Saturday, October 19, 2019

በኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ዙርያ አዲስ ዜና - በኦስሎ፣ኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ''በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ'' አሰባሳቢነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የኖቤል ሽልማት ዙርያ ከአቀባበል እስከመስተንግዶ ባለው ዝግጅት ዙርያ ተወያዩ (Gudayachn Exclusive)


በስብሰባው ላይ ከተሳተፉ የኦስሎ ኖርዌይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በከፊል 

ጉዳያችን / Gudayachn 
ጥቅምት 8/2012 ዓም (ኦክቶበር 19/2019 ዓም)

የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ  

የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ያደረጉትን ንግግር በሙሉ የያዘ መፅሐፍ በተለያዩ ጥራዞች ''ፍሬ ከናፍር'' በሚል ስም ይታወቃል።መፅሐፉ ንጉሡ በእያንዳንዱ በዓል፣የውጭ እንግዳ ሲቀበሉ እና በእራት ግብዣ ላይ ሁሉ ያደርጉት ንግግር በሚገባ በቀን፣በወር እና በዓመት ተለይቶ የተፃፈ መፅሐፍ ነው።መፅሐፉን በገበያ ላይ ባያገኙት በእርግጠኝነት አዲስ አበባ ከኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ዋና መስርያ ቤት ጀርባ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቤተ መዘክር (ወመዘክር) መፅሐፍት ቤት ጎራ ብሉ አያጡትም።በእዚህ መፅሐፍ ላይ በእያንዳንዱ ዓመት  ኢጣልያ ከኢትዮጵያ ከተባረረች ጊዜ ጀምሮ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ወደ ውጪ አገር ለትምህርት ሲሄዱ በቅድምያ ንጉሰ ነገሥቱን ቤተ መንግስት ሄደው አግኝተው መሰናበት እና ምክር ለመቀበል ሲሄዱ ለተማሪዎቹ ያደረጉት ንግግር የመፅሐፉ አንዱ አካል ነው።በእዚህ ጊዜ ንጉሡ የሚያደርጉት ንግግር ላይ ለትምህርት የሚሄዱ ተማሪዎችን የሚሉት አንድ የተለመደ ዓረፍተ ነገር አለ። ይሄውም የወጣቶቹ ወደ ውጪ መሄድ የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ መሆኑን ንጉሡ ደጋግመው የሚጠቀሙበት አነጋገር ነው። ወጣቶቹ በውጭ አገር በሚቆዩበት ጊዜ ሁሉ እና በኃላ መስራት ያለባቸው ሁሉ የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ መሆኑን አበክረው የተናገሩበት ንግግር በተደጋጋሚ ይገኛል።የንጉሡ ምክርም ይሄው የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ በሚል ዓረፍተ ነገር የተሞላ ነው።ዛሬ በኦስሎ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ያደርጉት ስብሰባም የሚያስታውሰው የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ በሚል ሃሳብ ዙርያ ነው።

የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ - በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የዛሬው የኦስሎ ስብሰባ  

ዛሬ ጥቅምት 8/2012 ዓም  የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያውያን ታሕሳስ 10/2019 ዓም እኤአ ኦስሎ፣ኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በተገኙበት የሚሰጠው የኖቤል ሽልማት መርሐግብር ላይ የኢትዮጵያውያን ሚና ምን መሆን አለበት በሚል ሃሳብ ዙርያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በኖርዌይ (ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ) ሰብሳቢ አቶ ፍቅሩ፣ከኤርትራ ማኅበረሰብ እና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የተገኙ ሲሆን በመርሐግብሩ መጀመርያ ላይ አቶ ጌታቸው በቀለ የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ሰብሳቢ የኖቤል ሽልማቱ ከኢትዮጵያን አልፎ አፍሪካውያን የፈጠረው ልዩ ስሜት ከደቡብ አፍሪካ እስከ ምዕራብ አፍሪካ ያሉ የመገናኛ ብዙኃን በርካታ ዘገባዎች እያቀረቡ መሆኑን፣ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከኖቤል ሽልማቱ  በፊት በጉግል ፍለጋ የነበረው ቁጥር በአማካይ ወደ ሰላሳ አራት ሚልዮን የነበረ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ  ባለፈው ሳምንት የኖቤል ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው ከተገለጠ በኃላ ቁጥሩ በአስር እጥፍ አድጎ ወደ ሶስት መቶ አርባ ሚልዮን  ማሻቀቡ ኢትዮጵያን በምን ያህል ደረጃ በመላው ዓለም በበጎ ጎኑ እንዳስጠራት ለማወቅ እንደሚቻል ገልጧል። 

በመቀጠል የኖቤል ሽልማት ምንነት እና በኖርዌይ የምንኖር ኢትዮጵያውያን የሚጠበቁብን ስራዎች በተመለከተ ማብራርያ የሰጡት  አቶ ለማ  ናቸው። አቶ ለማ በንግግራቸው መግቢያ ላይ ሽልማቱ የፈጠረው ደስታ ታላቅ መሆኑን አውስተው፣ይህንን ታላቅ ዕድል በሚገባ በመጠቀም የኢትዮጵያን ስም ከፍ ማድረግ እንደሚቻል አብራርተዋል።በተጨማሪም የሽልማቱ ምክንያት ከኤርትራ ጋር በተፈጠረው ሰላም ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ  በአገር ውስጥ በሰሩት መልካም ተግባር መሆኑን ካብራሩ በኃላ የኖቤል ሽልማት የሚሰጠው ድርጅት ኖቤል ኢንስቲትዩት እንደሚባል እና  የተሸላሚዎችን ታሪክ በመላው ዓለም የማስተዋወቅ ሥራ በመስራት የሕዝብ ግንኙነት ሥራ የሚሰራው  ''ኖቤል ሴንተር'' የሚሰኝ  መሆኑን አብራርተዋል።

ከስብሰባው ተሳታፊዎች በከፊል 

ከእዚህ በተጨማሪ አቶ ለማ በሶስቱ ቀናት የሚኖሩትን መርሃግብሮች በተመለከተ የሚኖሩ ክንውኖችን ከመርሐግብሩ አንፃር ሲያብራሩ፣ ታህሳስ  9/2019 ዓም ጋዜጣዊ መግለጫ ኦስሎ ላይ እንደሚሰጥ፣ በቀጣዩ ቀን ታህሳስ 10/2019 ዓም  ሽልማቱ የሚሰጥበት ቀን ሲሆን በእዚሁ እለት ምሽት ላይ በሁሉም የኖቤል ሽልማቶች ላይ እንደሚደረገው በርካታ የኖርዌይ ድርጅቶች በሕብረት  የሚያዘጋጁት በብዙ ሺህ የሚቆጠር የኖርወያውያን፣የውጭ ዜጎች እና ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የጧፍ ማብራት ሰላማዊ ሰልፍ ከማዕከላዊ ኦስሎ በተለምዶ ''ነብሩ'' ተብሎ ከሚጠራው ቦታ እስከ ግራንድ ሆቴል ድረስ እንደሚኖር እና ግራንድ ሆቴል ሰገነት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከኖርዌይ ንጉሳውያን ቤተሰብ ጋር ብቅ ብለው  ለተሰላፊዎች የክብር ሰላምታ እንደሚሰጡ ገልጠዋል። በቀጣዩ ቀን ከእዚህ በፊት የተሸለሙ መሪዎች እንደሚያደርጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ  ከኖርዌይ ባለስልጣናት ጋር ኦፊሻል ውይይት የሚያደርጉበት ቀን ሊሆን እንደሚችል ይህ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚኖራቸው መርሐግብር ጋር አብሮ የሚሄድ መሆኑን ገልጠዋል። ከእዚህ በተጨማሪ የኖቤል ሽልማት እንደተደረገ ዓመቱን ሙሉ ልዩ ኤግዚቢሽን ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ገልጠው በመጨረሻም አቶ ለማ የአቀባበሉ ስነ ስርዓት ሁሉን በእኩልነት ያሳተፈ እንዲሆን፣ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ያለበት፣ሰንደቅ ዓላማ በተመለከተ ኦፊሻል መንገድ መጠቀም እና የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በማዕከልነት ማስተባበሩ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በመቀጠል የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሩ ይህንን ስብሰባ ያዘጋጀው የኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክን  አመስግነው፣የኖቤል ሽልማቱ የተሰጠበት ቀን ኮሚኒቲው ምሽቱን ጥሪ አድርጎ ደስታውን በአንድነት መግለጡን  እና በዕለቱ ከኖርዌይ ቴሌቭዥን ዘጋቢዎች መገኘታቸውን ገልጠዋል።ከእዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኮምኒቲ  የኖቤል ሽልማት ዝግጅት በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ለማግኘት ጥረት ማድረጉን እና ኤምባሲውም በራሱ መረጃ እየጠበቀ መሆኑን እንደገለጠ አስታውቀዋል።ከእዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ የምንም እና ማንም የፖለቲካ ድርጅት አቀንቃኝ አለመሆኑን አፅንኦ ሰጥተው አሁንም ከሁሉም ስብስቦች ጋር  ለመገናኘት እየሞከረ መሆኑን ገልጠዋል።

ስብሰባው በተከታይ በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው በቀለ አወያይነት ተሰብሳቢዎቹ በኖቤል ሽልማቱ ስነ ስርዓት ሰሞን በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሚና እና የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በማገዝ ሊሰሩ የሚገባቸው ስራዎች ዙርያ  ተሰብሳቢዎቹ ሃሳብ ሰጥተዋል። ከተሳታፊዎች ከተሰጡት ሃሳቦች ውስጥ -

'' እኔ በሕይወቴ ያላየሁት ጉዳይ ነው ያየሁት'' አሉ አንድ እናት ስለ ኖቤል ሽልማቱ ሲናገሩ በመቀጠል '' ዜናው ሲነገር ነጮቹ ድንገት መጥተው  ከበቡኝ እየሳሙ 'ግራቱለረ' የምስራች! አሉኝ።ቀኑን ሙሉ ስሳም የዋልኩት፣ልጄ ድንገት ደውሎ 'ግራቱለሬ' ማሚ ብሎ ደስታው ሲቃ እየተናነቀው አናገረኝ።ትምህርት ቤቱ ተማሪው ሁሉ ከቦት ደስታውን እየገለጡለት እንደሆነ  ነገረኝ።ይህ ብቻ አይደለም።የትምህርት ቤቱ የክፍል ልጆች ጋር ተሰብስበው በዓል አደረጉ።ይህ ጉዳይ በልጆቻችን ላይ የፈጠረው የሞራል ልዕልና  በቃላት የምገልጠው አይደለም።እባካችሁ ልጆቻችን የኢትዮጵያን መከራ ስናወራ ሲሰሙ ነው ያደጉት። ቢያንስ ደስታ እስኪ የሚሰሙበት ጊዜ እንዲሆን ይህንን የኖቤል ሽልማት አስመልክቶ አንድ አይነት  ትልቅ ዝግጅት ማዘጋጀት አለብን።ይህንን ዝግጅት ላይ ለመገኘት የኖርዌይ ተወላጆች ሁሉ እየጠየቁ ነው እና ይህ ጉዳይ  ሊታሰብበት ይገባል'' ብለዋል።

ሌላ እናት ቀጠሉ '' የሽልማቱ ቀን በርካታ ቴክስት ከኖርዌይ ተወላጆች ደረሰኝ።ብዙዎቹ የጉዲፈቻ ኢትዮጵያውያንን ያሳደጉ ናቸው። ሁሉም የሚያሳድጉዋቸው ልጆች ይህንን ደስታ የሚያሳዩበት አንድ አይነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበት  የጋራ ደስታ መግለጫ በዓል እንዲዘጋጅ እና በእዚህ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ቃል ገብተዋል። ስለሆነም እባካችሁ ከእኛ ይልቅ ልጆቻችን የሚኮሩበት እና በአገራቸው የሚኮሩበት መልካም ዕድል እንፍጠር'' ብለዋል።


ስብሰባው በመቀጠል ከኤርትራ ማኅበረሰብ የመጡ አቶ ንጉሡ አስተያየት የሰጡ ሲሆን በአስተያየታቸው ''እኔ አሁን ኤርትራ ቀድሞ የኢትዮጵያ ክፍለ አገር የመጣሁ የዓቢይ ወጤት ደጋፊ ነኝ።አብረናችሁ ነን።ኢትዮጵያ እና ኤርትራ አንድ ሕዝብ ነን በእዚህ  ዝግጅት ላይም አብረናችሁ ነን'' ብለዋል።

በመጨረሻም  ስብሰባው ከመጠናቃቁ በፊትበሚከተሉት ነጥቦች ላይ የጋራ መግባባት ተደርሶበት  ስብሰባው ተፈፅሟል። እነኝህ በጋራ መግባባት የተደረሰባቸው ነጥቦች -

 • የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ቀድም ብሎም እንደገለጠው ከኖቤል ሽልማቱ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ወደ ኦስሎ ሲመጡ ለሚኖረው የክብር አቀባበል፣እስከ የሚመለሱበት ጊዜ ያለው ዝግጅት ዙርያ የሚያስተባብር አንድ ግብረ ኃይል  በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እንዲመሰረት እና ወደ ሥራ እንዲገባ፣ይህ ኮሚቴ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን፣
 • የኢትዮጵያ ኤምባሲ (ስዊድን ፣ስቶኮልም የሚገኘው) ከኢትዮጵያ ኮሚንቲ ጋር አብሮ እንዲሰራ እና ዝግጅቱ ውበት ያለው እንዲሆን መስራት እንዲጀመር፣
 • ኢትዮጵያን ባላቸው የግልም ሆነ የቡድን ግንኙነት (ኔትዎርክ) የኖቤል ሽልማቱ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስም የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን በኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን  ይህንን ታሪካዊ እና አገራዊ ፋይዳ ያለው ዝግጅት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት  እና በባለቤትነት እንዲያስተናግዱ እና  አስፈላጊውን ጥሪ ከኮምንቲ እንዲጠብቁ፣
 • አንድ ልዩ የደስታ መግለጫ መርሃግብር ሁሉንም ኢትዮጵያውያን፣አፍሪቃውያን እና የኖርዌይ ተወላጆች የሚያሳትፍ ዝግጅት እንዲኖር  በእዚህ ዝግጅት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሚገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይም  ኢትዮጵያውያንን የሚያገኙበት መልካም አጋጣሚ እንዲፈጠር የሚሉት ዋና ዋና ነጥቦች ነበሩ።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ በተሰጡት ሃሳቦች ዙርያ አስተያየት ከሰጠ በኃላ በስብሰባው መደሰቱን እና በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶች  መገኘታቸው እና አሁንም በዝግጅቱ ማማር ዙርያ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አብረው እንዲሰሩ እና በተቀናጀ መልክ  ለመስራት እና የኢትዮጵያን ስም ከፍ ለማድረግ ለመስራት ጥሪ አቅርቦ የዕለቱ ስብሰባ ተፈፅሟል። 


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

የ“መደመር” መፅሐፍ ምርቃት ስነ ስርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር

ጉዳያችን / Gudayachn

ጥቅምት 8/2012 ዓም (ኦክቶበር 19/2019 ዓም)
=======================
Today's Historical speech of Ethiopian prime minister Abiy Ahmed (PhD) on the launch of his new book ''MEDEMER". The 280-page book examines and outlines the economic, political and foreign policy directions of Ethiopia. 
Source = EBC


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Friday, October 18, 2019

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የኖቤል ሽልማቱ የኢትዮጵያን ስዕል በመላው ዓለም ቀይሮታል። አፍሪካ ስትፈልገው የነበረው መሪ ይህ ነው።የደቡብ አፍሪካ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን Africa should celebrate Abiy Ahmed for winning the Nobel Peace Prize:

ጉዳያችን / Gudayachn
አፍሪካ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የኖቤል ሽልማት  እጅግ መደሰት አለባት።አፍሪካ ስትፈልገው የነበረው መሪ ነው።ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት ፖለቲካ ተከተሉ፣ ከየትኛውም ጎሳ መጡ በእዚህ ሽልማት መደሰት አለባቸው።ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ሽልማት አይደለም።ይህ ለአፍሪካም የተሰጠ ነው።የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማቱ የኢትዮጵያን ስዕል በመላው ዓለም ቀይሮታል። የደቡብ አፍሪካ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን 
Africa should be proud. This is the leader that we Africans are looking for.
Source =SABC


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Monday, October 14, 2019

ቆይታ ከሙሐዘ ጥበባት ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ጋር ክፍል 1

ማን ምን አለ?
ኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥን (ኢሳት)
ጥቅምት/2012 ዓም 


ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Friday, October 11, 2019

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የኖቤል ሽልማት ማግኘታቸው ለአፍሪካ ያለውን አንደምታ ዋናው የደቡብ አፍሪቃው ብሮድካስት ቴሌቭዥን በሚገባ ተንትኖታል (ቪድዮ)

በቅድምያ ጉዳያችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከመላው ዓለም የኖቤል ሰላም  የ2019 ዓም እኤአ አሸናፊ በመሆናቸው ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያው ወዳጆች በሙሉ እንኳን ደስ አለን! ለማለት ትወዳለች።

Source = SABC (South African Broadcasting Corporation)


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Wednesday, October 9, 2019

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በተመለከተ በኦስሎ፣ኖርዌይ ቅዳሜ ታላቅ ሕዝባዊ ስብሰባ ተጠርቷል።

ጉዳያችን / Gudayachn 
መስከረም 28/2012 ዓም (ኦክቶበር 9/2019 ዓም)
+++++++++++++++++++ 
በጉባኤው ላይ መሳተፍ በርቀት ከመቆጨት ያለፈ አንድ እርምጃ ነው።
 • በኦስሎ የሚገኙ ሁለቱም አጥብያዎች ካህናት እና ምእመናን በአንድነት በስብሰባው ላይ ይሳተፋሉ።
 • ከኦስሎ ውጪ  ለሚገኙ አጥብያዎች  ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሙሉ እንዲያውቁት መልዕክት ደርሷል።
 • ከኦስሎ ውጪ የሚመጡ ተሳታፊዎች ይኖራሉ።
በመጪው ቅዳሜ ጥቅምት 1/2012 ዓም (ኦክቶበር 12/2019 ዓም)  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የሰሜን አውሮፓ አህጉረ ስብከት የኦስሎ፣ኖርዌይ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ ገብርኤል ወአቡነ ተክለ ኃያማኖት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ሰበካ ጉባኤ አስተባባሪነት  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት በተመለከተ ሕዝባዊ ስብሰባ ተጠርቷል። በተመሳሳይ መልኩ በሀገር ቤት ከሃምሳ ከተሞች በላይ እና በባህር ማዶ በአሜሪካ እና አውሮፓ ተመሳሳይ ጥሪዎች በሰላማዊ ሰልፍ መተላለፋቸው ይታወቃል።


በኦስሎ፣ኖርዌይ በመጪው ቅዳሜ የሚደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ ሊቃነ ጳጳሳት፣ካህናት እና በርካታ ምእመናን እንዲሁም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ውጪ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚገኙ እንዳሉ ለማወቅ ተችሏል።ቅዱስ ሲኖዶስ በድንገተኛ ስብሰባው ላይም የቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታይ ያልሆኑ ሁሉ አጋርነታቸውን እንዲገልጡ ባሳሰበው መሰረት በእዚህ ጉባኤ ላይም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በእዚሁ ዓውድ የሚታይ ነው።

በመጨረሻም በኦስሎ የሚደረገው ስብሰባ በሌሎች አካባቢዎች ከሚደረጉ ሰልፎች በተለየ ምእመናን በአንድነት ስብሰባዎችን በማዘጋጀት መምከር ሌላው አማራጭ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰውን ፈተና የመቃወምያ መንገድነት በር የሚከፍት መልካም ሃሳብ እንደሚሆን ይታመናል።

አንዲት ናት ቤተክርስቲያን አንዲት ናት (በማኅበረ ቅዱሳን የመዝሙር ልዑክ የተዘጋጀ አዲስ መዝሙር)


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Tuesday, October 8, 2019

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰባት ነጥቦች ዙርያ መግለጫ አወጣ (የመግለጫው ሙሉ ቃል በድምፅ እና በጽሁፍ)

መስከረም 27/2012 ዓም (ኦክቶበር 8/2019 ዓም) 
መግለጫው በጽሁፍ  ከኦድዮ ስር ያገኙታል።
ምንጭ - ዘ-ሐበሻ
የመግለጫው ፅሁፍጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Friday, October 4, 2019

ሰበር ዜና - የአዲስ አበባ ነዋሪ በዕጣ ደርሶት የነበረው 23 ሺህ ኮንደሚንየም በመጪው ሰኞ ተነጥቆ ''ለባለተረኞች'' በኦፊሴል በሚሌንየም አዳራሽ ሊታደሉ ነው (Gudayachn Exclusive)

ጉዳያችን GUDAYACHN 

መስከረም 24/2012 ዓም  (ኦክቶበር 5/2019 ዓም)

በአዲስ አበባ ዙርያ ከዓመታት በፊት ለልማት ተነስተው የነበሩ እና በምትኩ ለእርሻም ሆነ ለመኖርያ ቦታ ተሰጥቷቸው  የነበሩ የኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን ቀድሞ ከተሰጣቸው ምትክ ካሳ በተጨማሪ በሚመጣው ሰኞ በሚሊንየም አዳራሽ በሚደረግ ስነ ስርዓት የኮንደምንየም እደላ ሊደረግ መሆኑን ከአዲስ አበባ ተሰምቷል።

መረጃውን በተመለከተ ጉዳያችን ለማጣራት እንደሞከረችው ከእዚህ በፊት ካሳ ተሰጥቷቸው  የነበሩት ብዛት ሶስት ሺህ ሲሆኑ የተቀሩት 20 ሺህ የሚሆኑት በውሸት የተፈናቀሉ ነበሩ በሚል ስም ከተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች ውስጥ ተመርጠው የሚመጡ እና ካለምንም ዕጣ እና ክፍያ የሚሰጣቸው መሆኑ ተሰምቷል።በሌላ በኩል ለእነኝህ አካላት የሚሰጠው የኮንደምንየም እደላ ልዩ የብድር አገልግሎት ይመቻችላቸዋል የሚል መረጃ አለ።የተረጋገጠው ጉዳይ ግን የአዲስ አበባ ሕዝብ በዜግነት መብቱ ተመዝግቦ እና ዕጣ አውጥቶ ኮንደሚንየም  እየጠበቀ ቢሆንም  ከ23 ሺህ የማያንሱ ኮንደሚንየም ቤቶች በሙሉ ከላይ ለተጠቀሱት አካላት የሚሰጥ መሆኑ ነው።

በኮንደሚንየም አሰጣጡ ኢ-ፍትሃዊ አካሄድ ደግሞ ቀድሞ ካሳ ለተሰጣቸው ድጋሚ ኮንደሚንየም ሲሰጥ፣በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሁለቴ እና ሶስቴ እየተሰጠ ሲሆን ለምሳሌ በቤተሰብ ውስጥ ለቤተሰቡ ሶስት መኝታ ክፍል ከተሰጠ በኃላ በቤተሰቡ ውስጥ ላሉ ከአስራ ስምንት ዓመት በላይ የሆኑ ልጆች ላሏቸው ለልጆቹ ለብቻቸው ሌላ የኮንደሚኒየም ቤቶች እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እያለ ዛሬ በአዲስ አበባ የእረቻ በዓል ዋዜማ በሚል በመስቀል አደባባይ የኦሮምያ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ  ''የኦሮሞ ሕዝብ የተሰበረው እዚህ ነው፣የነፍጠኛ ስርዓትን ዛሬ ሰበርነው፣የኦሮምያ ሕዝብ ደስ ይበልህ'' የሚል አደገኛ የዘር ቀስቃሽ ንግግር (ምናልባትም የሁቱ እና ቱትሲ ግጭት የመሰለ  ንግግር) መናገሩ ከፍተኛ ውጥረት ኢትዮጵያ ውስጥ ፈጥሯል።

የአቶ ሽመልስ ንግግር የኦዴፓ ድብቅ እና ከፋፋይ ዓላማ በግልጥ ያሳየበት ብቻ ሳይሆን ኦዴፓ ከፅንፍ ኃይሎች ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ እየሰራ መሆኑ ግልጥ ማሳያ ሆኗል።ሌላው የንግግራቸው ማሳያ አሁን ለውጡ ሙሉ በሙሉ ሐዲዱን እየለቀቀ መሆኑን ማሳያ ተደርጎ መወሰድ ይችላል።

ለኢትዮጵያ ነፃነት ከታገሉ የኢትዮጵያ ነፍጠኛ  አርበኞች መካከል ፋሺሽት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት  ወቅት 1928 ዓም አዲስ አበባ 
Determined Ethiopian young patriot NEFTEGNA at the beginning of the second world war, when Italy invaded Ethiopia in 1935.ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com

Wednesday, October 2, 2019

ከ2 ሚልዮን ምዕመናን በላይ የተገኙበት የዛሬው የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ንግሥ በዓል ላይ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ያስተላለፉት ሙሉ መልዕክት (ቪድዮ)

መስከረም 21፣2011 ዓም  ግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም ገዳም ቀጥታ ስርጭት 


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

የኦሮሞ ድርጅቶች ተፈራረሙ ወይንስ ተፈራሩ? (የጉዳያችን ምልከታ)

 Bildergebnis für oromo patriots 
ታላቁ የኢትዮጵያ አርበኛ ጀነራል ጃጋማኬሎ

ጉዳያችን/Gudayachn
መስከረም 21/2011 ዓም (ኦክቶበር 2/2019ዓም)

=========================
ትናንት ማክሰኞ መስከረም 20/2011 ዓም ወደ 14 የሚጠጉ ድርጅቶች በጋራ ለመስራት መፈራረማቸውን ለአምስተኛ ጊዜ በመፈራረም አሳይተዋል።የፊርማው ድባብ በራሱ የሚነግረን ነገር ግን የተለየ ነው።
ለመሆኑ የተፈራረሙት ማን ከማን ጋር ነው ብለን ብንጠይቅ መልሱ ቀላል ነው።ለሃያ ሰባት ዓመታት ኦህደድ የኦነግ ድርጅቶችን ሸኮና እየሰበረ አላስገባ ካላቸው ኃይል ጋር ነው።ይህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው የኦህዴድ (የአሁኑ ኦዴፓ) የኦነጎችን ፕሮፋይል ደካማና ጠንካራ ጎን ሲያጠና ነው የኖረው።በእርግጥ የኦነግ አንጃዎች እና ኦዴፓ በአንድ ነገር ላይ ይስማማሉ።ይሄውም ኢትዮጵያዊ ቅኝትን ማጥፋት፣የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ተሰሚነት ማደብዘዝ፣ያለፈውን ታሪክ በአዲስ የእረቻዊ የታሪክ ትርክት መፃፍ እና ሌሎች ላይ አብረው የሚያልሙት ጉዳይ ነው። ይህ ግን ሁሉም ኦዴፓ ውስጥ ያለ ሃሳብ አይደለም።ሃሳቡ ቢኖርም እንደማያዋጣ ጠንቅቀው የሚያውቁ ብዙ ናቸው።ስለሆነም ግቡ ላይ ቢስማሙም አካሄድ ስልት ላይ ግን ይለያያሉ።

በአካሄድ ከሚለያዩት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ይጠቀሳሉ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልችት ያላቸው ጉዳይ አሁንም የኦነግ እንደአንዳንዶች አባባል የማይጠራ የበግ ሽንፍላ የማጠብ ያህል ማለቂያ የሌለው ያረጁ እና የጃጁ ጥያቄዎች እራሱ ኦነግ ቤተ መንግስት ቢገባም ያማይመልሳቸው ጥያቄዎች ናቸው።እነኝህ ጥያቄዎች የ21ኛው ክ/ዘመንን የማይመጥኑ ብቻ ሳይሆኑ ያለፈው እና የድሮው ስራቶችንም ያማይመጥን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ አይነት ጥያቄ ያለው ግን ግቡ እና ዓላማው ኢትዮጵያዊነትን በፅንፍ የእስልምና ሃሳብ የመተካት ነው። ከኦነግ አንጃዎች ውስጥ ብዙዎቹ የኦኤምኤን ባለቤት ሃጅ ጀዋርን ጨምሮ የሚያገናኛቸው ይሄው ኢትዮጵያን ወደ ፅንፍ የእስልምና አብዮት መምራት ነው።ሁሉም ለኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሰብዓዊ ጋሻ ከመጠቀም ያለፈ ቅንጣት ታህል አይፈልጉትም። ቢፈልጉት ኖሮ ሀገር ቤት ከገቡም በኃላ በኦሮሞ ስም እንደ አሜባ እየተራቡ ባልተከፋፈሉ ነበር።

የትናንቱ የኦሮሞ ድርጅቶች ተፈራረሙ ዜና ተፈራሩ በሚለው ቢቀየር የተሻለ ነበር።የፊርማው ስነስርዓት ሲደረግ ጀዋር ጮክ እያለ ለማንበብ እየቸገረው ድምፁን እየቆራረጠ በኦሮምኛ ሲያነብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳቃቸው መጥቶ አይናቸውን ከወዲያ ወዲህ ይወስዱ ነበር። አሁን መሰረታዊው ጥያቄ ፅንፈኛው ክፍል ዓቢይን ለመምታት በፊርማ ሊያዘናጋ እየሞከረ ነው ወይንስ ዓቢይ የፅንፈኛውን አካል ጋር ተስማማ? የሚለው ነው። ይህ ጥያቄ በደንብ መመለስ ያለበት ነው።የፊርማው ስነ ስርዓት የመፈራራት ውጤት ነው።ግቡም ጊዜ መግዣ ነው።ፅንፈኛው አካል ዓቢይ ከስልጣን መውረድ እንዳለበት ያልማል።በቀላሉ ሊያደርጉ እንደማይችሉ ደግሞ ገብቷቸዋል።ዓቢይ የምንፈልገው አይደለም።የኢትዮጵያን ለውጥ ከቱንስያ ከፍ ማድረግ ነበረብን።አሁን ቆጨን እና ሌሎችም ሲሉ የነበሩ ዛሬ ፊርማ ያሉት አንድ ዓቢይ ሊያስረን ነው ብለው ስለፈሩ።ግልጥ እርምጃ የኦዴፓ ሰዎች መውሰድ ስለጀመሩ።ይህም በቀጥታ ማፈንን የጨመረ በመሆኑ ጉዳዩ ሳይከፋ የተለመደው ፊርማ ማንጋጋት መፍትሄ ነው ብለው ስላሰቡ ነው።

''ሀሎ ዓብይ ፊርማ ስነ ስርዓቱ አንተ ባለህበት መሆን አለበት'' አቶ ለማ ወደ ዓቢይ ደውለው።
''እባክህ ስራዬን ልስራበት።ከፈለጉ ወደ አስመራ መልሳቸው አርባ ዓመት ከገማ አስተሳሰብ ጋር አታነካካኝ።ካመንቅበት እንደሚሆን አድርገው'' ዓቢይ 
'' ግዴለህም እንደመንግስት ስንሆን መታገስ አለብን።ይህንን ብቻ ዓቢይ የአንተ መገኘት በጣም አስፈላጊ ነው።ሰጥቶ መቀበል አርገውታል።አንተን በአደባባይ ማሳየት እንደ ሾው ነው።ሆነም አልሆነም ምን ያህል እንደታገስን የሚያስረዳ ነው የሚሆነው።እረቻ ላይ ነገር ከተበላሸ ብዙ መዘዝ አለው።እሺ በለኝ።'' አቶ ለማ።

ዓቢይ ወደ አዳራሽ ሲገባ የምንሊክ ግብር የመሰለ ከአክትቪስት እስከ ጋዜጠኛ ተሰብስቧል።ዓቢይ የውሸት ዕቃ ዕቃ የሚጫወት ነው የመሰለው።ኦነግ ምን ሲሰራ እንደነበር ሪፖርቱ አለው።ከህወሓት ጋር እነማን ምን እንደተባባሉ ቃል በቃል ሰምቶታል።ይህ ፊርማ ዓቢይ ከጀዋር ጋር ተሰለፈ ለመባል የገበያ ዋጋ እንዳለው ያውቃል።ለማን ማስቀየም አልፈለገም።ሁሉንም ከኢረቻ በኃላ ይደርሳል።ስለሆነም ስልችት እያለው እና ሳቁ እየመጣ ተፈራረመ።እንደ ኦህዴድ -ኦዴፓ ሆኖ ፈረመ።ፈርሞ ሲወጣ ዘወር ዘወር ብሎ አየ እና ''ነጋቲ'' ብቻ ብሎ ወጣ። ፊርማ ሳይሆን መፈራራት።የእውነት ሳይሆን ዓቢይን በማዘናጋት ለመምታት እና ስልጣን ለመቆጣጠር የስልት ፊርማ መሆኑ ገብቶታል።የለማ የዋህነት እና ፅንፈኛውም የእኛው ነው ነገሮችን ማረቅ አለብን የሚለው አባባል የቆየ  ግን የማይሰራ መሆኑ ገብቶታል።ስለሆነም ቀጣዩ እርምጃ እና ሂደት ላይ ብቻ ነው ዓቢይ እያሰበ የወጣው።የኦነግን ፋይል ደህንነት መስርያቤት እያለ ሲያነበው ነው የኖረው።ወደ ሰውነት ማደግ ያልቻሉ የጫጩ አስተሳሰቦች እንዳሉበት ያውቃል።ስለሆነም ወደ ቀጣዩ ሂደት ላይ ማትኮር እንዳለበት ገብቶታል።

ለማጠቃለል ፍጥጫው  በፊርማው ባሰበት እንጂ አልተሻሻለም።የሚሻሻል ቢሆን ኖሮ ከአምስት ወር በላይ ፈጀብን እያሉ መናገር አይሳፈልገውም ነበር።በትክክል ከታሰበ የፈጀባቸው አምስት ወር አይደለም አርባ ዓመት ነው።ከአርባ ዓመት በኃላም ስለ አንድ ኦሮሞ እያወሩ አስራ አራት ሆነው ተቀመጡ እንጂ አንዳች አልፈየዱም።ከአርባ ዓመት በኃላ ከአስመራ ሀገር ውስጥ ገብተው ጥይት አንጣጡ ባንክ ዘረፉ እንጂ አንዳች ፋይዳ ለኦሮሞ ሕዝብ አላመጡም።ኦሮሞ ይነሳል! ኢትዮጵያዊነቱን በደሙ ያስከብራል።ያን ጊዜ ለፅንፍ አውሬ ሊሰጡት ያሰፈሰፉ ሁሉ እውነተኛ ፍርዳቸውን ያገኛሉ።የወለጋ ሕዝብ የደረሰበትን እና አሁን እየደረሰበት ያለውን ይመስክር።በሰላም አርሶ መብላት እና ነግዶ ማትረፍ ሕልም የሆነበት በኦነግ እና ውላጆቹ አስተሳሰብ የተነሳ ነው።ከኦነግ ያረጀ አስተሳሰብ ጋር እሄዳለሁ የሚል ማንኛውም ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም ሆኑ የኦዴፓ ለኦነግ አሸርጋጆች ሁሉ የሚፋረዳቸው የኦሮሞ ሕዝብ ነው።ይህ ዕውነት አይዘገይም። ባጭሩ የኦሮሞ ድርጅቶች ተፈራረሙ ከማለት ተፈራሩ ማለቱ የተሻለ ነው።ጀግኖቹ እነ ጀነራል ጃጋማኬሎ ደምተው ባቆዩት ሀገር ፅንፈኛ አይፈነጭባትም።ጉዳዩ እየጠራ መጥቷል።ኢትዮጵያዊነት ያነገቡ ከምር የሚነሱበት የደውል ድምፅ ከፍ ብሎ እየተሰማ ነው።

 
ጉዳያችን GUDAYACHN 
www.gudayachn.com

Sunday, September 29, 2019

በኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉት አቴቴ፣ጨሌ፣ዋቀፈና፣እሬቻ የጣኦት አምልኮ ናቸው? ወይንስ አይደሉም?

''ለጣኦት የተሰዋ አትብሉ'' ክርስትናም እስልምናም ያዛል።
እሬቻ የፀሐይ አምላክ ልጅ ኦራ ከተሰኘ ጣኦት ጋር ይገናኛል።
ይህንን ልዩ ዶክመንተሪ 'ኦድዮ' እስከመጨረሻው ካዳመጡ በኃላ ለጥያቀዎቹ መልስ ያገኛሉ።
(ልዩ ጥናታዊ ዶክመንተሪ የራድዮ ዝግጅት ያድምጡ)
========================
ሸገር ራድዮ ስንክሳር  መርሐግብር  ርዕስ = ''አቴቴ''
መርሐግብሩ አየር ላይ የዋለው መስከረም 10/2019 ዓም (ሴፕቴምበር  22/2019 ዓም)


ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Sunday, September 22, 2019

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በምዕመኖቿ ላይ የሚፈጸመው ግፍና መከራ እንዲቆም፣ ዛሬ ዕሁድ ብቻ ከሰላሳ በላይ በሚሆኑ የኢትዮጵያ ከተሞች ሰልፍ ተደረገ።የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ሰልፎቹን ተቀላቅሏል።ለንደንም ሰልፍ ነበር።(ከሃያ በላይ ፎቶዎች ይመልከቱ)

Breaking news ethiopia ሰበር ዜና ኢትዮጵያ 

in over thirty cities in ethiopia, Hundred Thousands TAKE TO STREETS TO PROTEST REPEATED ATTACKS AGAINST Ethiopian orthodox tewahido church (see over 20 pictures)

Today Ethiopian Orthodox Tewahido church followers and religious leaders have another round huge demonstration, protesting burning of the churches and repeated attacks on its followers, was held in over thirty cities in Ethiopia and in London. Last thursday,there was similar demonstration in Washington DC in front of Ethiopian Embassy. Muslim Ethiopians have also joined in all demonstrations showing their solidarity with Ethiopian christians.(see photos below Amharic version)
ጉዳያችን ዜና / Gudayachn News
 መስከረም 11/2011 ዓም (ሴፕቴምበር 22/2019 ዓም)
=================
 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን እና አባቶች በቤተ ክርስቲያንና ምዕመኖቿ ላይ ግፍ የፈጸሙት አካላት በሕግ እንዲጠየቁ፣በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ እና መንግስት ለችግሩ ትኩረት እንዲሰጥ በመጠየቅ  ከሰላሳ በላይ በሚሆኑ የኢትዮጵያ  ከተሞች ዛሬ  ሰልፎች ተካሂደዋል።
በያዝነው ሳምንት አጋማሽ ላይ በዋሽንግተን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን እና አባቶች በኢትዮጵያ ኤምባሲ ፊት ለፊት ሰልፍ ያደርጉ ሲሆን ዛሬ በለንደን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ በተገኘበት ሰልፍ መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።በሀገር ቤት የተደረገው ሰልፍ ከሰላሳ በላይ በሚሆኑ ከተሞች የተደረገ ሲሆን ከእነኝህ ውስጥ  በባሕር ዳር፣ በደብረ ማርቆስ፣ በብቸና፣ በደጀን፣ በሞጣ፣ በደብረ ብርሃን፣ በማጀቴ፣ በጫጫ፣ በአረርቲ፣ በመሐል ሜዳ፣ በፍኖተ ሠላም፣ በቡሬ፣ በመርዓዊ፣ በእንጅባራ፣ በደባርቅ፣ በዳባት፣ በአዲ አርቃይ፣ በጯሂት፣ በወልድያ፣ በቆቦ፣ ሮቢት፣ በላልይበላ፣ በውጫሌ፣ በወረኢሉ፣ በደላንታ፣ በኮን፣ በዳንግላ፣ በዱር ቤቴ፣ በአዲስ ዘመን እና በሌሎችም ከተሞች ተካሂደዋል፡፡
በልዩ ልዩ ከተሞች የተደረጉ ሰልፎች ፎቶዎች ከእዚህ በታች ይመልከቱ።
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia

Ethiopia
Ethiopia

Ethiopia

Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Ethiopia
Washington DC


London
ለንደን /London

ለንደን /London


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Wednesday, September 18, 2019

Huge Protest Held Against the Persecution of the Orthodox Church in Ethiopia

 • Large numbers of Muslims also joined the protests in support of their Christian compatriots.


On Sunday 15th September 2019 in the Ethiopian capital of Addis Ababa and other towns across Ethiopia, thousands of people poured into the streets to protest against the unprecedented atrocities that are being committed against the Ethiopian Orthodox Tewahedo Church and her faithful.
While the organizing committee in Addis Ababa had postponed the demonstration by two months to give time for talks with government bodies, the demonstrations outside Addis Ababa took place.

Reports from Bahir Dar, Gondar, Dessie, Kombolcha, Jimma, Debre Berhan, Debre Tabor, Tsegede, Dessie, Kombolcha and Gondar states that large numbers of Muslims also joined the protests in support of their Christian compatriots.
In Addis Ababa however, there was a very large police presence on the streets to prevent the demonstrators reaching Mesqel Square from their respective Church compounds. However, the demonstrators thronged the compounds of several Churches in the city (by singing, clapping and ululating,) demanding an end to the persecution of the Orthodox Church.
Huge banners thanking Patriarch Krill of Moscow and All Russia and President Putin of the Russian Federation were on display as well.
The above video shows protesters on the grounds of the Lideta Le Mariam (Nativity of the Virgin Mary) Monastery, in the large courtyard between the two Churches of the Monastery.
Source: OCP

Source : Serbian Orthodox Church 

Monday, September 16, 2019

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን ሁሉን አቃፊ የሆነ ፖለቲካዊ ዕሳቤ መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፓርቲ በመመስረት እና ሚናውን በማስፋት የኢትዮጵያ ህልውናን በትክክል ማረጋገጥ ይቻላል። (ጉዳያችን ሃሳብ)

በእዚህ ፅሁፍ ስር የሚመከተሉትን ንዑስ ርዕሶች ያገኛሉ - 

 • የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በፖለቲካ አደረጃጀት ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጉ ይገባል፣
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን ሁሉን አቃፊ የሆነ ፖለቲካዊ  ዕሳቤ ምንድነው?
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያበረከተችውና አሁን ያለችበት ፈተና፣
 • ''ኢትዮጵያን ለመምታት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ምታ!'

================================
ጉዳያችን / Gudayachn
መስከረም 5/2012 ዓም (መስከረም 16/2019 ዓም)
=================================

ወቅታዊው ሃገራዊ ሁኔታ

የኢትዮጵያ ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ ዓይነተኛ አያያዥ ኃይል ካላገኘ ከኢሕአዴግ መሰነጣጠቅ ተከትሎ የሀገሪቱ ፖለቲካ ማባርያ ወደ ሌለው የእርስ በርስ እልቂት እንዳይመራ ያሰጋል።ክልሎች በራሳቸው የታጠቀ ኃይል በማደራጀት ላይ ተጠምደዋል።ሌላው ቀርቶ ክልሎች ያላቸውን የሚሊሻ ብዛት ራሱ ማዕከላዊ መንግስት የሚያውቀው አይመስልም።ይህ ደግሞ አደገኛ መንገድ ነው።ዛሬ መስከረም 5/2012 ዓም የኬንያው ዘ ስታንዳርድ ጋዜጣ በኢትዮጵያ እና ኬንያ በኩል ያለው መንገድ መዘጋቱን መዘገቡን ጠቅሶ ዋዜማ ራድዮ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ገልጧል።በሌላ በኩል ሸገር ኤፍ ኤም ራድዮ  በምሽት የዜና እወጃው ላይ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር  አምባሳደር መለስ ዓለምን ደውሎ ባናገራቸው መሰረት ጉዳዩ ውሸት ነው በሚል በደፈናው ለአዲስ ዓመት ለማክበር ሞምባሳ ነበርኩ የእኛ እና የኬንያ ግንኙነት ጥሩ ነው።በሚሉ ንግግሮች አልፈውታል። እንደ ዘስታንዳርድ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ኬንያ ድንበሩን ለመዝጋቷ ምክንያቷ ሕገ ወጥ ንግድ በመበራከቱ መሆኑን እና በየቀኑ ከ30 እስከ 50 የሚደርሱ ካሚዮኖች ጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ሕገ ወጥ ሸቀጦችን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚያግዙ እና ብዙዎቹ መጋቢ መንገዶችን ስለሚጠቀሙ ታከስ ሳይከፍሉ የሚገቡ መሆናቸውን በመጥቀስ ነው።እነኝህ መሣርያዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚያስገባው ማን ነው? ለምን ተግባር? መንግስት በአግባቡ ድንበር እየጠበቀ ነው? መንግስት መዋቅር ውስጥ  በተለይ በኦዴፓ ውስጥ የገቡ የመንግስት ኃላፊዎች ድንበር ጠባቂዎች፣የግምሩክ ባለስልጣናት ከፅንፍ ኃይሎች ጋር ተባብረው  የጦር መሳርያ እንዲገባ እያደረጉ ላለመሆናቸው ዋስትናው ምንድነው? 

ይህ በጣም ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ሁኔታ ለማሳየት የቀረበ ማሳያ ነው እንጂ በመንግስታዊው መዋቅር ውስጥ የሚታየው ወጥ ያልሆነ እና የልዩ ልዩ ኃይሎች መጠቀምያ የሆነው ቢሮክራሲ ኢትዮጵያ ወደ አደገኛ ሁኔታ እየሄደች ለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው። ጠቅላይ ምንስትር ዓቢይ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ መስከረም 3/2012 ዓም ለሸገር ''ጨዋታ'' በተሰኘ ፕሮግራም ላይ ቀርበው ሲናገሩ ''የመንጋ ሂደት በአዲሱ ዓመት የሚቀጥል አይሆንም'' ሲሉ ተደምጠዋል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእዚህ ቃለ መጠየቃቸው ላይ  ባብዛኛው የሚነበብባቸው የየዋህ ፖለቲከኛ እሳቤዎች እንጂ መረር ያለ የኢትዮጵያን አድነት በሚያቅፍ መልኩ የማዕከላዊው መንግስትን ሚና የሚያጎላ ሆኖ አልታየም።ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያነሱት የመደመር ዕሳቤ  በትክክልም የሚያማልል ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ መልካም መንገድ የሚያስዝ ሊሆን ይችላል።ይህ ግን ከጠንካራ የማዕከላዊ መንግስት የማስፈፀም አቅም ጋር ካልሄደ ተግባራዊነቱን አሳሳቢ ያደርገዋል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ያበረከተችውና አሁን ያለችበት ፈተና 


ኢትዮጵያ በዘመናት ጉዞዋ እንደ ጅማት እና ክር ሆኖ ታሪክ ማንነቷን ካቆዩት ውስጥ ቀዳሚዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነች።ከክርስቶስ ልደት በፊት በሕገ እግዚአብሔር እና በኦሪት ስርዓት የፀኑ ነገስታቶቿ በአራተኛው ክ/ዘመን በብሔራዊ ሃይማኖት ሆኖ በቤተ መንግስት የታወጀው ክርስትና እስከ 20ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ድረስ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ሕይወት ላይ የራሷን አሻራ ከማቆየቷ በላይ ኢትዮጵያ በነፃነት እንድትዘልቅ መንፈሳዊ እና ሞራላዊ ልዕልና በማጎናፀፍ የመሪነት ሚና ተጫውታለች።ከእዚህ በተጨማሪ ቤተክርስቲያኒቱ ከፊደል ገበታ እስከ ከፍተኛ የፍልስፍና እሳቤዎች እንዲሁም መሪ ነገሥታቱን ከልጅነታቸው በሞራል፣በመንፈሳዊ ሕይወትና በፍትሃዊ አሰራሮች ሁሉ አሰልጥና ለመሪነት በማብቃት የቤተ ክርስቲያን ድርሻ ብቸኛ እና መተኪያ የሌለው ሆኖ ከሁለት ሺህ ዘመናት በላይ  የዘለቀ አንፀባራቂ ታሪክ ነው።ይህ በእንዲህ እያለ ግን ላለፈው ግማሽ ክፍለዘመን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የደረሰው ፈተና በርካታ ጥፋት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ከማድረሱም በላይ በውጤቱ ኢትዮጵያ አንድ በሞራል እና በመንፈሳዊ ሕይወት የበለፀገ ትውልድ በማጣቷ ምክንያት  በጎሳ የሚያምን፣ሙሰኛ እና በገዛ ወገኑ ላይ ገጀራ የሚያነሳ ትውልድ በኢትዮጵያ ምድር  እንዲበቅል ምክንያት ሆኗል።


ከእዚህ በባሰ ሁኔታ ደግሞ በቅርብ በኢሕአዴግ ውስጥ በመጣው የጥገናዊ ለውጥ ተከትሎ ቤተ ክርስቲያንቷ በባሰ አደገኛ ሁኔታ ላይ ወድቃለች።ይሄውም ለውጡን ተከትሎ ወደ ሀገር የገቡት  የጎሳ እና አክራሪ የፅንፍ ኃይሎች ጋር ኢሕአዴግ በገጠመው ግንባር በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ  ቀጥተኛ ዘመቻ ከፍቷል።ለእዚህም ማሳያው የኦሮምያ ቤተ ክህነት ለመመስረት የተደረገው ሙከራ ላይ የመንግስት ስውር ድጋፍ፣ ብፁዓን ጳጳሳት መንግስትን ባናገሩበት ሂደት ያገኙት አጥጋቢ ያልሆነ ምላሽ እና ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን መንግስት  ለሚደርሰው ጥፋት ለማስቆም እርምጃ ይውሰድ የሚለውን ጥያቄ ለመጠየቅ በሚልዮን የሚቆጠር ሕዝብ በጎንደር፣ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ደብረ ታቦር እና ሌሎች ከተሞች ያደረጉት ሰልፍ በኢትዮጵያ የመንግስት ዜና ማሰራጫዎች አለመዘገቡ ትልቅ ቁጣ በመላው ሀገሪቱ ፈጥሯል።ከእዚህ በተጨማሪ ሰሚ ያጣው የቤተ ክርስቲያኒቱን ህንፃዎች የማቃጠል እና ምመናኗን የማሰደድ ተግባር ሁሉ የሚመሩት የቤተ ክርስቲያኒቱን  እሳቤዎች የሚያስጠብቅ የፖለቲካ ፓርቲ አስፈላጊ መሆኑን ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞችን ሁሉን አቃፊ የሆነ ፖለቲካዊ  ዕሳቤ ምንድነው?


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች ሁሉን አቃፊ የሆነ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ዘመናት አሻግሯል።

 • አቃፊው ፖለቲካ የእስልምና መስራች መሐመድ ቤተሰቦችን ተቀብሎ ያስተናገደ ፖለቲካ ነው።
 • አቃፊው ፖለቲካ የይሁዲ  እምነት ተከታዮችን ከአንድ ሺህ ዓመት በላይ አስጠልሎ ወደ ሀገራቸው የሸኘ አቃፊ ፖለቲካ ነው። 
 • አቃፊው ፖለቲካ ከምፅዋ እስከ ሞያሌ፣ከፈርፈር እስከ አኮቦ ከእስልምና አማኞች ጋር ጎን ለጎን በአንድነት እና በመከባበር የዘለቀ፣ኢትዮጵያን እንደ ደም ስር እና ጅማት ያስተሳሰረ አቃፊ ፖለቲካ ነው። 
 • አቃፊ ፖለቲካው ኢትዮጵያ በፋሺሽት ጣልያን ስትወረር ከደቡብ እስከ ሰሜን ሕዝብ አስተባብሯል።
 • አቃፊ ፖለቲካው በየትኛውም ዓለም ያልታየ መከባበርን፣እምነት ያልለያቸው ኢትዮጵያውያን በአንድ እድር፣እቁብ፣ሰርግ እና ሃዘን ሁሉ እንዴት እንደሚኖሩ አስተምሮ በፍቅር አስተሳስሯል።
ይህ አቃፊ ፖለቲካዊ እሳቤን ለመናድ መሞከር ኢትዮጵያን ለመናድ የመሞከር የእብደት ሥራ አሁን በኢትዮጵያ እየተሰራ ነው። የእብደት ስራውን እየሰሩ ያሉት የፅንፍ የጎሳ ድርጅቶች እና ኦዴፓ ውስጥ የተሰገሰጉ አደገኛ  ግለሰቦች እና የውጭ ተባባሪዎቻቸው ቅንጅት ሁሉ ነው።

''ኢትዮጵያን ለመምታት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ምታ!''

ኢትዮጵያ በዘመኗ ሁሉ የመጡባት ጠላቶቿ ቀዳሚው የኢትዮጵያ ኃይል አለበት ብለው የደመደሙት እና ቀድመው የሚያጠቁት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ነው።በዘጠነኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ላይ የተነሳችው እና የአክሱም ስርወ መንግስት የናደችው ዮዲት ጉዲት ተብላ በታሪክ የምትጠራው ሴት እና ሰራዊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የተቀናጀ ዘመቻ በማድረግ፣በማቃጠል እና እና ምዕመናንን በመፍጀት  ኢትዮጵያን ለማዳከም ሞክራለች፣ከክልበኃላ 1500 ዓም በኃላ የተነሳው እና በቱርክ የታገዘው ግራኝ መሐመድ የመጀመርያ ኢላማው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ቱርካዊ አማካርዎቹም ሆኑ ግራኝ መሐመድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በመበተን ኢትዮጵያን ገልብጦ እንደፈለገ ሊሰራት ሞክሮ አልተሳካለትም።ግራኝ መሐመድ ይህንን ያድርግ እንጂ ሁሉን አቃፊዋ ቤተ ክርስቲያን ግን የግራኝ መሐመድን ካባ ሳይቀር በቅርስነት ይዛ መርጦለ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በሙዚየሟ  በመስታወት አስቀምጣ ለጎብኚዎች አሁን ድረስ ታሳያለች።


በ1928 ዓም ኢትዮጵያን የወረረው ፋሺሽት ጣልያን  ዋና ኢላማው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነበረች።ፋሺሽት ጣልያን የቤተ ክርስቲያኒቱን ጳጳሳት አቡነ ጴጥሮስን ጭምር በአደባባይ በጥይት ከመደብደብ እስከ በአንድ ቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ የደብረ ሊባኖስ መነኮሳትን ገደል በመጨመር ሁሉ  ጥፋት በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አድርሳለች።ዛሬም  የባዕዳን ተልኮ አስፈፃሚዎች የፅንፍ ጎሰኘንት አራማጆች እና በመንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ አስፈፃሚዎች በመንግሥትነት ተከስተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማጥፋት ግልጥ ዘመቻ ላይ ናቸው።ይህ የጥፋት እና የጥላቻ ስሜታቸውን መታገስ አቅቷቸው ምእመናኑ በአደባባይ ያሰሙትን ድምፅ ግብር ከፍሎ ለሚያስተዳድራቸው ሕዝብ የመገናኛ ብዙሃን እንዳይዘግቡ በማገድ እኩይ ተግባር ተገልጧል።ይህ ብቻ አይደለም ቤተ ክርስቲያኒቱ ከጅጅጋ እስከ ሲዳማ፣ከከፋ እስከ ጅማ በቃጠሎ ስትጠቃ እና ምዕመናኗ ሲሰደዱ የሚከላከል መንግስታዊ አካል አለመኖሩ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመልካም እሳቤዎቿ ላይ ተመስርታ ልጆቿን በፖለቲካ አደረጃጀት መደራጀት የወቅቱ ቀዳሚ እና ዋነኛ ጥያቄ አድርጎታል።

የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች በፖለቲካ አደረጃጀት ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጉ ይገባል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ራሷን የቻለች የኢትዮጵያ የደም ስር እና የጀርባ አጥንት አያያዥ ነች።በኢትዮጵያ የተነሱ ቅራኔዎች ሁሉ ለመፍታት የቤተ ክርስቲያኒቱ ሚና የግድ አስፈላጊ ነው።ቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ 1966 ዓም ድረስ መንግስታዊ ጥበቃ ስለነበራት የሀገር አንድነትም ሆነ ሰላም ተጠብቆ ለመቆየት ችሏል።በአሁኑ ወቅት የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅርስ፣ማንነት፣የጋራ እና አቃፊ ዕሴት ሁሉ ጠባቂ አጥቶ ከፍተኛ አደጋ ላይ ነው። አሁን ይህንን የሚጠብቅ ንጉሰ ነገስት መንግስት የለም።ይህንን ክፍተት በዘመናዊው የፖለቲካ መንገድ ማለትም የተደራጀ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ ወይንም አደረጃጀት ኢትዮጵያ ከሌላት ለሀገሪቱ እንደ ሀገር ለመቀጠል እጅግ አደኛ ነው። 

ይህ ማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ በፖለቲካ አደረጃጀት ትደራጅ ማለት አይደለም።የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ  ሂደት ሁሉ የነበረ ወደፊትም የሚኖር እና ምድራዊውን ሳይሆን ሰማያዊ ሕይወትን መሰረት ያደረገ ነው። ሆኖም ግን ''የቄሳርን ለቄሳር'' ካለ መፅሐፉ የእግዚአብሔርን ጉዳይ ስናወራ የቄሳርን ሥራ ግን ረስተነዋል።በመሆኑም ቤተ ክርስቲያኒቱ ቀድሞ በነገሥታቱ ሕጋዊ ከለላ የነበራት ቤተ ክርስቲያን በዘመናዊው የፖለቲካ አደረጃጀት የተደራጁ ልጆች  ባለመነሳታቸው ከመቼውም ጊዜ በላይ አደገኛ ክፍተት ተፈጥሮባታል።ክፍተቱ ደግሞ በቀጥታ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ አንድነት መፍረስ ላይ በትክክል እየተንፀባረቀ ነው።ለእዚህ ነው የኦርቶዶክሳውያን ፖአለቲካዊ አደረጃጀት ክፍተቱን የመሙላቱ ፋይዳ አንገብጋቢ የሚያደረገው።

ይህንን ክፍተት ይህ ትውልድ መሙላት ካልቻለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ለአደጋ የሚያጋልጣት ትውልድ እንዳይሆን ያሰጋል።ይህ ጉዳይ የሃይማኖት ልዩነት የሚፈጥር የሚመስላቸው አሉ።አንዳንዶች  ሌሎችም በሃይማኖት እንዲደራጁ በር የሚከፍት ነው የሚሉም አሉ።ሆኖም ግን አሁን የኢትዮጵያን አንድነት ለማምጣት የእስልምናም ሆነ የሌሎች እምነቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በተስፋ እንደሚጠብቁ መረዳት ያስፈልጋል።አሁን ያለው የኢትዮጵያን የነበረ ዕሴት መናድ ላይ ማንኛውም  ኢትዮጵያዊ የዕምነት ድርጅት አይስማማም።ምክንያቱም ጉዳዩ የህልውና ጉዳይ ነው።የመጥፋት እድሉ ሁሉም ላይ የመጣ ነው። ስለሆነም የጋራ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ጎልብቶ በፖለቲካ ኃይልነት መውጣት እና  የኢትዮጵያን እሴቶች ከበታኝ ኃይሎች መታደግ ወቅታዊ እና አንገብጋቢው ጉዳይ መሆኑን የማይረዳ የማንኛውም የእምነት ድርጅት  የለም። በእርግጥ ኢትዮጵያን ለመበተን የሚያልሙ ኃይሎች ይህ ጉዳይ አይዋጥላቸውም። ኢትዮጵያን ለመበተን እንደሚያስቡት የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን መበተን ፈፅሞ በቅርብ የማይሳካላቸው ግን ጊዜ የሚወስድ ድምፅ አጥፍቶ ውስጥ ውስጡን በመሄድ ብቻ ሊሳካ እንደሚችል ያስባሉ።

ለማጠቃለል የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጉ የሚገባበት ወሳኝ እና ታሪካዊ ጊዜ ላይ ነን።መልፈስፈስ እና መዘግየት በራሱ አደጋ አለው። አንዳንድ የዋሃን ዛሬም ፖለቲካ ከእምነት ጋር ይጣረሳል፣ እያሉ ስሌት ውስጥ የሚገቡ ይኖራሉ።እነኝህኞቹ ንጉስ ዳዊት ንግስናው፣ንጉስ ሰለሞን ሀገር ማስተዳደሩ፣ንጉስ  ቆስጠንጢኖስ በእናቱ ንግስት ዕሌኒ አማካይነት የክርስቶስን መስቀል ማግኘቷ ሁሉ ፖለቲካ ብለው ይተዉት እያሉ ነው። ነገሥታቱ አብርሃ ወአፅብሃ  ለሀገር መትረፋቸው፣ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ስላሴ ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ መስመር መምራታቸው ሁሉ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ይዘው መሆናቸውን የመዘንጋት ያህል ነው። አሁንም ወቅቱ ኢትዮጵያ እራሷን በአግባቡ የምታይበት ወሳኝ ጊዜ ነው። በድጋሚም  የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆች ተደራጅተው ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊታደጉ ይገባል።ጉዳዩ ከተራ ሰላማዊ ሰልፍ እና ድርድር በላይ ከፍ ያለ አደገኛ ሁኔታ ነው የሚታየው።

አለን ሁሉን በእግዚአብሔር አልፈን (ቪድዮ)


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Friday, September 13, 2019

የሰልፉ ቀን መቀየር ጥያቄውን አጠንክሮ የሚያወጣ ነው::ቀጣይ ስራዎች ምን መሆን አለባቸው:?

ጉዳያችን/ Gudayachn
መስከረም 3/2012 ዓም (ሴፕቴምበር 14/2019 ዓም )
++++++++++++++++++++++++++++++
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እየደረሰባት ያለውን ቃጠሎ፣ምእመናኖቿን ላይ የደረሰው እንግልት እና ስደት እንዲቆም ሶስት ዓላማዎች የያዘ ጥያቄ መንግስትን ለመጠየቅ ለመስከረም 4 ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የነበረው ዕቅድ ለጥቅምት 30 መተላለፉን አስተባባሪው ኮሚቴ ዛሬ መስከረም 2/2012 ዓም ገልጧል።ሰልፉን በተመለከተ ጉዳያችን ላይ የወጣው ዝርዝር ዘገባ ለማንበብ  ይህንን  ገፅ ይጫኑ።

የሰልፉ ጥሪ መደረጉ በራሱ ምን በጎ ነገር አመጣ?

የሰላማዊ ሰልፉ መጠራት በራሱ የሚከተሉትን መልካም ነገሮች ይዞ መጥቷል። እነርሱም -

 • ከቤተ ክህነት እስከ  ቤተ መንግስት የኦሮቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተፅኖ ከማሕበራዊው ጉዳይ በላይ የተሻገረ አገር አንቀጥቅጥ አጀንዳ የማንቀሳቀስ አቅሙ ታይቷል።
 • ከጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ ክልል ባለስልጣናት ድረስ የቤተ ክርስቲያን አጀንዳ ለውይይት ቀርቧል።
 • እጅግ የጠነከረ ኦርቶዶክሳዊ አንድነት እና መተሳሰብ እና መናበብ ፈጥሯል።
 • አጀንዳው ዓለም አቀፍ ህብረት ፈጥሯል።በአሜሪካ እና አውሮፓ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት  ጥያቄውን ደግፈው እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
 • ኦርቶዶክሳዊው ወጣት በመጪው ጊዜ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲያውቅ ጥሩ ማሳሰቢያ ሆኖታል።
 • ኦርቶዶክሳዊው ከመንግስት ጋር ጨምሮ የመደራደር አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ከፍ አድርጎ መጥቷል።
 • ቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ አስተዳደራዊ መዋቅሯን ለማሻሻል ያላትን ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አጎልቶታል።
 • የጎጥ ፖለቲካውን አደናብሮታል።ኦርቶዶክሳዊው ህብረት የጎጥ ፖለቲካውን የመደርመስ አቅም እንዳለው በግልጥ አመላክቷል።
አሁንም ችግሩ ግዙፍ ነው

ከላይ የተጠቀሱት መልካም ገፅታዎች የድል መጨረሻ ተደርገው የሚቆጠሩ አይደሉም። በትንሽ ነገር የረኩ መስሎ መቅረብ በራሱ ትልቁ ችግር ነው።በአሁኑ ደረጃ ምንም የተሰራ ነገር የለም።ከላይ የተጠቀሰው መልካም ተፅኖ እንዳለ ሆኖ ፣በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያጠላው  ጥላ ግን ገና አልተገፈፈም።ይልቁንም በእንቅስቃሴው ሳብያ የኦሮዶክሳውያኑ መነቃቃት ለበታኝ ኃይሎች እንደ  ድንገተኛ መብረቅ አስደንግጧ ቸዋል።ቀድሞም በስጋት ሲያዩአት የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን ለመጉዳት አሁን በደነበረ መንፈስ ምንም ከማድረግ አይመለሱም።ከእዚህ በተጨማሪ መንግስት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉት የፅንፍ ኃይሎች የመንግስትን ፖሊሲ  የሚያስፈፅሙ መስለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመጉዳይ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም።ሰሆነም አሁንም ችግሩ ገና ግዙፍ ነው።

በቀጣይ ምን ይደረግ? 

አሁን ባለው የሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የሚከተሉት ተግባራት ቢከናወኑ መልካም ነው። እነርሱም - 

1ኛ) የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ እራሱን በሚገባ ማጠናከር አለበት።ይሄውም ግብ እና የውስጥ መተዳደሪያውን አዘጋጅቶ ከኮሚቴ በዘለለ ስያሜውን ከፍ አድርጎ እና የስራ ዘርፍ አውጥቶ  መንቀሳቀስ፣

2ኛ) ከኮሚቴ ከፍ ባለ ደረጃ የተደራጀው አካል ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቀርቦ ቡራኬ እና መመርያ መቀበል፣

3ኛ) ከኮሚቴ ከፍ ባለ ደረጃ የተደራጀው ኮሚቴ ውጫዊው የቤተ ክርስቲያኗ ጉዳይ ላይ ከማትኮሩ በተጨማሪ  የማኅበራት ሕብረት ከመፍጠር ባለፈ የቤተክርስቲያን ውስጣዊ አስተዳደር ማዘመን ላይም በውስጡ ያሉትን አካላት የማስተባበር ስራውን መቀጠል፣

4ኛ) የጥያቀዎቹ ምላሾች በተለይ ቤተ ክርስቲያንቷን ከሚገዳደሯት አካሎች አንፃር ፈረንጆቹ እንደሚሉት  ''የካሮት እና ዱላ'' ፖሊሲ መከተል ።ቤተ ክርስቲያንን የሚገዳድሯት አካሎች በፀሎት እና በልመና የሚመለሱ አይደሉም።በሰላማዊ መንገድ ካሮት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ተፅኖ መፍጠርያ ልዩ ልዩ  መንገዶች ማቀድ ያስፈልጋል።ከእዚህ ውስጥ አንዱ ሰልፍ ሊሆን ይችላል።ሰልፍ ግን ባብዛኛው  ትልቅ የተፅኖ መፍጠርያ መንገድ ይሆናል እንጂ ሌሎች ሰላማዊ የተቃውሞ መንገዶች እና የሕግ አገልግሎት ሁሉ የያዘ ጠንካራ አካሎች ያስፈልጋሉ። ይህ አሰራር በተለይ በመንጋ ለሚያስቡ የፅንፍ ኃይሎች ትምህርት ሰጪ በሆነ መንገድ የማስፈፀም አቅሙን ያሳድገዋል፣

5ኛ) ኦርቶዶክሳዊነት ላይ ያጠሉት ጥላዎች  ፅንፍ የያዙ አክራሪ እስልምና ኃይሎች፣ የሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) እና ሌሎች ስጋቶች ዙርያ ጥርት ያለ መረጃ ኮሚቴው መስጠት ወይንም ልዩ የማንቅያ ትምህርቶች እንዲሰጡ መግፋት።

6ኛ) እንቅስቃሴው ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ መልክ እንዲይዝ እና ሁሉን አቃፊ እንዲሆን ማድረግ  እና ከመንግስት የተጠየቁት ምላሾች ከተገኙ በኃላ ኮሚቴው እራሱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማሳደግ እና በአባቶች ቡራኬ ማቆየት  የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው። 

ከምዕመናን  ምን ይጠበቃል።  

ምዕመናን ሁለት ቁልፍ ተግባራት ይጠበቅባቸዋል። አንድኛው በሕበረትም ሆነ በግል በየትኛውም ቦታ በሀገር ፍቅር ጉዳይ፣በሀገር አንድነት ጉዳይ ላይ ሁል ጊዜ ቀዳማዊ ተፅኖ ፈጣሪ መሆን እና ከአስተባባሪ ኮሚቴው የሚመጡ መመርያዎችን በማክብበር በህብረት ተፅኖ የመፍጠር አቅሙን ማሳደግ። የሚሉት ተጠቃሾች  ናቸው።

አዎን! ኦርቶዶክሳዊው ማኅበረሰብ ላይመለስ ተነስቷል።ለኦርቶዶክሳዊውም ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ አጀንዳ የለም። ኦርቶዶክሳዊው ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነቱን ደግሞ ማንም እንዲነጥቀው ዕድል መስጠት የለበትም።የኢትዮጵያን ዕጣ ከሚወስኑት የሀገሪቱ ባለመብት ዜጎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ኦርቶዶክሳውያንን ዘሎ ምንም አይነት ፖሊሲ መቅረፅ እንደማይቻል አሁንም ትምህርት ሰጪው መሆን ያለበት ኦርቶዶሳዊው ወጣት ነው።  በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሕይወት ውስጥ  ሁሉ የኦርቶዶክሱ   ማኅበረሰብ መብቱን የማስከበር ሚና በከፍተኛ ደረጃ የማሳደግ ስራው አሁንም የሁሉም ባለ ድርሻ አካል ግዴታ መሆኑን ማወቅ አለብን።ስለሆነም የሰላማዊው ሰልፍ ወደ ጥቅምት 30/2012 መራዘም ከላይ የተጠቀሱትን ተባራት ከማከአወን ባለፈ የመደራደር አቅምን የሚያሳድግ ዕድል ከመስጠቱ በላይ አደረጃጀቱ እስከ ገጠር ድረስ የመድረስ እና ተፅኖ የመፍጠር አቅም ማሳደግ አስፈላጊ ነው። 

አንተውም ከቶ! (ቪድዮ)
++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++++
ከመስከረም 4 ቀን በአዲስ አበባ የተጠራው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
++++++++++

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሐገረ ስብከት ካህናት፣ ሰባኪያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ኅብረት፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት ና ምሩቃን እና የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች እና በመስከረም 4 ቀን በዲስ አበባ ሊካሄድ የታሰበው ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች ሰላማዊ ሰልፉን አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
በአገራት የታሪክ ግንባታ ላይ የሃይማኖት የተቋማት አስተዋጽኦ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ በተለይ ተቋማቱ ከአገራቱ እድሜ የማይተናነስ የዘመን ርዝማኔ ሲኖራቸው ከሚተረከው የአገሪቱ ታሪክ ላይ የእነርሱ እጅ ያልገባበትን፣ አሻራቸው ያላረፈበትን ዘርፍ ለይቶ ለማውጣት እስኪከብድ ድረስ የአገር ታሪክ እና የሃይማኖት ተቋሙ ታሪክ እንደ ድርና ማግ የተገመደ ሲሆን ይስተዋላል፡፡
በአገራችን በኢትዮጵያ ያለውም እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ የሌሎቹ እምነቶችና ባህሎች አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ ኢትዮጵያን ያለ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማሰብም ሆነ የወደፊት እጣዋንም በአዎንታዊ መንገድ መተለም ፈጽሞ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ የቤተ ክርስቲያኗን ስም ሳያነሱ ለመተረክ መሞከር እስከሚያዳግት ድረስ ቤተ ክርስቲያን የአገር የልብ ትርታ ሆና ኖራለች፡፡ በአገራችን ስልጣኔ ላይ ዘርዝሮ ለመጨረስ የሚያዳግት አሻራን አሳርፋለች፡፡
ምእመኗን ሌት ከቀን ስለሳላም በማስተማር እርስ በእርሱ በመከባበር እና በፍቅር ከመኖር አልፎ የሌላውን እምነት እና ባሕል አክብሮ እንዲኖር አድርጋለች፡፡ ትምህርት የመንግስት የፖሊሲ አካል ባልነበረበት ዘመን ትምህርት ሚኒስተር፣ ባህል እና ቱሪዝምን ማሳደግ ቦታ ባለገኝበት ዘመን የባህል እና የቅርስ ጠባቂ ሆናለች፡፡
አገር በተወረረበት ዘመን ጽላቷን ሳይቀር ተሸክማ ከጦሩ ፊት ተሰልፋለች፡፡ ዓለምና አገር ለሥነ- ጽሑፍ፣ ለሥነ ሥዕል፣ ለኪነ- ጥበብ፣ ለኪነ-ሕንጻ እና መሰል ጥበቦች ባእድ በነበረበት ዘመን ለአገራችንና ለዓለም እስከ ዛሬ የሚመራመርበትን የጥበብ ፋና አብርታለች፡፡ ከግብርና እስከ ሥነ ከዋክብት፣ ከዘመን አቆጣጠር እስከ መድኃኒት ቅመማ፣ ከሕግ ቀረጻ እስከ ደን ልማት፣ ከቤተሰብ አስተዳደር እስከ ስነ-መንግሥት፣ ከዜማ ፈጠራ እስከ ማኅበራዊ እሴት ግንባታ ያላትን ኃብተ ጥበብ ሁሉ ለኢትዮጵያ እያበረከተች ከራሷ ሕልውና በላይ ስለ አገር ኖራለች፡፡ በየትኛውም የታሪክ ዕይታ እና መንገድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ሊደራደር ከመጣ አካል ጋር ለውይይት የተቀመጠችበት ዘመን የለም፡፡ እርሷ እየነደደች እና እየከሰመች አገርን አጽንታለች፡፡ ለዚህ ውለታዋ ግን ወሮታ የጠየቀችበት፣ ለዚህ መስዋእትነቷ ዘካሪ የሻተችበት ዘመን የለም፡፡
ይሁንና ወርቅ ላበደረ ጠጠር እንዲሉ ዛሬ ዛሬ በኢትዮጵያ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ጡት የመንከስ ያህል አጠያያቂ ምልክቶች እየታዩ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፤ ካህናት እና ምእመናን ተወልደው ባደጉባት ምድር ታርደዋል፣ ያፈሩት ሃብት ንብረትም ሁሉ የእሳት አሊያም የቀማኛ ቀለብ ሆኗል፤ከሕጻን እስከ አረጋዊ፣ ካልጋ ቁራኛ እስከ ነፍሰ ጡር ድረስ ኦርቶዶክሳዊያን አንስቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተደፍረዋል፡፡ መከራ የበረታባቸው ለዘመናት የኖሩበትን ቀየ ለቀው ወደማያውቁት ቦታ ተሰደዋል፡፡ በጠረፉ የኢትዮጵያ ክፍል የተጀመረው ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ወደ መሃል ከተማ በሚያስደንቅ ፍጥነት እየገሰገሰ ይገኛል፡፡
ይህ ሁሉ ሲሆን እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች እና ምእመናን ከዛሬ ነገ ጉዳዮን የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ይፈቱታል በሚል ተስፋ የየመንግስት ተቋሙን በር ስናንኳኳ ቆይተናል፡፡ ቢሆንም ጩኽታችንን በሚፈለገው ፍጥነት የሚሰማ የሚፈታም ሆነ መልስ የሚሰጥ አካል አልታየም፡፡ ከዚህም ሲያልፍ ለሁሉም ችግር ኃይል እና ነውጥ መፍትሔ ተደርጎ በሚወሰድበት በዚህ ዘመን ለሰላም እና ለአገር ባለን ጥልቅ ፍቅር ሕጋዊ ጥያቄ አቅርበን በሕግ ከተሾመው ሕጋዊ አካል ሕጋዊ መፍትሔ መፈለጋችን በሚያሳዝን ትርጉም እየተሰጠው እና ከፍርሃት እየተቆጠረ መሳለቂያ ከመሆን የዘዘለ ጠብ የሚል መፍትሔ ሊመጣ አልቻለም፡፡
በመሆኑም እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዲስ አበባ ከተማ የምንገኝ ካህናት፣ የሰባኪያን እና ዘመሪያን ኅበረት፣ የሰንበት ትምህርት ቤቶች አንድነት ፣ የመንፈሳዊ ማኅበራት ማኅበራት፣ የወጣቶች እና የጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት፤ የነገረ መለኮት ምሩቃን እና የመንፈሳዊ ኮሌጅ ተማሪዎች ኅብረት፡ በመስከረም 4 ቀን 2012 ዓ/ም ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ጥሪ ማድረጋችን ይታወቃል፡፡
ይህ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ከቀረበበት ማግስት ጀምሮ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ራስ ከሆነው ከቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ጀምሮ፣ በአገርም ይሁን በውጩ ዓለም ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ልጆች ሁሉ በአንድ ልብና መንፈስ በታላቅ ቁጭት ያሳየውን የመንፈስ ዝግጅት እና ተነሳሽነት በቃላት ሊገልጹት ከሚችሉት በላይ ነበር፡፡ ከብረት የጠነከረው ይህ የኦርቶዶክሳዊያን ኅብረት እና ተነሳሽነት እናቱ ስትታመምበት እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ አርፎ እንደማይተኛ እና የትእግስቱን ያህል ቁጣውም ምን ያህል የገዘፈ እንደሆነ ለብዙዎች ትልቅ ትምህርት የሰጠ እንደሆነ ሁሉም የተረዳው እውነታ ነው፡፡
በተጨማሪም ስለ አገር ሰላም፣ ስለ ሕዝቦች አንድነት፣ ፍትሕና እውነተኝነት የሚገዳጋቸው የሌሎች እምነቶች ተከታይ ወንድም አኅቶቻችን ሁሉ ህመማችንን ተጋርተው ከጎናችን እንደሚቆሙ እየገለጹልን ይገኛሉ፡፡
ዛሬ በጋራ መሰለፋችን እና ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ክብር በአንድ መቆማችን በብዙ ልመና ሊከፈቱ ያልቻሉ ጠንካራ በሮችን ለማስከፈት ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት አስተባባሪ ኮሚቴው
1. ጳጉሜ 5/ 2011 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስተር ጽ/ቤት ተወካይ፣ ከፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ ከአዲስ አበባ ም/ከንቲባ እና ጽ/ቤት ተወካዮች ጋር
2. ጳጉሜን 6/2011 ከኢ.ፌ.ድ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር
3. መስከረም 2/2012 ዓ/ም ከኦሮምያ፣ ከደቡብ፣ ከአማራ፣ ከሶማሌ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ጋር በአካል ተገናኝተን ውይይቶችን የጀመርን ሲሆን ከሐረሪ እና ቤኒሻንጉል ክልሎች እና ከድሬዳዋ መስተዳድር ጋር ለውይይት ቀጠሮ ተይዟል፡፡
4. መስከም 2/2012 ዓ/ም ከፌድራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ አዲስ አበባ፣ ኦሮምያ፣ አማራ፣ሱማሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ ድሬዳዋ እና ሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ በነዚህ ውይይቶችም ከአሥር ቀናት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ኮሚቴው ይዞት የተነሳውን እና ቤተ ክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለመፍታት በየክልሎቹ ዝርዝር ማስረጃ ቀርቦ ውይይት እንዲደርግባቸው እና ለጥቄዎቹምምላሽ እንዲሰጣቸው እና በቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ከላይ ከተጠቀሱት የመንግስት አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በባለቤትነት ችግሩን ለመፍታት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ .
በመንግስት ጥያቄያችንን ሁሉ ይመልሰዋል የሚል እምነት ባይኖረንም በየደረጃው ያሉ አካላት ቸልታ እና የማናለብኝነት ስሜት ወጥተው ለቤተ ክርስቲያናችን ዘብ ሲቆም መመልከት እንሻለን፣ አገራችን ደጋግመን እንደምለው አንዳንዱ የፈለገውን ከሕግ የተጻረረ ተግባር በተለይ በኦርቶዶክሳዊያን ላይ እየፈጸመ ያለአንዳች ጠያቂ የሚኖርባት ሌላው ደግሞ ስለአገር እና ስለአንድነት በሚወስደው ኃላፊነት የተሞለበት አካሄድ እየተገፋ ከሌሎች ጋር ሲገነባት በኖራት አገር ላይ ባይተዋር ሆኖ የሚሰደድባት አገር መሆኗ ተቋጭቶ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ እጁን ያነሳ ሁሉ የሚጠየቅባት፣ ጣቱን የቀሰረው ሁሉ የሚሰበስብባት ለፍትህ የሚተጋ መንግስት ያለባት አገር ስትሆን መመልከት ሕልማችን ነው፡፡
እየጮህን ያለነው የኦርቶዶክሳዊያን ብቻ ሰላም ይከበር ብለን አይደለም፣ የእምነት ነጻነት ሰፍኖ አገራችን በእምነታቸው የተነሳ የተደፉ አንገቶች ቀና ብለው ሁሉም በመከባበበር የሚኖርባት ሰላማዊ አገር ስትሆን ለመመልከት ነው፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ከራሳችን እምነት ተከታዮች ጎን ብቻ ሳይሆን በእምነታቸው የተነሳ ከሚገፉት ጎን ሁሉ በማስመሰል መንፈስ ሳይሆን ከአያት ቅድም አያቶቻችን በወረስነው ለፍትህ የመወገን መንፈስ አብረን እንቆማለን፡፡ ለዚህ ነው ጉዟችን ኦርቶዶክስን ብቻ ሳይሆን አገርን ጭምር ለመታደግ የታለመ ነው የምንለው፡፡ በመሆኑም ስለሃይማኖታችን እና ሥለአገራችን ሰላም ስንል እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎቻችን እንኪመለሱ ድረስ ትግላችንን በሰላማዊ መንገድ እንደምንቀጥል ቃላችን የጸና ነው፡፡
የተከበራችሁ ኦርቶዶክሳያን እና ኦርቶዶክሳዊያት በዚህ መንፈስ እና ዓላማ ተቃኝቶ የተጀመረው የኅብረት ጉዟችን ከገዳም እስከ ከተማ ድረስ ካሉ አባቶች ጋር በመመካከር እና በጸሎታቸው በመታገዝ ከዚህ አድርሰነዋል፡፡ በብዙዎቻችሁ ውስጥ ያለው የመንግስት አካላት ቃል ከመግባት የዘለለ እርምጃ ላይሄዱ ይችላሉ የሚለው ስጋት ግን በእኛም ውስጥ ስላለ፤ ከላይ ያልናቸውን ጥያቄዎቻችንን በቅድመ ሁኔታ ጭምር አቅርበን እስክንወያይ እና የሚመጣውን ተግባራዊ ለውጥ ለመመልከት እስክንበቃ ድረስ ለመስከረም 4 ቀን 2011 ዓ/ም የጠራነውን ሰላማዊ ሰልፍ በሁለት ወራት በመግፋት የተገባልን ቃል የማይተገበር ከሆነ አሊያም የሚያረካ ካልሆነ ለጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ/ም ሰላማዊ ሰልፉ የሚደረግ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
እኛ የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች በሚደረገው በየትኛውም ውይይት ላይ ከራሳችን ፍላጎትም ይሁን አንዳንዶች ከሚሰጉት የፍርሃት መንፈስ በጸዳ ስሜት የቤተ ክርስቲያናችንን እና የእናንተን የእምነቱን ተከታይ ኦርቶዶክሳያን ፍላጎት እና ጥያቄ ብቻ አስቀድመን የምንቆም መሆናችንን በህያው እግዚአብሔር ስም ቃል እየገባን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ልጆች ሁሉ ያሳያችሁት ተነሳሽነት እና ኅብረት ሳይሸራሸፍ ለችግራችን ሁሉ ቁልፍ መፍትሔ በሆነው ጸሎታችሁ፣ በሃሳባችሁ እና በቻላችሁት ነገር ሁሉ ከጎናችን እንድትቆሙ በእናት ቤተ ክርስቲያን ስም ጥቄያችንን እናቀርባለን፡፡
በዚህ አጋጣሚ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በምናደርገው እና በምናቀርበው ጥያቄ ዙሪያ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር የምንመካከርባቸው ሰፋፊ መድረኮችን የምናዘጋጅ እንዲሁም ቢያንስ በአሥራ አምስት ቀን አንድ ጊዜ የተለያዮ መንፈሳዊ እና ሕዝባዊ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የእያዳንዱን የውይይት ሂደት፣ውሳኔ፣ውጤት እና ቀጣይ አቅጣጫ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ምእመናን እና የኦርቶዶክሳዊያን ሰላም እና ድኅንነት የሚያስጨንቃቸው አካላት ሁሉ የውይይቱ አካል እንዲሆኑ ለማድረግ የምንጥር መሆናችንን ቃል እንገባለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የቤተ ክርስቲያናችንን እና የአገራችንን ሰላም ይመልስልን!!!!
መስከረም 4 ቀን በአዲስ አበባ የተጠራው የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ
መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ


Monday, September 9, 2019

ሰበር ዜና - ጅማ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ዛሬ ጥቃት ለመፈፀም ተሞክሯል።የሽብር ጥቃት እየደረሰ የመንግስት ለዘብተኝነት ብዙዎችን አስቆጥቷል።


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች በደረሰባቸው በደል ሳብያ -
 • ለመንግስት አቤት ለማለት የሄዱ ጳጳሳት በቂ ምላሽ ሳያገኙ መመለሳቸው እና ይህንን ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣው መግለጫ በመንግስት ሚድያዎች በሚገባ ሳይተላለፍ ሶስተኛ ቀኑን ማሳለፉ።
 • እራሱን የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ  በማለት የሚጠራው ቡድን እንደ ቅዱስ ፓትርያሪኩ እራሱን ሰይሞ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት በኦኤምኤን ቴሌቭዥን ሲያስተላልፍ መታየቱ፣
 • በጅማ በአደባባይ ዛሬ ሰኞ ጳጉሜን 5 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት ለማቃጠል የተደረገው ሙከራ እና ምሽቱን የጅማ ሕዝብ ወጥቶ ቤተ ክርስቲያኑን እየጠበቀ መገኘቱ ሁሉ ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሷል።
ቅዱስ ሲኖዶስ ወቅታዊውን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ላይ አስቸኳይ ጉባኤ ካካሄደ በኃላ ጳጕሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ በመግለጫው ተራ ቁጥር 4 ላይም  የሚከተለው ጥሪ ለመላው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች ተላልፏል፡፡
“እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ በሀገራዊ የኃላፊነት ስሜት ታግሶ እና ችሎ፤ ሞቱ፣ እሥራቱ፣ ዛቻው፣ ስደቱ እና እንግልቱ ሳይበግረው ሀገር በአንድነት እና በፍቅር እንዲሁም በመተሳሰብ እንድትቀጥል ታሪክ የማይረሳው መሥዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን አገልጋይ ካህናት እና መላውን ምእመናንን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በአጠቃላይ መላው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ላሳያችሁት ትዕግስት የተመላበት ሀገራዊ ኃላፊነት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያመሰገነ እንደ አሁን ቀደሙ ሁሉ ትዕግስት የተመላበት ሀገራዊ ኃላፊነታችሁ እንደተጠበቀ ኾኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን፣ ወደፊትም ሊደርስ የታቀደውን ግፍ እና ጥፋት በአንድነት እና በኅብረት ከእኛ ከመንፈስ ቅዱስ አባቶቻችሁ ጋር በመሰለፍ በጽናት ቤተ ክርስቲያናችሁን እንድትጠብቁ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡”

ቅዱስ ሲኖዶስ በሰጠው መግለጫ መሰረት ኦርቶዶክሳውያን የሀገሪቱን ሕግ አክብረው የደረሰባቸውን ግፍ ለማሳሰብ ለመስከረም 4 ቀን ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ተገቢውን ፈቃድ ጠይቀዋል።የሰልፉ አስተባባሪዎች የአዲስ አበባ አስተዳደርን ለማስፈቀድ በጠየቁት ጥያቄ ላይ እንደ ገለጡት ሰልፉ ሶስት ዓላማዎችን የያዘ ነው።እነርሱም -

1ኛ / በካህናት፣ ምእመናን እና ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለመቃወም፣ ለሁሉም አካላት ለማሳወቅ እና እንዲቆም ለመጠየቅ፣
2ኛ/ አጥፊዎች በሕግ እንዲጠይቅ እና በቀጣይም ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይደርስ መንግሥት ሕጋዊ ዋስትና እንዲሰጥ፣
3ኛ/ በዚህ ጥቃት መስዋዕትነት ለተቀበሉ አካላት ቋሚ መታሰቢያ እንዲቆም፣ በሃይማኖታቸው ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ነበሩበት እንዲመለሱና ለሚገባው አካል ተገቢው ካሳ እንዲከፈል ለመጠየቅ የሚሉት ናቸው።

የሰልፉ አስተባባሪዎች-  
★ የሰ/ት/ቤቶች አንድነት፤ 
★ የመንፈሳዊ ኰሌጅ ተማሪዎችና ምሩቃን፤ 
★ በሰ/ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን፤ 
★ የወጣቶችና ጎልማሶች ማኅበራት ኅብረት፤
★ የሠለስቱ ምዕት ማኅበራት ኅብረት፤
★ የአእላፋት ድምፅ የካህናትና ምእመናን ተናሥኦት ኅብረት፤
★ የጽዋ ማኅበራት 

ሲሆኑ ሰልፉ ፍፁም ሰላማዊ የማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተቀጥላ ያልሆነ፣ ሆኖም ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የተፈፀሙ የሽብር ድርጊቶች ሁሉ እንዲቆሙ መንግስት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያሳስብ ነው። 


በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው በደል ለማስቆም መስከረም 4 ቀን የሚደረገው ሰልፍ ዓለም አቀፍ መልክ ይዟል።ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጣውን መግለጫ በመደገፍ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የሚደርሰው በደል መቆም አለበት በሚል በጀርመን እና በስዊድን የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦሮቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት መግለጫ ያወጡ ሲሆን መስከረም 4 በተመሳሳይ ቀን በሰሜን አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እና በጀርመንም ሰልፉ እንደሚደረግ ተሰምቷል።በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቆንስላ ባለባቸው በሎሳንጀለስ እና ሚኒሶታ ተመሳሳይ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተሰምቷል።

ኦርቶዶክሳውያን ለታወጀባቸው ሽብር በዋናነት ተጠያቂ የሆኑት የፅንፍ የሃይማኖት እና የብሔር ቡድን ተጠያቂ ሲሆን በውስጥ ፅንፈኛ ብሔርተኞች እና የአካባቢው ሽብርተኛ ቡድኖች እንዳሉበት ይጠረጠራል። ዓላማው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ማዳከም እና ከሕዝቡ መነጠል በመቀጠልም ሙሉ በሙሉ ለመምታት መሆኑ በብዙ ማስረጃዎች የተረጋገጠ ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ ግን መንግስት አሁንም ተገቢውን ምላሽ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አለማድረጉ እና ግልጥ የሆነ የሽብር ሥራ የሚሰሩትን የጦር ሰራዊቱ አስፈላጊውን ፀጥታ የማስከበር ሥራ እንዳይሰራ ተገቢው መመርያ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አለመሰጠቱ እንደ ትልቅ እንቅፋት ተቆጥሯል። በመሆኑም ቤተክርስቲያኒቱን እና ከሃምሳ ሚልዮን በላይ የሚሆነውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሀገሪቱን አደጋ ላይ የሚጥል አሰራር ከመንግስት እየታየ ነው።

በመሆኑም ኦርቶዶክሳውያን ጉዳዩን በቀላሉ ተመልክተው እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡበት ጉዳይ ሳይሆን ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሰላማዊ መንገድ ለቤተ ክርስቲያኑ ዘብ መቆም ያለባቸው እጅግ ወሳኝ ወቅት አሁን ነው።ተዋህዶ  ሃይማኖቴ መዝሙር (ቪድዮ)


ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

Sunday, September 8, 2019

በዘር የሚያምኑ ሚድያዎች ዕድሉ እስከተሰጣቸው ድረስ የሩዋንዳ ችግር ኢትዮጵያ በር ላይ እንደሆነ ማወቅ አለብን።ኢትዮጵያ ''ሲሬስ'' ችግር ውስጥ ገብታለች:: አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ኦስሎ፣ኖርዌይ የተናገሩት (ጉዳያችን ልዩ ዘገባ -Gudayachn exclusive)


ከጉባኤው ተሳታፊዎች በከፊል 

ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ጳጉሜን 2/2011 ዓም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የቀድሞው አርበኞች ግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ በኦስሎ፣ኖርዌይ የምስጋና ዝግጅት ተዘጋጅቶላቸው ነበር።በዝግጅቱ ላይ ቁጥሩ ከፍ ያለ የኖርዌይ ነዋሪዎች የተገኙ ሲሆን በዝግጅቱ ላይ የቀድሞው አርበኞች ግንቦት 7 በኖርዌይ ለሚኖሩ እና ባለፉት ዓመታት ለዲሞክራሲ ትግል  አስተዋፅኦ ላደረጉ ኢትዮጵያውያን የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን  የምስክር ወረቀቱን የቀድሞው የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር ዶ/ር ሙሉዓለም እና አቶ አንዳርጋቸው ሰጥተዋል።

በዝግጅቱ ላይ አቶ አንዳርጋቸው በቅርቡ ያሳተሙትን ''ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር'' ቅፅ 1 መፅሐፍ ዙርያ ማብራርያ የሰጡ ሲሆን ከመፅሐፉ ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ ከመስጠታቸው በላይ በወቅታዊ ጉዳይ ዙርያ ያላቸውን ሃሳብ ለተሰብሳቢዎች አካፍለዋል።በእዚህ ዘገባ ላይ በተለይ በዋናነት  በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተናገሩትን እና በተወሰነ ደረጃ ደግሞ በመፅሐፋቸው ዙርያ ያነሷቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ይደረጋል።

ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ በተመለከተ

አቶ አንዳርጋቸው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የገለጡበትን ዓረፍተ ነገር የኢትዮጵያ ጉዳይ ግልጥ ያልሆነ መንገድ ላይ ነው ያለው። የመፍረስ አደጋ ያንዣበባት ለመሆኑ ምክንያቱ ብሔርን መሰረት ያደረገው ህገ መንግስት ነው በሚሉ ዓረፍተ ነገሮች ሲሆን በመቀጠል ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታን በተመለከተ የሚከተሉትን ነጥቦች አንስተዋል።እነርሱም -
 • የማዕከላዊ መንግስት የመምራት ሚና በሌለበት ሁኔታ እና ክልሎች በታጠቀ ኃይል ተጠናክረው እያለ ማንኛውንም ችግር  ለመፍታት አስቸጋሪ ነው።
 • የተረኝነት ስሜት የሚለው ችግር አሁን ቢሰማም ነገ የሚያስበውም እንዳይቀጥል የሚሰራው ሥራ ነው  ወሳኙ።ተረኛ ስሜት ሁሉም ጋር አለ።ኦሮሞው ውስጥ ኦዴፓ የተረኝነት ስሜት የሚያራምድ እንዳለ ሁሉ ዓማራ ውስጥም እንዲሁ አለ።
 • እኔ መቼም አልጋ በአልጋ ላይ ነን ብዬ አላውቅም።እኔ ከእዚህ በፊት እንዳልኩት ለውጡ ትልቁ ስህተቱ በራሱ ኢህአዴግን ይዞ ለለውጥ መነሳቱ በራሱ ስህተት አለው።
 • ትልቁን አጀንዳ ትተን ትንንሾቹ አጀንዳ ላይ ብቻ ከተጠመድን ሳናውቀው ከጠላቶች ጋር እየተባበርን ነው ማለት ነው።
 • ኢትዮጵያ ''ሲሬስ'' ችግር ውስጥ ገብታለች።ከእዚህ በፊትም እንዳስቀመጥኩት በእዚህ የጎጥ ፖለቲካ ከቀጠልን  በፐርሰንት እንዳልኩት 80% አደጋ ውስጥ ስትሆን 20% ነው የመዳን ዕድሏ።
 • የኢትዮጵያ ፈዲራሊዝም ለክልሎች ስልጣን ሰጥቶ ማዕከላዊውን አዳክሟል።ይህ በየትም ዓለም የሌለ ነው።ህንድ ትልቅ የፌድራል አስተዳዳር ያላት ሀገር የክልል አስተዳደሮች መሳርያ የመታጠቅ መብት የላቸውም፣ሌላው ቀርቶ ማዕከላዊ መንግስት የክልል ምክር ቤቶች የወሰኑትን ውሳኔዎች ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት አለው።
 • በዘር የሚያምኑ ሚድያዎች ዕድሉ እስከተሰጣቸው ድረስ የሩዋንዳ ችግር ኢትዮጵያ በር ላይ እንደሆነ ማወቅ አለብን።

 • ኢትዮጵያ ውስጥ ክልሎችን መለያየት እና ሀገር ማድረግ ፈፅሞ አይቻልም።የሚሞክር ካለ ቀጥታ ማባርያ የሌለው ጦርነት ውስጥ ነው የሚገባው።ቼክ እና ስሎቫክ ሲለያዩ በቀጥታ መለያየት የቻሉት ጥርት ያለ ልዩነት ከድንበር ጋር  ስላላቸው ነው።ኢትዮጵያ ውስጥ የተዋሃደ ሕዝብ ነው ያለው።ነገ ተነስቶ አንዱ ክልል ልገንጠል ቢል በማግስቱ ድንበሩ ላይ ያለ ነው ጦርነት የሚከፍቱት።
 • አሁን መሰራት ያለበት ትልቁ ስልታዊ ሥራ ማዕከላዊ መንግስትን ማጠናከር ነው።የታጠቁ የክልል ኃይሎች ትጥቅ መፍታት እና የዘር ፕሮፓጋንዳ የሚነዙ ሚድያዎች መስተካከል አለባቸው።ማዕከላዊ መንግስት ስልጣን በሌለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ እና ሌሎች ስራዎች ሁሉ ከባድ ናቸው።
 • ዓማራን በተመለከተ ''ታርጌት'' ሆኗል ወይ? አዎን! ይህንን እኔ ወያኔዎች ውስጥ ቀድሜ የተናገርኩ እኔ ነኝ። 
 • ኢትዮጵያ ውስጥ ዓማራነት ከኢትዮጵያዊነት የሚለይ ነገድ ማውጣት ከባድ ነው።አማርኛ በራሱ ያሰባሰበው ማኅበረሰብ እንጂ ወደ ነገድ አደገ ማለት አይቻልም።ይህ ነው ኢትዮጵያን እስካሁን እንደ ኢትዮጵያ ሆና ፀንታ እንድትቆም ያደረጋት።
 • ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚባለው ቢያንስ ከሁለት ብሔር የወጣ ውሁዱ ኢትዮጵያዊ እስከ 40% መድረሱ ነው የሚነገረው እና ኢትዮጵያዊነትን ትተን ወዴት ነው የምንሄደው?


ለአቶ አንዳርጋቸው ስጦታ ሲበረከትላቸው 

ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር በተሰኘው መፅሐፍ በተመለከተ የሚከተለውን ብለዋል -


 • መፅሐፉን እንድፅፍ ያነሳሳኝ ከ1966 ዓም ጀምሮ የተንሳው እንቅስቃሴ መሰረቱ ምን እንደሆነ ለመግለጥ ነው ከ1870 የጀመርኩት።
 • መፅሐፉን በተመለከተ የሚነሱ ሃሳቦች በትክክል አንብቦ ወጥ የሆነ ሂስ ሳይሆን ብጥስጣሽ  ሃሳቦች ናቸው ያየሁት። ከእዚህ የተገነዘብኩት ብዙዎች መፅሐፉን አላነበቡትም ብዬ ገምቻለሁ።
 • መፅሐፉ ላይ ከተነሱት ሃሳቦች አንዱ ''የአያቶቼ ጥጃ ማሰርያ'' የሚለው አዲስ አበባን በተመለከተ የጠቀስኩት ላይ ሃሳቡን ብዙ ሰው የተገነዘበው አይመስለኝም።እኔ ሃሳቤ አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ሆና ሳለ ከተማዋ ላይ የሌለ የይገባኛል ጥያቄ  እና ሌሎች ቃላት የሚያነሳው ከአዲስ አበባ በርቀት ወለጋ ወይንም አርሲ ያሉ ናቸው።እኔ ያልኩት ከተማው ጉዳይ ያገባኛል ለማለት ከሆነ እዚሁ የኖርኩት እኔም የሚመለከተኝ የቅርቡ ሰው አያቶቼ ጥጆች ያሰሩበት እያለሁ የሩቁ ሰው ለምን መለያየት ይፈጥራል ከሚል ነው።ይህ ነው የሃሳቡ ጭብጥ።
 • አዲስ አበባ የሰፋችው በሠራዊት እነርሱን ተከትሎ በመጣው የሴተኛ አዳሪ፣ሰራተኛው ነው የሚለውን ከራሴ ያመጣሁት ከራሴ አይደለም ከራስ ዕምሩ የወሰድኩት ነው።ይህ ሃሳብም በከተማው ባለቤትነት ካነሳችሁ የከተማው ባለቤትነት እና ከተማዋን የገነቡት ዝቅተኛው የከተማው ነዋሪ ነው፣ይህንን ሕዝብ ወዴት ልትገፉት ነው? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንዲሆን ነው።
 • መፅሐፉን እስከመጨረሻው ያነበበ ሰው የሚረዳው እና እኔም ላንፀባርቀው የሞከርኩት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ነው።መፅሐፉን አንብቡት እና ሂስ ብትሰጡ ደስ ይለኛል።መፅሐፉ ላይ ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮች አሉበት። የቻይናው ማኦ ሴቱንግ በፃፈው ላይ ከጃፓን ጋር ለመዋጋት እንደ ኢትዮጵያውያን የደፈጣ ውጊያ ማድረግ ከቻልን ብቻ ነው ልናሸንፍ የምንችለው ያለበት እና ሌሎች በርካታ ነጥቦች መፅሐፉ ውስጥ ተካቷል።
በመጨረሻም አቶ አንዳርጋቸው በመርሃግብሩ ከመዘጋቱ በፊት የተዘጋጀላቸው ልዩ ስጦታ ተበርክቶላቸው የመርሃግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።ጉዳያችን GUDAYACHN
 www.gudayachn.com

Friday, September 6, 2019

በኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤ/ክርስቲያን ላይ ሰሞኑን የነበረው ሁኔታ ለቤተክርስቲያን የደወል ድምጽ ነው::ወደፊት ምን ይሰራ?


ጉዳያችን GUDAYACHN
ጳጉሜን 1/20119 ዓም (ሴፕቴምበር 7/2019 ዓም)

ያሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሲኖዶሳዊ እውቅና ውጪ በኦሮምያ ክልል የቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ነን ያሉ በእነ ቀሲስ በላይ የሚመራው ቡድን ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል።በሰላሳ ቀናት ውስጥ ምላሽ ይሰጠኝ የሚል የማስፈራርያ መግለጫ የሰጠው ኮሚቴ መግለጫ ከመስጠቱ በፊት መግለጫ ይሰጥበታል በተባለው አዳራሽ (በኦሮምያ የባህል ማዕከል) ወጣቶች ጉዳዩን በመቃወም ተሰብስበው ከሄዱ በኃላ፣ ወጣቶቹን ለመበተን ብቻ መግለጫው ቀርቷል በሚል የማታለያ ንግገር ወጣቶቹ እንዲሄዱ ከተደረገ በኃላ፣ኦኤምኤን  እና አዲስ ቲቪ ወደኃላ ቀርተው መግለጫው እንዲሰጥ መደረጉ ለማወቅ ተችሏል።

መግለጫው ሕጋዊ ሰውነት ያላትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀደም ብላ በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት በኦሮምያ የቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ የተባለ አካል እንደማታውቅ አስታውቃ ነበር። ጉዳዩን ተከትሎ ቅዱስ ሲኖዶስ ከነሐሴ 30 ጀምሮ በተፈጠረው ቤተክርስቲያንን የማወክ ሙከራ ዙርያ ስብሰባ የተቀመጠ ሲሆን በእዚሁ ዕለት የኦሮምያ ክልል  ምክትል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ተወካይ ሙ/ጥ/ዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተገኙ ሲሆን በቀጣዩ ቀን ጳጉሜን 1 ቀን ብፁዓን አባቶች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ጋር በቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ዙርያ ተወያይተዋል።

በኦሮምያ ክልል የተቀጥላ ቤተ ክህነት አደራጆች ጀርባ 


በኦሮምያ ክልል  የተቀጥላ ቤተ ክህነት ለማደራጀት  የተገዳደሩት አካላትን በመደገፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸው ያለበት አካሎች የመንግስት ባለስልጣናት፣የፅንፍ ጎሳ ፖለቲካ አራማጆች፣የአክራሪ እስልምና ተከታይ የሆኑ እና የህወሓት አክትቪስቶች አሉበት።በመሆኑም እነኚህ አካላት በፕሮፓጋንዳ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደር መገዳደር ሽፋን ሲሰጡ ተስተውለዋል።


ከእዚህ በተጨማሪ በቅርቡ የታየው በፅንፈኛ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና በህወሓት ቡድን መሃል እንደአገናኝ ሆነው የሚንቀሳቀሱ አካሎች በኦሮምያ የቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ እያለ እራሱን የሚጠራውን ቡድን ሲያወድሱ ተስተውሏል። ለምሳሌ የሰሜን አሜሪካ የትግራይ ልማት ማኅበር ሰብሳቢ አቶ አሉላ  በኦኤምኤን ቴሌቭዥን ላይ ቀርቦ ሲናገር  የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ በኢትዮጵያ ያሉት ቤተ እምነቶች ''የደርግ ቤተ እምነቶች ናቸው'' በማለት ሲነቅፍ ተሰምቷል።


ቀጣይ የቤተ ክርስቲያን አደጋዎች

አሁን ባለው ሁኔታ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ግልጥ በሆነ አደጋ ላይ እንደሆነች እየታየ ነው።ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ማደርያ ሆና አደጋ ላይ ነች ማለቱ በራሱ አስቸጋሪ ቢሆንም፣በሰው ሰውኛው የመረዳት አቅም ግን ግልጥ የሆኑ አደጋዎች ከፊቷ ተደቅነዋል።የመጀመርያው አደጋ በኦሮምያ ክልል ቤተ ክርስቲያኒቱን  ለማወክ የሜፈልጉ ቡድኖች  ሙከራ ሲሆን፣ ሁለተኛው  ቤተ ክርስቲያኒቱን በኃይል ለመቆጣጠር የሚደረግ ጥረት ነው።ይህ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመቆጣጠር የመሞከር ሂደት ከጀርባው ሌላ ኃይል ያለ በማስመሰል እና ተራ ውንብድና አስመስሎ በማይፈልጉት ካህን ላይ ጥቃት ማድረስን ሁሉ ይጨምራል።ባጭሩ ተራ ዱርየዎች በማደራጀት የሚፈልጉትን ለማስፈፀም መሞከርን ሁሉ ይጨምራል ማለት ነው።በእዚህ ሂደት ውስጥ ግን መንግስት በአግባቡ መቆጣጠር ካልቻለ የቤተ ክርስቲያን ጉዳት ብቻ ሳይሆን የሚከተለው የሰው እና የንብረት መጥፋትም ሁሉ ሊያስከትል ይችላል። ለእዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት የታችኛው የመንግስት መዋቅር ተገቢ ጥበቃ ለቤተ ክርስቲያን እያደረገ አለመሆኑ ነው።

ወደፊት ለችግሩ መፍትሔነት ምን ይሰራ?


የሚከታተሉት ዋና ዋና ተግባራት መሰራት የሚገቡ ስራዎች ቢሆኑ ተገቢ ይመስለኛል። እነርሱም  -


ቤተ ክርስቲያን 


 • በፍጥነት ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ልዕልናዋን መልሳ ማስከበር።በሀገር ውስጥ በራሷ መርሃግብር በመሄድ ሃገራዊ የእርቅ ፣የሰላም እና የልማት መርሃግብሮች እያዘጋጀች መሄድ ይኖርባታል፣ለምሳሌ በትግራይ ሕዝብ እና በዓማራ መካከል ሕዝብ ለሕዝብ የማገናኝት ሥራ፣የፀጥታ አደጋ ይኖርባቸዋል በተባሉ ቦታዎች ቀድማ በመገኘት፣
 • ለእዚህም ውስጣዊ አስተዳደሯን በአጭር ጊዜ ማዘመን፣
 • በቤተ ክርስትትያንቱ የገንዘብ ብክነት የሚጠየቁ ሰዎች በቤተክርስቲያኒቱ ፍትህ መንፈሳዊ እና በቤተ ክርስቲያኒቱ ስርዓት መሰረት ብይን እየሰጠች ከቦታቸው እያነሳች ውስጧን ማስተካከል እና በሁሉም የአገልግሎት ክፍሎቿ አቅም ያለው የሰው ኃይል ማግኘት፣
 • ብቃት ያለው የሚድያ አገልግሎት እንዲኖራት ማድረግ፣
 • የውጭ ግንኙነቷን ማሳደግ ለምሳሌ ከእህት አብያተ ክርስቲያናት ጋር፣
 • ሀገር አቀፍ የወጣቶች መርሃ ግብር በብዛት ማዘጋጀት 
 • በማኅበራዊ ዘርፍ አገልግሎቷን ማስፋት፣
ከምእመናን ከሚጠበቁት ውስጥ 
 • ምእመናን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ  በየትኛውም የቤተክርስትያኒቱ ጉዳይ መከታተል ፣
 • በቤተ ክርስቲያን እና ልጆቹ ላይ ምንም አይነት የማስፈራርያ አደጋ ቢፈፀም በፅናት ከቤተ ክርስቲያን  ጋር መቆም እና መመከት፣
 •  ምዕመናን ከፖለቲካ ጉዳይ ራሳቸውን ማራቅ አቁመው በብዛት እና በጥራት ወደ ፖለቲካው ዓለም ገብተው ሀገራቸውን የመምራት እና ኃላፊነት የመውሰድ እንቅስቃሴ ማድረግ፣
 • የቤተ ክርስቲያን የሕግ ክፍል  በአዲስ መልክ ማጠናከር እና ጀረጃውን ከፍ  እንዲል ማስድረግ።
የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው።

ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ርስቲያንን የማያውቁ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ ጥላቻ ያለባቸው ግለሰቦች  በኢትዮጵያ የፖለቲካ  የስልጣን ተዋረድ ውስጥ ስልጣን ላይ በብዛት መኖራቸው ቤተ ክርስቲያንን እየጎዳ ለመሆኑ ምንም አሌ የሚባል ጉዳይ የለውም።ሁኔታው ለቤተ ክርስቲያን ደወል ነው።ደውሉን ሰምቶ ቤተ ክርስቲያንን ለማገዝ መነሳት ከምእመናን ይጠበቃል።

የዓለም ማዕበል ጎርፍ 

ጉዳያችን/Gudayachn
ሴፕቴመብር  7/2025 ዓም) 

በኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ዙርያ አዲስ ዜና - በኦስሎ፣ኖርዌይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ''በኢትዮጵያውያን የጋራ መድረክ በኖርዌይ'' አሰባሳቢነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የኖቤል ሽልማት ዙርያ ከአቀባበል እስከመስተንግዶ ባለው ዝግጅት ዙርያ ተወያዩ (Gudayachn Exclusive)

በስብሰባው ላይ ከተሳተፉ የኦስሎ ኖርዌይ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን በከፊል  ጉዳያችን / Gudayachn  ጥቅምት 8/2012 ዓም (ኦክቶበር 19/2019 ዓም) የኢትዮጵያ ስም እንዲልቅ   የቀዳማዊ አፄ ኃ...