ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, May 30, 2024

ሻብያ አስመራ ሲገባ ያልተወለደው የኤርትራ አዲሱ ትውልድ ብሶት በ1960ዎቹ አስተሳሰብ ላይ የቆመውን የአቶ ኢሣያስ አስተሳሰብ ላይ ተነስቷል።



ባለፈው ሳምንት በኦስሎ በአስለቃሽ ጢስ የተበተነው የኤርትራ አዲሱ ትውልድ ተቃውሞ በሻብያ ላይ።
Source : VG Norwegian Newspaper


ሻብያ አስመራ ሲገባ በእናቱ ማህጸን የነበረው የኤርትራ አዲሱ ትውልድ የቆየችው ኤርትራ


በኤርትራ አዲስ ትውልድ ተፈጥሯል። ይህ ትውልድ ሻብያ ሲመሰረት ወይንም አስመራ ሲገባም ገና በእናቱ ማህጸን የነበረ ወይንም ገና ያልተጸነሰ ነው። ይህ ትውልድ የቆየችው ኤርትራ ቤተሰብ መስርቶ የማይኖርባት፣ከቤተሰብ ውስጥ በትንሹ አምስት ሰው የተሰደደበት አልያም አባትና ልጅ ሳይቀሩ በግዳጅ ውትድርና በሳዋ ስልጠና የሚገናኙባትና የሚተክዙባት ሀገር ነች የገጠመችው።


ይህ ትውልድ በኤርትራ ብቻ ሳይሆን በመላዋ ኢትዮጵያም ሲኖር የሻብያና ህወሓት በ1990 ዓም ግጭት ተከትሎ ኤርትራዊ ነኝ ብሎ የማያውቀው ትውልድ በህወሓት በድንገት እየተጫነ እስከ 70 ሺህ የሚሆኑ ወደ ኤርትራ ሲጫን እና ኤርትራም ከገባ በኋላ ለግዳጅ ወታደራዊ ግዳጅ ወደ ሳዋ ሲላክ የነበረው ይህ አዲስ ትውልድ ነው።


ይህ አዲስ ትውልድ የሻብያ ቁምጣ እና የጠፍር ጫማ ያደረጉ ታጣቂዎችን አያውቃቸውም።አልያም በ1985 ዓም የኤርትራ ህዝብ ከባርነት እና ከነፃነት አንዱን ምረጡ የሚለው ''የህዝብ ውሳኔ'' ሲቀርብ አያውቁም።እነርሱን የተቀበለቻቸው ኤርትራ ትምሕርት አስተምራ ሥራ የምትሰጥ ወይንም ቤተሰብ አፍርተው የሚኖሩባት ኤርትራ አይደለችም። ያገኟት ኤርትራ ሕገ መንግስት የሌላት፣ሕግ አውጭም፣ አስፈጻሚም አቶ ኢሳያስ የሆኑባት ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱ ምጣኔ ሃብትም ሆነ ፖለቲካ አቶ ኢሳያስ አእምሮ ላይ ያለ የማይታወቅ ዕቅድ ያላት ሀገር ሆና ነው ያገኟት።


በሶስት ዓመታት ውስጥ ብቻ በትንሹ 2,500 ኤርትራውያን  በሜደትራንያን ባህር ውስጥ ሰምጠዋል የተረፉትን የሻብያ ወኪሎች ያሳድዷቸዋል።


 ኤርትራዊው ቄስ  ሙሴ ዘራይ እና ''ሀበሻ ኤጀንሲ'' የተሰኘ ድርጅታቸው  በተለይ በ ሜዴትራንያን በኩል አልፈው ለመምጣት የሚሞክሩትን ኤርትራውያንም ሆኑ ኢትዮጵያውያንን በመርዳት  ይታወቃሉ።ድርጅታቸው በስደተኞቹ ዙርያ ያደረገውን ጥናት እና ያሉትን መረጃዎች ትናንት ጥቅምት 21/2006 ዓም (Oct.31/2013) ለፈረንሳይ የዜና አገልግሎት (ኤኤፍፒ) እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች መግለጫ ሰጥቷል።በመግለጫው ላይ የተተኮሩት ሁለት ነጥቦች የነበሩ ሲሆን በወቅቱ ጉዳያችን እንደሚከተለው ከትባው ነበር።


ከመግለጫው ነጥቦች የመጀመርያው  ከባህር ጉዞ የተረፉትን ስደተኞች ችግር ለጣልያን መንግስት የሚያስተረጉሙት የሻብያ መንግስት ሰላዮች መሆናቸውን እንደደረሱበት እና ጉዳዩን ከኢኮኖሚ ጋር ብቻ እያስተሳሰሩ ፖለቲካዊ ምክንያት እንዳላሰደዳቸው በመናገራቸው ችግር ከመፍጠራቸውም በላይ የስደተኞቹን መረጃዎች ለሻብያ መንግስት በሚስጥር እየላኩ ብዙ ቤተሰቦች ችግር ላይ መውደቃቸውን ገልፀዋል።


በሌላ በኩል እርሳቸው እና ድርጅታቸው ለጉዳዩ ቅርብ የመሆናቸውን ያህል እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2010 ወዲህ አሁን እስካለንበት 2013 ዓም በሶስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ወደ አውሮፓ ለመሻገር ሲሞክሩ በሜደትራንያን ባህር ውስጥ ሰምጠው የቀሩት ኤርትራውያን ቁጥር በትንሹ  2,500 መሆኑን ቄስ ሙሴ ተናግረዋል።ዜናውን የጀርመኑ DW ራድዮ እና የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ለመላው ዓለም አሰራጭተውታል።ይህንኑ መግለጫ ተከትሎም አዲሱ የኤርትራ ትውልድ በመላው ዓለም ተቃውሞውን በአቶ ኢሳያስ መንግስት ላይ  ማሰማቱ ይታወቃል።


አዲሱ የኤርትራ ትውልድ ጥያቄ እየገፋ ነው። ፎቶ ፡ቢቢሲ

የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርቲያን በሻብያ ደጋፊ እና ተቃዋሚ ምዕመናንና አገልጋዮች መከፋፈል።


በ1983 ዓም ግንቦት ወር አስመራን የተቆጣጠረው ሻብያ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ጵጵስና ትተዳደር የነበረችው ቤተክርስቲያን የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ስር ሆና ከአሌክሳንደርያ የኮፕት ቤተክርስቲያን ጋር እንድትገናኝ የአቶ ኢሳያስ ትዕዛዝ ነበር። ይህንን ተከትሎ አዲሱ የኤርትራ ትውልድ ሲነሳ ግን በውጭ ሃገራት የሚገኙ ቤተክርስቲያኖችን አሰራር ላይ አጥብቆ መመርመር ጀመረ። በእዚህም ሳብያ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት በየዓመቱ የውጭ ምንዛሪ ከምዕመኑ እየሰበሰቡ ወደ ሻብያ ፈሰስ መደረጉን ተቃወመ።ወደ ሃገርቤት በፐርሰንት የሚልኩት ደግሞ ለሀገር ልማት ነው በሚል ለማሳመን ሞከሩ። አዲሱ ትውልድ ግን አልተቀበለም። ቤተክርስቲያን የፖለቲካ መናሃርያ ልትሆን አይገባም በሚል የራሱን ቤተክርስቲያን መለየት ጀመረ። ለእዚህ አብነት በኖርዌይ እና ሌሎች ሀገሮች የሚገኙ የኤርትራ ኦርቶዶክስ እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች የወሰዱትን እርምጃ መመልከት በቂ ነው።


ያለፈው ሳምንት በአስለቃሽ ጢስ በኖርዌይ የተበተነው የሻብያ ተቃዋሚዎች የኖርዌይን ጋዜጦች ትኩረት ስቧል።


ባለፈው ሳምንት እኤአ ግንቦት 25/2024 ዓም የኤርትራውያን የአዲሱን ትውልድ ተቃውሞ በኦስሎ ይዞ የወጣው ቬጌ የተሰኝው ጋዜጣ የኤርትራውያን ተቃውሞ ከዘገቡት ጋዜጦች ውስጥ ነው።የጋዜጣው ዘጋቢዎች Bastian Lunde Hvitmyhr እና Vilde Elgaaen ሁነቱን ካቀረቡበት አቀራረብ መሃል እንዲህ የሚል ይገኝበታል : -


''ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች 33 ዓመታት መሙላቱን ለማክበር በሁሉም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ኤርትራውያን ለድግሱ በተዘጋጀው አዳራሽ ተሰብስበዋል።የሙዚቃውድምጽ ያስተጋባል።ብዙዎች በቀለማት ያሸበረቀ ነጭ ልብስ ለብሰዋል።ከአዳራሹ ውጪ የነበረው ገጽታ ግን የተለየ ነበር።በዓሉን የሚቃወሙ ሰልፈኞች በፖሊስ ላይ ድንጋይ ከመወርወር አልፈው መንገዱን በመዝጋታቸው ፖሊስ በመቶ የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን በአስለቃሽ ጢስ ተኩሶ ለመበተን ተገዷል በማለት የዘገበው የኖርዌይ ጋዜጣ ጉዳዩ የትውልድ ልዩነት መሆኑን እና አዲሱ ትውልድ የሻብያን አስተሳሰብ እና አካሄድ እንደሚቃወም ሲገልጽ እንዲህ በማለት አስቀምጦታል።


''Av dem som er i Norge i dag, er det mange som kom allerede under krigen og noen er fortsatt positive til regimet, fordi minnet de sitter igjen med er frigjøringskampen, og følelsen av at man fortsatt må ofre for at landet skal forbli selvstendig.... Andre som har flyktet senere kan være mer kritiske da de har opplevd hvordan regimet ble, og mener at dette bare er en retorikk regimet bruker for å beholde makten.'' VG: Feiret nasjonaldagen: –⁠ Hvorfor blir vi stemplet som regimestøttere?

አሁን ላለው የኤርትራ አገዛዝ አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው ቀደም ብለው በጦርነቱ ጊዜ የወጡ እና የሚያስታውሱት የነፃነት ትግሉን ጊዜ ሲሆን በኋላ የመጡት ግን የሚያውቁት የገዢውን (ሻብያን ማለት ነው) ስልጣኑን ለማቆየት በሚል በተለያየ ጊዜ የሚሰጣቸውን ዲስኩሮች ነው።

ለማጠቃለል የኤርትራ አዲስ ትውልድ ለአቶ ኢሣያስ ወሳኝና ትውልዳዊ ጥያቄ ይዞ ተነስቷል። አቶ ኢሳያስም ሆኑ ሻብያ ኤርትራን ከሠላሳ ዓመታት በላይ ሲያስተዳድሩ ላለማሳደጋቸው የሚሰጡት አንድም አሳማኝ ምክንያት የላቸውም። አንዱ አሳፋሪው ጉዳይ እና አዲሱን ትውልድ ለመሞገት እና ከጥያቄው ለመሸሽ ምንም ዓይነት የሞራል አቅም ሊኖር አይችልም። አንድ ሺህ ኪሎሜትር የባሕር በር ይዞ ሠላሳ ዓመት በሰላም ኖሮ ሀገሩን ማሳደግ አለመቻል ብቻ ሳይሆን አዲሱ ትውልድን ተሰዳጅ የማድረግ የዕድገት ስሌት ምንም ዓይነት ምክንያት ቢደረደር አያሳምንም። አዲሱ የኤርትራ ትውልድም እየጠየቀ ያለው ችግሩ መሪው እና አስተሳሰቡ ላይ ነው የሚል ነው።በእዚህም ከአውሮፓ እስከ እስራኤል ከ አሜሪካ እስከ ኖርዌይ፣ጀርመንና ስዊድን የአቶ ኢሳያስን አገዛዝ የተቃወመው ትውልድ አሁን ወደ አንድ ምዕራፍ መሸጋገሩ በግልጽ እየታየ ነው።አሁን ጥያቄው የኤርትራን አዲስ ትውልድ ጥያቄ የኢትዮጵያ ወጣቶችም ሊያግዟቸው አይገባም ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው።


=====================////////============









No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...