ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, August 9, 2024

''ኢትዮጵያ ልታመልጥ ነው።'' የግብፅ፣የሱማልያ፣የቱርክና የአቶ ኢሳያስ ጭንቀት ጨምሯል። እውን ብልጽግና ''ኒዎ ሊበራሊዝምን'' ሳያላምጥ ውጧል?

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀ ስላሴ በኢትዮጵያ የግብጽ አምባአደር መሐመድ ኦመር ጋድ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተወያዩ በኋላ (ፎቶ ውጉሚ)


==========
ጉዳያችን ወቅታዊ
==========

የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ በየቀኑ ብዙ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ።በጥቃቅን እና ቅጥልጣይ ጉዳዮች ላይ ብቻ ካተኮርን ትልቁ ሀገራዊ ስዕል ይጠፋል ብዬ አስባለሁ። እንደ ሀገር ብዙ መቀረፍ ያሉብን እራሳችን የፈጠርናቸውም ባዕዳን ያቦኳቸውም ችግሮች አሉብን። ሙስና፣የጸጥታ ችግር፣ጎሰኝነትን ማቀንቀን እና ድህነት ወቅታዊ ችግሮች ሆነው በመሬት ላይ የሚታዩ ችግሮች ናቸው። ሁሉንም ግን በበጎ ህሊና፣በህብረት እና ጠንክሮ በመስራት የሚቀረፉ ለመሆናቸው ቅንጣት ያህል የሚያጠራጥር ጉዳይ የለም።

ከጥቃቅን እና ቅጥልጣይ ጉዳዮች ወጥተን ትልቁ ኢትዮጵያ እየሔደችበት ያለውን ጎዳና ስንመልከት እና ወደመንገድ የገባችበትን አገባብ ተመልክተው የተደናገጡትን የቅርብም የሩቅም ሀገሮች ስንመለከት ከፍተኛ መራወጥ ላይ መሆናቸውን እንመለከታለን። ይህ በእንዲህ እያለም በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው መንግስት ከሰሞኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር ተያይዞ ብልፅግና ''ኒዎ ሊበራሊዝምን '' ሳያላምጥ ዋጠ የሚል አዲስ ፕሮፓጋንዳ ተከፍቷል።በሁለቱም ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንሽ እንበል።

''ኢትዮጵያ ልታመልጥ ነው።''  የግብፅ፣የሱማልያና የአቶ ኢሳያስ ጭንቀት ጨምሯል።

ግብጽ በእስራኤል ፍልስጤም ጉዳይ ተወጥራ ከርማ አንድ ዓይኗን ኢትዮጵያ ላይ ጥላ ከርማለች።ቱርክ ወደ 15ኛው ክ/ዘመን የምስራቅ አፍሪካ የባሕር ጠረፍ መቆጣጠር የናፈቃት ትመስላለች። በዘመኑ ቱርክ ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ዛንዚባር ያለውን የባሕር ጠረፍ የተቆጥጠረችበት ''ወርቃማ ዘመን'' የምትለው ጊዜን ለማምጣት ሱማልያን ሰፈር ለማድረግ እየሞከረች ነው።በሊያ ጉዳይ ባላንጣ የሆኑት ግብፅና ቱርክ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር ግን አፍ ለአፍ ገጥመው ማውራት ከጀመሩ ሰንብተዋል። አሁን ዘግይቶ የተሰሙ ዘገባዎች ደግሞ ግብጽ በሱማልያ ጦሯን ለማስፈር ማሰቧ ብቻ ሳይሆን የሚሰፍረው ጦር ደግሞ በኢትዮጵያ ድንበር አጠገብ መሆኑ ነው የተሰማው።

በእዚህ ሁሉ መሃል ወጡ እንዳማረላት ወይዘሮ ከካይሮ እስከ ሞቃዲሾ ደብዳቤ በመጻጻፍ እና እራሳቸው ካይሮ ላይ ብቅ ጥልቅ ያበዙት አቶ ኢሳያስ ናቸው።አቶ ኢሳያስ ሠላሳ ሦስት ዓመታት ሙሉ ልማት ያላመጡላት ግን ወጣቶችን በውትድርና በማሰልጠን የተጠመዱት አቶ ኢሳያስ ግራ መጋባታቸው በግልጽ እየታየ ነው። አቶ ኢሳያስ አንዳንዴ ''ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ'' እንዲሉ የግብፅ አማካሪ ብቻ ሳይሆን አልሲሲ ከሚያስቡት በላይ ገፊ ሀሳብ እያመጡ የቆስቋሽነት ሚና የሚጫወቱት ለግብጾች ኢትዮጵያን በሚገባ የሚያውቁ ''ኤክስፐርት'' ነኝ የሚል አቀራረባቸው ነው ሲሉ አንድ የምዕራብ ዲፕሎማት መናገራቸው ተሰምቷል። 

በሌላ በኩል አቶ ኢሳያስ ሎተሪ ያመለጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስመራ ድረስ ሔደው ስለ ምጣኔ ሐብታዊ ትስስር በተለይ የአቶ ኢሳያስ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ ምጣኔ ሐብት እንዲቀርብ እና በምላሹ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ጂዮግራፊያዊ ወደብ በር እንዲከፍቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ ያሳዩት ዘገምተኝነት ነው። በወቅቱ የነበረውን ስምምነት ተከትሎ ወደ አሰብ የሚወስደው መንገድ ዕድሳት መጀመሩን እና መፋጠኑን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሳይቀር ተመልክተን ነበር። ሆኖም ግን አቶ ኢሳያስ ወደነበሩበት የ ''ስኩዌር ዋን '' ጉዳይ ሲመለሱ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዩን ወደ አደባባይ አመጡት። በመቀጠልም 120 ሚልዮን ሕዝብ በ20 ኪሎሜትር የባሕር እርቀት ላይ ታፍኖ ቢኖር ማንም በሰላም ውሎ እንደማያድር ይህ ተፈጥሯዊ ጉዳይ እንጂ ብዙ ትንተና እንደማያስፈልገው በግልጽ ተናገሩ። ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ ከሱማሌ ላንድ ጋር የባሕር ወደብ ብቻ ሳይሆን የባሕር ኃይል ሰፈርም እንደሚኖራት እኤአ ጥር 1፣2024 ዓም አዲስ አበባ ላይ ይፋ ሆነ። 

''ኢትዮጵያ ልታመልጠን ነው '' የሚለው የግብፅ፣ቱርክ፣ሱማልያ እና የአቶ ኢሳያስ ጭንቀት የኢትዮጵያ በቀይባሕር በኩል የመከሰቷ ጉዳይ ቀዳሚ ቦታ ይዟል። ይህንን ጉዳይ ደግሞ ከእነኝህ ሀገሮች ውጭ ዓለም አቀፋዊው ነባራዊ ሁኔታ በግልጽ መግለጫ አያውጣ እንጂ የኢትዮጵያን በቀይባሕር የመከሰት ጉዳይ የተቃወመ የለም። ይልቁንም አቶ ኢሳያስ ከየመን ሁቲ አማጽያን ያላዳኑት የቀይባሕር ባለ 120 ሚልዮን ህዝብ ሀገር እና በምስራቅ አፍሪካ ግዙፍ ምጣኔ ሐብት ያላት ኢትዮጵያ የተሻለ የንግድ መስመሩን ልትጠብቅ እንደምትችል ዓለም ገብቶታል።

ይህ በእንዲህ እያለ ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካን ብቻ ሳይሆን የግብጽና የኤርትራን ጂኦፖለቲካ የመሳብ ሚና (Pulling role) ኢትዮጵያ በሁለት መንገዶች እየተጫወቸች መሆኑ በግብፅም ሆነ በኤርትራ ላይ ጥላውን አጥልቷል። ይህ ጥላ ደግሞ ኢትዮጵያ አመለጠችን በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ አስከትሏል። የኢትዮጵያ የመሳብ ሚና በግብጽ አንጻር የተከሰተው በዓባይ ግድብ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቅ ተረጋግጧል።በአጭሩ የግብፅ የቧንቧ ውሃ መክፈቻና መዝግያ በኢትዮጵያ እጅ መገኘቱን ዓለም አቀፍ ኃይሎች ግልጽ ሆኖላቸዋል። ኢትዮጵያ ደጋግማ የአባይ ውሃን በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እንደምታምን መግለጿ ይታወቃል።ይህም ሆኖ ግን የጂኦ ፖለቲካውን የመሳብ አቅሟ ከግብፅ አንጻር መቶ ከመቶ የተረጋገጠ መሆኑ ላይ የሚጠራጠር የለም።

በሌላ አንጻር የኢትዮጵያ በህንድውቅያኖስና የቀይባሕር አካፋይ አካባቢ በባሕር ኃይል ይዛ መከሰቷ በጂቡቲም ሆነ በኤርትራ በኩል ከመሬት ሌላ በባሕር ኃይል መገኘቷ የኤርትራን ጂኦ ፖለቲካ ላይ በቀጥታ ያጠላበታል። ይህ ጥላ ደግሞ ያድጋል። አድጎ የት እንደሚደርስ አሁን ለመናገር አይቻል ይሆናል። ነገ ግን ይቻላል።

ቱርክ በሌላ በኩል ሱማልያ ከረጅሙ የእርስበርስ ጦርነት እንዳገገመች በመጀመርያ ከኢትዮጵያ ቀጥላ የተገኘች ሀገር ነች። ቱርክ በሱማልያ ግዙፍ የአይሮፕላን መንደርደርያ፣መዝናኛ ሆቴል እና ሌሎች ስራዎች ላይ መሰማራት የጀመረችው ቀድማ ነው። በያዝነው ዓመት ኢትዮጵያ ከሱማልያ ላንድ ጋር የወደብ ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ደግሞ የወታደራዊ ስምምነት ከሱማልያ ጋር ለመፈጸም አልዘገየችም። ቱርክ ሱማልያ ላይ ያላት ፍላጎት የተፈጥሮ ሃብት ዝርፍያ እና አካባቢያዊ ተጽኖ ፈጣሪ ሆኖ መከሰት ፍላጎቷ ነው።ይህም ሆኖ ቱርክ ግብጽ ወደ ሱማልያ እንድትመጣባት አትፈልግም። ግብጽና ቱርክ በሊብያ በነበረው ጦርነት በነከሩት እጅ መጠን መቆሳሰላቸው ቢታወቅም ኢትዮጵያን ለመክበብ እና የሱማልያን የተፈጥሮ ሃብት ለመዝረፍ ግን ለመስማማት ሲሞክሩ ይታያሉ።
ይህም ሆኖ ግን ቱርክ በኢትዮጵያ ያላት መዋዕለ ንዋይ እና ከኢትዮጵያ ጋር መጣላት በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአፍሪካ አንጻር ያለውን ወጪ ስላሰሉት በኢትዮጵያ እና በሱማልያ መካከል የሰላም ንግግር አንካራ ላይ ማስጀመራቸው እና ሰሞኑንም ሁለተኛውን ክፍል ንግግር ለማድረግ እየተዘጋጁ ነው። እዚህ ላይ ግን ግብፅ፣ቱርክ፣ሱማልያ እና አቶ ኢሳያስ የገባቸው ጉዳይ አንድ ነገር ነው። ኢትዮጵያ ልታመልጣቸው መሆኑ ገብቷቸዋል። ሊያስቆሟት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ነገር ግን አልቻሉም። አሁን እየሞከሩት ያለው ከበባ ለመፈፀም ነው። ቱርክ እና ግብጽ በሱማልያ በኩል፣ አቶ ኢሳያስ በሰሜን በኩል ኢትዮጵያን ለመክበብ ይሞክራሉ። ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር በኩል መከሰቷ የሚያማቸው እንግዲህ ከበባው የተሟላ የማያደርገው ይሄው የኢትዮጵያ በባህር በር በኩል መከሰት ነው።

እውን ብልጽግና ''ኒዎ ሊበራሊዝምን'' ሳያላምጥ ውጧል?

ሰሞኑን አንድ ወዳጄ ደወለልኝና የእርሱ አባባል ነው፣ስለ ቃሉ ይቅርታ እየጠየኩ ''አንድ እንቁራሪት የዋጠ የሚመስል ዩቱበር ያቀረበውን ዘገባ ሰማህ?'' አለኝ። ዘገባው አቶ መለስን የኒዎ ሊበራል ተከላካይ እና የሀገር ሉዓላዊነት ጠባቂ አድርጎ ያቀርብና ብልፅግና ''ኒዎ ሊበራሊዝም ሳያላምጥ የዋጠ'' በማለት ያቀርበዋል።

ዘገባውም ሆነ ዘጋቢው አፍቃሪ ህወሓትም ቢሆንም የሚነገረን ታሪክ ግን የጥንት ታሪክ ሳይሆን በሕይወታችን ያየነውን እና የምናውቀውን ጉዳይ ነው። አቶ መለስ ''ልማታዊ መንግስት '' በሚል በዓለም ንግድ ማዕከል የነገሩን እና ሀገር ውስጥ መሬት ላይ የሰሩትን ማስታወስ ነገሩን ግልጽ ያደርገዋል። እዚህ ላይ ኢትዮጵያ በወታደራዊው መንግስት ዘመን በነበራት ምጣኔ ሀብት ደረጃ አቶ መለስ አቆይተዋታል የሚል ክርክር እያነሳሁ አይደልም። በመኖር ብቻ የሚመጣም ዕድገት አለ። ነገር ግን ልማታዊ መንግስት ብለው ኢትዮጵያን በምጣኔ ሀብት መንገድ የገፏት ወዴት ነበር? ብሎ መጠየቅ ግን ተገቢ ነው።

አዎን! አቶ መለስ በዓለም ንግድ ኮንፍረንስ ላይ የግል ባንክ አናስገባም፣ ቴሌን አንሸጥም ብለዋል። ቀጥለው ግን ወደፊት ግን እናደርጋለን የሚል ጨምረውበታል። ወደ ፊት ያሉት በ2016 ዓም ነው ወይንስ በፊት አይታወቅም። እርሳቸውን ሞት ስለቀደማቸው። አቶ መለስ ግን ይህንን ካሉ በኋላ የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት በአፍሪካ ግዙፍ ብለው አቦይ ስብሐት በጠሩት በትግራይ ልማት ማኅበር የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ጠፍረውት በዓለም መድረክ ግን ልማታዊ መንግስት ነን የሚል ንግግር ማሰማታቸውን የዘነጋን ካለን የማስታወስ ችግራችን እንጂ በዘመናችን ያየነው እውነት ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ በጎሳ በተደራጀ የምጣኔ ሀብት አደረጃጀት ተፈርዶባት፣ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ብድር ወስዳ ጨርሳ ኮሜርሻል ብድር የገባች ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ 'ግሎባል ፋይናንሻል እንተክግርቲ'' የተሰኘ አለምአቀፍ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት ከ 2000  እስከ 2009 ዓም እኤአ   ብቻ ከኢትዮጵያ ከ 11.7(አስራአንድ ነጥብ ሰባት ቢልዮን ዶላር) ቢልዮን ዶላር በላይ በህገወጥ መንገድ መውጣቱን የገለጠው በአቶ መለስ የልማታዊ መንግስት ስም በተጀቦነ ፖሊሲ በክሉ መሆኑን ከረሳነው እናስታውሰው።

በዶ/ር ዐቢይ የሚመራው የብልፅግና መንግስት ''ኒዎ ሊበራሊዝምን '' ሳያላምጥ ውጧል? የሚለውን ጥያቄ የጠየኩት መጀመርያ ለራሴ ነው። ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአማካሪ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ጋር የሄዱበት መንገድ ''ኒዎ ሊበራሊዝምን '' ሳያላምጡ የዋጡ መሪ አያደርጋቸውም። ይህንን ለመረዳት በመጀመርያ ኒዎ ሊበራሊዝም ምንድን ነው? የሚለውን በመጠኑ ማሳየት ያስፈልጋል።

ከቀዝቃዛው ጦርነት ማክተም ጀምሮ የኒዎ ሊበራሊዝም ፖለቲካል-ኢኮኖሚ ፍልስፍና በአለማችን ላይ በምዕራቡ ዓለም ሰፍኖ የቆየ ብቻ ሳይሆን የምስራቁን የኮሚኒስት ዓለም መገዳደርያ ርዕዮተ ዓለም ሆኖ በአዲስ መልክ ተነቃቃ። አዲሱ ሊበራሊዝም (Neo-liberalism) እንደ ሰደድ እሳት በተለያዩ አህጉሮችና ሀገራት ውስጥ እንዲቀጣጠል ያደረገው በእንግሊዝ የጠቅላይ ሚኒስትር ታቸር ወደ ስልጣን መምጣት እና በአሜሪካ ደግሞ የሮናልድ ሬገን ዋይት ሃውስ መግባት ለኒዮ ሊበራሊዝም መስፋፋት ወርቃማ ዘመኑን አመጣ። ኒዎ ሊበራሊዝም መሰረታዊ ፍልስፍናው ምጣኔ ሀብቱን ለግል ባለሃብቱ በመልቀቅ መንግስት ያለውን ሚና በሂደት እየለቀቀ ይምጣ የሚል ሃሳብ ገዢው ሀሳብ ነው። 

ይህንን መሰረታዊ ሃሳብ በምጣኔ ሀብት ጠበብት የራሱ የሆነ መከራከርያ ነጥቦች ቢይቀርቡበትም በኢትዮጵያ ግን ከኒዎ ሊበራሊዝም አንጻር የአቶ መለስ እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ አፈጻጸም በትንሽ ብልጭታ አንስተን መሄዱ ብዙ ነገር ግልጽ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ። የአቶ መለስ የምጣኔ ሀብት አፈጻጸም ግዙፉን የምጣኔ ሀብት ባለቤትነት ኤፈርት ተቆጣጥሮ የቀረውን የመንግስት ተቋማት ደግሞ አሁንም በጎሳዊነት ላይ የተመሰረተ አሿሿም ላይ የተመሰረተ አካሄድ ተከትለዋል። ለምሳሌ የሜቴክን እንቅስቃሴ ማስታወስ በቂ ነው። ሜቴክ የህወሃት የጦር ሹማምንት የግል ንብረት በመሰለ መልኩ በኢትዮጵያ ሃብት ሲመዘብር ምዝበራውም በጎሳ በተደራጁ ግለሰቦች ኪስ እንዲገባ ተደርጎ ኖሯል።

የአቶ መለስ ልማታዊ እየተባለ የተጠራው ፖሊሲ የመንግስትን ተቋማት አጠናክራለሁ ቢልም ቁልፍ የሆኑ የኢትዮጵያ የገንዘብ ተቋማት ከማዳከም አልፎ ለመዘጋት እሩብ ጉዳይ አድርሶት ለውጡ መጥቷል። ለእዚህ ማሳያ የሚሆነው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ላይ የደረሰው ጥፋት ነው። የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በተለይ ከ5 ቢልዮን ብር በላይ ዕዳ የገባው በብሔር የተደራጁ ብድር በጋምቤላ ለታደሉት ጠፍ መሬት በመስጠት ነበር። ከኒዎ ሊበራል የራኩ ነኝ። ኒዎ ሊበራልን ሳላላምጥ አልውጥም አሉ የተባሉት አቶ መለስ በተቃራኒው የመንግስታዊ ቁልፍ ተቋማትን ግን በእዚህ ደረጃ ሲያጎሳቁሉ ተዉ ያለ የለም።

ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የደከሙባትን ቁልፍ መንግስታዊ ተቋማት ያጠናከረችባቸው ዓመቶች ናቸው። በኪሳራ መንገድ ላይ ሲቆዝም የነበረው የልማት ባንክ ዛሬ ከኪሳራ ወጥቶ በርካታ የሀገሪቱን ማክሮ ፕሮጀክት ላይ መሳተፍ ጀምሯል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መስርያቤቱን ከመጨረስ አልፎ የነበሩበትን የተበላሹ ብድሮች ከመቀነስ አልፎ አሁን መልሶ የመሪነቱን ሚና በሚገባ እየተጫወተ ነው። የኢትዮጵያ ቴሌ ኮምዩኒኬሽን ዛሬ ከግዙፍ የመንግስት ተቋማት አንዱ ከመሆን አልፎ የገንዘብ ማስተላለፍ ስራ አልፎ በሚሰጠው የኦንላይን ክሬድት ጨምሮ ከ70 ሚልዮን በላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ ተደራሽ ያደረገው ባለፉት አምስት ዓመታት ነው። 

ለማጠቃለል የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግስት ባለፉት አምስት ዓመታት ያሳየን የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ጭልጥ ብሎ የኒዎ ሊበራል መንገድን የተከተለ ላለመሆኑ ማሳያው የመንግስት ሚና ከምጣኔ ሀብቱ ውስጥ መገለል አይደለም ዋና ተዋናይ መሆኑን የሚያምን መሆኑን ለማወቅ ባለፉት አምስት ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ ያጠናከራቸው ቁልፍ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን መመልከት ነው። ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ከዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ጋር በነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም ድርድር ላይ የመንግስትን ቁልፍ የምጣኔ ሀብት ተዋናይነት ለድርድር አለማቅረብ ብቻ ሳይሆን ዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍልን መደጎም የሚለውን ሀሳብ የዓለም ባንክ የማይደግፈው ሃሳብ ቢሆንም መንግስት ለድርድር ያላቀረበው ብቻ ሳይሆን መንግስት በመሪነት የሚፈጽመው መሆኑን ገልጾ የገባበት ስራ ነው። በኒዎ ሊበራል ሀሳብ መንግስት በፍጥነት ከሁሉም የምጣኔ ሀብት ሚና ይውጣ የሚለው አባባል ሳትቀበል መሄድ የሚከፈልበት ዋጋ አለ። መንግስት ''ኒዎ ሊበራልን '' ሳያላምጥ ዋጠው ከማለት፣ የመንግስት በምጣኔ ሃብት ዘርፍ የሚጫወተውን ሚና እያጎላ የግል ዘርፉን ለኢንቨስትመንት በሚያግዝ መልኩ ለምሳሌ የውጭ ምንዛሪ ተመን እጁን አነሳ የሚለው አገላለጥ የተሻለ ነው። በውጭ ምንዛሪ ተመን አንጻርም አሁንም የአንበሳው ድርሻ የሚይዘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመሆኑ ተመኑ ላይ አሁንም መንግስት በሚፈልገው መንገድ የማጥላት ዕድሉ ከተወሰኑ ወራት በኋላ አይመጣም ማለት አይቻልም። ምክንያት አሁንም አብዛኛውን የውጭ ምንዛሪ በንግድም ሆነ በብድር እጁ የማስገባት የአንበሳው ድርሻ የመንግስት መሆኑ ከኢትዮጵያ አንጻር ቢያንስ በአሁኑ ሰዓት ግልጽ ነው። ባጭሩ መንግስት ''ኒዎሊበራሊዝምን '' ሳያላምጥ ሲውጥ ቢያንስ በገሃዱ ዓለም አላየንም።ዩቱብ ላይ ግን እንደመጣ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ማውራት ይቻል ይሆናል።
========================//////=============


 


No comments:

በኢትዮጵያ የእገታ ወንጀል ተሳታፊ አራት አካላት ናቸው። ለችግሩ የመፍትሄ አካላት ሁለት ናቸው።ሁለቱ አካላት ምን ይስሩ?

======= ጉዳያችን ======= በኢትዮጵያ ዜጎችን እያገቱ ገንዘብ የሚቀበሉ ወንጀለኞች ከተራ ወንጀለኝነት አልፎ በታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ ማግኛነት መዋል ብቻ ሳይሆን ዜጎችን የማሸበርያ ፋሺሽታዊ ተግባር ሆኗል። እገታ የ...