ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, April 18, 2013

'' እስረኛ እንኳን እየበላ ነው የሚቀጣው'' የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተመለከተ ዕይታ

በቀል ሃይማኖታዊ መሰረት የለውም

  •  '' እስረኛ እንኳን እየበላ ነው የሚቀጣው ......ፈርኦንም ሕዝቡን በምግብ አልቀጣም ......ለመለመን ከኮሌጁ ግቢ ውጭ ስለተከለከልን ከውስጥ ሆነን በአጥር ስር ነው የምንለምነው '' የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች 

  • ''ምግብማ እግዚአብሔርስ እስራኤላውያንን መቼ በምግብ ቀጣ እየመገበ ነው.....'' አቡነ ህዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ

  • ''ጉዳዩ እርስዎን ይመለከታል ተብዬ ነው ወደ እርስዎ የደወልኩት'' የኢሳት ራድዮ ጋዜጠኛ መሳይ ለአባ ሰረቀ በአማርኛ ላቀረበላቸው ጥያቄ
  • ''አይ ውል ፋይንድ አውት'' አባ ሰረቀ በአማርኛ ላቀረበላቸው ጥያቄ በእንግሊዝኛ ሲመልሱ 

የ ቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች የአስተዳደር እና የመምህራን ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባነሱት ጥያቄ ኮሌጁ በማን እንደተዘጋ አልታወቀም።ይህ ማለት በኮሌጁ አስተዳደር አይደለም ለማለት ባይቻልም ተማሪዎቹ ለቀው እንዲወጡ የተደረገበት ማስታወቂያ ፊርማ እና ስም የሌለው ግን የኮሌጁ ማህተም ብቻ ያለበት መሆኑ ተነግሯል። በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በብዙ ሌሎች ተቋማት ውስጥ እርምጃዎች ሲወሰዱ የሚመለከተው አስተዳደር ሽባ ሆኖ የማይታዩ እጆች ግን ሲያሽከረክሩት ማየት የተለመደ ነው። በቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅም የሚስተዋለው ይሄው ነው።አቡነ ህዝቅኤል የቅዱስ ሲኖዶስ ፀሐፊ ስለጉዳዩ ሲጠየቁ የማያውቁ ሆነው መቅረባቸው ከሁሉም ደግሞ 
''ጉዳዩን የሚመለከተው ቦርዱ ነው ቦርዱ ስብሰባም ላይ ትናንት ተገኝቻለሁ'' ብለው ''ውሳኔውን ግን አልነገሩኝም '' ማለት  አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን ቤተክህነቱን ከሚመለከታቸው በላይ አለቆች እንዳሉባት የሚያመላክት ነው።

የኮሌጁ የኃላ ታሪክ

በ 1942 ዓም እኤአ በ ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ የተመሰረተው የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በታህሳስ 1961 ዓም እኤአ በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ስር ሆኖ አገልግሎቱን እንዲሰጥ ተደረገ።ሆኖም ግን የንጉሡ ዘመን በደርግ ስርዓት ሲተካ ኮሌጁ የመዘጋት ዕድል ገጠመው። ይሄውም በ 1970 ዓም እንደሀገራችን ዘመን አቆጣጠር ኮሌጁ ሲዘጋ በወቅቱ የነበሩት ተማሪዎች ወደ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እንዲዛወሩ እና የኮሌጁ ህንፃ ለአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ሳይንስ ፋክልቲ እንዲሰጥ ተደረገ። የደርግ መንግስት ወድቆ ኢህአዲግ ስልጣን እንደያዘ አቡነ ጳውሎስ መንበረ ጵጵስናውን ያዙ።አቡነ ጳውሎስ ካደረጉት ነገር አንዱ የኮሌጁ እንደገና የማስከፈት ሂደትን ''ኮሌጁ ለቤተክርስቲያኒቱ ይመለስ'' የሚል የድጋፍ መጠየቅያ  ፊርማ  አሰባስቦ መንግስት ኮሌጁን እንዲመልስ መጠየቅ እና ማስመለስ ነበር።

ኮሌጁ ከተመለሰ ወዲህ በቀን እና በማታ መርሃግብር በዲግሪ እና በዲፕሎማ ደረጃ ብዙ ተማሪዎችን አስመርቆ አውጥቷል። ስለቤተክርስቲያን አስተምሮ የጠለቀ እውቀት ያላቸው በኮሌጁ የትምህርት ሂደትም ሆነ ይዘት 'ኦርቶዶክሳዊ እና ኢትዮጵያዊ ይዘት ይኑረው' የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ቆይቷል።ለእዚህም መነሻ የሚያደርጉት ከኮሌጁ የተመረቁ ጥቂት ምሩቃን ከቤተክርስቲያን አስተምሮ ውጭ  የሚስያስተምሩበትን ሁኔታ እና ቀድመው በቤተክርስቲያኒቱ መሰረተ እምነት የማያምኑ ከኮሌጁ ለመመረቅ እና የቤተክርስቲያንን መድረክ ለማግኘት የገቡበትን ሂደት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።ይህንን ችግር ለመፍታት ቤተክርስቲያን ባብዛኛው በእርሷ የውስጥ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በመክረሟ እና ሊቃውንቷም ቢናገሩም የመደመጥ ዕድል ስላላገኙ ጉዳዩ በአንዳንድ ማህበራት የማሳሰቢያ መልክት ማለፍ አልቻለም።

አፍሪካን ባዳረስን ነበር

አሁን የተነሳውን በተማሪዎች እና በኮሌጁ መሃከል ያለውን አለመግባባት ምክንያት እንግዲህ ከላይ ስለኮለጁ የኃላ ታሪክን ከግንዛቤ ማስገባት ቢገባም የቤተክርስቲያን አስተዳደር የመታገት ቀጣይ ሂደት ግን ማሳያ መንገድ ከመሆን አያልፍም።ኢትዮጵያ ብዙ የመስርያ እና ወደላቀ ደረጃ የመድረሻዋን መንገድ የሚዘጉባት የታሪክ አጋጣሚዎች ታይተዋል። ለምሳሌ የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በጥራት አገልግሎቱን መስጠት ቢችል ዛሬ ቢያንስ በ አስር የአፍሪካ ከተሞች ቅርንጫፍ ኮሌጆችን ወይንም ከእዝያ በላይ በተለያዩ የአፍሪካ ዩንቨርስቲዎች ውስጥ በትብብር ስልጠና የመስጠት ደረጃ በደረስን ነበር። እዚህ ላይ የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያንን መጥቀስ ተገቢ ነው። የግብፅ ቤተክርስቲያን አማኞች በቁጥር ጥቂት ሆነው እና በእስላም አክራሪዎች ብዙ በደል ቢደርስባቸውም የሀገራቸውን ምጣኔ ሀብት ጉልህ ተሳታፊ ከመሆን አልፈው ገዳማት እና ኮለጆቻቸውን በባህር ማዶ መስረተዋል።


ወደ እኛ ጉዳይ ስንመጣ ግን ከተመሰረተ ከ ስልሳ አመት በላይ የሆነው ኮሌጅ ዛሬ ተማሪዎቹ አባሮ ለማኝ እያደረገ ነው። የችግሮቹን ምንጮች ስንመለከት ግን ከሁለት በኩል ይመነጫሉ።አንዱ ከእራሷ ከቤተክርስትያን አስተዳደራዊ ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ከመንግስታቶቻችን(ከደርግ እና ከኢህአዲግ)ይመነጫሉ። ጉዳዩን ግልፅ ለማድረግ ኮሌጁ ከእድገቱ የተገታበት አንዱ ምክንያት ለ 17 አመታት በደርግ መንግስት መዘጋቱ ሲሆን ከተከፈተ በኃላም በአግባቡ እና በስርአት ለማስተዳደር እና ኦርቶዶክሳዊ እና ኢትዮጵያዊ ቃናውን ሳይለቅ ብቁ መንፈሳዊ እና በዘመናዊ ትምህርት የበሰለ ምሩቅ ለማውጣት ሁለት ችግሮች ተጋርጠውበት ቆይተዋል።አንዱ በሀገሪቱ የመናገርም ሆነ ሃሳብን የመግለፅ መብት መታፈንን እንደ መልካም አጋጣሚ የወሰዱ የቤተክህነት ''የመንግስት እንባ ጠባቂ ነን'' ባዮች ችግሩን ስያድበሰብሱት ከመክረማቸውም በላይ ከኮሌጁ የሚወጡ አንዳንድ ምሩቃንን የሃይማኖት አስተምሮ መሰረታዊ ችግር እንዳለባቸው እያወቁ የእነርሱን ስሜት እስከተጋሩ ድረስ በፀጋ መቀበላቸው ሲሆን በሌላ በኩል በቤተክህነት የሰፈነው ሙስና በአንድ ላይ የቤተክርስቲያንቱን ልዩ ልዩ አካላት ሲያዳክሙ ኮለጁንም አብረው መደቆሳቸው የሚለው ተጠቃሽ ነው። በተለይ  የቤተክህነት ''የመንግስት እንባ ጠባቂ ነን'' ባዮች የቤተክርስትያንቱን ሊቃውንት ከመግፋት አልፈው በሀገርውስጥ ምንም የመናገር መብት እንዳይኖራቸው መድረክ በመከልከል እና ገፋ ስል ደግሞ በተለያየ የፖለቲካ ስም በመለጠፍ ከሀገር እንዲሰደዱ ያደርጉት ድርጊት ለኮለጁ መጠናከር አይነተኛ አስተዋፅኦ ያደርጉ የነበሩ ሊቃውንትን አሳጥቷል።

ለመብት ከመነሳት ያለፈ ምን ምላሽ ይኖረዋል?

ለማጠቃለል የቅድስት ስላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ችግር ከላይ የተነሱት የኮሌጁ የገጠሙት ሃይማኖታዊ የትምህርት ስርዓት የማስፈን እና የመቅረፅ ችግር እንዳለ ሆኖ አጠቃላይ ችግሩ ግን ሀገራችን ያለችበት የአፈና ስርዓት ውጤት ነው።አፈና ባይኖር ዜጎች የተሰማቸውን የመናገር፣ ሃሳባቸውን የመግለፅ እና ችግራቸውን ካለፍርሃት በአንድ አዳራሽ ተሰብስበው እውነቱን በመነጋገር በተፈታ ነበር። የቤተክህነት የመንግስት እንባ ጠባቂ ነን ባዮችም እንዲህ እነሱ የወሰዱት እርምጃ ሁሉ ከመንግስት አንፃር ሁሌ ትክክል ነው እየተባለ  የሰሩት ሙስና እና አላግባብ መበልፀግ ቤተክርስቲያንን እየቀበረ ባልሄደ ነበር። በመሆኑም በጥቃቅን ክስተቶች ከማተኮር አጠቃላይ ሃገራዊ ችግራችንን መፍታት የጥቃቅን ችግሮችን የመፍታት ፋይዳውን ማሰብ ጠቃሚ ይመስለኛል።ሕግ ሰዎች በምግብ እንዲቀጡ አያዝም።ይህንን የፈፀሙም ሆነ ያስፈፀሙ ከሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ከሰብአዊነት አንፃርም ወንጀል እንደሆነ ይኖራል።ምግብ ከልካዮቹም ወቃሽ ከሳሽ የሌለባቸው የሆኑት ''ጌታዋን የተማመነች በግ ላቷን ከውጭ ታሳድራለች'' እንዲል የግል የመበቀል ስሜታቸውን እና ፈላጭ ቆራችነታቸውን የማሳያ መንገድ ሲያደርጉ ለመብት ከመነሳት ያለፈ ምን ምላሽ ይኖረዋል?
 
ለግንዛቤ እንዲረዳን የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ከሀገር ቤት አልፈው በውጭ ሃገራት ሁሉ የመንፈሳዊ ኮለጆቻቸውን እየመሰረቱ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል ከድህረ-ገፅ ያገኘሁት በአውስትራሊያ የሚገኘው ፖፕ ሺኖዳ ሶስተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅ የትምህርት አይነቶቹን ዝርዝር ብቻ መጥቀስ ብዙ ነገር የሚያሳይ ነው። 
ይቆየን 
ጌታቸው 
ኦስሎ

Coptic Orthodox Theological College, Sydney Australia
Pope Shenouda III Coptic Orthodox
TheologicalCollege
SYDNEY, AUSTRALIA
 
 Source- http://www.coptictheology.com/diploma.php 

2 comments:

Anonymous said...

mindnew eyehone yalew? betekihnet endet qerbo ayanagirm? yemenafiqan new kalu lemin aynegrunim? yatefu kalus lemin ayqetum? wey hagere?

Anonymous said...

ketinant binzegeym kenege enqedmalen ayzon!!!!!!!!

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...