ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, May 30, 2019

ያልታወቀ ወታደር ጉዳይ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጻፈ


  
ጉዳያችን / Gudayachn
ግንቦት 22/2011 ዓም (ሜይ 30/2019 ዓም)
===============

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር!

ኢትዮጵያን እንደ ሀገር ዛሬ ያለችበት ደረጃ እንድትደርስ የራሳቸውን ኑሮ፣ሕይወት እና ክብራቸውን ሳይቀር ሰውተው የሞቱላት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ወታደሮች ባለውለታችን ናቸው። ወታደር ሲባል የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ከተመሰረተ ጀምሮ ወዲህ ያለውን ወታደር ጉዳይ ይመለከታል።መከላከያም የኢትዮጵያ የመከላከያ ቀንን ኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር ከመሰረተችበት ጊዜ ዘንድሮ ለ115ኛ ጊዜ መከበሩ ይበል የሚባል ነው።ከዘመናዊ ጦር በፊትም ሆነ በጣልያን ወረራ ወቅት በዱር በገደል ተንከራተው ነፃነት ላመጡ አርበኞች የአርበኞች የድል ሐውልት አራት ኪሎ ላይ በንጉሡ ዘመን ቆሞላቸዋል።የእኔ ትውልድ ደግሞ የሚያውቀው ወ ታ ደ ር  የሚለውን ክቡር ቃል ነው።ወታደር ለወገኑ እና ለሀገሩ ሲል ስጋውን ለአሞራ የሰጠ፣ ደሙን በአፈር ላይ ለማፍሰስ የወሰነ እና አጥንቱን ዓለት ላይ ለመከስከስ የወሰነ የፍቅር ሰው ነው።ወታደር እንደ ክርስቶስ እራሱን አሳፎ ሰጥቶ ወገኑ እና ሃገሩ ግን በሰላም እንድትኖር ሳይሞት በአይነ ህሊናው ስጋው እንዲዘለዘል የፈቀደ የፍቅር ሰው ነው።


ይህ የአንድ ወታደር መስዋዕትነት ምን ማለት እንደሆነ፣ለምን እንደሞተ፣ለመሞት ያስቆረጠው የሀገር ፍቅር ጉዳይ ሁሉ ከእኔ ትውልድ በታች ላለው  ለአሁኑ ትውልድ በሚገባ አልሰረፀም ወይንም ሆን ተብሎ ላለፉት አመታት እንዲደበዝዝ ተደርጎ ቆይቷል።ወታደር ማለት የደርግ ወታደር ከሚል ቃል ጋር ብቻ እያሟሹ የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው።ይህ ምን ያህል ኢትዮጵያን እንደጎዳት እና አሁን ይህንን የማስተካከል ሥራ ካተሰራም ትልቅ አደጋ እንደሚጠብቀን ማወቅ ብልህነት ነው። ስለሆነም ይህ የአልታወቀ ወታደር ግዙፍ ሃውልት እና አደባባይ እጅግ ያስፈልገናል።ላለፉትም ወደፊት ለሚመጡትም ወታደሮቻችን ደግሞ ልዩ ሃውልት እና ከስሩ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ሁሉ ያካተተ ማዕከል ያስፈልጋል።

ያታወቀው ወታደር ማን ነው?

ያልታወቀው ወታደር አድዋ ላይ የወደቀው የጋምቤላ ገበሬ ነው፣ያልታወቀው ወታደር በጥቁር አንበሳ ሰራዊት ስር ሆነው ጣልያንን ካርበደበዱት ጀግኖች ውስጥ ነው፣ያልታወቀው ወታደር በ1950 ዎቹ ውስጥ ሱማልያ ስትወረን በረሐ የወደቀው ጦር አባል ነው፣ያልታወቀው ወታደር በ1969 ዓም በሱማሌ በረሃ አሸዋ የበላው ኢትዮጵያን ብሎ የተደፋው ወታደር ነው፣ያልታወቀው ወታደር በባድማ ጦርነትን በፈንጅ ላይ የተረማመደው የሰሜን ሸዋ ወታደር ነው፣ያልታወቀው ወታደር የኢትዮጵያን ክብር ብሎ በኮንጎ የሞተው እና በኮርያ ጦርነት የቆሰለው ወታደር ነው፣ያልታወቀው ወታደር በምፅዋ ውግያ በጎጥ ሳይሆን የያኔዋ ኢትዮጵያዊቷ ኤርትራ  ለባዕዳን የሚያጋልጣት መከራ ውስጥ አትገባም ብሎ የተደፋው ወታደር ነው።ያልታወቀው ወታደር ቤተሰቡ እና እግዚአብሔር የሚያውቀው ታሪክ ይልተፃፈለት ስለ ፍቅር ብቻ ብሎ ድፍት እንዳለ የቀረው ወታደር ነው። ይህ ወታደር ብሔራዊ ዓርማ እና የምልክት ቦታ ያስፈልገዋል።

ያልታወቀ ወታደር ሐውልት ሃገራዊ ፋይዳ ምንድነው?

ሃገራዊ ፋይዳው እጅግ ብዙ ነው።ከእዚህ ውስጥ፟

1) ይህ ትውልድ ይህ ያልታወቀ ወታደር ለምን እንደሞተ ደጋግሞ እንዲያስብ ዕድል ይሰጣል።ይህም ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ዋጋዋ ስንት እንደሆነ ከልቡ እንዲጽፍ ይረዳዋል።

2) ኢትዮጵያን አሁን ላለንበት ዘመን ያደረሱን ወታደሮች ሚስቶች፣እናቶች፣ አባቶች እና ልጆች ዛሬም ድረስ አባቶቻቸው፣ባሎቻቸው እና ወንድሞቻቸው ሁሉ ህይወቱ ለሰጠው ወታደር ዋጋ ተሰጥቶት ሲመለከቱ ህሊናቸው ያርፋል።በሐውልቱ ዙርያም ሆነ በአደባባዩ መጥተው ይዘክሩበታል።

3) መጪውም ሆነ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ጦር የስነ ልቦና ልዕልናውን ከፍ ያደርገዋል።ሕዝብ የሚሰጠው ዋጋ ለነገ መስዋዕትነት ዝግጁ ያደርጋቸዋል።

4) ትውልድ ያስታርቃል።በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል ለሀገር ብለው የወደቁ ወታደሮች በሙሉ በአንድ ሐውልት ስር መግለጥ መከፋፈል ያጠፋል።የእርስ በርስ ጦርነት ታሪኮችን ወደ በጎ ታሪክ ይቀይራል።ሁሉም የሚወከልበት አንድ የጋራ ነጥብ ሲፈጠር ንዑስ ታሪኮች በሙሉ በግዙፉ ሃውልት ስር ይጠቃለላሉ። ይህ ማንንም አያነታርክም።በኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ውስጥ የኦሮሞ ጄኔራሎች፣የዓማራ ወታደሮች፣የትግራይ የጦር አባላት፣የጋምቤላ ምልምል ወታደሮች፣ከሱማሌ፣አፋር፣ጉራጌ፣ወዘተ ሁሉ በሰራዊቱ ውስጥ ሆነው ለኢትዮጵያ ደማቸውን ከአፈር ደባልቀዋል።ይህ ታሪክ በአንድ ሃውልት ሲጠቃለል ትውልድ ያስታርቃል።

ሐውልቱ ምን ይምሰል? 

ሐውልቱ እጅግ ግዙፍ፣ረጅም፣ ከፊቱ ላይ የሚነበበው አራት መልኮችን በአንድ ላይ የሚነበብበት መሆን አለበት። እነርሱም ደግነት፣ፍቅር፣ቁርጥ ልቦና፣ጀግንነት እና አስደንጋጭነት ናቸው።እነኝህን እንዴት በአንድ ግዙፍ ያልታወቀ ወታደር ፊት ላይ ይታያል? የሚል ጥያቄ ቢነሳ ስራው የባለሙያዎቹ መሆኑን ብቻ ነው  እዚህ ላይ መናገር የምችለው።እነኝህ ገፅታዎች ግን ከሕፃናት እስከ አዋቂ ግዙፉን ያልታወቀ ወታደር ፊት በመመልከት ከአዕምሯቸው የማይጠፋ ፊት እንዲያቆዩ ይረዳቸዋል።ይህ ደግሞ ከአንድ ሺህ ገፅ ትረካ የበለጠ ትልቅ የትውፊት ሽግግር ነው።

የሐውልቱ ገንዘብ ከየት ይምጣ?

አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ወቅት ለእዚህ ግዙፍ ሐውልት በጀት መመደብ ሊያስቸግራት ይችላል።ከእዚህ ሁሉ በላይ ሐውልቱ በመንግስት በጀት ከሚሰራ ይልቅ እያንዳንዳንዱ ሰው የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ላለፈው አንድ መቶ ዓመት በቤተሰቡ ውስጥ አንድም ቢሆን የወታደር ቤተሰብ ያለው ከአንድ ብር ጀምሮ እንዲያዋጣ ማድረግ እና ይህንን ገንዘብ ወደ ሥራ እንዲቀየር ማድረግ ይቻላል።

ማጠቃለያ 

ኢትዮጵያ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በብዙ የነበረ እሴቶቿ ላይ አደጋ እራሷ በራሷ አድርሳለች።ይህ ደግሞ አሁን ላለው የጎሳ አስተሳሰብ ለሰፈነበት ትውልድ ዳርጎናል።ተማሪዎች ወደ ክፍል ጧት ሲገቡ ብሔራዊ መዝሙር ዘምረው የማይገቡ ልጆች ያሳደገች ኢትዮጵያ ዛሬ ብዙ መስራት አለባት።ስለሆነም ሀገራዊ ርዕይ ለማጉላት እና ትውልዱን በእዚህ በጎ ሃሳብ ላይ ለማሳፈር አንዱ እና ቁልፉ ጉዳይ ይህንን ያልታወቀ ወታደር ሃውልት መስራት እና የኢትዮጵያ አንዱ ስዕል እንዲሆን ማድረግ ነው።በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የተሰዋው ወታደር አለመታሰቡ መጪ ዘመናዊ ወታደር የሚሆን ትውልድ ያሳጣናል።ስለሆነም ጉዳዩ እጅግ አንገብጋቢ ነው።ተስፋ አለኝ ይህ ሃሳብ ዋጋ እንደሚያገኝ እና ወደ ሥራ እንደሚገባ።


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...