ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, December 15, 2015

ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት /ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/


ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት
/ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን/
===================================

አዬ፣ ምነው እመ ብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
እስከመቼ ድረስ እንዲህ፣ መቀነትሽን ታጠብቂባት?
ልቦናሽን ታዞሪባት?
ፈተናዋን፣ ሰቀቀኗን፣ ጣሯን ይበቃል ሳትያት?
አላንቺእኮ ማንም የላት….
አውሮጳ እንዲሁ ትናጋዋን፣ በፋሽስታዊ ነቀርሳ
ታርሳ፣ ተምሳ፣ በስብሳ
ሂትለራዊ እባጭ ጫንቃዋን፣ እንደኮረብታ ተጭኗት
ቀና ብላ እውነት እንዳታይ፣ አንገቷን ቁልቁል ጠምዝዟት
ነፍሷን ድጦ ያስበረከካት
ሥልጡን፣ ብኩን፣ መፃጉዕ ናት፤ ….
እና ፈርቼ እንዳልባክን፣ ሲርቀኝ የኃይልሽ ውጋገን
አንቺ ካጠገቤ አትራቂ፣ በርታ በይኝ እመ ብርሃን
ቃል ኪዳኔን እንዳልረሳት፣ እንዳልዘነጋት ኢትዮጵያን፡፡
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እሸሸግበት ጥግ አጣሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ
እማማ ኢትዮጵያን መንፈሴ፣ ተፈትቶ እንዳይከዳት ሠጋሁ …
አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከእናቴ ማኅፀን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
ከወዟ ወዜን ቀፍፌ
በሕፃ እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ፤
በጋው የእረኛ አደባባይ፣ ክረምት እንደወንዙ ፍሳሽ
በገጠር የደመና ዳስ፣ በገደል ሸለቆ አዳራሽ
ከቆቅ እና ከሚዳቋ፣ ከዥግራ ጠረን ስተሸሽ
በወንዝ አፋፍ ሐረግ ዝላይ፣ መወርወር መንጠልጠል ጢሎሽ
ከፍልፈል ጋር ሩጫ ስገጥም፣ ከቀበሮ ድብብቆሽ
ከናዳ ጫፍ ሣር አጨዳ፣ ለግት ላሜ ትንሽ ግጦሽ
ለጥጃዬ የሌት ግርዶሽ 
ለጥማድ በሬዎች ራት፣ ለማታቸው ትንሽ ድርቆሽ
ለግልገሌ ካውሬ ከለል
እማሳው ሥር ጎጆ መትከል
ለፀሐይ የሾላ ጠለል፣ ለዝናብ የገሳ ጠለል
ውሎ የንብ ቀፎ ማሰስ፣ ያበባ እምቡጥ ሲፈነዳ
የግጦሽ ሣር ሲለመልም፣ ሲሰማሩ ሰደድ ሜዳ
አዝመራው ጣል ከንበል ሲል፣ ከብቱ ለሆራ ሲነዳ
ፈረስ ግልቢያ ስሸመጥጥ፣ ከወፎች ዜማ ስቀዳ
ልቤ በንፋስ ተንሳፎ፣ በዋሽንት ዋይታ ሲከዳ …..
ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?

ያቺን የልጅነት የምሥራች? የሕፃንነት ብሥራት
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን፣ የምኞት የተስፋ ብፅአት
ያቺን የልጅነት እናት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፣ ጥርሶችሽን ትነክሺባት?
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ባገልግሎትሽ ስዋትት
ከዜማ ቤት እቅኔ ቤት፣ ከድጓ ቤት እመጻሕፍት
ካንቺ ተቆራኝታ ዕድሌ፣ ካንቺ ተቆራኝታ ነፍሴ
ከቀፈፋ ደጀሰላም፣ ከቤተልሔም ቅዳሴ
እኰ፣ ቀፎ ዳባ ለብሶ
ቅኔ ዘርፎ ግስ ገሦ
መቅደስ አጥኖ ማኅሌት ቆሞ
በልብስ ተክህኖ አጊጦ፣ በብር አክሊል ተሸልሞ
እመ ብርሃን ያንች ጽላት፣ ነፍስ ላይ በእሳት ታትሞ
የመናኒው ያባ ተድላ፣ ረድ ሆኜ፣ አብሮኝ ታድሞ
ሕይወቴ እምነትሽን ጸንሶ
ሥጋ ፈቃዴ ተድሶ
ለሕንፃሽ መዲና ቆሞ፣ ለክብርሽ ድባብ ምሰሶ
ሥሜን በሥምሽ ሰይሜ፣ ሆነሺኝ የእምነቴ ፋኖስ
ለዋዜማሽ ግሸን ማርያም፣ ለክብርሽ ደብረ ሊባኖስ
ስሮጥ፣ በወንበሩ አኖርሺኝ፣ በአንበሳው በቅዱስ ማርቆስ
ታዲያ ዛሬ ኢትዮጵያ ስትወድቅ፣ ከምትሰጪኝ የፍርሃት ጦስ
ምነው በረኝነት እድሜ፣ ዓይኔን በጓጎጣት የሎስ
የጋኔል ጥንብ አንሳ ከንፎ፣ ወርዶ በጨለማ በርኖስ
ባክሽ እመ ብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ
ጽናት ስጪኝ እንድካፈል፣ የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣
ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ፣ ከነደደችበት እቶን
የሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን፡፡ …..
አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ
እምፀናበት ልብ አጣሁ፡

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com 

No comments: