ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, February 18, 2014

ለመግደል የሚፈለገው መስፈርት ኢትዮጵያው መሆኑ ብቻ ነበር።የካቲት 12 የሰማዕታት ቀን


ስድስት ኪሎ የሚገኘው የካቲት 12 የሰማዕታት ሃውልት ላይ 

ዘመኑ 1929 ዓም የካቲት ከገባ ገና አስራ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።የ አዲስ አበባ አየር ደመናማ ነበር። የተለመደው የበልግ ዝናብ ሊመጣ ዳር ዳር የሚል ይመስላል። አዲስ አበባ መንገዶች በጣልያን ወታደሮች ይታመሳል። ሰሜን ሸዋ ላይ የሚዋጋው አንዳንዴም አዲስ አበባ መግብያ በር ደረሰ እየተባለ የሚወራለት የ አርበኛው የራስ አበበ አረጋይ ሰራዊት በየ ጠጅ ቤቱ በ ቅኔ አዘል ግጥም ይሞገሳል። ቅኔው የገባቸው ባንዳዎችም አዝማሪውን እየጠቆሙ ፍዳውን ያሳዩታል። አዝማሪው ገና አለ ገና በሚል መልክ ውግያው ይቀጥላል የሚል ቃና ያለው ግጥም  ያንቆረቁራል-

 '' የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፣
  ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ''

እየተባለ ሴት ወንዱ ለውጊያ የተዘጋጀበት አርበኛ ሆኖ መሞት የተናፈቀበት  ጊዜ ነበር። የስድስት ኪሎ የያኔው ቤተመንግስት የአሁኑ ዩንቨርስቲ ከአዲስ አበባ በግድም በውድም በተሰበሰቡ ባብዛኛው ሴቶች ና ሕፃናት ተሞላ። እብሪት የተሞላበት የግራዝያኒ ንግግር ተጀመረ። በንቀት ያየው ሕዝብ ላይ ስለ ''ታላቂቱ ጣልያን'' መደስኮር ጀመረ። ግን ብዙ አልቆየም አብርሃም እና ሞገስ ሕዝቡን ጥሰው ከፊቱ ደረሱ ሰባት ቦንቦችን አከታትለው ወረወሩበት፣ግራዝያን ቆሰለ፣ የ አየር ኃይሉ ኃላፊ ተገደለ። አብርሃም እና ሞገስ በ ቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስትያን በኩል ባለው የ ቤተመንግስቱ የ ጋራ  አጥር ዘለው ወጡ እና ታክሲ ይዞ ወደሚጠብቃቸው ስምዖን ገሰገሱ፣ ስምዖን በታክሲ ወጣቶቹን ይዞ ነጎደ፣ እንጦጦ ተራራ ላይ ውጥተው አዲስ አበባን ቁልቁል አይዋት፣ ግራዝያን በቆሰለበት ሆኖ አዋጅ አውጆ ለካ የ አዲስ አበባ ወንድ ከሴት ሕፃን ከአዋቂ ሳይባል በ ጥይት፣በ አካፋ እና በዶማ በተገኘው ሁሉ መፈጀት ተጀምሯል።

ሶስቱ ወጣቶች ተቃቅፈው ተላቀሱ።ጊዜው እስኪመሽ ጠበቁ እና ስምዖን ወደ ደብረሊባኖስ ይዟቸው ነጎደ።ለ ሰሜን ሸዋ ራስ አበበ አረጋይ ቅርብ የሆነችው -ደብረሊባኖስ አመቺ መስመር እንደሆነች ሁሉም አምነውበታል። ስምዖን ተልኮውን ፈፅሞ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። አብርሃም ና ሞገስ ከ ራስ አበበ አረጋይ ጦር ጋር ተቀላቀሉ።

የካቲት አስራ ሁለት ቀን  ከ ሰላሳ ሺህ በላይ ነዋሪዎች ሰማአትነት ተቀብለዋል። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ቤቶች ተቃጥለዋል። ግድያው በመንገድ ላይ የተገኘ ማንኛውም ሰው ላይ ሲሆን ለመግደል  የሚፈለገው መስፈርት ኢትዮጵያው መሆኑ ብቻ ነበር።

ስድስት ኪሎ የሚገኘው የካቲት 12 የሰማዕታት ሃውልት

የ አብርሃም ፣የ ሞገስ ና ስምዖን የ ሀገር ፍቅር እስከ መቃብር


ስምዖን 

ስምዖን አብርሃም እና ሞገስን ደብረሊባኖስ ወደ ሰሜን ሸዋ መንገድ ከሚያውቃቸው አርበኞች ጋር አገናኝቶ ተመለሰ።ብዙም አልቆየ በፋሽስቱ ጥቁር ለባሾች ተይዞ በብዙ መከራ እና ስቃይ ተገደለ። የታሪክ ምሁራን እንዳስቀመጡት ስምዖን የእጁም ሆነ የእግሩ ጥፍር በጉጠት እየተነቀለ ጣቶቹን እየሰባበሩ አሰቃይተው ገደሉት።

አብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም 

አብርሃም ደቦጭ ና ሞገስ አስገዶም ከራስ አበበ አረጋይ የአርበኞች ጦር ጋር ከተቀላቀሉ በኃላ ራስ አበበ አረጋይ ልዩ እንክብካቤ እንዲያገኙ አደረጉ።ቆይተው ግን የነበራቸውን የትምርት ደረጃ በመረዳት ከሀገር ውጭ ወጥተው ለሀገራቸው ቢሰሩ ይጠቅማሉ ብለው በማሰብ ከስንቅ እና ገንዘብ ጋር ወደ ሱዳን እንዲሄዱ መከሯቸው። ሆኖም  ግን በጉዞአቸው ላይ ሱዳን ሊገቡ ትንሽ ሲቀራቸው  ፎቶዋቸው በገጠር ባሉ የፋሺሽት ወታደሮች ሁሉ ተናኝቶ ነበርና በፋሺሽቶች  ተይዘው በስቅላት ሰማዕት ሆኑ።በኃላ ግን አፄ ኃይለሰላሴ በ ሱዳን በኩል ጣልያንን ከእንግሊዝ ሰራዊት ጋር ሆነው ድል ሲያደርጉ የ አብርሃም እና  የሞገስ አስከሬን ተቆፍሮ ወጥቶ አሁን አዲስ አበባ በሚገኘው የ ቅድስት ስላሴ አርበኞች ሃውልት ስር እንዲያርፍ አድርገዋል።

ጉዳያችን GUDAYACHN

የካቲት12/2006 ዓ.ም. 

www.gudayachn.com

የ ፅሁፉ መርጃዎች 

፩/ http://www.ethioobserver.net/forgoten_heroes.ሕትም በ ፍቅረ ቶሎሳ 

፪/ ኢሳት ራድዮ የካቲት 11/2004 ዓም 

፫/ ግሎባል አልያንስ ኢትዮጵያ http://www.globalallianceforethiopia.org No comments: