ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Tuesday, November 30, 2021

የጠ/ሚ/ር ዓቢይ ጦሩን ለመምራት ወደ ግንባር መውረዳቸው በራሱ የሚያሳየው የመንግስታቸውን መረጋጋት እና ጥንካሬም ብቻ ሳይሆን ብቃታቸውን፣ድፍረታቸውን እና ትህትናቸውንም ጭምር ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ ሰራዊቱ በቀጣዩ ቀን የሚቆጣጠራትን ጋሸናን ከርቀት እያመለከቱ 
ኅዳር 21/2014 ዓም  

===============
ጉዳያችን / Gudayachn
===============

ማመስገን እና ማድነቅ በእኛ ባህል ''ሙያ በልብ ነው'' የሚለው አባባል እየያዘን ይሁን ወይንም መልካም የሰራ ሲመሰገን አይናቸው የሚቀላው እያሸማቀቁን በዓይናችን መልካም የሰራን እያየን እና ልባችን እያደነቀ ከአንደበታችን አውጥቶ ማድነቅ እና ማመስገን ይተናነቀናል ወይንም ዝም ማለት ልማድ አድርገነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ የመምራት አቅማቸው፣ብቃታቸው፣ድፍረታቸውእና ትሕትናቸው ሁሉ ኢትዮጵያን ወደ ውጤት እንደሚመሯት ያለፉት አራት ዓመታት በትክክል አመላካቾች ናቸው።ስለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ብዙ ስለተባለ ከእዚህ በፊት ወደተባሉት ጉዳዮች አልገባም።ነገር ግን ከሰሞኑ የሽብርተኛው ህወሓት ላይ ለሚወሰደው እርምጃ አመራር ለመስጠት ወደ ግንባር በወረዱበት ጉዳይ እና አመላካች ነጥቦቹ ላይ ብቻ አተኩራለሁ።የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደግንባር መውረድአሁን ባለንበት ዓለም በተለይ በአፍሪካ ያልተለመደ ነው። በእርግጥ በኢትዮጵያ በታሪካችን ነገስታቶቿ እና መሪዎቿ ኢትዮጵያ በሚገጥማት ጦርነት ሁሉ አብረው ከሰራዊታቸው ጋር ይዘምቱ ነበር።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከቤተመንግስት ስርዓት ጀምሮ የኢትዮጵያ የሆነው ዋጋ እንዲያገኝ ሲጥሩ በብዙ መልክ ታይተዋል።ከቤተ መንግስት እድሳት ኢትዮጵያ እንግዶች ስትቀበል የምታነጥፈው ምንጣፍ ቢጫ መሆን ድረስ ብዙ ተግባራትን ኢትዮጵያዊ ለማድረግ ያሳዩትን ጥረት እና ተግባር በቀላሉ መመልከት ይቻላል።

የጠ/ሚ/ር ዓቢይ ጦሩን ለመምራት ወደ ግንባር መውረዳቸው በራሱ የሚያሳየው የመንግስታቸውን መረጋጋት እና ጥንካሬም ብቻ ሳይሆን ብቃታቸውን፣ድፍረታቸውን እና ትህትናቸውንም ጭምር ነው።ነጥብ በነጥብ እንመልከተው።

የመንግስታቸው መረጋጋት 

የተረጋጋ መንግስት በውስጡ ያለው እና ስጋት የሌለበት መንግስት መሪ ነው ከቤተመንግሥቱ ወጥቶ ለቀናት ምናልባትም ለሳምንታት ወደ ዘመቻ የሚሄደው።የአፍሪካ መሪዎች ቤተመንግስታቸውን አይደለም ወደ ውጭ ሀገር ለጉብኝት ወይንም ለስብሰባ ደርሰው እስኪመጡ ስልጣናቸውን አያምኑትም።በውስጡ የተረጋጋ እና ጠላት ሲያወራ እንደከረመው ከውስጥ ከሃሳብ ክርክር ያለፈ በምርጫ ወደ ስልጣን የመጣ መንግስትን ለመገዳደር የሚያስብ አለመኖሩን እርግጠኛ ናቸው።ይህ ጉዳይ ለብዙ የውጭ መንግሥታት ግልጥ ነው። የአሜሪካ ኤምባሲ እንደ ጧት ቁርስ 'በኢትዮጵያ ስጋት አለ' የሚል ፅሁፍ ሲፅፍ ቢውልም ነገሩ የተገላቢጦሽ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ሄደው የጦር አመራሩ ላይ ብቻ ማትኮራቸው አሁንም የሚያሳየው በውስጥ የመንግስታቸው መረጋጋትን እና በጣም የሚያምኗቸው እና የሚታዘዙላቸው ባለስልጣናት መኖራቸውን የሚያመላክት ነው።

 
ጥንካሬ፣ብቃት እና ድፍረት 

ከመሪ ከሚጠበቁት ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥ ጥንካሬ፣ብቃት እና ድፍረት ተጠቃሾች ናቸው።ጥንካሬ በመንግስታቸው ላይ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ለመጣው ግፊት እና ማዋከብ ሳይረበሹ ስራቸው ላይ አትቁረዋል።ብቃት ለመጡት ግፊቶች በብቃት ምላሽ ሰጥተዋል።ድፍረት በተመለከተ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ ሕብረት ከሚድያ እስከ ልዑካን እየላኩ ማስፈራራት እና የግል ገዳይ እስከመቅጠር ድረስ ለተደረገው ሙከራ ካለአንዳች መርበትበት ወደ ዋናው ኢትዮጵያን ወደማቆም ሥራ ላይ አትኩረዋል።እዚህ ላይ አንድ የብቃት ጉዳይ ማንሳት ተገቢ ነው።የውጭ መንግሥታትም ሆኑ የውስጥ ባንዳዎች አንዱ ጥረታቸው መረጃ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ነው። ከእዚህ አንፃር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ ዋዜማ ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሚኒስትሮች የሰጡትን ማብራርያ ለሕዝብ ተላልፎ ነበር።

በእዚህ መግለጫ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳችም በሚቀጥለው ቀን አዋጅ እንደሚወጣ የሚያሳይ ምልክት ከገለጣቸው ለመረዳት አይቻልም ነበር። ይልቁንም በጉርድ ጥቁር ሸሚዝ ለብሰው በሰጡት መግለጫ ከቃላት እስከ የሰውነት እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት አዋጅ እንደሚወጣ የሚጠቁም ጉዳይ የለውም።ይህ በጠላት ላይ በድንገት ለመድረስ አመችቷል።በደሴ የተሰራው ሸፍጥ በአዲስ አበባ እንዳይደገም የአዋጁ በድንገት መውጣት የራሱ ፋይዳ ነበረው።ይህ ብቃት ነው።በተለይ ታዳጊ ሀገሮች ብቻ ሳይሆን የዓለምን መንግሥታት ያሰቡትን ቀድመን እናውቃለን የሚሉት የሃያላኑ ደህንነት ሊያውቁት ባልቻሉት መንገድ ነው አዋጁ የወጣው። የመንግስት ብቃት አንዱ መገለጫ የሚሰራውን ቀድሞ የማይነዛ ግን የሚሰራ መሆኑ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደፋርነት በብዙ መልኩ ሊገለጥ ይችላል።በምድር ላይ ያለ ማንም መንግስት በኢትዮጵያ ጥቅም እስከመጣ አልደራደርም ማለት በራሱ የደፋርነት ብቃት ማሳያ ነው።አሜሪካ በእግሯ እና በጥፍሯ በኢትዮጵያ ላይ ዘምታለች።ከሚድያ እስከ የኢኮኖሚ እቀባ፣ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አፍሪካን መዞር እስከ የጅቡቲ ጦሯ ለማስፈራራት ሞክራለች።ይህንን ሁሉ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና መንግስታቸው ለመቋቋም ያሳዩት ፅናት ሁሉም የተመለከተው ነው።

ትሕትናቸው 

ድፍረት፣ብቃት እና ጥንካሬ በራሳቸው ትሕትና ካልተላበሱ በሰውም በፈጣሪም ማስወቀሳቸው አይቀርም።የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም አመራር የሚታይበት አንዱ ገፅታ በትዕቢት የታሸ አለመሆኑ ነው።አንዳንድ ሰዎች መሪ ከድሆች ጋር ስቅመጥ፣ እራሱን ዝቅ አድርጎ ከተራ ዜጎች ጋር ሲያወራ፣ አጎንብሶ ችግኝ ሲተክል ወይንም ችግኝ ሲያጠጣ ለታይታ አድርገው ያስባሉ።ይህ ግን ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት የነበረባት ስብራት ምን ያህል ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ስለማይረዱት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሕዝብ በቴሌቭዥን ማየቱ አሁን ያሉት ሕፃናት፣ታዳጊዎች እና ወጣቶች እንዲሁም አዋቂዎች ሁሉ በአካባቢያቸው ማድረግ ያለባቸውን እየነገሩ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ስንት ወጣት እና ሕፃናት ነገ ይህንን ለማድረግ አስበው እንደሚያድሩ የሚረዳው ጥቂት ነው።የድሆች ቤቶች እያፈረሱ በአዲስ እንዲሰራ ሲያስጀምሩ ስንት ባለ ሚልዮነር ሃብታም እራሱን እንዲወቅስ እና በያለበት ያሉ ድሆችን መርዳት እንዳለበት አስቦ እንዲያድር እንደሚያደርግ የሚዘነጋ ብዙ ነው። እነኝህ ሁሉ የትህትና መገለጫዎች ናቸው። አንድ ወቅት በፓርላማ ገለጣቸው  ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ''ክብራችንን ከምንሸጥ ዝቅ ብለን ስልጣን ትተን ወደምናውቀው የመደብ መኝታ የመውረድ ችግር የለብንም'' ማለታቸውን ማስታወስ ተገቢ ነው።አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ግንባር ሄደው የሚመሩት ውግያም በራሱ የጀግንነት መገለጫ ብቻ ሳይሆን የትሕትናም ማሳያ ነው።ከሰራዊቱ ጋር አብሮ መሬት እየተኙ፣የበላውን እየበሉ፣የጠጣውን እየጠጡ አብሮ ዝቅ ብሎ መስራት የትሕትና መገለጫ ነው።

ለማጠቃለል የጠ/ሚ/ር ዓቢይ ጦሩን ለመምራት ወደ ግንባር መውረዳቸው በራሱ የሚያሳየው የመንግስታቸውን መረጋጋት እና ጥንካሬም ብቻ ሳይሆን ብቃታቸውን፣ድፍረታቸውን እና ትህትናቸውንም ጭምር ነው።ከመጀመርያው ጀምሮ ሽብርተኛው ህወሓት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ  ከታች ከጠጅቤት እስከ ሸራተን ኦፊስ ባር እና በማኅበራዊ ሚድያ ሁሉ ወኪሎቹን እየላከ  የከፈተው የውሸት ዘመቻ እጅግ ጥቂቶች ዛሬም ላይ ይዘው ለመንገታገት ቢሞክሩም ዕውነታው ግን በጊዜ ሂደት እየገለጠ መጥቷል።''እውነት እና ንጋት እያደር ይጠራል'' እንዲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያሳዩት ትጋት በራሱ በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአፍርካውያንም ጭምር ታላቅ አክብሮትን አትርፈዋል።አፍሪካውያን የኢትዮጵያ ዓይነት መሪ ቢኖረን ኖሮ ሀገራችን በአሸባሪ አትሰቃይም ነበር የሚሉ የአፍሪካ ጋዜጦች ከወደ ምዕራብ አፍሪካ እየተነበቡ ነው።አመራሩ ግሩም ነው።ትጋቱ እና ኢትዮጵያን የመውደዱ ልክ ደግሞ ድንቅ ነው።

=========///========


No comments: