በእዚህ ጽሑፍ ስር
- ሲቪል አቬሽን፣
- ባለ 10ቱ ትዕዛዛት፣ባለ 30 መክሊት ወይንስ ባለ 60 መክሊት
- ለአሜሪካ ኤምባሲ የተጻፈው ደብዳቤ ጉድ
- የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰራተኛ መስራት አቃተኝ
- ቶሎ ወደ ናይሮቢ ሒዱ
==============
ጉዳያችን/Gudayachn==============
ማሳስቢያ ፡ በእዚህ ጽሑፍ ላይ የሚጠቀሱት ድርጅቶች ስም አሁን ያሉበትን ወቅታዊ ሁኔታ ላይገልጽ ይችላል።ታሪኮቹ ግን እውነተኛ ናቸው።
ሙስና የሚለውን ቃል ብዙ ጊዜ ከመስማት የተነሳ ብዙዎች አቅልለው ይመለከቱታል።የአስከፊነቱን ክርፋት የምንረዳው ግን የወጋቸው ሰዎች ምን ያህል ሃገር ይጠቅሙ እንደነበር ስናስብ ነው።በእዚህ ጽሑፍ ላይ የቀረቡት ታሪኮች በሙሉ እውነተኛ እና የእዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከባለታሪኮቹ በቀጥታ ያገኘው እና በኢትዮጵያ በተለያዩ ዓመታት ውስጥ በሙሰኞች የተወጉ አሳዛኝ ታሪኮች ናቸው።ታሪኮቹ የሙስናው ስብጥር እና አካሄድ በትንሹ ያሳያል።ይህንን በሰፊው እና በብዛት ሲፈጸም በሃገር ደረጃ ያለው ግዙፍ ውድቀት ለመመንዘር ይረዳል።
ሲቪል አቬሽን
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሥራ ከጀመርኩ ገና ሁለት ዓመት ነበር።በኢትዮጵያ አየርመንገድ ግቢ ውስጥ ብቸኛው የባንክ አገልግሎት ሰጪ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር።ባንኩን ከሚገለገሉት ውስጥ የኢትዮጵያ አየርመንገድ፣ሲቪል አቬሽን እና የኢትዮጵያ ንግድ ቱሪስት ንግድ ሥራ ድርጅት የሚባሉ ነበሩ። አንድ ቀን ጧት የቁጠባ ሒሳብ ክፍል ላይ አገልግሎት እየሰጠሁ በጣም ንቁ የሆነች እና ከካናዳ ወደ ሃገሯ ገብታ ለመስራት ልጆቿን ይዛ ጠቅልላ መጥታ በሲቪል አቬሽን ድርጅት ውስጥ በተማረችው የኢንጅነሪንግ ሙያ ታገለግላለች።ወደ ባንኩ ስትመጣ ለሃገር ስለመስራት፣ስለየውጭ ሃገር ኑሮ አንዳንድ ነገሮች ጣል አድርጋ ትሄዳለች። ይህ ብቻ አይደለም ወጣቷ ወ/ሮ ለሲቪል አቬሽን ስፖርት ክለብ የቅርጫት ኳስ ቡድን እንዲጠናከር የራሷን ድርሻ መወጣቷን አሁንም ባንኩ ጋር በምትመጣበት ጊዜ ካጫወተችኝ የማስታውሰው ነው።
የቅዳሜ ጧት ለቅሶ
ወጣቷ ወ/ሮ አንድ ቅዳሜ ጧት ወደ የቁጠባ ሒሳብ ክፍል መጣች። ካውንተሩ በደንበኞች ተጣቧል።ወጣቷ ቱታ ለብሳለች።ያን ቀን ፊቷ ከእዚህ በፊት እንደነበረው አይደለም። እንቅልፍ የተኛች አትመስልም።ሌላ ጊዜ ፈገግ ብላ ስቃ እያወራች ነበር በገንዘብ ማውጫ 'ቫውቸር ' ላይ የምትጽፈው። ያን ቀን ግን ቀና ብላ ከጎኗ ያሉትን የሲቪል አቬሽን ባለስልጣናት ገልመጥ አድርጋ አይታ የገንዘብ ማውጫው ላይ ጽፋ ''እቸኩላለሁ! ቶሎ አሳልፍልኝ '' ብላ ከባንክ ደብተሯ ጋር ሰጠችኝ።የጻፈችውን የገንዘብ መጠን ስመለከት ሁሉንም ገንዘብ ለማውጣት የሚያዝ ነው። የወረፋ መጠበቅያ ቶክን እየሰጠሁ ''ሰላም ነው አይደል?'' አልኳት።''ቆይ ገንዘቡን ካወጣሁ በኋላ መጣሁ'' ብላኝ ወደ የገንዘብ ካውንተሩ ሄደች።
ከደቂቃዎች በኋላ ተመልሳ መጣች።ካውንተሩ ላይ የነበሩ ደንበኞች ሁሉ ተስተናግደው ሄደዋል። እንደመጣች ምንም ሳትናገር አይኖቿ ላይ እንባዋ ግጥም ብሏል። ወዲያው አንድ ዘመድ ሞቶባት እንደሆነ ወድያው ገመትኩ። ግምቴ ግን ልክ አልነበረም።
''ዛሬ ቻው ልልህ ነው የመጣሁት '' አለች። ቀጠለችና ''ቅድም ዝም ያልኩህ የሲቪል አቬሽን አለቆቼ እዚህ ስለነበሩ ማውራት ስላልፈለኩ ነው '' አለችና ''መሔዴ ነው።አላሰራ አሉኝ። እኔ ሕልሜም ምኞቴም ሃገሬ መስራት ነበር።ነገር ግን አላሰሩኝም።እንደነሱ እንድሰርቅ ይፈልጋሉ። እኔ ደግሞ ከድሃ ሃገሬ ላይ የመስረቅ ሞራል የለኝም።ይህንን ከማደርግ እዛው የማልወደው ካናዳ ልጆቼን ይዤ ለመመለስ ወስኛለሁ።'' ብላ ጧ! ብላ ማልቀስ ጀመረች።ከእርቀት አካውንታቱ እና ምክትል ሥራ አስኪያጁ ይመለከታሉ።ወዲያው ተከታትለው መጡ እና ''አላለፈልሽም እንዴ ያንቺ፣ምንድነው ችግር አለ?'' አለ ምክትል ሥራ አስኪያጁ አቶ ጉታ። ችግር እንደሌለ ገንዘቧን እንደወሰደች ሳግ በተናነቀው ቃላት እራሷ ነገረቻቸው። አካውንታቱ እና ሥራ አስኪያጁ ከሄዱ በኋላ ፈተና ያለ ነው ታግለሽ እንዴት አትቋቋሚም? ወዘተ እያልኩ ቀባጠርኩ። እርሷ ግን ሥራውን ትታ ዩንቨርስቲ ሥራ አግኝታ እንደነበር ነገር ግን የትም ብትሔድ እንደማይለቋት፣ የተከራከረቻቸው ጉዳዮች ከባድ እንደሆኑ እና ለራሷም ሆነ ለቤተሰቧ ከሃገር መውጣት ብቻ አማራጭ መሆኑን በሃዘን አስረዳችኝ። ከፊቷ ላይ የሚነበበው ከገነት ወደ ሲኦል የሚገፉት ሰው የሚሰማው ዓይነት ስሜት ነበር የሚታይባት። ባለፉት ጊዜያት ሁሉ ስትነግረኝ የነበረው በሃገር የመስራት ሞራል፣የሃገር ፍቅሯን ሁሉ እንደገደሉባት ገባኝ።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ እጅግ ብዙ ብሩህ አዕምሮ ያላቸው ወጣት ኢትዮጵያውያን በሙስና መረብ በተተበተበ መዋቅር እንዲሰቃዩ እና በመጨረሻ አቅመ ቢስ ሆነው ሥራቸውን እንዲለቁ ወይንም የባርነት መንፈስ ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ እንደተደረጉ ቤት ይቁጠረው።የሲቪል አቪየሽኗ ወጣት ወይዘሮ ግን ሁሌ የደረሰባትን አስታውሳለሁ።በጊዜው የሲቪል አቬሽን ባለስልጣናትን ስመለከት በጅምላ ጥሩ ስሜት አይሰማኝም ነበር።
ባለ 10ቱ ትዕዛዛት፣ባለ 30 መክሊት ወይንስ ባለ 60 መክሊት
አውሮፓ ውስጥ የሚኖር በአገልግሎቱም የማውቀው ካሕን ነበር።የአውሮፓ ኑሮውን ትቶ ወደ ሃገር ቤት ገባ።በቤተክርስቲያን ትምህርቱ ዕውቀቱ ያላቸው እንደነገሩኝ የትኛውም ቦታ ሊያገለግል የሚያስችል ትምሕርት አለው። ሃገር ቤት በገባ ከወራት በኋላ ደወልኩለት። የትኛውም አጥብያ ቤተክርስቲያን እያገለገለ እንደሆነ ጠየኩት።
''አዬ ባለ 30 ወይንስ ባለ 60 መክሊት ነህ?'' ብለው ጠየቁኝ አለኝ።ይህ ምን ማለት ነው? በማለት ጠየኩት። ነገሩ እንዲህ ነው። አዲስ አበባ ሃገረ ስብከት በኩል አጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ለመቀጠር ጉቦ የሚቀበሉ የሃገረስብከቱ ሰራተኞች የሚቀበሉትን ጉቦ መጠን ለመግለጽ የሚጠቀሙት አስር ሺ አምጣ ለማለት ባለ 10ቱ ትዕዛዛት፣ 30 ሺህ አምጣ ለማለት ባለ 30 መክሊት እና 60 ሺህ አምጣ ለማለት ባለ 60 መክሊት የሚል ቋንቋ ይጠቀማሉ።
በአሁኑ ጊዜ በእየአጥብያ አብያተ ክርስቲያናት ሊቃውንቱ የሚሰጡት ጉቦ ስለሌላቸው በመጠለያ ተቀምጠው ጸሎታቸውን አድርሰው ሲመለሱ።ምንም ትምህርት የለላቸው ግን ከየትም ቃርመው ያገኙትን ጉቦ እየከፈሉ ይቀጠራሉ።ጉቦ የመስጠትም ሆነ የመቀበል ኃጢአትነት የተረዱ ግን እየተከዙ ዘመን ይገፋሉ። ይህ እውነተኛ ታሪክ ነው።
ለአሜሪካ ኤምባሲ የተጻፈው ደብዳቤ ጉድ
የሙስና ልክ ዐይን ያወጣ አካሄያዱ እፍረት የለሽ ነው። ይህ ደግሞ በእምነት ተቋማት ሲሆን የበለጠ አስጸያፊ ነው።ጊዜው በፓትርያሪክ አቡነ ጳውሎስ ጊዜ ነው።የአሜሪካ ኤምባሲ አንዲት ወጣት ለቪዛ ኢንተርቪው ትቀርባለች። ወጣቷ ለቃለ መጠይቁ ለመቅረብ ከያዘችው ሰነድ ውስጥ የድጋፍ ደብዳቤ አብሮ ተያይዟል።ቃለ መጠይቅ አድራጊው ኦፊሰር ሰነዶቿን በሙሉ እያየ ምልክት ካደረገ በኋላ የድጋፍ ደብዳቤዋ ጋር ሲደርስ ግራ ገባው። የድጋፍ ደብዳቤው የተጻፈው ከቤተክህነት ነው። የወጣቷ ስም የሙስሊም ስም ነው። ኦፊሰሩ ቀና ብሎ ወጣቷን ተመለከተ እና ሃይማኖሽ ሙስሊም ነሽ አይደል? ብሎ ጠየቀ። አዎንታዊ መልስ አገኘ።ታድያ እንዴት ቤተክህነት ለምን ዓይነት ሥራ የድጋፍ ደብዳቤ ጻፈልሽ? ማለት በእምነት አትገናኙም።ተሳሳትኩ? ብሎ ጠየቀ። ወጣቷ ሌላ መቀባጠር ውስጥ ገባች።ደብዳቤው ሲጣራ በጉቦ ከቤተክህነት አንድ ማኅተም ያዥ የጻፈው ነው።
የእዚህ ዓይነት በርካታ ጉዶች በየቦታው አሉ። በውጭ ሃገር ሃይማኖታዊ በዓል ሳይኖራቸው።በዓል እንደሚያደርጉ አድርገው መዘምራን ናቸው፣ሰባክያን ናቸው እያሉ ዘመዶቻቸውን ወደ ውጪ የሚያወጡ የሃይማኖት ተቋማት ሙስና ቤት ይቁጠረው።ለማንኛውም የቤተክህነት ጉዳይ ብዙ መታየት ያለበት ጉዳይ አለ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሰራተኛ መስራት አቃተኝ
ወጣቱ የህክምና ዶክተር ነው።ለአጭር ጊዜ ስልጠና ወደ አውሮፓ መጣ።ከስልጠናው ጊዜ ውጭ ከተማ ላሳየው ሻይ ቡና እንላለን።አንድ ቀን በሚሰራበት የአንድ ክልል የጤና ሚኒስቴር ስር ያለ ቢሮ ያለውን የሙስና ዓይነት ከራሱ መንፈሳዊ ህይወት ጋር እየፈተነው እንደሆነ ነገረኝ። መጀመርያ ጉዳዩን ሳልረዳ። ሙስና ሙስና ነው አልተባበርም፣አልፈልግም ብሎ መሞገት ነው ምን ምክር ያስፈልገዋል አልኩት። ቡናውን ፉት ብሎ ጉዳዩን ማስረዳ ጀመረ። ነገሩ እንዲህ ነው፣
ወጣቱ በሚሰራበት የጤና ቢሮ ውስጥ አለቃው በርካታ ስልጠናዎች እንዲዘጋጅ ያደርጋል። ስልጠናውን የሚሰጣቸው ሰራተኞች ከሰለጠኑበት በላይ አበል ይከፈላቸዋል።በመጀመርያ ስልጠናው አስፈላጊ ሆነም አልሆነ ስልጠና ውሰዱ ይባላሉ። ሰራተኞቹ ስልጠና አንወስድም ማለት አይችሉም።የሥራው አካል ነውና።ሥልጠናው እንዲሰጥ የሚደረግበት ድርጅት ግን በአለቃው ዕውቅያ የሆነ እና የራሱ ኮሚሽን እንዳለው ይታወቃል። በእዚህ ሁኔታ ስልጠናው የሙስና ሥራ እንዳለበት እያወቀ ስልጠናውን አልፈልግም ማለት አለመቻል እና አበሉን መውሰድ ለእዚህ ወጣት ዶክተር ከእመንቱ ጋር እያወቀ እያጠፋ እንደሆነ ተሰምቶታል።
ቶሎ ወደ ናይሮቢ ሒዱ
የባሕር ማዶ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው። ድርጅቱ በኤችአይቪ ላይ የሚሰራ ነው። በአዲስ አበባ ቅንጡ በሆነ ህንፃ ላይ ቢሮውን ከፍቷል። በዶክትሬት ደረጃ ያሉ ከፍተኛ ባለሙያዎች ቀጥሯል። ከእነኝህ ባለሙያዎች ውስጥ አንዱ ባለሙያ ያጫወተኝ ነው። የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ለጊዜው ሃገሩ ይቆይና የውጭ ሃገር ዜጋ ነች።የሚገርመው ከሃገሯ የሚላከውን በጀት አለአግባብ በጥቅም በምትተሳሰራቸው ድርጅቶች የሥራ ውል እንደሰጠች እያደረገች ባጀቱን ታጣጣዋለች።
''አንድ ቀን አለኝ'' ይህ ኢትዮጵያዊ ባለሙያ ''አለቃችን ድንገት ወደ ቢሮዬ መጣች እና በሁለት ቀን ውስጥ ሸራተን የኤች አይቪ ግንዛቤ መስጫ ስልጠና ከተለያዩ የመንግስት መስርያቤቶች ሰዎች ጠርተው ስልጠና ስጥ '' አለችኝ።''ቀጠለችና በሚቀጥለው ሳምንትም ሁላችሁም የክፍሉ አባላት ናይሮቢ የሦስት ቀን ስልጠና ትሄዳላችሁ '' አለችና ከፍሉ ወጣች። በኋላ ይህ ባለሙያ ከሥራ አስኪያጇ እንደተረዳው የዓመቱ የሒሳብ ሪፖርት መዝጊያ ስለሆነ ባጀቱን ለመጨረስ ብቻ በሸራተን እና የናይሮቢ ስልጠና ለማጥፋት ተፈልጎ ኖሯል።ሃገር ውስጥ በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲውል የተላከው ገንዘብ እንዲህ በግርግር ስብሰባ ይባክናል።ይህ ባለሙያ አለቃውን በጉዳዩ ላይ ሞግቷል። ያገኘው መልስ። ገንዘቡን የምታመጣው የኔ ሃገር ያንተ እንዲህ መሆን አልገባኝም የሚል መልስ ቃል በቃል ተሰጥቶት ነበር።
ባጠቃላይ ከላይ ለማቅረብ እንደተሞከረው በኢትዮጵያ ያለው ሙስና የማይዳስሰው ተቋም እና ቦታ የለም። ሙስናው በገንዘብ ኦዲት ብቻ ሳይሆን ሥራው በተሰራበት የሥራ ሂደትንም በመመርመር የሚገኝ ነው። ከስራው በጀት ላይ ስንት ተወሰደ ሳይሆን የሥራው ሂደት በመመርያው መሰረት ነው ወይንስ ከመመርያ ውጭ ነው? የሚለው እና የሂደቱ ጤናማነት ሁሉ መመርመር ይገባዋል።ኢትዮጵያ ሙስናን ለመዋጋት በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ቢሮ ስር የሚታዘዝ አዲስ ኮሚቴ ተመስርቷል።ኮሚቴው ሥራው እንዲሳካ እና ኢትዮጵያ ሃብቷን እንድታድን ሙስናን የምናይበት መንገድ እና የሚገባበት ጓዳ ጎድጓዳ ሁሉ መፈተሽ የሕዝብም ሃላፊነት ነው።ይቅናሽ ኢትዮጵያ!
==========///////==========