ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, May 30, 2019

ያልታወቀ ወታደር ጉዳይ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጻፈ


  
ጉዳያችን / Gudayachn
ግንቦት 22/2011 ዓም (ሜይ 30/2019 ዓም)
===============

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ዛሬ ያለችበት ደረጃ እንድትደርስ የራሳቸውን ኑሮ፣ሕይወት እና ክብራቸውን ሳይቀር ሰውተው የሞቱላት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ወታደሮች ባለውለታችን ናቸው። ወታደር ሲባል የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ከተመሰረተ ጀምሮ ወዲህ ያለውን ወታደር ጉዳይ ይመለከታል።መከላከያም የኢትዮጵያ የመከላከያ ቀንን ኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ከመሰረተችበት ጊዜ ዘንድሮ ለ115ኛ ጊዜ መከበሩ ይበል የሚባል ነው።ከዘመናዊ ጦር በፊትም ሆነ በጣልያን ወረራ ወቅት በዱር በገደል ተንከራተው ነፃነት ላመጡ አርበኞች የአርበኞች የድል ሐውልት አራት ኪሎ ላይ በንጉሡ ዘመን ቆሞላቸዋል።የእኔ ትውልድ ደግሞ የሚያውቀው ወ ታ ደ ር  የሚለውን ክቡር ቃል ነው።ወታደር ለወገኑ እና ለሀገሩ ሲል ስጋውን ለአሞራ የሰጠ፣ ደሙን በአፈር ላይ ለማፍሰስ የወሰነ እና አጥንቱን ዓለት ላይ ለመከስከስ የወሰነ የፍቅር ሰው ነው።ወታደር እንደ ክርስቶስ እራሱን አሳፎ ሰጥቶ ወገኑ እና ሃገሩ ግን በሰላም እንድትኖር ሳይሞት በአይነ ህሊናው ስጋው እንዲዘለዘል የፈቀደ የፍቅር ሰው ነው።


ይህ የአንድ ወታደር መስዋዕትነት ምን ማለት እንደሆነ፣ለምን እንደሞተ፣ለመሞት ያስቆረጠው የሀገር ፍቅር ጉዳይ ሁሉ ከእኔ ትውልድ በታች ላለው  ለአሁኑ ትውልድ በሚገባ አልሰረፀም ወይንም ሆን ተብሎ ላለፉት አመታት እንዲደበዝዝ ተደርጎ ቆይቷል።ወታደር ማለት የደርግ ወታደር ከሚል ቃል ጋር ብቻ እያሟሹ የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው።ይህ ምን ያህል ኢትዮጵያን እንደጎዳት እና አሁን ይህንን የማስተካከል ሥራ ካተሰራም ትልቅ አደጋ እንደሚጠብቀን ማወቅ ብልህነት ነው። ስለሆነም ይህ የአልታወቀ ወታደር ግዙፍ ሃውልት እና አደባባይ እጅግ ያስፈልገናል።ላለፉትም ወደፊት ለሚመጡትም ወታደሮቻችን ደግሞ ልዩ ሃውልት እና ከስሩ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ሁሉ ያካተተ ማዕከል ያስፈልጋል።

ያታወቀው ወታደር ማን ነው?

ያልታወቀው ወታደር አድዋ ላይ የወደቀው የጋምቤላ ገበሬ ነው፣ያልታወቀው ወታደር በጥቁር አንበሳ ሰራዊት ስር ሆነው ጣልያንን ካርበደበዱት ጀግኖች ውስጥ ነው፣ያልታወቀው ወታደር በ1950 ዎቹ ውስጥ ሱማልያ ስትወረን በረሐ የወደቀው ጦር አባል ነው፣ያልታወቀው ወታደር በ1969 ዓም በሱማሌ በረሃ አሸዋ የበላው ኢትዮጵያን ብሎ የተደፋው ወታደር ነው፣ያልታወቀው ወታደር በባድማ ጦርነትን በፈንጅ ላይ የተረማመደው የሰሜን ሸዋ ወታደር ነው፣ያልታወቀው ወታደር የኢትዮጵያን ክብር ብሎ በኮንጎ የሞተው እና በኮርያ ጦርነት የቆሰለው ወታደር ነው፣ያልታወቀው ወታደር በምፅዋ ውግያ በጎጥ ሳይሆን የያኔዋ ኢትዮጵያዊቷ ኤርትራ  ለባዕዳን የሚያጋልጣት መከራ ውስጥ አትገባም ብሎ የተደፋው ወታደር ነው።ያልታወቀው ወታደር ቤተሰቡ እና እግዚአብሔር የሚያውቀው ታሪክ ይልተፃፈለት ስለ ፍቅር ብቻ ብሎ ድፍት እንዳለ የቀረው ወታደር ነው። ይህ ወታደር ብሔራዊ ዓርማ እና የምልክት ቦታ ያስፈልገዋል።

ያልታወቀ ወታደር ሐውልት ሃገራዊ ፋይዳ ምንድነው?

ሃገራዊ ፋይዳው እጅግ ብዙ ነው።ከእዚህ ውስጥ፟

1) ይህ ትውልድ ይህ ያልታወቀ ወታደር ለምን እንደሞተ ደጋግሞ እንዲያስብ ዕድል ይሰጣል።ይህም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ዋጋዋ ስንት እንደሆነ ከልቡ እንዲጽፍ ይረዳዋል።

2) ኢትዮጵያን አሁን ላለንበት ዘመን ያደረሱን ወታደሮች ሚስቶች፣እናቶች፣ አባቶች እና ልጆች ዛሬም ድረስ አባቶቻቸው፣ባሎቻቸው እና ወንድሞቻቸው ሁሉ ህይወቱ ለሰጠው ወታደር ዋጋ ተሰጥቶት ሲመለከቱ ህሊናቸው ያርፋል።በሐውልቱ ዙርያም ሆነ በአደባባዩ መጥተው ይዘክሩበታል።

3) መጪውም ሆነ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ጦር የስነ ልቦና ልዕልናውን ከፍ ያደርገዋል።ሕዝብ የሚሰጠው ዋጋ ለነገ መስዋዕትነት ዝግጁ ያደርጋቸዋል።

4) ትውልድ ያስታርቃል።በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ለሀገር ብለው የወደቁ ወታደሮች በሙሉ በአንድ ሐውልት ስር መግለጥ መከፋፈል ያጠፋል።የእርስ በርስ ጦርነት ታሪኮችን ወደ በጎ ታሪክ ይቀይራል።ሁሉም የሚወከልበት አንድ የጋራ ነጥብ ሲፈጠር ንዑስ ታሪኮች በሙሉ በግዙፉ ሃውልት ስር ይጠቃለላሉ። ይህ ማንንም አያነታርክም።በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ የኦሮሞ ጄኔራሎች፣የዓማራ ወታደሮች፣የትግራይ የጦር አባላት፣የጋምቤላ ምልምል ወታደሮች፣ከሱማሌ፣አፋር፣ጉራጌ፣ወዘተ ሁሉ በሰራዊቱ ውስጥ ሆነው ለኢትዮጵያ ደማቸውን ከአፈር ደባልቀዋል።ይህ ታሪክ በአንድ ሃውልት ሲጠቃለል ትውልድ ያስታርቃል።

ሐውልቱ ምን ይምሰል? 

ሐውልቱ እጅግ ግዙፍ፣ረጅም፣ ከፊቱ ላይ የሚነበበው አራት መልኮችን በአንድ ላይ የሚነበብበት መሆን አለበት። እነርሱም ደግነት፣ፍቅር፣ቁርጥ ልቦና፣ጀግንነት እና አስደንጋጭነት ናቸው።እነኝህን እንዴት በአንድ ግዙፍ ያልታወቀ ወታደር ፊት ላይ ይታያል? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ስራው የባለሙያዎቹ መሆኑን ብቻ ነው  እዚህ ላይ መናገር የምችለው።እነኝህ ገፅታዎች ግን ከሕፃናት እስከ አዋቂ ግዙፉን ያልታወቀ ወታደር ፊት በመመልከት ከአዕምሯቸው የማይጠፋ ፊት እንዲያቆዩ ይረዳቸዋል።ይህ ደግሞ ከአንድ ሺህ ገፅ ትረካ የበለጠ ትልቅ የትውፊት ሽግግር ነው።

የሐውልቱ ገንዘብ ከየት ይምጣ?

አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ወቅት ለእዚህ ግዙፍ ሐውልት በጀት መመደብ ሊያስቸግራት ይችላል።ከእዚህ ሁሉ በላይ ሐውልቱ በመንግስት በጀት ከሚሰራ ይልቅ እያንዳንዳንዱ ሰው የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ላለፈው አንድ መቶ ዓመት በቤተሰቡ ውስጥ አንድም ቢሆን የወታደር ቤተሰብ ያለው ከአንድ ብር ጀምሮ እንዲያዋጣ ማድረግ እና ይህንን ገንዘብ ወደ ሥራ እንዲቀየር ማድረግ ይቻላል።

ማጠቃለያ 

ኢትዮጵያ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በብዙ የነበረ እሴቶቿ ላይ አደጋ እራሷ በራሷ አድርሳለች።ይህ ደግሞ አሁን ላለው የጎሳ አስተሳሰብ ለሰፈነበት ትውልድ ዳርጎናል።ተማሪዎች ወደ ክፍል ጧት ሲገቡ ብሔራዊ መዝሙር ዘምረው የማይገቡ ልጆች ያሳደገች ኢትዮጵያ ዛሬ ብዙ መስራት አለባት።ስለሆነም ሀገራዊ ርዕይ ለማጉላት እና ትውልዱን በእዚህ በጎ ሃሳብ ላይ ለማሳፈር አንዱ እና ቁልፉ ጉዳይ ይህንን ያልታወቀ ወታደር ሃውልት መስራት እና የኢትዮጵያ አንዱ ስዕል እንዲሆን ማድረግ ነው።በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የተሰዋው ወታደር አለመታሰቡ መጪ ዘመናዊ ወታደር የሚሆን ትውልድ ያሳጣናል።ስለሆነም ጉዳዩ እጅግ አንገብጋቢ ነው።ተስፋ አለኝ ይህ ሃሳብ ዋጋ እንደሚያገኝ እና ወደ ሥራ እንደሚገባ።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Monday, May 27, 2019

በጋዜጠኞች ላይ ለሚደርሰው ጥቃት መፍትሄው - መደራጀት!

የጉዳያችን ማስታወሻ 
ግንቦት 19፣2011 ዓም (ሜይ 27፣2019 ዓም) 
=================
''ጋዜጠኝነት አንባቢዎች የታሪክ ምስክር ሲያደርግ ፣ ልብወለድ ፅሁፍ ግን ተደራሾቹ ድርሰቱን እንዲኖሩት አንድ ዕድል ይሰጣቸዋል።'' ጆን ሄርሴ 
'' Journalism allows its readers to witness history, fiction gives its readers an opportunity to live it.'' John Hersey.
=================
foto from gorjnews.ro

በያዝነው የፈረንጆቹ 2019 ዓም ''ዘ ኒዎርከር'' (The NEW YORKER) ሚያዝያ 22 ዕትም  እውቁን ጋዜጠኛ ጆን ሄርሴ የተመለከተ ፅሁፍ አውጥቶ ነበር።በእዚሁ ፅሁፉ ላይ ግለሰቡ የጋዜጠኝነት ሙያ ዘመናዊ ቅርፅ የሰጠ እንደሆነ ያትታል።ጆን ሄርሴ ''ሂሮሽማ'' በተሰኘው መፅሐፉ ነው ብዙዎች የሚያውቁት።ከላይ ይህ ጋዜጠኛ እንደማይዋሽ የገለጠበት ማስረጃ የታሪክ ምስክር እራሱ ሕዝብ መሆኑን በጥሩ አገላለጥ አስቀምጦታል።

አሁን በንኖርበት ዓለም ሕዝብን ከህዝብ፣መንግስት ከሕዝብ  እና መንግስትን ከመንግሥታት  ጋር በማገናኘት የጋዜጠኞች ሚና እጅግ ከፍ ያለ ነው። ጋዜጠኛ የህዝብ ዓይን ነው።ባለሥልጣኑ፣ነጋዴው፣ወታደሩ እና ፖሊሱ ሁሉ የሚሰራውን ካለምንም ፍርሃት ወደ አደባባይ የሚያወጣ ጋዜጠኛ ነው። ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ዘመን ከማንም ያልወገነ፣ነገር ግን ከህዝብ እና ሀገር ጋር ብቻ የቆመ ጋዜጠኛ በእጅጉ ያስፈልጋታል።

ጋዜጠኛ በየትኛውም ዓለም መንግስት እና አምባገነን ቡድኖች የሚፈሩት ትልቁ ጣኦት ነው።ጋዜጠኛ የሰሩትን ወንጀል ብቻ ሳይሆን ያሰቡትን ዕቅድ ሁሉ ስለምያጋልጥ እንደተፈራ ብቻ ሳይሆን እንደተጠቃ ይኖራል። ባደጉት ሀገሮች ሳይቀር ጋዜጠኞችን በድብቅ ማጥቃት፣በጥቅማቸው ላይ ሴራ መስራት እና እስከ ቤተሰብ የወረደ ማስፈራራት ሁሉ በጋዜጠኞች ላይ ይፈፀማሉ። እነኝህ ሁሉ ተግባራት ጋዜጠኛው የወንጀለኛ ቡድኖችን የወንጀል ሥራ ወደ ሕዝብ እንዳያወጣ ከመፍራት የሚነሱ ድርጊቶች ናቸው።

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ የአሐዱ ራድዮ ጋዜጠኛ ታምራት አበራ ከራድዮ ጣብያው ውስጥ ድረስ መሳርያ አንግበው በገቡ የኦሮምያ ፖሊሶች ተይዞ ለሶስት ቀናት ታስሮ መለቀቁ ተሰምቷል።ይህንኑ ጋዜጠኛ ሊጠይቅ የመጣው  ሌላ ጋዜጠኛም እንዲሁ ታስሮ መለቀቁ ሌላው የሳምንቱ ዜና ነው። በመጀመርያ ደረጃ ያ! የመከራ ዘመን አልፎ ይሄው አንድ ጋዜጠኛ ሶስት ቀን መታሰሩ የምናማርርበት ዘመን በመድረሳችን ብቻ እግዚአብሔርን ማመስገን ይገባል።ይህ ካለፈው ግፍ ጋር ሲነፃፀር ቅንጦት ይመስላል። ነገር ግን አይደለም። የጋዜጠኛው የታሰረበት ምክንያት ከአመት በፊት በዘገበው ጉዳይ መሆኑ እና ራድዮ ጣብያ ድረስ የታጠቁ ፖሊሶች ሄደው ማሰራቸው መልዕክቱ ቀላል አይደለም።

በአፍሪካ እያቆጠቆጡ ያሉት አዳዲስ አሸባሪ ቡድኖች እራሳቸውን በመንግስት መዋቅሮች ውስጥ አንገታቸውን እየቀበሩ የማሸበር ተግባራቸውን ሕጋዊ ሽፋን ሊሰጡት ሲሞክሩ አዲስ ክስተት አይደለም።እንደ ኬንያ እና ዩጋንዳ ለመንግስት ቅርበት ያላቸው ጠበቆች እና የፀጥታ አካላት የተቻቸውን ጋዜጠኛ በቀጥታ በመንግስት ሳይሆን የምያስጠቁት ሕጋዊ በሚመስሉ አካላት ግን በሌላ ጉዳይ እየተፈጠረ ነው።ይህንን የማሸበር ሥራ በመስራት በኢትዮጵያ አሁን ያለው መንግስት ሥራ የተጠለሉ ነገር ግን መንግስት እንደአካል ያልላካቸው የራሳቸውን ስልጣን በመጠቀም በሌላ መዋቅር ከሚሰሩት አካል ጋር እየተመሳጠሩ ጋዜጠኞችን ማሸማቀቅ ይዘዋል።ይህንን ተግባር መንግስት ባለው መውቃር ለጋዜጠኞች በቂ ጥበቃ እና ልዩ መብት እንዲሰጣቸው ማድረግ አለበት።

በጋዜጠኞች ላይ ለሚደርሰው ጥቃት መፍትሄው

ጋዜጠኞች ላይ ጥቃት በግልፅም ሆነ በስውር መፈፀም በተለይ እውነቱን በሚጋፈጡ ላይ የነበረ ነው ተብሎ የሚተው ጉዳይ አይደለም።መፍትሄ አለው። መፍትሄው ጋዜጠኞች ደረጃውን የጠበቀ በሰው ኃይል፣በሕግ ባለሙያ እና በገንዘብ የተደራጀ የሙያ ማኅበር ያስፈልጋቸዋል።ይህ ማኅበር ከየትኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላማከለ ነገር ግን በሀገራዊ እና  ሁሉም ጋዜጠኞች ሊመሩበት በሚገባው መሰረታዊ ሃገራዊ እና የህዝብ ጥቅም ላይ የተመሰረተ መመርያ ሊኖረው ይገባል።በእርግጥ ከኢትዮጵያ አንፃር አሁን ባለው ሁኔታ ጋዜጠኛ ማን ነው? ምን መስፈርት ያሟላ ነው ጋዜጠኛ የሚባለው? የጋዜጠኞች ማኅበር በአባልነት ማቀፍ ያለበት በምን መስፈርት አውጥቶ መሆን አለበት እና የሕግ ጥበቃም ሆነ ለሚደርስባቸው የኢኮኖሚ ሆነ አካላዊ ጉዳት ከጎናቸው የሚሆነው እንዴት ነው? የሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች የመለሰ ጠንካራ የሙያ ማኅበር ማቆም ወይንም የነበረውን መልሶ ማዋቀር እና ሕይወት ያለው የሚንቀሳቀስ ማኅበር ማድረግ አለባቸው። ይህ ካልሆነ ጥቂቶች ተሰብስበው በሚሰሩት የሽብር ተግባር ብዙዎች ጋዜጠኞች ከሙያው ስነ ምግባር የራቁ ይሆናሉ።የሙያ ማኅበሩ መልሶ ማንሰራራት በጋዜጠኞች ላይ አለአግባብ የማስፈራራት፣የማሰር እና የማንገላታት ተግባር የሚፈፅሙ ባለስልጣናትን አሽትቶ ደርሶ ማጋለጥ እና ማሳጣት በመቀጠልም ለፍርድ ማስቀረብ ሁሉ የሙያ ማኅበሩ ተግባር ይሆናል።ጋዜጠኞች አሁንም ተደራጁ! ቅፅራችሁን ሳታስደፍሩ በነፃነት ለኢትዮጵያ ለመናገር ቅድምያ ጠንካራ ማኅበር ይኑራችሁ።ያን ጊዜ ማንም አይደፍራቹም።

ጋዜጠኛው በቴዎድሮስ ሞሲሳ  (ዜማ)ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Monday, May 20, 2019

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ቀድሞ ለተፈጠረባችሁ እስኪ ፀባችሁን ከፈጠረው ጋር ሞክሩት።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
ግንቦት 12/2011 ዓም (ሜይ 20/2019 ዓም)

መሪዎች ቀድመው ሲወለዱ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም አዲስ አይደለም 

በኢትዮጵያ ዘመኑን የቀደሙ መሪዎች ሲነሱ አዲስ ክስተት አይደለም።ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የዘመነ መሳፍንት ሰፍሳፋነት እና ራስ ወዳድነት ተሻግረው የተፈጠሩ መሪ ነበሩ።አፄ ምንሊክ በአውሮፓ ስልጣኔ የሚያስቡ፣መኪና ሲያስገቡ ዙርያቸውን ባሉ ሲወገዙ ተሻግረው ሄደው ቀድመው መፈጠራቸውን ያስመሰከሩ ናቸው።በዘመናቸው ስለ አካባቢ ጥበቃ የሚያስብ ዓለም በሌለበት በመሰረቱት ካቢኔ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ መወያያ ሆኖ ስነ ምህዳሩ ወደፊት የሚገጥመውን ችግር ተገንዝበው ስለ በሃር ዛፍ መምጣት ውሳኔ የሚያሳልፉ በዘመናችን ያሉ መሪዎች የሚሸሹትን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ዋጋ የሰጡ መሪ ነበሩ።

 መሪዎች ለሀገራቸው የሚሰሩት ሥራ እና የሚያቅዱት ዕቅድ ለአንዳንዶች ምን ያህል የማይገባቸው እንደሆነ አንዱ ማሳያ ምሳሌ የፈረንሳዩን ምልክት የሆነው የፓሪስ ማማ -ኤፌል ታወር (Eiffel Tower) እንዲገነባ እኤአ 1887 ሲወሰን ሕልሙ እና ርዕዩ ያልገባቸው በፈረንሳይ መንግስት ላይ ተነስተውበት  የነበረ መሆኑን ማስታወስ በቂ ነው።የፓርሱ ኤፌል ታወር ፕሮጀክት መታቀዱን የፈረንሳይ መንግስት ሲያስተዋውቅ ሀሳቡ ያልገባቸው ወይንም ሆን ብለው የመቃወምያ ርዕስ ያገኙ የመሰላቸው በፈረንሳይ የወቅቱ መንግስት ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ከመውጣት እስከ ፊርማ ማሰባሰብ ዘምተውበት ነበር።ሕልመኛው የፈረንሳይ መንግስት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጁሌስ ግሬቪ  (Jules Grevy) ግን በጉዳዩ ገፋበት እና በጀቱ እንዲፀድቅ አስወስነው ግንባታው  እኤአ በ1887 ዓም ተጀምሮ በ1889 ዓም እንዲጠናቀቅ ተደረገ።ማማው  1063 ጫማ ርዝመት ያለው ሲሆን ያን ጊዜ ጥቅም የለውም የተባለው ማማ ዛሬ የፈረንሳይ ቀዳሚ ምልክት ሆኗል።ምልክት ብቻ አይደለም።ለፈረንሳይ ቱሪዝም ዋና መዳረሻ ከመሆኑ በላይ ለምሳሌ እኤአ በ2015 ዓም ብቻ  7 ሚልዮን የሚሆን ሕዝብ ከመላው ዓለም ጎብኝቶታል።ቁጥሩ በእየዓመቱ እየጨመረ የመጣ ለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
የፈረንሳዩ ዝነኛው ማማ ኤፈል ታወር  

ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚቃወሙ እነማን ናቸው?

አሁን ላለንበት ዘመን ቀድመው የተፈጠሩ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሰዎች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ይፈታል ብለው ከሚያስቡት የተለመደ መንገድ ይልቅ የተለየ ዕሳቤ ይዘው መጥተዋል።ይህ ዕሳቤ መደመር የተሰኘው ዕሳቤ ነው።ዕሳቤው በአጭሩ አገላለጥ ያለፈውን ቂም እና ቁርሾ በመተው ወደ አዲስ በልዩነት ሕብረት መሄድ ላይ ያጠነጥናል። ሀሳቡ ከእዚህ ባለፈ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገር የሽግግር መንገዱ ሁሉን እያቀፈ እና እያረቀ የመሄድ መንገድ ይከተላል።በእዚህ ሁሉ ሂደት ላይ ብዙዎች ብዙ ያሉበት አሁን እያሉበት ስለሆነ ዝርዝር ጉዳዩ ላይ እዚህ ላይ ለማንሳት አልፈለኩም። ማንሳት የፈለኩት ግን አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸው ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች ለምን እንደሚያስደነግጣቸው ምክንያቱን ለማስረዳት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች የሚያስደነግጣቸው ሰዎች መነሻ እና መድረሻቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ በምክንያታዊ ሀሳብ መሞገት ሳይሆን ተራ እና የወረደ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም ለማጥላላት የመሮጥ መንገድ ብቻ ሲከተሉ ነው የሚታዩት።ቀድመው የተፈጠሩ መሪዎች የሚያስቡት ዛሬ ላይ ላልደረሱ ሁል ጊዜ አይገባቸውም።አይገባቸውም ብቻ ሳይሆን የሀሳቡ ጠላት የሚሆኑበት ጥግ በራሱ ቀድሞ በተፈጠረው መሪ እንደ አደጋ ያዩታል።

በኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚነሱት እና ብቸኛ የዕውቀታቸው ልክ ማኅበራዊ ሚድያን በተለይ ፌስ ቡክን ብቻ ያደረጉ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚቃወሙበት ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ ስላልገባቸው ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ጉዳዩ ከግል ስግብግብ ባሕሪም ይመነጫል።ግማሾቹ በውጭ ሀገር በስደት በኖሩበት ዘመን በተለያየ ጊዜ ሲመሰርቱ እና ሲያፈርሱ ለነበረው የፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ ታክከው በስልጣን ወንበር ላይ ለመንጠላጠል ሲያልሙ ስለነበር የለውጡ በድንገት በእንዲህ አይነት መንገድ መከሰት አስደንግጧቸው መቃወም የዛሬ አርባ ዓመት እንደጀመሩ አእምሯቸውን ማስተካከል አቅቷቸው ዝም ብለው የቀጠሉ ናቸው። እነዚህ አሁን እየተቃወሙ መሆናቸውን ልብ አላሉት ይሆናል።መተዳደርያ ስላደረጉት ምክንያታዊነት ብሎ ነገር የላቸውም።

በሌላ በኩል  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ሆነው የሚታዩት በቅርቡ የወጡት ደግሞ አዲስ በቀል የጎሳ ድርጅቶች ናቸው።እነኝህ ዋስትና የማጣት ችግርን እንደዋና ምክንያት ያንሱት እንጂ ዋስትና ላለመኖሩ በቂ ማሳያ ቢያንስ ያለፈውን አንድ ዓመት ተንተርሳችሁ አምጡ ሲባሉ የሚያነሱት የፀጥታውን መታወክ ነው።የፀጥታው መታወክ ደግሞ የክልል ያውም የወረዳ አስተዳዳሪዎች ደረጃ እየተያያዘ የተፈጠረ እና በፅንፈኛ ብሄረተኞች ቅስቀሳ የተፈፀመ እንጂ አንድም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖሊሲ ምክንያት እንዳልሆነ በግልጥ የታየ ነው።በእርግጥ የፀጥታ አጠባበቁ ላይ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ ዘገየ የሚለው ወቀሳ በራሱ ያለ እና ብዙዎች የሚደግፉት ጉዳይ ቢሆንም  ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚወቅሱ ሰዎች የሚያነሱት ስር ነቀል ወቀሳ ጋር ፈፅሞ አይመጣጠንም። አንዳንድ ጊዜ ብሄርተኛ አክትቪስቶች ሕዝቡን ለማታለል የሚጠቀሙበት ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማጥላላት ልክ ጣልያን ኢትዮጵያን ሲወር ያልተወቀሰበት ጭፍን የጥላቻ እና ልክ የለሽ ብልግና የታየበት ነው።ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጣ ምላሽ መስጠት ያለበት ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሚያመጧቸው ሃሳቦች፣ንግግሮች ሁሉ አንዳቸው ከአንዳቸው የማይጣረሱ ለአንድ ዘመናዊ መንግስት አስፈላጊ ጉዳዮች ከመሆናቸው ባለፈ በምንም ዓይነት  የምያስወቅሱ ጉዳዮች የሉበትም።ይህ ማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይወቀሱ፣የማይከሰሱ ናቸው እያልኩ አይደለም።የወቃሾቹ የወቀሳ ዲግሪ ለተመለከተው ግን ፍፁም ፀረ ኢትዮጵያዊ የሆነ ይልቁንም ችግራቸው ሳያውቁት ጎሰኝነቱ አይሎባቸው ፀረ ኢትዮጵያ እንደሆኑ የሚያሳብቅ ነው።ሰው ፅዳቱን ተቃውሞ፣ የአዲስ አበባን ልማት ተቃውሞ፣ የመናገር ነፃነትን ወቅሶ እንዴት ነው ተቃዋሚ ነኝ የሚለው።ለመሆኑ ምን ዓይነት ዘመናዊ መንግስት ነበር ሲያልሙ የነበሩት ? ለኢትዮጵያስ ምን ዓይነት መሪ ነበር የሚመኙላት? የሚገርመው የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ሲያንስ በውጭ ሆኖ ለኢትዮጵያ ምን ላድርግ ከማለት ይልቅ ወይንም የትረስት ፈንዱን ከመደገፍ ይልቅ ምንዛሪ ማነሱ ላይ አስር ትንታኔ እየሰጡ የሚውሉ ጋዜጠኞች ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዱላታል? ኢትዮጵያ ሃሳብ የሚያመነጭላት፣ ይህንን ካልቻለ በገንዘብ የሚደግፋት እና የተቸገረ ሕዝቧን የሚደግፍ እንጂ መተዳደርያው በጎ አሳቢውን፣ቀን ከሌሊት በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚለፋውን ጠቅላይ ሚኒስትር በመውቀስ እና አቃቂር በማውጣት እንቅልፍ ያጡ ባናኞች ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዱላታል? ጉዳዩ የብዙዎችን ልብ አሳዝኗል።ነገር ግን ሕዝብ ከማዘን ባለፈ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆም ለእራሱም ሆነ ለኢትዮጵያ ህልውና መስራት የወቅቱ ጥያቄ ነው።

ለማጠቃለል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አንዳንዶች እንደሚያስቡት የድሮው ስርዓት ናፋቂ አይደሉም።ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔር አቀንቃኝም አይደሉም።የሁሉንም ሕመም በማዕከላዊነት እያስተናገዱ ነገር ግን ከአለፈው ስህተት የተማረች እና ዘመናዊ ትውልድ ተሻጋሪ መንግስት ያላት ሀገር መኖር ላይ ከሌሎች ጋር እየሰሩ እንደሆነ ብቻ ነው እስካሁን ያለው ሁኔታ የሚያሳየው።ነገም ከእዚህ የተለየ እንደማይሆን የእስካሁኑ መንገድ አመላካች ነው።ይልቅ ወገን የኢትዮጵያን መከራ አታርዝምባት።አንተ/አንቺ እንደግለሰብ እናንተ እንደ ቡድን ለኢትዮጵያ ምን እንስራ? አሁን ያለው መልካም ርዕይ ሁሉንም የሚጠቅም እንዲሆን ዋስትናውን ማረጋገጥ ላይ ለመስራት ዛሬ ለመጪው ትውልድ ለምን አሻራ እንጣል? ብሎ ማሰቡ የተሻለ ነው።ብዙ ንትርክ አሳለፍን።ስልጣን ያጣውም፣የሚፈልገውም እኩል እየዬ! የሚልባት ሀገር አናድርጋት።በሰለጠነ መልክ ሀሳብ መግለጥ፣መሞገት እንልመድ።ቀድመው የተፈጠሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በመጪው ዘመን የሚጠቅም ሥራ እያቀዱ ሲነግሩን ሰከን ብለን እንረዳው።በመንጋ አንነዳ።ጠቅላይ ሚኒስትሩም በእዚህ ሳምንት መጨረሻ ለሸገር ልማት በተዘጋጀ ራት ግብዣ ላይ -

''አቧራ ማስነሳት ቀላል ነው።አሻራ ማስቀመጥ ግን ሲጀመር ፈታኝ ሲፈፀም ደግሞ አስመስጋኝ ነው።ላሊበላ አሻራ ነው፣አክሱም አሻራ ነው፣ፋሲለደስ አሻራ ነው፣ የጀጎል ግንብ አሻራ ነው፣የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት አሻራ ነው፣ጥላሁን ገሠሠ አሻራ ነው፣ አሊቢራ አሻራ ነው፣የአድዋ ድል አሻራ ነው።አሻራ አይጠፋም።አቧራ ግን ለጊዜው ይነሳል።ለጊዜው ያስነጥሰናል ትንሽ ቆይቶ ግን ይጠፋል።ኢትዮጵያ ከአባቶቻችን የወረስናት ብቻ ሳትሆን ከልጆቻችንም የተዋስናት ናት።'' ብለዋል።

አዎን! ይህ ተራ ሙገሳ አይደለም።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ቀድመው የተወለዱ መሪ ናቸው።ምክንያት - ቀድመው ያስባሉና።ከእዚህ በፊት ቀድመው የተወለዱ መሪዎቿን ያመከነች ምድር በእዚህ ትውልድ ዘመን የዓብይን ሃሳቦች የማምከን አቅም የላትም። ምክንያቱም ሀሳቦቹ የሚልዮኖች ሀሳቦች ናቸው።ጥቂቶች ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል።ይህም ሆኖ እናከብራቸዋለን።የምናከብራቸው ግን ከሥርዓት አልበኝነት ውጭ እስከተቃወሙ እና የሌላውን ሀሳብ እስካከበሩ ድረስ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ቀድሞ ለተፈጠረባችሁ እስኪ ፀባችሁን ከፈጠረው ጋር ሞክሩት።ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሱን አልፈጠረም።የፈጠረው በጊዜ ለክቶ ፈጥሮታል።የፈጠረው ደግሞ አልተሳሳተም።

የአዲስ አበባ የወንዝ ተፋሰስ ፕሮጀክት (ቪድዮ)

የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አስተባባሪ ከአርክቴክት መስከረም ታምሩ ጋር  ውይይት በፋና ቀለማት (ቪድዮ)ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Wednesday, May 8, 2019

የአዲሱ ትውልድ ፖለቲካ ተጀምሯል።ከወጣት ናትናኤል ፈለቀ ጋር የተደረገ አዲስ ቃለ መጠይቅ (ቪድዮ)

ጉዳያችን /Gudayachn
ሚያዝያ 30/2011 ዓም 
አቶ ናትናኤል ፈለቀ የዞን 9 ጦማርያን ኢ-መደበኛ እንቅስቃሴ አባል ነበር።ለሕግ፣ለዲሞክራሲ  እና ፍትህ መከበር  በእስር ዋጋ ከፍሏል።በአሁኑ ወቅት ግንቦት 1 እና 2 የሚመሰረተው  አርበኞች ግንቦት 7 ጨምሮ  የሰባት ፖለቲካ ድርጅቶች አዲሱ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነው።

ቪድዮ ምንጭ = ናሁ ቴሌቭዥን ዩቱብ


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Monday, May 6, 2019

ጉዳያችን ዓቢይ ዜና - አዲሱ እና ግዙፉ ዜግነትንና ማኅበራዊ ፍትሕን መሰረት ያደረገው ፓርቲ መስራች ስብሰባውን በእዚህ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ያደርጋል።አርበኞች ግንቦት 7 ጨምሮ ሌሎች ስድስት ፓርቲዎች በውህደት ይከስማሉ።


ጉዳያችን/ Gudayachn
ሚያዝያ 29/2011 ዓም (ሜይ 7/2019 ዓም)

በዜግነት ፖለቲካ የሚያምኑ ስድስት የፖለቲካ ድርጅቶች ማለትም የአርበኞች ግንቦት ሰባት፣ሰማያዊ ፓርቲ፣ኢዴፓ፣የጋምቤላ  ክልል ብሔራዊ ንቅናቄ፣የቀድሞው አንድነት ፓርቲ እና መኢአድ ከስመው በውህደት አዲስ ፓርቲ እንደሚመሰርቱ እና የሜመሰረተው ፓርቲ መስራች ጉባኤውን ግንቦት 1 እና 2/2011 ዓም አዲስ አበባ ላይ እንደሚያደርግ የአስተባባሪው ግብረ ኃይል መጋቢት 19/2011 ዓም በሰጠው መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል።

በእዚህም መሰረት በአይነቱ እና በአደረጃጀቱ ከእዚህ በፊት በኢትዮጵያ ከተመሰረቱት ፓርቲዎች የተለየ ማለትም ከወረዳ ተነስቶ ወደላይ የሚወጣ አደረጃጀት እና ውክልና የያዘ አመሰራረት በመከተል በኢትዮጵያ ካለው 547 የምርጫ ወረዳዎች ውስጥ እስካሁን 312ቱን የሸፈነ እና ቁጥሩ እንደሚጨምር የተነገረ የወረዳ ሥራ አስፈፃሚ እና የጠቅላላ ጉባኤ ተወካዮች ምርጫ ተደርጎ 1200 የሚደርሱ የመስራች ጉባኤው ተሰብሳቢዎች በመጪው ሐሙስ ግንቦት 1 እና 2/2011 ዓም በሚመሰረተው አዲሱ ፓርቲ ላይ ለመገኘት አዲስ አበባ ይታደማሉ።

አቶ ናትናኤል ፈለቀ እና ሌሎች የመስራች ጉባኤው ግብረ ኃይል አስተባባሪዎች ዛሬ በሰጡት መግለጫ ለማወቅ እንደተቻለው በአሁኑ ሐሙስ እና ዓርብ የሚደረገው መስራች ጉባኤ የሚከተሉትን ዓበይት ተግባራት እንደሚያከናውን ለማወቅ ተችሏል። እነርሱም : -

  • የአዲሱን የውሑድ የፖለቲካ ፓርቲ ፕሮግራም እና ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ማፅደቅ፣
  • የአዲሱን ፓርቲ ስያሜ ማውጣት እና ማፅደቅ፣
  • የፓርቲውን ዓርማ መወሰን፣
  • የፓርቲውን መዝሙር ማፅደቅ፣
  • የፓርቲውን ረቂቅ መተዳደርያ ደንብ ማፅደቅ የሚሉት ይገኙበታል።
ይህ መስራች ጉባኤ ከመካሄዱ ቀደም ብሎ ለ348 ከየወረዳው ለተወከሉ የአሰልጣኞች ስልጠና የተሰጠ እና እነርሱም በየወረዳው ወርደው አስመራጭ ኮሚቴ አስመርጠው ከመጡ በኃላ የመስራቹን ተወካዮች ለማግኘት መቻሉን ለማወቅ ተችሏል።ይህ በዜግነት እና ማኅበራዊ ፍትህ ላይ መሰረት ያደረገው ፓርቲ ከ107 ፓርቲዎች ጋር ቁጥር እየቆጠሩ ''ፓርቲ ቢበዛ'' የሚል አስተያየት የሚሰጡ ከእውነታው ጋር የተቃረኑ እና ይህንን አዲሱን ፓርቲ ፈፅሞ ከእዚህ በፊት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ከታዩት የፖለቲካ ፓርቲዎች የተለየ መሆኑን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው።

ኢትዮጵያ በድምፃዊ ፀሐዬ ዮሐንስ 


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

የአማርኛ ትምህርት ቤት ያለህ! ጉዳያችን አዲስ ሀሳብ


ጉዳያችን አዲስ ሀሳብ
ሚያዝያ 28/2011 ዓም (ሜይ 6/2019 ዓም)
የአንድ ሀገር ሕዝብ ስልጣኔ በበሰለ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ በተሸጋገረ የቋንቋው  ጥልቀት እና ምጥቀት ይለካል።ስልጣኔ የህንፃ እና የፋብሪካ መደርደር ብቻ አይደለም።ስልጣኔ የአንድ ወቅት ክስተት ሆኖ እንዳይጠፋ እና ተሻጋሪ እንዲሆን የቋንቋ መኖር አስፈላጊ ነው።ቋንቋ ከቋንቋ አይበላለጥም።ይህ ማለት ግን ጥንታዊ መሰረት የያዘ ፊደል፣የቃላት ሀብት፣በውስጡ የያዛቸው የታሪክ መድበሎች ሁሉ ግን አንዱን ቋንቋ ከሌላው የበለጠ የበለፀገ ነው አይደለም የሚለው አያከራክርም ማለት አይደለም።

የጉዳያችን የዛሬ መነሻ እና መድረሻ ስለ ቋንቋ ለማተት አይደለም። ጉዳዩ የአማርኛ ቋንቋ አሁን ባለንበት ዘመን ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት አለው? ብሎ ለመጠየቅ እና የሚመለከታቸው ሁሉ በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲሹበት  ለማሳሰብ ነው።ጉዳያችን በእዚህ ዓመት አዲስ ሃሳብ በሚል ርዕስ አልፎ አልፎ ሃሳቦችን ለመሰንዘር እና በዓመቱ መጨረሻ ላይ የትኞቹ ተከናወኑ? የትኞቹ የሚሰማቸው አጡ? በሚል ሀሳብ ለማንሸራሸር ማቀዷን እና በእዚህም መሰረት በያዝነው የ2011 ዓም ወደ ሶስት የሚሆኑ ሃሳቦች መነሳታቸው እና አሁን ይህ አራተኛው ሀሳብ መሆኑን ለማስታወስ እፈልጋለሁ።ይህ ማለት በአዲስ ሀሳብ ስር የሚቀርቡትን እንጂ ሌሎች ዘገባዎች እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን ሳይጨምር ማለት ነው።

የአማርኛ ትምህርት ቤት ያለህ!

በሐያ አንደኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያ በሯን ለውጭው ዓለም ለመክፈት እየሞከረች ነው።በቅርቡ በተፈጠረው የመንግስት ለውጥ (ጥገናዊ ለውጥ) ወዲህ ብቻ ኢትዮጵያ ላይ መላው ዓለም ትኩረቱን መድረጉን ብቻ ሳይሆን ከኢንቨስትመንት እስከ ቱሪስት ማዕከል ለመጠቀም በርካታ ዓለም አቀፍ የገበያ አጥኚዎች ትኩረታቸው ሆነናል። ሰሞኑን ኢትዮጵያ ደርሶ የመጣ አንድ ወዳጄ ምን ተመለከትክ ስለው ከተመለከተው ውስጥ ከዋጋ ንረት በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገር ዜጎች በብዛት ወደ ሀገሪቱ መግባት መውጣታቸውን ነው ብሎኛል።

በጥገናዊ ለውጡ ሂደት ወደፊትም በርካታ የውጭ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ማሳያዎች አሉ። ከእነዚህ ማሳያዎች ውስጥ -

  • አፍሪቃውያን ወደ ኢትዮጵያ ካለ ቪዛ እንዲገቡ መፈቀዱ።
  • የቻይና ኩባንያዎች የበለጠ ፕሮጀክቶች እየወሰዱ መሆናቸው፣
  • ለስደተኞች የተሰጠው የመስራት መብት፣
  • የቱሪስት ፍሰቱ መጨመሩ እና 
  • መንግስት ታላላቅ የሀገሪቱ ኩባንያዎችን በከፊል ወደ ግል ለማዞር እያስጠና መሆኑን እና የውጭ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ የበለጠ የመምጣታቸው ፋይዳ መጨመሩን ነው።
እነኝህ እና ሌሎች ጉዳዮች የሚያሳዩን ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ሰላሟን ጠብቃ መሄድ ከቻለች እና የፖለቲካ ሁኔታው በትክክል መስተካከል ከቻለ የብዙ የውጭ ዜጎች መዳረሻ መሆናችን ነው።ይህ በራሱ በበጎ ልንመልከተው የሚገባ ነው።ከውጭ ዜጎች የምንማረው እና የምናገኛቸው በርካታ ነገሮች አሉ።የሙያ ክህሎት፣አሰራሮች፣የስራ ትጋት እና ቴክኖሎጂ ሁሉ የማግኘት ዕድሎች አሉ።በአንፃሩ ሌሎች አሉታዊ ጉዳዮች የሉም ማለት ግን አይደለም።አሉታዊ ጉዳዮች ላይ መንግስትም ሆነ ህዝቡ ቀድሞ እያጠና የማረም እርምጃ መውሰድ ይችላል።

ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው የውጭ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የሚገጥማቸው አንዱ ችግር የቋንቋ ጉዳይ ነው።በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎች የሚነገረው እና የጋራ ቋንቋ ሆኖ ያለው በአሁኑ ሰዓት አማርኛ ነው። አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋም ነው።ወደፊት ሌሎች ብሔራዊ ቋንቋዎች ሊኖሩን ይችላሉ።ይህ በራሱ ችግር የለውም።አሁን ግን ስለ አማርኛው እናውራ።

በየትኛውም የዓለም ክፍል የሀገራቸውን ብሔራዊ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች በእየከተሞች ማግኘት ትልቅ እና አድካሚ ሥራ አይደለም።ከስልሳ ሚልዮን ሕዝብ በላይ ተናጋሪ ያለው አማርኛን ልማር ብሎ አዲስ አበባ ላይ በሥራ የተጠመደ አንድ የውጭ ዜጋ ግን የት ነው ሄዶ የሚማረው? በርካታ ቻይናዎች አማርኛ የተማሩት የት ነው? አሜሪካኖቹ አማርኛ የት ይማሩ? የአፍሪካ ሕብረት አማርኛ መጠቀም አለበት እያሉ የሚሟገቱ አፍሪቃውያን የት ትምህርት ቤት ገብተው ይማሩ? በልማድ በራሳቸው ካልተማሩ ደረጃ የወጣለት አንድ የአማርኛ ትምህርት ቤት አዲስ አበባ ላይ አለ? ትምህርት ቤቱስ በትምህርት ሚኒስትር ደረጃ ወጥቶለት አማርኛ ለተማረው ሰው ሰርጠፍኬቱ እውቅና አለው? አንድ በአማርኛ ትምህርት በቂ ትምህርት ዕውቀት ያለው ሰው ወይንም ባለ ሀብቶች ሰብሰብ ብለው በብዙ የኢትዮጵያ እና የውጭ ሀገር ከተሞች  አዲስ አበባን ጨምሮ ቢከፍቱ እና ትምህርት ሚኒስትር ደረጃ ቢያወጣለት ትልቅ ገበያ የለውም? ብዙ አፍሪካውያን፣ቻይናውያን፣ሌላው ቀርቶ ውጭ የተወለዱ በሺህ የሚቆጠሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ትምህርት ቤቱን አያጥለቀልቁትም? ባለ ሀብቶች እና ባለ ዕውቀቶች ተጠቀሙበት።ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአማርኛ ደረጃ አውጡለት።ስለ አማርኛ ብዙ እንደምትቆረቆሩ የምትነግሩንም ብዙ ከምታወሩ ይህንን ፍሬ ያለው ሥራ ስሩና ትውልድ አሻግሩ።ሀገር ጥቀሙ። 
ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Friday, May 3, 2019

ዶ/ር አንማው አንተነህ በኢትዮጵያ የዘውግ እና የኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ዙርያ የሰጡት ቃለ ምልልስ (ቪድዮ)

>> ብሔርተኛ ዲሞክራሲያዊነት ብሎ ነገር የለም።ብሔርተኝነት ወደ አውሬነት  ነው የሚቀይርህ።ብሔርተኛ ሆኖ ዲሞክራሲያዊ መሆን ፈፅሞ አይቻልም።
>> ብሔርተኝነት አምስቱን የስሜት ሕዋሳት ያሳጣል።
>> ብሔርተኝነት ውስጥ ሆኖ እንነጋገር ብሎ ነገር አይገባኝም።አንድ ከረጢት ውስጥ ቀድሞ ገብቶ በአንድ አስተሳሰብ ተለጉሞ እንዴት ይነጋገራል?
ሙሉ ቪድዮዎቹን ይመልከቱ።


ቪድዮ ክፍል አንድ
===============


ቪድዮ ክፍል ሁለት 
===============

ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

ወቅታዊ የዓለም ሁኔታ እንድንነታረክ ዕድል የሚሰጥ አይደለም።ብንነቃ መልካም ነው።

========== ጉዳያችን ወቅታዊ ========== የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ዓለም በወሳኝ የእጥፋት(turning point) ታሪኮች ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የእጥፋት ጊዜዎች የዋዛና የፈዛዛ ጊዜ አይደሉም።መላው ዓለ...