===============
ጉዳያችን /Gudayachn
===============
ብሉምበርግ የተሰኘው የአሜሪካ ድረገፅ በፖለቲካ እና ፖሊሲ አምድ ስር የአድሚራል ጄምስ ስታርቪድስን አሜሪካ ኢትዮጵያን መውረር አለበት በሚል (በሰላም አስከባሪ ስም ነው የጠቀሱት) የፃፉትን በተመለከተ በብዙዎች ዘንድ እንደ ድንገት ደራሽ እያዩት ነው። ይህን እንደሚያደርጉ ሊብያን፣ሶርያን፣ዩጎዝላቭያን እና የመንን አየን።አሁን እኛ የማይሸነፍ ሃገር ህዝብ ነን እና ካለፉት የመማር እድልም ስላለን እራሳችንን አድነን አፍሪካን እንዴት እናድን? ነው ጥያቀው።ኢትዮጵያን በአድዋ ወረራ ጊዜ በ1928 ዓም ጣልያን ተመልሶ ሲመጣ ተመልሳ እንዳትነሳ ብትደረግ ኖሮ አፍሪካ ነጻ ባልወጣ።የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ባልተመሰረተ ነበር።አሁን አፍሪካን ሊበሏት ሲፈልጉ ካለፈው ትምህርት ወስደው ቅድምያ ኢትዮጵያን መምታት ነው ዕቅዱ።
እዚህ ላይ ሶስት ነጥቦችን ማስታወስ አለብን -
1) ያልጠበቅነው እና ከእዚህ በፊት በኢትዮጵያ ያልተሞከረ ድንገቴ ጉዳይ አይደለም።
ኢትዮጵያን ባዕዳን ሊወሯት እንደሚፈልጉ ከልጅነታችን አልሰማንም? ቀድሞስ ኢትዮጵያን ወርረው ለመቆጣጠር የሞከሩ ሀገሮች እንደነበሩ አላነበብንም? ሁሉንም የምናውቀው ነው።ዛሬ የአሜሪካ አድሚራል የፃፉት ውሸት ነው ብለን ማጣጣል ፈፅሞ የለብንም። ጦርነት የሚፈጠረው ሜዳ ላይ ሳይሆን አዕምሮ ላይ ነው። ሂትለር ዓለምን ከመውረሩ በፊት ወረራውን ያቀደው አዕምሮው ላይ ነው። አዕምሮው ላይ ያለውን ሃሳብ በአንድበቱ አውጥቶ ሌሎችን አማከረ ቀጥሎ ሰራዊት አሰልጥኖ ወደ ሥራ ቀየረው።
የአሜሪካው አድሚራል ጄምስ ስታርቪድስ በሃሳቡ ያለውን በፅሁፍ ላይ ሲያሰፍር ከማንም የአሜሪካ ባለስልጣን ጋር ሳይወያይ፣ሳያብላላ እና በመፃፉ የሚያመጣውን መዘዝ ሳያውቅ የፃፈው አይደለም።በእዚህ ደረጃ ላይ ያለ ሰው የፃፈው ድንገቴ አይደለም።ስለዚህ ቀድሞ መተንፈሱ እና የፍላጎታቸውን ልክ መተንፈሱ መልካም ነው።ስለሆነም የማናውቀው አልሆነም እና የመጀመርያው መጀመርያ አንደነግጥም! አንፈራም! ለሀገር የመጨረሻው ስጦታችን መሞት መሆኑን እያንዳንዱ ሰው በአዕምሮው ማስቀመጥ አለበት።አድሚራሉ በእዚህ ፅሁፉ ሞሶሎኒ፣ሞሶሎኒን ሸቶናል፣ገምቶናል።አሟሟቱም እንደ አድሚራል ወይንም እንደ ግራዚያ እንዲሆን መምረጥ የራሱ የአድምራሉ ነው።
2) ''ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው።አስቀድሞ ማለት አሾክሿኪውን ነው።''
ጠላት ኢትዮጵያን አይጥላትም።ሊያደማት፣ሊያንገላታት በጊዜያዊ ድል ሊፈነጥዝ ይችላል።ሆኖም ግን ፈፅሞ ጠላት አሸንፎን አያውቅም ወደፊትም አያሸንፈንም። እኛን የሚገዳደረን የውስጥ ባንዳ ነው።በጣልያን ወረራ ጊዜ የኢትዮጵያ አርበኞች ዋና ፈተና ባንዳ እንጂ ሰላቶ ፋሽሽት ጣልያን አልነበረም። አሁንም ቀድሞ ለጠላት መንገድ ጠራጊ ባንዳ እና አሾክሿኪ ነው።ኢትዮጵያ አሁን ከሽብርተኛው ህወሓት ጋር የገጠምነው ጦርነት ከአሾክሿኪው ጋር ነው።አሁን አሜሪካን ጋር ሆኖ እያሾከሾከ ኢትዮጵያን ከሸጣት ውስጥ አንዱ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ነው።ይህ ሰው በኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያን ለባዕዳን ከሸጣት ውስጥ ከቀንደኞቹ ውስጥ ሆኖ በመጪው ትውልድ የኢትዮጵያ ታሪክ መፅሐፍ ላይ ከእነ ፎቶው ተሰቅሎ ትውልድ ሲረግመው የሚኖር ሰው ነው።ዛሬ አድሚራሉ በኢትዮጵያ ላይ የድፍረት ቃል እንዲናገር መንገድ የጠረገው እና አብልታ አጠጥታ ያሳደገችው እናቱን ከባዕድ ጋር እየዶለተ ካራ ከሚስሉት ውስጥ ይህ ሰው አንዱ ነው።
ሆኖም ግን አሾክሿኪው ብርሃነ ገብረ ክርስቶስ ብቻ አይደለም።ዛሬ ኢትዮጵያውያንን በጎሳ ለመከፋፈል ከሚድያ እስከ መሳርያ አንስተው እየወጉ ያሉ ሁሉ በባንዳነት ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሱ ናቸው።እነኝህን ሁሉ በማስተባበር ኢትዮጵያን ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ያህል ያቆሰላት፣የከፋፈላት እና የባዕዳን ፈረስ የሆነው ህወሓት ነው።የባዕዳንን ፈረስ ሳይመቱ ባዕዳንን መምታት አይቻልም።ስለሆነም አሁን ኢትዮጵያ የገጠማት የጠላት ጥያቄ ፋሽሽት የጠየቀው ነገ አሜሪካ ኢትዮጵያን ለመውረር እመጣለሁ የሚለው ጥያቄ አንድ ነው።ስለሆነም ''ጠላትማ ምን ጊዜም ጠላት ነው። አስቀድሞ ማለት አሾክሿኪውን ነው።''
3) ሃገር ወዳድ የነቁ እና የሰሉ አነቃቂዎች በመላዋ ኢትዮጵያ ማሰማራት
አነቃቂዎች በኢትዮጵያ የጥንት ታሪክ ውስጥ አሸናፊ እንድትሆን ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።አንዳንዶች የማኅበራዊ ሚድያ ከመጣ ወዲህ አንቂዎች የተፈጠሩ አድርገው ያስባሉ።ሆኖም ግን ኢትዮጵያ ከባእዳን ጋር ያደረገችው ጦርነት በአሸናፊነት እንድትወጣ ካደረጉት ውስጥ አነቃቂዎች ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል።አዝማሪ በግጥም እና በዜማ፣እረኛው በዋሽንት፣ባለቅኔው በቅኔ፣ሸሁ በስብከት፣ካህኑ በምክር፣ፎካሪው በፉከራ ሁሉም ኢትዮጵያ ጠላት ሲገጥማት ለሕዝቡ የሞራል ልዕልና ስንቅ ያስታተቁ ናቸው።ሰው በተፈጥሮው ስሜቱ እንደጊዜው ይቀያየራል።አነቃቂዎች ግን ይህን ሁሉ ጠብቀው የሀገር ፍቅር ስሜቱን ያንሩታል፣የነቁታል፣ከመከራ በኃላ ያለውን መልካም ጊዜ በተስፋ ያሳዩታል፣ሞት ምንም አለመሆኑን እና ክብሩን ያመለክቱታል።
ስለሆነም ዛሬም ኢትዮጵያ አንቂዎች፣በገበያ ላይ፣በከተሞች አደባባይ ላይ የሚናገሩ፣በየቤቱ እየሄዱ የሚያስረዱ ሰዎች ያስፈልጋሉ።በወታደራዊው መንግስት ዘመን የህዝብ አንቂዎች ካድሬ በሚል ስም ተሰጥቷቸው የኢትዮጵያ የነበረው ባህል ተረሳ።አሁን ግን እንደ አዲስ ማነቃቃት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብን 79% ያህል የገጠር ነዋሪ ነው። ይህ ሕዝብ ስንቱ ራድዮ እና ቴሌቭዥን ወይንም ስልክ ይጠቀማል? ደግሞስ አንቂ በራድዮ ከሚሰማ ይልቅ በአካል የሚያቀርበው የበለጠ ኃይል አለው።ይህ ማለት ዘመናዊ መገናኛ መጠቀም አያስፈልግም ማለት አይደለም። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ከተሞች ባልተስፋፉባት ሀገር የህዝብ አንቂዎች አደባባይ መውጣት አስፈላጊ ነው። እኛ የአደባባይ አንቂነቱን ከስልጣኔ ጋር አገናኝተን ተውነው እንጂ እንደ እንግሊዝ ያሉ ሀገሮች ከተሞቻቸው መናፈሻ ቦታ ላይ ማንም ሰው ንግግር የሚያደርግባቸው ክፍት መድረኮች ሁሌ አሉ።በእዚህም ብዙ ዕውቀት አሁን ድረስ ይገበይበታል። ይህ ህዝብን ማንቃት ከጥንት የግሪክ ዘመን ጀምሮ እነ አርስቶትልን፣በዘመናዊው ዘመን ደግሞ እንደ እነ በርናንድ ሾውን የመሰሉ ተናጋሪዎች አፍርቷል።
ሕዝብ ያወቀ ቢመስለንም ያላወቀ፣በልዩ ልዩ ወሬ ግራ የተጋባ ወይንም በደካማ የምኞት መናወዝ ለሀገሩ ከመቆም ሊዘናጋ ይችላል።በእዚህ ጊዜ አነቃቂዎች የሚነግሩት ያፀናዋል።ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ከዘማቹ ጋር በታዳጊ ወጣትነታቸው ደራሲ አዲስ ዓለማየሁ ጣልያን ከመግባቱ በፊት ከወዳጆቻቸው ጋር ሕዝቡን ለማንቃት ኃላፊነት የወሰዱት በእየገበያው እየዞሩ ህዝቡ ለጦርነት እንዲዘጋጅ በማድረግ ነበር። በእዚህም ብዙ ሕዝብ ቆርጦ እንዲገባ ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።የህዝብ አንቂዎች ለጦርነት ብቻ አይደለም። ሰላም መጥቶ ሕዝብ ወደ ልማት ሲዞር የልማት ስራውን ተረድቶት እና ወዶት እንዲሰራ መቀስቀስ ይፈልጋል።እዚህ ላይ በቀላሉ ሕዝብ በመገናኛ በመንገር ሊረዳው ይችላል ተብሎ ሊታሰ ይችላል።ነገር ግን እንዲህ በብዙ ማማለል ሁሉ በማታለል ሀገር ለመውረር የሚፈልግ እንደ አሜሪካ ያለ ሀገር በተመለከተ ነገሩን ከስር የማስረዳት እና የቆረጠ ሕዝብ ዝግጅት ይፈልጋል።
ባጠቃላይ ይህ ትውልድ ልደናገጥ አይገባውም።ይልቁንም ሞትም ቢመጣ ዕድለኛ ትውልድ እንደሆነ ማሰብ አለበት።ኢትዮጵያን በደማቸው አስከብረው ለእኛ ያስተላለፉት የአባቶቻችን ዕድል እኔ ደረሰኝ።ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ኃላፊነቱ ከአምላክ ተሰጠኝ ብሎ በሃዘን ሳይሆን በደስታ፣በማማረር ሳይሆን በሀገሩ ውድነት እና ብርቅነት ምክንያት አባቶቻችን የገጠማቸው ጠላት ዛሬም እጃችን ላይ ልጥልልን እንደመጣ ማሰብ አለብን።ዛሬ ኢትዮጵያውያን አቅማችንን አናስተውለውም እንጂ ግዙፍ ነን።በመላው ሀገር ያለው ስርጭታችን፣የተማረ የሰው ኃይል፣እምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ከሁሉም ጋር ኢትዮጵያን ስጠብቅ የነበረ ወደፊትም የሚጠብቅ የአባቶቻችን አምላክ ከእኛ ጋር ለዘላለም አለ።ተወረርን እንጂ አልወረርንም።መጡብን እንጂ አልመጣንባቸውም። ይህ ብቻ በራሱ ለሀገራችን ለመሞት በሞራል ልዕልና እና በአሸናፊነት መንፈስ እንድንነሳ የሚያደርግ ታላቅ ስንቅ ነው።
====================///==============
No comments:
Post a Comment