ጀነራል ሰዓረ መኮንን
ዶ/ር አምባቸው መኮንን
- የጀነራል ሰዓረ መኮንን ግድያ ከሀገር ውስጥ ሴራ ይልቅ የውጭ እጅ ምናልባትም የባህርዳሩን ግርግር ቀድሞ የሚያውቅ ግድያ እንዲፈፀም በከፍተኛ የገንዘብ ኃይል አቀናበረው ቢባል የበለጠ ድምፀት ይሰጣል።
===================================
ጉዳያችን/Gudayachn
ሰኔ 17/2011 ዓም (ጁን 24/2019 ዓም)
========================================
አይዞሽ! ኢትዮጵያ
ሰኔ 15/2011 ዓም በባህር ዳር ከተማ የዓማራ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንን እና የርዕሰ መስተዳድሩ የአረጃጀት ዘርፍ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ ተሰውተዋል።በአዲስ አበባ ደግሞ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀኔራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራ መሰዋታቸውም የያዝነው ሳምንት መጨረሻ አሳዛኝ ዜና ነበር።የባህር ዳሩ ግድያ የተመራው በብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ፅጌ መሪነት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ፕሬስ ሴክሬተራት አቶ ንጉሡ ጥላሁን ሰኔ 16/2011 ዓም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
የደረሰው ሁሉ እጅግ የሚያሳዝን ነው።በግድያው ህይወታቸውን ያጡት ሁሉ አሟሟት የሚያሳዝን ቢሆንም የማዕከላዊ ፖለቲካን (ከአክራሪነት በራቀ መልኩ) የሚያራምዱት እና ብዙ በጎ ሕልም የነበራቸው ዶ/ር አምባቸው መኮንን እና ከዘረኘነት የፀዳ ሰራዊት መመስረት አለብን በሚል መርሃቸው የሚታወቁት በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሳይቀር ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የጦር ሰው ጀኔራል ሰዓረ መኮንን ላይ የተፈፀመው ግድያ ከሁሉ የከፋ በሀገር ላይ የተፈፀመ ወንጀል ነው።ኢትዮጵያ በታሪክ ሁሉን ተቃዋሚ እና የተለያየ ሃሳብ አራማጆችን አቅርባ ካለምንም ስጋት እንዲወጡ እና እንዲገቡ ፈቅዳ ባለችበት ዘመን በእዚህ ደረጃ በጥይት ወደመነጋገር ያረጀ እና ያፈጀ ዘመን የመመለስ በሽታ በራሱ ትልቅ ህመም ነው።የጀነራል ሰዓረ መኮንን ግድያ እንዴት ከባህርዳሩ ጋር ተገናኘ? የሚለው ጥያቄ አሁንም የሚጠየቅ ነው።ሁለቱን ለማያያዝ የድርጊቶች ሂደት እስካሁን አልታዩም።
የጀነራል ሰዓረ መኮንን ግድያ ከሀገር ውስጥ ሴራ ይልቅ የውጭ እጅ ምናልባትም የባህርዳሩን ግርግር ቀድሞ የሚያውቅ ግድያ እንዲፈፀም በከፍተኛ የገንዘብ ኃይል አቀናበረው ቢባል የበለጠ ድምፀት ይሰጣል።በእዚህ የውጭ ተንኮል ዙርያ ግን ከህወሓት ዙርያ ካሉ ሰዎች እስከ የትኛውም አክራሪ በእጅ አዙር እጁ አለበት የለበትም የሚለው ወደፊት የሚገለጥ ጉዳይ ነው።በተለይ ጄኔራሉን በመግደል ጦሩ ውስጥ የመከፋፈል ዓላማ ያለው ማንም ኃይል ይህንን ከማድረግ አይመለስም።በሌላ በኩል የዶ/ር ዓብይ አስተዳደር በእንዲህ አይነት ተግባር ተሰማርቷል እያሉ በማኅበራዊ ሚድያ ላይ ትንታኔ ለመስጠት የሚሞክሩ አስቂኞች ግን ብዙ ያልተረዱት ነገር አለ።ይሄውም ሲጀመር ጀነራል ሰዓረ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በለውጡ ሂደት ላይ የኃይል ሚዛኑን በተለይ ከትግራይ ጋር ካለው አንፃር ሁለቱም የምከባበሩ እና አንዳቸው ለአንዳቸው አስፈላጊ መሆናቸውን በደንብ የተረዱ ናቸው።በመቀጠል ሁለቱም በወታደራዊ ዲስፕሊን ጥሩ ደረጃ ያላቸው እና በመርህ ላይ የሚያምኑ ናቸው።ስለሆነም የጀነራል ሰዓረ ሞት ከህወሓት ይልቅ ሀዘኑ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ነው። ይልቁንም ህወሓቶች ጄኔራሉን ህወሐትን እንደከዱ አድርገው በማኅበራዊ ሚድያ ሰፊ ዘመቻ የከፈቱባቸው ሳሞራን በጡረታ አስወጥተው እርሳቸው ከአቢይ ጋር ይታያሉ በሚል እንደነበር የአንድ ዓመት ትዝታ ነው።አሁን ''የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም '' የደረሰውን ሁሉ በሃዘን እና በቁዘማ ከማሳለፍ እኩይ ተግባሩን በራሱ ወደ በጎ ተግባር የመቀየር እና ያለፉትን አካሄዶች መለስ ብሎ የመመልከት የውዴታ ግዴታ የሚሰጥ ወቅት ላይ ነን።
ከባህርዳሩ እና ከአዲስ አበባው ግድያ በኃላ ሶስት አካላት ሶስት ነገሮችን መማር አለባቸው
በባህርዳሩ እና በአዲስ አበባው ግድያ ዙርያ ሶስት አካላት ማለትም -
- የኢትዮጵያ ሕዝብ፣
- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ እና
- አክራሪ ኃይሎች (hardliners) የሚከተሉትን ሶስት ነገሮች በትምህርትነት መውሰድ አለባቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ
አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን በኢትዮጵያ ላይ ያለውን ለውጥ በአንክሮ የሚከታተል፣ከልዩነት ይልቅ አንድነትን የሚናፍቅ ሆኖም ግን በብሔር አክራሪ ኃይሎች ድምፅ የተሰላቸበት እና አንዳንዱ ደግሞ የተደናገረበት ሁኔታ ነው ያለው።ይህ ከቅዳሜው አደጋ በፊት የነበረ አስታሳሰብ አድርጎ መውሰድ እና ከቅዳሜው ግድያ በኃላ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ድርጊቱ የደውል ያህል የሚወስደው መሆን አለበት።ስለሆነም ሕዝብ በዋናነት ማድረግ ያለበት ብሔራዊ አንድነት እና ሕብረት ማጠናከር ነው።የሃይማኖት፣የማኅበረሰብ እና የክልል አደረጃጀት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን የበለጠ ሊያተኩሩበት የሚገባ ጉዳይ ይሄው ብሔራዊ አንድነት ላይ ያተኮረ መሆን አለበት።በመሆኑም ዝምታን የመረጡ ሁሉ በእዚሁ ጉዳይ ላይ አትኩረው ለመስራት የሚነሱበት ጊዜ አሁን ነው።
እዚህ ላይ አሁንም የብሔራዊ አንድነት እና ኢትዮጵያዊነት ላይ እንደሚያተኩሩ ደጋግመው የነገሩን ለእዚህም እየሰሩ እንደሆነ ለአንድ ዓመት ያህል የተመለከትናቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አካሄድን ማገዝ አሁንም ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው።ይህ ስለ ኢትዮጵያ ሲባል የሚደረግ እንጂ ግለሰብ ከመውደድ የተነሳ የሚደረግ አይደለም።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ያህል አሁን ያለውን የኢትዮጵያ እና የአካባቢ ሀገሮች ውስብስብ ፖለቲካ የመረዳትም ሆነ በትዕግስት የመፍታት ክህሎት እና ስብዕና ያለው መሪ ለመሆኑ የሚነሳ ጥያቄ የለም።ስለሆነም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይን በርታ! የማለት እና የማገዝ ታሪካዊ ኃላፊነት አሁንም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከእዚህ በፊት ከነበረባቸው ኃላፊነት በበለጠ አሁን ባለችው ኢትዮጵያም ያለባቸው ታሪካዊ ኃላፊነት ጨምሯል።የባሕርዳሩ እና የአዲስ አበባው ግድያ በኃላ ግን የሀገሪቱ ለውጥ በቶሎ መፋጠን እንዳለበት የሚያሳይ አዲስ ምልክት የመመልከቻቸው ጊዜ አሁን እንደሆነ ሁኔታው በራሱ አመላካች ነው። በረጅም ጊዜ ይመጣሉ ያሉት የለውጥ ሂደት በተለይ ብሔራዊ አንድነትን በሁለት እና ሶስት ዓመታት በሂደት እየደመሩ የመሄድ ስልት አሁን ካለው የአክራሪ ኃይሎች የስልጣን ሙከራ አንፃር ሲታይ በፍጥነት መወሰን የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መድረሳቸውን የሚያሳይ ነው።ለእዚህ ደግሞ ኢህአዴግ ከአጋር ድርጅቶች ጋር የምፈጥረው ውህደት ይኖራል ያለውን ሃሳብ በጊዜ ሰሌዳ ከአሁኑ ማሳወቅ እና ቢዘገይ በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ይህንን መፈፀም እና የጎሳ ፖለቲካዊ አደረጃጀትን ቢያንስ በኢህአዴግ ደረጃ ማክሰም ወቅቱ የሚጠይቀው ሁኔታ ነው።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ከእዚህ በፊት በከፍተኛ ሁኔታ ሲቀርብባቸው የነበረው ጥያቄ አንዱ የአክራሪ ኦነግ ቡድኖች በኦዴፓ መዋቅር ውስጥ እና በምዕራብ ወለጋ ለተፈፀሙት ስርዓት አልበኝነት ተግባሮች ያሳዩት መለሳለስ ከአሁን በኃላ መቀየር እንዳለባቸው ማሰብ አለባቸው።በተለይ በእዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልፈቱበት የፈለጉት የራሱ የሆነ መንገድ ቢኖርም በአክራሪ ኃይሎች በኩል መለሳለሱ ሌላ ትርጉም እየተሰጠው ስለሆነ አሁን ቆንጠጥ ያለ እርምጃ በአክራሪ የኦነግ ኃይሎች ላይ አጠናክረው እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ህዝቡ ሊረዳው በሚችለው መጠን በተግባር ማሳየታቸው በዓማራ ክልል ያለውን የአክራሪ ኃይሎች ወደ ማዕከላዊ አስተሳሰብ የመምጣት ሂደት ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ አለው።
አክራሪ ኃይሎች (hardliners)
በየትኛውም የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ ላይ ለዘብተኛ እና አክራሪ ኃይሎች መኖራቸው የታወቀ ነው።በእዚህ አገላለጥ አክራሪ ኃይሎች (hardliners) በተለይ በኦሮምያ፣በትግራይ እና በዓማራ ስም 'ዋልታ ረገጥ' አስተሳሰብ የሚይራምዱ አደረጃጀቶች፣ኃይሎች እና አክትቪስቶችን ነው።እነኝህ አካላት መሰረታዊ የአክራሪነት መነሻቸው ሶስት ነገሮች ላይ ያጠነጠነ ነው።እነርሱም ያለፈ የተሳሳተ ትርክት፣የወደፊቱ ላይ ያላቸው ስጋት (አለመተማመን) እና ከግለሰቦቹ የግል የስልጣን እና የመታወቅ ፍላጎት የሚመነጭ ነው።ከእዚህ ሁሉ የከፋው እና አሁን መታከም ያለበት ግን የወደፊቱ ላይ ያላቸው ስጋት ወይንም አለመተማመን ትልቁን ድርሻ የሚይዝ እና አደገኛው ነው።በእዚህም ሳቢያ የማዕከላዊ ስልጣኑን በተቻለ መጠን ተፅኖ ባሳረፈ መልኩ መቆጣጠርን እንደ ብቸኛ መንገድ አድርገው ያዩታል።ሆኖም ግን ከአሁን በኃላ አንዱ በብቸኝነት የተቆጣጠረው የስልጣን አካሄድ የበለጠ ደም አፋሳሽ መሆኑን የዘነጉት ይመስላሉ።
እነኝህ አክራሪ ኃይሎች (hardliners) በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የለውጥ ሂደት ላይም አስቸጋሪ ጋሬጣ ሆነዋል።ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ በመሃል ሆነው የእነኝህን አክራሪ ኃይሎች ፍላጎት ለማመጣጠን በንግግራቸው እና በሹመት አሰጣጥ ላይ ሁሉ ሲቸገሩ በግልጥ ይታያል።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእዚህ ደረጃ ሲቸገሩ ግን ሕዝብ እና ማዕከላውያን እንዲሁም ኢትዮጵያዊነት የሚያስቀድመው አብዛኛው ሕዝብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ደግፎ መቆም የሚገባው ለእዚህ ነው።ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ብዙሃኑ ማዕከላዊው እና ኢትዮጵያዊነት አራማጁ ከዝምታ መንፈስ መውጣት ያለበት ለእዚህ ነው።
አክራሪ ኃይሎች (hardliners) በህወሓት፣በኦነግ - ኦዴፓ፣ በአብን እና አክትቪስቶች በኩል በተለይ ከቅዳሜው የባህር ዳር እና የአዲስ አበባ ግድያ በኃላ ቆም ብለው ማሰብ የሚገባቸው ወሳኝ ጊዜ ላይ መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው።ምክንያቱም በአክራሪ አካሄድ አገር እንዴት በአንድ ቀን ወደለየለት ትርምስ ልትገባ ትችላለች ብሎ አለማሰብ የበዛ የራስ ወዳድነት ስሜት ነው።ለማክረር በራሱ ሀገር ያስፈልጋል።በሌለ ሀገር ምንም ነገር አይኖርም።ስለሆነም የከረረ አስተሳሰቦች ወደ መሃል የሚመጡበት መንገድ ላይ ማተኮር እና የጎሳ ፖለቲካው አደገኛ መሆኑን የዶ/ር ዓቢይ መንግስት ተገንዝቦ የማስተካከል ስራዎችን ሲሰራ ቢይናስ የመለሳለስ እና የመተማመኛ ሂደቶች ላይ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል።በመሰረቱ የአክራሪ ኃይሎች (hardliners) ማቆጥቆጥ በራሱ ህወሓት/ኢህአዴግ ሰራሽ እንጂ ኢትዮጵያዊ መሰረት የለውም።ስለሆነም ኢትዮጵያዊ መሰረት ሲጠናከር አክራሪ ኃይሎች (hardliners) ቦታቸው እየጠፋ ይሄዳል።ይህ ግን በሂደት እና በሥራ የሚመጣ እንጂ የማኅበራዊ መስተጋብር ሂደቶች በአንድ ሌሊት ተሰርተውም ሆነ ተደምስሰው የሚያድሩ አይደሉም።
ለማጠቃለል ኢትዮጵያ አሁንም አይዞሽ! ልንላት ይገባል።ይህ ለውጥ ሲጀመር አሁን ከምናየው በላይ ፈተናዎች ሲጠበቁ ነበር።አሁን እየገጠመ ያለው የእዚህ አካል ክፋይ ነው።የቅዳሜው የባህርዳር እና የአዲስ አበባ ክስተትም አስተማሪ ሆኖ ማለፍ አለበት።ይሄውም ሕዝብ አንድነቱን በበለጠ መጠበቅ፣ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለበለጠ ተግባራዊ ውሳኔ የሚነሱበት፣ኢህአዴግ ከጎሳዊ ፖለቲካ ግንባርነት ወደ ውሁድ የሚቀየርበት እና አክራሪ ኃይሎች ወደ መሃል የሚመጡበት እና እራሳቸውን የሚወቅሱበት እስከሆነ ድረስ ኢትዮጵያ በተሻለ መልኩ ችግሩን ትወጣዋለች።ከእዚህ በተረፈ ግን በተለይ በኦዴፓ ውስጥ ያሉ አክራሪ ኃይሎች ከአሁን በኃላ በአጋጣሚው መንግስት ወደ ለየለት የአምባገነን ስርዓት ለመቀየር የሚያደርጉት ጥረት የበለጠ ሌላ አክራሪ ኃይል በሌላው በኩል ይፈጥር እንደሆነ እንጂ መፍትሄ አይሆንም።የዓቢይ መንገድ እና ለሁሉም አባት ለመሆን የሚያሳየውን መንግስታዊ ባህሪ የተላበሰ አካሄድ እያገዙ አክራሪ ጎሳዊ ፖለቲካን ሞርዶ ሃገራዊ ማድረግ ለአክራሪ ኃይሎች የቀረበ የመጨረሻው መጨረሻ አማራጭ ነው።ይህንን ማድረግ ካልቻሉ ግን ሳይወዱ በግድ ለብሔራዊ ጥቅም ሲባል መደረጉ አይቀርም።
ጉዳያችን GUDAYACHN
www.gudayachn.com