ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, April 9, 2018

ህወሓት የዶ/ር ዓብይን የትግራይ ጉብኝት ለምን ፈራችው? ኢትዮጵያዊነት በሱማሌ ኢትዮጵያም ክልል የጎሳ ፖለቲካን ማሳፈር ጀምሯል፣ እና አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ሙት ዓመቱ ሲታወስ (የጉዳያችን ማስታወሻ)


ጉዳያችን/Gudayachn
ሚያዝያ 2/2010 ዓም (አፕሪል 10/2018 ዓም)

በእዚህ ማስታወሻ ስር 
  • ህወሓት የዶ/ር ዓብይን የትግራይ ጉብኝት ለምን ፈራችው? 
  • ኢትዮጵያዊነት በሱማሌ ኢትዮጵያም ክልል የጎሳ ፖለቲካን ማሳፈር ጀምሯል፣ እና  
  • አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ሙት ዓመቱ ሲታወስ (ሁለት ቪድዮዎች) ይገኛሉ።

ኢትዮጵያዊነት በሱማሌ ኢትዮጵያም ክልል የጎሳ ፖለቲካን ማሳፈር ጀምሯል

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ሁለት ኃይሎች በዋናነት ታይተዋል።እነርሱም የኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት እና የጎሳ ፖለቲካን ማዕከል ያደረጉ ነበሩ።የጎሳ ፖለቲካ ግን በሂደት ከአርባ ዓመት በፊት በነበረው የሶሻሊስ ርዕዮት ጋር በተዛመደ መልኩ ሳይሆን መሰረቱን ብቻ በሶሻሊስት መንገድ ያስቀመጠ የሚመስል ግን ውስጡ በርካታ ሸፍጥ፣ሙስና፣ጭካኔ የተሞላበት እንደሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ግልጥ ሆኗል።ከ1966 ዓም አብዮት ጀምሮ ስለ ጎሳ አብዮት ሲያቀነቅኑ የነበሩ በዘመነ ህወሓት ወቅት ባገኙት የጎሳ ፖለቲካ ውስጥ እየተሰገሰጉ  ከህወሓት ጋር ስለ ጎሳ ፖለቲካ ሲሰብኩ ቆይተው ዛሬ ሺዎችን በሞት ሌሎች አስር ሺዎችን ወደ እስር ቤት ወርውረው እስካለፈው ሰኞ ድረስ የኢትዮጵያ ፓርላማም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ስለ ኢትዮጵያዊነት ሳይወራባቸው መጋቢት 24/2010 ዓም ዶ/ር ዓብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመረጡ  የ27 ዓመቱን በኢትዮጵያዊነት አጀንዳ ላይ የተደረገ አድማን ለመጀመርያ ጊዜ ሰበሩት።

ይህ የኢትዮጵያዊነት ስሜት በአቶ ለማ እና ዶ/ር ዓብይ በእራሱ በህወሓት መንደር ውስጥ ተስተጋብቶ ባለፈው ቅዳሜ ጅጅጋ ላይ ተደግሟል።የኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ እና የአካባቢው  ነዋሪ ከፍተኛ ባለስልጣን ወጥቶ ለመቀበል አደባባይ የወጣው ምናልባት ከኮለኔል መንግስቱ ዘመን ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 29/2010 ዓም ነው።ከጅጅጋ አየር መንገድ ጀምሮ ዳር እና ዳር የተሰለፈው ሕዝብ በደስታ ስሜት እና ኢትዮጵያዊነት በፈነቀለው ሳግ እና ሆታ ሲታይ የጎሳ ፖለቲካ ምን ያህል ስሜቱን ጎድቶት እንደነበር የሚያሳይ ነበር።በጅጅግ አየር መንገድ እና ጉባኤው በተደረገበት አዳራሽ እንደ ቀስተ ዳምና ዙርያውን የተሰቀለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በተጨማሪ እያንዳንዱ የጉባኤው ተሳታፊ በእጁ የያዘውን ሰንደቅ ዓላማ በእየንግግሮች መሃል ሲያውለበልብ እና ስሜቱ እየተፈነቀለ ሲነሳ እና ስቀመጥ መመልከት በራሱ ልዩ ስሜት ይፈጥር ነበር።
የጅጅጋው ስብሰባ መጋቢት 29/2010 ዓም 

ከጅጅጋው ትይንት ግን ሁለት ነገሮችን መመልከት ይቻላል።አንዱ ክልሉ አቤት የሚልበት ያጣ የነበረ እና በአንድ በኩል የክልሉ ፕሬዝዳንት ቅጥ ያጣ እና ጨካኝ አገዛዝ ያስመረረው መሆኑን እና በሌላ በኩል ህዝቡ ምን ያህል ኢትዮጵያዊነቱን በሚገባ የሚያውቅ መሆኑን ሁሉም እንዲረዳለት አጋጣሚ አጥቶ የነበረ መሆኑን መረዳት ይቻላል።ከእዚህ በተጨማሪ ህወሓት የሚያቀነቅነው የጎሳ ፖለቲካ ያተረፈለት እልቂትን እና ስደትን መሆኑን በሚገባ መረዳቱን በአደባባይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተናግሯል።

ህወሓት የዶ/ር ዓብይን የትግራይ ጉብኝት ለምን ፈራችው?

ዶ/ር ዓብይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኃላ ህወሓት በሃሳብ ደረጃ የበተናትን ኢትዮጵያን የመሰብሰብ እና ስነ ልቦናዊ አንድነት ለመፍጠር ጥረት እያደረገ እንደሆነ በትክክል እየታየ ነው።በአንድ ሳምንት ውስጥ በሱማሌ ክልል የፈጠሩት በተለይ በሕዝብ ዘንድ የፈጠሩት የአብሮነት ስሜት እጅግ ከፍተኛ ነው። ይህንኑ ጉዞ በመቀጠል በመጪዎቹ ጊዜዎች ወደ አምቦ እና መቀሌ ጉዞ እንደሚያደርጉ እየተሰማ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ መቀሌ የሚያደርጉት ጉዞ ላይ ግን ህወሓት ከአሁኑ ብርክ አስይዞታል።ለእዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ላለፉት አርባ ዓመታት ሲያስደነብርበት የነበረውን  የጎሳ ፖለቲካ እና የትግራይ ሕዝብ ህወሓት ከሌላ በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቃት እንደሚደርስበት የሚተርከውን ተረት ዶ/ር ዓብይ ውሃ ላይ የተጣለ ኩበት እንደሚያደርግበት እና ቢያንስ ወጣቱን ክፍል ልብ እንደሚከፍልበት የሰጋው ህወሓት በአፈ ቀላጤዎቹ አማካኝነት አዲስ ፕሮፓጋንዳ ከፍቷል።ይህም ሆኖ ግን በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ በርካታ የስርዓቱ ደጋፊ ወጣቶች አንዳንዶቹ እንደ ስልት ሌሎች ደግሞ የመጪው ጊዜ እውነታ ይሄው ነው በሚል የኢትዮጵያዊነት ስሜት ሲያንፀባርቁ እየታዩ ነው።ኢትዮጵያዊነትን በማውራት ብቻ የሚገለጥ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ግን የዶ/ር ዓብይ መቀሌ ላይ ሄደው የሚያደርጉት ንግግር (በትግርኛ እና በአማርኛ እንደሚናገሩ ይጠበቃል) የትግራይ ወጣት በሁለት ምክንያቶች እንደሚደግፈው ይታወቃል።ይሄውም አንድ: - የህወሓት ህወሓት ከሌለ ሌላው ሕዝብ ይበላሃል እያለ የሚተርከው ትርክት ቁልፍ በሆኑ አገላለጦች  በተሞሉ የዶ/ር አብይ ንግግሮች ስለሚንኮታኮቱ እና ሁለት: - ወጣቱ የክልሉ ሕዝብ ከቀደሙት የህወሓት አመራሮች ጋር በተለያየ ጊዜ ግጭት ውስጥ የገባ እና አስተሳሰባቸው ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ስለተረዳ ይህንን ስሜቱን የምያቀጣጥልለት አንዳች ኃይል በሚፈልግበት በእዚህ ወሳኝ ወቅት  የሚደረግ ንግግር ስለሆነ። የዶ/ር ዓብይ ንግግርም ዘመናዊ አስተሳሰብ ያለፈውን የአርባ ዓመት የእነ አቦይ ስብሐት የተንኮል ድር የያዘ የአስተሳሰብ ጥግ በሚንድ መልኩ የሚነገር ስለሚሆን ነው። ሌላው ቀርቶ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ልጆች ሳይቀሩ ዶ/ር ዓብይን ማታ ማታ ሲያደንቁ መስማት ለአዛውንት የህወሓት  አባላት ራስ ምታት ሆኗል።ስለሆነም የዶ/ር ዓብይ የመቀሌ ንግግር በህወሓት መንደር እንደ ጦር እየተፈራ ነው።

 አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ሙት ዓመቱ ሲታወስ

የሶስት ዘመን ትውልዶችን ያገናኘው አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሰሰ ከእዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ዘጠነኛ ዓመቱን ሚያዝያ 11 ቀን ይሞላዋል።ጥላሁን በደረሰበት ጉዳት ለትውልድ እና ለሀገር በማሰብ ሆድ ይፍጀው ብሎ በይቅርታ የኖረ የትውልድ አባት ነው።መስከረም 17/1933 ዓም ወሊሶ የተወለደው ጥላሁን ገሰሰ ወደ አዲስ አበባ የመጣው በጭነት መኪና ላይ ተጭኖ እንደነበር ታሪኩን የሚያውቁ ያወሳሉ።በ1995 ዓም ስለ ጥላሁን አንጋፋው ድምፃዊ መሐሙድ አህመድ በእንባ እየታጠበ ሲናገር እንዲህ ብሏል።

“እኔና ጥላሁን አንድ ቀን ወደ ወሊሶ ሔደን ነበር። ወሊሶ አያቱ አሉ። እርሳቸውጋ ተጫውተን ስንወጣ ጥላሁን ገሠሠን ሰላም የሚለው ሰው በዛ። በረንዳ ላይ ከሁሉም ጋር ይጫወታል። በዚህ ጊዜ አያቱ እኔን ወደ ጓሮ ወሰዱኝና ሳር ከመሬት ነጭተው በእጄ አሲያዙኝ። ከዚያም እንዲህ አሉኝ። “በምድር የሰጠሁክን በሰማይ እቀበልሃለሁ። ጥላሁን እናትም አባትም የለውም። እህት ወንድም የለውም። ያለኸው አንተ ነህ። ልጄን አደራ። አንተ ነህ ወንድሙ አንተ ነህ ያለኸው! ብለውኛል። ይሔን ታሪክ ለጥላሁን ገሠሠ ነግሬው አላውቅም። ገና ዛሬ ለናንተ መናገሬ ነው። ግን ሁል ጊዜ ይሄ አደራ አብሮኝ ስላለ ጥላሁን ገሠሠ በሄደበት ሁሉ እኔ ከጀርባው አለሁ። የአደራ ጓደኛዬ ነው''

ጥላሁን ገሰሰ እስካሁን በስሙ የተሰየመ አደባባይ፣ሙዜም ወይንም የአደባባይ መታሰብያ የለውም።የሶስት ትውልድ አገናኝ እንደመሆኑ ግን መታሰቢያ ማስቀመጡ ለኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ ያለው ፋይዳ ቀላል እንዳልሆነ ብዙዎች ይናገራሉ። 



ከእዚህ በታች ድምፃዊ ዳዊት ፅጌ የጥላሁንን የልደት ቀን በማስመለከት ለሕዝብ ያቀረበው ዜማ እና እራሱ ጥላሁን ያዜመው ዜማ ይመልከቱ።
ዳዊት ፅጌ 
ጥላሁን ገሰሰ 

ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

No comments: