መንደርደርያ - ኢትዮጵያ በታሪካዊው ምርጫ ዋዜማ
ወቅቱ ኢትዮጵያ አዲሱን ምዕተ ዓመት ልትቀበል ሽር ጉድ እያለች የነበረበት
ወቅት ነበር።በኢትዮጵያ በ1997 ዓም የተደረገው ምርጫ ውጤት በሕወሓት/ኢህአዴግ (የዚያን ጊዜው
ኢህአዴግ) የኢትዮጵያ ሕዝብ በአደባባይ በግልፅ ከተካደ በኃላ የኢትዮጵያውያን ምሁራን ስደት
በአዲስ መልክ የተንቀሳቀሰበት ጊዜም ነበር።ከእዛን ጊዜ በፊት ለትምህርት ወደውጭ የሚሄዱ ወጣቶች ሁሉም ባይሆኑም የሀገሪቱ መንፈስ
የምርጫ ንፋስ እየሸተተው እና ትውልዱም ከአሁን በኃላ በኢትዮጵያ ምድር ስልጣን በደም መፋሰስ ሳይሆን በሰላማዊ ምርጫ ሊሆን
ነው የሚል ከፍ ያለ ሕልም ሁሉም ሰንቆ የነበረበትም ወቅት ሆኖ አልፏል።በተለይ በምርጫው ክርክር ወቅት ሁለት ነገሮች ገሃድ ሆኑ።አንድኛው ኢትዮጵያ ከሕወሓት/
ኢህአዴግ ውጭ እጅግ አቅም ያላቸው እና ሀገሪቱን በአጭር ጊዜ ወደተሻለ ደረጃ የማድረስ ርዕዩም ሆነ ልምዱ ያላቸው ምሁራን እንዳሉ
በግልጥ ታየ። ሁለተኛው ሀገሪቱን የመራ ያለው ስርዓት ቀድሞ ሕዝብ ከሚያውቀው እና ከምገምተው በላይ ከአቅም በታች በሆኑ እንደ
ወቅቱ አጠራር (ከአፍንጫ እንሰ ከንፈር ብቻ የሚያስቡ) ሰዎች የሞሉበት እንደሆነ ታወቀ።ብዙ ሰው አቶ በረከትን፣አቶ ስዩም
መስፍንን እና ሌሎች የሕወሓት ባለስልጣኖች ቀድሞ ከሚያውቃቸው በታች እጅግ ዝቅ ያለ አቅም እንዳላቸው
አወቀ። ማወቅ ዕዳ ነው እንደሚባለው ይህንን ማወቁ ቀድሞ ከነበረው የለውጥ ስሜት የበለጠ በናረ መልኩ ምርጫው ሃገርን የማዳን ሥራ
አካል መሆኑን ሕዝብ አመነበት።ሃገርን የማዳን ሥራ የሚለው አስተሳሰብ በሕዝብ ዘንድ መስረፅ የጀመረው በቅርብ የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ታሪክ ውስጥ በሁሉም ሕዝብ ዘንድ የተናኘው በእዚሁ በከሸፈው ምርጫ ወቅት ነበር። ይህ ትክክል አስተሳሰብ ነው።የተሳፈርክበት መኪና
ሹፌር
ከአቅም በታች መሆኑን ስትረዳ መክናውንም አንተንም ሲቀጥል እራሱ ሹፈሩንም ለማዳን መነሳት ተገቢ ነው።የኢትዮጵያ ህዝብም ያደረገው
ይህንኑ ነው።የበለጠ ሲያውቅ የበለጠ ሃገሩን ለማዳን በሰላማዊ መንገድ ቆረጠ።
ከ1997 ዓም ምርጫ ክሽፈት በኃላ የኢትዮጵያውያን ስደት
አመታት በነጎዱ ቁጥር የኅብረተሰብ አስተሳሰብ፣አኗኗር እና የትግል መንገድ ሁሉ ይቀየራል።ከ1997 ዓም
ወዲህ ኢትዮጵያ በበርካታ አሰቃቂ የፖለቲካ ምች ተመታለች። ከአዲሱ ሚሊንየም ማለትም ከ2000 አመተ ምህረት ወዲህ ብቻ የዓለም ምሁራንን ፍልሰት ስታትስቲክስ ጠቅሶ የሱዳን ትሪቡን ጋዜጣ እንደዘገበው በምሁራን ፍልሰት በአፍሪካ ቀዳሚ ኢትዮጵያ
መሆኗን እና በዓለም አቀፍ ደረጃም ቀላል ቦታ እንደሌላት መዘገቡን የእዚህ ፅሁፍ ፀሐፊ
ያስታውሳል።ባጭሩ በአሜሪካ፣አውሮፓ እንዲሁም አፍሪካ ሳይቀር ለትምህርት የተላኩ ወጣቶች ሙሉ
በሙሉ በሚባል ደረጃ ሳይመለሱ የቀሩት በተለየ መልኩ ከ1997ዓም ወዲህ ነው። ይህ ሁኔታ በደርግ የስልጣን ዘመን የነበረ ቢሆንም ደርግ በወደቀባቸው የመጀመርያ ዓመታት የመሻሻል
አዝማምያ ታይቶ ነበር።
በንጉሡ ዘመን የምሁራን ስደት ችግር ተብሎ የማይታሰብ እንደነበር እና ለትምህርት የሄዱ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች
ይልቁንም የምረቃ ጊዜ ሳይደርስ ወደ ሀገር ቤት እየመጡ የዲግሪ ሰርተፍኬታቸው ይላክላቸው እንደነበር ወቅቱን የሚያስታውሱ
የሚናገሩት ጉዳይ ነው። በእንግሊዝኛ የሚታተመው "ኢትዮጵያን ሄራልድ" እኤአ 2015 ህዳር 10 ቀን
" The Menace of Brain Drain On Ethiopia's Development" በሚል ርዕስ
ሥር ባውጣው ዘገባ ላይ እንዲህ የሚል ፅሁፍ ይገኛል።
" Prior to 1974 revolution virtually all
Ethiopians who attended university in the country remained at home and the vast
majority of those who studied overseas returned to Ethiopia. According to one
study, only one Ethiopian physician was working outside the country as recently
as 1972. The brain drain has not always been a problem in Ethiopia."
" ከ1966 አብዮት በፊት በውጭ ሀገር ዩንቨርስቲዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን
ውስጥ ብዙዎቹ ወደ ሀገራቸው ይመለሱ ነበር።አንድ ጥናት እንደሚያሳየው በ1964 ዓም ከኢትዮጵያ ውጭ ቀርቶ ለሌላ ሀገር ይሰራ የነበረ
ኢትዮጵያዊ አንድ ሀኪም ብቻ ነበር።የምሁራን ፍልሰት በእራሱ ለኢትዮጵያ ችግር ተብሎ የሚወራ አልነበረም"
የኢትዮጵያውያን ስደት በሕወሓት ዘመን እጅግ የከፋ እና ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ዘመን ደርሶባቸው
የማያውቅ መከራ ነው።ድንበር የለሽ ሀኪሞች ድርጅት (MSF) የኢትዮጵያውያን ስደት ጦርነት
ወደሚደረግባት የመን ጭምር መሆኑ ምን ያህል አሰቃቂ ጉዳይ በሀገራቸው እንደገጠማቸው የሚያመላክት መሆኑን በገለጠበት እኤአ
2008 ዓም ላይ ያቀረበው አመታዊ ሪፖርት ላይ በአንድ ወቅት ከደረሱት ስደተኞች ላይ በተወሰደ መረጃ ከስደተኞቹ
ውስጥ 30% ሴቶች ሲሆኑ የቀሩት 70% ወንዶችን ጨምሮ ከሁለቱም ፆታዎች
ውስጥ 54% የሚሆኑት በትዳር ይኖሮ የነበሩ እና ትዳራቸውን ትተው የተሰደዱ መሆናቸውን ይገልጣል። ይህ በገሃዱ አለምም የምናውቀው
እውነታ ነው።በአረብ ሃገራት ተሰደው ከሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን እናቶች በትዳር ላይ እንደነበሩ እና ልጆቻቸውን እና ባለቤቶቻቸውን
ትተው የተሰደዱበት ጉዳይ የከፋ የምጣኔ ሀብት መገለል ይህም የፖለቲካ ተፅኖ ውጤት እንደሆነ የታወቀ ነው።ባጭሩ ግን ስደት የሀገር
መፍረስ ዳርዳርታ ነው።እዚህ ላይ ሀገር ማዳን የሚለው ፅንሰ ሃሳብ ምን ያህል ዋጋ
የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን መረዳት አያስቸግርም።ጥያቄው ማን ነው ሃገርን የማዳን ኃላፊነት መውሰድ የሚገባው? የሚለው ነው።
የኢትዮጵያ አደገች ፕሮፓጋንዳ እና የስልጣን መጠበቅያ
መሣርያነቱ
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከአዲሱ ሚሊንየም (2000ዓም) ወዲህ በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ ብዙ ጉዳዮች እየተቀያየሩበት
መጥተዋል።በሀገር ውስጥ በምርጫ ማጭበርበር እፍረት ያልተሰማው ሕወሓት አቶ መለስን ከፊት አስቀድሞ ኢትዮጵያ እያደገች ነው የሚል
አዲስ ትርክት ይዞ ብቅ አለ።አቶ መለስ ልማታዊ መንግስት መርሆዎች የሚል ፅሁፍ ሲበትኑ አጫፋሪ ካድሬዎች በሚገባ እንዲያዳንቁ ከተላለፈ
ሚስጥራዊ ትእዛዝ ጋር ነበር።የአቶ መለስ ዜናዊ ልማታዊ መንግስት አገላለፅ ግን ውስጠ ወይራ መሆኗን ይልቁንም የአንድ ጎሳ የበላይነትን
ለማውጣት ውስጣዊ አጀንዳ የያዘ ነው የሚሉ ብዙዎች ናቸው።ከላይ በሚታየው ገፅታው ግን የአቶ መለስ ዜናዊ ፅሁፍ የመንግስትን ሚና
ሲገልፅ
" Role of the government should be limited to the
protection of individual and property rights, enforcement of contracts, and
safeguarding competition among economic actors"
" የመንግስት ሚና መሆን የሚገባው የግለሰብ መብትን እና የንብረት መብትን ማስከበር
እንዲሁም በምጣኔ ሃብቱ ውስጥ ለሚኖሩ የእርስ በርስ ውድድሮች ዋስትና መስጠት ነው" ይላል።ይህ አባባል ግን ከእውነታው
እና በገሃዱ ዓለም አቶ መለስ እና አስተዳደራቸው ሲያደርግ ከነበረው ጋር ፈፅሞ የተቃረነ ነበር።በሕወሓት ዘመን መንግስት ለግለሰቦች
ነፃነት እና ንብረት ዋስትና ሲሰጥም ሆነ ለጤናማ ውድድሮች ዋስትና የሰጠው መቼ ነው? ሌላው ቀርቶ በከተማ ቦታ ይዞታ
ላይም ሆነ በገጠር መሬት ላይ ኢትዮጵያውያን ካለምንም ዋስትና ከቦታቸው የተነቀሉት በሕወሓት ዘመን ነው።የአቶ መለስ ፅሁፍ በሀገር
ውስጥም ሆነ በውጭ ባሉ ምሁራን ይህንን ያህል የከበደ ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ከልማት ጥናቶች የተገለበጠ መሆኑ ስለታወቀ ትኩረትን
ከካድሬዎች ባለፈ አልሳበም። አቶ መለስ ግን በዙርያቸው ያሉትን የእራሳቸውን ተቀናቃኞች ለማጥቃት አዲስ ሃሳብ ይዘው የመጡ መስለው
ታይተውበታል።
ከእዚሁ ጋር ተያይዞ ሕወሓት እንደ ጊዜያዊ የአመፅ ማስታገሻ ክኒን የተጠቀመበት ኢትዮጵያ በሁለት ዲጅት
እያደገች ነው የሚለውን አባባል ነው።ለእዚህም ከሙሰኛ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኃላፊዎች ጋር በመሞዳሞድ ኢትዮጵያ አደገች የሚል
ሪፖርት መዥጎድጎድ ጀመረ።ሆኖም ግን የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ባለሙያዎችም ሆኑ አቶ መለስ እና ስርዓታቸው አንዲት ሀገር በጠቅላላ
ምርት ድምር በማስላት አደገች የሚለው መርህ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) ሳይቀር ከተተወ እና ሀገሮች ማደጋቸው
የሚለካው በተለያዩ መስፈርቶች ማለትም እያንዳንዱ ግለሰብ ካለው የትምህርት፣የጤና፣የገበያ፣የዲሞክራሲ እና ነፃነት ዕድል አንፃር
መሆኑን ያውቃሉ።ሆኖም ግን በዓለም አቀፍ መድረክም እድገትን አስር የማይሞሉ የስርዓቱ ሰዎች በጠቀራመጡት ሀብት አንፃር
ሪፖርት እያቀረቡ ህዝቡ አደገ እያሉ ሲናገሩ ምንም አይነት እፍረት አላሳዩም። በእዚህ በቁጥር ማምታታት የአፍሪካ ሀገሮች
"ከእጅ አይሻል ዶማ" እንዲሉ በእየቤታቸው እሳት ስላለ የኢትዮጵያ እድገት እያሉ መለፈፋቸው አልቀረም። እዚህ ላይ
ኢትዮጵያ እድገት ፈፅሞ የላትም በ1983 ዓም በነበረችበት ቦታ ነች እያልኩ አይደለም።የከተሞች ማደግ፣የግንባታ መስፋፋት እና የመንገዶች
መገንባት አዎንታዊ ነገር ግን በብዙ ብድር እንደተሰሩ ይታወቃል።ጥያቄው ግን ይህ ልማት ነው ወይንስ የቁጥር እድገት ነው? የሚለው
ነው። ልማት እያንዳንዱ ሰው ሕይወትን የማሻሻል ኃይል አለው።የእድገት ቁጥር ግን የጥቂቶች ሀብታምነትን እና የብዙሃኑን የምጣኔ
ሀብት ባርያ መሆንን ያሳያል።
ኪኒን ጨምርልኝ
የሕወሓት የራስ ምታት ክኒን ማለትም አድገናል የሚለው ፕሮፓጋንዳ ለጥቂት ጊዜ ጎማውን ለማሽከርከር ጠቀመው
እንጂ ብዙም አላራመደውም ይልቁንም 11% የምትለዋ ትርክት በእየሻይ ቤቱ መቀለጃ ሆነች።ከ1997 ዓም የምርጫ ክህደት
በኃላ ሕወሓት ሕዝቡንም ሆነ ሚድያውን በሥራ የወጠረባቸው ጉዳዮች የመጀመርያው የሚሊንየም አከባበር ግርግር በመቀጠል የልማታዊ መንግስት
ሃሳቦች ፕሮፓጋንዳ እና ኢትዮጵያ በሁለት ዲጅት አደገች የሚሉት ሁሉም ብዙ እርቀት አላስኬድ አሉ። የእዚህን ጊዜ አዲስ ሕዝብ የሚወጥር
ጉዳይ ይዞ መምጣት ተፈለገ።የአባይ ግድብ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ካርድ ተመዘዘ። ይህ የግድብ ሥራ ለኢትዮጵያ ያለው ጥቅም ምንም
የለም ከሚል እሳቤ መነሳት አይቻልም።ጉዳዩ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ዘመን ጀምሮ ብዙ ተብሎበታል።በንጉሱም ዘመን የተያዙ እቅዶች
እንደነበሩ እና የግብፅ ደህንነቶች በብርቱ ጉዳዩን ሲከታተሉ እንደነበር ይታወቃል። ስለሆነም ግድቡን በጭፍን ማጥላላት በጎ ሃሳብ
አይደለም።እስካሁንም በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚኖር ኢትዮጵያዊ የእዚህ አይነት ሃሳብ ሲያንፀባርቅ አልታየም።የስርዓቱ ደጋፊዎች
ግን ለፕሮፓጋንዳ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ያላለውን ሲናገሩ ግን ተሰምተዋል። የኢትዮጵያ ቴሌቭዥንም
አስተጋብቶላቸዋል። የአባይ ግድብ ጉዳይ በሕወሓት በኩል ሲቀርብ ግን ታስቦበት እና ታልሞ ሳይሆን የመቆያ ክኒን ጨምርልኝ መልክ
ነው።ሕዝብ የሚወጥር፣በተስፋ የሚያስፈነድቅ እና ሕወሓትን ጀግና የሚያስብል ሃሳብ ተደርጎ ተወሰደ።ለእዚህም ማስረጃው እቅዱ በአምስት
ዓመቱ የልማት እቅድ ላይ የሌለ እና የበጀት ምንጩም የድሀውን ኢትዮጵያዊ ጎጆ የበለጠ የሚያሟጥጥ መሆኑ ነበር።በሌላ በኩል ሕወሓት
የመጀመርያ የአባይ ቦንድ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ዋሽንግተን ላይ ሲያዘጋጅ ጀምሮ ኢትዮጵያውያንን አርቲስት እና አክቲቪስት ታማኝ በየነን
ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን በስብሰባው ለመሳተፍ ሲሄዱ ከበር ላይ እየመረጠ አስቀራቸው።በእዚህም የአባይ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን
ሁሉ ጉዳይ ሳይሆን የፖለቲካ መሳርያ መሆኑን በይፋ አወጀ።
በአባይ ግድብ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም ሆኑ የውጭ ባለሙያዎች የሚሰጡት ሁለት መሰረታዊ ሃሳቦች
አሉ። በቅድምያ ግን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውሃ ማመንጨት አቅም እንዳላት እና ይህንን መጠቀም እንዳለባት የሁሉም ስምምነት ነው።ምሁራኑ
ግን የሚያነሱት ሁለት ነጥብ።አንደኛ ኢትዮጵያ በእርሻ ምርት እራሷን ሳትችል ይህንን ያህል ግዙፍ የሀገር ሀብት የሚበላ ፕሮጀክት
ላይ ሙሉ ኃይሏን ማሳረፍ ሃገሩን ሊያፈርስ የሚችል አደገኛ ውሳኔ ነው የሚል ነው።ለእዚህም ማስረጃው ፕሮጀክቱ የመንግስትን ለልዩ
ልዩ ወጪ መዋል የሚገባው ሀብት ከመውሰዱ በላይ እያንዳንዱ ምስኪን ኢትዮጵያዊም ከጉሮሮው እየነጠቀ እንዲያዋጣ ማድረጉ በእራሱ ድህነትን
ማስፋፋት ነው የሚል ሲሆን። ሁለተኛው ደግሞ በአሁኑ ዘመን ግዙፍ ግድብ መገንባት በጥቂት አመታት ውስጥ ግድቡ በደለል ሲሞላ ግድቡን
ለማፅዳት የሚጠይቀው ወጪ በእራሱ የግድቡን መስርያ ለማከል ይቃጣዋል የሚል ነው።ለእዚህም አማራጭ የሚያቀርቡት በአውሮፓም ሆነ ሌሎች
ሃገራት እንደሚደረገው በርካታ አነስተኛ ግድቦችን ማብዛት እና ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይቻላል።ይህም ከፀጥታ ጥበቃም ሆነ የመስኖ ስራን
ከማስፋፋት አንፃር ብዙ ጥቅም አለው የሚለው ይጠቀሳል።
ከእዚህ በተለየ ግን የሕወሓት መንግስት በግድቡ ግንባታ ላይም ካለጨረታ የሰጠው የጣልያኑ ኩባንያ እና የሕወሓት
የንግድ ድርጅቶች በስራው ላይ ካለምንም ተቀናቃኝ መግባት የግንባታውን አላማ ከላይ ከተጠቀሱት ችግሮች በላይ አላማ እንዳለው የሚናገሩ
ብዙዎች ናቸው።ይህም ሆኖ ግን አሁን አሁን ስለ ግድቡ ጉዳይ መሰረት የተጣለበትን ዓመት ከማክበር ባለፈ ወሬው እየራቀ መምጣቱ የብዙ
ኢትዮጵያውያን የሹክሹክታ ወሬ ሆኗል።
ከሶስተኛው ክኒን በኃላ የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ህወሓት ለማስታገሻነት የተጠቀመበት ነገር ግን ምንም
ፍሬ ያልያዘለት የጥልቅ ተሃድሶ ጉዳይ ነበር።አቶ ኃይለማርያም ትልቅ ተሃድሶ፣ሙስና እያሉ ጫፍ መናገር ስጀምሩ በደረሰባቸው ከባድ
የአንድ ወገን ምት አሁን ሙስና የምትል ቃል ከንግግራቸው አውጥተው እና ለገሃር ላይ የሚገኘው የፀረ ሙስና ኮሚሽን
መስርያ ቤት ሲፈርስ እና በአርብቶ አደር መስርያ ቤት ሲገባ የመክሰስ መብቱም በፖሊስ ኮሚሽን ስር ሲወድቅ እያዩ ድምፃቸውን አጥፍተዋል።
የኪኒን ጋጋታ ያላስቆመው ሕዝብ ሆ! ብሎ ተነሳ
ሕወሓት በእየዘመኑ ያወጣቻቸው የማስታገሻ ኪኖች አለምስራታቸው ብቻ ሳይሆን ህዝብን ዘላለም ማታለል አይቻልም
እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከእየአቅጣቸው በስርዓቱ ላይ ተነሳ።በባዮሎጂ ትምህርት አንድ ባክተርያ ለማጥፋት በተደጋጋሚ የምትሰጠው
መድሃኒት ከእረጅም ጊዜ በኃላ ባክቴርያም ሊለምደው እና የመገዳደር አቅሙን ሊያጎለብትበት እንደሚችል ይገለጣል። የኢትዮጵያ
መሰረታዊ ችግር ማለትም የነፃነት፣የዲሞክራሲ፣የፍትህ እና የእኩል ተጠቃሚነት ችግሮች ሳይፈቱ ሕወሓት እራሷን እና ደጋፊዎቿን
ለመደለል ያቀረበችው ክኒን ሁሉ አልሰራ አለ። ሕዝብ በቃኝ ብሎ ተነሳ።በኦሮምያ፣በዐማራ፣ጋምቤላ፣አፋር፣ቤንሻንጉል ወዘተ አመፆች
ተቀጣጠሉ።
በመጀመርያ ደረጃ ሕወሓት አመፆቹን የአካባቢው የአስተዳደር ችግሮች እንጂ የብሔራዊ ጉዳይ አይደሉም በሚል
ዝቅ ለማድረግ ብዙ ጥረት አደረገ።እውነታው ግን ይህ አልነበረም።አመፆቹ እያየሉ በአስር ሺዎች
ወደ እስር ቤት እየተጋዙ ብዙ ሺዎች እንደወጡ የቀሩበት ሕወሓት ላለፉት 26 ዓመታት ገጥሞት የማያውቀው የህዝብ የቆረጡ ድምፆች
ነበሩ። በመጨረሻ ግን አመፁ እንደማይቻል ሲታወቅ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በያዝነው 2009 ዓም መጀመርያ
ላይ ታወጀ።ሕወሓት አዲስ የሞት ድግስ የያዘ ክኒን ይዛ ብቅ አለች።የኮማንድ ፖስት የሚባል ክኒን። የኮማንድ ፖስት
የተሰኘው ክኒን ግን እራሷን ህወሓትን ይዞ ወደ ሞት የሚያወርድ መሆኑን በደንብ አላወቀችውም ማለት አይቻልም።አማራጭ ስታጣ የተገኘውን
ሁሉ መድሃኒት ነው ብሎ መውሰድ ተስፋ የቆረጠ ሰው ተግባር ነው።ሕወሓትም ተስፋ ቆረጠች።አዋጅ አወጀች።አዋጁ ስድስት ወር ላይ ያበቃል
ተብሎ ህወሀትን ሊያሽላት ስላልቻለ አላዋቂ ሀኪሞች የሕውሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ተሰበሰቡ እና እንደገና አራዘሙት።
የቅርቡ የኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ፖለቲካ ለውጦች
የሕወሓት የሞት ድግስ የያዘው አዋጅ በእዚህ ዓመት ከመታወጁ ቀድም ባሉት ወራትም ሆነ ወዲህ በኢትዮጵያ
የፖለቲካ መድረክ ላይ አዳዲስ የሚባሉ የቅርፅ እና የይዘት ለውጦች መታየት ጀምረዋል። በሀገር ውስጥ የሕወሓት ተጣማሪ እንደሆኑ
የሚናገሩት ብአዴን እና ኦህዴድ ተፈረካክሰው የቀራቸው አንዳንድ ምልክቶች ናቸው።ሕወሓት ግን አሁንም እንደሚመቹ አድርጎ እንደገና
ለመጠገን ሙከራ እያደረገ ነው።ያለፉት አይነት አሻንጉሊት አድርጎ ለመቅረፅ ግን ፈፅሞ የማይቻል ሆኗል።ምክንያቱም አመፆቹ የተነሱት
ከታች ካለው ሕዝብ እስከ ማዕከላዊ አመራር ደረጃ ባሉት ሁሉ ስለሆነ ይህንን ሁሉ መጠገን በእራሱ ሕልም ሆኖ ቀርቷል። እዚህም ላይ
ሕወሓት አንዳንድ መጠቀም የፈለጋቸው አዳዲስ እና አስቂኝ ኪንኖች ብልጭ ብለዋል። ለምሳሌ የኦሮምያ የኢኮኖሚ አብዮት እና
የዳሸን ቢራ ጉዳይ ይጠቀሳሉ።የኦሮምያ የኢኮኖሚ አብዮት ምንም አይነት የፖለቲካ ስልጣን የሌለውን ኦህዴድ በተስፋ ዳቦ መሬቱ እና
በመሬቱ ላይ ያሉ መዋለ ንዋይ ሁሉ ያንተ ነው የሚል ቃላት እየተጠቀሙ የነበረውን ጥቂት ስራዎች ማወክ ከተያዘ ሰነባብቷል።በእዚህም
ክልሉን የበለጠ ወደ ኃላ የመውሰድ እና በመጨረሻ ሕወሓት ሲረጋጋ ከአዲስ እቅድ ጋር ለመዋጥ መሆኑን የማይረዳ ሰው የፖለቲካ ሀሁ
ገና ያልተገለጠለት ሰው ብቻ መሆን አለበት።
ሌላው በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ የታዩት አዳዲስ ክስተቶች ውስጥ በተለይ በውጭ ሃገራት መሰረታቸውን
ያደረጉቱ ውስጥ የዐማራ የዘውግ ድርጅቶች መሰባሰብ እና የአርበኞች ግንቦት 7 ጥምረት ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የሚሉት ዋነኞቹ ናቸው።የዐማራ
የዘውግ ድርጅቶች በመጀመርያ መነሻ አመታት ላይ በርካታ ጥያቄዎችን አስነስተው ነበር።በመጀመርያ ደረጃ የነበረው በሶሻል ሚድያ ላይ
ከመብዛታቸው የተነሳ የጥያቄዎቹ ቅርፅ ብዙ ክርክሮች አስነስተው ነበር።ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በዋሽንገተን ከተደረገው ዓለም
አቀፍ የአማራ ጉባኤ ወዲህ የድርጅቶቹ መሰባሰብ በተወሰነ መልኩ እየታየ ነው። በተለይ የዐማራ የዘውግ ፖለቲካ የፅንፈኛ
የዘውግ ፖለቲካን የማስፋፋት ዕድል ይፈጥራል ለሚሉ ሃሳቦች በእዚሁ በዋሽንግተኑ ጉባኤ ላይ ወረቀት ካቀረቡት ውስጥ የዳግማዊ መዐሕድ
የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስጋናው አንዱ ዓለም የዐማራው መደራጀት የፅንፈኛ ፖለቲካን የሚያከሽፍ መሆኑን ሲገልጡ :
-
" የአማራው የአማራነት ጥያቄዎች ግን ይሄንን እንደልብ ሲፈነጭ የቆየ የአክራሪ ብሄረተኞች
አደጋ ሚዛን በመስጠት ያረግበው ነበር። አማራው ራሱን ችሎ እንደ አንድ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ሀይል ብቅ ማለት የእነዚህ አክራሪ
ብሄረተኞች ህልውና መክሰም መንስኤ ነው። ለዛ ነው ብንዘገይም እንኳ አሁንም በቶሎ አማራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ይሄንን ሁሉ ለአርባ
አመት የተዛባ ሚዛን ማስተካከል ታሪካዊ ግዴታችን የሆነበት ጊዜ ላይ ነን የምንለው" ብለዋል።
በእርግጥ ይህ አባባል በእራሱ በርካታ የተቃርኖም ሆነ የሚደግፍ ሃሳቦች ሊንሸራሸሩበት ይችላሉ።ጉዳዩ ፖለቲካም
ነው እና አንዳንድ ሁኔታዎች የሚያመጡት በጎም ሆነ በጎ ያልሆነ ተፅኖ ለመፈተሽ የጊዜ እና የአካባቢያዊ ለውጦችን በሚገባ መፈተሽ
ይጠይቃል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ አንድነት ጎራ ቀዳሚ ሚና የያዘው የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የእራሱ የሆነ ስልታዊ
መንገዶች እየሄደ መሆኑን መመልከት ይቻላል።ድርጅቱ በመጀመርያ ከነበረበት ወደ ኤርትራ ለምን? የሚሉ ጥያቄዎች አልፎ አሁን
ውጤቶችን የመለካት ደረጃ ላይ ደርሷል።በማኅበራዊ ሚድያ ላይ በጭፍን የሁሉንም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች በመተቸት የማጥላላት
ዘመቻ ላይ የተጠመዱቱን ትተን ለሀገር በመቆርቆር የአርበኞች ግንቦት 7 ከሚነሳበት ወቀሳ አንዱ ጥምረት በዛ የሚል ነው።
"ድርጅቶች በዙ እና ጥምረት በዛ" የቀድሞ እና የዘንድሮ ወጎች
በቀደሙት አመታት ይሰሙ የነበሩ ድርጅቶች በዙ የሚሉ ድምፆች በአሁኑ ጊዜ ጥምረት በዛ የሚሉ ሆነው ማግኘት
በራሱ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከማናቸውም አይነት ትችት እንደማይድን አንዱ ምስክር ነው።በተለይ የአንድነት ድርጅቶች ከብሄር ድርጅቶች
ጋር መቀናጀት ለመፍጠራቸው መሰረቱ ምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ በእራሱ የወቅቱ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ እና ጎልቶ እየወጣ
ያለ ጥያቄ ነው።እዚህ ላይ ግን ድርጅቶች በዙ በተባለባት ሀገር ውስጥ ጥምረት መብዛቱ በእራሱ ችግር ሊሆን ይችላል ወይ? ብሎ መጠየቅ
ተገቢ ነው።ስለሆነም ጥምረት መፈጠሩ በእራሱ በአደጋነት ሊፈረጅ አይገባም ማለት ነው። ከእዚህ ይልቅ የሚፈጠሩ ጥምረቶች ያላቸው
በጎ እና በጎ ያልሆኑ ጎኖች ምንድናቸው? ብሎ መፈተሹ ተገቢ ነው።የኢትዮጵያ ሀገር አድን የጋራ ንቅናቄ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ እና
መጪ የፖለቲካ ጉዳይ አንፃር መፈተሹ አስፈላጊ የሚሆነውም እዚህ ላይ ነው።
ፖለቲካ ከግለሰቦች ስብዕና በላይ የዘለለ ተልዕኮ አለው
በአርበኞች ግንቦት 7 እና የብሔር ድርጅቶች መካከል የተደረጉት የጥምረት መግለጫ ለመጀመርያ ጊዜ
የተሰማው በ ጳጉሜ 3፣ 2007ዓም ምሽት ነበር።
በእዚህ ዜና ላይ በኤርትራ የሚንቀሳቀሱ አራት በትጥቅ ትግል የተሰማሩ ኃይሎች የጋራ ንቅናቄ
መመስረታቸው ተነግሮ ነበር።በእዚህም መሰረት
1ኛ/ የአፋር ድርጅቶች የጋራ ንቅናቄ፣
2ኛ/ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣
3ኛ/ የአማራ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ እና
4ኛ/ አርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ
በጋራ ለመስራት በመስማማት የኢትዮጵያ ሀገር አድን በዲሞክራሲ የጋራ ንቅናቄን መመስረታቸውን
አስታውቀዋል። በእርግጥ የትግራይ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት እና የአማራ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ በጥምረቱ ላይ ለመቀናጀት የሚቀሩ
ስራዎች እንዳሉ መጠቀሱ እና ሂደት ላይ ነው መባሉ ይታወሳል።
በቅርቡ በጥቅምት ወር 2009 ዓም ጥምረት የተፈጠረበት መድረክ ደግሞ በአቶ ሌንጮ
ለታ እና በምክትላቸው ዲማ ነገዎ የሚመራው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግምባር፣ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው አርበኞች ግንቦት
7፣ በዶ/ር ኮንቴ ሙሳ የሚመራው የአፋር ህዝብ ፓርቲና አቶ በቀለ ዋዩ የሚመራው የሲዳማ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ የተመሰረተው
ነው።ይህ ጥምረት በኢትዮጵያ የመልክዓ ምድር ሽፋን አንፃር የተሻለ መሠባጠር የታየበት ሲሆን የሚነሱበት ሁለት ጥያቄዎች ግን አሁንም
አሉ። እነርሱም ጥምረት የፈጠሩት ድርጅቶች በተለይ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር በአሁኑ ወቅት ያለው ተሰሚነት ምን ያህል ነው የሚል
እና የድርጅቱ መሪዎችም በ1984 ዓም አካባቢ በዐማራ ላይ በተነሱ ጭፍጨፋዎች እጃቸው አለ የሚሉ ናቸው።ሆኖም ግን ግለሰቦችን ከድርጅቶች
ነጥሎ ማየት እና ግለሰቦቹ አጠፉ የሚባለውን ጥፋት በውጭ ሃገራት የመክሰስ መብት ያለው ኢትዮጵያዊ የተባለው ማስረጃ አሰባስቦ ከመጠየቅ
ይልቅ በፖለቲካ መድረኩ ላይ መታየታቸው ብቻ ጥፋት እንደሆነ መገለፁ አስቸጋሪው ጉዳይ ነው።ከእዚህ በተለየ ደግሞ አሁንም ጥምረቱ
ለምን ዐማራዊ ድርጅቶችን አላቀፈም የሚለው ጥያቄ ነው።ሆኖም ግን ጥምረቱ ለእነኝህ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠቱ እንዳለ ሆኖ የድርጅቶች
ጥምረት በእራሱ ለኢትዮጵያ መጪ የፖለቲካ ሁኔታ በእራሱ እንደ አደጋ ሊታይ ፈፅሞ አይችልም። ምክንያቱም ፖለቲካ
ከግለሰቦች ስብዕና በላይ የሆነ ተልዕኮ ስላለው ነው።ግለሰቦች በግለሰቦች ይተካሉ። የፖለቲካ መስመሩ እና ዓላማው እንዲሁም ድርጅታዊ
አቅም ግን የሚገነባው በአባላቱ እና በመላው ሕዝብ ፈቃደኝነት ነው።
ኢትዮጵያዊ ውል በአስተማማኝ መልኩ መልሶ ሳይታሰር ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ማውራት እንዴት ይቻላል?
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን ፖለቲካ ማንም
በማኅበራዊ ሚድያ ውስጥ ገብቶ የሚተችበት አደገኛ ዕድል ፈጥሯል።አደገኛ ያልኩበት ምክንያት በሙያው በበሰሉ ሰዎች ሳይሆን
በግብታዊነት እና ሻይ እና ቡና ሲጠጡ በሰሙት ውይይት ላይ ብቻ ተመርኩዘው ያንንም እንደ ትልቅ የእውቀት ምንጭ እየቆጠሩ
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ድርጅቶች ሳይንሳዊ ባልሆነ መልክ የሚተቹ መብዛታቸው እና ሕዝብ ማሳሳታቸው እጅግ አደገኛ ክስተት ነው።
በማናቸውም ጥምረት ላይም ሆነ አደረጃጀት ላይ ማንኛውም አይነት ጥይቄዎች፣አስተያየቶች እና ስጋቶች ሊገለጡ ይችላሉ። ጥምረት
እና መተባበር ግን በእራሱ አደጋ ሊሆን ፈፅሞ አይችልም።
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ በርካታ
ተቺዎች የሚያነሱትን ያህል ለኢትዮጵያ አደጋ ነው ወይ? የአቅም፣የአፈፃፀም እና የታክቲክ ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ።እነኝህ በሂደት
እየጠሩ የሚሄዱ አበይት አስፈላጊ ጉዳዮች ናቸው።ጥምረት መፍጠር፣መወያየት፣በመጪው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሰለጠነ መልክ
መደራደር ግን ለነገ የማይባሉ ዛሬ መጀመር ያለባቸው ቁልፍ ተግባራት ናቸው።የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ከኦሮሞ፣አፋር እና
ሲዳማ ጋር ብቻ ሳይሆን በቅርቡ በጀርመን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በተገኙበት ከኦጋዴን ተቃዋሚ ኃይል ጋር የጋራ መግባብያ ሰነድ
ተፈርሟል።ውጤታቸው አመርቂ ይሁንም አይሁን እነኝህ ተግባራት ለነገዋ ኢትዮጵያ ወሳኝ ተግባራት ተደርገው መወሰድ
አለባቸው።
ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚደገሱ የባዕዳንም
ሆኑ የስልጣን ጥመኛው ስርዓት ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም የሚሆን እልቂት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያዘጋጁ የታመነ
ነው። ብልህ ፖለቲከኛ ደግሞ በዛሬ ላይ ብቻ ሳይሆን በነገ አደጋዎች ላይ ከአሁኑ እያነጣጠረ እና ችግሮችን የመፍታት
ሥራ እየጀመረ መሄድ ዋና ተግባሩ ነው።ሕወሓት ከስልጣን ቢወርድም የኦጋዴን ጉዳይ ሆነ የአፋር ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ ለመጪው የኢትዮጵያ
ፀጥታም ሆነ ልማት ቀላል የማይባል መንገጫገጮችን ማስከተሉ ሳይታለም የተፈታ ነው። ስለሆነም ዛሬ ላይ በጋራ ርዕይ ላይ
የተመሰረተ የኢትዮጵያዊነት ውል ላይ መነጋገር፣መተማመን እና ቢያንስ መስማማት ባይቻል ተቀራርቦ መነጋገር በእራሱ ለነገዋ
ኢትዮጵያ ላይ አንድ ብሩህ እርምጃ ነው። ኢትዮጵያዊ ውል በአስተማማኝ መልኩ መልሶ ሳይታሰር ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ
ማውራትስ እንዴት ይቻላል? ስለሆንም ሃገራዊ ንቅናቄውን በሚገባ መረዳት እና ዘግይተንም የምንመጣው ወደ እንደዚህ
አይነቱ ንቅናቄ በመሆኑ ከአሁኑ መስተካከል የሚገባውን እያገዙ ጅምሩን ማበረታታት ከአንድ ንቁ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ተግባር
ነው።ሃገራዊ ንቅናቄው በአሁኑም ሆነ በመጪው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የሚከተሉት አዎንታዊ ተፅኖዎች መፍጠር ይቻላል። እነርሱም
; -
1/ ትልቅ ሃገራዊ ግንባር የመፍጠር
አቅም ይኖረዋል፣
2/ በነገዋ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ በሂደት
በሚመጣ ለውጥ ከብሄር አስተሳሰብ ወደ ሃገራዊ አጀንዳ ላይ የተመሰረተ አደረጃጀት እንዲዳብር ይረዳል፣
3/ በነገዋ ኢትዮጵያ ላይ አዲስ የግጭት
አጀንዳ ለመፍጠር ለሚፈልጉ ባእዳን መንገዱን ይዘጋል፣
4/ በመጨረሻም የኢትዮጵያ ህገ
መንግስታዊ ስርዓትም ሆነ የሀብት እኩል ተጠቃሚነት የተረጋጋ ያደርጋል።
ባጠቃላይ ስለ ኢትዮጵያ ስንናገር
ስለመላዋ ኢትዮጵያ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለብን።መላዋ ኢትዮጵያ ደግሞ የተለያዩ አመለካከቶች፣የፖለቲካ ብስለቶች፣ ባህላዊ
አመጣጦች እና ምጣኔ ሃብታዊ መሰረቶች አሏት። ይህንን ሁሉ አስተባብሮ ወደ አንድ ሀገር ጉዳይ ለማምጣት በእራሱ ጥበብ፣ትዕግስት
እና ፅናት ይጠይቃሉ።
ብዙዎቻችን የዘመኔ ሰዎች በፅሁፎች
መካከል የአውሮፓውያን ምሁራን እና ታዋቂ ሰዎች የተናገሩት ንግግር የማድነቅ ሆኖም ግን የሀገራችን ሰዎች (ዓለም ያደነቃቸው)
አባባሎች ብዙም ትኩረት አለመስጠት አባዜ ተጠናውቶናል።በመሆኑም ለእዚህ ፅሁፌ መደምደምያ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ
ስላሴ ለሀገራቸው በሚሰሩት ሥራ ላይ ምን ያህል የአላዋቂዎች ወሬ ያውካቸው እንደነበር በገለፁበት አረፍተ ነገር ላይ
የተጠቀሰው አነጋገር የኢትዮጵያን ሃገራዊ አንድነት ለማቆም እና ኢትዮጵያዊ ውል በአስተማማኝ መልኩ መልሶ ለማሰር
መፅናት እንደሚገባ አመላካች ሆኖ ስላገኝሁት በእዚሁ ፅሁፌን ልደምድም። ንጉሡ በእራሳቸው እጅ በፃፉት "ሕይወቴ እና
የኢትዮጵያ እርምጃ" በሚለው መፅሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ ነበር ይሉት : -
" የተበላሸውን ለማቅናት፣ያልተጀመረውም ሥራ እንዲጀመር ለማድረግና አዲሱን ስልጣኔ ለማግባት
እሳቤና ይልቁንም አሮጌውን ልማድ ለሚወደው ሕዝብ አጋዥ ስለነበረው በሁለት ብረት መካከል እንዳለ እንጨት
አጣብቀውኝ የተቻለኝን እየሰራሁ ጊዜውን አሳለፍኩ።በመዝናናት ሰውነትን ደስ የሚያሰኝ ሥራ በመስራት የማሳልፈው ጊዜ ጥቂት
ነበር።ከተጀመረው ከሀገሩ ውስጥ ሥራ ያቃናሁትና አዲስ የሰራሁት፣ከውጭ ሀገርም የስልጣኔ ሥራ በሀገር ውስጥ እንዲገባ ያደረግሁት
በእየተራ ተፅፎ ይገኛል።በእዚህም ላይ የአዲሱ ስራችን መሰናክል የሚሆን በውስጥ ወይንም በውጭ ሰዎች የሚወራ አንዳንድ የውስጥ
እና የውጭ ችግር በእየጊዜው ይደርስብን ነበር እና ሽብር እንዳይሆን እና የሰው ደም እንዳይፈስ በጎሳ መለያየትን እንዳይስከትል
ስራውን ሁሉ በትግስት መስራት የሚያስፈልግ ሆነ"
ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ፣1965።
ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ፣1965።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com
ዋቢ ማጣቀሻዎች
===============
- Development state, Meles Zenawi, 2012
- Ethiopian Herald, Nov.102015
- MSF Report, 2008
- Zehabesha, 2016
- ሕይወቴ እና የኢትዮጵያ እርምጃ ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፣1965