ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, July 9, 2024

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።



==========
ጉዳያችን ወቅታዊ
==========

የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለም በፖለቲካ፣ምጣኔሃብት ግንኙነት እና የወታደራዊ አሰላለፎች በየጊዜው የተለያዩ ቅርጽ እየያዙ ብቻ ሳይሆን ፍጥጫዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ እያየሉ መጥተዋል።

እነኝህ ለውጦችበበለጠ በቅርብ ቀጣይ ጊዜም ቀጣይ ለመሆናቸው ብዙ ማሳያዎች ቢኖሩም፣የተወሰኑትን ለመጥቀስ፡
  • የመካከለኛው ምስራቅ ከአርባ ዓመታት በላይ በመለስተኛ ግጭት ውስጥ ቆይቶ አሁን በእስራኤል እና በኢራን እንዲሁም ከሊባኖስ ጋር ያለው ግጭት ከቱርክ እስከ ኳታር ያዘለው ሌላ ደመና አለ።
  • አውሮፓ ሩስያ ከዩክሬን በመቀጠል ትወረኛለች በሚል ስጋት ላይ ነው።የኔቶ ጉባዔ ዋና አጀንዳው ዩክሬን ይሁን እንጂ የሩስያ ቀጣይ መንገድ ወዴት ነው? የሚለው ውዥንብር ላይ የጠራ አቋም መያዝ የጀርባ አጀንዳ ነው።
  • አሜሪካ በቀጣዩ ምርጫ የሚመጣው ገና አልታወቀም። ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ለኔቶም ሆነ ለአውሮፓ ጸጥታ አሜሪካ የምትገፈግፈው ገንዘብ ትክክል አይደለም ባይ ናቸው። አውሮፓ ከእዚህ አንጻርም የጸጥታ ዋስትናው ላይ መደናገር አለ።
  • ሩስያና ሰሜን ኮርያ ከሰሞኑ ያደረጉት የቆየውን የወታደራዊ ትብብር ማደስ ሩቅ ምስራቅ ላይ ያለውን አሰላለፍ ቀይሮታል።
  • ብሪክስ የአሜሪካንን ዶላር አስቀርቶ በራሱ በሃገራቱ ገንዘብ ንግድ ለማካሄድ ስራ ጀምሯል።
  • ምስራቅ አፍሪካ የሚሆነው ሁሉ የኢትዮጵያን አካሄድ ተከትሎ ወዴት እንደሚሄድ አላወቀም።ጂቡቴ ኢትዮጵያ ከሱማልያ ላንድ ጋር በወደብ እና የባሕር ኃይል ጣብያ የመመስረት ውል ተከትሎ ገቢዋ እንደሚቀር አውቃ ሱማሌ ላንድን ለመበጥበጥ ስታሰላስልና ስትሞክር ተይዛለች።
  • ሱማልያና የአቶ ኢሳያስ ኤርትራ ጧት ማታ እየተገናኙ በኢትዮጵያ ላይ ይዶልታሉ።ግብጽ በእያንዳንዱ የኤርትራና የሱማሊያ ዱለታ ላይ ሁሉ አለች።
  • ሱዳን በጦርነት እየታመሰች ነች፣ሱማልያም በፈረሰ መንግስት ላይ የተቀመጠ መንግስት አላት።ኬንያ በውስጥ የታመቀ የብሶት ጠኔ ላይ ለመሆኗ የሰሞኑ አመጽ ማሳያ ነው።
  • ቀይ ባሕርን የአቶ ኢሳያስ አስተዳደርም ሆነ የሳውዲ ባሕር ኃይል የሚያልፉትን መርከቦች ከሁቲ አማጽያን ለማስጣል የማይችሉ መሆናቸውን የዓለም ንግድ ሲታወክ ምንም ማድረግ አለመቻላቸውን ዓለም ተመልክቷል።
  • ዓለምን ሰላሟን ለማስጠበቅ አቅም ያለውም ሆነ ተጽዕኖ ፈጣሪ ተቋም አልባ ሆናለች።የዓለምን ሰላም ማስጠበቅ አንዱ ስራው ሆኖ የተመሰረተው የተባበሩት መንግስታት የምስራቅና የምዕራብ መራኮቻ ብቻ ሳይሆን ''ሳንድዊች '' ሆኖ የሚናገረው የማይሰማ፣የሚለው የማይደመጥ ሆኗል።ለእዚህ ማሳያው በዩክሬንም ሆነ በመካከለኛው ምስራቅ ባለፉት ወራት ውስጥ ለተፈጠረው ግልጽ ጦርነት አንዳች ሚዛን የሚደፋ የመፍትሄ ሃሳብ አቅርቦ ያልተደመጠበት መሆኑን ብቻ መመልከት በቂ ነው።
ከላይ ያለው ወቅታዊው የዓለማችን ሁኔታ የሚከተሉትን አዝሎ እንደሚመጣ ግልጽ ያልሆነልን ካለን ቢያንስ መገመት ብንጀምር መልካም ነው። አዝሎ ከሚመጣቸው ጉዳዮች ውስጥ ፡
  • የአለማችን የምግብ ቀውስ ሊባባስ ይችላል።
  • በማናቸውም ጊዜ ምንም ሊሆን ይችላል።
  • በቅርብም ሆነ በሩቅ ሀገሮች መሃከል ጦርነቶች፣ወረራዎች እና ግጭቶች በማንኛውም ሰዓት ሊፈጠሩ ይችላሉ።ምሽት በሰላም ተኝቶ ማለዳ ላይ የአንድ ሃገር ይዞታ በአየር እየተደበደበ መመልከት ሊደጋገም ይችላል።
  • የአካባቢ ''ግልገል ኃያላን '' ይህንን የዓለም አቀፍ ህግ መላላት ተከትለው በተፈጥሮ ሃብት ሲመኟቸው የኖሩ ሀገሮችን ለመውረር እና የውስጥ ቀውሳቸውን ለማስታገስ ሊሞክሩ ይችላሉ።
  • የዓለማችን የኃያላን ሀገሮች ፍጥጫ እና ግጭት በቀጥታ ሳይሆን በ''ግልገል ኃያላን'' በኩል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ይሮጣሉ።
  • የቀኝ አክራሪዎች እና የስደተኛ ጠል ፓርቲዎች በወቅቱ የዓለም ችግር እያስታከኩ በሀገራቸው የበለጠ የመደመጥ ዕድል የሚያገኙበትና የዘረኝነት አካሄዶች የበለጠ ሊባባሱ ይችላሉ።
ወቅታዊ የኢትዮጵያ፣የአፍሪካ እና የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።

ከላይ በመጠኑ ለመዘርዘር የተሞከሩት እየመጣ ያለው እና ወቅታዊው የዓለማችን ሁኔታ ለኢትዮጵያ ከአደጋ ይልቅ ባብዛኛው ዕድል ይዘው መጥተዋል። ይህ ግን እኛው በኛው ካልገፋነው እና ካላጨናገፍነው ነው።ይህ ወቅት የዓለም  የእጥፋት(turning point) ወቅት ነው።ብዙ ሀገሮች የዓለም እጥፋት ወቅት በተነሱላቸው መሪዎች ተጠቅመው ሃገራቸውን አስፈንጥረዋል። ኮርያ፣ሲንጋፖር፣ታይዋን፣ህንድ በምስራቁና የምዕራቡ ፍትግያ ውስጥ በአንዱ ጎራ ከመግባት እስከ ገለልተኝነት ፖሊሲ ተከትለው ሃገራቸውን ያስፈነጠሩ ናቸው።

ኢትዮጵያ በጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥ፣በህዝብ ብዛት፣በመላው ዓለም በሰለጠነ የሰው ኃይል፣በታሪክ ሃብት ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ በነበራት እና በቀላሉ መልሳ ልታነሳው የተዘጋጀ ማንንነት ባለቤት መሆኗ እና የተፈጥሮ ሃብቷ ጭምር የሩቅም ሆነ የቅርብ ሀገር የምታማልል ሃገር ነች።ኢትዮጵያ ይህንን የእጥፋት ጊዜ እጅግ ስልታዊ በሆነ መንገድ መጥቀም ከቻለች ትልቅ ዕድል ከፊቷ ይጠብቃታል።

ኢትዮጵያ ዛሬ በጎጥና በመንደር የሚነተርካት፣ ልጆቿን በጦርነት የሚማግድ አጀንዳ የሚፈለፍልባት፣ የእኔ መንደር ሰው ብቻ ስልጣን ሲይዝ ሀገር ይረጋጋል እያለ የሚሰብክባት፣በልጆቿ ግጭት ባሕር ማዶ ሆኖ በጦርነት ስም ገንዘብ እየሰበሰበ የማይሞላ ሆዱን የሚሞላ ሰው አያስፈልጋትም። ጊዜው ለኢትዮጵያ ወሳኝ ጊዜ ነው። ወቅቱ ኢትዮጵያ የዓለም እጥፋት እንዲያስፈነጥራት መስራት የሚገባበት ጊዜ ነው።ይህንን ለማድረግ ብዙ ዕድሎች መንገዶች ከፊታችን አሉ።የውስጥ ንትርኮችን ለማጥገግ የምክክር ኮሚሽን ጥረት እያደረገ ነው።የዓለምን የእጥፋት አካሄድ ብቻ ሳይሆን ምን ላይ ማትኮር እንዳለባት የሚረዳ መሪ ኢትዮጵያ አላት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለያዩ ንግግሮቻቸው የዓለም የእጥፋት ጊዜን መጠቀም እና ሀገር ማስፈንጠር እንደሚገባ እና እንደሚቻል ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥ ቁልፍ ጉዳዮች በሚል ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚሰሩት ስራዎችን ስንመለከት ብዙ ጉዳዮች ለኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች አሉ።ይህ ማለት የሚያስከፉ፣የሰዎች ሞት፣መፈናቀል እና ስደት ቆሟል ማለት አይደለም። እነኝህ ፈተናዎች ግን እኛው በሚድያ፣በውሸት ትርክት፣ለገንዘብ እና ለስልጣን ተብሎ የሚደረግ የስግብግብ ''ኤሊት '' ፖለቲካና የባዕዳን ሴራ ውጤት መሆኑን ለማመን ብዙ እርቀት መሄድ አያስፈልግም።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የዓለምን እጥፋት ተከትሎ እየሰራች ላለቸው ማሳያዎች በርካታ ማሳያዎች አሉ።ከእነዚህ ውስጥ ፡ የዲፕሎማሲው በሱዳን ጉዳይ ሳይቀር የመካከለኛውን ምስራቅ የሚገዳደር ደረጃ እንዲደርስ ብቻ ሳይሆነ የግብፅ ቦታ እሲኪደበዝዝ ድረስ እየተሄደ ያለው ሂደት፣ኢትዮጵያ ከሦስት አስር ዓመታት በላይ ሳታነሳው የቆየው የባሕር በር ጉዳይ በግልጽ ይዛ የወጣችበት ሁኔታ፣በምግብ ራስን ለመቻል የምትሰራው ስራ፣ኢትዮጵያን አረንጓዴ ለማልበስ የተደረጉት ዘመቻዎች፣ ቱሪዝምን ያማከሉ የሪዞርት ግንባታዎች፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጄንስ ስራ፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ ያለው ለውጥ፣ የመከላከያ ማዘመን ሁሉ የዓለም የእጥፋት ሂደት ውስጥ በብዙ እንዴት ለማትረፍ እንደምትችል እና የሚገባትን ቦታ ለመያዝ የምታደርገው ጥረት አካል ሆኖ ይታየኛል። ከውጭ ሆነን ጦርነት የምንጎስም፣መንግስት እንደሸሚዝ ለመቀየር የምንመኝ፣ የእኔ ሰፈር ሰው ቤተመንግስት ካልገባ ኢትዮጵያ አትኖርም እያልን የምንሰብክ ሁሉ በኢትዮጵያ ወሳኝ ጊዜዋ ላይ ቆመን ለማሰናከል የምንታትር የልጅ እርግማን ሆነንባታል። ያልገባን ካለን፣ እስኪገባን ዝም ብንል። የዓለም እጥፋት ኢትዮጵያን እንዲያስፈነጥር የገባን ካለን ዝምታችንን ሰብረን፣ ኢትዮጵያን እና ለኢትዮጵያ የሚለፉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ብናበረታታ እና ሀገር ብናግዝ። ከእዚህ ውጪ ለኢትዮጵያ እናቷን ሙቀጫ እንደምትወቅጥ ዘነዘና ባንሆንባት? ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።
_________________________________





No comments:

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...