ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, May 1, 2017

ወያኔ የዘራብንም ሆነ ቀደም ብለው የነበሩ የጋራ ቁስሎቻችን የሚሽሩት እኛው ተመካክረን በምንመሰርተው መንግስት እንጂ ወያኔ ለክቶ እና ሰፍቶ በሚወረውርልን ድርጎ አይደለም። የኦሮምያ ልዩ መብት በአዲስ አበባ የሚለውን አዲስ ረቂቅ አዋጅ ይመለከታል


========================
ጉዳያችን / Gudayacn
ሚያዝያ 23፣2009 ዓም (ሜይ 1፣2017)

ወያኔ የኢትዮያን ሕዝብ እርስ በርስ አባልቶ እድሜውን ለማራዘም ከእዚህ በፊት ያልጫረው መሬት ያልቧጠጠው ገደል የለም።አሁን ደግሞ  የኃይል ሚዛን ያገኘ መስሎት የኦሮምያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ የሚል አጀንዳ በማራገብ ህዝቡ እንዲገዛለት ለማድረግ እየሞከረ ነው።በሀገራችን ታሪክ ያወያኔን ያህል በሕዝብ ደም የተጫወተ እና ለመጪዋ ኢትዮጵያ ሳይቀር አረመኔያዊ ቢላዋ የሚስል መንግስት ኢትዮጵያ ገጥሟት አያውቅም።

አሁን ወሳኙ ሕዝብ ነው።ሕዝብ መምረጥ ያለበት የወያኔ እድሜ ማራዘምያ ክኒንን ሳይሆን ኢትዮጵያ በዘለቄታ ከወያኔ ከፋፋይ እና ዘረኛ ስርዓት የምትላቀቅበትን መንገድ ነው።የኦሮምያ ክልል ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ ላይ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ የሚለውን ካርድ ወያኔ አሁን የመዘዘው በስርዓቱ ላይ የሚደረገው አጠቃላይ ተቃውሞ ውስጥ አዲስ አበባ እንዳትሳተፍ ለማስፈራራት ነው።ይህንኑ አጀንዳ የሚያራግቡ በውጭ ሀገር እና በሀገር ውስጥም ያሉ የኦሮምያ አክትቪስቶች አሉ።እነርሱ ግን ምክንያታዊ ከሆነ የሰው ልጁ ታሪክ  እና የከተሞች እድገት ሂደት ጋር የተቃረኑ፣ ተማርን የሚሉት የባህር ማዶ ትምህርት የድንቁርና ምንጭ ሆኖባቸው ጭንቅላታቸውን ቀስፎ የያዛቸው፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የአኗኗር ዘይቤ፣ባህል፣እርስ በርስ ግንኙነት እና እምነት ሁሉ ደፍጥጠው ከወያኔ እኩል በተመረዘ ቂም በአጭር መንገድ ያውም በወያኔ ድርጎ አላማቸውን ያሳኩ የሚመስላቸው ናቸው።

በመጀመርያ ደረጃ አንድ የኦሮምኛ ተናጋሪ ጥቅሙ የሚከበረው ሃገራዊ፣የዜግነት፣የቡድን እና ግለሰባዊ መብቱ ሲከበርለት እንጂ ወያኔ በፈጠረው የኦሮምያ ክልል በሚል የተሰፋ ልብስ ውስጥ ነው ወይ? ይህ ጉዳይ ፈፅሞ ሊያምታታን አይገባም።ይህ ጥያቄ በእራሱ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነው የሚለው አባባል የተሳሳተ ነው።ኦሮሞ ማለት የተለየ ፍጡር ሳይሆን ከአጠገባችሁ የምታውቁት በሪሳ፣ገመቹ፣እና ሌሎች ሁሉ ናቸው። የኦሮሞ ማኅበረሰብ  የወያኔን ከፋፍለህ ግዛ እና የኦሮምያ ልዩ ጥቅም በአዲስ አበባ በሚል መቀሌን የኢትዮጵያ ዋና ከተማ የማድረግ እና አዲስ አበባን የማፍረስ ሥራ ይቀበላል ብሎ ማሰብ በእራሱ ስህተት ነው።

የእዚህ ረቂቅ አዋጅ ዓላማዎች የሚከተሉት ናቸው።

1/ ስልጣኑ ሁሉ በሕወሓት ስር መሆኑ እየታወቀ ጥቂት የኦሮሞ አክትቪስቶችን የመደለል ሥራ፣

2/ የአዲስ አበባ ሕዝብን እኔ ከስልጣን ከወረድኩ በዙርያህ ካለው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ጋር ግጭት ትፈጥራለህ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ፣

3/ የአዲስ አበባን እድገት ስልታዊ በሆነ መንገድ አዳክሞ የኢንዱስትሪ እና የዋና ከተማ ማዕከልነትን ወደ መቀሌ የመጎተት አላማ። ለምሳሌ በረቂቅ አዋጁ ጋር አዲስ አበባን እና የኦሮምያ ክልልን እንደ ሁለት ሀገር ድንበር አድርጎ ሲያስቀምጥ እንዲህ ይላል።

 "በዚህ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ 
(1) በተደነገገው መሰረት የተቀመጠውን የወሰን ምልክት ከተደረገበት በኋላ በማናቸውም ምክንያት መስፋት የማይቻል ሲሆን ወሰኑንም ክልሉ እና አስተዳደሩ የማክበር ግዴታ አለባቸው፡፡ 
3) ይህ አዋጅ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ወሰን ተከልሎ ምልክት መደረግ ይኖርበታል፡፡"  ይላል።
4/  የአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎችን ስያሜ ለምሳሌ አራት ኪሎ፣ ስድስት ኪሎ፣መርካቶ የሚሉት ስሞች ሁሉ እንዲቀየሩ በማድረግ የታሪክ ማዛባት መፍጠር በእዚህም ከ4 ሚልዮን የማያንሰውን የአዲስ አበባ ሕዝብ መብት ጨፍልቆ ታሪክ አልባ ማድረግ የሚሉት ይጠቀሳሉ።
ባጠቃላይ ወያኔ የህዝብ ማዕበል እየገፋው እንደሚሄድ ሲረዳ መጨረሻ ላይ ከሚወስዳቸው ርምጃዎች ውስጥ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ የሚያፋጅ ሥራ ላይ ማተኮር እንደሚሆን የታወቀ ነው።ውጤቱ ግን ምን ይሆናል?
የእዚህ የነበረ ነገር ግን በ1997 ዓም በምርጫ ሲሸነፍ እንደመዘዘው ያለ ካርድ የመምዘዙ ጉዳይ የተበላ እቁብ ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ኦሮምኛ ተናጋሪው ህዝብም ጭምር በትግሉ ሂደት በስሏል።ምናልባት ጥቂት የፖለቲካ ብስለቱ የጎደላቸው አክቲቪስቶች አሁንም ወያኔን አላወቁት ከሆነ በተዘጋጀላቸው ቦይ የመንጎድ መብታቸው እንደተጠበቀ ነው።የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ከቀረው ማኅበረሰብ ጋር እንዴት እንደሚኖሩ የእራሳቸው የከበረ ባህል፣እምነት እና ወግ አላቸው።እነኝህ እሴቶቻችን ለሕብረታችን እና አብሮ መኖራችን ዋስትና ናቸው።በእርግጥ ወያኔ እነኝህንም እሴቶች ለመጉዳት በርካታ ጥረት ሲያደርግ ኖሯል።የተወሰኑትንም ለማቁሰል ሞክሯል። ፈፅሞ ማጥፋት ግን አልቻለም።

ስለሆነም ወያኔ ለሚመዘው ለእዚህ አይነቱ የቆየ ካርድ መፍትሄው እራሱ ወያኔ የሚያወጣው ሕግ ሕጋዊ አለመሆኑን እና ሕጋዊ መንግስት እስኪመሰረት ድረስ የሽግግር መንግስት አስፈላጊነት ላይ አበክሮ መግፋት ነው።አንድ መንግስት ውድቀቱ አፋፍ ላይ ሆኖ የሚያወጣው ሕግ በእራሱ የቁራ መጮህ ማለት ነው።ውድቀት አፋፍ ላይ ያለ መንግስት የአዋጅ ጋጋታ መደርደሩ የተለመደ የአምባገነን መንግስት የውድቀት ዋዜማ ደውል ነው።ይህ የታሪክ ሂደት ነው።አሁን ለችግሮቹ መፍትሄው ዘለቄታ የሆነ የግለሰብ እና የቡድን መብቶች የሚከበሩበት እውነተኛ የፌድራል መንግስት ኢትዮጵያ እንዲኖራት የወያኔ መንግስት በሽግግር መንግስት እንዲተካ መታገል ነው።ይህ ደግሞ የሁሉም ኢትዮያዊ ኦሮምኛ ተናገረ አማርኛ፣ትግርኛ ተናገረ አፋርኛ የእራሱ ህልውና ጉዳይ ነው።ይህ ባይሆን ወያኔ ለጥቂት በሙስና ለተጨማለቁ እና ፍርፋርያቸውን ለሚቃርሙ ግለሰቦች እና ቡድኖች ሲባል የማያልቅ ችግር ውስጥ መግባት ነው።በመሆኑም ወያኔ የሚመዘውን የእራስ ምታት ማስታገሻ ካርድ በሚገባ ይግባን።ነፋስ እንደሚወስደው ገለባ ሳንሆን ዋናው ሃገራዊ ጉዳይ ላይ እናተኩር። ወያኔ የዘራብንም ሆነ ቀደም ብለው የነበሩ የጋራ ቁስሎቻችን የሚሽሩት እኛው ተመካክረን በምንመሰርተው መንግስት እንጂ ወያኔ ለክቶ እና ሰፍቶ በሚወረውርልን ድርጎ አይደለም።  

ጉዳያችን GUDAYACHN

 www.gudayachn.com

No comments: