ጉዳያችን/ Gudayachn
መጋቢት 19፣2009 ዓም ( march 28,2017)
መጋቢት 19፣2009 ዓም ( march 28,2017)
የእስያ መሰረተ ልማት እና መዋለ ንዋይ ባንክ ቦርድ አባላት
(Foto: AIIB)
በአለማችን ላይ መሰረታዊ የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከመቀየር አንፃር የገንዘብ ተቋማት ያላቸው ሚና ቀላል የሚባል አይደለም።ላለፈው ግማሽ ክ/ዘመን እና በተለይ ከ 1980 ዎቹ እንደ ´አውሮፓውያን አቆጣጠር ማለትም ከሶቭየት ህብረት መበተን በኃላ የዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ተፅኖ በአፍሪካ፣ላቲን አሜሪካ እና ሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ውስጥ ቀላል አልነበረም።በተለይ በ1990ዎቹ ውስጥ የነበረው የዓለም ባንክ መዋቅራዊ ለውጥ ፕሮግራም ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙ አፍሪካ ሀገር ህዝቦችን ሕይወት አመሰቃቅሎ እና ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል።የመዋቅራዊ ለውጥ መርሃ ግብሩ ጉድለት በእራሱ በዓለም ባንክ የተወቀሰው በርካታ ማኅበራዊ፣ምጣኔ ሃብታዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ካስከተለ በኃላ መሆኑ ሌላው ህመም ነበር።
ባለፈው ዓመት መጀመርያ ላይ ከወደ ቻይና የተሰማው የግዙፍ ዓለም አቀፍ ባንክ ምስረታ ግን አዲስ ታሪክ ይዞ መጥቷል።ከአንድ ዓመት ከሶስት ወራት ዝግጅት በኃላ እንደ ኤውሮፓውያኑ የጊዜ ቀመር በጥር ወር 2016 ዓም በሩን የከፈተው የእስያ መሰረተ ልማት እና መዋለ ንዋይ ባንክ (Asian Infrastructure Investment Bank - AIIB)መሰረታዊ ፍልስፍናው ግልፅነት፣ተጠያቂነት፣ከጥገኝነት የፀዳ እና አረንጓዴ ልማትን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ይናገራል።
በሌላ በኩል ባንኩ የዓለም ባንክ ላለፉት አመታት ሲወቀስባቸው የነበሩትን የሀገሮች የተጭበረበረ የምጣኔ ሀብት እድገት ሪፖርት ማውጣት እና ሙስና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በእዚህ ባንክ እንዳይታዩ ከወዲሁ መሰረት የጣለ ይመስላል።በመሆኑም የባንኩ ቀዳሚ መመርያ መልካም አስተዳደር (Good governance) መሆኑን እና የተሳሳተ ሪፖርት ይዞ መውጣት ፈፅሞ እንደማይታሰብ ባንኩ በመተዳደርያው ላይ ያትታል።ይህ ምን ያህል ተአማኒነት አለው? የሚለው እራሱን የቻለ ጥያቄ ነው።እርግጥ በሙስና ደረጃ ቻይና የተሻለ ወሳኝ እርምጃ የምትወስድ ሀገር ነች።ይህንን ግን አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ ሀገሮች ላይ ታደርገዋለች ወይ? የሚለው ጥያቄ እራሱን የቻለ መልስ ይፈልጋል።
"ቀን እባብ ያየ ምሽት ላይ በልጥ ይደነብራል" ነው ነገሩ እና የቻይና "ስግብግብነት" የሚታይበት የአፍሪካን ምጣኔ ሀብት የመቆጣጠር አባዜን ላለፉት አስር አመታት የተመለከተ ሰው ሚዛናዊነትን መጠበቅ ባይችል አይፈረድበትም።
ባጠቃላይ ግን የዓለም ባንክን የሚገዳደር ግዙፍ ከጀርባ በቻይና የተደገፈ ነው የተባለ የገንዘብ ድርጅት አድማሱን እያሰፋ ነው።አባል ሀገሮቹ ከአውሮፓ እንደ ጀርመን እና ደንማርክ፣ሩስያ ከመካከለኛው ምስራቅ እንደ ኢራን እና እስራኤል ከሩቅ ምስራቅ ቻይና እና ህንድ እንዲሁም አውስትራሊያ አህጉርን ጨምሮ እና ካናዳ እና ሌሎች ሀገሮችን አካቶ አቅሙን እየገነባ ነው።አሜሪካ እና ጃፓን አባልነት ላለመግባት ያንገራገሩበት ይሄው ባንክ እንግሊዝ፣ስዊዘርላንድ፣ግብፅ እና በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀብሏል።ዋና መስርያ ቤቱን በቻይና ዋና ከተማ ቤጂንግ ፋይናንሻል መንገድ ቁጥር ቢ9 ያደረገው ይሄው ባንክ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ብዙ ሀገሮችን ወደ አባልነት እያሰባሰበ ነው።
ከእዚህ በታች በባንኩ እድገት እና የምዕራቡ ዓለም በተለይ የአሜሪካ ስሜት ዙርያ የተደረገ አጭር የቪድዮ ውይይት ነው።
የውይይት ርዕስ : - "አሜሪካ ለምን በእስያ መሰረተ ልማት እና የመዋለ ንዋይ ባንክ መጠናከር ስጋት አደረባት? " የሚል ነው።
Why is the US so threatened by the rise of the AIIB?
Video source: World Finance Video
የውይይት ርዕስ : - "አሜሪካ ለምን በእስያ መሰረተ ልማት እና የመዋለ ንዋይ ባንክ መጠናከር ስጋት አደረባት? " የሚል ነው።
Why is the US so threatened by the rise of the AIIB?
Video source: World Finance Video
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com