ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Sunday, June 16, 2019

''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች


Picture source = Beautiful Artist (America X Reader)

ጉዳያችን / Gudayachn
ሰኔ 9/2011 ዓም ( ጁን 16/2019 ዓም)

የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የቋንቋ ዎች ጥናት ማዕከል በ1993 ዓም ባሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይ አማረ የሚለውን ቃል ሲተረጉም  ተዋበ፣ቆነጀ፣ውል አለ፣አሰኘ  የሚል ትርጉም ይሰጠዋል።በሀገራችንም ''ያማረ ሁሉ አይበላም'' የሚባል የቆየ አባባል አለ።አባባሉ በዋናነት ከላይ የሚያዩት ውስጣዊ ምንነቱ ያልታወቀ ሁሉ እንደማማሩ ላይሆን ይችላል የሚል መልዕክት አለው።መፅሐፍ ቅዱስም ''ሰይጣን ራሱ የብርሃንን መልአክ እንዲመስል ራሱን ይለውጣልና'' (2ኛ ቆሮ 11፣14) በማለት የሚያምር ሰይጣን ስላለ ተጠንቀቁ በማለት ያስጠነቅቃል። 

ሰይጣን ርኩስ መንፈስ እንጂ የሚዳሰስ ስጋ አይደለም።ሆኖም ግን በፍጡራን ስጋ ላይ አድሮ ክፉ ሥራ ያሰራል።በፍጡር እባብ ላይ ያደረ ሰይጣን አዳምን ሲያስት በሚያምር መልክ መከሰቱ ሌላው ማሳያ ነው። ሰይጣን ቀንድ እና ጥፍሩን ብቻ አሹሎ ሳይሆን በሚያምር ሥራ፣በሚያምር አቀራረብ፣በሽንገላ ፈገግታ፣ለሰው ልጅ የሚቆረቆሩ በሚመስሉ ሰዎች፣የሃይማኖት ሰው በሚመስሉ ሰዎች፣ለጋሾች መሆናቸው በሚታወቁ ሰዎች፣ሲናገሩ ለሰው ልጅ በጎ የሚያስቡ በሚመስሉ ሰዎች ስር ሁሉ የሰይጣን ገንዘብ የሆነ ሥራ ይሰራል።


''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች የኢትዮጵያውያን ዋነኛ ጠላቶች  ናቸው።መልካም፣የዋህ፣ለሌላው የሚያስቡ፣ቅን እና ታጋሽ ኢትዮጵያውያን ሁል ጊዜ የሚነደፉት ''በሚያምሩ'' ሰይጣኖች ነው። ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች የተነደፉ ኢትዮጵያውያን በሚደርስባቸው እና እየደረሰባቸው ያለው መንገላታት ከሚገመተው በላይ ነው።''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ተቆነጃጅተው በጎ እንደሚሰሩ መስሎ በመታየት እየነደፉ ያልነደፉ መስለው ሲቁለጨለጩ መመልከት ሌላው አስገራሚው እውነታ ነው።''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ኢትዮጵያውያን ላይ በሶስት መልክ ይከሰታሉ።በእነኝህ በሶስት መልክ  የሚከሰቱት ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በሶስት ቦታዎችም ተንሰራፍተዋል።እነርሱም : -  • በሀገር ቤት በትናንሽ የስልጣን ወንበሮች ላይ፣
  • በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሐል እና 
  • በየትኛውም ቦታ የሚገኙ የእምነት ቦታዎች ነው።


''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በሀገር ቤት በትናንሽ የስልጣን ወንበሮች ላይ  


በሀገር ቤት የሚገኙ ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ከወረዳ እስከ ሚኒስትር መስርያቤቶች ውስጥ በኃላፊነት ተቀምጠው ተቆነጃጅተው አደባባይ የሚታዩ ነገር ግን በውስጥ የሰይጣን ሥራ እየሰሩ የሚገኙ ናቸው።ቀድመው የለውጥ ሐዋርያ መስለው ዲስኩር ላይ ቀዳሚ ናቸው።ምናልባትም በማያውቃቸው መሐል  ሲጎማለሉ ለለውጥ የቆሙ አልያም በጎ የሕዝብ አሳቢ መስለው ይታያሉ።ውስጣቸው ግን ነጣቂዎች፣በዘር ፖለቲካ የተነከሩ፣የገንዘብ ጥማታቸውን ለማርካት ሺዎች የሚፈናቀሉበትን መንገድ ማታ ማታ ሲሸርቡ ያመሻሉ። መግደል፣ክህደት እና ሸፍጥ የውስጥ ገንዘባቸው ነው።ከላይ ስታዩ ግን ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ናቸው እና ደጎች፣በንግግራቸው የሚያፈዙ፣እራሳቸውን ለሕዝብ የሰጡ የሚባል ስም አትርፈዋል። የሚያምር ሁሉ የሚበላ የሚመስለው ምስኪን ሕዝብ ጉዳዮችን በአንክሮ ማየት ትቷል እና ማማራቸውን ብቻ እንጂ ውስጣቸው ነጣቂ ተኩላ መሆናቸውን አይረዳም።የጊዜ ጉዳይ እንጂ ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች አንድ በአንድ በሕዝብ ዓይን ውስጥ የሚገቡበት እና የተቀቡት መዋብያ ተገልጦ ሰይጣንነታቸው የሚታወቅበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሐል


በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሁለት ተከታታይ ትውልድ ስደት ውጤት ናቸው።ሁለቱ ትውልዶች በሀገራዊ ጉዳይ የጋራ ርዕይ ቢኖርባቸውም በአካሄድ የተለያየ እሳቤ ሊኖራቸው ይችላል።የሚያሳዝነው ግን ከሁለቱም ትውልድ ውስጥ የማይታወቁ ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በብዙሃኑ በውጭ የሚኖሩ የዋህ፣ቅን እና በጎ አሳቢዎች መሐል ሆነው ስያምሷቸው ኖረዋል።በውጭ ሀገር የሚኖሩ ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ቅድምያ በጎ አድራጊ ለመምሰል ከቤተሰባቸው ጀምሮ የወሬ ዘመቻ ይከፍታሉ። ዋና መሳርያቸው የአውሮፓ እና የአሜሪካ ዋጋው የቀነሰ የስልክ ወሬ ነው።ሐሜት ጧት ፈጥረው፣ከቀትር በኃላ አሳድገው፣ምሽት ላይ ስልካቸውን ከፍተው የፈጠሩትን ሃሜት እንደ ዶሮ እንቁላል ታቅፎ የሚፈለፍልላቸው ሁነኛ ሰው ይመርጣሉ።ብዙ ጊዜ ለሀሜት መፈልፈያነት የሚመረጡ ሰዎች የዋሆች እና ቅኖች ከመሆናቸው የተነሳ የሃሜት ፈልፋይ እና አሰራጭ መሆናቸውን ላያውቁ ይችላሉ ወይንም   እያወቁ በይሉኝታ ተይዘው  በሃሜት ውጉ የተባሉትን ይወጋሉ።

በውጭ ሀገር ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በሚፈጥሩት የሃሜት ጦር ተወግተው ካሰቡት በጎ ሥራ ሁሉ እርግፍ አድርገው የተዉ ወይንም ''የሀበሻ ነገር አያሳየች'' ብለው ከማኅበራዊ ኑሮ ሁሉ እራሳቸውን አግልለው የሚኖሩ በጣም ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉ። ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በቁጥር በጣም በጣም ጥቂት ናቸው። ነገር ግን በጣት የሚቆጠሩ ሆነው ብዙ ሺዎችን የማመስ አቅም አላቸው።ምክንያቱም አይታወቁማ! እነርሱ ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ስለሆኑ የሚታየው የተቆነጃጀው ማንነታቸው እንጂ ሰይጣናዊ የሃሜት ጦራቸውን የሚያውቅ የለም። በውጭ ሀገር ባሉ ማኅበራዊ ድርጅቶች፣የህዝብ የእርስ በርስ ግንኙነት ሁሉ የሚበጠበጠው በእነኝህ እጅግ ጥቂት በሆኑ ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች መሆኑን የሚረዳ እጅግ ጥቂት ነው።ይህ የሚያውቀውም  ልናገር ቢል የሚሰማው የለም።''የሚያምር'' ሰይጣን የሚታወቁበት ጊዜ እንደደረሰ ሲረዱ በጎ ስራዎችን ይጨምራሉ።የበለጠ ይቆነጃጃሉ።የእዚህ ጊዜ ሕዝብ ከንፈሩን እየመጠጠ ያሞግሳቸዋል።

በውጭ ሀገር ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት በቀድሞው ኢህአዴግ/ህወሓት መዋቅር ውስጥ በጥቅም እየተያዙ ዲያስፖራውን ለመበጥበጥ እና የእርስ በርስ ግንኙነቱን ለማላላት እና እንዳይቃወም ለማድረግ ተጠቅሞበታል።በአንድ ብዙ ኢትዮያውያን የሚኖሩበት የውጭ ሀገር  ከተማ ውስጥ ''የሚያር'' ሰይጣን ከተገኘ (ከተገኘች) በከተማው ውስጥ የቀድሞውን መንግስት ይቃወማሉ የተባሉ ሰዎችን በወዳጅነት ቀርበው፣ በፈገግታ እየሸነገሉ ከጀርባ ግን በፈጠራ ወሬ እንዲያሙ ተልኮ ይሰጣቸዋል።''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ናቸው እና እነርሱ ይታመናሉ።

''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ሁል ጊዜ አሸናፊ አይደሉም።ማንም የማይከታተላቸው እና የማያውቃቸው ይመስላቸዋል።በውጭ ሀገር ከሀገር ቤት ጀምሮ የምታውቁት ወዳጅ፣ከቤተሰብ ጀምሮ የምያውቃችሁ አሳቢ፣ የቅርብ ዘመድ ይሆንና ከእናንተ መሃል ሌላው ሰው ከጥንት የምታውቁት ወይንም የቅርብ ዘመዳችሁ መሆኑን በማያውቅበት ሁኔታ ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ለራሳችሁ ወዳጅ፣ወይንም ዘመድ ሲያማችሁ እና ብዙ እርቀት የተንኮል ሥራ ሲሰራ የእየቀን እኩይ ተግባር እጃችሁ ላይ ይወድቃል።በሀገር ቤት በአንዳንድ መስርያ ቤቶች ውስጥ ፀሐፊዎች የዋና ሥራ አስኪያጁ ዘመድ መሆኗን ሳያውቅ በሃሜት  የተጠመደ ሰራተኛ አይነት ውሰዱት።

''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በዕምነት ቦታዎች 

''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በተለይ በዕምነት ቦታዎች ውስጥ  ተቀባብተው ሲገቡ ምዕመኑን እርስ በርሱ እንዳይፋቀር፣እንዳይተሳሰብ እና ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ነጥለው የሃሜት ሸክማቸውን ያራገፉባቸው ሁሉ የተጫኑት ውሸት እውነት ስለሚመስላቸው ''የሚያምሩት'' ሰይጣኖች በእውነትም የሚያምሩ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ ብዙዎች ከአገልግሎት፣ሌላውን ከመርዳት እና ከቅን ሥራ ሁሉ ''በሚያምሩ'' ሰይጣኖች እየተወጉ እያዘኑ ከእምነታቸው ይርቃሉ አልያም እያዘኑ ለሚያምኑት አምላክ ያመለክታሉ።''የሚያምኑት'' ሰይጣኖች ግን የወጉትን እያዩ በፈገግታ እየሸነገሉ ምንም እንዳላደረጉ ይታያሉ።


''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በእምነት ቦታዎች የዋሃንን ሲወጉ ከእራሳቸው በቀር የገዛ ቤተሰባቸው፣ልጆቻቸው እና የትዳር አጋሮቻቸው ሁሉ እንዳያውቁ አድርገው ነው። በቤተሰባቸው መሃል ሁሌም ቅኖች ሆነው ለመታየት ከፍተኛ የፕሮፓጋንዳ ሥራ ይሰራሉ።በመቀጠል በቤተሰባቸው መሃል በዘሩት የሐሰት ወሬ የሚወጉትን ሰው እንዲጠላ አዲስ ትርክት ይፈጥሩለታል።ትርክቱ በዙርያቸው ለሚገኙ የቅርብ ዘመዶች፣አንደኛ ደረጃ ቤተሰቦች፣የቅርብ ወዳጆች እና የአገልግሎት ክፍሎች ውስጥ ለይተው ይመቹኛል ባሏቸው ሰዎች ሁሉ መርጠው የመርዛማ የጥላቻ ዘመቻቸው አካል እንዲሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የአካል፣የስልክ እና የጥቅም መደለል ሥራ ሁሉ ይሰራሉ።በተለይ በስልክ ዘመቻቸው ወቅት የገዛ ቤተሰብ በማይሰማበት ጊዜ ይመርጣሉ። ከእዚህ ሁሉ በኃላ በሐሰት የወጉትን ሲመለከቱ  በሽንገላ ፈገግታ እየተመለከቱ መርካታቸውን ከፊታቸው መደበቅ ያቅታቸዋል።በእዚህ ሳብያ ብዙ ሰው ከእምነቱ እንዲርቅ፣ሰው እንዲጠላ እና ሰው ሁሉ ክፉ ነው ብሎ እንዲያስብ ያደርጉታል።ምክንያቱም ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች መጀመርያ ሥራ የሚጀምሩት ሊያጠቁ በፈለጉት ሰው ዙርያ ነው።በዙርያው (ዋ) ያሉትን ሰዎች በስልክ የፈጠራ ሀሜት ከምዘብዘብ የሰሙትን በጎ መረጃ ሁሉ አጣመው ትንታኔ በመስጠት የዋሆችን ይወጋሉ።በእርግጥ ማንኛውም ሥራ በሥራ ልምድ እንደሚዳብር ሁሉ ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች እየቆዩ ሲሄዱ በልምድ እየተካኑ ስለሚሄዱ ካህኑን ከምዕመኑ፣ ሸሁን ከሙስሊሙ ለመለየት አንዲት ጫፍ ፈልገው አስፍተው በመንገር ዱላ እስከማማዘዝ የመድረስ ልምድ አላቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች የሚሰሩት ሁሉ ትክክል እንደሆነ እራሳቸውን ለማሳመን ምክንያት ይሰጡታል።ምክንያታቸው ግን ሕሊናን የማሸነፍ አቅም ስለሌለው ውስጣቸው እራሳቸውን መውቀሱን አያቆምም።

በእምነት ቦታዎች የሚታዩት ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች አንዱ አስገራሚ ድርጊታቸው ቀድመው የተበደሉ መስለው ማጮህ ነው። ቀድመው የተበደሉ መስለው መታየት አንዱ የመቆነጃጀች ዘዴ ነው።ቀድሞ መጮህ ''ጥሩ የሚያምር'' ሰይጣን ለመሆን ይመቻል።ቀድመው ከጮሁ በኃላ የስልክ እና የአካል ሃሜታቸውን ለመርጨት ይመቻል።ምክንያቱም ከንፈሩን እየመጠጠ የሚሰማ ያገኛሉ።በሌላ በኩል ደግሞ አመቺ የመሰላቸው ጊዜ  በጣም ግልጥ የሆኑ ለመምሰል በመነጋገር የሚያምኑ ሁሉ መስሎ በመቅረብ ለእየብቻ እያሙ ያቆሰሏቸው  ሰዎች እስኪገረሙ ድረስ በግልጥ የሚያወሩ መስለው ይታያሉ።ይህ ሌላው አስገራሚ ''የሚያምሩ'' ሰይጣን ገፅታቸው ነው።

ለማጠቃለል

 ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች የኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ ችግር አንዱ እና ዋነኛው እየሆነ መጥቷል። በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሃል ያደረሱት ጉዳት ቀላል አይደለም።በመጀመርያ ደረጃ የህዝቡን የእርስ በርስ ግንኙነት አበላሽተዋል።በሁለተኛ ደረጃ ማኅበራዊ ድርጅቶች አቅመ ቢስ እንዲሆኑ አድርገዋል።በሶስተኛ ደረጃ ብዙ አቅም ያላቸው ሀገር ወዳድ፣በጎ አሳቢ እና ቅን ኢትዮጵያውያን በራሳቸው በወገናቸው እንዲመረሩ እና በጅምላ ኢትዮጵያውያንን እንዲሸሹ አድርገዋል።''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ሌት ተቀን በስልክ እና በአካል የወረወሩባቸው የውሸት ጦር ስለሚዘገንናቸው ከእዚህ ሁሉ ጊዜ እና ፈጣሪ ይፍረድባቸው ብለው ተቀምጠዋል።ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን እንደሀገር ኢትዮጵያውያንን እንደ ማኅበረሰብ ጎድቷቸዋል።

ለእዚህ ሁሉ መፍትሄው ግን ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች የሚለዩበትን ዋና መለያ ሃሜት ቀድሞ አውቆ ያላቸውን የተለየ ሃሳብ ለባለቤቱ እንዲነግሩ ነግሮ የወሬ ጊዜ ማሳጠር ነው። ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች በውለታ የገዟቸው አልያም በዝምድና ፍሬ የሌለው ''ወሬ'' በስልክ በማውራት የምያደክሟቸው ሁሉ ለመልካም የአዕምሮ ጤንነታቸው ማሰብ እና ''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ወደ በጎ ህሊና እንዲመለሱ ሲሆን በመምከር ካልሆነ መከራ እስኪመክር  በትዕግስት በመጠበቅ ለሰው ሁሉ በጎ ህሊና በመያዝ መኖር አለባቸው።''የሚያምሩ'' ሰይጣኖች ወደ ሰዋዊ ልቦናቸው ካልተመለሱ ክፋታቸው መገለጡ  የማይቀር ነው።ሕዝብ ግን መታወክ የለበትም።

ጉዳያችን GUDAYACHN 
 www.gudayachn.com

No comments:

ለፕሮፌሰር መራር፣ልደቱ፣ጀዋርና ኢንጅነር ይልቃል ዘፈን ይህችን ዜማ እንምረጥላቸው።

በቅድምያ ስለ አራቱም የመግቢያ ማስታወሻና ወቅታዊ ሁኔታቸው። አራቱም ከመስከረም በኋላ መንግስት የለም ብለው ኢትዮጵያን ለእርስ በርስ ጦርነት ሊነክሯት ሞክረዋል።ዝርዝሩን፣ከእነማን ጋር መክረው እንደነበር፣ለኢትዮጵያ ደግሰው...