አሜሪካኖቹ ስለ ሃገራቸው ቀደም ስላሉት አመታት ሲናገሩ(ስለ ሁለት መቶ አመት ታሪክ ቢሆንም) የሚጠቀሙበት አንዲት ብሂል አለቻቸው።'' መስራች አባቶቻችን'' የምትል።ስለ ህገ መንግስታቸውም ሆነ ስለ የነፃነት ቀን ሲያወሱ ''መስራች አባቶቻችን'' የምትለው ቃል አትለያቸውም።አውሮፓውያንም ተመሳሳይ ሁኔታ ይጋራሉ።ህገ መንግስታቸው ከረቀቀ ከመቶ ዓመታት በላይ የሆናቸው በየዘመኑ አንዳንድ ማሻሻያ ከማድረግ በላይ መሰረቱን ሳያናጉት ይሄው ዛሬም አሉ።ለዚህም ሳይሆን አይቀርም ብዙዎች የአውሮፓ ሃገራት ምክር ቤቶች የመጀመርያውን ምክር ቤት ወይንም ፓርላማ መስራችዋን ሀገር እንግሊዝን ጨምሮ ስፍራቸውን ሳይቀይሩ የመስራች አባቶቻቸውን በማሰብ ቀደምቶቻቸው በሰሩት ህንፃዎች አሁን ድረስ የሚገለገሉት ።የካቲት 23/2004 ዓም (ማርች 2 /2012) የዓድዋ ድል አንድ መቶ አስራ ስድስተኛ ዓመቱ ታስቦ ይውላል። ዘንድሮ ደግሞ ብዙ ወጣቶች ታሪኩ በሚገባ ለትውልድ መተላለፍ አለበት ብለው ከሃገር ውጭ ባሉ ከተሞች እንደሚከበር እይተወሳ ነው።ጥሩ ጅማሮ ነው።በርቱ ማለት ደግሞ ጤናማ ና ኃላፊነት የሚሰማው ሰው ሁሉ አስተሳሰብ ነው።
ቅድመ የ ዓድዋ ድል (1885 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር)
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 16 /1885 ጀርመን በርሊን ከተማ በሚገኘው ውብ በሆነው የ ሀገሪቱ ቻንስለር ቬን ቢስማርክ ባለስልጣን መኖርያ ህንፃ ሳሎን ፌሽታ በ ፌሽታ ሆኗል።ሶስት ወር ሙሉ አሰልቺ ውይይት የተደረገበት ዋና ዋናዎቹ የ አውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ተሰብስበው '' አንተ ይሄን ያዝ አንተ በእዚህ ውረድ''ተባብለው የ አፍሪካ ካርታ እንደምግብ በመካከላቸው ተዘርግቶ ከወታደራዊ ዘመቻ በፊት አፍሪካን የተከፋፈሉባት ቀን ነበረች። በ እዚህ ስብሰባ ከ 80 በ መቶ በላይ የ አፍሪካ መሬት በ ሃሳብ መስመር እያሰመሩ ተከፋፈሉት። የ በርልኑ ''General act of Berlin conference '' በ ታሪክ ባብዛኛው የሚታወቀው '' The division of Africa '' ወይንም ''scramble of Africa'' (አፍሪካን የ መቀራመት ጉባኤ) ተብሎ ነው ።በ እዚህ ጉባኤ ላይ ጀርመን፣ኦስትሮ-ሀንጋሪ፣ቤልጅየም፣ደንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ታላቅዋ ብሪታንያ፣ጣልያን ፣ኔዘርላንድ፣ፖርቱጋልን ጨምሮ የተገኙ ሲሆን ቅኝ ግዛትን ሕጋዊ ሽፋን ለመስጠት የተሞከረ ና በዚሁ መሰረት በ 1914 በ ፈረንጆቹ አቆጣጠር አብዛኛው የ አፍሪካ ግዛት በ ቅኝ ገዢዎች የወደቀበት ሁኔታ ነበር።