ካፒቴን ኃይለመድህን አበራ (ፎቶ ከማኅበራዊ ድረ-ገፅ)
ካፒቴን ኃይለመድህን አበራ ለኢትዮጵያ ተላልፎ አይሰጥም።
ቀደም ብሎ አቶ ሬድዋን ሁሴን የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ ድርጊቱ በተፈፀመበት ቀን የኢትዮጵያ መንግስት አንዳንድ የአለም አቀፍ ውሎችን ተንተርሶ የስዊዘርላንድ መንግስት አሳልፎ እንዲሰጥ እንደሚጠየቅ ፍንጭ ሰጥተው ነበር።ሆኖም ግን የስዊዘርላንድ መንግስት በምድሩ ላይ ያረፈው አይሮፕላን ጉዳይ የሚዳኘው በሀገሩ ፍርድ ቤት መሆኑን አምኖ ምርመራው ከማለቁ በፊት ለካፒቴን ኃይለመድህን አማካሪ ጠበቃ መድቦለታል።በብዙዎች እምነት ምርመራው እየተከናወነ ጠበቃ ማግኘቱ በብዙ መንገድ ካፒቴን ኃይለመድህንን እንደሚረዳው ያስረዳሉ።በሌላ በኩል ትናንት የካቲት 14/2006 ዓም ኢሳት ቴሌቭዥን በሰበር ዜና እንደገለፀው ለስዊዘርላንድ ፈድራል ፖሊስ ዲፓርትመንት በኢሜል የካፕቴን ኃይለመድህንን ጉዳይ በጠየቀው መሰረት ክፍሉ በፅሁፍ ምላሽ መስጠቱን ለማወቅ ተችሏል።በምላሹ መሰረት ኃይለመድህን በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ፣ እስካሁን ወንጀለኛ ተብሎ እንደማይጠራ፣ምርመራው መቀጠሉን፣ጠበቃ እንደተመደበለት እና ፍርድቤት ሲቀርብ ቀሪው የፍርድቤት ተግባር እንደሆነ ያብራራል።
ዛሬ '' የአጃንስ ፍራንስ ፕሬስን'' ዘገባ ጠቅሶ ''ሲ ቢ ኤስ8'' እንደገለፀው ደግሞ የስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት ካፒቴኑ በማረፍያ ቦታ እንዲቆይ እና ምርመራው እንዲቀጥል አዟል።ይህ ማለት ከማዕከላዊ የፖሊስ ምርመራ ጣብያ ወደ ማረፍያ ቤት የመዞሩ ሁኔታ ቀድሞ ከነበረበት የተሻለ ማረፍያ እንደሚሆን ይገመታል።ምናልባት ማረፍያ ቦታው ላይ የተሻለ የግለሰብ ነፃነት የሚሰጠው እና ለምሳሌ አለም አቀፍ ዜና ለመከታተል ይረዳው ይሆናል የሚል ግምት አለ።በእርግጥ በምዕራቡ አለም እነኚህ መብቶች በምርመራም ላይ ሳለ የማይከለከሉ መሆናቸው ይታወቃል።
ድርጊቱን በተመለከተ የኢትዮጵያውያን ስሜት
በሌላ በኩል የአይሮፕላኑ ጄኔቭ ላይ ማሳረፍ ተከትሎ በሀገር ቤት የተለያዩ ስሜቶች መፈጠራቸውን ከሀገርቤት የሚወጡ ዘገባዎች ያመላክታሉ።ስሜቶቹ ''ኢትዮጵያን በዓለም አዋረደ'' ከሚሉት የተወሰኑ በቅን ከሚሰነዘሩ እስከ መንግስት ደጋፊዎች የሚሰሙ ቢሆንም በአብዛኛው በውጭም ሆነ በሀገር ቤት ያለው ሕብረተሰብ ዘንድ ግን አንዳች አደጋ ካለመድረሱ እና የደንበኞችን ክብር ሳያዋርድ በሰላም ማከናወኑ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሚልዮን ኢትዮጵያውያንን ብሶት ለማሰማት የቻለ ጀግና! ነው ብለው የሚናገሩ እና የሚፅፉ ናቸው። ከእዚህ የተረፉት ጥቂቶች ደግሞ ''ቆዩ እስኪ እርሱ የሚለውን እንስማ'' አንቸኩል የሚሉ ናቸው።''የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሶስት ሺህ ሰራተኞችን ዋይታ ነው ይዞ የመጣው''አሁን ስዊዘርላንድ የሚኖረው ሚካኤል መላኩ የተባለ የቀድሞ የአየር መንገዱ የበረራ ደህንነት ሰራተኛ
አሁን ስዊዘርላንድ የሚኖረው ሚካኤል መላኩ የተባለ የቀድሞ የአየር መንገዱ የበረራ ደህንነት ሰራተኛ ለኢሣት በሰጠው ቃል ደግሞ አየር መንገዱን ከዘጠኝ አመት በላይ እንደሚያውቅ ጠቅሶ በአየር መንገዱ ውስጥ ከፍተኛ የአስተዳደር እና የዘር መድሎ ችግር መኖሩን ይህም ከስርዓቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን፣ለእዚህ ማሳያ ያደረገው ጠንካራው የአየር መንገዱ የሰራተኛ ማኅበር በትናንሽ ማለትም የአብራሪዎች ሰራተኛ ማህበር፣የአስተናጋጆች የሰራተኛ ማህበር፣የቴክኒሻኞች የሰራተኛ ማህበር እየተባለ ለስርዓቱ የታዘዙ ካድሬዎች እየመሩት መሆኑን አብራርቷል። ይሄው የቀድሞ የአየር መንገዱ የበረራ ደህንነት ሰራተኛ ሚካኤል መላኩ ስለ ካፒቴን ኃይለመድህን ሲናገር ደግሞ እንዲህ አለ -''አውቄዋለሁ።በጣም ነው የማደንቀው የሚገርምህ እስከ ሮም ድረስ ከሁሉም የአየር ትራፊኮች ከራዳር እንዲሰወር አድርጎ ነው የበረረው በኃላ ነው ራዳር እንዲታይ ያደረገው። ከፍተኛ የመብት መጣስ ደርሶበት ነው።ሌላ ሊሆን አይችልም።የኢትዮጵያ አየር መንገድን የሶስት ሺህ ሰራተኞችን ዋይታ ነው ይዞ የመጣው''
ጉዳያችን
የካቲት 14/2006 ዓም
(ከጉዳያችን ማናቸውንም ፅሁፍ ድረ-ገፅ ላይ ሲለጥፉ ምንጩን መግለፅ ጨዋነት ነው)