ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, April 24, 2018

Wednesday, April 18, 2018

ከእመቤቴ ሌላ የምጠራው ምስክር የለኝም ሁሉን የማማክራት ገመናዬን ሸፋኝ እርሷ ነች፣ አርቲስት መሰረት መብራቴ ከሰርግ ስነ ስርዓቷ በኃላ እያለቀሰች የተናገረችው (ሙሉ ቃለ ምልልሱን ያዳምጡ)

ጉዳያችን / Gudayachn
ሚያዝያ 10/2010 ዓም (አፕሪል 18/2018)

''ክርስቲያን በሁለት ሰይፍ የተሳለ ነው።በመንፈሳዊ ሕይወትም ፊት አውራሪ በስራውም ጎበዝ መሆን አለበት'' አርቲስት መሰረት መብራቴ

አርቲስት መሰረት መብራቴ በኢትዮጵያ የፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ቀዳሚ ከሚባሉ አንስት ተዋናይ ውስጥ ነች።መሰረት በኪነጥበቡ ዓለም ጠንካራ ስብዕና፣ የጎላ ኢትዮጵያዊ ለዛ እና መልካም ስነ ምግባር የሕይወቷ ፍልስፍናዎች እንደሆኑ በተለያዩ ጊዜ በሰጠቻቸው ቃለ መጠይቆች ገልጣለች።ባለፈው ሳምንት  አዲስ አበባ የድምፃዊት  እጅጋየሁ ሽባባው ወንድም ከሆነው ከአቶ ዘውዱ ሽባባው ጋር የጋብቻ ስነስርዓቷን ፈፅማለች።ሰይፉ ፋንታሁን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ቃለ መጠይቅ አድርጎላት ነበር።
የቃለ መጠይቁን ሙሉ ቃል እና የአርቲስት መሰረትን መንፈውሳዊ መዝሙር በተከታታይ ከእዚህ በታች ያዳምጡ።


የአርቲስት መሰረት መብራቴ መንፈሳዊ መዝሙር 

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Monday, April 16, 2018

ድምፃዊት ሚካያ ሞት ባይቀድማት የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ አንድ እርምጃ የመውሰድ አቅሟ ትልቅ ነበር (ጉዳያችን ማስታወሻ)

ጉዳያችን / Gudayachn 
ሚያዝያ 8/2010 ዓም (አፕሪል 17/2018)

ድምፃዊት ሚካያ 
  • ድምፃዊት ሚካያ ብሔር ብሔር በሚባልበት ዘመን ውስጥ ስለ አትዮጵያ ትውልዷን ያስተማረች፣ጠንካራ ትውልድ እንዲመጣ ሕልሟን ያስቀመጠች የሀገር ባለ ውለታ ነች።ዛሬ ኢትዮጵያ ስሟን እንደገና የሚማፀን ትውልድ ብትመለከት እንዴት ደስ ባላት ነበር።
ድምፃዊት ሚካያ ከአምስት ዓመት በፊት በድንገት ከእዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች።በዩንቨርስቲ ትምህርቷም ስኬታማ የነበረችው ድምፃዊት ሚካያ ከእዚህ ዓለም በሞት ከመለየቷ በፊት በሴቶች ሕይወት ላይ ያጠነጠነ አዲስ የራድዮ መርሃ ግብር አየር ላይ ለማዋል ዝግጅት ላይ ነበረች።ሚካያ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በአዲስ አበባ  ቤተለሄም አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በንጉሡ ዘመን GCA (Girls Christian Academy)  በደርግ ዘመን ስሙ የአብዮት ቅርስ በተሰኘው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች። በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የመጀመርያ ዲግሪዋን በቋንቋዎች ጥናት የያዘች ሲሆን በአንድ ወቅት አለባቸው ቶክ ሾው ላይ ቀርባ የወደፊት ሕልሟን ስትገልጥ በድምፅ ከመጫወት በላይ በፊልም ትወና መስራት እንደምትፈልግ እና ሀገሯን ማስጠራት ሕልሟ እንደሆነ መናገሯ ይታወሳል።

ሚካያ ከእዚህ ዓለም በሞት በ2006 ዓም ታህሳስ ወር ላይ ስታልፍ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የማስተርስ ትምህርቷን ልታጠናቅቅ ጥቂት ወራት ቀርተዋት ነበር።አርቲስቷ በአፍሪካ ኮራ የሙዚቃ ውድድር ተመርጣ ከ20 ምርጦቹ ውስጥ ከመሆኗ በላይ የውድድሩ አጋማሽ ድረስ በጥሩ ውጤት ደርሳ ነበር።ለውድድር ከመቅረቧ በፊት ስራዋ በፈረንሳይኛ እና እንግሊዝኛ ተተርጉሞ ቀርቦ አድናቆትን አግኝቶም ነበር።በጥቂት ስራዎቿ የኢትዮጵያን ኪነጥበብ ወደ ዓለም መድረክ ታመጣለች ተብላ ተስፋ የተጣለባት ሚካያ በሁለት ሳምንት የተሰማት ድንገት ህመም ሳብያ ሲብስባት ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተወስዳ በ37 አመቷ ሕይወቷ በድንገት አልፏል።ድምፃዊት ሚካያ ብሔር ብሔር በሚባልበት ዘመን ውስጥ ስለ አትዮጵያ ትውልዷን ያስተማረች፣ጠንካራ ትውልድ እንዲመጣ ሕልሟን ያስቀመጠች የሀገር ባለ ውለታ ነች።ዛሬ ኢትዮጵያ ስሟን እንደገና የሚማፀን ትውልድ ብትመለከት እንዴት ደስ ባላት ነበር።
በኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ አንጋፋዎቹ በሚታሰቡበት ወቅት በአጭር ጊዜ ብዙ ተስፋ የሚጣልበት ሥራ የሰሩ አርቲስቶችን አለመርሳት ተገቢ ነው።
ከእዚህ በታች የሚካያን ሁለት ዜማዎች በተከታታይ ያድምጡ።
ሀገሬ 

ሰበቤ ሁን ሲልህ ጉዳያችን GUDAYACHN www.gudayachn.com

Friday, April 13, 2018

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ እያደረጉት ያለው ጉዞ ቅድምያ የሚሰጠው የነበረ ትክክለኛ ጉዞ ነው (የጉዳያችን ማስታወሻ)

ጉዳያችን / Gudayachn
ሚያዝያ 6/2010 ዓም (አፕሪል 14/2018)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ ቅድምያ ወደ ሱማሌ፣በመቀጠል ወደ አምቦ፣መቀሌ እና በመጪው ጊዜ ደግሞ ወደ ባህር ዳር እና ጎንደር መሄዳቸው ትክክል ነው? አይደለም ? ቅድምያ ወደ ካብኔ ምስረታ መሄድ የለባቸውም ነበር? የሚሉ አስተያየቶች እዚህም እዝያም ይሰማሉ።ይህ ግን ከትክክለኛ የስልት እሳቤ አንፃር መመልከት ያልቻሉ ሰዎች አተያይ ነው።ስለሆነም  ቅድምያ ለጉዞ መስጠታቸው ትክክል ነው።ለእዚህም ማስረጃ የሚሆነው ከጉዞዎቹ ምን ተገኙ የሚለውን ለመለካት ስንችል ነው።ውጤቱ የሚለካው ደግሞ በቀላሉ በሚለካ የፖለለቲካ ውጤት ሳይሆን አጠቃላይ ሀገሪቱ ከነበረችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ማመሳከር ሁሉ ይፈልጋል።በእዚህም መሰረት ዶ/ር ዓብይ ከጉዟቸው የሚከተሉትን የማይተኩ ውጤቶች አግኝተዋል። እነርሱም : -

1/ ከጉዞ በፊት ወደ ስልጣን እንደመጡ በሕወሓት በኩል የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልልን ከኢትዮጵያ ፖለቲካ የመነጠል እና የህወሓት ጥገኛ ብቻ የማድረግ ሙከራ ከሽፏል።በእዚህም ሳብያ የኢትዮጵያ ሱማሌ ባለስልጣናት የዋለለ አካሄድ ይኖራል ቢባል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ሕዝብ ልብ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ ተችሏል።ለእዚህም ከጅጅጋ አየር ማረፍያ ጀምሮ የተሰለፈው ሕዝብ በነቂስ መውጣቱ ለአለቆቹ ማስተላለፍ የፈለገው መልክት ነበር። 

2/ በአምቦ ባደረጉት ጉብኝት እና ንግግር ደግሞ የኦሮሞ ማኅበረሰብ በምን ያህል ቁጥር አብሯቸው እንደቆመ ለህወሓት አሳይተውበታል።ይህ ብቻ አይደለም ለቄሮ ታገሱን ለውጥ እናመጣለን በሚል ንግግር ያለፈውን ትግል አወድሰው መጪውን አብረው እንደሚሄዱ የፖለቲካ ኃይሉን አጠናክረው ተመልሰዋል።

3/ ዛሬ በመቀሌ ያደረጉት ጉብኝት ደግሞ እራሱን የቻለ ስልት የያዘ ይመስላል።አንዳንዶች ለምን ሰማዕታት ሃውልት የአበባ ጉንጉን አስቀመጡ? የሰማእታት ሃውልት መሰራት ያለበት ከደርግ ወገንም ለሞቱት ጭምር ነው መሆን ያለበት የሚሉ ሃሳቦች አንስተዋል። ትክክል ናቸው። ይህንን ሃሳብ ትክክል ቢሆንም ወደ ተግባር ለማምጣት ግን ዶ/ር ዓብይ በበቂ ሁኔታ የፖለቲካ ስልጣኑን መረከብ አለባቸው።መቀሌ ላይ ያደረጉት ንግግር በዋናነት በትግርኛ በመናገር እና የትግራይን ጥንታዊነት በማንሳት ህዝቡ በጠላትነት እንደህዝብ እንዳልተፈረጀ ለትግራይ ሕዝብ ለመንገር አጋጣሚውን ተጠቅመውበታል። ይህም ጉዳዩ ከመሪዎቹ ጋር ሳይሆን ሕዝብ እንደ ሕዝብ እንዳይደነበር ነግረውበታል።ይህ ደግሞ መልካም አጋጣሚ ነው።

ባጠቃላይ ዶ/ር አብይ እነኝህን ጉዞዎች ማድረጋቸው እና በቀጣይ ቀናት ወደ ባህር ዳር እና ጎንደር ማምራታቸው አስፈላጊ ነበር። እነኝህን ጉዞዎች ካቢኔ ከመመስረት በፊት ማስቀደማቸው በእራሱ ትክክለኛ ስልት ነው። በጉዟቸው ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስልጣን በፓርላማው ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ዘንድ መረጋገጡን እና  ተስፋ እንዳጫረ ሁሉ ለህወሓት በግልጥ ነግረውታል።በእዚህም ህወሓት እርሳቸውን የሚጋፋ ከሆነ በጉብኝታቸው ወቅት ለድጋፍ ከወጣው ሕዝብ ጋር ሁሉ መጋጨት እንደሆነ በግልፅ የፖለቲካ ማሳያ መንገድ ለህወሓት የነገሩበት የጥበብ መንገድ ነው።ከእዚህ ሁሉ ግብኝት እና የፖለቲካ ኃይል ማሰለፍ በኃላ ወደ ካቢኔ ምስረታ የመሄዱ ሂደት ከተፅኖ  ፈጣሪነት አቅም ጋር ስለሚሆን የዶ/ር ዓብይ አቅም ቀድሞ ከነበረው ጎልብቶ እንዲገኝ አድርጎታል።በሌላ በኩል በጉዞዎቹ ላይ የተገኘው የህዝብ ድጋፍ የተመለከቱ የውጭ ኃይሎች ሁሉ ዶ/ር አብይ ያሰለፉት የህዝብ ብዛት እንዲመለከቱ ያደረገ ብቻ ሳይሆን ሂደቱ በህወሓት ቢደናቀፍ ምክንያታዊ ያልሆነ ነገር ግን የስልጣን ጥማት ብቻ መሆኑን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ክስተት ሆኗል።ስለሆነም የዶ/ር ዓብይ ጉዞ ትክክለኛ እና ውጤታማ ነበር።ለመጪው ለውጥም ትልቅ የፖለቲካ ጉልበት የሚሰጣቸው ይሆናል።

ድምፃዊ ማዲንጎ አፈወርቅ - ጎዳናው (ዜማ)

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Monday, April 9, 2018

ህወሓት የዶ/ር ዓብይን የትግራይ ጉብኝት ለምን ፈራችው? ኢትዮጵያዊነት በሱማሌ ኢትዮጵያም ክልል የጎሳ ፖለቲካን ማሳፈር ጀምሯል፣ እና አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ሙት ዓመቱ ሲታወስ (የጉዳያችን ማስታወሻ)


ጉዳያችን/Gudayachn
ሚያዝያ 2/2010 ዓም (አፕሪል 10/2018 ዓም)

በእዚህ ማስታወሻ ስር 
  • ህወሓት የዶ/ር ዓብይን የትግራይ ጉብኝት ለምን ፈራችው? 
  • ኢትዮጵያዊነት በሱማሌ ኢትዮጵያም ክልል የጎሳ ፖለቲካን ማሳፈር ጀምሯል፣ እና  
  • አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ሙት ዓመቱ ሲታወስ (ሁለት ቪድዮዎች) ይገኛሉ።

ኢትዮጵያዊነት በሱማሌ ኢትዮጵያም ክልል የጎሳ ፖለቲካን ማሳፈር ጀምሯል

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ሁለት ኃይሎች በዋናነት ታይተዋል።እነርሱም የኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት እና የጎሳ ፖለቲካን ማዕከል ያደረጉ ነበሩ።የጎሳ ፖለቲካ ግን በሂደት ከአርባ ዓመት በፊት በነበረው የሶሻሊስ ርዕዮት ጋር በተዛመደ መልኩ ሳይሆን መሰረቱን ብቻ በሶሻሊስት መንገድ ያስቀመጠ የሚመስል ግን ውስጡ በርካታ ሸፍጥ፣ሙስና፣ጭካኔ የተሞላበት እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጥ ሆኗል።ከ1966 ዓም አብዮት ጀምሮ ስለ ጎሳ አብዮት ሲያቀነቅኑ የነበሩ በዘመነ ህወሓት ወቅት ባገኙት የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ እየተሰገሰጉ  ከህወሓት ጋር ስለ ጎሳ ፖለቲካ ሲሰብኩ ቆይተው ዛሬ ሺዎችን በሞት ሌሎች አስር ሺዎችን ወደ እስር ቤት ወርውረው እስካለፈው ሰኞ ድረስ የኢትዮጵያ ፓርላማም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ስለ ኢትዮጵያዊነት ሳይወራባቸው መጋቢት 24/2010 ዓም ዶ/ር ዓብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመረጡ  የ27 ዓመቱን በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ላይ የተደረገ አድማን ለመጀመርያ ጊዜ ሰበሩት።

ይህ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በአቶ ለማ እና ዶ/ር ዓብይ በእራሱ በህወሓት መንደር ውስጥ ተስተጋብቶ ባለፈው ቅዳሜ ጅጅጋ ላይ ተደግሟል።የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ እና የአካባቢው  ነዋሪ ከፍተኛ ባለስልጣን ወጥቶ ለመቀበል አደባባይ የወጣው ምናልባት ከኮለኔል መንግስቱ ዘመን ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 29/2010 ዓም ነው።ከጅጅጋ አየር መንገድ ጀምሮ ዳር እና ዳር የተሰለፈው ሕዝብ በደስታ ስሜት እና ኢትዮጵያዊነት በፈነቀለው ሳግ እና ሆታ ሲታይ የጎሳ ፖለቲካ ምን ያህል ስሜቱን ጎድቶት እንደነበር የሚያሳይ ነበር።በጅጅግ አየር መንገድ እና ጉባኤው በተደረገበት አዳራሽ እንደ ቀስተ ዳምና ዙርያውን የተሰቀለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በተጨማሪ እያንዳንዱ የጉባኤው ተሳታፊ በእጁ የያዘውን ሰንደቅ ዓላማ በእየንግግሮች መሃል ሲያውለበልብ እና ስሜቱ እየተፈነቀለ ሲነሳ እና ስቀመጥ መመልከት በራሱ ልዩ ስሜት ይፈጥር ነበር።
የጅጅጋው ስብሰባ መጋቢት 29/2010 ዓም 

ከጅጅጋው ትይንት ግን ሁለት ነገሮችን መመልከት ይቻላል።አንዱ ክልሉ አቤት የሚልበት ያጣ የነበረ እና በአንድ በኩል የክልሉ ፕሬዝዳንት ቅጥ ያጣ እና ጨካኝ አገዛዝ ያስመረረው መሆኑን እና በሌላ በኩል ህዝቡ ምን ያህል ኢትዮጵያዊነቱን በሚገባ የሚያውቅ መሆኑን ሁሉም እንዲረዳለት አጋጣሚ አጥቶ የነበረ መሆኑን መረዳት ይቻላል።ከእዚህ በተጨማሪ ህወሓት የሚያቀነቅነው የጎሳ ፖለቲካ ያተረፈለት እልቂትን እና ስደትን መሆኑን በሚገባ መረዳቱን በአደባባይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተናግሯል።

ህወሓት የዶ/ር ዓብይን የትግራይ ጉብኝት ለምን ፈራችው?

ዶ/ር ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኃላ ህወሓት በሃሳብ ደረጃ የበተናትን ኢትዮጵያን የመሰብሰብ እና ስነ ልቦናዊ አንድነት ለመፍጠር ጥረት እያደረገ እንደሆነ በትክክል እየታየ ነው።በአንድ ሳምንት ውስጥ በሱማሌ ክልል የፈጠሩት በተለይ በሕዝብ ዘንድ የፈጠሩት የአብሮነት ስሜት እጅግ ከፍተኛ ነው። ይህንኑ ጉዞ በመቀጠል በመጪዎቹ ጊዜዎች ወደ አምቦ እና መቀሌ ጉዞ እንደሚያደርጉ እየተሰማ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መቀሌ የሚያደርጉት ጉዞ ላይ ግን ህወሓት ከአሁኑ ብርክ አስይዞታል።ለእዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ላለፉት አርባ ዓመታት ሲያስደነብርበት የነበረውን  የጎሳ ፖለቲካ እና የትግራይ ሕዝብ ህወሓት ከሌላ በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቃት እንደሚደርስበት የሚተርከውን ተረት ዶ/ር ዓብይ ውሃ ላይ የተጣለ ኩበት እንደሚያደርግበት እና ቢያንስ ወጣቱን ክፍል ልብ እንደሚከፍልበት የሰጋው ህወሓት በአፈ ቀላጤዎቹ አማካኝነት አዲስ ፕሮፓጋንዳ ከፍቷል።ይህም ሆኖ ግን በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በርካታ የስርዓቱ ደጋፊ ወጣቶች አንዳንዶቹ እንደ ስልት ሌሎች ደግሞ የመጪው ጊዜ እውነታ ይሄው ነው በሚል የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሲያንፀባርቁ እየታዩ ነው።ኢትዮጵያዊነትን በማውራት ብቻ የሚገለጥ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ግን የዶ/ር ዓብይ መቀሌ ላይ ሄደው የሚያደርጉት ንግግር (በትግርኛ እና በአማርኛ እንደሚናገሩ ይጠበቃል) የትግራይ ወጣት በሁለት ምክንያቶች እንደሚደግፈው ይታወቃል።ይሄውም አንድ: - የህወሓት ህወሓት ከሌለ ሌላው ሕዝብ ይበላሃል እያለ የሚተርከው ትርክት ቁልፍ በሆኑ አገላለጦች  በተሞሉ የዶ/ር አብይ ንግግሮች ስለሚንኮታኮቱ እና ሁለት: - ወጣቱ የክልሉ ሕዝብ ከቀደሙት የህወሓት አመራሮች ጋር በተለያየ ጊዜ ግጭት ውስጥ የገባ እና አስተሳሰባቸው ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ስለተረዳ ይህንን ስሜቱን የምያቀጣጥልለት አንዳች ኃይል በሚፈልግበት በእዚህ ወሳኝ ወቅት  የሚደረግ ንግግር ስለሆነ። የዶ/ር ዓብይ ንግግርም ዘመናዊ አስተሳሰብ ያለፈውን የአርባ ዓመት የእነ አቦይ ስብሐት የተንኮል ድር የያዘ የአስተሳሰብ ጥግ በሚንድ መልኩ የሚነገር ስለሚሆን ነው። ሌላው ቀርቶ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ልጆች ሳይቀሩ ዶ/ር ዓብይን ማታ ማታ ሲያደንቁ መስማት ለአዛውንት የህወሓት  አባላት ራስ ምታት ሆኗል።ስለሆነም የዶ/ር ዓብይ የመቀሌ ንግግር በህወሓት መንደር እንደ ጦር እየተፈራ ነው።

 አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ሙት ዓመቱ ሲታወስ

የሶስት ዘመን ትውልዶችን ያገናኘው አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ከእዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ዘጠነኛ ዓመቱን ሚያዝያ 11 ቀን ይሞላዋል።ጥላሁን በደረሰበት ጉዳት ለትውልድ እና ለሀገር በማሰብ ሆድ ይፍጀው ብሎ በይቅርታ የኖረ የትውልድ አባት ነው።መስከረም 17/1933 ዓም ወሊሶ የተወለደው ጥላሁን ገሰሰ ወደ አዲስ አበባ የመጣው በጭነት መኪና ላይ ተጭኖ እንደነበር ታሪኩን የሚያውቁ ያወሳሉ።በ1995 ዓም ስለ ጥላሁን አንጋፋው ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ በእንባ እየታጠበ ሲናገር እንዲህ ብሏል።

“እኔና ጥላሁን አንድ ቀን ወደ ወሊሶ ሔደን ነበር። ወሊሶ አያቱ አሉ። እርሳቸውጋ ተጫውተን ስንወጣ ጥላሁን ገሠሠን ሰላም የሚለው ሰው በዛ። በረንዳ ላይ ከሁሉም ጋር ይጫወታል። በዚህ ጊዜ አያቱ እኔን ወደ ጓሮ ወሰዱኝና ሳር ከመሬት ነጭተው በእጄ አሲያዙኝ። ከዚያም እንዲህ አሉኝ። “በምድር የሰጠሁክን በሰማይ እቀበልሃለሁ። ጥላሁን እናትም አባትም የለውም። እህት ወንድም የለውም። ያለኸው አንተ ነህ። ልጄን አደራ። አንተ ነህ ወንድሙ አንተ ነህ ያለኸው! ብለውኛል። ይሔን ታሪክ ለጥላሁን ገሠሠ ነግሬው አላውቅም። ገና ዛሬ ለናንተ መናገሬ ነው። ግን ሁል ጊዜ ይሄ አደራ አብሮኝ ስላለ ጥላሁን ገሠሠ በሄደበት ሁሉ እኔ ከጀርባው አለሁ። የአደራ ጓደኛዬ ነው''

ጥላሁን ገሰሰ እስካሁን በስሙ የተሰየመ አደባባይ፣ሙዜም ወይንም የአደባባይ መታሰብያ የለውም።የሶስት ትውልድ አገናኝ እንደመሆኑ ግን መታሰቢያ ማስቀመጡ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ያለው ፋይዳ ቀላል እንዳልሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። ከእዚህ በታች ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ የጥላሁንን የልደት ቀን በማስመለከት ለሕዝብ ያቀረበው ዜማ እና እራሱ ጥላሁን ያዜመው ዜማ ይመልከቱ።
ዳዊት ፅጌ 
ጥላሁን ገሰሰ 

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...