ወደ የሚፈልጉት ቋንቋ ይቀይሩ Translate to different Languages

Thursday, May 4, 2023

በአማራ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ በመመካከር፣በመግባባትና በሽምግልና ብቻ ነው የሚፈታው።በአማራ ክልል ጸብ ከምታባብሱ የመረጃ አዛቢዎች በላይ የአማራም ሆነ የመላዋ ኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የለም።


 

በአማራ ክልል ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ፈጽሞ ወደ የደም ማፋሰስ ሊያመራ የሚገባው ጉዳይ ሊሆን አይችልም። ህዝብም ሆነ መከላከያ ፈጽሞ ምንም ዓይነት ግጭት እንዲፈጠር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሚያጋድል በቂ ምክንያት አለመኖሩንም ጭምር ያምኑበታል። ይህም ሆኖ ግን ከውጪ ሆነው በአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት እንዲነሳ ግፋ በለው የሚሉ እና በሰራዊቱም ውስጥ መንግስት አላስፈላጊ እርምጃ እንዲወስድ እና ህዝብ በመከላከያ ላይ ቅሬታ እንዲኖረው የሚፈልጉ ይጠፋሉ ማለት አይቻልም። ከእዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያን የጸጥታ መደፍረስ ከሱዳን ጋር ተያይዞ ምስራቅ አፍሪካን ለማበጣበጥ የሚፈልጉ ደግሞ የራሳቸውን የቤት ሥራ አይሰሩም ማለት አይቻልም።

የመረጃ አዛቢዎች መከላከያን ሊያጠቅ የመጣ ታጣቂ እንዳለ ይነግሩታል። በሌላ በኩል ደግሞ መከላከያ የሆነ ብሔር ወክሎ የመጣ አድርገው የመከላከያን ቁመና ለማውረድ የሚሞክሩ ደግሞ ሕዝቡን በሌላ አቅጣጫ ለማስደንበር ይሞክራሉ።ከእዚህ ሁሉ ጋር ደግሞ እራሱ መንግስት ከመጀመርያው የልዩ ኃይልን ወደ መደበኛ ሰራዊት የማስኬድ ሂደት አስመልክቶ መንግስት ከአማራ ክልል ጋር ያደረገው የኮሚኒኬሽን መንገድ መልክ ባለው አካሄድ አለመሆኑ ሌላው አሁን ላሉት አለመግባባቶች ያደረሱ ናቸው።

ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን መከላከያ አይገድሉም።መከላከያም ለሀገር ሕልውና የቆመን የመግደል ፍላጎት የለውም። ይህ በእንዲህ እያለ ግን የመረጃ አዛቢዎች በተለያዩ የማኅበራዊ ሚድያ ገጾች እየተጠቀሙ በተከታታይ የሚለቋቸው መረጃዎች የሰራዊቱን አመራሮችንም ሆነ ከህዝቡ የወጡ ታጣቂዎችን የማስደንበር ሥራ በመስራት ነገሮች ከሚገባ በላይ እንዲጋጋሉ የማድረግ እኩይ ተግባር ላይ ተጠምደዋል።

 አሁን የተጀመሩ የሽምግልና እና ወደ ሕጋዊ የመግባባት መስመር የመምጣት ሂደቶች በጎንደር በጥሩ ደረጃ ተጀምሯል። ነገ ጧትም ከመከላከያ ጄነራሎች እና የሕዝብ ታጣቂዎች መሃል ቀጠሮ ተይዟል። ዛሬ ከቀትር በኋላም የመከላከያ ጄነራሎችም ሆኑ ታጣቂዎች በተማመነ መንገድ መነጋገራቸው ነው የተሰማው። ከእዚህ በፊትም በሰሜን ወሎ ተመሳሳይ መነጋገር ተደርጎ ጉዳዩ በመግባባት ካለቀ በኋላ አሁንም የመረጃ አዛቢዎች የተወሰኑትን ለማስደንበር መሞከራቸው ይታወቃል።

የአማራ ክልል የጦርነት አውድማ እንዲሆን የሚፈልጉ የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው የውስጥም ሆነ የውጭ ኃይሎች መኖራቸው የታወቀ ነው። ሆኖም ግን አማራን እንወክላለን የሚሉም ሆኑ የአማራ ህዝብ እንደተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ በ21ኛው ክ/ዘመን ወደ የተሻለ እድገት እንዲሻገር ይህ እርባና የለሽ እና የራስ የሆነ የቀኝ እጅ መከላከያን በመቁረጥ የአማራ ክልልም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያተርፈው አንዳች ነገር የለም። ስለሆነም በሁሉም አካባቢዎች ያሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣የኃይማኖት አባቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብም ጭምር በታጣቂዎች እና በመከላከያ መሃል በመሸምገል እና ሁሉንም ጉዳይ በህጋዊነት መልኩ እንዲያልቅ በማድረግ ሰላም የግድ መምጣት አለበት። በመንግስት በኩልም የሕዝብ ባሕላዊ ዕሴቶችን የማወቅ እና የማክበር ጉዳይም በአሁኑ የአማራ ክልል በተነሳው አለመግባባት ውስጥ መኖሩን ማመን አለበት። የወታደራዊ መንግስት እስከወደቀበት ጊዜ ድረስ የወልቃይት ህዝብ፣የቦረና የቀድሞ ሲዳማ፣አፋር እና የሱማሌ ቆላማ ቦታዎችን ላይ መሳርያ የመግፈፍ ሥራ ሙሉ በሙሉ ያልፈጸመው ይህንኑ የአንዳንዳ አካባቢዎች የባሕላዊ ዕሴቶች ዋጋ ስለሚያውቅ መሆኑም መረዳት ያስፈልጋል። በአማራ ክልልም ያለው ሁኔታም በደንብ መታየት ያለበት እና በሀገሪቱ ሕግ የመሳርያ ማስመዝገብ ሕግ ላይ አጥብቆ መስራት እና ሌሎች የጸጥታ ህጎች ላይ መስራት ይገባል። የነፍስ ወከፍ መሳርያዎች በተመለከተ ግን በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት መመዝገባቸው በቂ መሆኑን ቢያንስ በእዚህ ጊዜ በደንብ መረዳት ያስፈልጋል። አሁንም ግን በአማራ ክልል ጸብ ከምታባብሱ የመረጃ አዛቢዎች በላይ የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት የለም። ሰላም፣መረጋጋት እና መከላከያን በጋራ ማጠናከር የአማራ ክልልም ሆነ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የውዴታ ግዴታ ነው። በመከላከያም ሆነ በህዝቡ መሃል ሆነው የመረጃ መዛባት የሚፈጥሩ ቢያንስ የህዝብ ስቃይ እንዲታያችሁ ወደ ህሊናችሁ ተመለሱ።

==============/////===========
 

No comments:

ህወሓት ሰሜን ወሎ ራያን ወርሮ የገጠር ወረዳዎችን እየዘረፈ ነው። ህዝብ ሲዘረፍ እና በአስር ሺዎች ሲፈናቀሉ የመንግስት የፖለቲካም ሆነ የወታደራዊው አመራሮች ዝምታቸው ከተጠያቂነት አያድናቸውም።

በሰሞኑ የህወሓት ወረራ ቆቦ ተፈናቅለው የገቡ የሰሜን ወሎ ተፈናቃዮች  በከፊል ፎቶ፡ ቢቢሲ ሚያዝያ 20፣2024 እኤአ ''ቅጥ አምባሩ የጠፋው'' የፕሪቶርያው ውል   ''ስኩዌር ዋን&#...