- መንግስት በፍጥነት ሊሰራቸው የሚገቡት አምስት ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት
=========
ጉዳያችን አለርት
=========
የአረብሊግ አንዱ የሚታወቅበት መለያው እንደባዶ ቆርቆሮ ብዙ መጮህ እና ትንሽ ማድረግ ነው።በፍልስጤም እስራኤል ግጭት፣በሊብያ፣የመን እና ሶርያ መንግስታት መፍረስ ላይ ሁሉ ብዙ በመጮህ የሚታወቀው የአረብሊግ ነገር ግን አንድ የጋራ ሰላም አስከባሪ ልኮ በጋራ የቀጠናውን ችግር ሲፈታ አልታየም። ሰሞኑን በሱዳን ጉዳይ ላይም ስብሰባ ተቀምጦ ብዙ ንግግር ሰምቷል። የአረብ ሊግ በውስጡ የተለያየ የመከፋፈል ስንጥቆች ስላሉት በስሜት የአካፋ ያህል የሚናገረውን አንዲት ማንኪያ ያህል የማድረግ ልማድ እንደሌለው ብዙዎች በድርጅቱ ላይ የሚሰጡት ምስክርነት ነው።
ሊጉ በኢትዮጵያ የአባይ ግድብ አንጻር በግብጽ አነሳሽነት አማካይነት ያሳየው ድፍረት ግን እንዲሁ በቀላል የሚታይ አይደለም። የግብጹ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሳማህ ሃሰን ሸሪክ የአባይ ጉዳይ በአረብ ሊግ እያንዳንዱ መደበኛ ስብሰባ ላይ ቋሚ አጀንዳ እንዲሆን አስደርገዋል።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ልምድ ያላቸው ግለሰብ ናቸው።የዛሬ ሦስት ዓመት ጉዳያችን ስለግለሰቡ ማንነት የጻፈችውን በእዚህ ሊንክ ላይ ያንብቡ።
የአረብ ሊግ መደበኛ ስብሰባውን ባደረገ ቁጥር የአባይ ግድብ ጉዳይን እያነሳ መፈትፈቱን የኢትዮጵያ መንግስት እንደዋዛ ሊመለከተው አይገባም። ባሕር ተሻግረው የኢትዮጵያ ወንዞች ጉዳይ ይመለከተናል የመካከለኛ ምስራቅ ጉዳይ ነው የሚለው የአረብ ሊግ የድፍረት ድፍረት ወሳኝ የሆነ አጸፋዊ የዲፕሎማሲያዊ ምት ይፈልጋል። ለእዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ አቅሙም ሆነ ብቃቱ አላት። ነገር ግን ጉዳዩን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባት መንግስት የተረዳ አይመስልም። የአረብ ሊግ በኢትዮጵያ የውስጥ ወንዝ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ማሳለፉ የሰሞኑ ዜና ነው። የኢትዮጵያ መንግስትም ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መግለጫ አውጥቷል። ከመግለጫው በላይ ግን ከዲፕሎማሲያዊ መፋዘዝ ወጥቶ መንግስት በፍጥነት ሊሰራቸው የሚገቡ አምስት ተግባራት አሉ።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአረብ ሊግ ውሳኔ ዛሬ የሰጠው ምላሽ
መንግስት በፍጥነት ሊሰራቸው የሚገቡት አምስት ወሳኝ ዲፕሎማሲያዊ ተግባራት:
1/ የአፍሪካ ሀገሮችን የውሳኔው አደገኛነት እንዲገባቸው ማድረግ፣ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ሕብረት መርቶ ተጻራሪ መግለጫ ማሰጠት እና የዲፕሎማሲ ጉዞ ወደ አፍሪካ ሀገሮች መላክ።በእዚህ አንጻር የሚከተሉት ተግባራት መንግስት መከወን ይችላል።
- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ልዩ መልዕክት የያዘ ደብዳቤ ለአፍሪካ ሀገራት የሚያደርስ ከፍተኛ ልዑክ መላክ እና የአረብ ሊግ ጣልቃ ገብነትን ኢትዮጵያ ፈጽሞ የማትቀበለው ብቻ ሳይሆን በአፍሪካውያን ላይ የተቃጣ የቅኝ ግዛታዊ መንፈስ መያዙን ማሳየት፣
- ለአፍሪካ ቀንድ ቀጣይ የጸጥታ ስጋት መሆኑን በሚገባ ማስረዳት፣
- የአፍሪካውያን ጉዳይ በራሳቸው በአፍሪካውያን በግብጽ እና ኢትዮጵያ መካከል የሚታይ እንጂ የሌሎች ጣልቃ ገብነትን እንደማይቀበሉ የአፍሪካ ሀገሮችን ማግባባት እና ይህንኑ እንዲገልጹ ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ማቀጣጠል፣
- የአፍሪካ ሕብረት የአረብ ሊግን ውሳኔ እንዲቃወም ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተጽዕኖዋን በድርጅቱ ላይ ማሳየት አለባት፣
- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን የአፍሪካ ሕብረት ላይ በእዚህ ጉዳይ ከፍተኛ ተጽዕኖዋን ማሳየት አለባት። በሕብረቱ ስብሰባዎች ላይ የአረብ ሊግ የአፍሪካን ሉአላዊነት መዳፈሩን ደጋግማ መንገር አለባት።በመቀጠልም ኅብረቱ የአረብ ሊግን ውሳኔ በሌላ ውሳኔ እስኪሽር ድረስ ዲፕሎማሲዋን አጠናክራ መቀጠል አለባት።
- በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላከ ልዩ መልዕክት ለሀገራቱ እና ለተመድ ዋና ጸሐፊ በልዩ ልዑክ ተልኮ መስጠት እና ጉዳዩ የሉአላዊነት ጉዳይ መሆኑን ማስረዳት እና ሀገራት አቋም እንዲወስዱ መወትወት፣
- አሁን በመካከለኛው ምሥራቅ አንጻር ያሉትን የሀገራቱን አሰላለፍ ተመልክቶ በበቂ ሁኔታ አስልቶ መንቀሳቀስ
3/ የአረብ ሊግ አባል ሀገር የሆኑ ጎረቤቶቻችን ጂቡቲ፣ሱማሊያና ሱዳን የድርጅቱን ውሳኔ በብርቱ እንዲቃወሙ የጠነከረ ዲፕሎማሲያዊ ዘመቻ ማድረግ፣ ያሉትን የተጽዕኖ መንገዶች ሁሉ መጠቀም እና
4/ የአረብ ሊግ ውሳኔ ምን ያህል የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የተጻረረ እንደሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ መግለጽ።
- አስገራሚው ጉዳይ የአረብ ሊግ ውሳኔ በሚገባም የምሬት አቀራረብ የመንግስት መገናኛዎች ለኢትዮጵያ ህዝብ አልነገሩትም። ይህ መታረም ያለበት ነው።
- የመንግስትም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙሃን በሚገባ ጉዳዩ ምን ያህል የሉዓላዊነት ጥሰት እንደሆነ መግለጽ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጣውን እንዲገልጽ ሊደረግ ይገባል። ይህ በራሱ የዲፕሎማሲው አንዱ አካል ነው።
5/ የአረብ ሊግን ውሳኔ በመቃወም ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በውጭ ሃገር አጠቃላይ የተቃውሞ ሰልፍ በመላው ዓለም ሊያደርጉ እና ለሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም ሆነ መንግስታት ማሳወቅ አለባቸው። በተመሳሳይ በሀገር ውስጥም ኢትዮጵያውያን አደባባይ ወጥተው ሊቃወሙትና የሉዐላዊነቱን አደጋ በሀገር ውስጥ ያለው ህዝብ በሚገባ እንዲረዳው መደረግ አለበት።
ባጠቃላይ የአረብ ሊግ ውሳኔ ኢትዮጵያ በብርቱ ልትቃወመው እና በቀላሉ ልታየው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። ከመካከለኛው ምስራቅ ጋር ኢትዮጵያ ባላት ስልታዊ አቀማመጥ ብቻ ሳይሆን ባላት የህዝብ ብዛት እና ታሪካዊ ሃይማኖታዊ ዳራ ሳይቀር ኢትዮጵያን ለማጥፋት የሚፈልጉ አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ኢትዮጵያ በአባይ ግድብ አንጻር የምታደርገውን መንሰራራት እንደ የራሳቸው ስጋት አያዩትም ማለት ሞኝነት ነው። ኢትዮጵያን ለማጥቃት ደግሞ እንደ አንድ ምክንያት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉት በማይመለከታቸው የአባይ ጉዳይ እጃቸውን ለመንከር እንዳሰፈሰፉ በሚገባ እያሳዩን ነው። በቀጣይ ዓመታት የሚኖረው የዓለማችን የኃይል አሰላልፍ ደግሞ የአካባቢ ጉልበተኞች በአካባቢያቸው ያሉ ደካማ ሀገሮች የመውረር ስልት እንደሚይዝና የዓለምም የጸጥታ ስጋት እንደሚሆን የሚናገሩ ቀላል አይደሉም። ከመካከለኛው ሀገሮች ጋር ግብጽ የገባችው የወታደራዊ ስምምነቶች ደግሞ በአረብ ሊግ ስም አንዳንድ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ኢትዮጵያን በወታደራዊ ኃይልም ጭምር ለማጥቃት አይቃዡም ማለት አይቻልም። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት የአረብ ሊግን ውሳኔ ከመግለጫ ባለፈ በጠነከረ የዲፕሎማሲ ምት መመለስና አስተማሪ እንዲሆን የማድረግ ስራውን ከላይ በተጠቀሱት አምስት መንገዶች ቢከውን ጠቃሚ ነው። ጉዳዩ ለኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ ጎልቶ ያልተገለጸበት ምክንያትና ዲፕሎማሲውን በሚገባ አድምቶ እንዳይሰራ በራሱ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያዘናጉት ካሉም እራሱን ይፈትሽ። ጉዳዩ ግን በምንም መለኪያ አደገኛ የሉዐላዊነት ድፍረት ነው።
======================///////==================