ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, March 23, 2023

የተወካዮች ምክርቤት (ፓርላማው) አሰራሩ እና ውሳኔ አሰጣጡ የ21ኛውን ክ/ዘመን የሚመጥን፣ ኢትዮጵያ የመጀመርያ ፓርላማዋን ከከፈተች ከ80 ዓመታት በላይ እንደሆናት በሚያሳይ ልክ አይደለም።

አሁን በአራት ኪሎ የሚገኘው የኢትዮጵያ ፓርላማ ህንጻ በ1928 ዓም 

===========
ጉዳያችን
==========

የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክርቤት በድረገጹ ላይ የኢትዮጵያ ፓርላማ ታሪክ በሚለው ርዕሱ ስር እንዲህ የሚል ተጽፏል - 

''የቀዳማዊ  ኃይለሥላሴ  የመጀመሪያው ሕገ መንግስት  ከታወጀበት  ሐምሌ  9  ቀን  1923 ዓ.ም በኋላ ጥቅምት 24 ቀን 1924ዓ.ም የመጀመሪያው ፓርላማ መከፈቱን የታሪክ ድርሳናት ያሰረዳሉ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የፓርላማ ስርዓት በኢትዮዽያ  ሲሰራበት የቆየ  ሲሆን፤መገለጫዎቹ እንደ የመንግስታቱ ባህሪያ   የተለያዩ ናቸው.....በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የፅሁፍ ሕገ-መንግስት የወጣው በቀዳማዊ  ኃይለሥላሴ  ዘመነ መንግስት  በ1923 ዓ.ም  ሲሆን፤ የንጉሠ ነገሥቱ የንግስ በዓል  ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም  ከተከበረ በኋላ፤ ሐምሌ 9 ቀን 1923 ዓ.ም.  ንጉሱ በፊርማቸው ሕገ መንግስቱን  አፅድቀው፤ በፍቃዳቸው ለኢትዮዽያ ህዝብ የሰጡት የመጀመሪያው  ሕገ  መንግስት  በመባል ይታወቃል።

ይህ ሕገ መንግስት  ያስፈለገበት  ምክንያት ኢትዮዽያ ከነበረችበት ጥንታዊና ልማዳዊ አመራር ወጥታ ወደ ዘመናዊ አስተዳደር እንድትሻገር ብሎም ኢትዮዽያ በህገ መንግስት የምትተዳደር ንጉሳዊ አገር ነች ተብላ በዓለም እንድትታወቅ ለማድረግ ነው። ከታላላቅ መሳፍንትና መኳንንት ወገን 11 የኮሚቴ አባላት በንጉሱ ተመርጠው በራስ ካሳ ሊቀመንበርነት በየዕለቱ እየተሰበሰቡ በአምስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ ተመስርተው በሕገ መንግስቱ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ጥናት ካደረጉ በኋላ ፤ የሕገ መንግስቱ ረቂቅ ተዘጋጅቷል'' ይላል።

ኢትዮጵያ ፓርላማዋን አሁን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚገኝበት በአራት ኪሎ ላይ የተከለችው ገና ጣልያን ኢትዮጵያን ሳይወራት ነው። ከላይ የምትመለከቱት የፓርላማው ህንጻ የነበረው ዕይታ ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት በ1928 ዓም የነበረው ነው። ኢትዮጵያ የራሷ ፓርላማ ሲኖራት አፍሪካ ሙሉ በቅኝ ግዛት ውስጥ የሚዳክር ነበር።አፍሪካ ብቻ አይደለም።የደቡብ አሜሪካ እና የመካከለኛው እና ሩቅ ምሥራቅ ሃገሮችም በቅኝ ተገዢዎች ስር ነበሩ። ችግሩ የኢትዮጵያን ክብር፣አባቶቻችን ቀደም ብለው የሰሩት ገና ያልገባን፣ የሃገራችን ታላቅነት ገና ያልገባን ብቻ ሳንሆን የነበረውን አልቀን እና አሻሽለን ለትውልድ ማስተላለፍ የሚገባን ሲሆን ያለውን አጨቅይተን እና አዋርደን የምንኖር ትውልድ መሆናችን ያሳዝናል።

ለእዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ትናንት መጋቢት 13፣2015 ዓም የኢትዮጵያ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማው) የህወሃትን ከሽብርተኝነት ፍረጃ ያነሳበት ሂደት ምን ያህል የፓርላማውን ታላቅ ታሪክ እና በ21ኛው ክ/ዘመን እንደሚገኝ ፓርላማ እራሱን በሚመጥን ደረጃ አለማሳየቱ የሚያሳዝን የሆነበትን ሁኔታ ስመለከት ነው። 

በእዚህ ጽሑፍ ላይ ህወሃት ሽብርተኛ መባሉ እና ውሳኔው መነሳቱ ትክክል ነው አይደለም የሚለው ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባም። ምክንያቱም ህወሃት ሽብርተኛ ድርጅት እንደሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የወሰነው ገና ከስልጣን ሳይወርድ ነው። ህወሃት ሽብርተኛ ለመሆኑ የ27 ዓመት የስልጣን ዘመኑ ሥራ ብቻ ሳይሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ በትግራይ፣በአፋር እና በአማራ ህዝብ ላይ የፈጸመው በዘመናችን ያልታየው ሰውን ብቻ ሳይሆን የቤት እንስሣት እና ዕጽዋት ሳይቀር ለማጥፋት በአውሬነት ስሜት የተንቀሳቀሰ ለመሆኑ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክር ነው። እዚህ ላይ ግን መነሳት ያለበት የኢትዮጵያ ተወካዮች ምክርቤት ህወሃትን ከሽብርተኝነት ሰርዣለሁ ሲል የሄድበት ሂደት ምን ያህል የፓርላማውን ደረጃ የማይመጥን መሆኑን ማሳየት አስፈላጊ ነው። 

ለመሆኑ ፓርላማው ይህንን ህወሃትን ከሽብርተኝነት ሲሰርዝ መሄድ የነበረበት ሦስቱ ሂደቶች ምን ምን ነበሩ?

1/ የምክርቤቱ አባላት በሚገባ ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ቢያንስ ለተወሰኑ ቀናት አልተወያዩም

የተወካዮች ምክርቤት ከህወሃት መውደቅ በኋላ ብዙ መሻሻሎች ያሳያል የሚል የብዙ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ነበር።የምክር ቤቱ አባላት በ27 ዓመታት ውስጥ ከነበሩት በትምህርት ዝግጅትም ሆነ በአመለካከት ስብጥር የተሻለ ለመሆኑ ጥያቄ ውስጥ አይገባም። ነገር ግን አሁንም የሚናገሩት የካድሬ መንፈስ የተላበሱት እንጂ ሌላው ሲሞግት ብዙ አልታየም። የምክር ቤቱ አባላት ሃሳብ አቀራረብ በራሱ ዛሬም እንደ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በተቀመጡበት እጅ አውጥተው አፈጉባዔው በሰጧቸው ደቂቃ ብቻ መሆኑ አሰልቺም ሃሳብንም በደንብ ለማንሸራሸር የሚያመች አይደለም። 

ዛሬም ፓርላማው ድንገት ወይንም በአጭር ጊዜ የሚመጡለት አጀንዳዎችን አክለፍልፎ ማሳለፍ እንጂ ጉዳዩን የሚመረምርበት ጊዜ የለውም። ይህ ህወሃትን ከሽብርተኝነት የመሰረዝ ውሳኔ ለፓርላማው ታሪክም ተጠያቂ ላለመሆንም ሂደቱ ትክክል መሆኑም እርግጠኛ መሆን ነበረበት። ፓርላማው በአንድ ቀን ይህንን ያህል ግዙፍ ጉዳይ በተወሰኑ ሃሳቦች ሰምቶ እጅ አውጥቶ ወሰንኩ ማለቱ በራሱ አስቂኝ ሂደት ነው። የእዚህ ዓይነት ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ሁሉም አባላት ሃሳብ ካላቸው የፈጀውን ቀን ይፍጅ መስማት አለበት። የሁሉንም የመስማት የጊዜ ጥበት ቢኖር ከየክልሉ ቢያንስ የሦስት አባላት ሃሳብ እየወጡ ቆመው የሚናገሩበት መድረክ አዘጋጅቶ ለህዝብ በቀጥታ እየተላለፈ ሃሳባቸውን ማቅረብ አለባቸው። ህዝብም በምን ያህል ሙግት ጉዳዩ እንዳለፈ የማወቅ ሙሉ መብት አለው። ፓርላማዎች በብዙ ዓለማት በአጀንዳው ላይ አባላቱ የተወሰኑ ደቂቃዎች ቆመው ንግግር እንዲያደርጉ እና ሃሳባቸውን የሚያስረዱበት አግባብ ያዘጋጃል። ከ80 ዓመታት በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ፓርላማ ይህንን አሰራር እንዴት በ21ኛው ክ/ዘመን ሆኖም መማር አልቻለም? 

2/ ምክርቤቱ በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው ሃሳባቸውን እንዲሰጡ እና ይህ ሃሳብም ለህዝብ እንዲገለጥ አላደረገም።

አንዳንድ ሃገራዊ ጉዳዮች ቀላል ክርክር የሚፈልጉ ብቻ አይደሉም። መዘዛቸው ለትውልድም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ የሚተርፍ ችግር ይዘው እንዳይመጡ ጥንቃቄ ይፈልጋሉ፣የብዙ ባለሙያዎች ሃሳብ፣የተራው ህዝብም ሃሳብ ሁሉ ያስፈልጋል።ትናንት በህወሃት የሽብር ፍረጃ መነሳት ጉዳይ ላይ ቢያንስ ለሳምንት ያህል በተያዙ መርሃግብሮች ምክርቤቱ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ከፍተኛ መኮንኖች፣ የደህንነት ሚኒስትሩ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣የሕግ ባለሙያዎች፣በጦርነቱ የተጎዱ የክልል ባለስልጣናት እና ከውጭጉዳይ ሚኒስቴር ጭምር የፍረጃው መነሳት አንደምታ፣በሃገሪቱ የጸጥታ እና ደህንነት ላይ ያለው ተጽዕኖ ጭምር እንዲብራራለት መጠየቅ ከእዚህ በኋላ ቀደም ብሎ ጉዳዩን አስመልክቶ በመሰረተው አጥኚ ኮሚቴ (ይህ ኮሚቴ ፓርላማው የለውም) ጋር ተመካክሮ እና ተከራክሮ የጋራ አቋም መያዝ እና ድምጽ መስጠት ነበረበት። 

የእዚህ ዓይነት አካሄድ ለፓርላማ አባላቱ ለሚሰሩት ሥራ ብቻ ሳይሆን ለውሳኔያቸው ምክንያታዊነት እና ለሃገር ጠቃሚነት የሚያረጋግጡበት መንገድ ነው። ትናንት የታየው ግን የካድሬ ንግግር በሚመስል መንገድ ህወሃትን ከሽብር ፍረጃ ማንሳት የትግራይን ህዝብ ሽብርተኛ የተባለ ይመስል የሚናገሩ አንዳንድ ልወደድ ባይ አባላት የተመለከትንበት ነው።የህወሃት ከሽብርተኛ ፍረጃ መነሳት ማለት የትግራይ ህዝብ ቀድሞም ባልተፈረጀበት ፍረጃ ሌላ ስም የተሰጠው አድርጎ ለማቅረብ መሞከር ምክርቤቱ እንዴት ያሉ የካድሬ ሥራ ላይ የተሰማሩ እንዳሉ ማሳያ ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት የእዚህ ምክር ቤት አቅም ያላቸው አባላቱ እንዳይናገሩ የካድሬው ቀደም ቀደም ማለት ብዙ ነገር የሸፈነ ይመስላል።ስለሆነም ፓርላማው አባላቱ በአንድ ሃገራዊ አጀንዳ ላይ ሃሳባቸውን ቆመው በጽሑፍ ወይንም በቃላቸው የሚያቀርቡበት መድረክ ማመቻቸት እና የተመረጡ አባላት ሲከራከሩ እና ሃሳብ ሲንሸራሸር ማየት እንፈልጋለን። በእዚህ ሂደትም ይህንን የሚያዩ ወጣቶችም ሆኑ ታዳጊዎች ስለ ፓርላማ ብዙ እንዲማሩ ቢደረግ የተሻለ ነው።

3/ ምክርቤቱ ሰነድ አልመረመረም

በትናንትናው የፓርላማ ስብሰባ ላይ ምክርቤቱ በአንድቀን የቀረበለትን አጀንዳ ጉዳዩን በደንብ እንደመረመረ ሁሉ እጅ ሲያወጣ ያስገርማል። በህወሃት ከሽብርተኛ መነሳት ጉዳይ ላይ ምክርቤቱ ቀድም ብሎ ጉዳዩን የሚመለከት ኮሚቴ መመስረት፣በእዚህ መሰረት የፕሪቶርያ እና የናይሮቤ የስምምነት ሰነዶች በደንብ ማጥናት እና መተንተን፣በመቀጠል ስለአፈጻጸማቸው ትግራይ ድረስ ልዑክ ልኮ መሬት ላይ ያለውን አፈጻጸም መመልከት ይህ ባይሳካለት የመከላከያ ሚኒስትር ኢታማዦር ሹም ፓርላማ ቀርበው ከፕሪቶርያ ስምምነት አንጻር የቱ ተፈጸመ የቱ አልተፈጸመም፣ለምን የሚሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ እና በቂ ምላሽ ማግኘት ይገባው ነበር።ይህ ሁሉ ግን አልሆነም።ይህ ከሰማንያ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ፓርላማ ላላት ሃገር አሳፋሪ ነው።

ፓርላማው ወደፊት እንዲያሻሽል የምንፈልገው።
  • አባላቱ የሃገሪቱ የመጨረሻ የህዝብ ተወካይ፣ሕግ አውጪ እና አጽዳቂ መሆናቸው ከልብ እንዲሰማቸው እና እንዲታወቃቸው መሆን አለበት። የድርጅታዊ አሰራር እና የሸፍጥ አጀንዳ አቀራረቦችን ግልጽ በሆነ ተቃውሞ እና ''አካፋን አካፋ''በሚል አቀራረብ የመናገር ባሕል ማዳበር አለባቸው።
  • አንዳንድ ሃገራዊ ጉዳዮችን እና አጀንዳዎችን ጉዳዩን ከያዘው የመንግስት መስርያቤት፣ባለስልጣን (ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ) ላይም ቢሆን አጀንዳውን በስልጣናቸው ነጥቀው ወደ ውሳኔ እንዲደርስ የማድረግ፣የመመርመር እና ውሳኔ እንዲሰጥበት የማድረግ ሂደት ሊለምዱ ይገባል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ የአውቶብስ ግዢ ላይ ብዙ ንትርኮች ሲደረጉ ፓርላማው ዝም ብሎ ያይ ነበር።በእዚህ ጊዜ ፓርላማው ኮሚቴ ሰይሞ ጉዳዩ ተመርምሮ እንዲቀርብለት ማስደረግ ይችል ነበር።ይህ ለምሳሌ ቀረበ እንጂ በርካታ ጉዳዮች እንዲሁ ታልፈዋል።
  • ፓርላማው አንዳንድ ወሳኝ ሃገራዊ አጀንዳዎች በደንብ እንዲብላሉ በጉዳዩ ላይ ሃሳብ የሚያቀርቡ ለቀናትም ቢሆን ተዘጋጅተው መጥተው አለኝ ያሉትን ሃሳብ የመናገርያ አትሮኖስ ለአባላት ተዘጋጅቶ መናገር መቻል አለባቸው። እነኝህ ንግግሮች ደግሞ በቀጥታ ለህዝብ የሚደርሱ መሆን አለባቸው።ፓርላማዎች ለህዝብ ክፍት ናቸው።የብዙ ሃገሮች ፓርላማ ውሎ በቀጥታ ስርጭት ነው የሚተላለፉት።ሌላው ቀርቶ የፓርላማዎች ላይኛው ፎቅ ሁል ጊዜ ለማንም ህዝብ መጥቶ የሚባለውን እንዲመለከት ክፍት ይደረጋሉ።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀሩት ሦስት ዓመታት ገና ብዙ ወሳኝ ሃገራዊ አጀንዳዎች ይኖሩታል።የእስካሁኑ አለፈ።ከአሁን በኋላ ግን አቀራረቡም ሆነ የአጅነዳ አመራረጡ እና አባላቱ ቆመው የሚናገሩበት በቂ ደቂቃዎች ማመቻቸት ላይ እንዲሰራ መደረግ አለበት።የእዚህ ዓይነት አሰራርን የማዘመን ፋይዳ ከ80 ዓመታት በላይ የፓርላማ ታሪክ ላላት ኢትዮጵያ የሚያንስባት እንጂ የሚበዛባት አይደለም።በውሸት የካድሬ ወሬ የኖሩ መንግስታት አሳልፈን የእውነት የሆነ በሃሳብ ላይ የሚሞግት ፓርላማ ለማየት የሰማይ ያህል እንዴት ይህ ትውልድ እንዲርቀው ይፈረድበታል? ከምክር ቤቱ አፈጉባዔ ጀምሮ እያንዳንዱ አባል ለፓርላማ አባላት ያለው ክብር እንዲስተካከል ፓርላማውም እራሱን ያሻሽል፣አዳዲስ ሃሳብ እያፈለቀ ህጎችን እና አሰራሮችን ያሻሽል።የፈዘዘ እና በካድሬ ንግግር ብቻ ስልጡን የሆነ ፓርላማ ሃገር እንድታንቀላፋ ያደርጋል።በመጨረሻ እራሱም አንቀላፍቶ ያልፋል።

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ፓርላማ ምን ያህል በንጉሱ ዘመን ከነበረው ሳይቀር የወረደ እንደሆነ ለማየት አንድ በንጉሱ ዘመን በፓርላማ የነበረውን አንድ ጥያቄ እና አባላቱ ምን ያህል ለመረጣቸው ህዝብ እና ለሃገራቸው ንቁ እንደነበሩ የሚያሳይ ጉዳይ አንስቼ ጽሑፌን አበቃለሁ። በንጉሱ ዘመን የፓርላማ አባላቱ ጥያቄ ያነሳሉ። ጉዳዩ በእርዳታ የሚመጣ ገንዘብ ለትምህርት ቤት መስርያ የዋለ ይህንን ያህል ገንዘብ ነው ገንዘቡ ከዓለም ባንክ የተገኘ ነው የሚል ሪፖርት የገንዘብ ሚኒስትሩ ያቀርባሉ። የገንዘቡ መጠን እና በእዚያንጊዜ በእየጠቅላይ ግዛታቸው የተሰራው የትምህርት ቤት ብዛትና ወጪ ከነከናቸው።አባላቱ ከንክኗቸው አልቀሩም።ወደ ንጉሱ ጋር ቀጠሮ አስይዘው ገብተው እንዴት ይህንን ያህል ገንዘብ ወጣ ይለናል የገንዘብ ሚኒስትሩ ስናስበው ይህንን ያህል አይሆንም የሚል ክርክር ይዘው ነው የቀረቡት። ንጉሱም የትምህርት እና የገንዘብ ሚኒስትሩን ጠርተው የፓርላማ አባላቱ እያንዳንዱ የተሰሩትን ትምህርት ቤቶች በእየ ጠቅላይ ግዛቱ እየዞሩ እንዲያዩና የተሰራበትን ዋጋ ደምረው እንዲያመጡ ወጪ እንዲመደብ ያደርጋሉ።በእዚህ መሰረት የፓርላማ አባላቱ በእየጠቅላይ ግዛቱ እየዞሩ እያንዳንዱ ትምሕርትቤት የተሰራበትን ወጪ ደምረው ሲመጡ ወጪው ከተባለው በላይ ሆኖባቸው ወደንጉሱ ጋር ገብተው ጉዳዩን በማስረጃ መረዳታቸውንና የጠመኔና የቦርድ ሌሎች ወጪዎችን ሁሉ ተጨማሪ ወጪ እንደነበሩ ያረጋግጣሉ። ይህንን የሚያውቁ በፊልም ጭምር የተናገሩት ማስረጃ አለ። ዛሬ የእኛ ፓርላማ የት ነው ያለው? እንጠይቅ። በቀጣይ ሦስት ዓመታት የትልቅ ሃገርን ታሪካዊ ፓርላማ ዐውድ ቀሩና አሳዩን። ይህ በራሱ ለኢትዮጵያ ብዙ ነገር ማለት ነው። ውለታ ዋሉላት!
======================//////==========

Tuesday, March 21, 2023

የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማኅበራዊ ሚድያ ብጥስጣሽ መልዕክቶች ከመመዘን በመውጣት ኢትዮጵያን ብንጠቅማት እጅግ የተሻለ ነው።
=========
ጉዳያችን ምጥን
=========

የሃገራችንን የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች መለኪያዎቻችን አጠቃላይ ስዕል ከሚያሳዩ ዕይታዎች ይልቅ፣ በእየዕለቱ የውንብድና ሥራ በሕዝብ ላይ የሚሰሩ ለጊዜው በመንግስት መዋቅር ውስጥ ለመሸሸግ ህገመንግስቱም የክልል አደረጃጀትም የፈቀደላቸው በሚሰሩት ግፍ የኢትዮጵያን የወደፊት የፖለቲካ ሂደት ሙሉ በሙሉ የጨለመ አድርጎ ማሰብ አጠቃላይ ሁኔታውን በሚገባ ካለማየት የሚመጣ ነው። አንድ ምንም ጥያቄ ውስጥ የማይገባው ጉዳይ የሕግ የበላይነት ለማስፈን የራሱ የሆነ ፈተና ገጥሞታል። ይህ ፈተና የአፈጻጸም ብቻ ሳይሆን የታችኛው የክልሎች መዋቅር ከላይ ካለው በሙስና ከተነከሩ ባለስልጣናት ጋር እየተናበበ የራሱን የጎሳ አሰራር ለመዘርጋት በሁሉም መስክ ሲሮጥ ይታያል። ይህ ቡድን በምንም ፍጥነት ቢሮጥ ግን የሕዝብ ተቀባይነት አላገኘም። አሁናዊ ሁኔታዎችም የሚያሳዩን ይህንኑ ነው።ስለሆነም የኢትዮጵያዊነት መንገድ ከምንጊዜውም በላይ የበላይነቱን እየያዘ መሄዱ ያለው የህዝብ ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው ነው።

ትልቁ የሃገራችን የፖለቲካ ተስፋውም ይህ የበታኝ ኃይሎች አካሄድ በሕዝብ ተቀባይነት አለማግኘቱ ነው። የዛሬ አራት ዓመታት የነበሩ እጅግ ያገነገኑ የብሔርተኝነት ስሜቶች ዛሬ በእዛ ደረጃ አይደሉም። ይህ ማለት በሕዝብ ደረጃ ማለቴ ነው እንጂ የጎሰኝነት ፍም እንዳይጠፋ ከሚያርገበግቡት የጎሳ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ቡድኖች አንጻር አይደለም። እነኝህኞቹ አሁንም ይህንኑ የጎሳ ፍም ወደ ምጣኔ ሃብት አደረጃጀት እንዲሰርጽ እሩጫ ላይ ናቸው። ይህ በተለይ በኦሮምያ ክልል በቡድን ደረጃ የነበረው አስተሳሰብ አሁን የክልሉ ምክርቤት እና የክልሉ ቢሮክራሲ ሁሉ እንዲወታተብ የማድረጉ ሂደት እንደቀጠለ ነው። ይህም ግን አሁንም በኦሮምያ ክልልም ህዝብ በክልሉ የጽንፍ አመራር ተማሯል ብቻ ሳይሆን እራሱም በጎሳ ስም እየተዘረፈ በመሆኑ ክልሉ ላወጣው አደረጃጀት ሳይቀር ከጉጂ እስከ ባሌ ያሉ አባገዳዎች ሳይቀሩ ከፍተኛ ተቃውሞ መነሳቱ የሚያሳየን የጎሳ እና የጽንፍ አቀንቃኞች የሚሂዱበት መንገድ ሌላውን ሲሰድቡ በቀጣይነት የራሳቸውን ቆምንለት ያሉትን ህዝብ ለመብላት ሲነሱ እራሱ ህዝብ እንደሚበላቸው ማሳያ ነው። ይህንን በህወሃት መመልከት ይቻላል። ህወሃት ቆምኩለት ያለውን ህዝብ አደህይቶ በዛሬው ዕለት ሳይቀር የህወሃት ታጣቂ የነበሩ በመቀሌ ጎዳና ሰልፍ የወጡት በራሱ በህወሃት ላይ ነበር። ህወሃትም አስለቃሽ ጭስ የረጨው በእነኝሁ የእርሱን ስልጣን ለመጠበቅ አካለ ስንኩል በሆኑት ላይ ነበር።

የእዚህ ምጥን መልዕክት ማጠቃለያ ዋናው ሃሳብ የጎሳ አደረጃጀቶች ምን ያህል የግፍ ዓይነት የእኔ አይድለም በሚሉት ላይ ቢያሳዩም ይህ የጥንካሪያቸው መለኪያ አይደለም። ይህ የበለጠ ከራሳቸው ጎሳ ጋርም የሚያጣላ ብቻ ሳይሆን የሚዘርፉትን ዝርፍያ መሸፈኛ ካባ የሌላውን ጎሳ በማጥቃት እና ጠላት በመፍጠር ምን ያህል ለመሸፈን ቢሞክሩ መጨረሻ እኝሁ ወንጀለኞች የሚበሉት በራሳቸው ቆመንልሃል ባሉት ህዝብ የውሸት መደለያቸው ተንጠፍጥፎ ሲያልቅ ነው።ይህንን በትግራይም በኦሮምያም እያየነው ነው። በኦሮምያ ክልል ከጀዋር እና የጨፌ ስግስግ አክራሪዎች ይልቅ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የመደመር ሃሳብ በከፍተኛ ደረጃ በክልሉ ወጣቶች ዘንድ መነጋገርያ እና የተሻለ እንደሆነ በአማራጭነት እየተወሰደ ነው። ይህ እነጀዋር ዱላ ይዞ የሰው አናት እንዲመታ ሲመክሩት የነበረውን ወጣት በኢትዮጵያዊ ሃሳብ እያስተማረ ተንኮላቸውን ስላመከነባቸው ብሽቀታቸው ልክ አጥቷል። ሰሞኑን ከእነጀዋር ቡድን የተሰማው የጽሁፍ ጋጋታም አንዱ ምክንያት ይሄው ነው። በእዚህ ጊዜ የኢትዮጵያውያን የእኩልነት እና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲመጣ የሚናፍቁ ሁሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች እንድንፈስ በሚፈልጉት ቦይ ላለመፍሰስ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማኅበራዊ ሚድያ ብጥስጣሽ መልዕክቶች ከመመዘን መውጣት፣ስንጥቅ ልዩነቶችን ከሚያሰፉት ውስጥ ሳንሆን ስንጥቆችን ከሚደፍኑት መሆን ነው መፍትሄው።ተስፋ የሚያስቆርጡ ጉዳዮችን ስናጎላ ብንውል የአሁኑን ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድ እናመክናለን። ስለሆነም ሁኔታዎች በትክክል መመዘን እና የኢትዮጵያን አንድነት ለመፈታተን የሚሰሩ ስራዎችን ስልታዊ በሆኑ ሁሉን ባቀፈ እና ያሉትንም መልካም ጅምሮች በማበረታታት ወደፊት በመሄድ ሃገር ይሰራል፣ የኢትዮጵያ ጠላት መርዝ ይመክናል። ክፉውን ብቻ እያየን ዘለቄታዊ መልካም ሥራዎችን የምንሸፍን እንዳንሆን እና ካበላሸን በኋላ እንዳለፈው ትውልድ የምንቆጭ እንዳንሆን ዛሬን በሚገባ መመርመር፣በተስፋ እና በመፍትሄ አመንጪነት ስንጥቆችን የምንደፍን እና ትውልዱ መልካም ሥራ የሚሰራበትን ጊዜ በማኅበራዊ ሚድያ ክፉ ወሬዎች በማስጮህ ወደ የበለጠ ችግር እንዳይሄድ መንቃት ያስፈልጋል።የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በማኅበራዊ ሚድያ ብጥስጣሽ መልዕክቶች ከመመዘን በመውጣት ኢትዮጵያን ብንጠቅማት የበለጠ ጠቃሚ ነው። 

===================////====================== 

Friday, March 10, 2023

Friday, March 3, 2023

የገዳ ሥርዓት የዲሞክራሲ ምሣሌ ከሆነ ለዘመናት የኢትዮጵያ ምሰሶ የንጉሥ ዘውድ ለምን የስልጣኔያችን እና የህልውናችን መሰረት አይሆንም? የአማራ ክልል ህዝብ የኢትዮጵያ ምልክት የሆነውን የንጉሥ ዘውድ ምልክት ለመመለስ ይነሳ! ያለውም ሆነ መጪው ሕገ መንግስት ይደግፈዋል።=======
ጉዳያችን
=======

ኢትዮጵያ ጥንታዊት ሃገር፣ቀደምት የመንግስት ስሪት ያላት፣ሕግ ስጋዊ እና ሕግ መንፈሳዊ ከራሷ አልፎ ለዓለም ሕግ አስተዋጽኦ ያደረገች ጥንታዊት ምድር። ይህች ታላቅ ሃገር ስሟ ገንኖ እና ነፃነቷን አስጠብቃ የኖረችበት አንዱ እና ዋናው ምሰሷዋ የንጉሥ ዘውድ ምልክት ያላት ሃገር ስለሆነች ነው።ይህንን ምሰሶዋን፣ የህዝብ ብሶት አስታኮ የኢትዮጵያ ህዝብ (አሁንም ገና በቂ ምርምር ቢያስፈልግም) በ1966 ዓም አፍርሷል።ይህንን የኢትዮጵያ ምልክት በማፍረስ ሥራ ላይ በአንድም በሌላም የተሳተፉ የእኛ ታላላቆች የምሰሶው መኖር ቢያንስ አደጉ በሚባሉ ሃገሮች እንዳለው ለምልክት ማስቀመጥ እና በአስቸጋሪ ጊዜ ለችግር ፈቺነት ቢቀመጥ ኖሮ እያሉ የሚያወሩት ለብቻቸው ወይንም ከወዳጅ ዘመድ ጋር እንጂ በጥናት አቅርበው ምሰሶውን የማፍረሱ ፋይዳ ኢትዮጵያን እንዴት እንደጎዳ ሽንጣቸውን ገትረው ለመከራከር ብዙ ሲሽኮረመሙ ይታያል።

የእኔ ትውልድም የዘውድ ምልክት በተለይ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ የሚነግረውም ሆነ የነገረው የለም።የወታደራዊው መንግስት፣የህወሃትኢሃዴግ መንግስት እና አሁን ያለው የጽንፍመር መንግስትም ሁሉም ዘውድ እና ንጉስ ሲባል እንድንሸማቀቅ አድርገው ሲሰሩን ኖረዋል። አሁን ዓይን የመግለጫ ጊዜ ነው።እንደ ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ የነፃነቷ እና የአንድነቷ ምልክት ሆኖ የኖረውን የዘውድ ምልክት አፍርሳ ከግማሽ ክ/ዘመን በላይ ተንከራታለች።ይባስ ብላ ባለፉት ነገሥታት ሃውልት ሥርም ልጆቿ ቆመው ስለሃገራቸው፣ስለየጥቁር ህዝብ ነጻነት እና ስለየሰውልጆች ሰላም ሲሉ በውሃ ጥም እና በረሃብ ተንከራተው ያመጡትን የነጻነት ፋና እንዳይዘክሩ በጥይት በመሃል አዲስ አበባ እየተገደሉ ነው።ለእዚህ አብነት የሚሆነው የ127ኛው የዓድዋ በዓል በትናንትናው ዕለት የካቲት 23፣2015 ዓም ለማክበር በምንሊክ አደባባይ በተሰበሰበው ሰላማዊ ህዝብ ላይ የተፈጸመው ግድያ እና በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ቅጽረ ግቢ ላይ የተወረወረው አስለቃሽ ጋዝ አንዱ አብነት ነው።የኢትዮጵያ ጠላቶች አይደለም የኢትዮጵያ አንዱ ምሰሶ እና ምልክት ዘውዱን የነገስታቱን ሃውልስ ስር ስትቆም ይደነግጣሉ። መድኃኒቱ የዘውድ ምልክትህን መመለስ እና ሙሉ መብትህን ማሳየት ነው።

እንዴት ይመለስ? ችግሮች የሉበትም ወይ? ሌላ ክፍፍል አይፈጥርም ወይ? ለምን የአማራ ክልል? አሁን ያለውም ሆነ መጪው ሕገ መንግስቱ እንዴት ነው የሚደግፈው? እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች በአዕምሯችሁ እንደሚነሳ አስባለሁ። ወደ እያንዳንዱ ምላሽ ከመሄዴ በፊት ኢትዮጵያ ለምን በመስቀለኛ መንገዶች ላይ ስትሆን ሁሌ መሻገር ያቅታታል? የሚለውን ጥያቄ መመለሱ መቅደም ይገባዋል።
የዘመናዊ ትምሕርት ቀመስ ነን የሚሉ ምሑራን ሁሉ ይህ ጥያቄ ሲነሳ ወድያው ከአፋችሁ ነጥቀው የሚያነሱት የተቋም አለመኖር ነው። ሃገራችን ተቋም አልገነባችም ይሏችኋል። ተቋም ማለት የአውሮፓ እና አሜሪካ ዲግሪ ላላቸው ምሑራኖቻችን ዘንድ መሃል ከተማ ቢሮ ያለው የጸዳ ህንጻ እና ከረቫት ያደረጉ ባለሙያዎች የሚርመሰመሱበት፣በመላዋ ሃገሪቱ ቅርንጫፍ ያለው ወዘተ ይታያቸዋል።የእዚህ ዓይነት ተቋም በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መንደር የገባ እና እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በመንደሩ የሚያውቀው ዓይነት መዋቅር ሲያማትሩ ይታያሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት የገነባችው ከቤተመንግስቱ እስከ የገበሬ ቤት ድረስ የደረሱ ተቋማት እንዳሏት የአውሮፓ እና አሜሪካ ዩንቨርስቲ መጽሓፎች ላይ ስለሌሉ አያውቋቸውም። ኢትዮጵያ ግን በክርስትናም ሆነ የእስልምና የእምነት ተቋማቷ ሃገሩን በየጊዜው ካስተዳደሯ መንግስታት መዋቅር እና ተቋም በላይ ህዝቡን ይዘው ዘመናት ተሻግረዋል። ከእነኝህ በተጨማሪ እና ምናልባትም በመንግስት ስሪት ታሪኳ ዘመናትን ያሻገራት ምሰሶዋ ግን የዘውድ ምልክቷ ነው።

የዘውድ ምልክት የሃገር ምሰሶ ለመሆኑ ከኢትዮጵያ ታሪክ የበለጠ ማስረጃ ለማሰባሰብ መድከም ባያስፈልግም ምሑራኖቻችን ዓይናቸውን ገልጠው ያስተማሯቸውን የአውሮፓ ሃገራን የዘውድ ምልክት እና ንጉሶች ዛሬም መኖራቸው ለግድግዳ ጌጥ ሳይሆን ሃገር መንታ መንገድ ላይ ስትቆም የዘውድ ምልክቱ ተቋማዊ ሚና ጠቃሚ መሆኑን ስለሚያውቁ ነው ጃፓን፣እንግሊዝ፣ዴንማርክ፣ኖርዌይ፣ስዊድን፣ቤልጅየምን ጨምሮ በዓለም ላይ ወደ 43 ሃገሮች የዘውድ ምልክታቸውን ዛሬም ሳይጥሉ በዲሞክራሲያዊ የመንግስት ስሪት ውስጥ ሃገራቸውን እያበለጸጉ ነው።ኢትዮጵያ ከእነኝህ ሁሉ ሃገሮች በታሪክም፣በጥንታዊነትም ሆነ በመንፈሳዊ ሃብቶች ሁሉ በብዙ እጥፍ ትበልጣለች።የዘውድ ምልክቷን ግን አፍርሳ ጥላለች።

የመሽኮርመም ጊዜ ያብቃ!

የኢትዮጵያ ነገሥታት በዝባዥ፣ኋላ ቀር አስተሳሰብ እየተባልክ ያደክ ወጣት ይሄው ዛሬ የነግስታቱን በዘመናቸው የነበራቸውን የሥልጣኔ ጥግ፣የሕግ አክባሪነት፣ለሰው ልጅ ያላቸው ዋጋ እና ለአምላካቸው ያላቸው ፍቅር አሁን የጽንፍ መንገድ እየተከተሉ ሰው በቁም ከሚሰቅሉት፣ሕግ ምን እንደሆነ ከማያውቁ እና ለሆዳቸው ሃገራቸውን ከሸጡ ቡድኖች ጋር እያነጻጸርክ መፍረድ ነው። ዛሬ የምንሊክ ሃውልት ፊት እንዳትቆም ያደረጉህን ለመርታት ፍቱን መድሓኒቱ ዘውዱን እመልሳለሁ፣ንጉሴንም አነግሳለሁ ብለህ ፖለቲካውን መስቀል ብቻ ነው። ይህንን ደግሞ ለእልህ እና ለብሽሽቅ ሳይሆን የሃገር ምሰሶ ስለሆነ ከልብህ ታግለህ ምሰሶውን አቁመው። ይህ ለአንዳዶች የእብደት መንገድ ይመስላቸዋል።ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ አናቱ ላይ ስለዘውድ ክፉ የሚያወራ ጎጆ ለተሰራበት ሰው የእብደት መንገድ ሊመስለው ይችላል።ነገር ግን ሀውልቱን የፈራውን በአካል ስጋና ደም አልብሰህ ንጉሥ ሾመህ ነው ሥርዓት የምታስይዘው። በእዚህ ዙርያ የሚነሱ ጥያቄዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቀድም ብዬ ለመግለጥ ሞክርያለሁ። አሁን እያንዳንዱን ለመለስ እሞክራለሁ።

አሁን ባለችው ነባራዊ ሁኔታ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ከአሁኑ እና ከሚመጡት ሕገ መንግስቶች አንጻርስ እንዴት ይታያል?

አሁን ያለንበት የብልጽግና የጽንፍ ኃይሎች ኢትዮጵያን በሚያውኩበት እና ፈጽሞ ለማጥፋት በተነሱበት ጊዜ ይህ የዘውድ ጉዳይ ትልቅ ዕድል እና አጋጣሚ ሆኖለታል ማለት ይቻላል። ከፖለቲካው ዐውድ አንጻር ስንበለከት በተለይ አማራ እየተባለ እየተሰደደ፣እየተገደለ እና የዐድዋ በዓልን ለማክበር ከሃውልቱ ስር ለመቆም ያልተፈቀደለት የኅብረተሰብ ክፍል በኩራት ይዞት የሚነሳው ታላቅ ፖለቲካዊ ኃይል ዘውዱን በቦታው መመለስ ነው።

ለኢትዮጵያ የዘውድ ምልክት የመንግስት ስሪት ጉዳይ አይደለም።የከበረ የባሕላችን መገለጫም ነው። ይህ የእኔ ባሕል አይደለም የሚል መብቱ ነው።ቢያንስ ግን አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ለአማራ ማኅበረሰብ የዘውድ ሥርዓቱ እና ንጉስ መኖሩ የባሕሉ መገለጫ ነው።ለኦሮሞ የገዳ ሥርዓት ባሕሉ እንደሆነ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ የዘውድ ሥርዓት የባሕሉ መገለጫ ነው። አባ ገዳ ለኦሮሞ ባህላዊ መሪው እንደሆነ እና በክልሉ አስተዳደርም ሆነ በመንግስት ሥርዓት ውስጥ እንደማይገባ ሁሉ፣ ንጉስም ለአማራ ማኅበረሰብ በክልሉም ሆነ በመንግስት አስተዳደር ጣልቃ የማይገባ የባሕል መሪው፣መካሪው እና የቅርስ ባለ አደራው ነው። አሁን ሃውልት አይደለም እራሱን ንጉሡን ነው የማምጣት ተልዕኮ መሆን ያለበት። ይህ ትግል ይጠይቃል።ነገር ግን ህዝብ ሁሉ በአንድ ልብ ተስማምቶ የሰራውን ዓለሙ ቢቃወም እና ቢጮሕ የሚመጣ አንዳች ነገር የለም።

ከሕገ መንግስት አንጻር ለገዳ የተፈቀደ ባሕል ለአማራ ክልል የዘውድ እና የንጉስ ባሕላዊ ቅርስ የሚከልክል ህግ የለም።እያንዳንዱ ክልል የራሱን ባሕል የማበልጸግ፣የማሳደግ እና የመጠቀም ሙሉ መብት አለው።ይህ ህግ ደግሞ በአሁኑ ሕገመንግስት ብቻ ሳይሆን በመጪ መንግስታት ሕገመንግስት ላይም የማይሻር ነባራዊ ሕግ ነው።ስለሆነም የአማራ ክልል ይህንን የባሕላዊ ቅርስ ባለአደራ ንጉሱን እና የዘውድ ምልክቱን ከእነ ሙሉ ክብሩ የመመለስ ሙሉ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ መብት አለው።

ከኢትዮጵያ ነገስታት ታሪክ አንጻር ይህ ለእራሱ ለአማራ ክልልም ክፍፍል አይፈጥርም ወይ?

በኢትዮጵያ የነገስታት ታሪክ የጎንደር፣የሸዋ፣የወሎ፣የትግራይ እና የጎጃም ንጉስ የሚሉ ታሪኮች አሳልፈናል። እነኝህ ታሪኮች እያሉም ኢትዮጵያ የዘውድ ምሰሶዋ አስፈላጊ እንደሆነ በማወቋ ይዛው ኖራ ህልውናዋን አስጠብቃለች።አሁን ባለንበት ዘመን ዋናው እና አስፈላጊው የዘውድ ምልክቱን የአማራው ማኅበረሰብ በአንድ ድምጽ ቆሞ ባሕላዊ መገለጫዬ የቅርሴ ባለአደራ ነው ብሎ መነሳት እና ማስከበር ነው እንጂ አሁን በእጁ ያለው እና በ1966 ዓም ያፈረስነው የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የዘውድ ምክር ቤት ከመካከላቸው የሚመጥን ሰው የማዘጋጀት ሥራ ከመስራት በቀላሉ መጀመር ይቻላል። ዋናው ጽንሰ ሃሳቡን ይዞ መነሳት እና ለእዚህም በቂ የፖለቲካ፣የሞራል፣የስነ ልቦና እና የብቁ አደረጃጀት መገለጫ አድርጎ መጠቀሙ ነው አስፈላጊው ጉዳይ። ይህንን ደግሞ የብልጽግና አማራ ክልል የአሁን መሪዎች ቢቀበሉት እና ባሕላዊ ዕሴታችን ነው ብለው የበታኝ ኃይሎች የሚብከነከኑበትን ቁልፍ ጉዳይ ይዘው ወደ ፊት በመምጣት ቢጠቀሙበት እራሳቸው ይከብራሉ፣ታሪክ ይሰራሉ፣ከሕዝብም ከበሬታ ያገኛሉ። ሆኖም ግን እንደ ባለፉት ግማሽ ክፍለዘመናት እየተሽኮረመሙ ከታሹ ህዝብ የራሱን አደረጃጀት ፈጥሮ ቅርሱን እና ባሕሉን ለመጠበቅ መንቀሳቀስ እና ያለፉ ንጉሥ ሃውልት ስር ልቁም ሳይሆን እራሱን ንጉሡን ይዤ መጣሁ ወደ የሚል የላቀ የፖለቲካ ልዕልና መሻገር እና ምህዋሩን መዘወር መቻል አለበት።

ስለሆነም የዘውድ ምልክቱን እና ንጉሱን ከእነሙሉ ክብሩ በአማራ ክልል በቤተመንግስት መሰየሙ እና ማክበሩ የክልሉን የኖረ ባሕላዊ ዕሴት እና አንድነት ብቻ ሳይሆን ነገ የቀረው የኢትዮጵያ ክፍልም ምልክት እና መሰባሰብያ ሁነኛ የነበረ ዕሴት ፍለጋ ሲባዝን አንዱ አጋዥ እና የቀውጢ ጊዜ ምሰሶ እንደሚሆን አያጠራጥርም። አሁን ግን የአማራ ክልል ለሕልውናውም ሆነ ለውስጣዊ አንድነቱ ከገጠር እስከከተማ ለማጠናክር እንዲሁም ለፖለቲካ ልዕልና እና የሞራል ዕሴት በግርግር የወደቀውን የዘውድ ምልክቱን ማንሳት እና ወደ ቦታው የመመለስ ታሪካዊ አደራ ከፊቱ ተደቅኗል።

መደምደምያው 

ኢትዮጵያ የዘውድ ሥርዓቷን በማዘመን እና የፓርላማ ሥርዓት አድርጋ መቀጠል ካልቻለች ላለፉት ግማሽ ክ/ዘመን የደረሰባት መንከራተት እንደሚደርስባት ቀድመው በ1966 ዓም የተናገሩ ምሑራን ነበሩ። ከእነኝህ ውስጥ ቀዳሚው ደራሲ እና ዲፕሎማት ሓዲስ ዓለማየሁ ነበሩ። እኝህ የፍቅር እስከ መቃብር፣የልምዣት እና ሌሎች መጻሕፍት ደራሲ እና የኢትዮጵያ ባለሙሉ አምባሳደር ሓዲስ ዓለማየሁ የ1953 ዓም የእነጀነራል መንግስቱ ንዋይ እንቅስቃሴ እና የ1966 ዓም የኢትዮጵያ አብዮት ሲቀጣጠል በኢትዮጵያ የሚመጡት መንግስታት ምን ዓይነት ሊሆኑ እንደሚችሉ ቀድመው ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። ይሄውም ''ኢትዮጵያ ምን ዓይነት አስተዳደር ያስፈልጋታል?'' በተሰኘው መጽሓፋቸው ላይ ኢትዮጵያ የዘውድ ምልክቷን ካፈረሰች የሚገጥማትን ፈተና ዘርዝረው አስቀምተዋል።ዛሬ የሚገባው ካለ እና ጊዜው አሁን መሆኑ ለተረዳ፣እንዲሁም ይህንን በሙሉ ልብ ይዞ ሊነሳ ከሚገባ ውስጥ ባሕሉ እና የቅርስ ባላደራ እና መገለጫው የአማራ ክልል ከወደቀበት አቧራውን አራግፎ ቢያነሳው  እራሱንም ኢትዮጵያንም ይጠቅማል።የንጉስ ሃውልት ሥር አይደለም እራሱን ንጉሡን ነው የማመጣው ብሎ መነሳት የህልውናው ማጥበቅያ ሁነኛ ፖለቲካ ነው። ፖለቲካው ደግሞ ባለዐራት ጎማ ነው። ወደኋላም ያስኬዳል የኢትዮጵያ ታሪክ የዘውድ ታሪክ ነው እና እንዲሁም አሁን ላይ በታኝን ይመታበታል፣በዓለም አቀፍ ግንኙነት ይናኝበታል፣በመጨረሻም ለመጪ የሃገር ህልውና መሰረት ያጠብቅበታል።የዘውድ ጉዳይ ያለው የፈጣሪ ኃይል እና ከኢትዮጵያ ነፃነት እና ኃይል ጋር ያለውን ቁርኝት በተመለከተ በራሱ ሌላ አጀንዳ ነው። ይህም ግን የሚናቅ ጉዳይ አይደለም። ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ሰላም አጥታ የተንከራተተች ሃገር እና አሁንም ድረስ የዘውድ ምልክታቸው ከስልጣኔያቸው ጋር ያልተጋጨባቸውን ሃገሮች ለአብነት መመልከት ነው። የመጨረሻው መጨረሻ በአፍሪካ ያሉ መንግስታት የፌድራል ክልሎቻቸው ዘውድ እና ንጉሥ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ክብር ይሰጣቸዋል።ለምሳሌ በዑጋንዳ ማዕከላዊ ክፍል የቡጋንዳ ግዛት ንጉሥ አላት።በሌሎች የአፍሪካ ሃገሮችም በናሙናነት ማንሳት ይቻላል። በኢትዮጵያ አማራ ክልል የዘውድ ቅርሱን መልሶ የመጠበቅ ሙሉ ሕገመንግስታዊ መብት የማይሸራረፍ እና ማንንም እንዲገሰው መብት ሊሰጠው የማይችል ነው።

==============////===========