ከ2000 ዓመት በኋላ እንደ አዲስ እንመዘገባለን፣ እንደ አዲስም እንታወቃለን
ምንጭ-የዳንኤልዕይታዎችድህረገጽ (http://www.danielkibret.com/2013/04/2000.html)
ሰሞኑን የፌድራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖት ተቋማትን ለመመዝገብ የወጣ ረቂቅ መመሪያ› የሚል ወረቀት አስተያየት ይሰጥበት ዘንድ ለእምነት ተቋማት አሠራጭቷል፡፡ ይህ መመርያ የያዛቸውን ጉዳዮች እያንዳንዳቸውን እየነጠሉ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ወደፊት የምናደርገው ይሆናል፡፡ ለአሁኑ ግን መመሪያውን ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነባራዊ፣ ሉዓላዊና መንፈሳዊ ጠባያት ጋር በማዛመድ ብቻ እንመለከተዋለን፡፡
1. መመሪያው የቤተ ክርስቲያኒቱን ልዩ ሁኔታ ከግምት ያላስገባ ነው
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት 2000 ዓመታት በምድሪቱ ላይ የኖረች፣ የሰበከች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ክፉውንም ሆነ ደጉንም እኩል የቀመሰች፣ እንዲያውም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመሆንዋ ብቻ ልዩ ጉዳት የደረሰባትም ናት፡፡ በጣልያን ወረራ ጊዜ የተሠውትን ጳጳሳትና መነኮሳት ማሰቡ ብቻ ለዚህ የቅርብ ምሳሌ ነው፡፡ ይህቺ ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ሂደት ውስጥ በሀገሪቱ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሕይወት ውስጥ ልዩ የሆነና የማይተካ ሚና ተጫውታለች፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመሥርታ ሀገሪቱንም መሥርታለች፡፡
ይህንን ሁሉ ዘንግቶ በ2005 ዓም ላይ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ አዲስ ተመዝገቢ፣ እንደ አዲስ ፈቃድ አውጭ፣ እንደ አዲስ ደንብና መመሪያሽን አምጭ ማለት እጅግ አሳዛኝም አስገራሚም ነገር ነው፡፡ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ራሱ ከፈለገ መረጃ ሰብስቦ መመዝገብና ማወቅ ነበረበት እንጂ ሰነድ አምጭ፣ ደንብ አስገቢ፣ ፈቃድ አውጭና ልወቅሽ ማለት አልነበረበትም፡፡
ሀ/ የሚኒስቴሩ አንድን የሃይማኖት ወይም የእምነት ተቋም የሚመዘግበው የመመሥረቻ ጽሑፍ፣ መተዳደርያ ደንብና የመሥራቾቹ ቃለ ጉባኤ ሲቀርብለት ነው (ዐንቀጽ 7 ቁ.1) ይላል፡፡ አሁን ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የትኛውን ደንብ ነው የምናቀርበው? ዲድስቅልያ፣ ሲኖዶስ፣ ግጽው፣ አብጥሊስ፣ ፍትሐ ነገሥት፣ ሕገ መነኮሳት፣ ሥርዓተ ሕግ ወቀኖና፣ የኒቂያ ቀኖና፣ የቁስጥንጥንያ ቀኖና፣ የኤፌሶን ቀኖና፣ የሎዶቅያ ቀኖና፣ የቅርጣግና፣ ስንቱን? የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱስ የትኞቹን ሊቃውንት ሰብስቦ ነው ይህንን ሁሉ ሕግ አጥንቶ ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይጋጫል ወይስ አይጋጭም ብሎ አስተያየት የሚሰጠው፡፡
በሌላም በኩል የመሥራቾች ቃለ ጉባኤ መቅረብ አለበት ይላል፡፡ እኛ የነማንን ቃለ ጉባኤ ነው የምናቀርበው? የሐዋርያትን ነው ወይስ የሠለስቱ ምዕትን? የኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ነው ወይስ የአብርሃ አጽብሐን፣ የተሰዓቱ ቅዱሳንን ነው ወይስ የአቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንን?
ለ/ ቅርንጫፍ መክፈትን በተመለከተው በዐንቀጽ 14 ላይ ስለተከፈቱት ቅርንጫፎች አድራሻና አመራሮች በ30 ቀናት ውስጥ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ማሳወቅ ይገባል ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የ35ሺ አጥቢያዎቿን የሰበካ ጉባኤያት፣ የ110 ገዳማቷን አበምኔቶችና ምርፋቆች፣ ከስድሳ የሚበልጡትን አህጉረ ስብከቶችን ሥራ አስኪያጆች የመመሪያ ኃላፊዎች ሁሉ ታስመዘግባለች ማለት ነው?
ሐ/ በዐንቀጽ 23 ላይ ማንኛውም የእምነት ተቋም የተመረጡ መሪዎችና የሥራ ኃላፊዎችን ከዓመታዊ ሪፖርቱ ጋር ማቅረብ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ለመሆኑ ከቤተ ክርስቲያን አንፃር ‹የሥራ ኃላፊ› የሚለው ምን ማለት ነው? ክህነታዊ ኃላፊነትን ነው ወይስ አስተዳደራዊ ኃላፊነትን? ታድያ ጳጳስ ስትሾም፣ ካህን ስትሾም ቆሞስ ስትሾም፣ ዲያቆን ስትሾም፣ ንፍቅ ዲያቆን ስትሾም፣ አናጉንስጢስና አንባቢ ስትሾም ማሳወቅ ሊኖርባት ነው ማለት ነው? ለመሆኑስ በእነዚህ ላይ መወሰን ያለበት የፌድራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ነው ወይስ መንፈስ ቅዱስ? ለመሆኑ ዝርዝሩን ከተቀበለ በኋላ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባይስማማ ጳጳሱ ከጵጵስናው፣ ካህኑ ከክህነቱ ይሻራል ማለት ነው?
ደግሞስ ቤተ ክርስቲያን ከላይ የጠቀስናቸውን የሥራ ኃላፊዎች ዝርዝር በየዓመቱ የምታስገባ ከሆነ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መዝገብ ቤት በምን ያህል እንዲሰፋ ሊደረግ ነው? ያውም ስማቸውን ፣ ዕድሜያቸውን፣ የመኖርያ አድራሻቸውን፣ የስልክ ቁጥርና የኃላፊነት ድርሻቸውን ሁሉ ማካተት ያስፈልጋል ይላል፡፡ ስለዚህ በየገዳማቱ የሚገኙ አባቶች አበምኔት ለመሆን፣ መጋቢ ለመሆን ወይም ጓል መጋቢ ለመሆን የመኖርያ አድራሻና ቢመንኑም የስልክ ቁጥር ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው፡፡
መ/ በዐንቀጽ 27 ላይ እንደ አስፈላጊነቱ የምዝገባና የተሰጠውን ሕጋዊ ሰውነት ፈቃድ ሊያግድ ወይም ሊሠርዝ ይችላል ይላል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ያ የእምነት ተቋም አገልግሎቱን መስጠት አይችልም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አንድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያ ሰነድ አሟልቶ፣ ጊዜ ጠብቆ ፈቃዱን ሳያድስ ቢቀር ቅዳሴ ይቆማል፣ ሰዓታት ይታገዳል፣ ጾም ይቋረጣል፣ ክርስትና ይቀራል፣ ተክሊል አይኖርም፣ ፍትሐት አይደረግም፣ ገዳማት ይዘጋሉ፣ አጥቢያዎች ይታጎላሉ ማለት ነው? በዮዲትና በግራኝ፣ በጣልያንና በደርቡሽ የመከራ ዘመን ያልተቋረጠው፣ እግዜር የለም ባለው የደርግ ዘመን እንኳን ያልቆመ ውዳሴና ቅዳሴ፣ ሰዓታትና ማኅሌት፣ ፍትሐትና፣ ክርስትና በአንድ ሰርተፊኬት እጥረት ይታገዳል ማለት ነው? ታድያ ይሀ የእምነት ነጻነት ነው ተብሎ ሊነገርለት ይችላል?
2. መመሪያው የጋኑን በምንቸት ለመክተት የሚሞክር ነው
የቅርብ ዘመናት የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤቶት ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል 97% የሚሆነው ‹ሃይማኖተኛ› መሆኑን ገልጠውልናል፡፡ ሃይማኖት በሀገሪቱ ውስጥ ወሳኝ ሚና ካላቸው ነገሮች ዋነኛው ነው፡፡ የሕዝቡን ኑሮ፣ ጤና፣ አመለካከት፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ከሚወስኑት ጉዳዮች ዋነኛውም ሃይማኖት ነው፡፡ ይህ ሁሉ እየታወቀ ሃይማኖትን ያህል ነገር የሚወስንን ነገር በአንድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መመርያ ማውጣት እንዴት ተቻለ? በተለይም ይህ መመሪያ ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ አንጻር የቤተ ክርስቲያኒቱን ሉዓላዊነት የሚሽርና የቤተ ክርስቲያኒቱን ዓለም ዐቀፋዊ ጠባይ የሚገዳደር ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ አንድ ማኅበር፣ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ወይም ድርጅት እንድትመዘገብ፣ ፈቃድ እንድታወጣና ፈቃድ እንድታድስ፣ ችግር ከገጠመም ፈቃድዋን ተነጥቃ ሕልውናዋን እንድታጣ የሚያዝ መመሪያ እንዴት ነው ቢያንስ የሀገሪቱ ከፍተኛው አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንኳን ሳያየው በመመሪያ ደረጃ ብቻ እንዲወጣ የተፈለገው? የጋኑን በምንቸት ማለትም ይኼ ነው፡፡
- መመሪያው በአዲሱ ዘመን ንቅናቄ መንፈስ የወጣ ይመስላል
መመሪያው ሲወጣ የፍልስፍና መሠረቱ የአዲሱ ዘመን ንቅናቄ (The New Age Movement) የሚባሉትን የፕሮቴስታንት ክፍልፋዮች መሠረተ ሃሳብ መነሻ ያደረገ መሆኑን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ፡፡ ሃይማኖትን ለመመሥረት አነስተኛ ቁጥር ማስቀመጥ፣ ሃይማኖትን መመዘግብና እንደ ማንኛውም ድርጅት ፈቃድ መስጠትና መንጠቅ የመሳሰሉ ሃሳቦች ከእነዚህ አዲሱ ዘመን ንቅናቄ ፕሮቴስታንቶች ሃሳቦች የተወሰዱ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ እንደ አድቬንቲስት፣ ሜኖናይት፣ ሜቶዲስት የመሳሰሉ ጥንታውያንና ባለ መሥመር ፕሮቴስታንቶች (main line protestants) ይህንን ሃሳብ አይቀበሉትም፡፡ የእነዚህ ክፍልፋይ ፕሮቴስታንቶች ዋናው መርሕ ደግሞ ሊበራልነት ነው፡፡ እጅግ የሚገርመው ነገር ኢሕአዴግ ደጋግሞ የሚወቅሰው የሊበራል አስተሳሰብ እንዴት በፌድራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በኩል የሃይማኖት ተቋማት የምዝገባ መመሪያ ሆኖ ሊመጣ እንደቻለ ነው፡፡
መመሪያው እምነትን በተመለከተ ሊበራል የሆነውን ሃሳብ የሚከተሉትን የምዕራብ ሀገሮች ልምድ እንጂ ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙባቸውንና በዚህ ረገድም ነባርና ጥብቅ ሕግ ያላቸውን የምሥራቅ ሀገሮችን ልም ያካተተ አይመስልም፡፡ እንደ ግሪክ፣ ጣልያንና አርመን፣ ሩሲያና ሌሎች ሀገሮች ልምዶች በመመሪያው ውስጥ አይታይም፡፡
መመሪያው በአዲሱ ዘመን ንቅናቄ ፕሮቴስታንቶች መንፈስ የተዘጋጀ ነው የሚያስብለው ሌላው ነገር የተጠቀመባቸው ቃላት ናቸው፡፡ ሚኒስትሪና ፌሎውሺፕ፣ ቅርንጫፍ፣ የሚሉትን ቃላት ሲጠቀም፣ አጥቢያ፣ ሀገረ ስብከትና ገዳም የሚሉትን ቃላት ግን ለመጠቀም አልፈለገም፡፡
በአጠቃላይ መመሪያው እጅግ ከባድን፣ ታላቁንና ውስብስቡን የሀገሪቱን የሃይማኖት ጉይ አቅልሎ የተመለከተ፣ ከልኩ በላይ የሰፋውን ነገር፣ ከልኩ በታች ያጠበበ፣ የሀገሪቱን ነባር ባህልና ጠባይ ከግምት ያላስገባ፣ ኢትዮጵያን ዛሬ የተመሠረተች አድርጎ የሚቆጥር፣ ከሚያመጣው መፍትሔም የሚፈጥረው ችግር የሚበዛ ነው፡፡ መጀመርያውኑ ከዚህ የሚያንሡ ጉዳዮች በተወካዮች ምክር ቤት እየታዩ የ75 ሚሊዮንን የሃይማኖት ጉዳይ በአንድ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መመሪያ ለመደንገግ መሞከር ስሕተት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃም ሕጉ ነባሮቹን ከአዲስ ተመሥራቾች ያልለየ ነው፡፡
በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን አባቶችም ሆኑ ምእመናን በጥንቃቄ ሊያዩት ሃሳባቸውን በግልጥ ሊሰጡበትና የቤተ ክርስቲያንን ሉዐላዊነት በሚያስከብር መልኩ እንዲሄድ ሊያደርጉት ይገባል፡፡
ምንጭ-የዳንኤልዕይታዎችድህረገጽ (http://www.danielkibret.com/2013/04/2000.html)
ከእዚህ በታች ያለው ከጉዳያችን ጡመራ የተሰጠ አስተያየት ነው
ከእዚህ በታች ያለው ከጉዳያችን ጡመራ የተሰጠ አስተያየት ነው
ይህ ጉዳይ አጅግ አጅግ አደገኛ ችግር ይዞ የሚመጣ ነው።በሌላ አነጋገር ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመክፈል የሚደረግ ጥረት አካል ነው። ከእዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ በ ኢትዮጵያ ሕግ በብሄራዊነት የሚታወቀው ''የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተውህዶ ቤተክርስቲያን'' የሚል ብቻ ነበር።ማንም በእዚህ ስም ቢመጣ ሕጋዊ አይደለም።ይህ ሕግ በመጀመርያ ደረጃ የሚቃረነው የቤተክርስቲያንቱን አንድነት ነው።ከ እዚህ በፊት አንዳንዶች በቤተክርስቲያኒቱ ስም ሌላ ፈቃድ ለማውጣት ሲሞክሩ ጉዳዩ በእንጭጩ የተቀጨው ቤተክርስቲያኒቱ በነበራት ሕጋዊ መሰረትነት ነው።አሁን መንግስት ''እንደ አዲስ መመዝገብ የሚለው'' ሂደት ምን ማለት ነው? ምዝገባ ማለት በትንሹ የሚከተሉትን ማለት ነው።
1/ ቤተክርስቲያንን ለመክፈል የታቀደ ነው።
ማንም በሆነ ''ዶግማ መሰል'' ልዩነት ከቤተክርስቲያኒቱ ተለይቼ ፍቃድ ይሰጠኝ ቢል በትይዩ የተመዘገብችው ቤተክርስቲያን ፍርድ ቤት ልትከሰስ እና ንብረት እንድታካፍል ልታደርግ ትችላለች።ይህ ደግሞ በህንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የታየ ነው።ይህ እንደሚሆን ደግሞ መንግስት አይጠፋውም፣
2/ መንግስት ቤተክርስቲያንቱን አላውቃትም ማለቱ ነው።
አብራችሁ የኖራችሁት ሰው በድንገት ስምህን ንገረኝ፣ማነህ/ማነሽ? ብላችሁ የአእምሮ በሽተኛ ካልሆነ በቀር አላውቅህም/አላውቅሽም ማለቱ ለመሆኑ አያጠራጥርም፣
3/ የሀገሪቱን ታሪክ፣ክብር፣ማንነት እና 'የት መጣሽነት' በሙሉ ሰርዞ አዲስ ታሪክ ለመፃፍ የተጀመረ ፕሮጀክት አፈፃፀም
አካል ነው።
በመሆኑም ይህ ጉዳይ ከእዚህ በፊት በተበጣጠሰ መልክ ሲነገሩ፣አንዳንዶች እንደ ቀድሞው የህወሓት መስራች አቶ ገብረመድህን አይነቶች ደግሞ ከፅሁፍ ማስረጃ ጋር የወያኔ እቅድ በኢትዮጵያ ቤተርክስቲያን ላይ ያስነበቡንን ትክክለኛነት የሚያመላክት ማስረጃ ነው። በመጨረሻም በግንባር ቀድምትነት ከትግራይ አክሱም እስከ ሞያሌ ከሐረር እስከ ኢልባቦር በውጭ የሚኖረው የቤተክርስቲያኒቱ አማኝም ሆነ ያልሆነ በአንክሮ ተመልክቶ ሊቃወመው የሚገባ ለወደፊቱም ዘለቂታዊ ስራዎችን ማሰብ የግድ የሚል መሆኑን አመላካች ጉዳይ ነው።
ጌታቸው
ኦስሎ