ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Friday, March 10, 2017

የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ የወጣት ዮርዳኖስን ሕይወት እንዴት እንዳመሳቀለው (እውነተኛ ታሪክ እና ቪድዮ)

እውነተኛ ታሪክ 
ጉዳያችን/ Gudayachn 
www.gudayachn.com 
====================
ዮርዳኖስ ከንግድ ሥራ ኮሌጅ በባንክ እና ፋይናንስ ተመርቃ ሥራ ከያዘች አንድ አመቷ ነው።እንደተመረቀች ሥራ የያዘችው ከኮሌጁ ጎን የሚገኘው ባለ አስራ አንድ ፎቁ የቤቶች እና ቁጠባ ባንክ ነው።ዮርዳኖስ ከስራ በኃላ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ቀናት መርካቶ የሚገኘው ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የመዝሙር ጥናት ትሄዳለች።በእየሳምንቱ ቅዳሜ ከሰዓት በኃላ በ8 ሰዓት ላይ በቤተ ክርስቲያኑ የሰንበት ትምሕርት ቤት አዳራሽ የሚዘጋጀው ጉባኤ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቿ ጋር መዝሙር ታቀርባለች።ዮርዳኖስ ስለ ብሔር፣ኤርትራ ስለሚባል ሀገር የምታውቀው ነገር የላትም።እቤት አባት እና እናቷ ስለ ፖለቲካ ሲያወሩ ከመስማት በቀር ነገሩ አይገባትም።ለእርሷ ጧት ሥራ መግባት ከስራ በኃላ ከቦርሳዋ ውስጥ የማይለያትን ነጠላዋን ተከናንባ ቤተ ክርስቲያን ተገኝታ ትምህርት መማር ወይንም በመዝሙር ማገልገል ነው።

ዮርዳኖስ በእንዲህ አይነት ሕይወት ላይ እያለች ነው በ1990 ዓም አንድ ምሽት በለሆሳስ ቤተ ክርስቲያን የተማረችውን መዝሙር እየመላለሰች እያዜመች ነበር አዲስ አበባ አሮጌው አይሮፕላን ማረፍያ  አካባቢ ቶታል ሶስት ቁጥር አውቶብስ ማዞርያ የሚገኘው ቤቷ የደረሰችው።የቤቷን የብረት በር ዘበኛው እንዲከፍትላት ደውሉን ለመደወል ስትል በሩ ክፍት መሆኑን ተመለከተች። በልቧ ዘበኛው ሰፈራቸው የሚገኘው ሱቅ ሲሄድ በሩን ገርበብ አድርጎ እንደሚሄድ ስለምታውቅ እንዳይዘጋበት በማሰብ መልሳ ክፍቱን ትታው ወደ ግቢው ዘለቀች።የእናት የአባቷ ግቢ ተተራምሷል። አባቷ ጋቢ እንዳደረጉ በነጠላ ጫማ፣እናቷ እረጅሙን ቢጃማ እንደለበሱ ቆመዋል ስድስት የሚሆኑ ፖሊሶች እና ሶስት ሲቪል የለበሱ ሰዎች ከእናት እና አባቷ ጋር ድምፃቸውን ከፋ አድርገው ይናገራሉ።ሶስቱ ሲቪል ከለበሱት ሰዎች ውስጥ አንዱ " ምንም ልብስ መቀየር ብሎ ነገር የለም።አሁን ሁላችሁም ወደ ቀበሌ! እዝያ ቃላችሁን ሰጥታችሁ ውሳኔው ይነገራል።የመንግሥታችን ትዛዝ ነው " አለ በትግርኛ ቅላፄ በተሞላ አነጋገር።

ዮርዳኖስ ጉዳዩ አልገባትም እናቷ ልጃቸውን ሲያዩ አቅፈዋት ማልቀስ ጀመሩ።ጥቂት ቆይቶ ግቢው በጎረቤት ሰዎች ተሞላ። ጎረቤቱ እየመጣ ዮርዳኖስን፣ወንድሞቿን እና ወላጆቿን እያየ ለቅሶውን አቀለጠው።ዮርዳኖስ የያዘችውን ቦርሳም እንድታስቀምጥ አልተፈቀደላትም በቆመችበት ከወንድሞቿ፣ወላጆቿ ጋር ወደ ቀበሌ ተወሰደች።ጉዳዩ ለካ የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ኤርትራዊ ደም አለባቸው የተባሉ በሙሉ እየተለቀሙ ወደ ኤርትራ እንዲላኩ ስለተወሰነ ጉዳዩ እቤታቸው መምጣቱ ኖሯል።ዮርዳኖስ መጀመርያ ጉዳዩ የመሰላት የሆነ ወንጀል ተፈፅሞ ያንን ለማጣራት የሚደረግ እንደሚሆን አስባ ነበር።ነገሩ ሁሉ ተረጋግቶ ማታ ተመልሳ የምታጠናውን መዝሙር እና ቅዳሜ ስለሚከበረው የመንፈሳዊ ማኅበሯ ጉዳይ እያሰበች ከቤተሰቧ ጋር ፖሊሶቹ መኪና ላይ ወጣች።በልቧ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ነገሩን ሁሉ ለክፉ አታድርጉት ትላለች።ይህ ሁሉ ጉዳይ ለቤተሰቧ ችግር የማያመጣ ከሆነ በመጪው ቅዳሜ ሻማ ይዛ ልትመጣ ለመርካቶ ተክለ ሃይማኖት ተስላለች።ሆኖም ግን ዮርዳኖስ እና ቤተሰቧ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ከቤት እንደ ቀልድ ወደ ቀበሌ እንደወጡ አልተመለሱም።የሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ነው እና በሁለተኛው ቀን ዮርዳኖስ ከ  ወንድሞቿ እና ወላጆቿ ጋር ኤርትራ ወደተባለችው ምድር  ከተባረሩት 70 ሺዎች ውስጥ ተጨምረው ተላኩ። ዮርዳኖስ የሆነው ሁሉ ሕልም እየመሰላት አብራ ተሰደደች።ለምን እና ማን ይህንን ውሳኔ እንደወሰነ አታውቅም።

በወቅቱ ወደ ኤርትራ የተላኩት ተመልሰው ከኤርትራ ወጥተው ወደ ኬንያ፣የመን እና ሱዳን ተሰደዋል።የተሳካላቸው አውሮፓ እና አሜሪካ ገብተዋል።አንዳንዶቹ ዞረው ተመልሰው ኢትዮጵያ የመጡም አሉ። 

ዮርዳኖስ ስነ ልቦናዋም፣የተወለደችውም የምታውቀውም አዲስ አበባን እንጂ ኤርትራ የምትባል ምድር ናፍቃት አያውቅም።የማያውቁት አገር አይናፍቅም እንዲሉ።ሆኖም ግን ሕወሓቶች  እንደ ቀልድ ቢራ ፉት እያሉ የወሰኑት ውሳኔ ከቤቷ በረንዳ ላይ አስይዞ ከልጅነቷ እየመከሩ ያሳደጉ ጎረበቶቿን በእንባ እያራጨ ወደማታውቀው ምድር ገፋት። ይህ እውነተኛ ታሪክ እና እውነተኛ ስም ነው።

ከእዚህ በታች የምታዩት ቪድዮ በወቅቱ በሕወሓት ውሳኔ ከተባረሩት 70ሺዎች ውስጥ ኤርትራ ሲገቡ የነበረውን ሁኔታ ነው።የሚያለቅሱ አሉ፣ስሜታቸውን ማወቅ ያልቻሉ ነበሩ፣ግራ የተጋቡም ብዙዎች ናቸው።አንዳንዶቹ ያልተከፉ በሚመስል ስሜት እጃቸው ያወዛውዛሉ።ምናልባት ለስነ ልቦና እንደሚሆን መገመት ይቻላል እንጂ በእዚህ ወቅት ማንም ከነበረበት ቦታ ሲሄድ የእዛን ያህል ስሜት ሊኖረው አይችልም።ጉዳዩ አሳዛኝ መልኩ ያመዝናል እና።ዮርዳኖስ እና ቤተሰቧ ከእነኝህ ውስጥ ነበሩ ።ተወደድም ተጠላ የዮርዳኖስ ላይ የደረሰውን የዘመናችን የፖለቲካ ምስቅልቅል የሕወሓት የታሪክ ዶሴ ውስጥ ተፅፎ መጪው ትውልድም ሲያነበው ይኖራል።አንብቦ ምን እንደሚል አሁን ለመገመት አይቻልም።




ጉዳያችን GUDAYACHN

www.gudayachn.com

የመጀመርያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት የነበሩት ክብርት አምባሳደር ሣህለወርቅ ዘውዴን በክብር አለመሸኘት የኢትዮጵያን ክብር ብቻ ሳይሆን ለሴት ልጅ ያለንን የክብር ልኬት የሚያሳይ ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሣህለወቅ ዘውዴ ጉዳዩ የዲሞክራሲ ባሕላችን ያኋልዮሽ ጉዞ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የኢትዮጵያ ታዳጊ ሴትና ወንድ ልጆች የምናስተምራቸው ምንድን ነው? የመጀመርያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሲሰናበቱ እንዴት...