ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Saturday, September 23, 2017

የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን ስርጭት በአቡነ ማቲያስ መታገድ የቤተ ክርስቲያንን ተቋማዊ አቅም የመፈታተን ሌላው እኩይ ተግባር ነው።


ጉዳያችን/ Gudayachn
መስከረም 13 / 2010 ዓም (ሴፕቴምበር 23 / 2017)
+++++++++++++++++++++++++++
  • በወጣቶች የተገነባው እና ለእሩብ ክፍለ ዘመን አገልግሎቱን በነፃ የሚሰጥ ማኅበር - ማኅበረ ቅዱሳን በሕዝብ መሀክል ሰላም፣እርቅ እና መግባባት እንዲኖር የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም።
  • በቅርቡ በአማርኛ፣ኦሮምኛ እና ትግርኛ የጀመረው መንፈሳዊ መርሃ ግብርም ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተለየ ሀገራችን ለገጠማት የመለያየት ችግር አንዱ እና አይነተኛ የእርስ በርስ መከባበር ፣መተሳሰብ እና ትልቅ ትስስር የመገለጫ መንገድ ተደርጎ መታየት ይገባው ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ መሰረትነት ላይ ስለታነፀች እና ሐዋርያዊት በመሆኗ አሰራሯ በአንድ ፓትሪያርክ ወይም ሊቀ ጳጳስ የግል ውሳኔ ላይ ሳይሆን መንፈስ ቅዱስን አጋዥ አድርጎ በሚሰራው በ50 ዓም  ሐዋርያት በመሰረቱት ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሰረት ነው።አባቶቻችን አንድን የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ በቅዱስ ሲኖዶስ ስብስባ ሲወስኑ '' እኛና መንፈስ ቅዱስ'' ብለው ውሳኔያቸውን አስረግጠው ነገር ግን በትህትና ያሳውቁ ነበር።አሁን ባለንበት ዘመን ይህ ጉዳይ  በተለይ  ከዘመነ አቡነ ጳውሎስ ጀምሮ የአንድ አባት ውሳኔ የቤተ ክርስቲያኗ ውሳኔ እየተደረገ ብዙ ነገሮች እንዳይስተካከሉ እየተደረጉ ሲበላሹ ተመልክተናል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከ40 ሚልዮን ምእመናንን በላይ በስሯ ይዛ በ21ኛው ክ/ዘመን ለምእመናን የምትደርስበት አንድ ቴሌቭዥን ስለሌላት የማይቆጭ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጅ አልነበረም።ይህንን የተገነዘበው ማኅበረ ቅዱሳን ከኢቢኤስ ሳምንታዊ የአየር ጊዜ በመግዛት በሳምንት አንድ ጊዜ የትምህርት እና ልዩ ልዩ ገዳማት የተመለከተ ዘገባዎችን  ለምእመናን ማድረስ ጀመረ።ሆኖም ግን ከትንሽ ጊዜ በኃላ መርሃ ግብሩ እንዲቆም ተደረገ።ይህም ሆኖ ማኅበሩ በኤሌክትሮኒክስ ሚድያዎች በመጠቀም  መርሃ ግብሩን ቀጥሎ ነበር።ሆኖም የኤሌክትሮኒክስ ስርጭቱ በተለይ በኢትዮጵያ ለሚኖረው ምእመን በኢንተርኔት መቆራረጥ ሳቢያ እና ያለውም የኢንተርኔት አገልግሎት ለጥቂቶች ከመድረሱ አንፃር አገልግሎቱ በሚገባ መድረስ አልቻለም። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሀገር ቤት ከፍተኛ በጀት ተመድቦለት የሳተላይት ቴሌቭዥን ቤተ ክርስቲያን ልትጀምር ነው የሚል ዜና ሲነገር እና ተጀመረ ሲባል ማኅበረ ቅዱሳን ሁል ጊዜ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር ባፈነገጠ መልኩ ላለመሄድ ለሚያደርገው ጥረት አንዱ በጎ መንገድ ስለሆነ በቴሌቭዥን ጣቢያው ላይ አገልግሎቱን በነፃ እንዲሰጥ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የቴሌቭዥን ጣቢያውን በበቂ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የተክኖሎጂ ግብዓት ለማሟላት ጠየቀ።ይህንን አስመልክቶ ሐራ ዘተዋህዶ ትናንት መስከረም 12፣2010 ዓም  ጉዳዩን አስመልክቶ በዘገበው ዘገባ ላይ ማኅበሩ ለምን ከአሌፍ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአየር ሰዓት ለመግዛት እና በአማርኛ፣ኦሮምኛ እና ትግርኛ መርሃ ግብሩን ለመጀመር እንደተገደደ ገልጦ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ሲያስረዳ እንዲህ ማለቱን ፅፏል : -

ማኅበሩ፣ ከቤተ ክህነቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ ውል በመግባትና የአየር ሰዓት በመግዛት ለማገልገል ብቻ ሳይኾን፤ ድርጅቱን በሰው ኃይልና በቴክኖሎጂ ለማጠናከር በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄና ልመና አዎንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ፣ ትምህርተ ወንጌልን በዘመናዊ መገናኛ ዘዴዎች እንዲያስፋፋ ሙሉ እውቅና በተሰጠው መተዳደርያ ደንቡ የተጣለበትን ሓላፊነት ለመወጣት ሌላ አማራጭ ለመፈለግ መገደዱን በዋና ጸሐፊው በኩል በሰጠው ምላሽ አስታውቋል....ፓትርያርኩም፣ ከቤተ ክህነቱ ቴሌቭዥን ጣቢያ የአየር ሰዓት እንደማይሰጠውና ከሌላ አካል የአየር ሰዓት በመግዛት መጠቀም እንደሚችል፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ደረጃ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለቀረበላቸው ጥያቄ ቁርጥ ምላሽ የሰጡበት በመኾኑም፣ ደግሞ መጠየቁ አስፈላጊ ኾኖ እንዳላገኘው አስረድቷል''  ይላል።

ይህ ሁሉ ጉዳይ ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከተው በኢትዮጵያ ከተቋማዊ አሰራር  መስፈን ይልቅ የግለሰቦች ወይንም ቡድሎች የግል ውሳኔ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተቋማትን ምን ያህል እየገደለ መሆኑን እንመለከታለን።ማኅበረ ቅዱሳን የአየር ሰዓት ገዝቶ በአማርኛ፣ትግርኛ እና ኦሮምኛ መንፈሳዊ መርሃ ግብሩን ሲጀምር ቤሳ ቤስቲ ገንዘብ ከቤተ ክህነት ወስዶ ሳይሆን አባላቱ በሚያወጡት የገንዘብ ወጪ፣ነፃ የሰው ኃይል እና ምእመናን በጎ ፍቃድ ነው።ይህ በእራሱ ሊበረታታ እና ሊደገፍ የሚገባው ቅዱስ ተግባር ነበር። ሆኖም የዛሬዋ ኢትዮጵያ ነችና በነፃ የማገልገል መብትህም በግለሰቦች እንደፈለገ ሊገታ ይችላል።ይህ ደግሞ ሌላ ችግር ማስከተሉ አይቀርም። እዚህ ላይ ቤተ ክርስቲያን አንድነቷን ጠብቃ ከመሄድ አንፃር ሌላ ሚድያ ለምን አስፈለገ? ብለው የሚጠይቁ ሊኖሩ ይችላሉ። ጥያቄው በቅን እስከተነሳ ድረስ ጉዳዩን ከማኅበረ ቅዱሳን በቤተ ክርስቲያን መዋቅር እና ቤተ ክርስቲያን በሰጠችው የመተዳደርያ ደንብ ልክ እየሰራ መሆኑን ከመገንዘብ አንፃር መመልከት ያስፈልጋል። የቤተ ክህነቱ አቅም በሰው ኃይል አንፃር ውሱን ከመሆኑ አንፃር ማኅበሩ  በነፃ ለማገልገል ዕድል አልተሰጠውም።ይህ አልሆን ሲል በቤተ ክርስቲያን መዋቃር ስር ሆኖ በተሰጠው የአገልግሎት ደንብ መሰረት ስብከተ ወንጌልን በተገኘው ዘመናዊ መንገድ ለማሰራጨት አስቦ በጥረቱ በገዛው የቴሌቭዥን የአየር ሰዓትም እንዳያገለግል እገዳ ተጣለበት።ምናልባት የሚሰራጨው ስርጭት ላይ ኤዲቶርያል ቦርድ ከቤተ ክህነት እንዲጨመር እና ይዘቱ ሃይማኖታዊ መሰረቱን እንዳይለቅ እና የሚድያ ፖሊሲው ላይ ይህ ቢገባ ይህ ቢወጣ ማለት የቤተ ክህነቱ አባታዊ ድርሻ ነበር።ሆኖም ግን ስብከተ ወንጌል በቴሌቭዥን ' አታስተላልፉም አግጀዋለሁ ' የሚለው አገላለጥ ግን በእራሱ ሌላ አዲስ ችግር የመፍጠር አባዜ ተደርጎ መወሰድ አለበት። 

እንደ ኢትዮጵያ ላለች በሚልዮን የሚቆጠር ህዝቧ ሃይማኖትን የሁለንተናው መገለጫ ለሆነ ሕዝብ ከልዩነት እና እርስ በርስ በጎሳ ከመናቆር የመውጫው መንገድ አንዱ የጋራ እሴቱን ማለትም ሃይማኖቱን አክብሮ የመያዙ ፋይዳ ነው።በእዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሚና  በቀላሉ የሚታይ አይደለም።በተለይ በወጣቶች የተገነባው እና ለእሩብ ክፍለ ዘመን አገልግሎቱን በነፃ የሚሰጥ ማኅበር - ማኅበረ ቅዱሳን በሕዝብ መሀክል ሰላም፣እርቅ እና መግባባት እንዲኖር የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም።በቅርቡ በአማርኛ፣ኦሮምኛ እና ትግርኛ የጀመረው መንፈሳዊ መርሃ ግብርም ከሃይማኖታዊ ፋይዳው በተለየ ሀገራችን ለገጠማት የመለያየት ችግር አንዱ እና አይነተኛ የእርስ በርስ መከባበር ፣መተሳሰብ እና ትልቅ ትስስር የመገለጫ መንገድ ተደርጎ መታየት ይገባው ነበር።ሲሆን ማኅበሩ የቤተ ክህነቱን የቴሌቭዥን ጣቢያ ሙሉ በሙሉ በአደራ እንዲያስተዳድር እና ሕዝብን እንዲያስተምር ማድረግ  ይህ ካሳሳቸው ደግሞ የአየር ሰዓት ገዝቶ የሚያስተላልፈውን መርሃ ግብር አለማወክ ጤነኛ አስተሳሰብ ነው።


ከእዚህ በታች በአዲስ መልክ በአሌፍ ቴሌቭዥን የተጀመረው መርሃ ግብር ማስታወቂያ ቪድዮይመልከቱ።

ከእዚህ በታች ማኅበረ ቅዱሳን ነገ መስከረም 14፣2010 ዓም በሀገር ውስጥ እና በውጭ በምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ላይ የተጋረጠው የተሃድሶ እንቅስቃሴ በተመለከተ አዘጋጅቶ ለምእመናን በነፃ ሊያድለው የተዘጋጀውን ቪድዮ ቅንጫቢ ይመልከቱ።





ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Wednesday, September 20, 2017

የኢትዮጵያ የተቃውሞ የፖለቲካ መድረክ ኢትዮጵያን በተመለከተ ግልፅ የፖለቲካ አቅጣጫ መያዝ የሚያስፈልግበት ደረጃ ላይ ደርሷል



ጉዳያችን / Gudayachn
www.gudayachn.com 

በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ ከተካተቱት ንዑስ አርዕስቶች ውስጥ -

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣይ እርምጃ ምን መምሰል ይገባዋል?
የኢትዮጵያ የቅርብ ወቅታዊ ተግዳሮት ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ህዝብን የሚንጥ እና ሚልዮኖችን ከጎናቸው የሚያሰልፍ የፖለቲካ ራዕይ ለሕዝቡ ማሳየት ለምን አልቻሉም?
እና ሌሎችም...

መግቢያ 

ኢትዮጵያን ውክፕድያ በድህረ ገፁ ላይ እንዲህ ይገልፃታል-

''ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ የምትገኝ የረጅም ዘመን ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በአፍሪካ ነፃነታቸውን ጠብቀው ለመኖር ከቻሉ ሁለት አገሮች አንዷ ነች። በህዝብ ብዛት ከአፍሪካ ኢትዮጵያ ሁለተኛ ስትሆን፣ በቆዳ ስፋት ደግሞ አስረኛ ናት። ርዕሰ ከተማዋ አዲስ አበባ ናት።አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገሮች ዕድሜያቸው ከአንድ ምዕተ ዓመት የሚያንስ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ግን ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ ነገሥታት እና ንግሥተ ነግሥታት የተመራች ሀገር ናት። የሰለሞናዊው ሥርወ-መንግሥት የአመጣጡን ዘር እስከ አስረኛው ዓመተ ዓለም ድረስ ይቆጥራል። ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ የኖረባት ቦታ እንደሆነች ብዙ የሳይንሳዊ መረጃ ተግኝቷል። በበርሊን ጉባኤ በኩል የአውሮፓ ሀያላት ሀገሮች አፍሪካን ሲከፋፍሏት፣ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ጠብቃለች። የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል ከነበሩት ሶስት የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ ነበረች። ከአጭር የኢጣልያ ወረራ ጊዜ በኋላም ከየተባበሩት መንግሥታት መሥራቾች አንዷ ናት። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን ሲያገኙ፣ ሰንደቅ አላማቸውን በኢትዮጵያ ቀለሞች ማለትም በአረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ላይ ነው የመሠረቱት። አዲስ አበባ ደግሞ ለየተለያዩ በአፍሪካ ላይ ላተኮሩ አለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ ሆነች።'' ይላል

ወግ አጥባቂ የአረብ መንግሥታት እና ፍላጎታቸው

የዛሬ ሰላሳ ሰባት አመት በምዕራቡ አለም የተከፈተው የቀዝቃዛው ጦርነት እጅግ በተፋፋመበት፣ የኢትዮጵያ አብዮት ተጠምዞም ይሁን በጥቂት የወቅቱ 'ልሂቃን' ለደርግ በቀረበ ሃሳብ ወደ ሶሻሊዝም ስርዓት ሀገሪቱን ለማስገባት በሚውተረተርበት፣በደቡብ ምስራቅ የሀገራችን ክፍል በወቅቱ ከሶቭየት ህብረት ባገኘው የመሳርያ ድጋፍ የተመካው የሱማልያ-ዚያድባሬ መንግስት የኢትዮጵያን መሬት በኃይል የወረረበት ወቅት ነበር።በእዚህ ጊዜ ነበር የ’ፋይናንሻል ታይምስ’ ጋዜጣ የአፍሪካ ቀንድን ፖለቲካ ከቀዝቃዛው ጦርነት በዘለለ እይታ የሚያመላክት አንድ ፅሁፍ ይዞ የወጣው። ፅሁፉ እንዲህ የሚል ነበር

’’በወግ አጥባቂ የአረብ መንግሥታት በሳውድ አረብያ ቀንደኛነት በግብፅ፣ሱዳን እና ሶርያን ጨምሮ በቀይባሕር እና በአካባቢው ሃገራት የአረብ ወይንም የእስልምና መንግሥታት እንዲመሰርቱ የሚደረጉ ጥረቶች አሉ።’’
’’the conservative Arab states, marshalled by Saudi Arabia and including Egypt, Sudan and Syria, want to create a band of Arab or Muslim states along the shores of the Red Sea and its approaches.'' (Financial Times May 2 1977)

የ ሶስት ሚልዮን ሕዝብ አናሳነት  በፖለቲካ ስሌት አንፃር 

ከሱማልያ ጎን ቆማ የቀዝቃዛውን ጦርነት ትዋጋ የነበረችው ሶቭየት ህብረት (የዛሬዋ ሩስያ) ከቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ መውረድ በኃላ ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ ለማዞር አፍታም አልቆየችም።ለእዚህ ውሳኔ ካበቃት ጉዳይ አንዱ የኢትዮጵያ ስልታዊ ጠቀሜታ ዘለቄታዊ ጥቅሟን የሚያረጋግጥባቸውን ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮችን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ነበር።እነኚህም ኢትዮጵያ በአካባቢው ያላት በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ መካከል እንደ ድልድይ የምትጠቅም ብቸኛ መሬት መሆኗ እና በሕዝብ ብዛትም ሆነ በተፈጥሮ ሃብቷ ከአካባቢው ሃገራት የምታማልል መሆኗ ነበር።በሕዝብ ብዛት አንፃር ካላት ጠቀሜታ አንፃር ሶቭየት ህብረት ኢትዮጵያን እንደምትመርጥ የገለፀችበትን ሰነድ የሚያመላክተው አሁንም ከዛሬ ሰላሳ ሰባት አመት በፊት እ ኤ አቆጣጠር ግንቦት 14/1977 ዓም በሱማልያ የሶቭየት ህብረት አምባሳደር የተናገሩትን  'ዘ ኢኮኖሚስት' መፅሄት እንዲህ ፅፎት ነበር-
''መንግስቱ ኃይለማርያም ጥሩ ልጅ ነው።ሶሻሊዝም ኢትዮጵያ ውስጥ ካሸነፈ 30 ሚልዮን ወዳጆች በተጨማሪም የአሰብ እና ምፅዋ ወደብ ይኖሩናል።እናንተ ሱማሌዎች እኮ 3ሚልዮን ብቻ ናችሁ'' ነበር ያሉት።
‘Mengistu Haile Mariam is a good boy. If socialism wins in Ethiopia we will have 30 million friends there plus the ports of Assab and Massawa. You Somalis are only 3 million.’ (The Economist, May 14 1977)

እዚህ ላይ የ 3 ሚልዮን ሕዝብ አናሳነት  በፖለቲካ ስሌት አንፃር ኢትዮጵያን ዛሬም ከአካባቢው ሀገሮች በበለጠ ባላት የህዝብ ብዛት እና የተፈጥሮ ሀብት በተለየ ተመራጭ ሀገር እንደሚያደርጋት አያጠራጥርም።እዚህ ላይ ይህንን ተመራችነቷን ለመጠበቅ እና እንደሀገር እንዳትቀጥል ከገዛ መንግስቷ የሚገዳደሯት ፈተናዎች የመኖራቸውን እውነታ ሳንዘነጋ ማለት ነው።

መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ 

ይህ ከሆነ ዛሬ ሰላሳ ሰባት አመታት ተቆጥረዋል።በእነኝህ ሰላሳ ሰባት አመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሁኔታዎች ብቻ ሳይሆኑ አንድ ትውልድ አልፎ አዲስ ትውልድ ተተክቷል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ከ 30 ሚልዮን  በሶስት እጥፍ ወደ 90 ሚልዮን ተተኩሷል፣የባሕር በሯ ተዘግቷል፣ወጥ የነበረው የመንግስት ስሪት በጎሳ እና ቋንቋ ላይ በተመሰረተ አስተዳደር ተቀይሯል፣ከተሞች በመጠን ሰፍተዋል።በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ከገጠሩ ጋር ሲነፃፀር ግን በእነኝህ ሁሉ ከ ሶስት አስር አመታት በኃላም ከ 90 በመቶ ወደ 85 (83) በመቶ ነው ዝቅ ያለው።የህዝቡ የኑሮ ደረጃ እ አ አቆጣጠር በ 1970 ዎቹ ነፃነታቸውን ከተቀዳጁት የአፍሪካ ጥቁር ህዝቦች አንፃርም ገቢው ዝቅተኛ የሚባል እና ከእጅ ወደ አፍ ነው።ከላይ የተጠቀሱት 'ፋይናንሻል ታይምስ' እና 'ዘ ኢኮኖሚስት' ፅሁፎች ሲወጡ በአፍሪካ ቀንድ የነበረን አማላይነት በምድር ጦር፣በአየር ኃይል እና በባህር ኃይል የነበረን የበላይነት የተገለፀ ሲሆን ዛሬ በሕዝብ ብዛት እና ዙርያችንን ያሉት የትናንሽ ደካማ ሃገራት መኮልኮል አጉልቶ ካሳየን የበላይነት ባለፈ መድረስ የሚገባንን ደረጃ አለመድረሳችንን ለማረጋገጥ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም።

ባለፉት 37 አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የገጠማት ተግዳሮቶችን በሁለት መልክ ማስቀመጥ ይቻላል።እነርሱም የውስጥ ቁርሾ በአምባገነንነት መታገዝ እና የውጭ ግፊቶች ናቸው።የውስጥ ቁርሾው በተቻለ መጠን የሚቀልባቸው መንገዶች እንዳይኖሩ እልህ የተጋባው የአምባገነንነት እርምጃዎች በእሳት ላይ ቤንዚን የማርከፍከፍ ያክል ብዙዎች ሳያስቡት ቁርሾውን ለማባባስ ሰበብ እንዲሆኑ አደረጋቸው።ደርግ የእርስ በርስ ጦርነቶቹ በተቻለ መጠን ለማቅለል ከውስጥ የነበረበትን የህዝብ ድጋፍ ማጣት ስልጣንን ለሕዝብ በማስረከብ ሊያቀለው አልፈለገም።ይልቁንም ጦርነቶቹ የሰራዊቱን በሥራ መጠመድ ማምጣቱ የታያቸው ወገኖች እንደ መልካም እድልም ተመለከቱት።በዘመነ ኢህአዲግ/ወያኔ ደግሞ የውስጥ ቁርሾው በደርግ ዘመን ከነበረው የህዝብን ስልጣን ለሕዝብ ማስረከብ ብቻ ሳይሆን ''መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ፣ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ግንኙነት ላይ አደገኛ ጥላ አጠላ።የጎሳ ግጭቱ ከክልሎች የመሬት ግጭት አልፎ እስከ መንደር የከብቶች መሰማርያ ሜዳ ድረስ ኢትዮጵያውያን ተጋጩ።በእነኝህ የጎሳ ግጭቶች የተነሱ ፀቦችን ለማስቆም ዋናው ችግር ''የመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' መሰረት ያደረገውን የፌድራል  ስርዓት በትክክለኛ የመሬት አቀማመጥ እና የህዝቦች ታሪካዊ አሰፋፈር መሰረት ያደረገ የፌድራል ስርዓት መቀየር መሆኑ እየታወቀ ኢህአዲግ/ወያኔ የተጋጩትን የጎሳ አባላት መዳኘትን እንደ ትልቅ ግብ እየቆጠረ በዜና እወጃው ላይ በስኬት ዜናነት ማውራቱን ቀጠለ።

የመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ መዘዝ ለአፍሪካውያን እየተረፋቸው ነው

የመንግስታዊው የጎሳ ፖለቲካ ውጤት ከሀገር ውስጥ አልፎ ለጎረቤት ኬንያ የእራስ ምታት የሆነባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ።ይህም ምን ያህል ኢህአዲግ/ወያኔ ''የፌድራ ስርዓቱ ለአፍሪካ ምሳሌ ሆነ''  እያለ የሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ባዶ መሆኑን ያረጋግጣል። መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ ለቅርብ ኬንያ የየዕለት እራስ ምታት መሆኑ ፀሐይ የሞቀው ዜና ነው።ታህሳስ 27 ቀን 2004 ዓ/ ም ኢሳት ዜና ለእዚህ ጥሩ ማስረጃ ነው።ዜናው እንዲህ ይነበባል -

’በደቡብ ኢትዮጵያ የተፈጠረው የጎሳ ግጭት ድንበር ተሻግሮ ኬንያ ውስጥ የሚገኙ ጎሳዎችንም እያተራመሰ ነው ተባለ በደቡብ ኢትዮጵያ በቦረናና በገርባ ጎሳዎች መካከል ከግጦሽ መሬትና ከውሀ ጋር በተያያዘ በተነሳው ግጭት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች ተገድለዋል።
ግጭቱ ወደ ኬንያም ተስፋፋቶ በአካባቢው የሚገኙ 17 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸው ታወቋል።
ከአካባቢው ርቀት አንጻር እስካሁን ድረስ የተጠናከረ መረጃ ባይቀርብም፣ በሞያሌ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች እንደሚሉት በግጭቱ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፤ ብዙዎችም አካባቢውን እየለቀቁ ተሰደዋል።በኢትዮጵያ ሞያሌ ከተማ ደግሞ በሶማሊ እና በኦሮሞ ተወላጆች መካከል በቅርቡ የተፈጠረው ግጭት ፣ ዳግም ያገረሻል የሚል ፍርሀት መኖሩን የአካባቢው ነወራዎች ገልጠዋል።ሞያሌን የሶማሊ እና የኦሮሚያ ክልል ተወካዮች ከሁለት ከፍለው የሚያስተዳድሩዋት ሲሆን፣ በሁለቱ ብሄሮች ግጭት የከተማው ሰላም በተደጋጋሚ ሲደፈርስ ቆይቷል።
በቅርቡ ከትምህርት ቤት ንብረት ጋር በተያያዘ የተነሳውን ግጭት ተከትሎ የፌደራል ፖሊሶች አሁንም አካባቢውን እንደተቆጣጠሩት ነው።’’ የዜናው መጨረሻ

በሌላ በኩል ከውጭ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ገብተው ወደሚፈልጉት አቅጣጫ የመዘወር ግፊት የሚሰሩት ኃይላት ፍላጎት ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋብ ማለት በስተቀር ሌሎቹ ምክንያቶች ማለትም የአካባቢው እስልምና ተከታይ ሃገራት(ሳውዲ አረብያን ጨምሮ) በኢትዮጵያ ላይ የነበራቸው ግብም ሆነ ተግባራት ምንም ለውጥ አላመጡም።  ከእዚህ በተለየ የአለም ሃያላን መንግሥታት በሽብርተኝነት ጉዳይ፣በምጣኔ ሀብታቸው መዛባት እና ቻይና አዲስ አማራጭ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ በታዳጊ ሃገራት ላይ ያላቸው የበላይነት የመርገብ አዝማምያ አሳይቷል።ይህ መርገብ ግን ምናልባትም ከያዝነው አመት ጀምሮ ባለበት ላይቆይ ይችላል።የአራቱ የዓለም ኃይላት ማለትም የአሜሪካ፣የቻይና፣የአውሮፓ እና የሩስያ በግልፅ በወጣ የመገፋፋት ሂደት አለመኖር እና በተሸፈነ ዲፕሎማሲ ነገሮችን ማቀዝቀዛቸው ደካማ ሃገራት በጥቅማቸው ጉዳይ ላይ ከአንዱ ጋር የመቦደን ግዴታ  ውስጥ እንዳይገቡ እረድቷቸዋል።ይህ ሁኔታ ግን እሰከመቼ ድረስ እንደሚዘልቅ የምናየው ይሆናል።በተለይ ከባድ የምጣኔ ሀብት ቀውስ መምጣት እና እጅግ በተሳሰረው የአለም ምጣኔ ሃብት አንፃር ከአራቱ ሃያላን አንዱ ወይንም ሁለቱ አልያም ሶስቱ ተነጥለው የመሄድ አዝማምያ ከመጣ የአለም የኃይል ቁርሾ ወደ 1970ዎቹ የማይወርድበት ምክንያት አይኖርም።ምናልባት ‘ሲ ኤን ኤን’  ''ቀዝቃዛው ጦርነት'' የሚለውን የቀድሞ ፕሮግራሙን   ሰሞኑን እንደ አዲስ ልከልስልን የተነሳው በመጪው ላይ ያለው ስጋት አይሎበት ይሆን?

የኢትዮጵያ የቅርብ ወቅታዊ ተግዳሮት ምንድን ነው?

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ከ ሁለተኛው አለም ጦርነት አንስቶ  እስከ 1980ዎቹ እ አ አቆጣጠር ተጋግሎ የቆየው የቀዝቃዛው ጦርነት ኢትዮጵያ ወደራሷ የችግር ፈቺነት አቅም ሳያሸጋግር ''ለመንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' አስረክቧት ቀዘቀዘ።ቀድሞ በምዕራባውያን ትምህርት የተዋከበው የእድገት ስልት ቀጥሎ በመጣው በደርግ ሶሽያልስታዊ አስተሳሰብ ተተራምሶ ከዛሬ 22 አመት ገደማ ደግሞ በ''መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' ቅርፁም ሆነ ይዘቱ ትውልድ አሻጋሪ እንዳይሆን ሆነ።

ዛሬ የምዕራባውያን ''ሌክቸር'' መሰል አመራርም ሆነ የሶሻልስቱ አለም የማያላውስ ቀጭን ትዛዝ የኢትዮጵያ እራስ ምታቶች አይደሉም።የአካባቢ የአረብ መንግሥታት ግፊት ግን የቅርብ እና ከባድ የኢትዮጵያ ተግዳሮት ነው።ከኢህአዲግ/ወያኔ በፊት የነበሩት መንግሥታት በማዕከላዊነት ይዘውት የነበረውን የሀገር ጉዳይ በጎሳ ስለሸነሸነው ለአካባቢ ''ኢትዮጵያን አረብ ማድረግ አለብን'' እንቅስቃሴዎች እጅግ አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።ኢትዮጵያን አረባዊ የማድረጉ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በጥቁር ህዝቦች ላይም የተሞከረ እና የታቀደ ይልቁንም እስልምናን ከሃይማኖት ይልቅ ፖለቲካዊ ጥቅሙን ብቻ ነቅሶ የመንቀሳቀስ አላማ የያዘ ነው።


ኢትዮጵያን አረባዊ (እስላማዊ ሀገር ) በማድረግ ሂደት ላይ በጉልህ የተሳተፉ ውስጣዊ ኃይላት አሉ።እነርሱም-

 1/  የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስ እና ‘ፅፈኛ አጋር’ ተብዬ የጎሳ ድርጅቶቹ

  2/  ኢህአዲግ/ወያኔን እንቃወማለን የሚሉ ግን የመገንጠል አላማ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ለምሳሌ የ ዑጋዴን ነፃነት ግንበር የመሳሰሰሉ ናቸው።

እነኝህ ኃይላት የተለያዩ ይምሰሉ እንጂ ያጣላቸው የበላይ ለመሆን የሚደረግ ግፍያ ካልሆነ በቀር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው።ለምሳሌ ትግራይን የመገንጠል አላማ ይዞ በፕሮግራሙም አካቶ ይንቀሳቀስ የነበረው ህወሓት ዛሬም መንግስት ከሆነ በኃላም የቀድሞ የጎሳ ስሙን ካለመቀየሩም በላይ ለስልጣን ያበቃቸው አጋር ድርጅቶቹ ባብዛኛው በአንድም ሆነ በሌላ ኢትዮጵያን አረባዊ (እስላማዊ) ለማድረግ ከሚሹ ኃይላት በተገኘ የስልጠና፣የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ የተመሰረቱ ናቸው።ይህ ድጋፍ ዛሬም ድረስ እያገኙ ነው።

እነኝህ ኃይላት አላማቸውን ለማስፈፀም የሚሞክሩት እና የሚተገብሩት በአፈሙዝ ነው።ይህ ማለት በሌላ አገላለፅ መጭውም  የፖለቲካ መድረክ የሚስተናገደው በአፈሙዝ ስልጣን ላይ የሚወጣ የሚደመጥበት ነው ማለት ነው።አሁንም ለሰላማዊ የስልጣን ሽግግር አልታደልንም ማለት ነው።በእዚህ ሁሉ ውጥንቅት ውስጥ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነበረው አካሂድ ምን መምሰል ይገባዋል?

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣይ እርምጃ ምን መምሰል ይገባዋል? 

የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግርም ሆነ ወደ ነፃነት እና ዲሞክራሲ የሚደረገው ጉዞ በሁለት ጉዳዮች  የተወጠረ ነው።እነኝህ ሁለት ጉዳዮች ላይ የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች ግልፅ እና ጥርት ያለ መስመር ማሳየት አለባቸው።ይህ መስመር ዛሬ ያለውን ጥቂቱን ወይም ብዙውን ያስከፋል ወይንም ያስደስታል ከሚል አንፃር ሳይሆን መሰመር ያለበት መጪውን ዘመን ያገናዘበ ብሎም አዋጪ እና አማራጭ መስመር ከመሆን አንፃር ብቻ  መታየት ይገባዋል።እነኝህ ሁለት ጉዳዮች-

1/ ባለፈ ታሪክነት ማንነት ላይ የጠራ አቋም ማሳየት

2/  ከባለፈ ታሪክ፣ባህል፣ማንነት፣ከአሁኑ እና ከመጪው ትውልድ ማንነት አንፃር ወደፊት ሊኖር ስለሚገባው የመንግስት ቅርፅ በግልፅ ማሳወቅ


1/ ባለፈ ታሪክነት ማንነት ላይ የጠራ አቋም ማሳየት

የኢትዮጵያን  ያለፈ ታሪክ በአንድ ገላጭ አረፍተ ነገር ሊጠቃለል ወይንም ይህንን ከማለት ውጭ ይህንን ማለት አይቻልም የሚል አስተሳሰብ የሚራመድበት ወቅት ላይ አይደለንም።በሌላ በኩል ደግሞ በድፍኑ የጋራ የሚያደርገንን ታሪክን እንደምናምን ቆጥሮ በዝምታ እና በብዥታ መቀጠልም ህዝብን ከሚመራ የፖለቲካ ኃይል የሚጠበቅ አይደለም።ይህ ያለንበት ወቅት የአንድን የፖለቲካ ድርጅት ባለፈ ታሪክ ላይ ያለው አመለካከት በራሱ የፖለቲካ ፓርቲውን የወደፊት ራዕይ የሚያመላክት ያክል እንደማሳያ እየሆነ ለመምጣቱ ብዙ ማሳይዎችን መጥቀስ ይቻላል።

እዚህ ላይ ትልቁ ጉዳይ ዛሬ ያለው ትውልድ ስለአለፈው በጎም ሆነ በጎ ያልሆነ ታሪክ ቅንጣት ታክል ተጠያቂ ሊሆን አይችልም።እርሱ የሚጠየቀው ዛሬ በሚሰራው እና ነገ ሊሰራ ስለሚያስበው ታሪክ ነው።በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እና ታሪክን ተመርኩዘው ነገን በሚማትሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ዘንድ ሁለት አይነት ስሜቶች ይንፀባረቃሉ።

አስተሳሰብ አንድ - የባለፈው ታሪክን በዛሬ መነፀር የሚመለከት

የመጀመርያው ክፍል ባለፉት ዘመናት የተደረጉትን ታሪካዊ ሁኔታዎች ዛሬ 21ኛው ክ/ዘመን ላይ ሆኖ ለመገምገም የምፈልገው ነው።የዛሬ 600 አመት አፄ ዘርያቆብ ለምን እንዲህ አላሰቡም? እንዴት እንዲህ ይላሉ? እያለ በወቅቱ የነበረውን ስነ-ልቦና የማኅበረሰቡን ባህል፣እምነት እና ወግ ሳያጠና እንዲሁ ለዛሬ የኢትዮጵያ እሷነት መነሻ ሰበብ ሲፈልግ ከድሮ ታሪክ ጋር እያዛመደ መማሰን ሙያ ተብሎ ተይዟል።ይህ ክፍል ትልቁ ግቡ ስልጣን ነው።ስልጣን ለመያዝ ደግሞ ዛሬም ሆነ ነገ እንቅፋት ይሆኑኛል የሚላቸው ሁለት ''ደንቃራዎች'' ከፊቱ ይታዩታል። እነርሱም- በረጅም ዘመናት የተገነባው ያለፈው እና አሁን በሕዝቡ ልብ ውስጥ ያለው ኢትዮጵያዊነት ነው።ይህ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ ባለፈ ማንነት፣ታሪክ፣ባህል እና እምነት ላይ የተመሰረተ ነው።ስለዚህ ዛሬ ሰበብ አስባብ ፈልጎ ያለፈ ማንነትን የሚንዱ ናቸው ያላቸውን የህዝብ ግጭቶችን፣በነበሩበት ጊዜ ጀግና ያስብሉ የነበሩ በ 21ኛው ክ/ዘመን ግን ክፉ ተግባራትን እና ፈፅመው የሌሉ ታሪኮችን በመፍጠር የኢትዮጵያዊነት መሰረቶች እንዲናዱ ይሞክራል።

ለምሳሌ የብሔር ብሔረሰቦች ጉዳይ እና ፌድራሊዝም አስተዳደሮች  በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ ባልተፈጠሩበት ዘመን ለምን አልታወጁም ነበር? በሚል ውኃ ቀጠነ ንግግር ኢትዮጵያዊነትን ይሳደባል።ይልቁን ፌድራልዝም በአለም ሳይታወቅ እነ አባ ጅፋር የራሳቸውን ግዛት በራሳቸው ያስተዳድሩ እንደነበር ግን በጋራ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በሚያገናኛቸው ጉዳይ ላይ አብረው ይሰሩ እንደነበር አያስተውልም።በዚህ ክፍል ውስጥ የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስትን ጨምሮ በፅንፈኛ የእስልምና እምነት የፖለቲካ አላማቸውን ለማሳካት እስከሚፈልጉት ኃይሎች ድረስ የባለፈውን ታርክ በዛሬ መነፀር እያዩ ህዝብን ማደናገር እና የዛሬውን ትውልድ በማያውቀው ጉዳይ አበሳውን ሲያሳዩት መመልከት የተለመደ ነው።አሁን ባለንበት ዘመን በእዚህ አስተሳሰብ ሺዎች ተገለዋል፣ሌሎች አያሌ ሺዎች ከመኖርያቸው ተፈናቅለዋል።ከእዚህ ሲዘል ደግሞ ማስረጃ ለሌለው ተረት ሁሉ ሃውልት ይሰራ ባይ ነው። የእዚህ አስተሳሰብ አራማጆች ዋና ግባቸው ''እኛ ስልጣን ላይ ከሌለን እና የምንፈልገውን ካልፈፅምን ጭር አይልም ባዮች ናቸው።ለእዚህ እኩይ ተግባር የምተባበራቸው ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይል ጋር ለመተባበር ዝግጁ ናቸው።ኢትዮጵያዊነት፣አንድነት እና ህብረት ሲጠነክር ይደነግጣሉ።ምክንያት የእነርሱ አስተሳሰብ በጠንካራ ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ፊት ሞገስ እንደሌለው እና እነርሱንም ወደ ስልጣን ኮርቻ ላይ እንደማያፈናጥጣቸው ይረዳሉና።

አስተሳሰብ  ሁለት - የባለፈው በጎውን ይዘን ክፉውን ወቅሰን ያሁኑን ትውልድ ተጠያቂ ሳናደርግ ለወደፊቱ እናስብ

ሁለተኛው አስተሳሰብ የብዙ ኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ነው።ኢትዮጵያ በአንድ ምሽት በቤተ-ሙከራ ውስጥ የተሰራች ሀገር አይደለችም።የብዙ ዘመናት የህዝቦቿ አብሮ የመኖር፣የመተሳሰብ፣የመሰደድ፣የጦርነት፣የሰላም ሁሉ ውጤት ነች።ባለፈው ታሪካችን ብዙ አንድ የሚያደርጉን ነገሮች አሉ።ብዙ የዛሬ ማንነታችን ላይ አሻራ ያላቸው ማንም በቀላሉ እንዲነቅላቸው የማይፈቀዱለት የጋራ ታሪክ አለን።በአንፃሩ ደግሞ የሚያሳዝኑ ታሪኮች ባለቤትም ነን።ዛሬ የሚያስፈልገን ያለፈው አንድ የሚያደርጉንን አጉልተን ባለፈው ለተሰሩት ስህተቶች ምንም ተጠያቂ ባንሆን ወደፊት እንዳይሰሩ አርመን መኖር ብቸኛ አማራጫችን ነው።ከእዚህ በዘለለ ባለፈ አሳዛኝ ታሪክ ሊሽር የሚችለው በዛሬው ትልውድ በጎ የታሪክ ተግባር ነው ብለው ያምናሉ።

አሁን በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የሚታዩት አስተሳሰቦች ከላይ ከተጠቀሱት ከሁለቱ አንዱ እንደሆኑ ይታወቃል።የኢትዮጵያ ሕዝብም የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያላቸውን ግልፅ አስተያየት እና ይህ እይታቸው የነገውን የሀገራችንን መፃኢ ዕድል ማሳያ እንደሆነ አመላካች ነው።ኢትዮጵያ ነገ እንዴት እንድትሆን እንደሚፈልጉ ሁሉ የባለፈው ዕይታቸውም በግልፅ መቀመጥ ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።


 ከባለፈ ታሪክ፣ባህል፣ማንነት፣ከአሁኑ እና ከመጪው ትውልድ ማንነት አንፃር ወደፊት ሊኖር ስለሚገባው የመንግስት ቅርፅ በግልፅ ማሳወቅ


አሁን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ፣በሰላማዊ ትግልም ሆነ በትጥቅ ትግል ላይ እንደሆኑ የሚነገርላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ የጋር ነጥብ እና አሰልቺ ቋንቋ አለ። ይሄውም ''ዲሞክራሲያዊ የሆነ መንግስት'' ይመሰረታል የሚል ነው።ደርግም ሆነ ኢህአዲግ/ወያኔ ''ዲሞክራሲያዊ'' ያሉትን መንግስት ኢትዮጵያ እንዳጣጠመች ነግረውናል።ነገም ይህንኑ ተረኛው ስደግምልን መስማት ምንኛ ዘግናኝ ታሪክ መሆኑን ለአፍታም ማሰብ ይከብዳል።የብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሰረታዊ ችግር እና ሚልዮኖችን በአጭር ጊዜ ማሰለፍ ያልቻሉት ነገ የሚመሰርቱት መንግስትን በደፈናው ''ዲሞክራሳዊ'' ከማለት ባለለፈ መልክ አሁን ያለውንም ሆነ መጪውን ትውልድ የሚያማልል የኢትዮጵያን ታሪካዊ ዳራ ያገናዘበ ብሎም ነገ ተመንጥቃ የምታድግበትን አዲስ ሃሳብ ማፍለቅ አልቻለም።ኢህአዲግ/ወያኔ በትጥቅ ትግል ላይ ሳለም ይህንን ማድረግ አልቻለም ነበር።ግን ያስቀመጠው አንድ ሕዝቡን ያማለለ ጉዳይ ነበር ይሄውም ደርግ ይገረሰሳል የሚል ራዕይ ነበር።

ራዕይ ያሸፍታል፣ራዕይ ካላገኙት በቀር እረፍት ይነሳል፣ ራዕይ አያስበላም፣አያስጠጣም፣ዛሬን በጨለማ ያሳያል ነገን ግን በብሩህ ብርሃን አንቆጥቁጦ ያሳያል።የፖለቲካ ራዕዩን በትክክል የገለፀ እና ያ ራዕይ ደግሞ የሕዝብ ስስ ብልትን የነካ ሲሆን ሚልዮኖችን ያነቃንቃል፣ይፈነቅላል፣ሺ መትረጌስ ቢደገን ተራምዶት ይሄዳል።በትክክል የተቀመረ የፖለቲካ ራዕይ እንዲሁ ነው።ከእዚህ በተለየ ''ዲሞክራሲያዊ'' መንግስት ይመጣል በሚል ንግግር የትም አይደረሰም።በ 1997 ምርጫ ቅንጅት የሰራው ተአምር ይህ ነው።የራሱ ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር ሳይኖረው የህዝቡን ሥሥ ብልት የሚነካ ጉድለቱን የሚሞላ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ራዕይ ብልጭ አደረገ በአንድ ቀን ሚያዝያ 30/1997 ዓም ሰልፍ ብቻ በአዲስ አበባ ከ አንድ ሚልዮን ሕዝብ በላይ ደግፎት ተሰለፈ።

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ህዝብን የሚንጥ እና ሚልዮኖችን ከጎናቸው የሚያሰልፍ የፖለቲካ ራዕይ ለሕዝቡ ማሳየት ለምን አልቻሉም?


ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች በፖለቲካ ፓርቲዎቹ ላይ ይስተዋላል። አንደኛው የአመሰራረታቸው ሂደት ችግር ሲሆን ሁለተኛው የሕዝቡን ባህል፣እምነት እና ታሪክ ያገናዘበ ፕሮግራም ለማስተዋወቅ ድፍረት ማጣት ናቸው።

ሀ/ የአመሰራረታቸው ሂደት ችግር 


የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን በሰላማውም ሆነ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉት መካከል ነገ ሊያመጡልን ይችላሉ በምንላቸው በጎ ነገሮች ላይ አንዳቸውን ካንዳቸው የምንለይበት ነጥብ ካጣን ቆይተናል።ብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲመሰረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና እና ብቸኛ ችግር የዲሞክራሲ እጦት ችግር ብቻ ነው በሚል ትምህርት ቤት በተማሩት የምዕራቡ ፍልስፍና መግባብያነት ብቻ ይመሰረታሉ ወደ ትግል ይገባሉ።ኢትዮጵያን የሚያህል ከሶስት ሺህ አመታት በላይ የመንግስት ስሪት ያላት ሀገር ግን   ችግሯ የዲሞክራሲ ብቻ ሊሆን አይችልም።የማንነት መከበር፣በራስ ላይ ተመስርቶ የመፍጠር ክህሎት ማሳየት፣የራሷ የሆኑ የፖለቲካ ፍልስፍና እና ምጣኔ ሃብታዊ ተምኔቶች ማሳየት እነኝህ ሁሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መንገዱን በተጠና እና ሊደረስበት በሚችል ራዕይ ለሕዝቡ እንዲያሳዩ ተደርገው አልተመሰረቱም።ለእያንዳንዱ ወቅታውም ሆነ የቆየ የሀገራችን ችግር ''የዲሞክራሲ እጦት'' ነው ችግሩ እያሉ ህዝብን ማዘናጋት ለማንም አይበጅም።

ለ/  የሕዝቡን ባህል፣እምነት እና ታሪክ ያገናዘበ ፕሮግራም ለማስተዋወቅ ድፍረት ማጣት


ይህ ችግር ከመጀመርያው ከአመሰራረት እና ችግርን ከዲሞክራሲ ጋር  ብቻ በማያይዝ ላይ በተመሰረተ የፖለቲካ ፓርቲ አንፃር የሚከሰት ይልቁንም ፕሮግራሙ እራሱ ይህኛውን ቡድን እዳያስከፋ፣ያኛው እንዲደግፍ ወዘተ በሚል ፍርሃት የተሸበበ ማዕከላዊ መንገድ የያዘ ፕሮግራም ለመፈለግ የሚታታር አካህያድ ውጤት ነው።የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የህዝቡን ባህል፣እምነት እና ታሪክ ያገናዘብ የፖለቲካ ፕሮግራም ማንንም ከፋው ወይንም ደስ አለው ሳይሉ በእውነታው ላይ ተመስርተው እንዳይቀርፁ የሚፈሯቸው ያለፉት 40 አመታት የሀገራችን የፖለቲካ መድረክ ክስተትን ነው።ኢትዮጵያ በመንግሥትነት የኖረችው አሁንም ልድገመው ላለፉት 40 አመታት አይደለም ለ ሶስት ሺህ አመታት ከዛም በላይ ነው።

የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራሞች ሲቀረፁ ካለምንም ማጋነን መሰረት ያደረጉት ያለፉት 40 አመታት የአለማችንን እና የሀገራችንን የፖለቲካ የተደጋገመ እና አሰልቺ ቋንቋ ነው።የኢትዮጵያ ስነ-መንግስት ታሪክ ግን ሰፊ፣ትልቅ እና ለቀሪው አለም ብዙ ቁም ነገሮችን ያበረከተ ነው።ለሙሴ አስተዳደርን ያስተማረ ኢትዮጵያዊው ዮቶርን የሚያስበው የለም።መገናኛ በሌለበት ዘመን የኢትዮጵያ የስነ-መንግስት ጥበብ መዋቅሩ ምን እንደነበር ሊመለከት የሚፈልግ የፖለቲካ ፓርቲ የለም።አውሮፓ እና አሜሪካ የተፃፉ መፃህፍትን ግን ለመጥቀስ የምያክለን የለም። ለአለም ልዩ ልዩ መንግሥታት ሕጎች የኢትዮጵያ 'ፍትሃ ነገስት' በምን መልክ ለግብአትነት አውሮፓውያን እንድተጠቀሙበት  ሊመረምር የሚፈልግ የለም።ኢትዮጵያ ሊኖራት የሚገባው መንግስት ሕዝብ ሊታገልለት እና ሊሞትለት የሚችለው ልዩ ጥበብ እኛው ጋር እንደተደበቀ ለሕዝቡ ገልፆ ካለፍርሃት ሊነገረው፣ሊመራው እና ለእድገት ሊያበቃው የሚችል ጥበብ እንደሚያስፈልገው የፖለቲካ ፓርቲዎች ካላሰቡ ዛሬ የአስተሳሰብ ለውጥ የማመንጫ ሰዓት ላይ ይመስሉኛል። ከእዚህ በኃላ ኢትዮጵያውያን የምሸከሙት የመከራ ጫንቃም ሆነ የአስተሳሰብ ድግግሞሽ ጆሮ ያላቸው አይመስለኝም።

ባጠቃላይ 


የኢትዮጵያ የመንግስት ስሪት ቅጥ ባጣ አምባገነኖች እጅ ከወደቀ አስርተ አመታት አስቆጠረ።ይብሱን ዛሬ ሀገራችን ሕልውናዋን በሚፈታተን ''መንግስታዊ የጎሳ ፖለቲካ'' ውስጥ ተነክራ ህዝቧ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ውስጥ ይገኛል።ታሪካዊ ጠላቶቿ የዛሬ 40 አመት የደገሱትን ድግስ ዛሬም አልቀየሩም።ኢትዮጵያን አረባዊ ለማድረግም ሆነ የፅንፈኛ እስልምና አላማ ያነገቡ ኃይሎችአንዴ  በኦሮሞ ሕዝብ ስም ሌላ ጊዜ ባለፈ ታሪክ ስም እያሉ የሚፈልጉትን ግብ ለማድረስ ምቹ ሁኔታዎችን እየፈጠሩ ነው።የኢህአዲግ/ወያኔ መንግስትም እንደ ማስፈራርያ ወጥ በብዙ መልኩ ድጋፉን ሲሰጣቸው እና ''ከእኔ ጋር ከልሆናችሁ አደገኛ ሁኔታ ይፈጠራል'' እያለ ሲያስፈራራን ዘመናት አልፏል።አቦይ ስብሐት ይህንን ጉዳይ ደጋግመው  ለተለያዩ የዜና አውታሮች ገልፀውታል።

የህወሓት ፈጣሪው አቦይ ስብሐት አንድ ወቅት ለኢሳት በሰጡት ዘገባ ላይ '' ማንም በኃይል ስልጣን ሊይዝ አይችልም።ከሆነ ሌላው ክልል የራሱ ምክርቤት፣በጀት ወዘተ አለው የራሱን አማራጭ ይወስዳል።ስልጣን የሚይዝ ኃይል አዲስ አበባን ብቻ ይዞ ይቀመጣል እንዴ?'' በማለት ከኢህአዲግ በኃላ ኢትዮጵያ እንደምትበታተን ሁሉም የእራሱን መንግስት እንደሚያውጅ በተዘዋዋሪ ነግረውናል።አቦይ 22 አመት ቆይተው ሕዝቡን አለማወቃቸው አይደንቅም።

ቁም ነገሩ ግን ይህ አይደለም የአቦይ ንግግር የሚያመለክተው ኢህአዲግ/ወያኔ ኢትዮጵያን እየስራት ያለው ከእርሱ ውጭ እንዳትኖር ''እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል'' መርህ ላይ ተመስርቶ መሆኑን ነው።እዚህ ላይ ነው የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች የህዝቡን ያለፈ ታሪክ፣እምነት፣ባህል እና ጥበብ ያገናዘበ አዲስ የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብታዊ  ራዕይ የሚያሳይ ፕሮግራም (''ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ'' ከሚል መዝሙር ባለፈ) ማሳየት ያለባቸው።

በመሆኑም የተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች እና ፓርቲዎች አዲስ እና ባለ ራዕይ ፕሮግራማቸውን በተናጥል ወይንም ግንባር በመፍጠር አዲስ መንፈስ በመፍጠር ማሳየት ይገባቸዋል።ይህ አዲሱ ሀሳባቸው ኢትዮጵያን በጎሳ እና በፅንፈኛ የእስልምና አስተሳሰብ ለመምራት የሚፈልጉትን ለማቀፍ አይድከም።እነኝህን ኃይሎች በሚቃረን መልኩ የህዝቡን የልብ ትርታ ባዳመጠ እና የማይረገጥ የመሰላቸውን በመርገጥ ለድል ይበቃሉ።ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ በአንድነት ኃይሎች እና በበታኝ ኃይሎች ጎራ ተከፍሏል።ከአንድነት ኃይሎች ጎራ የዲሞክራሲ ጉዳይ ብቻ ሲለፈፍ ከበታኝ ኃይሎች በኩል ደግሞ የጎሰኝነት እና የፅንፈኛ እስልምና አስተሳሰቦች ይንፀባረቃሉ።አሁን ጥያቄው የአንድነት ኃይሎች ኢትዮጵያዊ ታሪክ፣እምነት እና ፍልስፍና የያዘ ጥበብ የተላበሰ ራዕይ ይዘው መውጣት እና ሕዝቡን ከአዙሪት 'ዲሞክራሲ' ከሚል ዲስኩር ማላቀቅ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ዲሞክራሲ አያስፈልገውም እያልኩ አይደለም።የህልውናው ጥያቄ ሲመጣ ግን ኢትዮጵያን በሁለት እግር የሚያቆም እና የሚያራምድ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ፍልስፍና በእጅጉ ተርቧል።ያን ጊዜ በኩራት እና በድፍረትይነሳል።በእዚህም አያቆምም  የበታኝ አስተሳሰብ የተጠናወታቸውን በምክርም በግሳፄም ያስተካክላል።የሩቅ ጠላቶቹን ያሳፍራል።የሚፈለገው ልማት እና እድገትም በራሱ ጊዜ መስመር ውስጥ ይስገባዋል።ከእዝያ በኃላ ማን ያቆመናል?


ጉዳያችን /Gudayachn
ጥር 5/2006 ዓም (ጃንዋሪ 2014)

ይህንን ፅሑፍ በየትኛውም ድረ-ገፅ ላይ ማውጣት ይቻላል።ግን ምንጩን ጉዳያችን ጡመራ መሆኑን መግለፅ ጨዋነት ነው።ፅሁፉ በመጀመርያ የወጣው በ 2006 (2014 እ ኤ አ) ነበር።





Friday, September 15, 2017

በቅማንት ስም የታቀደው የድምፅ መስጠት ተንኮል እንዳይሳካ ማድረግ ትውልድን ከእልቂት መታደግ ነው።


ጉዳያችን / Gudayachn 
መስከረም 6፣2010 ዓም (ሴፕቴምበር 16፣2017 ዓም)


የጎንደር አብያተ መንግሥታት 

የእንግሊዝ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ቢቢሲ) መስከረም 5፣2010 ዓም በድረ ገፁ ላይ ''ከኦሮሞ እና ሱማሌ ክልል ግጭት ጀርባ ምን አለ?'' (What is behind clashes in Ethiopia's Oromia and Somali regions) በሚል ርዕስ በዘገበው ዜና ላይ ከግጭቱ ጀርባ የሚጠቀሰው አንዱ እና አይነተኛ ምክንያት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2004 ዓም በ420 ቀበሌዎች በተደረገ የሕዝብ ውሳኔ ድምፅ መሰረት 80% የሚሆነው ቀበሌ ወደ ኦሮምያ መከለሉን እና እስከ አሁን ድረስ ለ10 ዓመት ወደ ተግባር አለመተርጎሙን ይገልጣል። ቢቢሲ እንደምክንያት ያደረገው ተግባራዊ አለምሆኑን ይበል እንጂ  የችግሩ መንስኤ ግን በህወሓት አስተባባሪነት በኦህዴድ እና አቻ የህወሓት ሸሪክ ድርጅቶች አማካይነት ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የስርዓቱ አንዱ መንገድ ሆኖ እያገለገለ ያለው በአዋሳኝ ድንበሮች እየተፈለገ የድምፅ መስጠት ስርዓት አንዱ የግጭት ማስነሻ  የተለመደ ሥራ መሆኑን አመላካች ነው። የድምፅ መስጠቱ ተግባር በኦሮምኛ እና ሱማልኝ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን መካከል የግጭት ሰበብ ተደርጎ አንዱ የማጣያ መንገድ ከሆነ በመጪው እሁድ በጎንደር ቅማንት እና ዐማራን ለመለያየት በተሸረበ ተንኮል ድምፅ እንዲሰጥ የመወሰኑ አንዱ እና ዋና ዓላማ በኦሮምኛ እና ሱማልኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን መሃከል እንደተፈጠረው ያለ ግጭት መፍጠር እና ሕዝብ ደም እንዲቃባ ማድረግ እንደሆነ በሚገባ መረዳት ይቻላል። 

በጎንደር ሕዝብ መካከል ግጭት ፈጥሮ ሕዝቡን ወደማያባራ ግጭት ለመምራት የታቀደውን ድምፅ የመስጠት ሂደት በአሁኑ ጊዜ በጎንደር ሁሉም አካባቢ የሚኖር ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ ተቃውሞታል። ሕዝብ አንለያይም ህወሓት ደግሞ ተለያዩ ሙግት ጎንደርን በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከቷታል። እዚህ ላይ መገንዘብ የሚገባው በጎንደር የነበረው ቅራኔ የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ያለውን መሬት ወደ ትግራይ የመከለል እና ያለመከለል ጉዳይ እና የዐማራ ማንነት ይከበርልኝ ጥያቄ እንጂ የቅማንት እና ዐማራ ጉዳይ የሚል የግጭት አርዕስት ፈፅሞ የአካባቢው የልዩነት መነሻ እንዳልነበር ነው።ሆኖም ግን ህወሓት የሰሜን ጎንደርን ለሶስት ለመክፈል እና ቅማንት ከዐማራ እንዲለያይ የሚሰራ ድምፅ ሕዝብ እንዲሰጥ የሚል አጀንዳ የቀረፀው ከእዚህ በፊት በሁለቱ መካከል ልዩነት ለመፍጠር  ከማኅበራዊ ሚድያ እስከ ገጠር ወረዳ የሚገኙ ካድሬዎች በኩል ሙከራ አድርጎ ከከሸፈ በኃላ ነው። 

በጎንደር በመጪው እሁድ ህወሓት ያቀደው ህዝብን ከህዝብ የመለያየት እና የማያባራ ግጭት የመፍጠርያ እኩይ ተግባር ማሳካት ማለት ለአሁኑ ብቻ ሳይሆን ለመጪው ትውልድ መቃብር መቆፈር ማለት ነው። ይህ ማለት ቅማንት በቅማንትነቱ የእራሱ መብት እና ባህል የመጠበቅ መብት የለውም ማለት አይደለም። ሆኖም ግን ህዝቡ በሀገር ሽማግሌ እና ለሺህ ዓመታት በኖረበት ዘይቤ የሚያስፈልገውን መብት ከወንድሙ እና ባህሉን መለየት ከማይቻለው የዐማራ ሕዝብ ጋር በተመቸው መንገድ እና በሰከነ ሁኔታ የሚመክርበት እንጂ የህወሓት አደገኛ የዘር ፍጅት መንዣ መሳርያ ለመሆን አይፈቅድም። በቅማንት ስም የታቀደው የድምፅ መስጠት ተንኮል እንዳይሳካ ማድረግ ትውልድን ከእልቂት መታደግ ነው።በመጨረሻም የጎንደር ኅብረት የህወሓትን የመለያየት ድምፅ ውሳኔ አስመልክቶ የጎንደር ሕዝብ እንዲደርሰው በላከው አስራ ሶስተኛ መልዕክት ''የፋሽሽቱ ወያኔ ጎንደርን የመከፋፈል አደገኛ ዘመቻ ኢትዮጵያን የማፈራረስ የመጨረሻው ደወል ነው'' በሚል ርዕስ ስር ባስተላለፈው መልዕክት የድርጊቱ መክሸፍ ትውልድን መታደግ መሆኑን አበክሮ ባስነበበት አንቀፅ ማስታወሻዬን እገታልሁ።እንዲህ ይነበባል : -

''ህዝቡ መከፋፈልን አንሻም ብሎ የተቃወመዉን ሕዝባዊ አቋም ወያኔ ከቁም ነገር ሳይቆጥር፤ አብዛኛዉን የክልል ተወካዮችን ተቃዉሞ ድምጽ ቀልብሶ በማስፈራራት የሃይል የበላይነቱን ለማሳየት በፌደራል ስም ጎንደርን ለመከፋፈል የሚያካሂደዉ ዘመቻ የመጨረሻ የስራቱ መቃብር ሊሆን እንደሚችል እና እራሱን በራሱ ለማጥፋት እያፋጠነ መሆኑን እንደገና የሞት መርዶ እርሙን እንዲያወጣ በጥብቅ እናሳስባለን። ጎንደርን ሕዝብ ታሪካዊ አንድነት ጠምዝዞ በጉልበት ለማንበርከክ የሚፈጸም ተደጋጋሚ ሥልጣንን ተገን ያደረገ የጥፋት ዘመቻ ለትግራይ ነጻ አዉጭ ግንባር የሞት ከፈን ከመሆን ሌላ የጥፋት ሴራዉን ሊያሳካ አይችልም''' የጎንደር ኅብረት  ለጎንደር ሕዝብ ያስተላለፈው ቁጥር 13 መልዕክት (የፋሽሽቱ ወያኔ ጎንደርን የመከፋፈል አደገኛ ዘመቻ ኢትዮጵያን የማፈራረስ የመጨረሻው ደወል ነው። ይድረስ ለጎንደር ህዝብ ቁጥር 13)

ሕፃን ሳዶር የነገው ትውልድን ስሜት ታሳያለች 


ጉዳያችን GUDAYACHN 

 www.gudayachn.com

Thursday, September 7, 2017

በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ የድንበር ውል አደረግን ሲሉህ ተቀምጠህ ለምትመለከት ትውልድ - ሞትህ ዛሬ መሆኑን ብታውቀው መፈጠርህን ትጠላ ነበር

አቶ አንዳርጋቸው እና አቶ ዓባይ የድንበር ስምምነት አደረግን ብለው ሲያውጁ 

ጉዳያችን / Gudayachn
ጳጉሜን 3 / 2009 ዓም (ሴፕቴምበር 8፣2017)


  • አሁን ወቅቱ ህወሓት የድንበር ውል አደረኩ እያለ በስማችን ሲነግድ በቴሌቭዥን መስኮት እየተመለከትን ከንፈር የምንመጥበት ሳይሆን አንተ ያሰመርከው የጎሰኞችን ድንበር አንቀበልም።በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ የድንበር አጥር ሊኖር አይገባም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብቱ ሊጠበቅ ይገባል ብለን በፅናት የምንነሳበት ወቅት ነው።
ኢትዮጵያ በህወሓት እና ግብረ አበሮቹ ትናንሽ አዕምሮ ፈርሳ አብቅታለች።ምድሯን በጎሳ ከፋፍለው ድንበር ያሉትን ሰረተው፣ የፈለክበት ተንቀሳቅሰህ እንዳትሰራ መታወቂያህ ላይ የጎሳ ስም ለጥፈውልህ በሕይወት አለሁ ካልክ ተሳስተሃል።ገዢዎች ዙርያህን ምን እየሰሩ እንዳሉ አልታየህም እንጂ መቃብርህን በግሬደር እየቆፈሩልህ ነው።ጥንርሳቸውን ብልጭ እያደረጉ እያሳዩህ የትኛው መቃብር ላንተ እንደሚስማማህ በእጃቸው ሲያማርጡህ ትንሽ የመደንገጥ ምልክት አታይባቸውም።ከእነርሱ ይልቅ ያንተ መደንዘዝ ያስደነግጣል።ከእነርሱ መደናበር እና አረመኔነት ይልቅ ያንተ በእራስህ እና በልጆችህ ላይ የተደገሰውን የጎሰኞች ድግስ ከቁሌቱ ትንሽ ለአፍንጫህ እንዴት እንዳልሸተተህ በቁም ያስበረግጋል።

ትናንት ጳጉሜን 2፣2009 ዓም የዐማራ ክልልን እወክላለሁ ያሉት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና ትግራይን እንደሰም አቅልጨ እንደገል ቀጥቅጨ የምገዛ ነኝ የሚሉት አቶ አባይ ወልዱ በዐማራ እና ትግራይ መካከል ታሪካዊ የድንበር ውል ተደረገ ብለው እንደ ሁለት የተለያየ ሀገሮች ውል እያስጨበጨቡ እና በሰበር ዜናነት በመገናኛ ብዙሃን ለቀው ምሽቱን የድራማ ምሽት አድረገውት አምሽተዋል። " ውሃ ሲወስድ አሳስቆ' እንዲሉ ሁሉም የውሉን አደገኛ ጥላ ከመመልከት ይልቅ ተስማሙ አልተስማሙም እያለ ማውራቱን ቀጥሏል። ከእዚህ ሁሉ ይልቅ ግን ህወሓት እና አጫፋሪው ብአዴን የህዝቡ ተወካይ ናቸው? ሕዝቡ የድንበር ግጭት ነበረበት? ግጭቱን እንደላብራቶሪ ፈጥረው እና አሳድገው የህዝብ ደም እንዲፈስ ያደረጉ የችግሩ መንስኤዎች እራሳቸው አይደሉም? ለመሆኑ የጎሳ ፈድራሊዝም ኢትዮጵያን ወደ እልቂት እየመራት መሆኑን ከበቂ በላይ ማስረጃ የለም? የትግራይም ሆነ የዐማራ ሕዝብ ለሺህ ዓመታት ሲኖር  ተከባብሮ ሲጣላ እየታረቀ የኖረ ሕዝብ አይደለም? በየትኛው የድንበር ውል ነው ለሺህ ዓመታት የሁለቱ ህዝቦች የኖሩት? የትኛው የውል ስምምነት ነው  የወልቃይት ሕዝብ ሽሬ ገበያ  ገብቶ ከብቱን እየሸጠ  የሽሬም ነጋዴ ወርቅ ለጎንደር ገበያ እየሸጠ እንዲኖር ያደረገው? በጣም በሕዝብ ላይ የተደረገ ሸፍጥ ነው።

በትግራይ እና ዐማራ ሕዝብ መካከል ልዩነት ሲፈጥር አይደለም በ1967 ዓም ማኔፈስቶው (እስካሁን ይህ ማነፈስቶ ተሽሯል የሚል ከህወሓት በኩል አልተሰማም ) የዐማራ ሕዝብን " ጠላት" በሚል ቃል በቃል ያስቀመጠ ህወሓት ኢትዮጵያን በጎሳ ሸንሽኖ የድንበር ውሎች ተደረጉ እያለ ቆይቶ የሚፈነዳ ቦንብ ሲያስቀምጥልህ ተቀምጠህ ለምትመለከት አንተ ትውልድ የመከራ ዘመንህን እያረዘምከው መሆኑን ማወቅ አለብህ። ህወሓት የድንበር ውል እያለ ሲያሳየን በዐማራ እና ትግራይ መካከል የመጀመርያ አይደለም።ከሳምንታት በፊት በኦሮሞ እና ሱማሌ መካከል የድንበር ውል ተደረገ የሚል  ዜና መልቀቁ አይዘነጋም።ሆኖም ከእዚህ ውል ተደረገ በተባለ ማግስት ጀምሮ በሁለት አካባቢ ነዋሪዎች መካከል የለየለት ጦርነት እስከአሁኑ ሰዓት ድረስ እየተደረገ ሲሆን የህወሓት ወታደሮች አድሏዊ በሆነ መልክ የሚጫወቱት አደገኛ ጫወታ ህዝብን ያሳዘነ ጉዳይ ነው።በእዚህ ግጭት ውስጥ ተራ የህዝብ ለሕዝብ መጨራረስ በቀል የታየ ሲሆን በትናንትናው እለትም በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሜኢሶን  ከተማ ትምህርት ቤት ተመዝግበው ወደ ቤታቸው የሚመለሱ ተማሪዎች ላይ በተጣለ ቦንብ አሰቃቂ አደጋ በተማሪዎች ላይ መድረሱ ይታወቃል።ይህ እንግዲህ የጎሳ ፖለቲካው አንዱ እና የቅርቡ ውጤት ነው። 

በዐማራ እና ትግራይ መካከል ውል ተፈረመ በተባለ በሰዓታት ውስጥ ሁለቱም ክልሎች የመገናኛ ብዙሃን በእየራሳቸው የሚጣረስ ዜና ይዘው ከመውጣታቸው በላይ ሁለቱም ተመሳሳይ ቦታዎች ወደ እኔ ተጠቃለሉ የሚል ዘገባ ይዘው ወጥተዋል። ይህ በእራሱ እንደ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነፃነት እና አንድነት ተምሳሌ ለሆነች ሀገር የመጨረሻ የውርደት ደረጃ ነው። ለነገሩ ሀገሪቱ ሳትሆን የውርደት ሸማው በእዚህ ዘመን ላለን ትውልዶች ነው።በገዛ ሀገራችን ድንበር ሲከለል ድንበር አንፈልግም አንለያይም ብለን የጎሰኞችን ድንበር ማፍረስ ያልቻልን ደካሞች! በገዛ ሀገራችን ያልወከልናቸው ጉግ ማንጉጎች ድንበር ተካለልን፣ተፈራረምን ብለው በሰበር ዜና ሲያሳዩን እናንተ ማን ናችሁ? በስሜ በድንበር ከወንድሜ የዐማራ ሕዝብ ከወንድሜ የትግራይ ሕዝብ ከወንድሜ የኦሮሞ እና ሱማሌ ሕዝብ እንድታካልሉኝ ስልጣን ቀድሞነገር መቼ ሰጠሁኝ? ብለን የማንጠይቅ ከንቱዎች። እኛ ነን የሞት ሞት  የሞትን። እኛ ነን መከራ የሚያንሰን። እኛ ነን ምን እያደረጉ እንደሆነ እና ነገ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጅ በልጆቻችን አንገት ላይ እያሰሩ እንደሆነ ያልገባን።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሓት እና ግብረ አበሮቹን የክልል ማካለል እና ኃላፊነት የጎደለው እጅግ የተለጠጠ የጎሳ ፖለቲካ እንክትክቱን ካላወጣ እና እራሱ በራሱ ተመካክሮ አኗኗሩን ካልወሰነ በኦሮምያ እና ሱማሌ በጉጄ እና ቦረና ቤንሻንጉል እና ዐማራ እና ሌሎችም ቦታችዎች በማራገብ ብዛት በተቆሰቆሱ የጎሳ ጠቦች ሕዝብ እንዳለቀ ነገ ይሄው ግጭት ወደ ከተሞች ተዛምቶ ኢትዮጵያ ልትወጣው ወደ ማትችለው ማቅ ህወሓት እና አጋሮቹ እንደሚከቷት መረዳት አለብን።እኛ ያልወከልናቸው በስማችን ድንበር ሲከልሉ ቆሞ ማየት ከወንጀሉ ጋር ከመተባበር እኩል ነው።ማን ወከላችሁ? እኛ መቼ ተጣላን? ጥሉም የድንበር ክልሉም ያለውናንተው አእምሮ ውስጥ ነው አታፋጁን! በአንድ ሀገር ውስጥ ድንበር የለም! ይህ ሃገርን የመክዳት እና የመከፋፈል ከባድ ወንጀል ነው! ብለን ልንቃወም ይገባል።የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዴት እንደሚኖር የሚያውቀው እራሱ ነው።በመሬት ድንበርተኝነት ገበሬው በሚገጥመው ክርክር ሁሉ እንዴት እንደሚፈታ የእራሱ ብሂል እና ዘይቤ አለው።እነኝህ ጥበቦች ናቸው ለሺህ ዓመታት የኖረች ሀገር ፈጥረው ለአፍሪካ በጭንቅ እና የጨለማ የቅኝ ግዛት ዘመን እረዳት እንድትሆን የረዳት። አሁን ወቅቱ ህወሓት የድንበር ውል አደረኩ እያለ በስማችን ሲነግድ በቴሌቭዥን መስኮት እየተመለከትን ከንፈር የምንመጥበት ሳይሆን አንተ ያሰመርከው የጎሰኞችን ድንበር አንቀበልም።በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ውስጥ የድንበር አጥር ሊኖር አይገባም። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ቦታ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብቱ ሊጠበቅ ይገባል ብለን በፅናት የምንነሳበት ወቅት ነው።ከእዚህ በተለየ ግን በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር ኢትዮጵያ ውስጥ  የድንበር ውል አደረግን ሲሉህ ተቀምጠህ ለምትመለከት ትውልድ - ሞትህ ዛሬ መሆኑን ብታውቀው መፈጠርህን ትጠላ ነበር።

ኢትዮጵያ - ቴዲ አፍሮ (ለሙዚቃው የተዘጋጀው ክሊፕ ቪድዮ)



ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Tuesday, September 5, 2017

የጎንደርን ሕዝብ እርስ በርስ ለማፋጀት መቀሌ ላይ ልዩ ቢሮ ተከፍቷል።በህወሓት መስከረም 7/2010 ዓም ቅማንት እና ዐማራ እንዲለያይ የሚያስገድድ አስገዳጅ የሕዝብ ድምፅ እንዲሰጥ ቀጠሮ ተይዟል።

ቅማንት እና ዐማራ በሚል እንዲለያዩ  ህወሓት የፈረደበት አዲስ  ትውልድ በጎንደር ተራሮች ላይ 

ጉዳያችን/ Gudayachn
ነሐሴ 30/2009 ዓም (ሴፕቴምበር 5/2017)
  • መቀሌ ላይ ለቅማንት ቢሮ ከፍቶ (እንደ ጠላት ሀገር የነፃነት ቢሮ መሰል አደረጃጀት አደራጅቶ) ዐማራ ጠላታችሁ ነው የሚል ስብከት እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።
  • መስከረም 7/2010 ዓም የቅማንት ሕዝብን ለመለየት በምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት ይፈፀማል የተባለው እና መቀሌ ላይ የተቀናበረው የድምፅ መስጠት ጉዳይ በኢትዮጵያ አዲስ የበቀል ምዕራፍ እንደሚከፍት ማወቅ ይገባል።
  • በተለይ ከወደ መቀሌ ሰፈር ያላችሁ ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ  ይህንን በሕዝብ  መካከል የፋሺሽታዊ ሥራ የሚሰሩትን ቢያንስ በዝምታ በማበረታታችሁ ወቅቱን ጠብቆ የመከራው ፅዋ በእራሳችሁ እና በልጆቻችሁ በኩል እንደሚደርሳችሁ ልታውቁት የገባል።
  • መቀመጫውን መቀሌ አድርጎ የዐማራ እና የቅማንት ህዝብን ለመለያየት ከተነደፈው መርሃ ግብር ውስጥ ከመስከረም 7 በኃላ የዐማራ ተወላጅ ያሏቸውን ንብረት ገፎ  ከመሬታቸው መንቀል ይገባል የሚል እቅድ ተይዟል።


ኢትዮጵያ በረጅሙ የመንግስት ስሪት ታሪክ እንደ ህወሓት ሙሉ ጊዜውን፣ሃብቱን እና የሰው ኃይሉን ሕዝቧን ለመከፋፈል እና እርስ በርስ ለማጫረስ እጅግ አረመኔያዊ ተግባር የሰራ መንግስት የለም።የቀደሙት ነገስታት በስልጣን ዘመናቸውም ሆነ ስልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት የእርስ በርስ ጦርነት በሕዝብ መካከል ጠብ ለመዝራት እና በውጤቱ ለመጠቀም ከመጣር ይልቅ በኃይል እና በጉልበት ማስገበር ላይ ያተኮረ የስልጣን ትግል ሲያደርጉ ብቻ ይታወቃሉ።ህወሓት ግን ኢትዮጵያን ጣልያን በአምስቱ ዓመታት እንደከፋፈለው የጎሳ ክልል ኢትዮጵያውያንን በጎሳ መልከዓ ምድር እና የመታወቂያ ወረቀታቸው ላይ ሳይቀር የጎሳ ስም እየፃፉ እጅግ አደገኛ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ  ሲያራምዱ ሃያ ስድስተኛ አመታቸውን ይዘዋል።ይህም ሆኖ ግን የኢትዮጵያውያን ጠንካራ ማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ትስስር አሁን እስካለንበት ሰዓት ድረስ እንደ ሀገር እንድንቀጥል አድርጎናል። ይህ ማለት ግን ማኅበራዊም ሆነ ሃይማኖታዊ እሴታችን በህወሓት መርዘኛ የጎሳ ፖለቲካ እጅጉን አልተጎሳቆለም ማለት አይደለም።

በአሁኑ ወቅት ህወሓት በሱማሌ እና በኦሮሞ መካከል፣ በቤንሻንጉል እና በዐማራ መካከል፣  በአፋር እና በዐማራ መካከል፣በሲዳማ እና በኦሮሞ መካከል እና በሌሎች በእዚህ ፅሁፍ ውስጥ ባልተካተቱ ኢትዮጵያውያን መካከል ሆን ተብሎ የተጠና ግጭት በመፍጠር የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም ሲሞክር ተስተውሏል።የእዚህ ፅሁፍ አቅራቢም በቦረና ጉጂ እና ኦሮሞ መካከል ህወሓት እንዴት ግጭት እንደፈጠረ በወቅቱ የተግባሩ ፈፃሚ የነበረ ግለሰብ አንደበት የሰማውን ታሪክ ያስታውሳል እና ሕዝብ የማጋጨት ለህወሓት የተካነበት የሙሉ ጊዜ ስራው እንደሆነ የሚነገረው አንዳች ስህተት እንደሌለበት ለመግለፅ በእማኝነት ለመግለጥ ይወዳል።

ህወሓት በኢትዮጵያውያን መካከል የሚፈጥራቸው የግጭት አይነቶች በመልክዐ ምድር እና ቋንቋ የሚለያዩትን ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ቋንቋ፣ባህል እና ሃይማኖት ያላቸው እንደ ቅማንት እና ዐማራ ያሉ ለዘመናት አብረው የኖሩ እና ልዩነታቸውን እራሳቸውም የማያውቁትን ሕዝብ ሁሉ ለመለያየት  እና የእልቂት ደም ለማፍሰስ ተዘጋጅቷል።ለእዚህም በመጪው መስከረም 7/2010 ዓም ቅማንት ከዐማራ የተለየ ዞን እንዲከለል እና በውጤቱም የመሬት ግጭት እንዲፈጠር መቀሌ ላይ ለቅማንት ቢሮ ከፍቶ (እንደ ጠላት ሀገር የነፃነት ቢሮ መሰል አደረጃጀት አደራጅቶ) ዐማራ ጠላታችሁ ነው የሚል ስብከት እያደረገ መሆኑ ተሰምቷል።በመሰረቱ የዐማራ እና የቅማንት ሕዝብ እርስ በርስ ተለያይቶ የማያውቅ እና ኢትዮጵያ በዘመናት በገጠማት የውጭ ወራሪ ሁሉ አብሮ የሞተ እርስ በርስ ልዩነት ብሎ ነገር የማያውቅ ሕዝብ ነው።በቅማንትም ሆነ በዐማራ መካከል የሚታወቀው አባባል ቅማንት ዐማራ ነው።ዐማራም ቅማንት ነው የሚል ሲሆን የዐማራ ሕዝብ በመልክዓ ምድር ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ሸዌ፣ ወሎዬ በሚል የተለምዶ አጠራር ከመታወቁም በላይ  ባደገበት አካባቢ ቅማንት፣ አገው፣ አርጎባ፤ ወይጦ፤ ቤተ እስራኤል ወዘተ በመባል ይታወቃል። ይህ ማለት ግን የተለያየ ሕዝብ አድርጎ ህወሓት ለመሳል እንደሚሞክረው አይደለም።

መስከረም 7/2010 ዓም የቅማንት ሕዝብን ለመለየት በምርጫ ቦርድ አስተባባሪነት ይፈፀማል የተባለው እና መቀሌ ላይ የተቀናበረው የድምፅ መስጠት ጉዳይ በኢትዮጵያ አዲስ የበቀል ምዕራፍ እንደሚከፍት ማወቅ ይገባል።የህወሓት አድናቂዎች አርቆ የማየት አቅም ባጠረው አዕምሮ  ይህንን የቅማንት እና ዐማራን የመለያየት ተንኮል የሚያደንቁት ህወሓት የተንኮል ምጡቅነት እያሉ ሊያደንቁት ሲዳዱ ተሰምተዋል።ይህ ነገ የምፀፀቱበት የአስተሳሰብ ድህነት መገለጫ ነው።ቅማንት እና ዐማራ በርካታ በማኅበራዊ እና ሃይማኖታዊ ትስስር ብቻ ሳይሆን በእዚህ ፅሁፍ የማይገለጡ በርካታ ውስጣዊ ትስስሮች አሏቸው።እነኝህ ትስስሮች በመካከላቸው ልዩነት ፈጥረው ለመለያየት የሚሞክሩትን ሁሉ መልሰው በሕብረት የሚነሱ ቀን እንደነበልባል እሳት የሚፋጁበት ቀኖች እሩቅ አይደለም።ህወሓት በርካታ ጊዜ ስህተት ሲሰራ ኖሯል።የወልቃይት ጉዳይ ሲነሳ እናቶችን ሳይቀር ክላሽ እያስያዘ ሰልፍ እየወጣ ሲፎክር በእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊም ሳይቀር ይህ ጉዳይ 'ጎረቤቴን ለመግደል ተዘጋጀሁ' የሚል መልዕክት ነው።ነገ እንደ እሳት የሚፋጅ ኃይል ይነሳል መዘዙን አትችሉትም የሚል ማሳሰቢያ ሲሰጥ የሰማ የህወሓት ሰው አልነበረም።አሁንም እንላለን የቅማንት እና ዐማራ ሕዝብ በመካከሉ የሚደረገውን የመለያየት ሥራ ዝም ብሎ የሚቀበል አይደለም።ለጊዜው ለኑሮ ብለው ውር ውር የሚሉ የተንኮል አስፈፃሚ የተገኙ መስለው ይሆናል።የህዝቡ መሰረት ግን ጥልቅ ነው።እንደ አሕዛብ እርስ በርሱ አይጋደልም።ለጊዜው አነስተኛ ግጭቶች ታዩ ብላችሁ ጮቤ ብትረግጡም ችግሩን ፈትቶ በጋራ ጠላቱ ላይ ይነሳል።ለዚያን ጊዜ የሚሆን በጎ ሥራ መስራት ዛሬ ነበር።ሰዓቱ ካለፈ በኃላ አልቃሽም አስለቃሽም አይገኝም። አሁንም ይህንን ጉዳይ ትክክል አይደለም የምትሉ የሀገር ሽማግሌዎች በተለይ ከወደ መቀሌ በኩል  ጉዳዩን ለመውቀስ ድፍረት ቢኖራችሁ ለእራሳችሁም ለልጆቻችሁም ውለታ እንደዋላችሁ ይቆጠራል።በቸልታ ብትተዉት እና ከእዚህ ባለፈ የሽሩድ ስራውን እያደነቃችሁ የደሙ ተካፋይ ከሆናችሁ የመከራው እሳት እጥፍ ሆኖ እንደሚመጣ ለማወቅ ሊቅ መሆን አይጠበቅም።በተለይ ከወደ መቀሌ ሰፈር ያላችሁ ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ  ይህንን በሕዝብ  መካከል የፋሺሽታዊ ሥራ የሚሰሩትን ቢያንስ በዝምታ በማበረታታችሁ ወቅቱን ጠብቆ የመከራው ፅዋ በእራሳችሁ እና በልጆቻችሁ በኩል እንደሚደርሳችሁ ልታውቁት የገባል።


ህወሓት ሕዝብ ለሕዝብ ለማጋጨት የቅማንት እና ዐማራ ሕዝብ የተለያየ ነው የሚል ትርክት ብቻ ሳይሆን ያመጣው በቅርቡ ሊተገብረው ያሰበው የሰሜን ጎንደርን ለሶስት መክፈል የሚል ሌላ የመከፋፈል ሃሳብ ነው።ይህንን ጉዳይ የሰሜን ጎንደር ሕዝብ በእጅጉ የተቃወመው ብቻ ሳይሆን ለትውልድ የሚቆይ በደል እንደተፈፀመበት እና ምላሹም አስከፊ እንደሚሆን ነው። የህወሓት ልሳን ተደርጎ የሚወሰደው ' አይጋ ፎረም' ነሐሴ 29/2009 ዓም የሰሜን ጎንደርን ለሶስት መከፈል በገለጠበት የሰሜን ጎንደር አስተዳደር ለሶስት የመከፈሉ ጉዳይ ለምን ይህን ያህል ትኩረት ሳበ? በሚል ርዕስ በፃፈው ፅሁፉ ላይ እንዲህ የሚል አረፍተ ነገር ይነበባል - 'የክልሉ አመራር በእጅጉ ተገፍቶና ተላልጦም ጭምር በሒደት የቅማንትን ማንነት እውቅና ከመስጠት አልፎ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ የሚያደርግ አዋጅ እንዲያጸድቅ መገደዱ አልቀረም፣'' ይላል። ይህ ማለት ጉዳዩ በህወሓት የተቀመመ አስገዳጅ ተግባር እንጂ የህዝብ ፈቃድ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው። ቂም፣ በቀል እና ጥላቻ ከመቶ ሚልዮን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር መግባት ትርፍ እና ኪሳራውን ማስላት ያልቻለው ህወሓት እና ግብረ አበሮቹ መጪውን ጊዜ በሚገባ መመልከት እንዳልቻሉ እና ተስፋ በቆረጠ ስሜት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ለሁሉም ግልጥ ነው።

ባጠቃላይ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ይህንን ከላይ የተጠቀሱትን ሕዝብ ከሕዝብ ለማጋጨት የሚድረግ የህወሓት እኩይ ተግባሮችን  ለዓለም ለማጋለጥ እና አስገዳጅ እርምጃ በስርዓቱ ላይ በመውሰድ ከደሙ በዝምታ ላለመተባበራቸው በግልጥ ማሳየት አለባቸው። 

ከእዚህ በታች የምትመለከቱት መርሃ ግብር መቀመጫውን መቀሌ አድርጎ የዐማራ እና የቅማንት ህዝብን ለመለያየት ከተነደፈው መርሃ ግብር ውስጥ ከመስከረም 7 በኃላ የዐማራ ተወላጅ ያሏቸውን ንብረት ገፎ  ከመሬታቸው መንቀል ይገባል የሚል እቅድ ተይዟል።ይህ ማለት የጎንደር ሕዝብ ከመሬቱ እንዲነቀል ይደረጋል ማለት ነው። 'የማን ቤት ፈርሶ የማን ሊበጅ' የምትለው አባባል በትክክል ቦታዋ በእዚህ አይነቱ የፋሺሽቶች አስተሳሰብ ወቅት መሆኑ አያጠራጥርም። 



ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

ሐያ ገዳማት የሚገኙበት በግሪክ የሚገኘው የአቶስ ተራራ ገዳማውያን አኗኗር (ቪድዮ)

ገዳሙ ከሰርብያ፣ሮማንያ፣ቡልጋርያና ሩስያ የመጡ ዓለምን የናቁ መነኮሳት ገድመውበታል።