ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Monday, May 20, 2019

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ቀድሞ ለተፈጠረባችሁ እስኪ ፀባችሁን ከፈጠረው ጋር ሞክሩት።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
ግንቦት 12/2011 ዓም (ሜይ 20/2019 ዓም)

መሪዎች ቀድመው ሲወለዱ ለኢትዮጵያም ሆነ ለዓለም አዲስ አይደለም 

በኢትዮጵያ ዘመኑን የቀደሙ መሪዎች ሲነሱ አዲስ ክስተት አይደለም።ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ የዘመነ መሳፍንት ሰፍሳፋነት እና ራስ ወዳድነት ተሻግረው የተፈጠሩ መሪ ነበሩ።አፄ ምንሊክ በአውሮፓ ስልጣኔ የሚያስቡ፣መኪና ሲያስገቡ ዙርያቸውን ባሉ ሲወገዙ ተሻግረው ሄደው ቀድመው መፈጠራቸውን ያስመሰከሩ ናቸው።በዘመናቸው ስለ አካባቢ ጥበቃ የሚያስብ ዓለም በሌለበት በመሰረቱት ካቢኔ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ መወያያ ሆኖ ስነ ምህዳሩ ወደፊት የሚገጥመውን ችግር ተገንዝበው ስለ በሃር ዛፍ መምጣት ውሳኔ የሚያሳልፉ በዘመናችን ያሉ መሪዎች የሚሸሹትን የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ዋጋ የሰጡ መሪ ነበሩ።

 መሪዎች ለሀገራቸው የሚሰሩት ሥራ እና የሚያቅዱት ዕቅድ ለአንዳንዶች ምን ያህል የማይገባቸው እንደሆነ አንዱ ማሳያ ምሳሌ የፈረንሳዩን ምልክት የሆነው የፓሪስ ማማ -ኤፌል ታወር (Eiffel Tower) እንዲገነባ እኤአ 1887 ሲወሰን ሕልሙ እና ርዕዩ ያልገባቸው በፈረንሳይ መንግስት ላይ ተነስተውበት  የነበረ መሆኑን ማስታወስ በቂ ነው።የፓርሱ ኤፌል ታወር ፕሮጀክት መታቀዱን የፈረንሳይ መንግስት ሲያስተዋውቅ ሀሳቡ ያልገባቸው ወይንም ሆን ብለው የመቃወምያ ርዕስ ያገኙ የመሰላቸው በፈረንሳይ የወቅቱ መንግስት ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ከመውጣት እስከ ፊርማ ማሰባሰብ ዘምተውበት ነበር።ሕልመኛው የፈረንሳይ መንግስት የወቅቱ ፕሬዝዳንት ጁሌስ ግሬቪ  (Jules Grevy) ግን በጉዳዩ ገፋበት እና በጀቱ እንዲፀድቅ አስወስነው ግንባታው  እኤአ በ1887 ዓም ተጀምሮ በ1889 ዓም እንዲጠናቀቅ ተደረገ።ማማው  1063 ጫማ ርዝመት ያለው ሲሆን ያን ጊዜ ጥቅም የለውም የተባለው ማማ ዛሬ የፈረንሳይ ቀዳሚ ምልክት ሆኗል።ምልክት ብቻ አይደለም።ለፈረንሳይ ቱሪዝም ዋና መዳረሻ ከመሆኑ በላይ ለምሳሌ እኤአ በ2015 ዓም ብቻ  7 ሚልዮን የሚሆን ሕዝብ ከመላው ዓለም ጎብኝቶታል።ቁጥሩ በእየዓመቱ እየጨመረ የመጣ ለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
የፈረንሳዩ ዝነኛው ማማ ኤፈል ታወር  

ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚቃወሙ እነማን ናቸው?

አሁን ላለንበት ዘመን ቀድመው የተፈጠሩ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ሰዎች የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ይፈታል ብለው ከሚያስቡት የተለመደ መንገድ ይልቅ የተለየ ዕሳቤ ይዘው መጥተዋል።ይህ ዕሳቤ መደመር የተሰኘው ዕሳቤ ነው።ዕሳቤው በአጭሩ አገላለጥ ያለፈውን ቂም እና ቁርሾ በመተው ወደ አዲስ በልዩነት ሕብረት መሄድ ላይ ያጠነጥናል። ሀሳቡ ከእዚህ ባለፈ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማሻገር የሽግግር መንገዱ ሁሉን እያቀፈ እና እያረቀ የመሄድ መንገድ ይከተላል።በእዚህ ሁሉ ሂደት ላይ ብዙዎች ብዙ ያሉበት አሁን እያሉበት ስለሆነ ዝርዝር ጉዳዩ ላይ እዚህ ላይ ለማንሳት አልፈለኩም። ማንሳት የፈለኩት ግን አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያቀርቧቸው ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች ለምን እንደሚያስደነግጣቸው ምክንያቱን ለማስረዳት ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘመን ተሻጋሪ ስራዎች የሚያስደነግጣቸው ሰዎች መነሻ እና መድረሻቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሀሳብ በምክንያታዊ ሀሳብ መሞገት ሳይሆን ተራ እና የወረደ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ስም ለማጥላላት የመሮጥ መንገድ ብቻ ሲከተሉ ነው የሚታዩት።ቀድመው የተፈጠሩ መሪዎች የሚያስቡት ዛሬ ላይ ላልደረሱ ሁል ጊዜ አይገባቸውም።አይገባቸውም ብቻ ሳይሆን የሀሳቡ ጠላት የሚሆኑበት ጥግ በራሱ ቀድሞ በተፈጠረው መሪ እንደ አደጋ ያዩታል።

በኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ የሚነሱት እና ብቸኛ የዕውቀታቸው ልክ ማኅበራዊ ሚድያን በተለይ ፌስ ቡክን ብቻ ያደረጉ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚቃወሙበት ምክንያት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀሳብ ስላልገባቸው ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። ጉዳዩ ከግል ስግብግብ ባሕሪም ይመነጫል።ግማሾቹ በውጭ ሀገር በስደት በኖሩበት ዘመን በተለያየ ጊዜ ሲመሰርቱ እና ሲያፈርሱ ለነበረው የፖለቲካ ፓርቲ ታሪክ ታክከው በስልጣን ወንበር ላይ ለመንጠላጠል ሲያልሙ ስለነበር የለውጡ በድንገት በእንዲህ አይነት መንገድ መከሰት አስደንግጧቸው መቃወም የዛሬ አርባ ዓመት እንደጀመሩ አእምሯቸውን ማስተካከል አቅቷቸው ዝም ብለው የቀጠሉ ናቸው። እነዚህ አሁን እየተቃወሙ መሆናቸውን ልብ አላሉት ይሆናል።መተዳደርያ ስላደረጉት ምክንያታዊነት ብሎ ነገር የላቸውም።

በሌላ በኩል  የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቃዋሚ ሆነው የሚታዩት በቅርቡ የወጡት ደግሞ አዲስ በቀል የጎሳ ድርጅቶች ናቸው።እነኝህ ዋስትና የማጣት ችግርን እንደዋና ምክንያት ያንሱት እንጂ ዋስትና ላለመኖሩ በቂ ማሳያ ቢያንስ ያለፈውን አንድ ዓመት ተንተርሳችሁ አምጡ ሲባሉ የሚያነሱት የፀጥታውን መታወክ ነው።የፀጥታው መታወክ ደግሞ የክልል ያውም የወረዳ አስተዳዳሪዎች ደረጃ እየተያያዘ የተፈጠረ እና በፅንፈኛ ብሄረተኞች ቅስቀሳ የተፈፀመ እንጂ አንድም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖሊሲ ምክንያት እንዳልሆነ በግልጥ የታየ ነው።በእርግጥ የፀጥታ አጠባበቁ ላይ መንግስት እርምጃ ለመውሰድ ዘገየ የሚለው ወቀሳ በራሱ ያለ እና ብዙዎች የሚደግፉት ጉዳይ ቢሆንም  ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚወቅሱ ሰዎች የሚያነሱት ስር ነቀል ወቀሳ ጋር ፈፅሞ አይመጣጠንም። አንዳንድ ጊዜ ብሄርተኛ አክትቪስቶች ሕዝቡን ለማታለል የሚጠቀሙበት ጠቅላይ ሚኒስትሩን የማጥላላት ልክ ጣልያን ኢትዮጵያን ሲወር ያልተወቀሰበት ጭፍን የጥላቻ እና ልክ የለሽ ብልግና የታየበት ነው።ይህ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁጣ ምላሽ መስጠት ያለበት ጉዳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሚያመጧቸው ሃሳቦች፣ንግግሮች ሁሉ አንዳቸው ከአንዳቸው የማይጣረሱ ለአንድ ዘመናዊ መንግስት አስፈላጊ ጉዳዮች ከመሆናቸው ባለፈ በምንም ዓይነት  የምያስወቅሱ ጉዳዮች የሉበትም።ይህ ማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማይወቀሱ፣የማይከሰሱ ናቸው እያልኩ አይደለም።የወቃሾቹ የወቀሳ ዲግሪ ለተመለከተው ግን ፍፁም ፀረ ኢትዮጵያዊ የሆነ ይልቁንም ችግራቸው ሳያውቁት ጎሰኝነቱ አይሎባቸው ፀረ ኢትዮጵያ እንደሆኑ የሚያሳብቅ ነው።ሰው ፅዳቱን ተቃውሞ፣ የአዲስ አበባን ልማት ተቃውሞ፣ የመናገር ነፃነትን ወቅሶ እንዴት ነው ተቃዋሚ ነኝ የሚለው።ለመሆኑ ምን ዓይነት ዘመናዊ መንግስት ነበር ሲያልሙ የነበሩት ? ለኢትዮጵያስ ምን ዓይነት መሪ ነበር የሚመኙላት? የሚገርመው የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ሲያንስ በውጭ ሆኖ ለኢትዮጵያ ምን ላድርግ ከማለት ይልቅ ወይንም የትረስት ፈንዱን ከመደገፍ ይልቅ ምንዛሪ ማነሱ ላይ አስር ትንታኔ እየሰጡ የሚውሉ ጋዜጠኞች ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዱላታል? ኢትዮጵያ ሃሳብ የሚያመነጭላት፣ ይህንን ካልቻለ በገንዘብ የሚደግፋት እና የተቸገረ ሕዝቧን የሚደግፍ እንጂ መተዳደርያው በጎ አሳቢውን፣ቀን ከሌሊት በኢትዮጵያ ጉዳይ የሚለፋውን ጠቅላይ ሚኒስትር በመውቀስ እና አቃቂር በማውጣት እንቅልፍ ያጡ ባናኞች ለኢትዮጵያ ምን ይፈይዱላታል? ጉዳዩ የብዙዎችን ልብ አሳዝኗል።ነገር ግን ሕዝብ ከማዘን ባለፈ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን በመቆም ለእራሱም ሆነ ለኢትዮጵያ ህልውና መስራት የወቅቱ ጥያቄ ነው።

ለማጠቃለል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አንዳንዶች እንደሚያስቡት የድሮው ስርዓት ናፋቂ አይደሉም።ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔር አቀንቃኝም አይደሉም።የሁሉንም ሕመም በማዕከላዊነት እያስተናገዱ ነገር ግን ከአለፈው ስህተት የተማረች እና ዘመናዊ ትውልድ ተሻጋሪ መንግስት ያላት ሀገር መኖር ላይ ከሌሎች ጋር እየሰሩ እንደሆነ ብቻ ነው እስካሁን ያለው ሁኔታ የሚያሳየው።ነገም ከእዚህ የተለየ እንደማይሆን የእስካሁኑ መንገድ አመላካች ነው።ይልቅ ወገን የኢትዮጵያን መከራ አታርዝምባት።አንተ/አንቺ እንደግለሰብ እናንተ እንደ ቡድን ለኢትዮጵያ ምን እንስራ? አሁን ያለው መልካም ርዕይ ሁሉንም የሚጠቅም እንዲሆን ዋስትናውን ማረጋገጥ ላይ ለመስራት ዛሬ ለመጪው ትውልድ ለምን አሻራ እንጣል? ብሎ ማሰቡ የተሻለ ነው።ብዙ ንትርክ አሳለፍን።ስልጣን ያጣውም፣የሚፈልገውም እኩል እየዬ! የሚልባት ሀገር አናድርጋት።በሰለጠነ መልክ ሀሳብ መግለጥ፣መሞገት እንልመድ።ቀድመው የተፈጠሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በመጪው ዘመን የሚጠቅም ሥራ እያቀዱ ሲነግሩን ሰከን ብለን እንረዳው።በመንጋ አንነዳ።ጠቅላይ ሚኒስትሩም በእዚህ ሳምንት መጨረሻ ለሸገር ልማት በተዘጋጀ ራት ግብዣ ላይ -

''አቧራ ማስነሳት ቀላል ነው።አሻራ ማስቀመጥ ግን ሲጀመር ፈታኝ ሲፈፀም ደግሞ አስመስጋኝ ነው።ላሊበላ አሻራ ነው፣አክሱም አሻራ ነው፣ፋሲለደስ አሻራ ነው፣ የጀጎል ግንብ አሻራ ነው፣የአባ ጅፋር ቤተ መንግስት አሻራ ነው፣ጥላሁን ገሠሠ አሻራ ነው፣ አሊቢራ አሻራ ነው፣የአድዋ ድል አሻራ ነው።አሻራ አይጠፋም።አቧራ ግን ለጊዜው ይነሳል።ለጊዜው ያስነጥሰናል ትንሽ ቆይቶ ግን ይጠፋል።ኢትዮጵያ ከአባቶቻችን የወረስናት ብቻ ሳትሆን ከልጆቻችንም የተዋስናት ናት።'' ብለዋል።

አዎን! ይህ ተራ ሙገሳ አይደለም።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ቀድመው የተወለዱ መሪ ናቸው።ምክንያት - ቀድመው ያስባሉና።ከእዚህ በፊት ቀድመው የተወለዱ መሪዎቿን ያመከነች ምድር በእዚህ ትውልድ ዘመን የዓብይን ሃሳቦች የማምከን አቅም የላትም። ምክንያቱም ሀሳቦቹ የሚልዮኖች ሀሳቦች ናቸው።ጥቂቶች ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል።ይህም ሆኖ እናከብራቸዋለን።የምናከብራቸው ግን ከሥርዓት አልበኝነት ውጭ እስከተቃወሙ እና የሌላውን ሀሳብ እስካከበሩ ድረስ ነው።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ቀድሞ ለተፈጠረባችሁ እስኪ ፀባችሁን ከፈጠረው ጋር ሞክሩት።ጠቅላይ ሚኒስትሩ እራሱን አልፈጠረም።የፈጠረው በጊዜ ለክቶ ፈጥሮታል።የፈጠረው ደግሞ አልተሳሳተም።

የአዲስ አበባ የወንዝ ተፋሰስ ፕሮጀክት (ቪድዮ)

የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አስተባባሪ ከአርክቴክት መስከረም ታምሩ ጋር  ውይይት በፋና ቀለማት (ቪድዮ)ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ ታላቅ ተልዕኮ የሚኖረው ሀገራዊ የምምክር ኮሚሽን በተመለከተ ምን ያህል እናውቃለን?

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ኮሚሽን አማካሪ ኮሚቴ አባላትን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ባካተተ መልኩ አዋቅሯል። በእዚህ ጽሑፍ ስር የሚከተሉት ነጥቦች ምላሽ ያገኛሉ፡  ኮሚሽኑ እንዴት ተመሰረተ?  የኮሚሽኑ 11 ኮሚሽነሮች እንዴት ተመ...