የኢትዮጵያ ወጣቶች ላለፉት አራት አስር አመታት በላይ የተቀበሉት መከራ ለአእምሮ የሚዘገንን እና ለመጪው ትውልድ ሰቀቀን ነው።በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ የደረሰውን ሁሉ በእዚህ አጭር ማስታወሻ መዘርዘር ከባድ ነው።ሆኖም ግን ከ1966 ዓም ለውጥ ወዲህ ለተፈጠሩት የፖለቲካ ኃይሎች ሰለባ በመሆን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ወጣት ነው።በእየጊዜው የሚነሱት መንግሥታትም ሆኑ በተቃዋሚ አንፃር የሚቆሙት የሰለባቸው መነሻ እና መድረሻ ወጣቱ ነው። የኢትዮጵያ ወጣቶች በቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር፣ በእርስ በርስ ጦርነቶች፣በስደት፣በሥራ አጥነት እና በረሃብ የተንገላቱባቸው አመታት አንድም በስልጣን ላይ ለነበሩት መንግሥታት የስልጣን ማስጠበቂያ አጥርነት ወይንም በተሳሳተ መንገድ የሚመሩ የስልጣን እና ህዝብን የመከፋፈል አባዜ የተጠናወታቸው ኃይሎች የስልጣን መወጣጫ መሰላልነት ማለቂያ ለሌለው ፈተና የተዳረጉ ናቸው።
ዛሬ ላይ ሆነን የምንረዳው ጉዳይ የኢትዮጵያ ወጣቶች እና ታዳጊ ወጣቶች ያሉበትን ሁኔታ የአገሪቱ በመንግሥትነት የተሰየመውን አካልም ሆነ በብሄር ኢትዮጵያዊነትን የሚያጥላላ ፖለቲካ የሚይራምዱ ተቃዋሚዎች ዘንድ ለሌላ የእልቂት ድግስ እየተዘጋጀ መሆኑን ነው።ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዘመኗ አይታ የማታውቀው ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚያወሩ ነገር ግን የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ በእየማህበራዊ ሚድያው ላይ በእሳት በማንደድ የሚዘባበቱ፣ በተቃዋሚነት የተሰለፉበት ወቅት ላይ እንገናኛለን።በመጀመርያ ደረጃ አንድ ተቃዋሚ የአንድ አገር ፖለቲካን፣ማኅበራዊ ኑሮ እና ምጣኔ ሐብት እኩል ተጠቃሚነት ጉዳይ ሲያነሳ የአገሪቱን ማንነት በሚንድ እና ሰንደቅ አላማዋን ክዶ የእራሱን ሰንደቅ አላማ ሰቅሎ ሊሆን አይችልም።ይህ የባዕዳን ወረራ እኩይ አቀራረብ ነው።
በእዚህ አይነት ሂደት ላይ የኢትዮጵውያንን ኢትዮጵያዊነት የሚፈታተኑ መንገዶችን የተከተሉ ሁለት፣ሶስት ተብለው የሚቆጠሩ ቢኖሩም ለእዚህ ፅሁፍ ግን በዋናነት የሚጠቀሱት ሁለት ክፍሎች አሉ።እነኝህን ክፍሎች በሁለት ስሞች መሰየም እንችላለን። እነርሱም 'ህወሃታውያን' እና 'ጀዋራውያን' በማለት መጥቀስ እንችላለን።
ህወሃታውያን መጀመርያ የተነሱበት እና በመግለጫቸው (ትግራይ ማኔፌስቶ 1968) ላይ እንደተገለፀው የትግሉ ማጠንጠኛ ትግራይን ከኢትዮጵያ የመገንጠል እና የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ገሸሽ አድርጎ ''የትግራይ''ያሉትን ''ሰንደቅ አላማ '' በሕዝቡ ዘንድ ማስረፅ ነበር።ቆይቶ ግን የትግራይም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አባቶቹ እና እናቶቹ ደማቸውን ያፈሰሱለት አጥንታቸውን የከሰከሱለት ሰንደቅ አላማ ጉዳይ ላይ የማይደራደር መሆኑን ሲረዱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አብረው ለመያዝ ተገደዱ።አሁን በሂደት በአዲሱ ትውልድ ላይ ለማስረፅ ባለመቻላቸው የአገሪቱ አንደነትን የሚያናጋ ማናቸውንም የጨርቅ አይነት በእየቦታው እያውለበለቡ የኢትዮጵያን መለያ ሰንደቅ አላማ ማኮሰስ ስራዬ ብለው ተያያዙት።
በተመሳሳይ ደረጃ 'ጀዋራውያን' በውስጣቸው ሁለት አይነት ስሜት ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ይዘው እየሄዱ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል።እነርሱም
1ኛ የኦሮሞ ሕዝብ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ድርሻ እኩል ተጠቃሚ መሆን አለበት የሚሉ ለእዚህም የኦሮሞ ባህላዊ እሴቶች በአግባቡ ተጠብቀው ለመጪው ትውልድ የሚተላለፉ እንዲሆኑ እና ለኢትዮጵያ እድገትም በግብአትነት የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ የሚፈልጉ እና
2ኛ የኦሮሞ ሕዝብን ጥያቄ ለብቻው ነጥለው በማስኬድ የህዝቡ የመብት ጥያቄ የእራሱ ወጥ አመራር እንዳይኖረው የሚያደርጉ፣ የኦሮሞ ህዝብ የደረሱበትን በደሎች ለስሜት መኮርኮርያ ብቻ ተጠቅመው በሚስጥር የተደራጁበት የፅንፈኛ እስልምና እምነት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለመጫን የሚሞክሩ፣ ለእዚህም ስኬት የኢትዮጵያ የሆነውን ነገር በሙሉ የቀደመውታርክንም ሆነ የአሁኑን ሰንደቅ አላማዋን ጨምሮ ከትውልዱ አእምሮ ውስጥ ለማስወጣት የሚጥሩ ናቸው።
የመጀመርያው ማለትም ኢትዮጵያዊነትን ከኦሮሞ ትግል ነጥሎ የማይመለከተው ክፍል፣ ፅንፈኛ አስተሳሰብ ለሚያራምደው የጀዋራውያን ክፍልን ከሚጠይቃቸው ጥያቄዎች ውስጥ ''የኢትዮጵያውያን ኦሮሞ ማሕበረሰብ ትግል ኢትዮጵያዊነትን ለምን አገለለው? ለምንስ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ለማግለል ወሰነ? የእዚህ ግቡስ ምንድነው? ለምንድነው የኦሮምያ ትግል መሪ ስውር የሆነው? ይህ አካሄድ ፅንፈኛው እስልምና መሰረት እንዲይዝ የተደረገ ስልት አይደለምን? በሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ይሰነዝራል። እነኝህ ጥያቄዎች ደግሞ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚያነሷቸው እና የሚሞግቱባቸው መሰረታዊ የሃሳብ አመክንዮ (logic) ነፀብራቅ ናቸው።
ከላይ ባጭሩ የጀዋራውያን የትግል ስልት ቀደም ብሎ በእራሱ ውስጥ ባለው ሁለት የአመለካከት ጫፎች የተወጠረ መሆኑን ተመልክተናል።ከላይ በተጠቀሱት ሁለቱም አስተሳሰቦች ለጊዜው በጀዋራውያን ጥቅል ስም ውስጥ ይግቡ እንጂ የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ እና እንቅስቃሴ ከፅንፈኛ እስልምና እንቅስቃሴ የእራሱ የሆነ አመራር የሚወጣበት እና ለኢትዮጵያ ማገር የሆነው የኦሮሞ ማኅበረሰብ የለውጥ ሐዋርያ የሚሆንበት መንገድ መፈለግ የኢትዮጵያውያን በተለይ ኦርሞኛ ከሚናገረው ኢትዮጵያው ማኅበረሰብ ወደ አደባባይ መውጣት እና ስለ ኢትዮጵያዊነት እና የኦሮሞ ማህበረሰብ እንደ ሌላው ወገኑ የእኩል መጠቀም እና መብት ጥያቄ መጠየቅ ሲችል ነው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ቀደም ባሉት አመታት የደረሰባቸው መከራ አልበቃ ብሎ አሁን በአዲስ መልክ ሌላ የእልቂት እና የስደት ምዕራፍ ላይ መሆናቸው ይታወቃል። በቅርቡ በኦሮምያ የተነሳው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መብታቸውን በጠየቁ ወጣቶች ላይ የህወሓት አጋዚ ሰራዊት ከ400 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች እና ታዳጊ ወጣቶችን መግደሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የልብ ድማት ነው።በእዚህ እንቅስቃሴ ላይ በተለይ በቤታቸው የእናት አባቶቻቸው የስቃይ ድምፅ ያንገፈገፋቸው ታዳጊ ወጣቶች ያደረጉት እንቅስቃሴ ቀላል የሚባል አይደለም።በእዚህ እንቅስቃሴ ላይ ጀዋራውያን ከበሰሉት ወጣቶች ይልቅ በ15 እና ከእዛ በታች የሆናቸው የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታዳጊ ወጣቶችን ከታንክ እና ወታደራዊ ጅፖች ፊት ባዶ እጃቸውን እንዲሰለፉ በመገፋፋት ያደረጉት ግፊት እና በምላሹ ሕወሃታውያን በጭካኔ የወሰዱት እርምጃ ለኢትዮጵያ ወጣት ሌላ አሳዛኝ የመከራ ገፈትን እንዲቀምስ አድርጎታል።ከግድያ የተረፉት በግብፅ እና ሱማልያ በረሃ እንዲሁም በሜዴትራንያን ባህር ለሞት መዳረጋቸው ይታወቃል።
ይህ ብቻ አይደለም የኢትዮጵያን ወጣቶች መከራ በጀዋራውያንም ሆነ በሕወሃታውያን የማያባራ ፈተና ውስጥ መሄዱ ቀጥሏል።ከግድያው፣እስራቱ እና ስደቱ ተርፎ ሌት ተቀን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ ለከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና ከዛሬ ግንቦት 22 እስከ ግንቦት 26/2008 ዓም ለመውሰድ ይዘጋጁ የነበሩ ከ200 ሺህ በላይ ወጣቶች በመላው አገሪቱ 800 በሚሆኑ የፈተና ጣቢያዎች ውስጥ ፈተና እንደጀመሩ ፈተናው ተሰርቆ በመውጣቱ ሳቢያ ፈተናው መሰረዙ ተነግሯቸዋል።ድርጊቱ ትውልዱን በእጅጉ የሚጎዳ ነው።
በእርግጥ ከእዚህ ጋር ተያይዞ የተነሱ ጥያቄዎችበማህበራዊ ሚድያ መንፀባረቁ ይታወቃል።ይሄውም አንዳንድ የጀዋራውያን ማህበራዊ ሚድያዎች ፈተናው መዘግየት አለበት ለፈተና ያልተዘጋጁ ተማሪዎች በተለይ በኦሮምያ ክልል ለአምስት ወራት አልተማሩምና የሚል ሃሳቦች ተንሸራሽረዋል። ይህ በግልጥ (ኦፊሻል በሆነ መንገድ) ከመግለጥ ይልቅ አሁንም በማህበራዊ ሚድያ በድርጅት መልክ ሳይሆን በግለሰቦች ደረጃ ተሰምቷል።ቀደም ብዬ የጠቀስኩት የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ትግል ኢትዮጵያዊ መልክ እና የታወቀ አመራር እንዳይኖር የመደረጉ ሁኔታ በእራሱ የእዚህ አይነት እንቅስቃሴዎች በማህበራዊ ሚድያ የተገኙ ከማለት የዘለለ ቅርፅ እና አካል ያለው አደረጃጀት ተከትሎ የሚሰጥ መግለጫ ስለሌለ አሁንም 'ጀዋራውያን' ከማለት ያለፈ ማብራራት አይቻልም።
ፈተናውን አውጥተን መልሶቹን በትነናል ያሉት የጀዋራውያን ማህበራዊ ሚድያዎችም ሆኑ በኦሮምያ ክልል ላለፉት አምስት ወራት የተረጋጋ የፈተና ሁኔታ አለመኖሩን ከግንዛቤ አስገብቶ ምንም አይነት መፍትሄ ያልሰጡት የህወሃታውያን ክፍል፣ ሁለቱም የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣትን ሕይወት ላይ በመረማመድ የተሳሳተ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚጥሩ ናቸው። በዛሬው እለት ጀዋራውያን በማህበራዊ ድረ-ገፅ 'ድል' ማድረጋቸውን የሚገልጥ ፅሁፍ ሲለቁ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስልቱ በእራሱ ከባህር ማዶ ተቀምጦ በአገር ቤት ባሉት የእዚህ ትውልድ ፍሬዎች ላይ በሕወሃታውያን የሚደርስባቸው መከራ አልበቃ ብሎ ሌላ የበቀል ውጋት ያህል የተሰነዘረ አድርገው ቆጥረውታል።
ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያውነቷን ከማያውቃት ፅንፈኛው የጀዋራውያን አካል በአገር ቤት ባሉ በወጣቶች እንግልት ፖለቲካዊ ትርፍ ለማግኘት ከሚሞክር አካልም ሆነ ኢትዮጵያን ላለፉት 25 አመታት በጎጥ ፖለቲካ የከፋፈላት የህወሃታውያን አስተሳሰብ እና ድርጊት የኢትዮጵያን ወጣት የማያባራ መከራ ውስጥ ከትቶል።ኢትዮጵያውያን ለሁሉም ኢትዮጵያ የጋራ ፖለቲካዊ፣ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ተጠቃሚነት በአንድነት እስካልተነሳን እና ለእዚህም እንደ አገር የሚከፋፍሉንን በሕብረት መግራት ካልቻልን የሚከፈለው ዋጋ ከባድ ያደርገዋል።ለእዚህም የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ትግል ካለመሪ እንዳይቀር እና ከፅንፈኛ እስልምና አራማጅ ጀዋራውያን እጅ ወጥቶ ለኦሮሞ ማህበረሰብም ሆነ ለመላው ኢትዮጵያውያን መብት ዘብ በቆሙ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ዜጎች እጅ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው።እዚህ ላይ ፅንፈኛ ጀዋራውያን ጉዳዩን ከኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋር ሌላው ማህበረሰብን ለማጋጨት የተጠቀሙበት ይህ ትውልድ ያልኖረበትን ያለፈ ታሪክ መዘዛም ሆነ ህወሃታውያን የእኩል ተጠቃሚነት እና የመብት ጥያቄ የሚያነሳውን ኢትዮጵያዊ የጥይት እራት የሚያደርጉበት እኩይ ተግባር ሁሉ መገታት የሚችለው አሁንም ኢትዮጵያዊነትን ባከበረ ተቃውሞ እንጂ ኢትዮጵያዊነትን ከመሰረቱ በመካድ እና ሰንደቅ አላማዋን በማጣጣል የባዕዳን ስሜት ያነገበ የፖለቲካ አካሄድ በሙሉ በፍጥነት አደብ እንዲገዛ መደረግ አለበት።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com