያልቅ ደግሞ ሙዜም ከሚሰራ ይልና ሌላ ትረካ ይጀምራል።አውርቶ አደር ስራው አውርቶ ማደር ብቻ ስለሆነ ማመስገን ብሎ ነገር አያውቅም። ሌላው ቀርቶ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያልታደሰው የብሔራዊ ቤተመንግስ ሲታደስ፣ሸረሪት ያደራባቸው የሀገር ቅርሶች በወጉ ሲቀመጡ፣የሳይንስ ሙዜም ሲሰራ፣ግዙፍ ብሔራዊ መጻሕፍት ቤት ተሰርቶ ሲያልቅ፣የብሔራዊ መዛግብት መረጃ ማዕከል ሲሰራ፣የስቶክ ኤክስቸንጅ ማዕከል ስራ ሲጀምር፣የጎንደር አብያተ መንግስታት ታድሰው ከተማው ሲደምቅ ሳይቀር አውርቶ አደር አይኑን እያሸ ይመጣል። ያው እንደለመደው ለማውራት።
የዘመናችን አውርቶ አደሮች ምሳሌ እንጥቀስ ብንል እጅግ ብዙ ናቸው።ከአክቲቪስት ጀዋርን ብንወስድ አንዲት ጉድጓድ ውሃ ላላስቆፈረለት እና አንዲት ብርጭቆ ውሃ እንዲጠጣ ያላደረገውን የኦሮሞ ወንድሞቻችንን በአውርቶ አደርነት ነግዶ ጨርሶ አሁን በኢትዮጵያ ስም አውርቶ ለማደር እየሞከረ ነው። አውርቶ አደሮች እንዲህ ናቸው። ከአንዱ ጎራ ወደ ሌላ ለመዝለል ችግር የለባቸውም።በዩቱብ በአማራ ክልል ህዝብ የሚነግዱት አውርቶ አደሮች ለህዝቡ አንድ ቀን አንዲት ሳንቲም ልከው የአንድ ትምህርት ቤት መገልገያ የሚሆን አንዲት ቾክ አልላኩለትም። በስሙ አውርተው እያደሩ ግን በዩቱብ የልጆቻቸውን የትምሕርት ቤት ወጪ ይሸፍናሉ። የኢትዮጵያ ጉዳይ በሰርቶ አደሮች እና በአውርቶ አደሮች መሃል የሚደረግ ፍልምያ ነው። ህዝብ አውርቶ አደሮችን እየለየ ብቻ ሳይሆን እያራገፈ እና በስሜ አትነግዱ፣ከጫንቃዬ ውረዱ እያለ ነው።የኢትዮጵያ ሀገራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ችግር ፈጣሪዎች አውርቶ አዳሪዎች ናቸው።በእዚህ ዘመን ''አውርቶ አደሮች'' እና ''ሰርቶ አደሮች'' ተለይተዋል።
የግሪክ አቴንሱ ''ኢትዮጵያዊው'' አውርቶ አዳሪው ''ዲያቆን'
ያልደረሰበትን ግጭት ሲተርክ የነበረ በቦታው ያለ ይመስላል።የዛሬ ዘጠኝ ዓመት የነበረ የቤተክርስቲያን ችግር ቪድዮ ለቃቅሞ በኪሱ ይዞ ይዞራል።አባቶችን ሲሳደብ የኢትዮጵያ ውሃ የጠጣ አዛውንት እና የሃይማኖት አባት ከሚከበርባት ምድር የመጣ አይመስልም።በቤተክርስቲያን ስም በከፈተው የማኅበራዊ ሚድያ አንድም ሃይማኖታዊ ነገር ሳይጽፍበት የጠላ ቤት ወሬ ብቻ ሳይሆን ፈጽመው ውሸት የሆኑ ጽሑፎች እየጻፈ፣ካህን ከካህን፣ምዕመን ከምዕመን ያጣላል። የአውርቶ አዳሪውን ''ዲያቆን'' ነገሩን የከፋ የሚያደርገው በቤተክርስቲያን መሃል ይዛሬ ዘጠኝ ዓመት የነበረ ጉዳይ እያነሳ ''ይሄኛው ቅዱስ፣ያኛው እርኩስ '' እያለ ህዝቡን ያለያያል።ሰዉ ጭቅጭቅ ሰልችቶት እርስ በርሱ እየተገናኘ ''ይሄ ሰው ግን ጤነኛ ነው?'' እያለ ያወራል። ይህ አውርቶ ማደር ለእርሱ የሙሉ ጊዜ ስራ አድርጎታል። ህዝቡ ደግሞ ሰርቶ አደር ነው።እንደእርሱ ሲያወራ አይውልም አያድርም። ለፍቶ ውሎ ሲገባ አውርቶ አደሩ የጻፈውን የውሸት ክምር የሚያይለት ይመስለዋል። ሰርቶ አደሩ ህዝብ ደግሞ የአውርቶ አደሩን ''ዲያቆን'' ነጭ ውሸት ከመሰልቸቱ የተነሳ ስለ አዕምሮው ጤንነት ተጠራጥሯል።
አውርቶ አዳሪው ''ዲያቆን'' ሲያጥላላቸው የነበሩት እና በውሸት ህዝብ ሲያታልል የነበረባቸው ጉዳዮች አንድ በአንድ እየተተረተሩ እውነታቸው ሲሰጣበት፣ ሲያጥላላው የነበረውን ጉዳይ አብራሪ ሆኖ ብቅ ይልና ሊያብራር ሲሞክር ሰርቶ አዳሪውን በሳቅ እየገደለው ነው።ሰርቶ አዳሪው ህዝብ ጊዜ የለውም።ይሰራል።ሰርቶ ገዳም ገዝቶ ሀገሩን ያስጠራል።አውርቶ አዳሪው ''ዲያቆን'' ሰርቶ አደሩ ህዝብ ገንዘቡን አውጥቶ የገዛውን ገዳም ለማዘጋት ቁና ሙሉ ደብዳቤ በያዘው የቤተክርስቲያን ማኅተም እየጻፈ ይልክና በማኅበራዊ ሚድያው ላይ ብቅ ብሎ ገዳሙ ሊያዘጉት ነው ይልና ''እሪ!'' ይላላ። ይህ ብቻ አይደለም።ወደ ሃገርቤት ቤተ ክህነት ሳፋ ሙሉ ደብዳቤ እየጻፈ ሰርቶ አደሮቹ የቤተክርስቲያን ፈቃዳቸውን ንጠቁልኝ እያለ ይጮህና በማኀራዊ ሚድያ መጥቶ ወደ ስርዓት አልመጡም፣መጡ እያለ ያላዝናል።ይህ አውርቶ አደር ''ዲያቆን'' ህዝብ አውኳል።በውሸት አባቶችን ተሳድቧል፣ከጳጳሳት ጋር ለማጣላት ሆን ብሎ በማስረጃ ያሉ እኩይ ተግባራት ፈጽሟል።
አውርቶ አደሩ ''ዲያቆን'' በቤተክርስቲያን የተነሱ ችግሮች እንዳይፈቱ፣ሰዎች እንዳይታረቁ ሌት ተቀን ይለፋል። ሀገረስብከት ከጳጳስ፣ጳጳስ ከካህን፣ካህን ከምዕመን ማጣላት እንደ ትልቅ ጥበብ ሲናገር እፍረት አይሰማውም። ለእዚህም በቂ ማስረጃዎች ተይዘውበታል።የመረጃ ማዛባት ላይ ሆን ብሎ እና ጉዳዬ ብሎ ሰርቶበት አሁን ከሽፎበታል። በእዚህ የማዛባት ስራው የቤተክርስቲያን ችግር እንዳይፈታ ሆን ብሎ እና አቅዶ ሰርቷል። ለምን? ምን ለማግኘት? ከእነማን ጋር አብሮ እየሰራ? የሚሉ ጥያቄዎች በቂ ምርመራ ይፈልጋሉ።እርሱ ኝ አድርጎታል።አሁንም አላቆመም።
የእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በህይወቱ አይደለም በድቁና ማዕረግ ያለ አንድ ቀን የሰርክ ጉባዔ የተማረ ምዕመን የእዚህን ያህል ''አካይስት'' መንገድ በራሱ ሀገር ህዝብ ላይ ሲፈጽምም ሆነ ቤተክርስቲያን ሰላም እንዳታገኝ ሲታትር ተመልክቶም ገጥሞትም አያውቅም።ይህንን ያህል የውሸት ክምር እየለጠፈ የሚዘልፋቸው አባቶች፣ምዕመናን እና ሰርተው የሚያድሩ በግሪክ ያሉ ኢትዮጵያውያን እጅግ ያዘኑበት ልክ ለመግለጽ ቃላት አይበቁም። እርሱ ግን ዛሬም በቤተክርስቲያኒቱ እየታከከ የመንደር የጠበበ አዎን የጠባባ ዓላማውን ለማራመድ በአውርቶ አደርነቱ ብቻ መቀጠልን ስራዬ ብሎታል።ስርቶ አደሩ ገዳም ገዝቶ ገና ለሌላ የበለጠ ስራ እየተጋ ነው። ቀድሞ አባቶቻችንን አላሰራ ያለው የአውርቶ አደር ውላጅ ግን ዛሬም ኢትዮጵያውያንን በአውርቶ አደር ሙያው ይሳደባል። በነገራችን ላይ ብዙ አውርቶ አደሮች የአዕምሮ ችግር የለባቸውም ብሎ ለመናገር አይቻልም።ማኅበራዊ ሚድያው ደግሞ አዕምሮ አይመረምርም። አውርቶ አደር የግድ የአዕምሮ ህክምና ለማግኘት ወደ ሃኪም ዘንድ ወይንም የስነ ልቦና ባለሙያ ማየት አለበት። አውርቶ አደር እንጀራው አይባረክም።ክፋቱ እራሱ ይበላዋል።ድቁናውን ግን መመርመር እና መልሶ ማዘግየት የሊቃነ ጳጳሳት ኃላፊነት ነው።እንጥፍጣፊ የእርቅ እና የክርስትና ሽታ የሌለው አውርቶ አደር እንዴት ''ዲያቆን'' ሆነ? የሁሉም ጥያቄ ነው።
=================////============