ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, December 25, 2015

ሰበር ዜና: አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢትዮጵያ መሬት ለሱዳን የመሰጠቱን ጉዳይ ዳግም አረጋገጡ።ንግግራቸው የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አስመስሏቸዋል።''በታሪካችን ያላየነው ረሃብ ላይ ነን'' አቶ ኃይለ ማርያም (ጉዳያችን ዜና)



ከግማሽ ክፍለዘመን በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ፓርላማ ማማ 

አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ዛሬ ታህሳስ 15/2008 ዓም በኢትዮጵያ ፓርላማ ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ ላይ በተለይ በኦሮምያ ክልል ለተነሳው ሕዝባዊ አመፅ እና በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው የድንበር ጉዳይ ላይ  የተለመደ አወዛጋቢ እና የበለጠ አወሳሳቢ ንግግሮችን ተናግረዋል።

በኦሮምያ የተነሳውን ሕዝባዊ አመፅ ችግሩን፣መነሻውን እና መፍትሄውን የጠቆሙበት አገላለፅ የእራሳቸውን እና የመንግስታቸውን መፍትሄ ቢስነት በአደባባይ በድጋሚ ያጋለጠ ነው።ችግሩ ገበሬው መረጃ አለማግኘቱ ነው ማለታቸው እና በውጭ ኃይሎች ቅስቀሳ ነው የሚለው እርስ በርሱ የተቃረነ አነጋገር በእራሱ ለእራሳቸውም በአግባቡ የገባቸው አይመስልም።ችግሩን መንግስት ስለ ፕላኑ አለመንገሩ ነው ያሉት እና አሁን መንግስታቸው እያናገረ ያለው በጥይት መሆኑን ለሚያስተውለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ንግግራቸው በሕዝቡ ላይ ከመዘባበት ያለፈ አንዳች የሚሰጠው ፋይዳ የለም።በመፍትሄነት ያስቀመጡትም ምንም አዲስ ነገር የሌለው እና አሁንም መልሰን እንነግረዋለን የሚለው አባባል ንግግሩ በጥይት እንደሆነ አመላካች ነው።ሕዝብ የሚባለው እና የሚደረገው ስላልገባው ነው የሚለው አባባል በእራሱ ለሕዝብ ያለን የንቀት ደረጃ አመላካች ነው።በሰላማዊ ሰልፍ እጆቻቸውን ወደ ሰማይ እየሰቀሉ ድምፃቸውን ያሰሙ ታዳጊዎችን በጥይት አረር ከመቱ (እንደ አቶ ኃይለማርያም አነጋገር 'ካናገሩ') በኃላ አሁንም እናናግራለን እያሉ መዘባበት በእራሱ ህዝብን የአላዋቂነት ጥግ ነው።

በሌላ በኩል የሱዳን እና የኢትዮጵያን የድንበር ማካለል ጉዳይ ላይ የጀመሩበት አረፍተ ነገር እና በመካከል እና በመጨረሻ ላይ የደመደሙበት ንግግር ኢትዮጵያ በእዚህ አይነት ደረጃ የባዕዳንን ጉዳይ የሚያስፈፅም መንግስት ኖሯት እንደማያውቅ በግልፅ የሚያሳይ ነው።

''በመሬት ጉዳይ ላይ የተደረገ ድርድር የለም። በኢትዮጵያ እና በሱዳን መሃል ያለው ድንበር በደንብ ስላልተስተካከለ በእርሱ ላይ ነው እየሰራን ያለነው'' ካሉ በኃላ የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር የሚናገሩ እስኪመስል ድረስ የኢትዮጵያን ክብር በሚነካ መልኩ ሱዳንን እየረበሽን ያለነው የእኛ ገበሬዎች ናቸው።አሁን የሚያርሱት መሬት የሱዳን መሬት ነው ብለው ለመከራከር ሞክረዋል።ይህ ማለት ባጭሩ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ሲያርሱት የነበረው መሬት በእራሳቸው አገር ጠቅላይ ሚኒስትር መሬቱ የሱዳን ነው እየተባሉ ነው ማለት ነው።በተለይ የሱዳን ወታደሮች ለስራ በወሰዷቸው ኢትዮጵያውያን ላይ ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ብቻ እጅግ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ስለመገደላቸው አንዳች ያልተነፈሱት አቶ ኃይለማርያም ይልቁንም የኢትዮጵያን ገበሬዎች በሱዳን ተገብተው ሲወቅሱ እንዲህ ብለዋል-  
''ከእኛ አካባቢ እየሄዱ ሱዳናውያንን እየገደሉ የሚመለሱ'' እንደሳቸው አገላለጥ ''ሽፍቶች''ናቸው ሲሉ ተደምጠዋል።በመቀጠል አቶ ኃይለማርያም እንዲህ አሉ: ''በርካታ ኪሎ ሜትሮች ሱዳን ውስጥ ገብተው የሚያርሱ እኛ የምናውቃቸው ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች አሉ''  በማለት እነኝህ መሬቶች ለጊዜው ለሱዳን አይሰጡ እንጂ የሱዳን መሆናቸውን ባረጋገጡበት ንግግራቸው በቀጣዩ የድንበር ማካለልም መንግስታቸው የሱዳን መሆናቸውን እንደሚያውቅ አሁንም እንደ ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሳይሆን እንደ ሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ባጠቃላይ ድንበሩን በተመለከተ ከተናገሩት መረዳት የሚቻለው ሁለት ጉዳይ ነው።አንዱ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የድንበር ማካለል ሂደት ላይ ናቸው የሚለው ዜና ትክክል መሆኑን።በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ አሁንም እንደ ኢትዮጵያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይሆን በሱዳን ወገን ተገብተው የኢትዮጵያን ገበሬዎች እና ባለ ሀብቶች የሱዳንን መሬት አረሱ እያሉ ይህ መሬት ለሱዳን እንደሚገባ በአንደበታቸው ሲናገሩ ተሰምቷል።በሌላ አነጋገር ለብዙ ትውልዶች መሬቱን ሲያርሱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከመሬታችን አንነቀልም ካሉ ከሱዳን ወታደሮች ጋር ተባብረው ገበሬዎቹን እና ባለ ሀብቶቹን የማባረር ሥራ እንደሚሰራ እየገለጡ ነው ማለት ነው።ምክንያቱም በአደባባይ መሬቱ የኢትዮጵያን አይደለም።ለጊዜው ነው ሱዳኖች የፈቀዱልን ካሉ በኃላ ይህንንም የሱዳን ውለታ መሆኑን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስረዳት ሲውተረተሩ ተሰምተዋል።

በመጨረሻም አቶ ኃይለማርያም ''በምግብ እራሳችንን ችለናል'' ብለው በተናገሩ በወራት ውስጥ በዛሬው እለት ደግሞ ካለ አንዳች እረፍት ''የገጠመን ድርቅ በታሪካችን ምናልባትም ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ አይተነው የማናውቅ በእኔ አመለካከት እጅግ የከፋ ድርቅ ነው'' ሲሉ ተደምጠዋል።ለድርቁ የሰጡት መፍትሄ ግን የበለጠ አስቂኝ ነው።መፍትሄዎቹ የሚመጡ እርዳታዎችን መቀበል እና የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ነው ይላሉ አቶ ኃይለማርያም።ጥያቄው ግን  ከእሩብ ክ/ዘመን አምባገነናዊ እና የከፋፍለህ ግዛ የኢህአዴግ/ህወሓት አገዛዝ በኃላ ኢትዮጵያ በታሪክ ያላየችው ርሃብ ላይ ነች ማለት እና የውሃ እጥረት ችግር ለሆንባት አገር የውሃ ጉድጓድ መቆፈር መፍትሄ ነው ማለት ምን አይነት የአስተሳሰብ ድህነት ነው? የሚል ነው።ባጭሩ አቶ ኃይለማርያም ህወሃቶች ስልጣን እንዲለቁ እና የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት ሿሚዎቻቸውን ቢመክሩ እና የመሸበት ቢያድሩ የተሻለ ነው።

ጉዳያችን GUDAYACHN
ታህሳስ 15/2008 ዓም (December 25/2015)

Wednesday, December 23, 2015

ሶማልያ ውስጥ ማንም ሰው የክርስቶስን ልደት በዓል እንዳያከበር ጥብቅ መንግስታዊ መግለጫ ተሰጠ።Somali government bans Christmas celebrations


ማልያ 

የሶማልያ መንግስት የሃይማኖት ጉዳይ ዳይሬክተር፣ሼክ መሐመድ ኬይሮው ማንም ሰው በሶማልያ ውስጥ የክርስቶስን ልደት እንዳያከብር ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላለፉ።ባለሥልጣኑ ''የልደት በዓል የሚያከብሩትን በሙሉ አስጠነቅቃለሁ።የክርስቲያኖች በዓል የሆነው የልደት በዓል  ለእስላማዊቷ አገር ምንም ማለት አይደለም'' ብለዋል። እንደ ሮይተርስ ዘገባ ባለሥልጣኑ በሞቃዲሾ በየትኛውም ስፍራ እና በሶማልያ ውስጥ የክርስቶስን ልደት የሚያከብሩ ካሉ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው የሚገልፅ ማሳሰብያ እና ትዕዛዝ ለሶማሌ ፖሊስ እና የደህንነት ቢሮ መተላለፉን ገልፀዋል።

ባለሥልጣኑ ይህንን ይበሉ እንጂ በሶማሌ በሺ የሚቆጠሩ የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ሰራዊት ይገኝባታል።ይህ ሰራዊት ደግሞ ከቡሩንዲ፣ዑጋንዳ እና ኬንያ  የተውጣጣ ሲሆን ባብዛኛው ክርስቲያኖች መሆናቸውን የሮይተርስ ዜና ያትታል።ኢትዮጵያም ሰራዊቷ በሱማልያ እንደሚገኝ መነገሩ ይታወሳል።

የሮይተርን ሙሉ ዜና ለማንበብ ከእዚህ በታች ያለውን ማያያዣ ይጫኑ።

ምንጭ: ሮይተርስ  Reuters   

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com 
ታህሳስ 13/2008 ዓም (December 23/2015)

Saturday, December 19, 2015

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ያዘጋጀው ሰልፍ ታህሳስ 8/2008 ዓም (ደሴምበር 18/2015 ዓም) በኖርዌይ ፓርላማ ፊት ለፊት ተደረገ።

የዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት ኖርዌይ ያዘጋጀው ሰልፍ ባለፈው ታህሳስ 8/2008 ዓም (ደሴምበር 18/2015 ዓም) በኖርዌይ ፓርላማ ፊት ለፊት ተደርጎ ነበር።የሰልፉ አላማ በኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመውን ግድያ፣በጎንደር ሕይወታቸው በወያኔ ወታደሮች የተገደሉትን በመቃወም እና ለሱዳን ሊሰጥ በዝግጅት ላይ ነው የተባለው የድንበር ውል በመቃወም ነበር።

ሰልፉ ከመሃል ኦስሎ ተነስቶ ወደ ኖርዌይ ፓርላማ በማምራት ለኖርዌይ ፓርላማ በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ እና የሰልፉን አላማ የያዘ ደብዳቤ በመስጠት ተፈፅሟል። የፓርላማው ተወካይም ሰልፈኞቹ ወዳሉበት በመምጣት ወረቀቱን ከተቀበለ በኃላ ለሚመለከተው ክፍል እንደሚያደርስ ለተሰብሳቢዎቹ ቃል ገብቷል።

ከእዚህ በተጨማሪ  በሰላማዊ ሰልፉ ላይ ከዲሞክራሲያዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ድጋፍ ድርጅት በኖርዌይ አመራር አቶ ዳንኤል አበበ፣ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት እና ዲሞክራሲ ንቅናቄ ዶ/ር ሙሉዓለም አዳም፣ ከኖርዌይ ሸንጎ አቶ ግደይ ዘርአፅዮን፣ከኢትዮጵያ ማኅበረሰብ በኖርዌይ ወ/ሮ ዙፋን አማረ ተገኝተው በአገራችን በስርዓቱ እየደረሰ ያለውን ግፍ በማብራራት ንግግር አድርገዋል።

የሰልፉን ፎቶዎች በከፊል ከእዚህ በታች ይመልከቱ (ፎቶ ጉዳያችን)










ሰልፈኛው ወደ ኖርዌይ ፓርላማ ሲያመራ 
 የኖርዌይ ፓርላማ ተወካይ 






ጉዳያችን GUDAYACHN BLOG

Tuesday, December 15, 2015

ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት /ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/


ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት
/ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/
===================================

አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺእኮ ማንም የላት….
አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፤ ….
እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ …
አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከእናቴ ማኅፀን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
በሕፃ እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
በገጠር የደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅ እና ከሚዳቋ፣ ከዥግራ ጠረን ስተሸሽ
በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም፣ ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፣ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ 
ለጥማድ በሬዎች ራት፣ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
ለግልገሌ ካውሬ ከለል
እማሳው ሥር ጎጆ መትከል
ለፀሐይ የሾላ ጠለል፣ ለዝናብ የገሳ ጠለል
ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
የግጦሽ ሣር ሲለመልም፣ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፣ ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፣ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፣ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ …..
ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?

ያቺን የልጅነት የምሥራች? የሕፃንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፣ የምኞት የተስፋ ብፅአት
ያቺን የልጅነት እናት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፣ ጥርሶችሽን ትነክሺባት?
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ባገልግሎትሽ ስዋትት
ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት፣ ከድጓ ቤት እመጻሕፍት
ካንቺ ተቆራኝታ ዕድሌ፣ ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ
ከቀፈፋ ደጀሰላም፣ ከቤተልሔም ቅዳሴ
እኰ፣ ቀፎ ዳባ ለብሶ
ቅኔ ዘርፎ ግስ ገሦ
መቅደስ አጥኖ ማኅሌት ቆሞ
በልብስ ተክህኖ አጊጦ፣ በብር አክሊል ተሸልሞ
እመ ብርሃን ያንች ጽላት፣ ነፍስ ላይ በእሳት ታትሞ
የመናኒው ያባ ተድላ፣ ረድ ሆኜ፣ አብሮኝ ታድሞ
ሕይወቴ እምነትሽን ጸንሶ
ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
ለሕንፃሽ መዲና ቆሞ፣ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ሆነሺኝ የእምነቴ ፋኖስ
ለዋዜማሽ ግሸን ማርያም፣ ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ፣ በወንበሩ አኖርሺኝ፣ በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ
ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ፣ ከምትሰጪኝ የፍርሃት ጦስ
ምነው በረኝነት እድሜ፣ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ
የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ፣ ወርዶ በጨለማ በርኖስ
ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ጽናት ስጪኝ እንድካፈል፣ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፣ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን፡፡ …..
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ፡

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com 

የህወሃት እና የሱዳን ግንኙነት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያለመ ነው። ''የአገሪቱ በጀት 100% ለመከላከያ ቢውልም አይበቃንም'' አልበሽር ''ሱዳን 70% በጀት ለመከላከያ እና ፀጥታ ታውላለች'' በሱዳን የእንግሊዝ አምባሳደር አሮን (ጉዳያችን ዜና)

Photo :-Sudan Tribune


ከትናንት በስቲያ እሁድ ታህሳስ 3/2008 ዓም  በሱዳን አየር ኃይል ማዘዣ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት አልበሽር ሱዳን ወደ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ መሸጋገር አለባት ብለዋል።ከእዚህ በተጨማሪም እጅግ በፈጣን ሁኔታ የሱዳንን ደህንነት ሊያስከብር የሚችል የአየር ኃይል መገንባት አለብን ብለዋል።የሱዳኑ ፕሬዝዳንት አገራቸው ለመከላከያ የምታወጣው በጀት በዝቷል የሚሉ ተቺዎቻቸውን በቁጣ ተናግረዋል።በመቀጠልም ''በዙርያችን ያሉ ፀጥታቸው የተናጋ አገሮችን ተመልከቱ። የአገሪቱ በጀት 100% ለመከላከያ ቢውልም አይበቃንም።የእራሳችን የጦር መሳርያ ፋብሪካ ያስፈልገናል....እጅግ በፈጠነ ሁኔታ ትልቅ አቅም ያለው የአየር ኃይል መገንባት አለብን'' ብለዋል ፕሬዝዳንት አልበሽር።በሌላ በኩል በሱዳን የእንግሊዝ አምባሳደር አሮን ''አሲያስ'' ለተሰኘ ጋዜጣ ሲናገሩ ''የሱዳንን ዕዳ መቀነስ ፈፅሞ አይታሰብም።ምክንያቱም እስከ 70% በጀት ለመከላከያ እና ለፀጥታ ጉዳይ እንጂ ለሌሎች የልማት ዘርፎች እንደ ትምህርት፣ጤና ለመሳሰሉት አታወጣም።'' ብለዋል።

ፕሬዝዳንት አልበሽር ባለፈው ሳምንት ጋምቤላ ኢህአዴግ/ህወሃት ''የብሔር ብሔረሰቦች በዓል'' የብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤት ባደረጋት አገር  በከፍተኛ ደረጃ የአገሪቱን ገንዘብ በሚያባክንበት ዝግጅት ላይ ተገኝተው ምሽቱን አዲስ አበባ መመለሳቸው እና ከህወሃት ባለስልጣናት ጋር መገናኘታቸውን የሱዳኑ ''ሱዳን ትሪቡን'' መዘገቡ ይታወሳል።በአሁኑ ወቅት ህወሃት እና የሱዳን መንግስት የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ በሚሰጥ እና ሕዝብን፣አገርንና ታሪክን በሚያዋርድ መልኩ በኢትዮጵያ ላይ በጥምር ሴራ እየሸረቡ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው።ህወሃት የኢትዮጵያ ህዝብን አንድነት በሚያናጋ መልኩ ጎሳ ከጎሳ የማጣላት እና ከውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያን የማዳከም ሥራ እየሰራ ለመሆኑን ብዙ እማኞችን መጥቀስ ይቻላል።በአገሪቱ ላይ የታወጀው የጎሳ ፌድራሊዝም 25 ዓመታት ያክል  ኢትዮጵያን ሰላም የነሳ መሆኑ እየታወቀ እና ውጤቱም በኦሮምያ እና በሌሎች ቦታዎች የበለጠ ፀጥታ የነሳ መሆኑ እየታየ ለችግሩ የበለጠ ''ቤንዚን የማርከፍከፍ'' ሥራ አሁንም በህወሃት እየተፈፀመ ነው።በሰሜን ጎንደር የ''አማራ እና የቅማንት'' ሕዝብ በሚል ሕዝቡን የመከፋፈል 'መንግስታዊ የዘር ፍጅት' እንዲፈፀም መደረጉን እና እስካሁን ከአንድ መቶ በላይ  ሕዝብ ማለቁን ኢሳት ራድዮ በታህሳስ 4/2008 ዓም ከአካባቢው ያነጋገራቸውን ነዋሪዎች ጠቅሶ ገልጧል። 


የእዚህ የ''አማራ እና የቅማንት'' ሕዝብ በሚል የመከፋፈል ሥራ ላይ የሱዳን የሞራልም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ ከወያኔ ጋር ሊኖርበት እንደሚችል የብዙዎች ጥርጣሬ ነው።ሱዳን ሰፊ የሆነውን የኢትዮጵያ ለም መሬት እና ወንዞች ወደ ግዛቷ ለማካለለ ከህወሃት ጋር መስማማቷ እና ሰሞኑን ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚችል ሲገለጥ ነው የሰነበተው። ዛሬ ታህሳስ 5/2008 ዓም በዋሽንግተን ኢትዮጵያውያን በሱዳን ኢምባሲ በር ላይ የድንበር ውሉን በመቃወም ትልቅ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግ ይታወቃል።


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com 
ታህሳስ 4/2008 ዓም (December 15/2015)

Source:- Sudan Tribune December 13/2015

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...